-
ማቴዎስ 21:33-41አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
33 “ሌላም ምሳሌ ስሙ፦ የወይን እርሻ+ ያለማ አንድ ባለ ርስት ነበር፤ ዙሪያውንም አጠረው፤ በዚያም የወይን መጭመቂያ ቆፈረ እንዲሁም ማማ ሠራ፤+ ከዚያም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።+ 34 ፍሬው የሚሰበሰብበት ወቅት ሲደርስ ድርሻውን እንዲያመጡለት ባሪያዎቹን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። 35 ገበሬዎቹ ግን ባሪያዎቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ ሌላውን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት።+ 36 ከበፊቶቹ የሚበዙ ሌሎች ባሪያዎች በድጋሚ ላከ፤ ይሁንና በእነሱም ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው።+ 37 በመጨረሻም ‘መቼም ልጄን ያከብሩታል’ በማለት ልጁን ላከው። 38 ገበሬዎቹ ልጁን ሲያዩት እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይሄ ነው።+ ኑ እንግደለው፤ ርስቱንም እንውረስ!’ ተባባሉ። 39 ስለዚህ ያዙትና ከወይን እርሻው ጎትተው በማውጣት ገደሉት።+ 40 እንግዲህ የወይኑ እርሻ ባለቤት ሲመጣ እነዚህን ገበሬዎች ምን የሚያደርጋቸው ይመስላችኋል?” 41 የካህናት አለቆቹና የሕዝቡ ሽማግሌዎችም “ክፉዎች ስለሆኑ ከባድ ጥፋት ያደርስባቸዋል፤ ከዚያም የወይን እርሻውን፣ ፍሬውን በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት።
-
-
ሉቃስ 20:9-16አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
9 ከዚያም ለሕዝቡ የሚከተለውን ምሳሌ ይነግራቸው ጀመር፦ “አንድ ሰው የወይን እርሻ+ አለማና ለገበሬዎች አከራየ፤ ወደ ሌላ አገር ሄዶም ረዘም ላለ ጊዜ ቆየ።+ 10 ወቅቱ ሲደርስ ከወይኑ ፍሬ ድርሻውን እንዲልኩለት አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎቹ ላከ። ይሁንና ገበሬዎቹ ባሪያውን ከደበደቡት በኋላ ባዶ እጁን ሰደዱት።+ 11 እሱ ግን በድጋሚ ሌላ ባሪያ ወደ እነሱ ላከ። ይሄኛውንም ደብድበውና አዋርደው* ባዶ እጁን ሰደዱት። 12 አሁንም ሦስተኛ ባሪያ ላከ፤ እሱንም ካቆሰሉት በኋላ አውጥተው ጣሉት። 13 በዚህ ጊዜ የወይን እርሻው ባለቤት ‘ምን ባደርግ ይሻላል? የምወደውን ልጄን+ እልካለሁ። መቼም እሱን ያከብሩታል’ አለ። 14 ገበሬዎቹ ልጁን ባዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይሄ ነው። ርስቱ የእኛ እንዲሆን እንግደለው’ ተባባሉ። 15 ከዚያም ከወይን እርሻው ጎትተው በማውጣት ገደሉት።+ ታዲያ የወይኑ እርሻ ባለቤት ምን የሚያደርጋቸው ይመስላችኋል? 16 ይመጣና እነዚህን ገበሬዎች ይገድላል፤ የወይን እርሻውንም ለሌሎች ይሰጣል።”
ሕዝቡም ይህን ሲሰሙ “ይህስ ከቶ አይሁን!” አሉ።
-