-
ማቴዎስ 17:1-8አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
17 ኢየሱስ ከስድስት ቀን በኋላ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን ብቻ ይዞ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ወጣ።+ 2 በፊታቸውም ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ።*+ 3 ከዚያም ሙሴና ኤልያስ ከእሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። 4 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፣ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው። ከፈለግክ በዚህ ስፍራ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ድንኳኖች እተክላለሁ” አለው። 5 ገና እየተናገረ ሳለም ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ ከደመናውም “በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው።+ እሱን ስሙት”+ የሚል ድምፅ ተሰማ። 6 ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲሰሙ በፍርሃት ተውጠው በግንባራቸው ተደፉ። 7 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ወደ እነሱ ቀርቦ ዳሰሳቸውና “ተነሱ። አትፍሩ” አላቸው። 8 ቀና ብለው ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ሌላ ማንንም አላዩም።
-
-
ማርቆስ 9:2-8አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
2 ኢየሱስ ከስድስት ቀን በኋላ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ብቻ ይዞ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ወጣ። በፊታቸውም ተለወጠ፤+ 3 ልብሱ በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ልብስ አጣቢ አጥቦ ሊያነጣው ከሚችለው በላይ እጅግ ነጭ ሆኖ ያንጸባርቅ ጀመር። 4 ደግሞም ኤልያስና ሙሴ ታዩአቸው፤ ከኢየሱስም ጋር እየተነጋገሩ ነበር። 5 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “ረቢ፣ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው። ስለዚህ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ድንኳኖች እንትከል” አለው። 6 እርግጥ፣ በጣም ስለፈሩ ምን ማለት እንዳለበት አላወቀም ነበር። 7 ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም “የምወደው ልጄ ይህ ነው።+ እሱን ስሙት”+ የሚል ድምፅ መጣ።+ 8 ከዚያም ድንገት ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንም አብሯቸው አልነበረም።
-