-
ማርቆስ 9:2-8አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
2 ኢየሱስ ከስድስት ቀን በኋላ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ብቻ ይዞ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ወጣ። በፊታቸውም ተለወጠ፤+ 3 ልብሱ በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ልብስ አጣቢ አጥቦ ሊያነጣው ከሚችለው በላይ እጅግ ነጭ ሆኖ ያንጸባርቅ ጀመር። 4 ደግሞም ኤልያስና ሙሴ ታዩአቸው፤ ከኢየሱስም ጋር እየተነጋገሩ ነበር። 5 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “ረቢ፣ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው። ስለዚህ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ድንኳኖች እንትከል” አለው። 6 እርግጥ፣ በጣም ስለፈሩ ምን ማለት እንዳለበት አላወቀም ነበር። 7 ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም “የምወደው ልጄ ይህ ነው።+ እሱን ስሙት”+ የሚል ድምፅ መጣ።+ 8 ከዚያም ድንገት ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንም አብሯቸው አልነበረም።
-
-
ሉቃስ 9:28-36አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
28 በመሆኑም ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን ያህል በኋላ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ለመጸለይ ወደ ተራራ ወጣ።+ 29 እየጸለየም ሳለ የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ነጭ ሆኖ አንጸባረቀ። 30 እነሆም ሁለት ሰዎች ይኸውም ሙሴና ኤልያስ ከእሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር። 31 እነሱም በክብር ተገልጠው፣ በኢየሩሳሌም ስለሚፈጸመውና ከዚህ ዓለም ተለይቶ ስለሚሄድበት ሁኔታ ይነጋገሩ ጀመር።+ 32 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስና አብረውት የነበሩት እንቅልፍ ተጫጭኗቸው ነበር፤ ሙሉ በሙሉ ሲነቁ ግን የኢየሱስን ክብር እንዲሁም አብረውት የቆሙትን ሁለት ሰዎች አዩ።+ 33 ሰዎቹ ከኢየሱስ ተለይተው ሲሄዱ ጴጥሮስ ኢየሱስን “መምህር፣ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው። ስለዚህ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ድንኳኖች እንትከል” አለው፤ ምን እየተናገረ እንዳለ አላስተዋለም ነበር። 34 ይህን እየተናገረ ሳለ ግን ደመና መጥቶ ጋረዳቸው። ደመናው ሲሸፍናቸው ፍርሃት አደረባቸው። 35 ከዚያም ከደመናው “የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው።+ እሱን ስሙት”+ የሚል ድምፅ መጣ።+ 36 ድምፁም በተሰማ ጊዜ ኢየሱስን ብቻውን ሆኖ አዩት። እነሱም ዝም አሉ፤ ያዩትንም ነገር በዚያን ወቅት ለማንም አልተናገሩም።+
-