ወደ ላይ የመውጣት መዝሙር።
132 ይሖዋ ሆይ፣ ዳዊትን፣
የደረሰበትንም መከራ ሁሉ አስታውስ፤+
2 ለይሖዋ እንዴት እንደማለ፣
ኃያል ለሆነው ለያዕቆብ አምላክ እንዴት እንደተሳለ አስብ፦+
3 “ወደ ድንኳኔ፣ ወደ ቤቴ አልገባም።+
ወደ መኝታዬ፣ ወደ አልጋዬ አልወጣም፤
4 ዓይኖቼ እንዲያንቀላፉ፣
ሽፋሽፍቶቼም እንዲያሸልቡ አልፈቅድም፤
5 ይህም ለይሖዋ ስፍራ፣
ኃያል ለሆነው የያዕቆብ አምላክም ያማረ መኖሪያ እስከማገኝ ድረስ ነው።”+
6 እነሆ፣ በኤፍራታ+ ስለ እሷ ሰማን፤
በጫካ በተሞላው ምድር አገኘናት።+
7 ወደ መኖሪያው እንግባ፤+
በእግሩ ማሳረፊያ ፊት እንስገድ።+
8 ይሖዋ ሆይ፣ ተነስ፤
አንተና የብርታትህ ታቦት፣+ ወደ ማረፊያ ስፍራህ ሂዱ።+
9 ካህናትህ ጽድቅን ይልበሱ፤
ታማኝ አገልጋዮችህም እልል ይበሉ።
10 ለአገልጋይህ ለዳዊት ስትል፣
የቀባኸውን ሰው ገሸሽ አታድርግ።+
11 ይሖዋ ለዳዊት ምሏል፤
የገባውን ቃል ፈጽሞ አያጥፍም፦
“ከዘሮችህ መካከል አንዱን
በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁ።+
12 ወንዶች ልጆችህ ቃል ኪዳኔንና
የማስተምራቸውን ማሳሰቢያዎች ቢጠብቁ፣+
የእነሱም ልጆች
ለዘላለም በዙፋንህ ላይ ይቀመጣሉ።”+
13 ይሖዋ ጽዮንን መርጧታልና፤+
የራሱ መኖሪያ እንድትሆን ፈልጓል፤+ እንዲህም ብሏል፦
14 “ይህች ለዘላለም ማረፊያ ስፍራዬ ነች፤
በእሷ እኖራለሁ፤+ ይህ ምኞቴ ነውና።
15 የተትረፈረፈ የምግብ አቅርቦት እንዲኖራት በማድረግ እባርካታለሁ፤
ድሆቿን እህል አጠግባለሁ።+
16 ካህናቷ መዳንን እንዲለብሱ አደርጋለሁ፤+
ታማኝ ሕዝቦቿም እልል ይላሉ።+
17 በዚያ የዳዊትን ብርታት እጨምራለሁ።
ለቀባሁት አገልጋዬ መብራት አዘጋጅቻለሁ።+
18 ጠላቶቹን ኀፍረት አከናንባለሁ፤
በራሱ ላይ ያለው አክሊል ግን ያብባል።”+