ከኤድስ የከፋ ነገር
“ምርመራው በሽታው እንዳለብህ አረጋግጧል። ኤድስ ይዞሃል።” ስልኩን ስዘጋው የመረመረኝ ሐኪም የተናገራቸው እነዚህ ቃላት በጭንቅላቴ ውስጥ አቃጨሉብኝ። ይህ የሆነው ባለፈው ዓመት አንድ ቀን ነበር። የአምላክን ምክር ሰምቼ ተግባራዊ አድርጌው ቢሆን ኖሮ ይህ ባልደረሰብኝ ነበር!
በዋሽንግተን ክፍለ ሀገር ውስጥ የይሖዋ ምስክር ሆኜ ነበር ያደግሁት። ወላጆቼ አምላክ የሚፈልግብንን ነገሮች በሚገባ አሳውቀውኝ ነበር። ስለዚህ በልጅነቴ ካገኘሁት ሥልጠና በጣም ተቃራኒ በሆነ መንገድ መኖር ስጀምር ብዙ ሰዎች እጅግ ተገርመው ነበር።
በትምህርት ቤት ውስጥ ባሉ ልጆች መወደድ በጣም የምመኘው ነገር ሆነ። በነሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ያላደረግሁት ጥረት አልነበረም። ሙከራዬ ሁሉ ሳይሳካልኝ ስለቀረ 15 ዓመት ሲሆነኝ ሁሉም ነገር ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ ታየኝ። እንዲያውም ራሴን ልገድል ሞክሬ ነበር፤ ግን ሳይሳካልኝ ቀረ።
ሁኔታውን የሚያሻሽልልኝ መስሎኝ ትንባሆና ማሪዋና ማጨስ ጀመርኩ። ግን አላሻሻለልኝም። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የይሖዋን ድርጅት ለመተውና ደስታ የሚገኝበት ሌላ ቦታ ለመፈለግ ወሰንኩ። ለትምህርት ቤት ጓደኞቼ ከእንግዲህ ወዲያ የይሖዋ ምስክር አይደለሁም ብዬ ነገርኳቸው። እነሱም ጥሩ ነው አሉኝ።
ሥነ ምግባር የጎደለውና ያልተረጋጋ ኑሮ
ውሎ አድሮ ሥራ አገኘሁ። እንዲሁም በርካሽ ዋጋ ኪራይ በሚገኝበት ሰካራሞችና ሴተኛ አዳሪዎች በሚኖሩበት ሰፈር ውስጥ አንድ አፓርታማ ተከራየሁ። እነሱም አጭበርብሮ ገንዘብ ማግኘት እንዴት ቀላል እንደሆነ ይነግሩኝ ጀመር። በነሱ እርዳታ ብዙም ሳልቆይ እኔም ዘዴውን ለመድኩት። በሁሉም ሰው መወደድና መደሰት የምፈልግ ሰው ነበርኩ፤ አሁን ግን የማንም መጠቀሚያ የሆንኩና በጣም የተከፋሁ ሰው ሆንኩ።
ወደ ቤቴ ተመልሼ ሁሉን ነገር እንደገና በመጀመር ሁኔታዬን ለመለወጥ ፈለግሁ። ወላጆቼና የበፊቱ ኑሮዬ ናፈቁኝ። ስለዚህ ይሖዋ እንዲረዳኝ ጸለይኩ። የከበደኝ ነገር ወደ ወላጆቼ ሄጄ ይቅርታ እንዲያደርጉልኝ መጠየቁ ነበር። ምስጋና ይግባቸውና ልባቸው ይቅርታ ለማድረግ ፈቃደኛ ሆነ።
ክርስቲያን ሽማግሌዎች አነጋገሩኝና ወደ ጉባኤ ለመመለስ ያለኝን ምኞት ገለጽኩላቸው። ይህ ለነሱም ሆነ ለኔ ቀላል አልነበረም። ዕፅ መውሰዴ ካመጣብኝ ችግር ሌላ ከባድ የአባለዘር በሽታም ነበረብኝ። የመረመረኝ ሐኪም ወደ ሐኪም ቤት ሳልሄድ አንድ ወር ብቻ እንኳን ቆይቼ ቢሆን ኖሮ እሞት እንደነበረ ነገረኝ። በራሴ ላይ ምን ዓይነት ጣጣ ነው ያመጣሁት!
ከጊዜ በኋላ ከውገዳ ተመለስኩ። እንዲያውም ከጎረቤት ጉባኤ አንዲት ወጣት አገባሁ። ነገሮች እየተሻሻሉ ሄዱ። እኔ ግን አሁንም ቢሆን የይሖዋን ፍቅር አላደነቅሁትም። ብርታት ለማግኘት በይሖዋ ላይ በመመካት ፈንታ ነገሮችን እኔው ራሴ ለመሥራት እሞክር ነበር።
ሁለት ዓመት ከማይሞላ ጊዜ በኋላ በጾታ ብልግና ምክንያት ከሚስቴ ጋር ተፋታሁ፤ እንዲሁም ተወገድኩ። ከአንዳንድ ዓለማውያን ጋር መዋል ጀምሬ ነበር። በመጀመሪያ ላይ ምንም ጉዳት የማያስከትል ይመስል ነበር፤ ይሁን እንጂ “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” የሚለው የማይለወጠው ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስጠንቀቂያ ትክክል ሆኖ ተገኘ።—1 ቆሮንቶስ 15:33
እንደገና ወደ መጥፎ ድርጊት መዘፈቅ
ካለሁበት ርቄ ከሄድኩ ቤተሰቤን ያን ያህል አልጎዳም ብዬ አሰብኩ። በሳን ፍራንሲስኮ ካሊፎርኒያ ውስጥ ሥራና መኖሪያ ለማግኘት ምንም አልተቸገርኩም። አንድ የአደንዛዥ ዕፅ ነጋዴ ዕፅ በማከፋፈል ሥራ እንድቀጠር ጠየቀኝ። የመጡትን ‘አዲስ የአደንዛዥ ዕፅ ዓይነቶች’ ሁሉ በመውሰድ በነፃ ከሚሞክርለት የተመረጠ ቡድን መሐል ነበርኩ። አሁን ደግሞ በሌላ መንገድ ታዋቂ ሆንኩ። የሚያውቁኝ ሁሉ (ብዙ የሚያውቁኝ ሰዎች ነበሩ) ዕፅ እንዳለኝ ያውቃሉ። በመንገድ ላይ፣ ቡና ቤት ውስጥ፣ ሥራ ቦታም ሳይቀር አንድ ነገር ለመግዛት ወደኔ ይመጡ ነበር።
ከዚህም ሌላ በጾታ ብልግና ውስጥ ለመዘፈቅ ጊዜ አልፈጀብኝም፤ ይህ እንደተወደድኩ እንዲሰማኝ የሚያደርገኝ መንገድ ነበረ። ከፍተኛ ተወዳጅነትም ነበረኝ። በጾታ ግንኙነት በመጠቀም ሌሎች ሰዎች የምፈልገውን እንዲያደርጉልኝ የሚያስችለኝን ብልሃት ተማርኩ። ለብዙ ዓመታት በዚህ ዓይነት ኖርኩ።
አንድ ጊዜ ከመጠን ያለፈ ከፍተኛ ትኩሳት ይዞኝ በጣም ደክሜ እንደነበር በደንብ ትዝ ይለኛል። የሚመረምረኝ ሐኪም በሽታዬ ምን እንደሆነ አላወቀም። ከጊዜ በኋላ ትኩሳቱ ለቀቀኝ። እስከ ሦስት ዓመት ድረስ ምን እንደያዘኝ ላውቅ አልቻልኩም ነበር።
በዚህ ጊዜ ውስጥ አጋንንትም ያስቸግሩኝ ጀመር። እንዲያውም አንድ ጊዜ ጥቃት አድርሰውብኝ ነበር። ጋኔኑ ሰውነቴ ውስጥ ሊገባብኝ እየሞከረ እንዳለ ተሰማኝ። አንድም ቃል ለመተንፈስ እንዳልችል ይታገለኛል። ሞክሬ ሞክሬ በመጨረሻ “ይሖዋ እርዳኝ!” ብዬ ለመጮህ ቻልኩ። ጋኔኑ ወዲያውኑ ሄደ።
ምን እንደተሰማኝ ገምቱ! በጾታ ብልግና የተጨማለቀ ኑሮ እየኖርኩና ለራሴ ብቻ እያሰብኩ እያለሁ ይሖዋ እንዲረዳኝ ለመጣራት ግን ደፈርኩ! በጣም አሳፈረኝ። ይሖዋ ይረዳኛል ብዬ እንዴት ልገምት እችላለሁ? ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ ገባሁ። አንድ ሰው እንዲገድለኝ በመፈለግ ሆነ ብዬ ሕይወቴን አደጋ ላይ እጥል ጀመር።
የመለወጥ ፍላጎት
አንድ ቀን ከጓደኞቼ ጋር ግብዣ ላይ እያለን ስለ ዓለም ጉዳዮች መወያየት ጀመርን። ስለ ወደፊቱ ሁኔታ ምን ታስባለህ? ብለው ሲጠይቁኝ ሳላውቀው አምላክ ለምድርና ለሕዝቦቹ ያለውን ዓላማ ነገርኳቸው። በጣም ተገረሙ። አንደኛው ግን በጣም ተናደደና ግብዝ ነህ አለኝ። ፍጹም ትክክል ነበር። ሁለት ዓይነት ኑሮ ነበር የምኖረው። በልቤ ግን ብቸኛው አዳኛችን ይሖዋ መሆኑንና ድርጅቱም ሊኖርበት የሚገባ ብቸኛ ቦታ መሆኑን አውቅ ነበር።
በዚህ ጊዜ ገደማ የኔና ከኔ ጋር የነበሩት የሌሎቹ ሕይወት መለወጥ ጀመረ። ብዙዎቹ ጓደኞቼ ኤድስ ይዟቸው አልጋ መያዝ ጀመሩ። በአንድ ወቅት ጤነኛ የነበሩ ሰዎች ቀስ በቀስ መንምነው ሲሞቱ ማየት ይከብድ ነበር። እነሱን ማጽናናት አቃተኝ። የተሻለ የሕይወት መንገድ እንዳለ ማወቄ ደግሞ ይበልጥ የሚያበሳጭ ነበር። በዚያን ጊዜ ወደ ይሖዋ ፍቅር መመለስ እንደምፈልግ አወቅሁ። ግን እንዴት?
ይሖዋ እንዲረዳኝ መጸለይ ጀመርኩ። መጸለይ ይከብደኝ ነበር። ያሳፍረኛል፤ ቆሻሻ እንደሆንኩም ይሰማኛል። አንድ ቀን ስልክ ተደወለልኝ። አክስቴ ነበረች፤ ካየኋት ከዘጠኝ ዓመታት በላይ አልፏል። መጥታ ልትጠይቀኝ እንደምትፈልግ ነገረችኝ። ምንም እንኳን የወላጆቼ ዓይነት ሃይማኖት ባይኖራትም ሕይወቴን ለመለወጥና እንደገና የይሖዋ ምስክር ለመሆን የምፈልግ መሆኑን ነገርኳት። ከልቤ መሆኑን ስለተረዳች ልትረዳኝ ፈለገች።
ለመመለስ የፈጀብኝ ረጅም ጊዜ
አክስቴ መንፈሴ እስኪረጋጋ ድረስ ከእርሷ ጋር እንድኖር ጋበዘችኝ። ይህ ሊረዳኝ ይችል እንደሆነ ስትጠይቀኝ እዚያው ቆሜ አለቀስኩ። ያስፈልገኝ የነበረው የመውጫ መንገድ ይህ እንደሆነ አውቅ ነበር። ስለዚህ የበፊት ጓደኞቼን ትቼ ሄድኩ። ቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ቀላል አልነበሩም፤ ቢሆንም ይሖዋ እንድቋቋማቸው እንደሚረዳኝ እተማመን ነበር። ሚልክያስ 3:7 እዚህ ላይ የሚሠራ ይመስለኛል:- “ወደ እኔ ተመለሱ፣ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።”
ከሷ ጋር መኖር እንደጀመርኩ ወዲያውኑ ሽማግሌዎችን አነጋገርኩ። ስለ ራሴ ሁኔታ እንዲሁም ይሖዋን ማገልገል በእውነት እንደምፈልግ ነገርኳቸው። እነሱም ሆኑ እኔ በምንም መንገድ በአንድ ጀምበር ከውገዳ ልመለስ እንደማልችል እናውቅ ነበር። ከዚህም በፊት እምነት የሚጣልብኝ ሆኜ አልተገኘሁም። አሁን ግን ቆርጫለሁ። ይሖዋ እንዲረዳኝ ሌት ከቀን ያለማቋረጥ ጸለይኩ። ደካማ ነኝ ብዬ አስብ ነበር። እውነትም የማይረዳኝ ባይኖር ደካማ ሳልሆን አልቀርም። ይሖዋ ሲረዳችሁ ግን የሚያስገርም ብርታት ይሰማችኋል።
በየቀኑ የሚያጋጥሙኝን ችግሮች ለመወጣት ስል ለረጅም ዓመታት ዕፅ እወስድ ነበር። አሁን ግን ያለ ዕፅ መኖር ነበረብኝ። እፈራ ነበር። ብዙ ሰው ባለበት አካባቢ መሆን ያስፈራኝ ጀመር። እዚያ አካባቢ ለረጅም ሰዓት ከቆየሁ ደግሞ ያመኝ ነበር። በዚያ ላይ ሲጋራ ለማቆም እየሞከርኩ ነበር። በፊት ግን በቀን አራት ፓኮ ሲጋራ አጨስ ነበር። እነዚህን ሁሉ ነገሮች እንድቋቋም የረዳኝ ብቸኛው ነገር ጸሎትና እየወሰድኩት ያለሁት የመስተካከል እርምጃ ይሖዋን እንደሚያስደስተው ሁልጊዜ ማስታወሴ ነበር። አዘውትሬ በስብሰባዎች ላይ በመገኘቴ መጽናናትና ሰላም አገኘሁ። ስለተወገድኩ ማንንም ማነጋገር የማልችል ብሆንም እዚያ ያሉት የወደፊት መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ፍቅርና ሞቅ ያለ መንፈስ ይሰማኝ ነበር።
በመጨረሻም አኗኗሬን ከለወጥኩ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ይሖዋ ተስማሚ በሆነው ጊዜ አገልጋዮቹ ከውገዳ ወደ ድርጅቱ እንዲመልሱኝ ገፋፋቸው። እርሱ መልሶ ሊቀበለኝ የሚችልበትን ትክክለኛውን ጊዜ ያውቃል። ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አያደርግም። ከዚያ በኋላ ጥቂት ጊዜ ቆይቶ ሐኪሙ ስልክ ደወለልኝና ኤድስ እንዳለብኝ ነገረኝ። ገላትያ 6:7 የሚለው እውነት ነው:- “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና።”
በመጀመሪያ ላይ አለቀስኩ። በአእምሮዬ ውስጥ ብዙ ዓይነት ሐሳቦች መጡብኝ። በፊት የፈጸምኳቸው ነገሮች በአንድ ጊዜ ታዩኝ። ይህ በሽታ በሰው ላይ ምን እንደሚያደርስና ሌሎች በበሽታው ለተያዘው ሰው የሚኖራቸውን አመለካከት ራሴው አይቸዋለሁ። ዓለም የሚሰጠኝ ነገር አለ ብዬ በመጠበቄ እንዴት ተሞኝቼ ኖሯል! ውድ የሆነውን ጊዜዬን ምን ያህል አባከንኩት!
ኤድስ ቢይዘኝም ያለኝ እርካታ
በዓለማዊ ጓደኞቻቸው ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት በመመኘት እኔ በነበርኩበት ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች እንዳሉ አውቃለሁ። የአምላክን ምክር ችላ ካላችሁት እኔ በዓለም ሳለሁ የደረሰብኝ ዓይነት ነገር አይደርስብንም ብላችሁ በማመን እባካችሁ አትሞኙ። የሰይጣን ዘዴዎች የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ውጤቱ ግን ምን ጊዜም ያው ነው።
ይሁን እንጂ ምንም ያህል መጥፎ የነበራችሁ ብትሆኑ ወይም ምንም ዓይነት ስህተት ብትሠሩ ይሖዋ አምላክን ከልባችሁ ልታስደስቱት ከፈለጋችሁና አጥብቃችሁ በመጸለይ ወደ እርሱ ከተመለሳችሁ እርሱ አሁንም ቢሆን ይረዳችኋል፤ ይቅርታም ያደርግላችኋል።
የደረሰብኝ ነገር ሁሉ አሁን ያን ያህል አያስጨንቀኝም። እርግጥ አልፎ አልፎ እተክዛለሁ፤ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ግን እረሳዋለሁ። አሁን የሚያሳስበኝ ይሖዋን የማስደሰቱ ነገር ብቻ ነው። እውነተኛው የደስታዬና የመጽናኛዬ ምንጭ እርሱ ነው። እርሱን ለማስደሰት የምችለውን ሁሉ ካደረግሁ በደንብ ይንከባከበኛል፤ እንዲሁም ይወደኛል።
ወደ ይሖዋ ሕዝቦች በመመለሴ በጣም አመስጋኝ ነኝ፤ ምክንያቱም ይሖዋ ማንነቱን በአርማጌዶን ከማሳየቱ በፊት ብሞትም እንኳን የትንሣኤ ተስፋ አለኝ። እመኑኝ፤ የይሖዋን ፍቅርና ሞገስ አጥቶ መኖር ከኤድስ እጅግ የከፋ ነገር ነው።—ራሱ እንደጻፈው።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በሌሎች ልጆች መወደድ በጣም የምመኘው ነገር ነበር