የወጣቶች ጥያቄ . . .
ይበልጥ ሀብታም ወደ ሆነ አገር መሄድ ይሻል ይሆን?
ታራ የትውልድ አገሯን ትሪንዳድን፣ ሼይላ ጃማይካን፣ ኤሪክ ደግሞ ሱሪናምን ለቀው ሄደዋል። ሦስቱም ወጣቶች የሄዱት ይበልጥ ሀብታም ወደሆነ አገር ነው። ለምን ይሆን?
“እኛ በትሪንዳድ የምንገኝ ወጣቶች” ስትል ታራ ትገልጻለች “በመጽሔቶች ላይና በቴሌቪዥን የምናያቸው ነገሮች ከፍተኛ ግፊት አሳድረውብናል። ይህም ሳናስበው ስለ ዩናይትድ ስቴትስና ስለ ሌሎች የበለጸጉ አገሮች ካለው እውነታ ውጪ የሆነ አመለካከትና ፍቅር እንዲኖረን አድርጓል።”
የሼይላም ገጠመኝ ከዚህ የተለየ አይደለም። “ሥራና የነፃ ትምህርት ለማግኘት ሰፊ አጋጣሚዎች አሉ ተብሎ ይነገር እንደነበረ አስታውሳለሁ።” ይሁን እንጂ እንዲህ ስትል ጨምራ ተናግራለች:- “ለምን እንደሆነ ባላውቅም በእነዚህ አገሮች የነበሩት ሰዎች የተቀረውን ታሪክ ፈጽሞ ጠቅሰውት አያውቁም። ምናልባት በእነዚህ አገሮች ያሉት ሁኔታዎች ያን ያህል የሚወራላቸው አለመሆናቸውን አምኖ መቀበሉ ሐፍረት ሆኖባቸው ሊሆን ይችላል።”
ያም ሆኖ ሰዎች ወደ እነዚህ አገሮች መጉረፋቸውን እንደቀጠሉ ናቸው። በሎስ አንጀለስ ታይምስ ላይ የወጣው ሪፖርት ከ1980 እስከ 1990 ባሉት ጊዜያት ወደ ሌሎች አገሮች የሚሄዱት ሰዎች ቁጥር በእጥፍ የጨመረ መሆኑንና በ2000 ዓመት ላይ ደግሞ እንደገና በእጥፍ ይጨምራል ተብሎ እንደሚታሰብ ያሳያል። በየዓመቱ ከ700,000 በላይ የሆኑ ሰዎች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ይጎርፋሉ። አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ኮትዲቭዋርና ሳውዲ አረቢያ በየዓመቱ እያንዳንዳቸው ከ50,000 በላይ ስደተኞች ይቀበላሉ። ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ ይበልጥ የተደላደለ ኑሮ በመሻት የሚሄዱ ናቸው።
ድሀ ወይም ታዳጊ በሆነች አገር ውስጥ የምትኖር ከሆነ በሀብታም አገር ውስጥ በመኖር ኑሮዬ ሊሻሻል ይችል ይሆን የሚል ጥያቄ መጥቶብህ ይሆናል። ይህ ከባድ ውሳኔ ነው። ታዲያ ጥበብ የተሞላበት ምርጫ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ለመወሰን አትቸኩል
የሱሪናም ተወላጅ የሆነው ኤሪክ እርምጃ ለመውሰድ ከመጣደፍ ይልቅ በቅድሚያ የቻልከውን ያህል ብዙ መረጃዎች መሰብሰብ እንደሚኖርብህ ያምናል። “በሱሪናምም እንኳ” ይላል ኤሪክ “አብዛኛዎቹ ቤተሰቦች በትልልቅ አገሮች የሚኖሩ ዘመዶች አሏቸው፤ ስለ ዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ወቅታዊ የሆነ መረጃ ማግኘትና እውነተኛውን ነገር ማወቅ ይኖርብሃል።”
ውሳኔ ላይ ከመድረስህ በፊት:- “ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል፤ መካሮች በበዙበት ዘንድ ግን ይጸናል” የሚለውን ነጥብ አስታውስ። (ምሳሌ 15:22) ስለዚህ ያሉህን አማራጭ ሁኔታዎች አንስተህ ከወላጆችህ፣ ከክርስቲያን ሽማግሌዎችና ተሞክሮ ካላቸውና ስለ አንተ ከሚያስቡ ሌሎች ሰዎች ጋር ጉዳዩን በግልጽ ተወያይበት።
የሰማኸውን ሁሉ አትመን
ራቅ ባሉ ቦታዎች የሚገኙ የበለጸጉ አገሮችን በማወደስ የሚነገሩ ወሬዎችን በምትሰማበት ጊዜ ትንሽ ጤናማ የሆነ ጥርጣሬ ማሳየቱ አይከፋም። አንድ ጥበብ ያዘለ ምሳሌ “ሞኝ ሰው የሚነግሩትን ሁሉ አምኖ ይቀበላል፤ ብልጦች ግን እርምጃቸውን በጥንቃቄ ይመለከታሉ” ይላል።—ምሳሌ 14:15 የ1980 ትርጉም
በጃማይካ ትኖር የነበረችው ሼይላ እንዲህ ብላለች:- “ላከናውናቸው ከምችላቸው ነገሮች ሁሉ የተሻለው ነገር ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መሄድ እንደሆነ የእንግሊዝኛ አስተማሪዬ አጥብቆ ነገረኝ። አንዳንድ ትልልቅ ሰዎች ወደ ካናዳ፣ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ወይም ወደ እንግሊዝ ከሄድኩ ማንኛውንም የሥራ መስክ ብመርጥም እንኳ ኑሮዬን ማሻሻል እንደምችል ነግረውኛል። በአጭሩ፣ ይህን የመሰለ ጥሩ አጋጣሚ አለመቀበል ሞኝነት እንደሆነ ገለጹልኝ።”
ታዲያ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መሄዷ ጠቅሟታልን? “ኑሮዬ በብዙ መንገድ ተሻሽሎልኛል፤ ሆኖም በጃማይካ የቀሩት ጓደኞቼም ኑሯቸውን ማሻሻል ችለዋል። አብዛኛውን ጊዜ አንዱን ችግር በሌላው ትለውጣለህ። የምትኖርበት ቦታ በራሱ ትልቅ ለውጥ አያመጣም።”
ከትሪንዳድ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሄደችው ታራ በዚህ ትስማማለች:- “ሰዎች የበለጸጉ አገሮችን ለትምህርት፣ ለሥራ፣ ብዙ ገንዘብ ለማግኘትና በተሻሉ ሁኔታዎች ሥር ለመኖር ጥሩ አጋጣሚ የሚያስገኙ አገሮች እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። አሁን ግን አገራቸውን ለቀው የሄዱት ብዙዎቹ ሰዎች በየትም ሥፍራ ያሉት ሁኔታዎች እየተባባሱ እንዳሉ እየተገነዘቡ ነው። አንዳንዶቹም ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰዋል።”
ትርፉንና ኪሳራውን አስላ
ሚዛናዊ ውሳኔ ለመወሰን እንድትችል በሌሎች አገሮች የተትረፈረፈ ሀብት እንዳለ ስለሚገልጹት የሚያጓጉ ሪፖርቶች ብቻ ማሰብ የለብህም። ወደ ሌላ አገር መሄድ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ሊያስከትል የሚችለውን ትርፍና ኪሳራ አስላ።
ለምሳሌ በምትኖርበት ቦታ ያለው ኢኮኖሚ መጥፎ ገጽታ ይኖረው ይሆናል። ይሁን እንጂ በዚያው በትውልድ አገር ውስጥ ሥራ ማግኘት የሚቻልባቸው አጋጣሚዎች የሉምን? “በትውልድ አገሬ” ትላለች ታራ “በተለይ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ለሌላቸው ሰዎች ሥራ የማግኘቱ ዕድል የመነመነ ነው።” ስለዚህ እሷ ወደ ሌላ አገር ስትሄድ ወንድሞቿ ግን እዚያው ቀሩ። “ሁለቱ ታናናሽ ወንድሞቼ የቤት ዕቃ፣ የሶፋና የመኪና ወንበር ጥገና ኮርስ ወሰዱ። በአሁኑ ጊዜ በፋብሪካዎች ውስጥ ይሠራሉ፤ሥራቸውን ከሚወዱ ሰዎችም ብዙ የግል ሥራ ያገኛሉ። እንዲያውም እኔ እዚህ ‘ጥሩ አጋጣሚዎች ባሉበት አገር’ ሆኜ ከምሠራው የተሻለ በትውልድ አገራቸው ሆነው ሳይሠሩ አይቀሩም።”
ወደ ሌላ አገር ከሄድክ አንዳንድ ከባህል ጋር የሚጋጩ ነገሮች ሊያጋጥሙህ አልፎ ተርፎም እንደ ውድ ነገር አድርገህ በያዝካቸው የግብረ ገብነት መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ኃይለኛና የማያቋርጥ ጥቃት ሊደርስባቸው ይችላል። ወደ ሌላ አገር መሄድ እንዲህ ዓይነት ዋጋ ሊከፈልለት ይገባልን? ከዚህም በተጨማሪ በበለጸጉ አገሮች ፍቅረ ነዋይ በሰፊው እየተዛመተ ነው። ይህ አንተን በመንፈሳዊ ምን ያህል ይነካህ ይሆን?
ዔሳው ከሠራቸው ስህተቶች መማር
ውሳኔዎች የሚያስከትሉትን ትርፍና ኪሳራ በማስላት ረገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው ዔሳው ከባድ ችግር ነበረበት። እጅግ አንገብጋቢ የሆኑትን ጉዳዮች ይኸውም መንፈሳዊነቱንና ቤተሰቡን በተደጋጋሚ ግምት ውስጥ ሳያስገባ ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ከወሰዳቸው ትልልቅ ውሳኔዎች አንዳንዶቹ ትልቅ ውድቀት አምጥተውበታል።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ያስጠነቅቃል:- “ስለ አንድ መብል በኩርነቱን እንደሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች [ቅዱስ ነገሮችን የሚያቃልል አዓት] ሰው እንዳይሆን ተጠንቀቁ።” (ዕብራውያን 12:16) ይህ የብኩርና መብት ቅዱስ ነገር ነበር። አምላክ የዔሳው ቤተሰብ ለሰው ዘሮች ሁሉ መዳን ቁልፍ የሆነው መሲሕ የሚመጣበት የዘር መስመር መሆን የሚችልበትን አጋጣሚ ፈጥሮ ነበር። (ዘፍጥረት 22:18) ሆኖም “ዔሳው ብኩርናውን አቃለላት።” ብኩርናውን ለአንድ የምስር ወጥ መብል ሲሸጥ ምንም አላንገራገረም! (ዘፍጥረት 25:30–34) ከሁሉ የላቀው ቅዱስ ንብረትህ ከፈጣሪህ ጋር ያለህ ዝምድና ነው። በምንም ነገር አትለውጠው፣ እንደ ትንሽ ነገር አትቁጠረው ወይም ለየትኛውም ቁሳዊ ጥቅም ብለህ አደጋ ላይ አትጣለው።—ማርቆስ 12:30
ከጊዜ በኋላ ዔሳው ያደገበትን ቀዬ ለቆ ወደ ሌላ ምድር በመሄድ ሁለት ኬጤያውያን ሴቶችን አገባ። እነዚህ ጋብቻዎች ከአንዳንድ ምክንያቶች አንፃር ሲታዩ ተገቢ ሊመስሉ ይችላሉ፤ ይሁን እንጂ ሴቶቹ የዔሳውን ወላጆች የይስሐቅንና የርብቃን አምላክ ስለማያመልኩ በመንፈሳዊ ረገድ ችግሮችን የሚያመጡ ብቻ ነበሩ። እነዚህ ሚስቶች ወላጆቹን “ያሳዝኑ ነበር።”—ዘፍጥረት 26:34, 35
ይበልጥ ሀብታም ወደሆነ አገር መግባት የሚያስችል ፈቃድ ለማግኘት ሲሉ ብቻ ማግባት ለወጣቶች ያልተለመደ ነገር አይደለም። 4,000 ሰዎች በትዳር ጓደኝነት ከህንድ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንደገቡ ተዘግቧል፤ በግምት 10,000 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ እንዲሁ ለማድረግ እየተጠባበቁ ነው። ይሁን እንጂ ጋብቻ ከአምላክ የተሰጠ ውድ ስጦታ ነው። እንዲያው የአንድን አገር ድንበር ለማለፍ ብቻ እንደሚያገለግል ትኬት አድርጎ በመጠቀም ሊራከስ አይገባውም። ‘ከማያምን ሰው ጋር በማይመች አካሄድ ብትጠመድ’ ይህ ሁኔታ ይሖዋንና ታማኝ የቤተሰብህን አባላት ምን ያህል ቅር እንደሚያሰኝም አስብ።—2 ቆሮንቶስ 6:14
ውሳኔህን በተሻለ መንገድ ሥራበት
ውሳኔህን በደንብ የመከተሉ ጉዳይ ከራሱ ከውሳኔው የበለጠ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ባለህበት አገር ለመቅረትም ሆነ ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ብትወስን ቁም ነገሩ ያለው ውሳኔህን ጥቅም ባለው መንገድ የምትሠራበት በመሆኑ ላይ ነው።
ባለህበት አገር ከቀረህ:- ወደ ሌላ አገር የሄዱትን ሰዎች አትተች። ውሳኔያቸው የራሳቸው ኃላፊነት ነው። (ሮሜ 14:4፤ ገላትያ 6:4, 5) በትውልድ አገርህ ብቻ ሊገኙ የሚችሉትን ውብ ነገሮችና ጥቅሞች ማድነቅን ተማር። ለሕዝቡ ከፍተኛ ፍቅር ማሳየትንና ከኑሮ ጋር የሚያደርጉትን ትግልና የሚገጥሟቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች በእነርሱ ቦታ ሆኖ የመመልከትን ባሕርይ አዳብር።
ወደ ሌላ አገር ከሄድክ:- አዲስ ልማዶችና ምናልባትም አዲስ ቋንቋ የምትማር እንደመሆንህ መጠን ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች በጥበብ ወስን። ቀደም ሲል አስፈላጊ ያልነበሩ ቁሳዊ ነገሮችን ለማካበት ስትል ለረጅም ሰዓታት በመሥራት አትጠመድ። አለበለዚያ ብዙም ሳይቆይ ለመንፈሳዊ ነገሮች ጊዜ ልታጣ ትችላለህ።
“በአሁኑ ጊዜ ባለው ዓለም ውስጥ ሥራ ማግኘት በጣም አስፈላጊ ነው” በማለት ሼይላ የሚሰማትን ሳትሸሸግ ገልጻለች። “ይሁን እንጂ ቤተሰብ፣ ጓደኞችና መንፈሳዊ ጉዳዮች ከዚያ የበለጠ አስፈላጊ ናቸው። ሌላው ነገር ሁሉ ሲያልፍ እኛን ደግፈው ሊያቆሙ የሚችሉት እነዚህ ናቸው።” መጽሐፍ ቅዱስ “በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና” ሲል ጥበባዊ ምክር ይሰጠናል። (1 ቆሮንቶስ7:31) በእርግጥም በኑሯቸው የሚሳካላቸው ሰዎች ለሥራና ለገንዘብ ተገቢውን ቦታ የሚሰጡ ይኸውም ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገርና መንፈሳዊ ነገሮችን ለመከታተል ቅድሚያ የሚሰጡ ናቸው።
አዲስ ጓደኞችን በጥንቃቄ ምረጥ። ኤሪክ “ገንቢ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ ከሚከተሉ ጓደኞች ጋር ግንኙነት መስርት” ይላል።
የግድ የሚያስፈልጉህን ነገሮች አትዘንጋ
ደስታ ለማግኘት የሚያስፈልጉን ነገሮች አይለወጡም። “የትም ቦታ እንኑር” ትላለች ሼይላ “ይሖዋ ከእኛ የሚፈልጋቸው ነገሮች ምን ጊዜም ያው ናቸው።” እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው? ኢየሱስ ቁልጭ ባለ አነጋገር አስቀምጦታል:- “ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው።” በቂ ምግብና ልብስ ስለማግኘት “አትጨነቁ።” “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።”—ማቴዎስ 5:3 አዓት፤ 6:31, 33
በእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች እየተመራህ መመላለስህ በየትኛውም አገር ውስጥ የተሻለ ኑሮ እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሀብታም አገሮች ካላቸው ትክክለኛ ገጽታ የበለጠ ማራኪ መስለው ሊታዩ ይችላሉ