የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g94 10/8 ገጽ 11-12
  • ትንባሆና ሳንሱር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ትንባሆና ሳንሱር
  • ንቁ!—1994
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ሕይወት እንደ ጭስ እየበነነ ነው
    ንቁ!—1999
  • አገርዎ ዋነኛ ዒላማ ተደርጎ ይሆን?
    ንቁ!—1994
  • የትምባሆ ጠበቆች በሞቃት አየር የተሞሉ ባሉኖቻቸውን መተኮስ ጀምረዋል
    ንቁ!—1999
  • ትንባሆ እና ጤንነትህ
    ንቁ!—1994
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1994
g94 10/8 ገጽ 11-12

ትንባሆና ሳንሱር

“ሳንሱር ይቁም! የማስተዋወቅ ነጻነትን የሚጨምረው የመናገር ነጻነት ልንከባከበው የሚገባ መብት ነው። በሲጋራ ማስታወቂያ ላይ እገዳ እንዲደረግ ብዙሐኑ አሜሪካውያን አይደግፉም።”—​“አስተያየታቸውን በስልክ እንዲሰጡ ከተደረጉት 1,500 ሰዎች በተገኘ ብሔር አቀፍ ጥናት” ላይ የተመሠረተ ጥር 1989 በአንድ ጋዜጣ ላይ የወጣ ማስታወቂያ። ታዲያ 1,500 ሰዎች “ብዙሐኑን አሜሪካውያን” ሊወክሉ ይችላሉን?

የትንባሆ አስተዋዋቂዎች ማስታወቂያዎቻቸው ሰዎች ሲጋራ ማጨስ እንዲጀምሩ አይገፋፉም ብለው ይከራከራሉ። ማስታወቂያዎቹ ልዩነት የሚያመጡት በተለያዩት የሲጋራ ዓይነቶች ስርጭት ላይ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ የሴት አጫሾች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ይህን አባባል አጠራጣሪ ያደርገዋል። ቢሆንም የትንባሆ አስተዋዋቂዎች ካላቸው ኃይል የሚመነጭ ሌላ ጎጂ ተጽዕኖ አለ።

በቅርብ ዓመታት የዩናይትድ ስቴትስ የትንባሆ ኩባንያዎች የምግብ ኩባንያዎችን በመግዛትና ትንባሆ የሚለው ቃል ከድርጅታቸው ስም እንዲወጣ በማድረግ ለራሳቸው ከበሬታ የሚያስገኝ ስም አትርፈዋል። በዚህ ምክንያት አሜሪካን ቶባኮ ካምፓኒ ወደ አሜሪካን ብራንድስ፤ አር ጄ ሬይኖልድስ ቶባኮ ካምፓኒ ወደ አር ጄ አር/ናቢስኮ፤ ብራውን ኤንድ ዊልያምሰን ቶባኮ ኮርፖሬሽን ወደ ብራውን ኤንድ ዊልያምሰን ኢንዳስትሪስ ተለውጧል። ታዲያ ይህ የስም ለውጥ ካስከተላቸው ውጤቶች አንዱ ምንድን ነው? በማስታወቂያ ድርጅቶች ላይ የሚኖራቸው ተጽዕኖ እንዲጨምር አድርጓል። እን⁠ዴት?

ከዚህ በፊት የትንባሆ ማስታወቂያ አውጥተው የማያውቁ መጽሔቶች እንኳን ማጨስንና የትንባሆ ምርቶችን የሚነቅፉ ጽሑፎች ለማውጣት ማመንታት ጀምረዋል። እርግጥ፣ የሚቀርባቸው ከትንባሆ ማስታወቂያ የሚገኝ ገቢ ላይኖር ይችላል። ግን የትንባሆ ቱጃሮች የገዟቸውና የምግብና የሌሎች ምርቶች ማስታወቂያ የሚያወጡት ኩባንያዎችስ? ትንባሆ ማጨስ መጥፎ መሆኑን የሚገልጹ ጽሑፎችን ወይም መግለጫዎችን እንዲያወጡ ሲጠየቁ ምን ሊያደርጉ ነው? በራሳቸው ላይ የሳንሱር ገደብ እንዲጥሉ የሚያስገድዳቸው ተጽዕኖ ይደርስባቸዋል።

በዚህ ረገድ ሰኔ 6, 1983 የወጣው የኒውስዊክ እትም ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። ከሰኔ 6 እትም በፊትና በኋላ የወጡ እትሞች ከሰባት እስከ አሥር ገጽ የሚይዝ የሲጋራ ማስታወቂያ አውጥተዋል። የሰኔ 6 ኒውስዊክ ግን 4.3 ገጽ የሚሸፍን “በማጨስ ላይ የተካሄደ ዘመቻ” የሚል አከራካሪ ጽሑፍ አውጥቶ ነበር። በዚህ እትም ላይ ምን ያህል ገጽ የሲጋራ ማስታወቂያ ወጥቶ ነበር? አንድም ማስታወቂያ አልወጣም። ደራሲ ዋይት እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል:- “የሲጋራ ኩባንያዎች ጽሑፉ እንደሚወጣ ሲያውቁ ማስታወቂያቸው እንዳይወጣ ጠየቁ። መጽሔቱ ይህን ጽሑፍ በማውጣቱ ከማስታወቂያ ያገኝ የነበረውን አንድ ሚልዮን ዶላር አጣ።”

ከማስታወቂያ የሚገኘው ገቢ የጋዜጦችና የመጽሔቶች ደመ ሕይወት ነው። የመጽሔቶችና የጋዜጦች አዘጋጆች የትንባሆ ኢንዱስትሪዎችን የሚተቹ ጽሑፎች ከማውጣታቸው በፊት በጥንቃቄ እንደሚያስቡ የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ። ያውም ያወጡ እንደሆነ ነው። አንድ ስለ ጤና የሚጽፉ ሰው “ለምሳሌ ያህል የልብ በሽታ በሚያስከትሉ ምክንያቶች ዝርዝር ውስጥ ማጨስን ባስገባ የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ ከዝርዝሩ መጨረሻ ላይ ያደርገዋል፣ ወይም ጨርሶ ያወጣዋል” ብለዋል። “ዜማውን የሚመርጠው ባለ ዋሽንቱን የቀጠረው ሰው ነው” የሚል የቆየ አባባል አለ። ራስን በራስ ሳንሱር ማድረግ በጊዜያችን በጣም ተስፋፍቷል።

ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል በጥቁሮች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ሁለት መጽሔቶች የትንባሆ ማስታወቂያዎችን ያወጡ በነበሩባቸው ስድስት ዓመታት ውስጥ ማጨስንና ጤናን የሚመለከቱ ጽሑፎች አንድም ጊዜ እንዳላወጡ ዘግቧል። በአጋጣሚ ብቻ የሆነ ነገር ሊሆን ይችላልን? የትንባሆ ማስታወቂያዎችን የሚያወጡ መጽሔቶች ያጎረሳቸውን እጅ ሊነክሱ እንደማይችሉ ግልጽ ነው። በዚህም ምክንያት የማጨስን አደገኛነት ከማጋለጥ ይታቀባሉ።

እነዚህ ስለ ትንባሆ፣ ስለ ማጨስና ስለ ማስታወቂያዎች የተመለከትናቸው ሁኔታዎች ጉዳዩ የብዙ ሰዎችን ጥቅም የሚመለከት መሆኑን እንድንገነዘብ አስችሎናል። ለትንባሆ ገበሬዎች መተዳደሪያቸው ነው። የትንባሆ ቱጃሮችና አሻሻጮች ደግሞ ያገኙ የነበረውን ወፍራም ትርፍ ያስቀርባቸዋል። ለመንግሥታት ከቀረጥ የሚያገኙትን ገቢ ያስቀርባቸዋል። በሚልዮን ለሚቆጠሩ አጫሾች ደግሞ ጤናቸውንና ሕይወታቸውን የሚመለከት ጉዳይ ነው።

አጫሽ ከሆኑ ወይም ማጨስ ለመጀመር እያሰቡ ከሆነ ምርጫው የግልዎ ነው። የዩናይትድ ስቴትስ የትንባሆ ከበርቴዎች ደጋግመው እንደሚያስገነዝቡት ሕገ መንግሥታዊ መብትዎ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ማለት በሳንባ ወይም በጉሮሮ ካንሰር፣ በልብና በደም ዝውውር በሽታዎች፣ በኤምፊዚማ፣ በበርገርስ በሽታ (በገጽ 9 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ይመልከቱ) እና በሌሎች ብዙ ቀሳፊ በሽታዎች ለሞት አደጋ መጋለጥም ሕገ መንግሥታዊ መብትዎ ነው ማለት ነው። በሌላ በኩል ግን ማጨስ ለማቆም የሚፈልጉ ከሆነ እንዴት ለማቆም ይችላሉ? ምን ነገር ያስፈልግዎታል? የሚያስፈልግዎት ለመተው የሚያነሳሳ ጠንካራ ምክንያት ነው።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዩናይትድ ስቴትስ ጤና አጠባበቅ አገልግሎት ኃላፊ የሆኑት ኩፕ ትንባሆ ማጨስ አደገኛ መሆኑን በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል

[ምንጭ]

Public Health Service photo

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ