በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ሕይወት እንደ ጭስ እየበነነ ነው
በመላው ዓለም እጅግ በጣም የደራ ገበያ ካገኙት ሸቀጦች አንዱ ትምባሆ ነው። ቁጥራቸው በጣም ከፍተኛ የሆነ ታማኝ ደንበኞች ያሉት ከመሆኑም በላይ ገበያው በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ይገኛል። ይህ ሁኔታ ያስደሰታቸው ኩባንያዎች ስለሚያጋብሱት ከፍተኛ ትርፍ፣ ስላገኙት የፖለቲካ ተደማጭነትና ልዩ መብት በጉራ ይናገራሉ። አንድ ሊወጡ ያልቻሉት ችግር ብቻ ገጥሟቸዋል። ጥሩ ጥሩ ደንበኞቻቸው እየሞቱባቸው ነው!
ዚ ኢኮኖሚስት እንዲህ ብሏል:- “በመላው ዓለም እጅግ አትራፊ ከሆኑት የፍጆታ ሸቀጦች አንዱ ሲጋራ ነው። ከዚህም በላይ በትክክለኛው አወሳሰድ እየተወሰደ ከተጠቃሚዎቹ መካከል አብዛኞቹን ሱሰኛ የሚያደርግና ብዙውን ጊዜም የሚገድል (በሕግ የተፈቀደ) ሸቀጥ ሲጋራ ብቻ ነው።” በዚህ ምክንያት የትምባሆ ኩባንያዎች ገደብ የሌለው ትርፍ ሲያጋብሱ በደንበኞቻቸው ላይ ግን በጣም ከፍተኛ የሆነ ኪሣራ ይደርሳል። የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል እንደሚለው ከሆነ አሜሪካውያን አጫሾች በማጨሳቸው ምክንያት በየዓመቱ የሚያጡት ዕድሜ ጠቅላላ ድምር አምስት ሚልዮን ዓመት ይደርሳል። ትምባሆ በማጨስ ለሚያሳልፉት ለእያንዳንዱ ደቂቃ አንድ ደቂቃ ያጣሉ ማለት ነው። “420,000 የሚያክሉ አሜሪካውያን በየዓመቱ በማጨስ ምክንያት ይሞታሉ” ይላል ኒውስዊክ መጽሔት። “ሕገ ወጥ በሆኑ ዕፆች ምክንያት ከሚሞቱት አሜሪካውያን 50 ጊዜ እጥፍ ይበልጣል ማለት ነው።”
ሞርታሊቲ ፍሮም ስሞኪንግ ኢን ደቨሎፕድ ካንትሪስ 1950–2000 የተባለው በብሪታንያ የካንሰር ምርምር ድርጅት፣ በዓለም ጤና ድርጅትና በአሜሪካ የካንሰር ማህበር የታተመ መጽሐፍ እንደሚለው በመላው ዓለም በዓመት ሦስት ሚልዮን ሰዎች፣ በእያንዳንዱ ደቂቃ ደግሞ ስድስት ሰዎች በማጨስ ጠንቅ ይሞታሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየውን የትምባሆ አጫሽነት አዝማሚያ በተመለከተ እስከ ዛሬ ከተደረጉት ምርምሮች ሁሉ ይበልጥ ስፋትና ጥልቀት ባለው መንገድ የተካሄደው ይህ ጥናት 45 አገሮችን ያካተተ ነበር። የብሪታንያ የካንሰር ምርምር ድርጅት ባልደረባ የሆኑት ሪቻርድ ፒቶ “በአብዛኞቹ አገሮች ወደፊት ሁኔታው ከአሁኑ በጣም የከፋ ይሆናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። “በአሁኑ ጊዜ የሚታየው የአጫሽነት አዝማሚያ ካልተለወጠ የዛሬዎቹ ወጣት አጫሾች መካከለኛ ወይም አረጋዊነት ዕድሜ ላይ በሚደርሱበት ጊዜ በትምባሆ ምክንያት የሚሞቱት ሰዎች ብዛት በዓመት 10 ሚልዮን ገደማ ይደርሳል። በየሦስት ሴኮንድ አንድ ሰው ይሞታል ማለት ነው።”
የዓለም ጤና ድርጅት ባልደረባ የሆኑት ዶክተር አለን ሎፔዝ “ማጨስ እኩያ የሌለው አደገኛ ልማድ ነው” ይላሉ። “ይዋል ይደር እንጂ ከሁለት አጫሾች መካከል አንዱ በዚሁ ልማድ ጠንቅ ይሞታል።” በተመሳሳይም በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ክፍል ባልደረባ የሆኑት ማርቲን ቬሲ “ባለፉት 40 ዓመታት የተሰባሰቡት እነዚህ ግኝቶች ከአጫሾች በሙሉ ግማሽ የሚሆኑት ውሎ አድሮ ይህ ልማዳቸው በሚያመጣባቸው ጠንቅ ምክንያት ይሞታሉ ወደሚል አስደንጋጭ መደምደሚያ ያደርሱናል። በእርግጥም በጣም የሚያስፈራ ነገር ነው” ብለዋል። ከ1950ዎቹ ዓመታት ወዲህ 60 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በማጨስ ምክንያት ሞተዋል።
ይህ ሁኔታ የትምባሆ ኩባንያዎቹን ጭምር አስደንግጧል። በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ከማጨስ ጋር ግንኙነት ባላቸው ምክንያቶች በየዓመቱ ሦስት ሚልዮን ሰዎች የሚሞቱ ከሆነና ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ ማጨስ የሚያቆሙ ከሆነ በየዓመቱ ከሦስት ሚልዮን የሚበልጡ አዳዲስ አጫሾች መገኘት አለባቸው ማለት ነው።
የትምባሆ ኩባንያዎች የሴቶች ነጻነት እያሉ በመለፈፋቸው ምክንያት አንድ አዲስ የአጫሾች ጎራ ተገኝቷል። በምዕራብ አገሮች የሴቶች አጫሽነት እንደ እንግዳ ነገር መታየቱ ከቀረ በርካታ ዓመታት ያለፉ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ እንደ ነውር ሲታይ ወደቆየባቸው አገሮች በመዛመት ላይ ነው። ለዚህ ለውጥ ምክንያት የሆኑት የትምባሆ ኩባንያዎች ናቸው። ሴቶች ባገኙት አዲስ ነጻነትና ብልጽግና እንዲፈነጥዙ ለመርዳት ይፈልጋሉ። ዝቅተኛ የኒኮቲንና የታር መጠን አላቸው የሚባሉ ለየት ያሉ የሲጋራ ዓይነቶች የሚያስከትሉት ጉዳት አነስ ያለ በመሆኑ አጫሽ ሴቶችን የሚያማልሉ ሆነዋል። ሌሎች የሲጋራ ዓይነቶች ደግሞ ጣፋጭ ሽታ ወይም ቀጠን ብለው ረዥም ቁመት ያላቸው ናቸው። ሴቶች ደግሞ እነዚህን ሲጋራዎች በማጨስ ይህን ዓይነት ቁመና እናገኛለን ብለው ያስባሉ። በእስያ አገሮች የሚወጡ የትምባሆ ማስታወቂያዎች በምዕራባውያን አለባበስ የዘነጡ የሚማርኩ ወጣት እስያውያን ሞዴሎችን ያሳያሉ።
ይሁን እንጂ ሴቶች “ነጻ” በወጡ መጠን ማጨስ በሚያስከትለው ጠንቅ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም የዚያኑ ያህል እየጨመረ ነው። በሳንባ ካንሰር የሚሞቱ ሴቶች ቁጥር ባለፉት 20 ዓመታት በብሪታንያ፣ በጃፓን፣ በኖርዌይ፣ በፖላንድና በስዊድን ከእጥፍ በላይ ጨምሯል። በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ ጭማሪው 300 በመቶ ደርሷል። አንድ የሲጋራ ማስታወቂያ “ቆንጂት፣ ዛሬ ብዙ ተሻሽለሻል!” ይላል።
አንዳንድ ትምባሆ አምራች ድርጅቶች የየራሳቸውን ስልት ፈጥረዋል። ካቶሊኮች በሚበዙባት በፊሊፒንስ የሚገኝ አንድ ኩባንያ የድንግል ማርያም ሥዕልና ከሥዕሉ ግርጌ ደግሞ የኩባንያው ሲጋራ መፈክር የሠፈረበት የቀን መቁጠሪያ በነጻ አድሏል። ለዓለም ጤና ድርጅት የእስያ ጤና አጠባበቅ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ሮዝማሪ ኤርበን “እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይቼ አላውቅም” ብለዋል። “የማርያምን ምሥል ከትምባሆ ጋር በማዛመድ የፊሊፒንስ ሴቶች ምንም ዓይነት ቅሬታ ሳይሰማቸው እንዲያጨሱ ለመገፋፋት ሞክረዋል።”
በቻይና ለአቅመ አዳም ከደረሱ ወንዶች መካከል 61 በመቶ የሚሆኑት አጫሾች እንደሆኑ ሲገመት ከሴቶቹ መካከል ግን የሚያጨሱት 7 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ምዕራባውያን የትምባሆ ኩባንያዎች ምዕራባውያን እህቶቻቸው እንደ ልባቸው የሚያገኙት “ደስታ” ለበርካታ ዓመታት ተነፍጓቸው በቆዩት መልከ ቀና ምሥራቃውያን ወይዛዝርት ላይ ዓይናቸውን መጣል ጀምረዋል። “ነጻ ሊያወጧቸው” ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ አንድ ደንቃራ ገጥሟቸዋል። በዚህ አገር አብዛኛውን ሲጋራ የሚያመርተው የመንግሥት ንብረት የሆነ የትምባሆ ኩባንያ ነው።
ቢሆንም ምዕራባውያን ኩባንያዎች ቀስ በቀስ ሸቀጦቻቸውን ማስገባት ጀምረዋል። አንዳንድ የትምባሆ ኩባንያዎች በሚያገኙት ጠባብ የማስተዋወቂያ አጋጣሚ በጣም መሰሪ በሆኑ ዘዴዎች የወደፊት ደንበኞች ማዘጋጀት ጀምረዋል። ቻይና ፊልሞችን ከሆንግ ኮንግ ታስመጣለች። በብዙዎቹ ፊልሞች ላይ የሚሠሩት ተዋናዮች ደግሞ ሲጋራ እንዲያጨሱ ገንዘብ ይከፈላቸዋል። የፊልሞቹ ተመልካቾች አጫሾች እንዲሆኑ የሚያግባቡበት ስውር ዘዴ ነው!
ቱጃሮቹ የአሜሪካ የትምባሆ ኩባንያዎች በገዛ አገራቸው የሚደርስባቸው ጥላቻ እየጨመረ በመሄዱ አዳዲስ ሰለባዎችን ለማግኘት መንጠቆቻቸውን አስፋፍተዋል። ዋነኛ ዒላማቸው ያደረጉት ታዳጊ አገሮችን እንደሆነ ሐቁ ያረጋግጣል።
በመላው ዓለም የሚገኙ የጤና ባለ ሥልጣኖች የማስጠንቀቂያ ድምፅ ማሰማታቸውን አላቆሙም። እንደሚከተሉት ያሉ የጋዜጣ ርዕሰ አንቀጾች ይወጣሉ:- “አፍሪካ አዲስ ቸነፈር ከሆነባት ሲጋራ የማጨስ ልማድ ጋር በመዋጋት ላይ ነች።” “በእስያ የሲጋራ ገበያ እየደራ በሄደ መጠን ጭሱ ሰደድ እሳት እየሆነ ነው።” “በእስያ የአጫሾች ቁጥር መጨመር የካንሰር ወረርሽኝ ያስከትላል።” “ሦስተኛው ዓለም አዲስ ፍልሚያ የገጠመው ከትምባሆ ጋር ነው።”
የአፍሪካ አሕጉር በድርቅ፣ በእርስ በርስ ጦርነትና በኤድስ ወረርሽኝ ክፉኛ ተጎድቷል። ቢሆንም ይላሉ እንግሊዛዊው ካርዲኦሎጂስት ዶክተር ኪት ቦል “ከኑክሊየር ጦርነት ወይም ከረሃብ ሌላ ሲጋራ የማጨስን ያህል የአፍሪካን የወደፊት ጤና የሚፈታተን ነገር አይኖርም።”
ታላላቅ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች የአገሬውን ገበሬዎች ቀጥረው ትምባሆ ያስተክላሉ። ገበሬዎቹ ለማገዶና ለቤት መሥሪያ በጣም የሚያስፈልጓቸውን ዛፎች ቆርጠው ለትምባሆ መቀቀያ ይገለገሉባቸዋል። ብዙ ትርፍ በማያስገኙላቸው የምግብ አዝርዕት ፋንታ ብዙ ገንዘብ የሚያስገኝላቸውን ትምባሆ ይተክላሉ። በጎስቋላ ኑሮ ውስጥ የሚገኙት አፍሪካውያን ከዚያችው ገቢያቸው አብዛኛውን ክፍል ለሲጋራ መግዣ ያውላሉ። በዚህ መንገድ የምዕራባውያን የትምባሆ ኩባንያዎች ካዝና እየደለበ በሄደ መጠን አፍሪካውያን ቤተሰቦች በበቂ ምግብ እጦት እየቀጨጩ መጥተዋል።
መላውን ታዳጊ ዓለም እንደ አንድ ትልቅ የንግድ መስክ የሚመለከቱት ምዕራባውያን ትምባሆ አምራች ኩባንያዎች አፍሪካን፣ ምሥራቅ አውሮፓንና ላቲን አሜሪካን ዋነኛ ዒላማቸው አድርገዋል። ከሁሉም በላይ ግን ብዙ ትርፍ እንዝቅባታለን ብለው የሚቋምጡት የበርካታ ሕዝቦች መኖሪያ የሆነችውን እስያን ነው። በቻይና ብቻ ያለው የአጫሾች ቁጥር ከጠቅላላው የዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ ብዛት ይበልጣል። በዚያች አገር 300 ሚልዮን የሚያክሉ አጫሾች ሲኖሩ በዓመት 1.6 ትሪልዮን ሲጋራ ያጨሳሉ። በመላው ዓለም ከሚጨሰው ሲጋራ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የሚጨሰው በቻይና ነው ማለት ነው!
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው “በእስያ አገሮች የትምባሆ መስፋፋት በጤና ላይ የሚያስከትለው መዘዝ እጅግ አስፈሪ እንደሆነ ሐኪሞች ይናገራሉ።” በመጪዎቹ ሁለት ወይም ሦስት አሥርተ ዓመታት ከማጨስ ጋር ዝምድና ባላቸው ምክንያቶች ይሞታሉ ተብለው ከሚታሰቡት አሥር ሚልዮን ሰዎች መካከል ሁለት ሚልዮን የሚያክሉት ቻይናውያን እንደሚሆኑ ሪቻርድ ፒቶ ገምተዋል። በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ከሚኖሩት ቻይናውያን ሕፃናት መካከል ሃምሳ ሚልዮን የሚያክሉት ከማጨስ ጋር ዝምድና ባላቸው በሽታዎች ሊሞቱ እንደሚችሉ ፒቶ ተናግረዋል።
ዶክተር ናይጀል ግሬይ እንደሚከተለው በማለት አጠቃላይ ሁኔታውን ገልጸዋል:- “ባለፉት አምስት አሥርተ ዓመታት በቻይናና በምሥራቅ አውሮፓ የታየው የትምባሆ ታሪክ በእነዚህ አገሮች በጣም ከባድ የሆነ የትምባሆ በሽታ ወረርሽኝ እንደሚመጣ ያመለክታል።”
የታይላንድ ፀረ ትምባሆ ዘመቻ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ፕራኪት ቫቲሳቶኪት “በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በየዓመቱ ለ400,000 ሰዎች ያለ ዕድሜያቸው መቀጨት ምክንያት የሆነ ምርት፣ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ዜጎቹን ለማስተው የሚጣጣረው ምርት ልክ የአሜሪካን ድንበሮች ሲሻገር እንዴት በተለየ አመለካከት ይታያል?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። “ያው ምርት ወደ ሌሎች አገሮች በሚላክበት ጊዜ የጤንነት ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑ ይቀራል?”
የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ለትምባሆ ንግድ መስፋፋት ዋነኛ ግብረ አበር ሆኗል። የትምባሆ ኩባንያዎች ከመንግሥት ጋር ጥረታቸውን በማቀናጀት በባዕዳን አገሮች፣ በተለይም በእስያ ገበያዎች ሰፊ ተቀባይነት ለማግኘት ተጋድለዋል። ለበርካታ ዓመታት የጃፓን፣ የታይዋን፣ የታይላንድና የሌሎች አገሮች በር ለአሜሪካ ሲጋራዎች ዝግ ሆኖ ቆይቶ ነበር። አንዳንዶቹ መንግሥታት የራሳቸው የትምባሆ ምርቶች ብቻ እንዲሸጡ ይፈልጉ ነበር። ፀረ ትምባሆ ቡድኖች የትምባሆ ምርቶች ወደየአገሮቻቸው እንዳይገቡ በተቃወሙ ጊዜ የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር በእነዚህ አገሮች ላይ የንግድ ማዕቀብ እንደሚጥል ዛተ።
ከ1985 ወዲህ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ከፍተኛ ጫና በማሳደሩ ብዙ የእስያ አገሮች በሮቻቸውን ከፍተዋል፤ በመሆኑም የአሜሪካ ሲጋራዎች ወደነዚህ አገሮች መጉረፍ ጀምረዋል። በ1988 ዩናይትድ ስቴትስ ወደ እስያ የምትልከው ሲጋራ መጠን 75 በመቶ አደገ።
ከማንም ይበልጥ የትምባሆ ጦርነቶች ተጠቂ የሆኑት ልጆች ሳይሆኑ አይቀሩም። ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን መዲካል አሶሲዬሽን ላይ የወጣ አንድ ጥናት እንዳለው “ከአዳዲስ አጫሾች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ልጆችና በአሥራዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው።”
በዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ በዩናይትድ ስቴትስ በአሥራዎቹ ዓመታት ውስጥ የሚገኙ ወጣት አጫሾች 3.1 ሚልዮን እንደሚደርስ ገምቷል። በየቀኑ 3,000 በየዓመቱ ደግሞ 1,000,000 አዳዲስ አጫሾች ይመለመላሉ።
አንድ የሲጋራ ማስታወቂያ ጨዋታና ፈንጠዝያ የሚወድ የካርቱን ግመል ሁልጊዜ በከንፈሩ ላይ ሲጋራ አንጠልጥሎ ያሳያል። ይህ የሲጋራ ማስታወቂያ በጤና ላይ የሚያስከትለውን ጠንቅ ያልተገነዘቡ በርካታ ወጣቶችን አታልሎ ለኒኮቲን ባርነት ዳርጓቸዋል። ይህ የሲጋራ ኩባንያ ይህን ማስታወቂያ ማሳየት በጀመረ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ሸማቾቹ ቁጥር 64 በመቶ አድጓል። የጆርጅያ ሕክምና ኮሌጅ (ዩ ኤስ ኤ) ባደረገው ጥናት በጥናቱ ከተካፈሉት የስድስት ዓመት ሕፃናት መካከል 91 በመቶ የሚሆኑት ይህን አጫሽ የካርቱን ገጸ ባሕርይ ለይተው እንደሚያውቁ ተናግረዋል።
ሌላው በስፋት የተሰራጨ የሲጋራ ማስታወቂያ ደግሞ እንዳሻው የሚኖር አንድ ጉልበተኛ ከብት ጠባቂ ያሳያል። አንድ ወጣት እንዳለው፣ ማስተላለፍ የተፈለገው መልእክት “የምታጨስ ከሆነ ምንም ነገር ሊገታህ አይችልም” የሚል ነው። በዓለም ውስጥ በብዛት በመሸጥ አንደኛ የሆነው የፍጆታ ሸቀጥ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ በሚገኙ አጫሽ ወጣቶች ዘንድ 69 በመቶ የሚሆነውን ገበያ እጁ ውስጥ ያስገባውና ከማንኛውም ሸቀጥ የበለጠ ብዙ ማስታወቂያ የተሠራለት ሲጋራ እንደሆነ ተነግሯል። ወጣቶች እንዲያጨሱ ተጨማሪ ማበረታቻ ለመፍጠር በእያንዳንዱ የሲጋራ ፓኮ ውስጥ ጂንስ፣ ኮፍያና በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅነት ያገኙ የስፖርት ልብሶች የሚያስገኙ ኩፖኖች ይከተታሉ።
ትምባሆ ማጨስን የሚቃወሙ ድርጅቶች ማስታወቂያ ያለውን ከፍተኛ ኃይል ስለተገነዘቡ በብዙ አገሮች የትምባሆ ማስታወቂያዎች በቴሌቪዥንና በራዲዮ እንዳይቀርቡ ለማስከልከል ችለዋል። ይሁን እንጂ ዘዴኞቹ የትምባሆ አስተዋዋቂዎች ይህን እገዳ ለመጣስ ከቻሉባቸው መንገዶች አንዱ በስፖርታዊ ውድድሮች ወቅት በስትራቴጅያዊ ቦታዎች ላይ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ማስቀመጥ ነው። በዚህ መንገድ በርካታ ወጣት ተመልካቾች ያሉት አንድ ጨዋታ በቴሌቪዥን በሚተላለፍበት ጊዜ ከዝነኛው ተጫዋች በስተጀርባ ግዙፍ የሆነው የሲጋራ ማስታወቂያ ሰሌዳ ይታያል።
በከተማ አደባባዮች ወይም በትምህርት ቤት በራፎች አጭር ቀሚስ ወይም የሽርሽር ልብስ የለበሱ ሴቶች ቆመው የማወቅ ጉጉት ላደረባቸው ወይም ማጨስ ለሚፈልጉ ወጣቶች በነጻ ሲጋራ ያድላሉ። በቪዲዮ መጫወቻ ቦታዎች፣ በዲስኮዎችና በዳንስ ቤቶች የሲጋራ ናሙናዎች በነጻ ይታደላሉ። የአንድ ኩባንያ የሽያጭ እቅድ ሾልኮ ወጥቶ ለፕሬስ ሰዎች ደርሷል። ጋዜጣው እንዳመለከተው አንድ በካናዳ የሚገኝ የሲጋራ ኩባንያ ከ12 እስከ 17 ዓመት ዕድሜ የሚገኙ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ወንዶችን ዒላማው አድርጓል።
ማጨስ ደስታ፣ አካላዊ ብቃት፣ ወንዳ ወንድነትና ታዋቂነት ያስገኛል የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ይፈለጋል። አንድ የማስታወቂያ አማካሪ “በምሠራበት ቦታ የ14 ዓመት ወጣቶች ማጨስ እንዲጀምሩ ለመገፋፋት በጣም እንጥር ነበር” ብለዋል። በእስያ የሚታዩ ማስታወቂያዎች ጤነኛና ወጣት ምዕራባውያን ስፖርተኞች እያጨሱ በባሕር ዳሮችና በኳስ ሜዳዎች ዱብ ዱብ ሲሉ ያሳያሉ። አንድ የንግድ አስተዋዋቂ መጽሔት “እስያውያን አጫሾች የምዕራባውያንን ማራኪ ሞዴልና አኗኗር ለመቅዳት በጣም ይፈልጋሉ።”
የትምባሆ አሻሻጮች በቢልዮን የሚቆጠር ዶላር በማስታወቂያዎች ላይ ካፈሰሱ በኋላ ከፍተኛ ውጤት ማግኘት ጀምረዋል። ሪደርስ ዳይጀስት ያቀረበው ልዩ ሪፖርት የወጣት አጫሾች ቁጥር እድገት በጣም የሚያስደነግጥ እንደሆነ አመልክቷል። “በፊሊፒንስ በአሁኑ ጊዜ ከ18 ዓመት በታች ከሚገኙ ልጆች መካከል 22.7 በመቶ የሚሆኑት ያጨሳሉ። በአንዳንድ የላቲን አሜሪካ ከተሞች በአሥራዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑ አጫሾች ሆነዋል። በሆንግ ኮንግ የሰባት ዓመት ልጆች ሳይቀሩ ያጨሳሉ።”
ይሁን እንጂ የሲጋራ ኩባንያዎች ከአገሮቻቸው ውጭ ባገኟቸው ድሎች በመፈንጠዝ ላይ ቢገኙም በገዛ አገሮቻቸው ከፍተኛ ችግር እየመጣባቸው እንደሆነ መገንዘብ ጀምረዋል። ከዚህ ችግር ለመውጣት ይችሉ ይሆን?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በጣም ጥሩ ደንበኞቻቸው ያለማቋረጥ ይሞታሉ
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
እስያ፣ አዲሱ የትምባሆ የእልቂት አውድማ
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ከአዳዲስ አጫሾች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ልጆችና አፍላ ወጣቶች ናቸው!
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በሲጋራ ጭስ ውስጥ የሚገኙ ቀሳፊ ንጥረ ነገሮች
የሲጋራ አምራቾች እስከ 700 የሚደርሱ የተለያዩ ኬሚካሎችን በምርቶቻቸው ውስጥ ሊያስገቡ ይችላሉ። ኩባንያዎቹ የእነዚህን ኬሚካሎች ዝርዝር በድብቅ እንዲይዙ ሕጉ ይፈቅድላቸዋል። ይሁን እንጂ ከፍተኛ ክብደት ያላቸው ማዕድናት፣ ፀረ አረሞችና ፀረ ተባዮች እንደሚገኙባቸው ይታወቃል። አንዳንዶቹ ኬሚካሎች በጣም መርዘኛ በመሆናቸው ጉድጓድ ውስጥ መቅበር እንኳ በሕግ የተከለከለ ነው። ከሰዎች አፍ እየተንቧለለ በሚወጣው የሲጋራ ጭስ ውስጥ አሴቶንን፣ አርሰኒክን፣ ብዩቴንን፣ ካርቦን ሞኖኦክሳይድንና ሳያናይድን ጨምሮ 4,000 የሚያክሉ ንጥረ ነገሮች እንደሚገኙ ይታወቃል። የአጫሾችና በአጫሾች አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ሳንባ ቢያንስ 43 ለሚያክሉ ካንሰር አምጪ ኬሚካሎች ይጋለጣል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የማያጨሱ ግን ለአደጋ የተጋለጡ
ከከባድ አጫሾች ጋር አብረህ ትኖራለህ፣ ትሠራለህ ወይም ትጓዛለህ? ከሆነ በሳንባ ካንሰር ወይም በልብ ሕመም የመያዝ ዕድልህ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። የዩናይትድ ስቴትስ የአካባቢ ጥበቃ መሥሪያ ቤት በ1993 ያካሄደው ጥናት ከአካባቢ የሚተነፈስ የትምባሆ ጭስ በአንደኛነት የሚመደብና እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ የካንሰር መንሥኤ እንደሆነ አመልክቷል። ይህ ሰፊ ሪፖርት ከሲጋራ ጫፍና ከአጫሾች በሚወጣው ጭስ ላይ የተደረጉ 30 የሚያክሉ ጥናቶችን ውጤት መርምሯል።
የአካባቢ ጥበቃ መሥሪያ ቤቱ በዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ በሳንባ ካንሰር ለሚሞቱ 3,000 ሰዎች ምክንያት ሌሎች የሚያጨሱትን የሲጋራ ጭስ መተንፈስ እንደሆነ ገልጿል። በሰኔ 1994 የአሜሪካ ሕክምና ማህበር አንድም ጊዜ አጭሰው የማያውቁ፣ ግን በአካባቢያቸው ለሚገኝ የትምባሆ ጭስ የተጋለጡ ሴቶች ከሌሎች ዕድሜያቸውን በሙሉ አጭሰው ከማያውቁ ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ በሳንባ ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው 30 በመቶ እንደሚበልጥ የሚያሳይ ጥናት በማውጣት የዚህን ድምዳሜ ትክክለኛነት አረጋግጧል።
በየዓመቱ ከ150,000 እስከ 300,000 የሚደርሱ ሕፃናት ለትምባሆ ጭስ በመጋለጣቸው ምክንያት በብሮንካይትስና በሳንባ ምች ይያዛሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በየዓመቱ ከ200,000 እስከ 1,000,000 የሚደርሱ ሕፃናት በትምባሆ ጭስ ምክንያት የአስም ሕመማቸው ይባባሳል።
የአሜሪካ የልብ ማህበር በየዓመቱ 40,000 የሚያክሉ ሰዎች በአካባቢ ትምባሆ ጭስ ምክንያት በሚመጣ የልብና የደም ሥር ሕመም እንደሚሞቱ ገምቷል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
መልከ ቀና እስያዊት ሞዴልና ዒላማዎቿ