የትምባሆ ጠበቆች በሞቃት አየር የተሞሉ ባሉኖቻቸውን መተኮስ ጀምረዋል
በ1940ዎቹ ዓመታት የለንደን ከተማ በጠላት ሠራዊት ተከባ ነበር። የጀርመን ተዋጊ አውሮፕላኖችና ሮቦት ቦምቦች በከተማይቱ ውስጥ ሽብር ከመፍጠራቸውም በላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትለዋል። ሁኔታው ይህን ያህል አደገኛና አሳሳቢ ባይሆን ኖሮ ግን የለንደን ነዋሪዎች በተመለከቱት ነገር መሳቃቸው አይቀርም ነበር።
በረዣዥም ገመዶች የተወጠሩ በሺህ የሚቆጠሩ ባሉኖች ከአናታቸው በላይ ተንሳፈዋል። የጀርመን አውሮፕላኖች ዝቅ ብለው እንዳይበሩና ከተቻለም አንዳንዶቹን ቦምቦች አየር ላይ አፈንድተው እንዲያስቀሩ ተብለው የተላኩ ባሉኖች ናቸው። የባሉኖቹ ምሽግ ብዙ ጥበብ የጠየቀ ይሁን እንጂ ውጤቱ የተሳካ አልሆነም።
የሲጋራ ኩባንያዎችም ተመሳሳይ በሆነ ወረራ ውስጥ ይገኛሉ። አንድ ወቅት በማይበገር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምሽግ ውስጥ ተደላድለው ይኖሩ የነበሩ ትላልቅ የትምባሆ ኩባንያዎች ከሁሉም አቅጣጫ ጥቃት እየተሰነዘረባቸው ነው።
የሕክምናው ማህበረሰብ የትምባሆን ጎጂነት የሚያረጋግጡ በርካታ ጥናቶች በማዥጎድጎድ ላይ ነው። ከትምባሆ አሻሻጮች ጋር ብርቱ ትግል የገጠሙት የጤና አጠባበቅ ባለ ሥልጣኖች ሁኔታውን መሣሪያ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው። እጅግ የተበሳጩ ወላጆች ልጆቻችን አግባብ ያልሆነ በደል እየተፈጸመባቸው ነው ብለው ያማርራሉ። ቆራጥ የሆኑ ሕግ አውጪዎች የሲጋራ ጭስ ከመሥሪያ ቤት ሕንጻዎች፣ ከምግብ ቤቶች፣ ከወታደራዊ ተቋሞችና ከአውሮፕላኖች እንዲወገድ አድርገዋል። በብዙ አገሮች የትምባሆ ማስታወቂያዎች በቴሌቪዥንና በራዲዮ እንዳይተላለፉ ታግዷል። በዩናይትድ ስቴትስ የክልል መንግሥታት ላወጡት የሕክምና ወጪ በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር ካሣ እንዲከፈላቸው ክስ በመመስረት ላይ ናቸው። ጠበቆች ሳይቀሩ ለዚህ ትግል ድጋፍ ሰጥተዋል።
በዚህ ምክንያት የትምባሆ ኩባንያዎች የተሰነዘሩባቸውን ጥቃቶች ለመከላከል የራሳቸውን ባሉኖች ወንጭፈዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ባሉኖች ብዙም ፋይዳ ያስገኙላቸው አይመስሉም።
የዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ በዚህ ባለፈው ዓመት ሁኔታው ያስቆጣቸው ሕግ አውጪዎችና የጤና አጠባበቅ መንግሥታዊ ባለ ሥልጣኖች በትምባሆ ኢንዱስትሪዎች ላይ በጣም ጠንካራ ጥቃት ሲሰነዝሩ በቅርብ ለመመልከት ችሏል። በሚያዝያ ወር 1994 የሰባት ትላልቅ የአሜሪካ የትምባሆ ኩባንያዎች ባለ ሥልጣናት በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ልዩ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ወንጀለኝነታቸውን ገሐድ ላወጡት አሐዛዊ መረጃዎች መልስ እንዲሰጡ ተደርጓል። በየዓመቱ 400,000 አሜሪካውያን በትምባሆ ጠንቅ ምክንያት ሲሞቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ደግሞ አልጋ ላይ ውለው ሞታቸውን ይጠባበቃሉ። በየዓመቱ በሲጋራ ሱስ የሚለከፉ ሰዎች ቁጥርም እጅግ ብዙ ነው።
ታዲያ ምን መልስ ሰጡ? በቀረቡባቸው ክሶች ተወጥረው የተያዙት ባለ ሥልጣናት የሰጡት የመከላከያ መልስ በጣም የሚያስገርም ነው። የአንድ የትምባሆ ተቋም ቃል አቀባይ “ትምባሆ ማጨስ . . . ከበሽታዎች መስፋፋት ጋር ቀጥተኛ ዝምድና እንዳለው ገና አልተረጋገጠም” ብለዋል። እንዲያውም የማጨስ ልማድ ጣፋጭ ምግቦችን እንደ መመገብና ቡና እንደ መጠጣት ካሉት አስደሳች ድርጊቶች የተለየ ምንም የሚያስከትለው ጉዳት እንደሌለ ተደርጎ ተገልጿል። አንድ የትምባሆ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ “በሲጋራ ውስጥ ኒኮቲን መኖሩ ሲጋራን ከጎጂ ዕፆች አያስመድበውም ወይም ሱስ ያስይዛል ሊያሰኘው አይችልም” ብለዋል። አንድ የትምባሆ ኩባንያ ሳይንቲስት ደግሞ “በሲጋራ ውስጥ የሚገኘው ኒኮቲን በማንኛውም መጠን ቢሆን ሱስ ያስይዛል የሚለው አባባል ትክክል አይደለም” ብለዋል።
ኮሚቴው የአጸፋ መልስ ሲሰጥ ሲጋራ ሱስ የማያስይዝ ከሆነ የትምባሆ ኩባንያዎች በምርቶቻቸው ውስጥ የሚገኘውን የኒኮቲን መጠን በጥንቃቄ የሚቆጣጠሩት ለምንድን ነው? ሲል ጠይቋል። ሌላው የትምባሆ ኩባንያ ባለ ሥልጣን “ለጣዕሙ ሲባል ነው” ሲሉ መለሱ። ከሲጋራው ጣዕም ማጣት ሌላ ምንም ዓይነት ክፋት የለውም ማለት ነው? ከእኚሁ ሥራ አስኪያጅ ኩባንያ ማህደር የተገኙ ኒኮቲን ሱስ እንደሚያስይዝ የሚያረጋግጡ በርካታ ጥናቶች ቢቀርብላቸውም በዚህ የክህደት ቃላቸው ጸንተዋል።
እኚህ ሰውና መሰሎቻቸው በትምባሆ ጠንቅ ምክንያት ምንም ያህል ብዙ ሰዎች ቢያልቁ ይህን አቋማቸውን የሙጥኝ ብለው የሚጸኑ ይመስላል። በ1993 መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ ሕክምና ማህበር ባለ አደራ ቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር ላኒ ብሪስቶ ለትምባሆ ኩባንያዎች ባለ ሥልጣናት አንድ ግብዣ አቅርበው ነበር። ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን መዲካል አሶሲዬሽን እንደሚከተለው ዘግቧል:- “የትላልቆቹ የአሜሪካ ትምባሆ ኩባንያዎች ባለ ሥልጣናት አብረዋቸው የሆስፒታል የመኝታ ክፍሎችን ተዘዋውረው እንዲጎበኙና ትምባሆ በማጨስ ምክንያት የሳንባ ካንሰር የያዛቸውንና በሳንባ መታወክ ምክንያት አልጋ ላይ የዋሉትን በሽተኞች እንዲመለከቱ ግብዣ አቀረቡላቸው። አንዳቸውም ቢሆኑ ግብዣውን አልተቀበሉም።”
የትምባሆ ኢንዱስትሪ ሥራ አጥነት እየተስፋፋ በሄደበት በዛሬው ዓለም ጥሩ ሥራ እንደሚፈጥር በኩራት ይናገራል። ለምሳሌ ያህል በአርጀንቲና የትምባሆ ኢንዱስትሪ ለአንድ ሚልዮን ሰዎች የሥራ ዕድል የከፈተ ሲሆን ለሌሎች አራት ሚልዮን ሰዎችም ከዚህ መስክ ጋር የተያያዘ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ከትምባሆ የሚገኘው ከፍተኛ የታክስ ገቢ ለትምባሆ ኢንዱስትሪ የብዙ መንግሥታትን ወዳጅነት አስገኝቷል።
አንድ የትምባሆ ድርጅት ለአናሳ የኅብረተሰብ ክፍሎች በርካታ ገንዘብ በመለገስ ለሕዝብ አሳቢ ድርጅት እንደሆነ የሚያስመስለው ድርጊት ፈጽሟል። ይሁን እንጂ የኩባንያው የምሥጢር ሰነዶች ይህ “የሕዝብ እድገት በጀት” የተመደበው የመራጮችን ድጋፍ ለማስገኘት እንደሆነ አጋልጠዋል።
ይኸው የትምባሆ ኩባንያ ለሙዚየሞች፣ ለትምህርት ቤቶች፣ ለዳንስ አካዳሚዎችና ለሙዚቃ ተቋሞች በርካታ ገንዘብ በመለገስ የሥነ ጥበብ ሰዎችን ወዳጅነት አትርፏል። የሥነ ጥበብ ድርጅቶች ባለ ሥልጣኖች የገንዘብ ችግራቸውን ለመወጣት ሲሉ የትምባሆ ድርጅቶችን ገንዘብ ለመቀበል ደፍረዋል። በቅርቡ ይኸው የትምባሆ ኩባንያ እነዚህ የሥነ ጥበብ ማህበረሰብ አባላት አንድ ፀረ ትምባሆ ሕግ እንዳይጸድቅ የተቃውሞ ድምፅ እንዲያሰሙ በጠየቀ ጊዜ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወድቀው ነበር።
ቱጃሮቹ የትምባሆ ኩባንያዎች ጥቅሞቻቸውን የሚጻረሩ ሕጎች እንዳይወጡ ሊረዷቸው ለሚችሉ የፖለቲካ ሰዎች ገንዘባቸውን መርጨት አያሳፍራቸውም። በከፍተኛ ሥልጣን ላይ የሚገኙ የመንግሥት ሹሞች የትምባሆ ኩባንያዎችን ጥቅም ሲያስጠብቁ ቆይተዋል። አንዳንዶች ከኢንዱስትሪው ጋር የጥቅም ትስስር አላቸው ወይም ኩባንያዎቹ እነርሱን ለማስመረጥ ላወጡት ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ወሮታ ለመመለስ ይገፋፋሉ።
አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባል ከትምባሆ ኩባንያዎች የ21,000 ዶላር ስጦታ እንዳገኙና በኋላም ለበርካታ ፀረ ትምባሆ ውሳኔዎች የተቃውሞ ድምፅ እንደሰጡ ሪፖርት ተደርጓል።
ብዙ ገንዘብ የሚከፈላቸው አንድ የትምባሆ ደጋፊ በአንድ ወቅት የክልል መንግሥት ምክር ቤት አባልና ከባድ አጫሽ የነበሩ ሲሆን በቅርቡ የጉሮሮ፣ የሳንባና የጉበት ካንሰር እንደያዛቸው አውቀዋል። በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ጸጸት የሚሰማቸው ሲሆን “ራስህ ባመጣኸው ጠንቅ ምክንያት አልጋ ላይ ሆነህ ስታጣጥር” ምን ያህል ሞኝ እንደነበርክ ታስተውላለህ በማለት በምሬት ይናገራሉ።
የትምባሆ ኩባንያዎች ለማስታወቂያ ሥራ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ ተቃዋሚዎቻቸውን አምርረው በመታገል ላይ ናቸው። አንድ ማስታወቂያ የሰዎችን ነጻነት የማስጠበቅ ፍላጎት በማነሳሳት “ዛሬ በትምባሆ ላይ፣ ነገስ?” የሚል ማስጠንቀቂያ አሰምቷል። ማስታወቂያው አክራሪዎች ናቸው የሚላቸው ከልካዮች ነገ ካፌይን፣ አልኮልና ሐምበርገር እንዲከለከል መሟገታቸው አይቀርም ማለቱ ነው።
የጋዜጣ ማስታወቂያዎች የዩናይትድ ስቴትስ የአካባቢ ጥበቃ ባለ ሥልጣን ሌሎች የሚያጨሱትን የትምባሆ ጭስ መተንፈስ ካንሰር ያመጣል ሲል ያቀረበውን በብዙ ጽሑፎች ላይ የተጠቀሰ ጥናት ውድቅ ለማድረግ ሞክረዋል። የትምባሆ ኢንዱስትሪ ክስ ለመመስረት እንዳሰበ አስታውቋል። አንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አንድ ኩባንያ በሲጋራዎቹ ውስጥ የሚገኘውን የኒኮቲን መጠን በመጨመር ሰዎችን ሱሰኞች እያደረገ ነው ሲል ወቀሳ ሰንዝሮ ነበር። ፕሮግራሙን ያቀረበው ጣቢያ ወዲያውኑ የ10 ቢልዮን ዶላር ክስ ቀረበበት።
የትምባሆ ኩባንያዎች ባለ በሌለ ኃይላቸው ቢዋጉም በጣም ብዙ ውንጀላ እየተቆለለባቸው መጥቷል። ባለፉት አራት አሥርተ ዓመታት ውስጥ 50,000 የሚያክሉ ጥናቶች ተካሂደው ትምባሆ ማጨስ አደገኛ መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች ተገኝተዋል።
የሲጋራ ኩባንያዎች የሚሰነዘርባቸውን ክስ ለመመከት ምን አድርገዋል? አንድ የሙጥኝ ብለው የያዙት ነጥብ አለ። ማጨስ የሚያቆሙ አጫሾች አሉ። ይህም ኒኮቲን ሱስ እንደማያስይዝ ያረጋግጣል ይላሉ። ያለው የስታትስቲክስ መረጃ ግን ይህን አይደግፍም። እርግጥ፣ 40 ሚልዮን የሚያክሉ አሜሪካውያን ማጨስ አቁመዋል። ሆኖም 50 ሚልዮን የሚሆኑ አሜሪካውያን አሁንም ያጨሳሉ፣ ከእነዚህ መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ለማቆም እንደሚፈልጉ ይናገራሉ። በየዓመቱ ማጨስ ለማቆም ከሚሞክሩት 17 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ሳይሳካላቸው ቀርቶ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ማጨስ ይጀምራሉ።
የሳንባ ካንሰር ቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው የዩናይትድ ስቴትስ አጫሾች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት ወደ ልማዳቸው ይመለሳሉ። የልብ ድካም ከደረሰባቸው አጫሾች መካከል 38 በመቶ የሚሆኑት ገና ከሆስፒታል ሳይወጡ ሲጋራ መለኮስ ይጀምራሉ። በማንቁርታቸው ላይ የወጣ ካንሰር በቀዶ ሕክምና ከተወገደላቸው አጫሾች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ዳግመኛ ለማጨስ ይሞክራሉ።
በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ በአሥራዎቹ ዓመታት ዕድሜ ያሉ አጫሾች መካከል ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ቢያንስ አንድ ጊዜ ማጨስ ለማቆም ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በተጨማሪም ለብዙ ወጣቶች ትምባሆ ማጨስ ይበልጥ ጠንከር ያሉ ዕፆችን ወደ መውሰድ የሚያመራ የመጀመሪያ እርምጃ እንደሆነ የሚያመለክት የስታትስቲክስ መረጃ አለ። የሚያጨሱ ጎረምሶች ከማያጨሱት ይልቅ ኮኬይን የመውሰድ ዕድላቸው 50 ጊዜ እጥፍ ይበልጣል። አንዲት በ13 ዓመት ዕድሜ ላይ የምትገኝ አጫሽ በዚህ አባባል ትስማማለች። “ሲጋራ ዕፅ ወደ መውሰድ የሚያሸጋግር በር እንደሆነ ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም” ስትል ጽፋለች። “ከሦስት ሰዎች በስተቀር፣ የማውቃቸው ሁሉ ዕፅ መውሰድ የጀመሩት ማጨስ ከጀመሩ በኋላ ነው።”
ዝቅተኛ የታር መጠን ያላቸው ሲጋራዎችስ? እነዚህ ሲጋራዎች በሁለት ምክንያቶች የተነሣ ይበልጥ አደገኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጥናቶች ያመለክታሉ:- አንደኛ፣ አጫሹ ሰውነቱ ማግኘት የሚፈልገውን ኒኮቲን ለማግኘት ሲል በብዛት ወደ ውስጥ ስለሚስብ በጭሱ የሚመረዙት የሳንባው ሕዋሳት መጠን ከፍተኛ ይሆናል። ሁለተኛ፣ “ጤነኛ” ሲጋራ ነው የማጨሰው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ስለሚኖረው ማጨስ ለማቆም ምንም ዓይነት ጥረት አያደርግም።
በኒኮቲን ላይ ብቻ ከ2,000 የሚበልጡ ጥናቶች ተደርገዋል። እነዚህ ጥናቶች ኒኮቲን የሰው ልጅ እስካሁን ካወቃቸው ከባድ ሱስ የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮች አንዱ እንደሆነና በጣም ጎጂ ከሆኑት ተርታ እንደሚመደብ አረጋግጠዋል። ኒኮቲን የልብ ምት ፍጥነት እንዲጨምርና የደም ሥሮች እንዲጠቡ ያደርጋል። በሰባት ሰኮንድ ውስጥ ወደ ደም ዘልቆ ስለሚገባ በደም ሥር ከሚወጋ መድኃኒት እንኳን በበለጠ ፍጥነት ይሠራል። አንጎል አምጣ፣ አምጣ እንዲል ስለሚያደርግ ከሄሮይን በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ኃይል ያለው ሱስ እንደሚያስይዝ አንዳንዶች ይናገራሉ።
የትምባሆ ኩባንያዎች ቢክዱትም እንኳ ኒኮቲን ሱስ የማስያዝ ባሕርይ እንዳለው ያውቃሉ? ይህን ካወቁ ረዥም ጊዜ እንደሆናቸው የሚያመለክቱ ፍንጮች አሉ። ለምሳሌ ያህል በ1983 የቀረበ አንድ ሪፖርት እንደሚያመለክተው የአንድ ትምባሆ ኩባንያ ተመራማሪ አይጦች ኒኮቲን መውሰድ የሚያስችላቸውን መሣሪያ ደጋግመው በመጫን ሱስ እንደያዛቸው የሚያሳይ ባሕርይ እንዳሳዩ ተመልክተዋል። ይህ ጥናት በትምባሆ ኢንዱስትሪው ግፊት ምሥጢር ሆኖ እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ በቅርቡ ይፋ እንደወጣ ተዘግቧል።
የትምባሆ ኩባንያዎቹ እጃቸውን አጣጥፈው በመቀመጥ ከየአቅጣጫው የሚወነጨፍባቸውን ውርጅብኝ ዝም ብለው አልተቀበሉም። በኒው ዮርክ ከተማ የሚገኘው የትምባሆ ምርምር ካውንስል ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል “በዩናይትድ ስቴትስ የንግድ ታሪክ ውስጥ እጅግ ብዙ ጊዜ የቆየ የማደናገሪያ ዘመቻ” ሲል የጠራውን እንቅስቃሴ ያካሂዳል።
ካውንስሉ በነጻ ምርምር ሽፋን የሚሰነዘርበትን ጥቃት ለመመከት በርካታ ሚልዮን ዶላር ወጪ አድርጓል። ይህ እንቅስቃሴ የተጀመረው በ1953 የስሎዋን ኬተሪንግ መታሰቢያ የካንሰር ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ኧርነስት ዊንደር በአይጦች ጀርባ ላይ የተቀባ የትምባሆ ታር እብጠት እንዳስከተለባቸው በተገነዘቡ ጊዜ ነበር። የትምባሆ ኢንዱስትሪ የራሱን ሳይንሳዊ ማስረጃ በማቅረብ የምርቱን ጎጂነት የሚያረጋግጡትን ግልጽ ማስረጃዎች ለማስተባበል ሲል ይህን ካውንስል አቋቋመ።
የዚህ ካውንስል ሳይንቲስቶች ከሌሎቹ የምርምር ማኅበረሰብ አባሎች ፈጽሞ ተቃራኒ የሆኑ ውጤቶች ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት ነው? በቅርቡ የወጡ ሰነዶች እንደሚያመለክቱት በጣም የረቀቀ የተንኮል መረብ ሸርበዋል። በገቡት የኮንትራት ውሎችና በትኩረት በሚከታተሏቸው የሕግ አማካሪዎች እግር ተወርች ከተያዙት የካውንስሉ ተመራማሪዎች ብዙዎቹ እያደገ የሄደው የጤንነት ሥጋት በበቂ ምክንያት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ተገንዝበዋል። ይሁን እንጂ ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል እንዳለው ካውንስሉ ሐቁ ሲቀርብለት “ማጨስ የጤና ጠንቅ መሆኑን የሚያመለክቱትን ጥናቶች አንዳንድ ጊዜ ችላ ብሎ ያልፋቸዋል ወይም ጥናቶቹ እንዲቋረጡ ያደርጋል።”
ጉዳት የማያስከትል ሲጋራ ለመፈልሰፍ የሚደረገው ምርምር በምሥጢር መካሄድ ከጀመረ በርካታ ዓመታት አልፈዋል። እንዲህ ያለ ምርምር እንደሚካሄድ ይፋ ቢወጣ ማጨስ ለጤና ጎጂ መሆኑን አምኖ መቀበል ይሆንባቸዋል። በ1970ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ላይ አንድ የትምባሆ ኩባንያ ጠበቃ “ጉዳት የማያስከትል” ሲጋራ ለመሥራት የሚደረገው ጥረት በሙሉ ከንቱ እንደሆነ ተቆጥሮ እንዲተውና ከዚህ ምርምር ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ሰነዶች በሙሉ እንዲወገዱ ሐሳብ አቅርበዋል።
ለበርካታ ዓመታት ከተደረጉት ምርምሮች ሁለት ነገሮች ግልጽ ሆነዋል:- ኒኮቲን በእርግጥ ሱስ ያስይዛል፣ ሲጋራ ማጨስም ለሞት ይዳርጋል። የትምባሆ ኩባንያዎች ይህን ሐቅ ሽንጣቸውን ገትረው በአደባባይ ቢክዱም ሐቁን አሳምረው የሚያውቁ መሆናቸውን በተግባራቸው ያሳያሉ።
የዩናይትድ ስቴትስ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር (ኤፍ ዲ ኤ) ኮሚሽነር የሆኑት ዴቪድ ኬስለር የትምባሆ ኩባንያዎች በሲጋራ ውስጥ የተወሰነ መጠን ያለው ኒኮቲን እንዲኖር እንደሚያደርጉ ሲያጋልጡ እንዲህ ብለዋል:- “ከዛሬዎቹ ሲጋራዎች አንዳንዶቹ ሱስ ለማስያዝና ሱሱን ለማቆየት በሚያስችል መንገድ . . . በጥንቃቄ የተሰላ የኒኮቲን መጠን የሚያዳርሱ የረቀቀ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ናቸው።”
የትምባሆ ኩባንያዎች ዓላማቸውና ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ የሚያረጋግጡ በርካታ የፈጠራ ባለቤትነት መብቶች እንዳሏቸው ኬስለር ገልጸዋል። እስካሁን ከታወቁት የትምባሆ ዝርያዎች ሁሉ የበለጠ የኒኮቲን ይዘት ያለው የትምባሆ ዝርያ ስላስገኙ አንድ የፈጠራ ባለቤትነት መብት ተሰጥቷቸዋል። የሲጋራን ኒኮቲን መጠን ከፍ ለማድረግ በፊልተሮችና በወረቀቶች ላይ ለሚፈጸም የቅመማ ሂደት ያገኙት ሌላ የፈጠራ ባለቤትነት መብትም አላቸው። አጫሹ ከሲጋራው ማለቂያ ይልቅ በመጀመሪያው ላይ ብዙ ኒኮቲን እንዲስብ የሚያስችል የፈጠራ ባለቤትነት መብትም አግኝተዋል። በተጨማሪም ከትምባሆው የሚወጣውን ኒኮቲን መጠን ከፍ ለማድረግ የአሞኒያ ውህዶች እንደሚጨመሩ የትምባሆ ኢንዱስትሪ ሰነዶች ያመለክታሉ። የኒው ዮርክ ታይምስ ሪፖርት “ወትሮ ወደ አጫሾች ደም ከሚገባው ኒኮቲን በእጥፍ የሚበልጥ ኒኮቲን ይገባል” ይላል። የዩናይትድ ስቴትስ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር ኒኮቲን ሱስ የሚያስይዝ ዕፅ እንደሆነ ከመግለጹም በላይ ወደፊት በሲጋራ ላይ ይበልጥ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ለማድረግ አቅዷል።
መንግሥታትም የሲጋራ ተጠቃሚዎች የሆኑበት መንገድ አለ። ለምሳሌ ያህል የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ከትምባሆ ምርቶች ከሚሰበስበው የፌደራልና የክልል ታክስ በዓመት 12 ቢልዮን ዶላር ያገኛል። ይሁን እንጂ የቴክኖሎጂ ግምገማ ፌደራል ቢሮ በማጨስ ምክንያት በሚባክነው ምርታማነትና የሕክምና ወጪ ምክንያት በየዓመቱ የ68 ቢልዮን ዶላር ኪሣራ እንደሚደርስ አስልቷል።
በእርግጥ የትምባሆ ኢንዱስትሪ ብዙ የኢኮኖሚ ጥቅምና በርካታ የሥራ ዕድል አስገኝቻለሁ በማለት፣ ለሥነ ጥበብ ድርጅቶች የልግስና እጁን በመዘርጋት፣ ትምባሆ በጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ሽንጡን ገትሮ በመካድ ራሱን ለመከላከል ልዩ ልዩ መልክ ያላቸው ባሉኖች ተኩሷል። እነዚህ ባሉኖች በለንደን ከተማ ላይ ካንዣበቡት ባሉኖች የበለጠ ፋይዳ ይኖራቸውና አይኖራቸው እንደሆነ ወደፊት የምናየው ነገር ይሆናል።
ይሁን እንጂ ግዙፎቹ ኩባንያዎች እውነተኛ ማንነታቸውን መደበቅ እንደተሳናቸው ግልጽ እየሆነ መጥቷል። በሚልዮን የሚቆጠር ትርፍ ሲያጋብሱ ሚልዮኖችን ፈጅተዋል። በሰው ሕይወት ላይ የሚደርሰው ከፍተኛ ጥፋት ግን እምብዛም ያሳሰባቸው አይመስልም።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ምንም ያህል ፋይዳ ያስገኙ አይመስልም
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አንድ መንግሥታዊ ጥናት ሌሎች የሚያጨሱትን የሲጋራ ጭስ መተንፈስ ካንሰር እንደሚያመጣ አመልክቷል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ኒኮቲን እስካሁን ከታወቁት ከፍተኛ ሱስ የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮች አንዱ ነው
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በሚልዮን የሚቆጠር ትርፍ ሲያጋብሱ ሚልዮኖችን ፈጅተዋል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
50,000 የሚያክሉ ጥናቶች፣ ምን አረጋግጠዋል?
ትምባሆ ከማጨስ ጋር በተያያዘ ተመራማሪዎች ከደረሱባቸው አሳሳቢ የጤንነት ችግሮች መካከል ለናሙና ያህል ጥቂቶቹ እነሆ:-
የሳንባ ካንሰር:- በሳንባ ካንሰር ከሚሞቱ ሰዎች መካከል 87 በመቶ የሚሆኑት አጫሾች ናቸው።
የልብ በሽታ:- አጫሾች በልብና በደም ሥር በሽታዎች የመያዝ ዕድላቸው ከማያጨሱት በ70 በመቶ ይበልጣል።
የጡት ካንሰር:- በየቀኑ 40 ወይም ከዚያ በላይ ሲጋራ የሚያጨሱ ሴቶች በጡት ካንሰር የመሞት ዕድላቸው ከሌሎች ሴቶች በ74 በመቶ ይበልጣል።
የመስማት ችግር:- ከሚያጨሱ እናቶች የሚወለዱ ልጆች ድምፅ የመለየት ችግር ያጋጥማቸዋል።
በስኳር በሽተኞች ላይ የሚያስከትለው ችግር:- የሚያጨሱ ወይም ትምባሆ የሚያኝኩ የስኳር በሽተኞች ለኩላሊት መድከምና ሬቲኖፓቲ ለሚባለው የዓይን ሕመም ይበልጥ የተጋለጡ ናቸው።
የደንዳኔ ካንሰር:- ከ150,000 በሚበልጡ ሰዎች ላይ የተደረጉ ሁለት ጥናቶች በማጨስና በደንዳኔ ካንሰር መካከል ግልጽ የሆነ ዝምድና እንዳለ አመልክተዋል።
አስም:- ሌሎች የሚያጨሱትን የሲጋራ ጭስ መተንፈስ የልጆችን አስም ሊያባብስ ይችላል።
አጫሽ የመሆን አዝማሚያ:- በእርግዝናቸው ወቅት ያጨሱ ከነበሩ ሴቶች የተወለዱ ሴት ልጆች አጫሽ የመሆን ዕድላቸው ከሌሎቹ በአራት እጥፍ ይበልጣል።
ሉኪሚያ:- ማጨስ ማየሎይድ ሉኪሚያ የሚያመጣ ይመስላል
በአካላዊ እንቅስቃሴ ወቅት ለሚደርስ ጉዳት መጋለጥ:- የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሠራዊት ጥናት እንደሚያመለክተው አጫሾች በአካላዊ እንቅስቃሴ ወቅት ለሚደርስ ጉዳት ይበልጥ የተጋለጡ ናቸው።
የማስታወስ ችሎታ:- ከፍተኛ መጠን ያለው ኒኮቲን መውሰድ አንድ ሰው ውስብስብ የሆነ ተግባር በሚያከናውንበት ጊዜ የአእምሮ ቅልጥፍናው እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል።
የመንፈስ ጭንቀት:- የሥነ አእምሮ ሐኪሞች በማጨስና በመንፈስ ጭንቀት እንዲሁም ስኪዞፍሬንያ በሚባለው የአእምሮ ሕመም መካከል ዝምድና መኖሩን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ለማግኘት ምርምር በማካሄድ ላይ ናቸው።
ራስን መግደል:- በነርሶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት አጫሽ ነርሶች ራሳቸውን የመግደል ዕድላቸው ከማያጨሱት በሁለት እጥፍ እንደሚበልጥ አመልክቷል።
በዚሁ ዝርዝር ላይ ሊጨመሩ የሚችሉ ሌሎች አደጋዎች:- የአፍ፣ የማንቁርት፣ የጉሮሮ፣ የቆሽት፣ የጨጓራ፣ የትንሹ አንጀት፣ የፊኛ፣ የኩላሊትና የማኅፀን አፍ ካንሰር፤ ስትሮክ፣ የልብ በሽታ፣ ሥር የሰደደ የሳንባ በሽታ፣ የደም ዝውውር በሽታ፣ የሆድ ዕቃ መቁሰል፣ የስኳር በሽታ፣ መሃንነት፣ አነስተኛ ክብደት ያለው ልጅ መውለድ፣ የአጥንት መልፈስፈስ፣ የጆሮ በሽታ። በመኖሪያ ቤቶች፣ በሆቴሎችና በሆስፒታሎች ላይ ለሚደርስ ቃጠሎ ዋነኛው ምክንያት ሲጋራ ማጨስ በመሆኑ የእሳት አደጋም በዚሁ ዝርዝር ውስጥ ሊካተት ይችላል።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ጭስ አልባ ትምባሆ፣ አደገኛ አማራጭ
ባለ 1.1 ቢልዮን ዶላሩን የሱረት ኢንዱስትሪ በግንባር ቀደምትነት የሚመራው ኩባንያ ማጣፈጫ በተጨመረለት ማጥመጃው እያማለለ አዳዲስ ሰዎችን ወደ ወጥመዱ ያስገባል። በጣም እውቅ የሆኑ ማጣፈጫ የተጨመረላቸው የሱረት ዓይነቶች አሉት። እነዚህ የሱረት ዓይነቶች የሚፈጥሩት “አነስተኛ የትምባሆ ስካር” የሚያረካቸው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው። የዚህ ትምባሆ ኩባንያ የቀድሞ ምክትል ሊቀ መንበር “ብዙ ሰዎች ለስለስ ባሉት ምርቶች ቢጀምሩም ውለው አድረው [ኃይለኛ የሆኑትን] መውሰድ ይጀምራሉ” ብለዋል። “ጠንካራ ሰዎች ኃይለኛውን ያኝካሉ። የበለጠ እርካታም ያገኙበታል” የሚሉ ማስታወቂያዎች ይነገራሉ።
ይህን የኩባንያውን ዘዴ ሪፖርት ያደረገው ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ኩባንያው “የኒኮቲን መጠን ከፍ እንዲል” ማድረጉን እንደካደ ጠቅሷል። በተጨማሪም ሁለት የኩባንያው የቀድሞ ኬሚስቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ስለጉዳዩ በሰጡት አስተያየት “ኩባንያው የኒኮቲን መጠን ከፍ እንዲል ባያደርግም ወደ ተጠቃሚዎች ሰውነት የሚገባው ኒኮቲን መጠን ከፍ እንዲል የሚያደርጋቸው ነገሮች አሉ” እንዳሉ ጆርናል ገልጿል። ከዚህም በላይ ኩባንያው የሱረት አልካሊነት ባሕርይ (alkalinity) ከፍ እንዲል እንደሚያደርግ ተናግረዋል። የሱረቱ አልካሊነት በጨመረ መጠን “ወደ ሰውነት የሚገባው ኒኮቲን መጠን ከፍ ይላል።” ጆርናል ሱረትንና የሚታኘክ ትምባሆን በተመለከተ የሚከተለውን ማብራሪያ አክሏል:- “አንዳንድ ጊዜ ሱረት የሚታኘክ ትምባሆ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል፤ ሆኖም ሱረት የሚታኘክ ሳይሆን የሚመጠጥ ደቃቅ ትምባሆ ነው። ተጠቃሚዎቹ በእጃቸው ቆንጠር ያደርጉና በጉንጫቸውና በድዳቸው መካከል ካስቀመጡት በኋላ በምላሳቸው እያላወሱ አልፎ አልፎ ምራቃቸውን ይተፋሉ።”
ለጀማሪዎች ከሚዘጋጀው ጣዕም የተጨመረበት ሱረት ወጥቶ ወደ ተጠቃሚዎች ደም የሚገባው ኒኮቲን መጠን ከ7 እስከ 22 በመቶ ይደርሳል። በጣም ኃይለኛ የሆነው ዓይነት አዲስ ተጠቃሚዎችን ቋቅ ሊላቸው ይችላል። “ወንድ” ነኝ ለሚሉ ሰዎች ደቃቅ ሆኖ የሚዘጋጅ ነው። በውስጡ ከሚይዘው ኒኮቲን ሰባ ዘጠኝ በመቶ የሚሆነው ወዲያው ወደ ተጠቃሚው ደም የመግባት ችሎታ አለው። በዩናይትድ ስቴትስ ሱረት መቅመስ የሚጀመርበት አማካይ ዕድሜ ዘጠኝ ዓመት ነው። ኃይለኛ ወደሆኑት ዓይነቶች ሳይሸጋገርና ከ“እውነተኛ” ወንዶች ጎራ ሳይቀላቀል ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ይኖራልን?
በዚህ መንገድ ወደ ሰውነት የሚገባው ኒኮቲን መጠን ከሲጋራ ከሚገኘው ኒኮቲን ይበልጥ ኃይለኛ ነው። ሱረት ወሳጆች በአፍ ካንሰር የመያዛቸው እድል ከሌሎች ሰዎች በ4 እጥፍ ሲበልጥ በጉሮሮ ካንሰር የመያዛቸው እድል ደግሞ በ50 እጥፍ ይበልጣል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እውቅ ሯጭ የሆነ ልጅዋ በአፍ ካንሰር የሞተባት አንዲት እናት በአንድ የትምባሆ ኩባንያ ላይ ክስ እንደመሠረተች በተሰማበት ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ የሆነ ሕዝባዊ ቁጣ ለጊዜው ፈንድቶ ነበር። ይህ ልጅ ገና በ12 ዓመት ዕድሜው በአንድ የውድድር ቦታ አንድ ጣሳ ሱረት በነጻ ከተሰጠው በኋላ በሳምንት አራት ጣሳ ሱረት እስከ መጨረስ ደርሷል። በምላሱ፣ በመንጋጋውና በአንገቱ ላይ ከፍተኛ ሕመም የሚያስከትሉ ቀዶ ሕክምናዎች ከተካሄዱ በኋላ በመጨረሻ ሐኪሞቹ ተስፋ ቆርጠው ተዉት። ይህ ወጣት በ19 ዓመት ዕድሜው ሞተ።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ማጨስ ማቆም የሚቻለው እንዴት ነው?
በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከኒኮቲን ሱስ ተላቅቀዋል። አንተም አጫሽ ከሆንክ፣ የብዙ ዓመታት አጫሽ እንኳን ብትሆን ይህን ጎጂ የሆነ ልማድ እርግፍ አድርገህ ለመተው ትችላለህ። ሊረዱህ የሚችሉ ጥቂት ሐሳቦች እነሆ:-
• ምን ዓይነት ስሜት ሊሰማህ እንደሚችል በቅድሚያ እወቅ። ማጨስ በምታቆምበት ጊዜ የመረበሽ ስሜት፣ መነጫነጭ፣ ማዞር፣ ራስ ምታት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ የሆድ ዕቃ መረበሽ፣ ረሃብ፣ አምሮት፣ በአንድ ነገር ላይ ማተኮር አለመቻልና መንቀጥቀጥ ሊያጋጥምህ ይችላል። እነዚህ ሁሉ ደስ የሚሉ ስሜቶች እንዳልሆኑ የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ በጣም ኃይለኛ የሆነው መጥፎ ስሜት እንኳን የሚቆየው ለጥቂት ቀናት ብቻ ሲሆን በሰውነት ውስጥ የተጠራቀመው ኒኮቲን እየወጣ ሲሄድ ቀስ በቀስ ይጠፋል።
• አሁን ደግሞ የአእምሮ ውጊያ ይጀምራል። ሰውነትህ ኒኮቲን ለማግኘት ከመናፈቁ በተጨማሪ አእምሮህ ከማጨስ ጋር ዝምድና ባላቸው ጠባዮች ተጠምዷል። ሳይታወቅህ ሲጋራ የምትጨብጥባቸውን ሁኔታዎችና ጊዜያት ለይተህ በማወቅ በእነዚህ ጊዜያት ሌላ ነገር ለማድረግ ጣር። ለምሳሌ ያህል ሁልጊዜ ከምግብ በኋላ የምታጨስ ከሆነ ምግብህን እንደጨረስክ ወዲያው ዞር ዞር ለማለት ወይም ሣህኖችን አነሳስተህ ለማጠብ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።
• እንደ ብስጭት ባሉ ምክንያቶች የተነሣ ማጨስ በጣም ሲያምርህ ይህ አምሮትህ አብዛኛውን ጊዜ በአምስት ደቂቃ ውስጥ እንደሚጠፋ አስታውስ። ደብዳቤ እንደመጻፍ፣ አካላዊ እንቅስቃሴ እንደማድረግና ጤናማ የሆነ ምግብ እንደ መቀማመስ ባሉ በሚያስረሱ ድርጊቶች አእምሮህን ለማስጠመድ ዝግጁ ሁን። ጸሎት ራስን በመግዛት ረገድ የሚሰጠው እርዳታ በጣም ከፍተኛ ነው።
• ያደረግኸው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካልህ ቀርቶ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። አስፈላጊው ነገር ሙከራህን አለማቆምህ ነው።
• ማጨስ ለማቆም የምታመነታው ክብደት የመጨመር ሥጋት ስለኖረህ ከሆነ ሲጋራ ማጨስ በማቆም የምታገኘው ጥቅም ጥቂት ኪሎ መጨመር ከሚያስከትለው ችግር ጋር ሊተካከል እንደማይችል አስታውስ። ሁልጊዜ ፍራፍሬ ወይም አትክልት ከአጠገብህ እንዳይለይ ማድረግ ሊረዳህ ይችላል። በተጨማሪም ብዙ ውኃ ጠጣ።
• ማጨስ ማቆም አንድ ነገር ሲሆን ከትምባሆ እንደራቁ መኖር ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ላለማጨስ ግብ አውጣ:- ለአንድ ቀን፣ ለአንድ ሳምንት፣ ለሦስት ወር፣ እንዲያም ሲል ለዘላለም።
ኢየሱስ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ብሏል። (ማርቆስ 12:31) ባልንጀራህን እንደምትወድ ለማሳየት ማጨስ አቁም። ራስህን እንደምትወድ ለማሳየት ማጨስ አቁም።—በተጨማሪም ንቁ! ጥቅምት–ታኅሣሥ 1994 ከገጽ 13–15 ላይ የሚገኘውን “ማጨስና ክርስቲያናዊ አመለካከት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።