የአስቤስቶስ ታሪክ ከሕይወት መድህንነት ወደ ሞት ጥላነት
ዩኤስ ኤ አሪዞና ውስጥ ለተጎታች ቤቶች በተዘጋጀ አንድ መንደር የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ቤት ንብረታቸውን ለመንግሥት ሸጠው አካባቢውን ለመልቀቅ መገደዳቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በመንደሩ ውስጥ የነበረው ማንኛውም ነገር፣ ከተጎታች ቤቶቹ አንስቶ ዕቃ የተባለ ነገር ሁሉ፣ የሕፃናት አሻንጉሊት እንኳ ሳይቀር ሙሉ በሙሉ ወድሞ በማጥለያ-ወረቀት፣ በጠጠርና በአፈር ንብር እንዲቀበር ተደርጓል። ይህ እርምጃ የተወሰደው ለምንድን ነው? በጨረር፣ በመርዘኛ ኬሚካሎች ወይም ደግሞ በተበከለ ውኃ ሳቢያ ነው? አይደለም። ሥፍራው የአንድ አሮጌ ፋብሪካ ዝቃጭ የተጣለበት ነበር። በአስቤስቶስ የተበከለ ነበር።
ይህ ያለንበት መቶ ዘመን አስቤስቶስ በከፍተኛ ነውጥ ውስጥ ያለፈበት ዘመን ነው ማለት ይቻላል። በአንድ ወቅት ትልቅ ግምት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም የኋላ ኋላ እንደ አልባሌ ነገር ተቆጥሯል። በኢንዱስትሪው ዓለም እንደ ብርቅ ይታይ እንዳልነበረና የብዙዎችን ሕይወት ከእሳት የታደገ ተብሎ እንዳልተወደሰ ሁሉ ዛሬ ቃል በቃል በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ተጠያቂ ተደርጎ በመወንጀል ላይ ይገኛል። አስቤስቶስ በግንባታው ኢንዱስትሪ ላይ ከአንዴም ሁለቴ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ይነገርለታል። መጀመሪያ አስቤስቶስን ለግንባታ የመጠቀም ዓለም አቀፍ አዝማሚያ ታይቶ የነበረ ሲሆን በኋላ ደግሞ ይህንኑ የግንባታ ዕቃ በጥድፊያ ለማስወገድ ተሞክሯል።
ትምህርት ቤቶች፣ ቢሮዎችና አፓርታማዎች ተዘግተዋል። ይህ ደግሞ በግብር ከፋዮች በቤት አከራዮችና በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አስከትሏል። ፍርድ ቤቶች በክስ ማዕበል ተጥለቅልቀዋል። ፍራቻ ራሱ የብዙዎችን ሕይወት ለውጧል። ይህ ሁሉ የአስቤስቶስ ጦስ ነው።
ይሁን እንጂ አስቤስቶስ ምንድን ነው? የሚገኘውስ ከየት ነው? በእርግጥ የሚባለውን ያህል አደገኛ ነው?
የተዥጎረጎረ ታሪክ
አስቤስቶስ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ግቡን ሳይመታ የቀረ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤት ወይም ላቦራቶሪ ውስጥ ተፈልስፎ መጨረሻው ያላማረ የፈጠራ ችሎታ ውጤት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አስቤስቶስ ከመሬት ተቆፍሮ የሚወጣ ማዕድን ነው። ወይም ደግሞ አስቤስቶስ የማዕድናት መደብ ነው ተብሎ ይበልጥ በትክክል ሊገለጽ ይችላል። የአስቤስቶስ ዓይነቶች ስድስት ሲሆኑ አንዳቸው ከሌላው ፈጽሞ የተለዩ ናቸው። ሆኖም በይዘት ደረጃ ሁሉም ጭረት (fiber) ያላቸው ከመሆኑም በላይ ሁሉም ሙቀት የመቋቋም ከፍተኛ አቅም አላቸው።
ሰዎች አስቤስቶስን በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲጠቀሙበት ኖረዋል። ከክርስቶስ ልደት በፊት ብዙ መቶ ዘመናት አስቀድሞ የፊንላንድ ገበሬዎች ለሸክላ ሥራ ይጠቀሙበት የነበረ ከመሆኑም በላይ ከእንጨት በተሠሩ ጎጆዎቻቸው ላይ ያሉትን ክፍት ክፍት ቦታዎች ይደፍኑበት ነበር። የጥንቶቹ ግሪኮች ለፋኖስ የሚሆኑ ክሮችን ለመሥራት ይጠቀሙበት ነበር። ጥንታውያኑ ሮማውያን ደግሞ የአስቤስቶስ ጭረቶችን ወደ ሸማነት በመለወጥ ፎጣ፣ የዓሣ መረብና አልፎ ተርፎም ሻሽ ይሠሩ ነበር። እነዚህን ጨርቆች ማጽዳቱ ቀላል ነበር። የሚንቀለቀል እሳት ውስጥ ብትጨምሯቸው ነጭ ሆነውና ጠርተው ይወጣሉ!
በመካከለኛው ዘመን ንጉሠ ነገሥት ሻርለማኝ ወደ እርሱ የመጡ አንዳንድ በርባሮሶችን ከአስቤስቶስ የተሠራ የጠረጴዛ ጨርቅ እሳት ውስጥ ጨምሮ ምንም ሳይሆን መልሶ በማውጣት መለኮታዊ ኃይል እንዳለው አድርጎ አሳምኗቸው እንደነበረ ይነገራል። በመካከለኛው ዘመን የነበሩ አንዳንድ ብልጣ ብልጥ ነጋዴዎች እሳት የመቋቋም ኃይላቸውን እንደ ማስረጃ አድርገው በመጥቀስ “ከእውነተኛው መስቀል” እንጨት የተሠሩ ናቸው እያሉ የአስቤስቶስ መስቀሎችን ይሸጡ ነበር!
ይሁን እንጂ አስቤስቶስ እስከ 19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ድረስ የማወቅ ጉጉት ከማሳደር አልፎ ብዙም የፈየደው ነገር አልነበረም። ይህ ሁኔታ በኢንዱስትሪው ዘመን ተለወጠ። በ1800ዎቹ ዓመታት የኢንዱስትሪው ዓለም አስቤስቶስ እሳትን ብቻ ሳይሆን ዝገትንም እንደሚቋቋምና ኤሌክትሪክ እንደማያስተላልፍ ተገነዘበ። ብዙም ሳይቆይ አስቤስቶስ ጣሪያ፣ ኮርኒስ፣ የወለል ንጣፍ፣ ከለላ (insulation)፣ አርማታ፣ የሲሚንቶ ቧንቧ፣ ሬንጅ፣ የቲያትር ቤት መጋረጃ፣ ፍሬን ሸራና አልፎ ተርፎም ማጥለያ ይሠራበት ጀመር። ውሎ አድሮ ወደ 3,000 ለሚጠጉ ግልጋሎቶች ዋለ።
ብዙም ሳይቆይ አስቤስቶስ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ ለሄደው ኢንዱስትሪ ምሰሶ ሆነ። በሶቭየት ኅብረት የዩራል ተራሮች፣ በሰሜናዊ ጣሊያን የአልፕስ ተራሮች፣ በዩናይትድ ስቴትስ ቨርሞንትና በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የአስቤስቶስ ክምችት ተገኘ። በ1970ዎቹ ዓመታት አጋማሽ የዓለም የአስቤስቶስ ምርት በዓመት ስድስት ሚልዮን ቶን ገደማ ደርሶ ነበር።
ያስከተለው መዘዝ
አስቤስቶስ በዚህ መልኩ በድንገት ከፍተኛ ተወዳጅነት ያግኝ እንጂ የራሱ የሆነ ስጋት ፈጥሮ ነበር። እንዲያውም ከ19 መቶ ዘመናት ቀደም ብሎ ሮማዊው ታሪክ ጸሐፊ ፕሊኒ በአስቤስቶስ ማዕድን ማውጫዎች የሚሠሩ ባሪያዎች የመተንፈሻ አካላት ችግር እንደሚታይባቸው ገልጾ ነበር። ፕሊኒ የማስጠንቀቂያ ድምፅ ካሰሙት በርካታ ሰዎች አንዱ ብቻ ነበር።
በ1900ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ በአውሮፓ የነበሩ ዶክተሮች የአስቤስቶስ ሠራተኞች በመተንፈሻ አካላት ሕመም ሕይወታቸው እየተቀጠፈ መሆኑን መገንዘብ ጀምረው ነበር። እንዲያውም በ1918 አንዳንድ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የአስቤስቶስ ሠራተኞች ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ዕድሜያቸው አጭር በመሆኑ ለእነዚህ ሠራተኞች የመድን ዋስትና ለመስጠት አሻፈረን ብለው ነበር። በ1930ዎቹ ዓመታት የተካሄዱ የአስከሬን ምርመራዎች ለአስቤስቶስ በእጅጉ መጋለጥ ለሞት ሊዳርግ እንደሚችል አረጋግጠዋል። በብዙ የአስቤስቶስ ዓይነቶች ውስጥ የሚገኙት ጥቃቅን የሆኑ የመርፌ ቅርፅ ያላቸው ቡረሌዎች እስከ ሳንባ አልፎ ተርፎም እስከ ዋና ህልፅ (abdominal cavity) ድረስ ዘልቀው ሊገቡና ረዘም ላለ ጊዜ እዚያው ሊቆዩ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ በሽታ የሚያስከትሉት አሥርተ ዓመታት ካለፉ በኋላ ነው። ከአስቤስቶስ ጋር ዝምድና ያላቸው በሰፊው የሚታወቁ አንዳንድ በሽታዎች ከዚህ ቀጥሎ ተዘርዝረዋል:-
አስቤስቶሲስ። በተለይ ረዘም ላለ ጊዜ ለአስቤስቶስ የተጋለጡ ሰዎችን በብዛት የሚያጠቃ ተስፋፍቶ የሚገኝ ሕመም ነው። ቀስ በቀስ ሳንባን የሚያቆረፍድና በሳንባ ውስጥ ያሉትን የአየር ማስገቢያዎች የሚያጠብ የሳንባ ህብረህዋስ ጠባሳ ነው። አስቤስቶሲስ የመተንፈስ ችግር የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ ሳንባ እንደ ሳንባምችና ብሮንካይተስ በመሳሰሉ በሽታዎች በቀላሉ እንዲጠቃ ያደርጋል። እነዚህ በሽታዎች ደግሞ በዚህ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ ሰዎች ይበልጥ አደገኞች ናቸው። አስቤስቶሲስ ፈውስ የሌለው በሽታ ሲሆን ለሞት ሊዳርግ ይችላል።
የሳንባ ካንሰር። የሳንባ ካንሰርም በእጅጉ ተስፋፍቶ የሚገኝ በሽታ ሲሆን ከአስቤስቶሲስ የበለጠ ብዙ ሰዎችን ለሕልፈተ ሕይወት ይዳርጋል። የሚያስገርመው ደግሞ ሲጋራ የሚያጨስ ሰው ለአስቤስቶስ ቢጋለጥ በሳንባ ካንሰር ሊያዝ የሚችልበት አጋጣሚ ከፍተኛ ነው። ሲጋራ ማጨስና ለአስቤስቶስ መጋለጥ በተናጠል ሊያስከትሉ የሚችሉት አደጋ ቢደመር እንኳ የዚያን ያህል የከፋ አይሆንም።
ሜዞቲሊኦማ። አልፎ አልፎ የሚከሰት እጅግ አደገኛ የሆነ ገዳይ የካንሰር ዓይነት ነው። በደረት ወይም ደግሞ በዋና ልህፅ ላይ የሚገኝን ገለፈት የሚያጠቃ በሽታ ነው። ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ለማዕድኑ በተጋለጠ ሰው ላይም እንኳ ሊከሰት የሚችል ሲሆን ምንም ምልክት ሳይሰጥ 40 ዓመት ያህል ሊቆይ ይችላል።
ኢንተርናሽናል ጆርናል ኦቭ ሄልዝ ሰርቪስስ እንዳለው ከሆነ አስቤስቶስ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ ከ1986 እስከ 2000 ባሉት ዓመታት ከሁለት መቶ እስከ ሦስት መቶ ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን በሚያሳዝን መንገድ አለጊዜያቸው ለሕልፈተ ሕይወት ይዳርጋቸዋል። ይህ እውነት ሆኖ ከተገኘ ቁጥሩ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያለቁትን የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች የሚተካከል ይሆናል።
የተጋነነ አመለካከት ነውን?
ይሁን እንጂ አስቤስቶስ የፈጠረውን ስጋት በተመለከተ ያለው አመለካከት በእጅጉ ተጋንኗል የሚሉ ሳይንቲስቶችም አሉ። አንዳንድ ሳይንቲስቶች አደጋውን በጣም በማጋነናቸው እንደ ወረርሽኝ የተስፋፋው “የአስቤስቶስ ጥላቻ” ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ አመዝኗል ይላሉ።
ለምሳሌ ያህል የሕክምና ኮሌጅ የሆነው የቬርሞንት ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ በሆኑት በብሩክ ሞስማን የሚመራ አንድ የሳይንቲስቶች ቡድን በሳይንስ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ሪፖርት ጽፎ ነበር። ሞስማንና ባልደረቦቻቸው ሰዎች ለአደጋው የሚጋለጡበትን ሁኔታ ፈጽሞ ጉዳት በማያስከትል ደረጃ ለመቀነስ በሚል አስቤስቶስን ከቢሮ ሕንፃዎችና ከትምህርት ቤቶች ለማስወገድ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መፍሰሱን አጥብቀው አውግዘዋል።
እንዲያውም አስቤስቶሱን ለማስወገድ ዕቅድ ከተነደፈላቸው ሕንፃዎች መካከል አንዳንዶቹ በውስጣቸው ያለው አየር የያዘው የአስቤስቶስ መጠን በውጪ ያለው አየር ካለው የአስቤስቶስ መጠን ያነሰ ነው ብለዋል! ልጆች በመብረቅ ሊመቱ የሚችሉበት ወይም ብስክሌት ሲነዱ ለአደጋ የሚጋለጡበት አጋጣሚ ይህን ያህል አነስተኛ መጠን ያለው አስቤስቶስ አደጋ ሊያስከትል ከሚችልበት አጋጣሚ በእጅጉ እንደሚበልጥ የሚያሳዩ አኃዛዊ መረጃዎችም ተጠቅሰዋል። ከዚህም ሌላ ብዙዎቹ አስቤስቶስን ለማስወገድ የተወሰዱት እርምጃዎች ጥድፊያ የተሞላባቸው ከመሆናቸውም በላይ የግብር ይውጣ ሥራዎች በመሆናቸው አቧራው ሁሉ በንኖ በሕንፃዎቹ ውስጥ ያለው የአስቤስቶስ መጠን እንዲጨምር አድርገዋል። ከዚህ ሁሉ አስቤስቶሱን ባለበት ትቶ እዚያው ማሸጉ ይመረጥ ነበር።
በተጨማሪም ብዙ የአውሮፓ አገሮች ስለ አስቤስቶስ ባወጧቸው ሕጎች ላይ እንደገለጹት የመርፌ ቅርጽ ያላቸው ጭረቶች የሚገኙት በሁሉም የማዕድኑ ዓይነቶች ላይ አይደለም። ክሪሲቲል አስቤስቶስ ረጅምና ጥምዝ ከሆኑ ጭረቶች የተሠራ ሲሆን ሳንባ እነዚህን ብናኞቸ በቀላሉ ማጥመድና ማስወጣት ይችላል። በዓለም ዙሪያ ከሚመረተው አስቤስቶስ መካከል 95 በመቶ የሚሆነው የክሪሲቲል አስቤስቶስ ዘር ነው። ለሜዞቲሊኦማ በሽታ ዋነኛ መንስኤ ነው ተብሎ የሚገመተው አምፈቦል አስቤስቶስ ጥቅም ላይ የሚውለው አልፎ አልፎ ነው።
በተጨማሪም ሞስማንና ባልደረቦቻቸው አንዲት የአስቤስቶስ ጭረት እንኳን ለሞት ልትዳርግ ትችላለች የሚለውን ‘የአንድ-ጭረት ጽንሰ ሐሳብ’ አይቀበሉትም። አስቤስቶስ በተፈጥሮ ያለ ነገር ነው። አንድ የሳይንስ መጽሔት አዘጋጅ እንዳሉት ከሆነ ሁላችንም በየዓመቱ ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጉ የአስቤስቶስ ጭረቶችን ከምንስበው አየር ጋር ወደ ውስጣችን እናስገባለን!
ያም ሆኖ ግን እነዚህ ነጥቦች የሁሉንም ሳይንቲስቶች አቋም የሚያለሳልሱ ሆነው አልተገኙም። በ1964 አስቤስቶስ የሚያስከትለውን ጉዳት በተመለከተ ትልቅ እመርታ የታየበት ጥናት ያካሄዱት ዶክተር ኧርቪንግ ጄ ሴልኮፍ አነስተኛ መጠን ላለው አስቤስቶስ መጋለጥ አደገኛ ሊሆን ይችላል የሚል ጠንካራ አቋም አላቸው። ብዙ ሳይንቲስቶች በእሳቸው አባባል ይስማማሉ። ይበልጥ የሚያሳስቧቸው ደግሞ የትምህርት ቤት ሕንፃዎች ናቸው። አደጋውን የሚያስከትሉት በአስቤስቶስ የተሸፈኑ ቧንቧዎችንና ውኃ ማሞቂያዎችን የመሳሰሉ አስቤስቶስ ያላቸው የተወሰኑ ነገሮች በመሆናቸው በሕንፃዎች ውስጥ ባለው አየር ውስጥ የሚኖረውን የአስቤስቶስ መጠን እንዲሁ መለካቱ ብቻ ትርጉም የለውም ይላሉ። የማወቅ ጉጉት ያደረባቸው ወይም ተንኮለኛ የሆኑ ልጆች እነዚህን ከአስቤስቶስ የተሠሩ ነገሮች ማግኘታቸውና መነካካታቸው አይቀርም። የጥገናና የጽዳት ሠራተኞች ሁልጊዜ ለዚህ የተጋለጡ ሊሆኑ ይችላሉ።
ሳይንቲስቶች ክሪሲቲል አስቤስቶስ በሚያስከትለው ጉዳት ረገድም የሐሳብ ልዩነት አላቸው። በ1990 የጸደይ ወር ላይ የተካሄደ አንድ ዓለም አቀፍ የሳይንቲስቶች ጉባኤ ክሪሲቲል የሌሎቹን የአስቤስቶስ ዓይነቶች ያህል አደገኛ እንደሆነ በመግለጽ ሳይንስ መጽሔት ላይ ለወጣው የሞስማን ሪፖርት ምላሽ ሰጥቷል። በተጨማሪም አንዳንዶች አስቤስቶስ የሚያስከትላቸውን አደጋዎች የሚያቃልሉ ሳይንቲስቶች የአስቤስቶስ ኢንዱስትሪ መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀምባቸው ናቸው ሲሉ ይከሳሉ። የአስቤስቶስ ኢንዱስትሪ ችሎት ፊት ቆመው እንዲመሰክሩለት ለአንዳንዶቹ ጉርሻ ይሰጣል ባዮች ናቸው።
ስግብግብነት የሚጫወተው ሚና
እንዲህ ዓይነቶቹ ክሶች እውነት ከሆኑ ተከሳሾቹን ስግብግቦች የሚያሰኙ ናቸው። ያም ሆነ ይህ ግን ሐቁ ስግብግብነት በዚህ መቶ ዘመን በአስቤስቶስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ያሳያል።
የአስቤስቶስ ኢንዱስትሪ ለአስቤስቶስ መጋለጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ከሠራተኞቹ በመደበቁ በከፍተኛ ስግብግብነት ሲወነጀል ቆይቷል። የአስቤስቶስ ፋብሪካ ባለቤቶች ሠራተኞቻቸው ሊደርስባቸው የሚችለውን አደጋ እንዳያውቁ በማድረጋቸው ብዙ ፍርድ ቤቶች የጉዳት ካሳ እንዲከፍሉ በይነውባቸዋል። ይህ ሁሉ ውዝግብ እያለም የአስቤስቶስ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን በአስቤስቶስ ላይ እገዳ ወዳልጣሉ ያልበለጸጉ አገሮች መላካቸውን ቀጥለዋል። በእነዚህ አገሮች ደግሞ የፋብሪካ ሠራተኞች ከአስቤስቶስ በሚገባ መጠበቅ የሚችሉበት የተሟላ ዝግጅት የለም።
አስቤስቶስን ለማስወገድ በሚካሄደው እንቅስቃሴም ስግብግብነት ይታያል የሚል ክስ ሲቀርብ ቆይቷል። ተቺዎች ለዚህ ዓላማ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ አጥብቀው ይቃወማሉ። ብዙውን ጊዜ በአንድ ካሬ ሜትር ላይ ያለን አስቤስቶስ ለማስወገድ ከ250 እስከ 500 የአሜሪካን ዶላር የሚወጣ ሲሆን ይህ አስቤስቶሱን ለመግጠም ከሚወጣው ወጪ ጋር ሲነጻጸር እንኳ መቶ እጥፍ ይበልጣል። ሙስና እንደሚፈጸም የሚገልጹ ሪፖርቶችም አሉ። አስቤስቶስን በማስወገድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ብዙዎቹ ተቋሞች ሕገወጥና አደገኛ የሆኑ የአስቤስቶስ የማስወገጃ ዘዴዎችን ሲጠቀሙ በቸልታ እንዲያልፏቸው ሲሉ ለመንግሥት ባለ ሥልጣናት ጉቦ ሲሰጡ ተይዘዋል። ምግባረ ብልሹ የሆኑ ከበርቴዎች ገንዘባቸውን ለመቆጠብ ሲሉ አግባብ ባልሆነ መንገድ አስቤስቶስን ከሚያስወግዱ ተቋሞች ጋር ይዋዋላሉ። የእነዚህ ተቋሞች ሠራተኞች ብዙውን ጊዜ ሥራቸው የሚያስከትለውን ጉዳት የማያውቁና ምንም መከላከያ የማያደርጉ ከመሆናቸውም በላይ አስቤስቶሱን ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በመናፈሻ ቦታዎች ሳይቀር የትም የሚጥሉ መሆናቸው ታውቋል።
አስቤስቶስና አንተ
ሆኖም በዚህ አሳዛኝ ታሪክ መካከልም ቢሆን የተስፋ ጭላንጭል ይታያል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙዎች አስቤስቶስ የሚያስከትላቸውን የተለያዩ አደጋዎች በመገንዘብ ላይ ናቸው። ብዙ መንግሥታት አንድም አስቤስቶስ በሚሰጠው ግልጋሎት ላይ ገደብ እየጣሉ ነው፤ አለዚያም ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ከዚህ ማዕድን ጋር ዝምድና ያላቸውን ሥራዎች የሚሠሩ ሠራተኞች መከላከያ እንዲጠቀሙ በማድረግ ላይ ናቸው።
ቤትህ ውስጥ ወይም በምትሠራበት ቦታ አስቤስቶስ እንዳለ የሚሰማህ ከሆነስ? በመጀመሪያ ደረጃ አስቤስቶስ መሆን አለመሆኑን በእርግጠኝነት ማወቅ የምትችለው በላቦራቶሪ ከተመረመረ ብቻ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መረበሽ የለብህም። አንዳንዶች በጣም ከመረበሻቸው የተነሳ አስቤስቶሱን ራሳቸው ለማስወገድ ሞክረዋል። ይህ ብዙውን ጊዜ ሕገወጥ ከመሆኑም በላይ አስቤስቶሱን እዚያው ባለበት መተዉ ሊያስከትል ከሚችለው የከፋ አደጋ ያስከትላል። ማንኛውንም እርምጃ ከመውሰድህ በፊት ባለሙያ አማክር። እንደ ሁኔታው አስቤስቶሱን እንዲያስወግድ አለዚያም እዚያው ባለበት እንዲያሽገው የምንፈቅደው በዚህ ረገድ ጥሩ ስም ያተረፈና ሕጋዊ ፈቃድ ላለው ተቋም ብቻ መሆን ይገባዋል።
አስቤስቶሱን ማስወገድ የምትችልበት ምንም መንገድ ከሌለ የቱንም ያህል አስቸጋሪ መስሎ ቢታይህ መከላከያ አጥልቀህ መሥራትህና ቃጫዎቹ እንዳይበኑ ዕቃውን ማራስህ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ግብፅ ውስጥ በ405 ሠራተኞች ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት ከአስቤስቶስ ጋር ዝምድና ያለው ሥራ በሚሠሩበት ጊዜ መከላከያቸውን የሚጠቀሙት 31.4 በመቶዎቹ ብቻ እንደሆኑ አመልክቷል።
በመጨረሻም፣ ከማጨስ መታቀብ ይኖርብሃል! በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአስቤስቶስ ሠራተኞች ላይ በተካሄደ አንድ ጥናት አጫሾች ከአስቤስቶስ ጋር ዝምድና ባላቸው በሽታዎች የመያዛቸው አጋጣሚ ከሌላው ሰው 50 በመቶ ገደማ የሚጨምር መሆኑ እየታወቀና ሠራተኞቹ ካንሰር እንዳይዛቸው በጣም የሚጨነቁ ሆነው እያለ 34 በመቶ የሚሆኑት አጫሾች ሆነው ተገኝተዋል።
እርግጥ ነው፣ አስቤስቶስ ምን ያህል አደገኛ ነው በሚለውም ሆነ አንድ ሰው ጉዳት ሊደርስበት የሚችለው ለምን ያህል የአስቤስቶስ መጠን ቢጋለጥ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ጠበብት አሁንም ድረስ አልተስማሙም። ምናልባትም የሰው ልጅ ‘ምድርን ማጥፋቱንና’ የምድርን የተፈጥሮ ሀብት ያለአግባብ መጠቀሙን የሚያቆምበት ጊዜ እስከሚመጣ ድረስ የተለያዩ አኃዛዊ መረጃዎችንና ጥናቶችን እየተሰናዘሩ መከራከራቸውን ይቀጥሉ ይሆናል። (ራእይ 11:18) እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ራስን ለአደጋ የማያጋልጠውን እርምጃ መውሰዱ ጥበብ ነው።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአስቤስቶስ ብክለት መከላከያ ክፍሎችን ጨምሮ ከአስቤስቶስ ጋር ግንኙነት ያለው ሥራ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ዓይነተኛ ምሳሌ። ከግራ ወደ ቀኝ:- 1. የሥራ ቦታ፤ 2. ዕቃ ማስቀመጫ ክፍል፤ 3. ብክለት መከላከያ ክፍል፤ 4. መታጠቢያ ቤት፤ 5. ብክለት መከላከያ ክፍል፤ 6. ከብክለት ነፃ የሆነ ክፍል