‘የምታከናውኑት ሥራ ለማኅበረሰቡ የሚያስገኘው ጥቅም ምንድን ነው?’
ሕንዳዊው ጋዜጠኛ ቻንድራካንት ፓቴል ይህን ጥያቄ ያቀረቡት በብሩክሊን ኒው ዮርክ የሚገኘው የዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት አባል ለሆነ ሰው ነበር። ሚስተር ፓቴል ዋና መሥሪያ ቤቱን ለመጎብኘት መጥተው በነበረበት ጊዜ ባዩትና በሰሙት ነገር በጣም ከመገረማቸው የተነሳ ወደ ሕንድ ሲመለሱ በጉጃራቲ ቋንቋ ለሚዘጋጅ ጋዜጣ አንድ ጽሑፍ ጻፉ።
ሚስተር ፓቴል የይሖዋ ምሥክሮች የሚከተሏቸውን አንዳንድ ትምህርቶች በሕንድ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ተቋማት ከሚከተሏቸው ትምህርቶች ጋር በማነጻጸር አብያተ ክርስቲያናት ከሚያስተምሩት የሥላሴ መሠረተ ትምህርት በተቃራኒ የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉን ቻይ አምላክ በሆነው በይሖዋ እንደሚያምኑና በአምልኳቸው ምስሎችን እንደማይጠቀሙ ጽፈዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የላቀ የሥነ ምግባር ደረጃ ሊኖራቸው የቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ዝሙትን፣ ፅንስ ማስወረድን እንዲሁም ጥላቻን ወይም ግድያን በተመለከተ የያዛቸውን ክርስቲያናዊ መመሪያዎች በጥብቅ በመከተላቸው መሆኑን ገልጸዋል። ምሥክሮቹ ሰላማውያን፣ አፍቃሪ፣ ታጋሽና ሌሎችን የመርዳት ዝንባሌ ያላቸው እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች በማዳረስ ረገድ ደፋርና ቀናተኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ከሕንድ የመጡት ጋዜጠኛ ‘የምታከናውኑት ሥራ ለማኅበረሰቡ የሚያስገኘው ጥቅም ምንድን ነው?’ ሲሉ ላቀረቡት ጥያቄ ያገኙት መልስ ምንድን ነው? እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- ‘ለጥያቄዬ ያገኘሁት መልስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በማንኛውም የኑሮ ዘርፍ ጠቃሚ ነው የሚል ነበር።’ ሚስተር ፓቴል በይበልጥ ማወቅ የፈለጉት የጤናና የሥራ መስኮችን በተመለከተ ያለውን ሁኔታ ነበር። ካገኙት ማብራሪያ ውስጥ የተወሰነውን በመጥቀስ እንዲህ ሲሉ ዘግበዋል:- ‘አንድ ሰው እንደ ሲጋራና አደገኛ ዕፆች የመሳሰሉትን ጎጂ ነገሮች እንዲያስወግድ የተሰጠውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ከተከተለና ሥርዓታማ ሕይወት ከመራ የተለያዩ ዓይነት በሽታዎችን ማስወገድ ይችላል። እንዲሁም ትጉዎች፣ ሥርዓታማ ሕይወት የሚመሩና ሐቀኛ የሆኑ ግለሰቦች ሥራ የማግኘት አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው። በተጨማሪም ችግሮችን በደግነትና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ መፍታት ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ያስችላል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ነገር ለሰዎች ማስተማር ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ ውጤት ያስገኛል።’
እኚህ ጋዜጠኛ በዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በተግባር ሲውሉ ተመልክተዋል። ጋዜጠኛው ያዘጋጁት ጽሑፍ የመንፈሳዊ እንቅስቃሴ ማዕከል በሆነው ቦታ የሚገኙት ትጉ ፈቃደኛ ሠራተኞች ያላቸውን ንጽሕናና የደስተኝነት መንፈስ አሞግሷል። አንተም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጥቅም ማግኘት ትችላለህ። የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ጥቅም ማግኘት የምትችልበትን መንገድ ለማሳየት ዝግጁዎች ናቸው።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ከበስተ ጀርባ የሚታየው ጋዜጣ:- Courtesy Naya Padkar, Gujarati Daily published from Anand, India