የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g93 7/8 ገጽ 30-31
  • ዓለምን ስንመለከታት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዓለምን ስንመለከታት
  • ንቁ!—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሐሰት ተአምራት
  • የዓመፅ ፊልሞች ውጤት
  • “አንድም ዝንብ የሌለበት ከተማ”
  • ከፍተኛ ወጪ የሚፈስባቸው ሠርጎችን ማበረታታት
  • ቴሌቪዥን ዓለምን አጥለቅልቋታል
  • ከቤተሰብም ደም መውሰድ አስተማማኝ አይደለም
  • የተፈለገበት ቦታ ደርሶ የማያውቅ እርዳታ
  • የሲጋራ ጭስ ያስከተለው ሙግት
  • በማስመሰል ስለሚሠሩ መድኃኒቶች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
  • በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለው ልዩነት ሰፍቷል
  • ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረው የዳቦ መጋገሪያ ቤት ይሄ ይሆን?
  • በኢየሱስ ላይ ሞት የፈረደበት ሊቀ ካህን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
ንቁ!—1993
g93 7/8 ገጽ 30-31

ዓለምን ስንመለከታት

የሐሰት ተአምራት

በኢንግላንድ የሚኖሩ አንድ ዶክተር በተአምራዊ ስጦታዎች የሚያምኑ ቤተ ክርስቲያኖችና የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያኖች ፈጽመዋቸዋል የሚባሉትን ተአምራት በመመርመር ወደ 20 የሚጠጉ ዓመታት አሳልፈዋል። በለንደን የሚታተመው ዴይሊ ቴሌግራፍ በዘገበው መሠረት ዶክተሩ የሚከተለው መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል:- “በተአምራዊ ስጦታዎች የሚያምኑ ቤተ ክርስቲያኖች ፈጸምናቸው የሚሏቸው ተአምራዊ ፈውሶች በአንድም የሕክምና ማስረጃ የተደገፉ አይደሉም።” ዶክተር ፒተር ሜይ በአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ፊት ቀርበው “ፈዋሾቹ” ፈጸምናቸው ስለሚሏቸው የተለያዩ ተአምራት እውነትነት ማስረጃ የሚሆን ነገር ለማግኘት ለበርካታ ዓመታት ያደረጓቸውን ተደጋጋሚ ጥረቶች ገልጸዋል። “ብዙውን ጊዜ” አሉ “ምንም የሚያቀርቡት ነገር የለም፤ የሚቀርቡት ሐሳቦችም ቀድሞውንም ያልሆኑ ነገሮች ናቸው።” ፈጽሞ ያልሆኑ ተአምራትን የሚገልጹ ዘገባዎችን በማውጣት ጥቅም የሚያገኙ መጽሔቶችንና ቪዲዮዎችን አውግዘዋቸዋል። ቴሌግራፍ በዘገበው መሠረት ዶክተር ሜይ ግኝቶቻቸውን ከብዙ የሥራ ባልደረቦቻቸው ግኝቶች ጋር አነጻጽረውታል። “አንዳቸውም ቢሆኑ” ይላሉ “ከክርስቶስ ተአምራት ጋር የሚነጻጸር ተአምር መፈጸሙን የሚያሳይ አንድም መረጃ ማቅረብ አልቻሉም።”

የዓመፅ ፊልሞች ውጤት

ቬጃ በተባለው የብራዚል መጽሔት ላይ በተደረገው ቃለ ምልልስ የፊልም ዲሬክተር የሆኑት ስቴቨን ስፔልበርግ በፊልሞች የሚተላለፈው ዓመፅ በተመልካቾች ላይ ስለሚያስከትለው ውጤት ተጠይቀው ነበር። ስፔልበርግ እንዲህ ብለዋል:- “በፊልሞች ወይም በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች የሚተላለፈውን ዓመፅ መመልከት ተመልካቾቹ በእውን ወይም በቴሌቪዥን ዜና ላይ ከሚታየው የበለጠ ያዩትን ነገር እንዲኮርጁ ያነሳሳቸዋል። ዓመፅ በፊልሞች ላይ ሲቀርብ በጣም አሸብርቆ፣ ለዓይን የሚማርክና በቀላሉ ለመከታተል የሚቻል ሆኖ ነው። ይህም ሰዎች ለሚያዩት ነገር ልዩ ስሜት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። ዓመፅ በዜና በሚተላለፍበት ጊዜ ግን ሰዎች ዓመፅ ምን ያህል ዘግናኝ እንደሆነ ለማስተዋል የተሻለ አጋጣሚ አላቸው። ዓመፅ በዜናዎች ላይ የሚቀርብበት ዓላማ በፊልሞች ላይ ፈጽሞ አይንጸባረቅም።” ስፔልበርግ ከታወቁት ፊልሞቻቸው መካከል አንዳንዶቹን (ጄውስ፣ የኢንድያና ጆንስ ተከታታይ ፊልሞች) በውስጣቸው በሚታየው የደም ማፍሰስ ተግባርና ዓመፅ ብዛት የተነሳ ወንድ ልጃቸው እነዚህን ፊልሞች እንዲያይ እንደማይፈቅዱለት አክለው ተናግረዋል።

“አንድም ዝንብ የሌለበት ከተማ”

በቻይና የቤጂንግ ከተማ ነዋሪዎች በዝንቦች ላይ ከባድ ጦርነት አውጀዋል በማለት ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቢዩን ዘግቧል። “ዓላማችን አንድም ዝንብ የሌለበት ከተማ መፍጠር ነው” ሲሉ ጤናን በተመለከተ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው አንድ ሰው ተናግረዋል። “እንዲሁ ዝንቦችን መግደል ብቻ ሳይሆን ንጹሕ ከተሞችን መፍጠር እንፈልጋለን።” “ብዙ ሰዎችን ለመቀስቀስ” በተደረገ አንድ ዘመቻ የከተማዋ ነዋሪዎች ዘመቻውን የሚያስታውቁ በጨርቅ ላይ የተጻፉ ማስታወቂያዎችን ለጠፉ፤ እንዲሁም ሁለት ሚልዮን ፓምፍሌቶችን አሠራጩ። ከዚያ ቀጥሎ በነበረው ልዩ “የማጥቃት እርምጃ በተወሰደበት ሳምንት” ወደ 15,000 ኪሎ ግራም የሚጠጉ ፍሊቶችንና 200,000 ዝንብ ለመግደል የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን በከተማዋ ውስጥ አከፋፈሉ። ከዚያ ቀጥሎ በነበረው ወር ሌላ የማጥቃት እርምጃ በተወሰደበት ሳምንት በዕድሜ የገፉ ሰዎችንና ልጆችን ያቀፉ 1,000 ቡድኖች 7,990 ኪሎ ግራም መርዘኛ መድኃኒቶችን በመጠቀም በዝንቦች ላይ ጥቃት አካሂደዋል። በሰኔ ወር ቤጂንግ ውስጥ አንዳንድ ሥፍራዎች በዝንቦች ከመጥለቅለቃቸው የተነሳ ለእያንዳንዱ ክፍል 33 ዝንቦች ይደርሱ ነበር። ዓላማው በ100 ክፍሎች ሁለት ዝንቦች ብቻ እስኪገኙ ድረስ መጠኑን ዝቅ ማድረግ ነው።

ከፍተኛ ወጪ የሚፈስባቸው ሠርጎችን ማበረታታት

አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታ ባለበት በዚህ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለሠርግ የሚወጣው ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከበደ መጥቷል። በአንድ አኃዛዊ ግምት መሠረት በአሁኑ ጊዜ አንድ መጠነኛ ሠርግ ለመደገስ 16,000 ዶላር ያስፈልጋል። የሠርግ ልብሶች በአማካይ ወደ 800 ዶላር የሚያወጡ ቢሆንም ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል እንደሚለው ከሆነ ብዙዎቹ ከ2,000 ዶላር በላይ ያወጣሉ። በአገሪቱ የሚገኙ በርካታ መጽሔቶች ስለ ሙሽሮችና ስለ ሠርግ ሥነ ሥርዓት ዕቅዶቻቸው የሚገልጹ ወሬዎችን ብቻ ይዘው ይወጣሉ። በየጊዜው የሚወጡ መጽሔቶች በቅርቡ ከሠርግ ዝግጅቶች ጋር የተያያዘ የንግድ ኢንዱስትሪንና እየጨመረ የሄደውን ዋጋ በማበረታታቸው ከፍተኛ ውግዘት ደርሶባቸዋል። ለምሳሌ መጽሔቶቹ የሠርግ ልብስ ከመግዛት ይልቅ የመከራየት ዝንባሌ ባላቸው ሙሽሮች የሚቆጡትን ለመጽሔቶቹ ከፍተኛ ክፍያ የሚከፍሉ የሙሽራ ልብስ ነጋዴዎች ቅር ላለማሰኘት ሲሉ ስለሚከራዩ የሠርግ ልብሶች የሚገልጽ ማንኛውንም ማስታወቂያ በጥቅሉ አግደዋል።

ቴሌቪዥን ዓለምን አጥለቅልቋታል

ቴሌቪዥን በዓለም ዙሪያ ምን ያህል የታወቀ ነው? ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቢዩን በዘገበው መሠረት ከአንድ ቢልዮን በላይ የሚሆኑ ቴሌቪዥኖች ምድርን አጥለቅልቀዋታል። ይህ ቁጥር ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረው የቴሌቪዥን ብዛት ከ50 በመቶ በላይ ይበልጣል። በጃፓናውያን ቤቶች ውስጥ የቴሌቪዥኖች ብዛት የውኃ መልቀቂያ ካላቸው የመጸዳጃ ቤት መቀመጫዎች ይበልጣል። በሜክሲኮ ውስጥ ስልክ ያለባቸው ቤቶች ወደ ግማሽ የሚጠጉት ብቻ ናቸው፤ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ቤተሰብ ቴሌቪዥን አለው ማለት ይቻላል። ብዙዎቹ አሜሪካውያን ደግሞ የፈለጉትን መርጠው ሊያዩ የሚችሉባቸው 25 ወይም 30 የቴሌቪዥን ጣቢያ መሥመሮች አሏቸው። ትሪቢዩን እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “የዚህች ምድር የቴሌቪዥን አብዮት በባሕል፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ላይ ያስከተላቸው ውጤቶች ስፍር ቁጥር የላቸውም። . . . ቴሌቪዥን የሚመለከቱ ሰዎች በሙሉ ባለፉት ሁለት የአሜሪካ ትውልዶች ላይ እንደተከሰተው የተቀረው የዓለም ኅብረተሰብ ለንባብ ያለውን ፍላጎት እንዲያጣ ያደርጉታል ብለው አንዳንዶች ያስባሉ።”

ከቤተሰብም ደም መውሰድ አስተማማኝ አይደለም

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአምስት ዋና ዋና ቦታዎች ላይ በተካሄዱ ከአንድ ሚልዮን በላይ የሚሆኑ የደም ልገሳዎች ላይ በመንግሥት የተደረገ አንድ ጥናት የባዕድ ሰዎችን ደም ከመውሰድ ይልቅ ከጓደኞች ወይም ከቤተሰብ አባሎች ደም መውሰዱ ይበልጥ አስተማማኝ ነው የሚለው የተለመደ እምነት ትክክል አለመሆኑን አጋልጧል። ለምሳሌ ያህል አንድ ምርመራ ከዘመዶችና ከጓደኞች የተለገሰው ደም 2.6 በመቶ ሄፒታይተስ ቢ የተባለው የጉበት በሽታ የተገኘበት መሆኑን አሳይቷል። በአንጻሩ ከባዕድ ሰዎች በተለገሰው ደም ይህ በሽታ የተገኘው 1.8 በመቶ በሚሆነው ውስጥ ነው። በተጨማሪም ከቤተሰብ አባሎችና ከጓደኞች የተለገሰው ደም ቂጥኝ፣ ሄፒታይተስ ሲ የተባለ የጉበት በሽታና ኤች ቲ ኤል ቪ–1 የተባለ ካንሰር የሚያስከትል ቫይረስ በላቀ መጠን የተገኘበት መሆኑ ታውቋል። “ጓደኞችህ ወይም ዘመዶችህ ደም እንዲለግሱህ ስትጠይቅ በበሽታ የመያዝህን አጋጣሚ እየቀነስከው አይደለም” በማለት በበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ፌዴራል ማዕከል የሚሠሩት ሌይል ፒተርሰን ተናግረዋል።

የተፈለገበት ቦታ ደርሶ የማያውቅ እርዳታ

በአፍሪካ ውስጥ ያለውን ረሃብና ድህነት ለማቃለል ከተላከው ዓለም አቀፋዊ እርዳታ መካከል እርዳታው እንዲደርሳቸው ታቅዶላቸው ለነበሩት ሰዎች የደረሰው 7 በመቶው ብቻ እንደሆነ የአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዘዳንት የሆኑት ፈርሃት ዮንስ ተናግረዋል። በሚልዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ልጆች በጣም አስጨናቂ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ መሆኑ ይህን አሳዛኝ ሁኔታ ይበልጥ የከፋ ያደርገዋል። በስፓኒሽ ቋንቋ እየታተመ የሚወጣው ኤል ፔስ የተባለው ጋዜጣ በአህጉሪቷ በሙሉ በቂ ምግብ ባለማግኘታቸው አቅማቸው ደካማ የሆነ 30 ሚልዮን ልጆችና የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው እድገታቸው በጣም የተጓተተ ሌሎች 40 ሚልዮን የሚሆኑ ልጆች አሉ። ከ44 የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ተወካዮች በሴኔጋል ዳካር ውስጥ ተሰብስበው የእርዳታ ሥርጭቱን በስፋት ለማካሄድና ለመከላከያ ኃይል ከሚያወጡት ወጪ ላይ ለመቀነስ ሐሳብ አቅርበዋል። የቀረቡት ሐሳቦች የእነዚህን ልጆች ሕይወት ዕጣ ፈንታ ለማሻሻል እንደሚያስችሉ ሁለት ዋና ዋና እርምጃዎች ተደርገው ታይተዋል።

የሲጋራ ጭስ ያስከተለው ሙግት

በቅርቡ በአውስትራሊያ ውስጥ የኒው ሳውዝ ዌልስ ወረዳ ፍርድ ቤት የቀድሞ አሠሪዎቼ ሲጋራ በሚጨስበት አካባቢ ለብዙ ዓመታት እንድሠራ በማድረግ ከባድ ለሆኑ የጤና እክሎች ዳርገውኛል በማለት ክስ ለመሠረቱት የ64 ዓመት ሴት ፈርዶላቸዋል። ቀደም ሲል እንዲህ ያሉ ክሶች በፍርድ ቤት ይታዩ የነበረ ቢሆንም አዲስ ምዕራፍ በከፈተው በዚህ ብያኔ ላይ ግን ፍርድ ቤቱ ክሱን ላቀረቡት ሴት 85,000 (የአውስትራሊያ) ዶላር ካሳ እንዲሰጣቸው ወስኗል። ዘ አውስትራሊያን የተባለው ጋዜጣ አንድ ችሎት ሲጋራ የሚያጨስ ሰው በጭስ የተበከለውን አየር የሚስቡትን ሲጋራ የማያጨሱ ሰዎች ጤና ሊጎዳ ይችላል ብሎ ሲበይን ይህ የመጀመሪያው ነው ሲል ዘግቧል። ምግብ ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ የዳንስ ምሽት የሚዘጋጁባቸው ቦታዎችና ሌሎች የሥራ ቦታዎች ሲጋራ የማይጨስበት የሥራ ክልል ካልፈጠሩላቸው በስተቀር ሲጋራ የማያጨሱ ሠራተኞቻቸው በከባድ የጤና እክሎች ሳቢያ ሊከሷቸው ስለሚችሉ ይህ ብያኔ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድርባቸው ይሆናል በማለት አንዳንዶች ያስባሉ።

በማስመሰል ስለሚሠሩ መድኃኒቶች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

በየዓመቱ ትክክለኛውን መድኃኒት እንዲመስሉ ተደርገው የተሠሩ የማታለያ መድኃኒቶችን በማጭበርበር የሚሸጡ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች በቢልዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ያፍሳሉ። ነገር ግን ተመሳሳይ እንዲሆኑ ተደርገው ከሚሠሩ ሌሎች ዕቃዎች በተለየ መንገድ “ትክክለኛውን መድኃኒት እንዲመስሉ ተደርገው የሚሠሩ የማታለያ መድኃኒቶች በጤና ላይ ከባድ ጉዳት ሊያስከትሉ አልፎ ተርፎም ሊገድሉ ይችላሉ” በማለት በዓለም የጤና ድርጅት ታትሞ የወጣ አንድ ጽሑፍ ያስጠነቅቃል። ብዙዎቹ የመፈወስ ኃይላቸው በጣም አነስተኛ በመሆኑ ወይም ጭራሽ የማይፈውሱ በመሆናቸው እንደ ወባ ወይም የስኳር በሽታ ባሉ ከባድ በሽታዎች የሚሠቃየውን ሰው ሊረዱት አይችሉም። እንዲያውም አንዳንዶቹ በሕግ የተከለከሉ ወይም መርዘኛ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን የያዙ ናቸው። “በቅርብ ጊዜ ሳልን ያስቆማል የተባለ መድኃኒት ከወሰዱ በኋላ የሞቱ ናይጄሪያውያን ልጆች እንዳሉ መነገሩ የእንዲህ ዓይነቱን የማጭበርበር ተግባር አደገኛነት አሳዛኝ በሆነ መንገድ ያረጋግጣል” በማለት ሪፖርቱ ይናገራል። ችግሩ በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ በሚኖሩ፣ እምነት በሚጣልበት ኩባንያ የተሠራ ጥሩ መድኃኒት በዝቅተኛ ዋጋ አገኘን ብለው በሚገዙ ድሀ ሰዎች ላይ የከፋ ነው። እላዩ ላይ የተጻፈው የመድኃኒት ስምም ሆነ የታሸገበት ነገር አንድን መድኃኒት ትክክለኛ ነው ሊያሰኘው አይችልም። እነዚህ መድኃኒቶች ልክ ትክክለኛውን መድኃኒት ሊመስሉ ይችላሉ።

በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለው ልዩነት ሰፍቷል

በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ታትሞ የወጣው ሂውማን ዴቨሎፕመንት ሪፖርት 1992 ባለፉት 30 ዓመታት በሀብታሞችና በድሆች መካከል የነበረው ልዩነት በእጥፍ ጨምሯል ይላል። በብሔራዊ አማካይ ቁጥሮች መሠረት በ1960 ከዓለም ሕዝብ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት ባለጠጎች 20 በመቶ ከሚሆኑት በጣም ድሀ ሰዎች ሀብታቸው 30 እጥፍ ይበልጥ ነበር። በ1989 ሀብታሞቹ 60 ጊዜ እጥፍ ይበልጡ ነበር ማለት ይቻላል። በግለሰብ ደረጃ ሲታይ አንድ ቢልዮን የሚሆኑት የዓለም ባለጠጎች በጣም ድኻ ከሆኑት አንድ ቢልዮን ሰዎች ቢያንስ ቢያንስ 150 ጊዜ እጥፍ በሀብት ይበልጡ ነበር።

ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረው የዳቦ መጋገሪያ ቤት ይሄ ይሆን?

አሶሴትድ ፕሬስ ባወጣው ሪፖርት መሠረት በግብጽ ፒራሚዶች አጠገብ የሚሠሩ አርኪዎሎጂስቶች በዓለም ላይ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ የዳቦ መጋገሪያ ቤት አግኝተዋል። ሰዎች ይህን የዳቦ መጋገሪያ ቤት ፒራሚዶቹን ይሠሩ ለነበሩት ሠራተኞች ዳቦ ለመጋገር ይጠቀሙበት የነበረ መሆኑን ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። የግብፅን ጥንታዊ ነገሮች የሚያጠኑትና የቁፋሮውን ሥራ ከሚያካሄዱት ዲሬክተሮች አንዱ የሆኑት ማርክ ሌነር “በዚህ ቦታ ይጋገር የነበረው የዳቦ ብዛት ቀላል አይምሰላችሁ። በአንድ ቀን ውስጥ 30,000 ሰዎችን በቀላሉ ለመመገብ የሚችል ነበር” በማለት ተናግረዋል። በዳቦ መጋገሪያው ቤት ውስጥ ይከናወን የነበረው ሥራ በጣም የሚያስፈራ፣ ከፍተኛ ሙቀት የነበረበትና ጥቁር ጭስ የሚወጣበት እንደነበረ ሌነር ገምተዋል። “እነዚህ ክፍሎች ዝናብ እንዳቋረ የሌሊት ሰማይ ይመስሉ እንደነበረ አያጠራጥርም” ሲሉ ተናገሩ። “45 ሴንቲ ሜትር ጥልቀት ያለው ለመቆፈር የማያስቸግር በአመድ የተሞላ ጥቁር መሬት ቆፍረናል።” የዳቦ መጋገሪያ ቤቱ ፒራሚዶቹ ይገነቡ ከነበረበት ወቅት አንስቶ ያሉትን ዓመታት ያስቆጠረ ነው የሚል እምነት አሳድሯል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ