ዓለማችን የተለወጠችው እንዴት ነው?
ዓለም ተለውጣብሃለችን? የጥንቷ ግሪክ ፈላስፋ የነበረው ሄራክሊተስ “ሁልጊዜ የሚኖር ነገር አለ ቢባል ለውጥ ነው” ብሏል። በሁላችንም ሕይወት ውስጥ ለውጥ የማያቋርጥ ሂደት ነው።
ያለፉትን 10, 20, 30 ወይም ከዚያ በላይ ዓመታት መለስ ብለህ ስትቃኝ ምን ለውጦች ተመልክተሃል? ለውጦች የስልጣኔና ባሕላዊ አስተሳሰቦችን አሽቀንጥሮ የመጣል መልክ ይዘው ሲመጡ ተመልክተህ ይሆናል። አንዳንዶች አዎንታዊ፣ ሌሎች ደግሞ አሉታዊ የሆኑ ለውጦችን እንደ ተመለከትክ ጥርጥር የለውም።
ዕድሜዎ ከ70 ዓመት በላይ ከሆነ ከወጣትነትዎ ጊዜ ጀምሮ ምን ለውጦች ተመልክተዋል? ቴሌቪዥን ያልነበረበትን፣ አውሮፕላኖች በሰዓት 160 ኪሎ ሜትር ብቻ ሲያዘግሙ የነበሩበትን፣ አብዛኞቹ ዓለም አቀፍ ጉዞዎች በባሕር ላይ ይደረጉ የነበሩበትን፣ በአደንዛዥ ዕጾች መጠቀም በጠባብ የኦፒየም ክፍሎች የተወሰነ የሚመስልበትን፣ አውቶሞቢሎች በጣም ጥቂቶች ስለነበሩ ተራርቀው ይሄዱ የነበረበትን ጊዜ ያስታውሳሉ። አዎን፣ በእርግጥ ዓለም ተለውጣቦታለች።
የተለወጠው ሸማች ኅብረተሰብ
ይሁን እንጂ ዓለም ለወጣቶችም ሳይቀር ተለውጣባቸዋለች። ከ45 ዓመታት በፊት የምዕራቡ ዓለም ምርትና ጥበብ የዓለምን ገበያ አጥለቅልቀውት ነበር። አሁን ግን በአውቶሞቢል ምርቶች፣ በኮምፒተሮች፣ በካሜራዎች፣ በቴሌቪዥኖችና በብዙ ዓይነት የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች መሪ ሆነው የሚገኙት በፓሲፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ የሚገኙ የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ናቸው።
ይህም የብዙ ዓመት ልምድ ያላቸው አንድ ቻይናዊ መንገደኛ ለንቁ! መጽሔት በተናገሩት ነገር ላይ ተገልጿል:- “ከ30 ወይም ከ40 ዓመታት በፊት መካከለኛ ኑሮ ያለው ቻይናዊ እንዲኖሩት የሚመኛቸው ነገሮች ብስክሌትና የስፌት መኪና ነበሩ። እነዚህ በወቅቱ የክብር ማሳያ ዕቃዎች ነበሩ። አሁን ያለው ምኞት ደግሞ ባለ ቀለም ቴሌቪዥን፣ የቪድዮ ካሴት ማጫወቻ፣ ማቀዝቀዣና ሞተር ቢስክሌት ማግኘት ነው።” በቻይናም ሆነ በሌላ ሥፍራ ሸማቹ ኅብረተሰብ ስሜቱንና ፍላጎቱን ለውጧል።
ብዙ አገሮች ኢኮኖሚያቸው ሲያድግ ይህ ዓይነቱ የአመለካከት ለውጥ አጋጥሟል። ዕድሜው በ40ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ የሚገኘው የካቶሎንያ (ስፓኝ) ነዋሪ የሆነው ፔድሮ “በስፓኝ ውስጥ ከ30 ዓመታት በፊት የነበረው የሰዎች ምኞት ትንሿን ባለ 600 ሲሲ ፊያት መኪና ማግኘት ነበር። አሁን ግን የእስፓኝ ሰዎች ምኞት የጀርመኑን ቢ ኤም ደብልዩ (BMW) ማግኘት ነው!” በማለት ተናግሯል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚኖረው ጃጊሽ ፓቴል በቅርቡ ወደ ትውልድ አገሩ ወደ ህንድ ስላደረገው ጉዞ እንደሚከተለው አስተያየቱን ሰጥቷል:- “አሁን በህንድ አውራ ጎዳናዎች ላይ ያሉትን አውቶሞቢሎች ብዛት ሳይ በጣም ተገረምኩ። አውራ ጎዳናዎቹ አሁንም ልዩ ልዩ በህንድ አገር የተሠሩ መኪኖች ይሽከረከሩባቸዋል፤ አሁን ግን በውጭ ኩባንያዎች የሥራ ፈቃድ በህንድ ውስጥ ከሚሠሩ ዘመናዊ መኪናዎችና ሞተር ብስክሌቶች ጋር አንድ ላይ ይጋፋሉ።”
በሳይንስ መስክ የተደረጉ ለውጦች
ሩቅ ሳንሄድ ከ25 ዓመታት በፊት ብዙ ሰዎች ጨረቃን ብዙ የምታመራምር ምስጢራዊ አካል እንደሆነች አድርገው ይመለከቷት ነበር። ከዚያ ወዲህ ሰው እግሩንና ሳይንሳዊ መሣሪያዎቹን በዚህች ሩቅ በምትገኝ አካል ገጽ ላይ አሳርፎ ለምርምር የሚሆኑ የኮረት ናሙናዎችን ይዞ መጥቷል። አሁን የአሜሪካ የህዋ በረራዎች ምልልሱን የዘወትር ተግባር አድርገውታል፤ ስለዚህ የዩናይትድ ስቴትስ የሳይንስ ሊቃውንት በጨረቃ ላይ ቋሚ የህዋ ጣቢያ ስለማቋቋምና በዚያውም ወደ ማርስ ስለ መሄድ እየተነጋገሩ ነው።
ከ15 ዓመታት በፊት ስለ ኤድስ የሰማ ማን ነበረ? አሁን ግን ዓለም አቀፍ መቅሰፍት ሆኗል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሽታውን በመፍራት ይኖራሉ።
ፖለቲካዊ ለውጦች
ከአራት ዓመታት ብቻ በፊት የማይበገር የሚመስል ግንብ የበርሊንን ከተማ ለሁለት ከፍሏት ነበር፤ ኮሚኒስቷ ሶቪየት ህብረትና ቀዝቃዛው ጦርነት ነበሩ። ዛሬ በርሊን የተባበረችው ጀርመን ዋና ከተማ እንድትሆን ተመርጣለች፤ እንዲሁም ከቀድሞዋ የሶቪየት ህብረት 15 ሪፑብሊኮች መካከል 11ዱ የነፃ አገሮች የጋራ ብልጽግና መሥርተዋል።
ከጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አብዛኛውን ጊዜ ካፒታሊስትና ኮሚኒስት ኃይሎች የሚነታረኩበትና ገለልተኛ መንግሥታት በመባል ይጠሩ የነበሩት ከማንኛው ወገን ለመሰለፍ ተቸግረው እርስ በርስ የሚፎካከሩበትና የጎሪጥ የሚተያዩበት መድረክ ሆኖ ነበር። ዛሬ የምሥራቁና የምዕራቡ መንግሥታት ስለ ሰላምና ደኅንነት እየተነጋገሩ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታትም ከቀድሞው ይበልጥ ኃይል አለው። በዓለም ዙሪያ ችግር ወዳለባቸው ቦታዎች ሁሉ ወታደራዊ ኃይሎች ሊልክ ይችላል። ከሦስት ዓመታት በፊት ዩጎዝላቪያና ቼኮዝሎቫኪያ በመባል የሚታወቁ አገሮች ነበሩ። ዛሬ ሁለቱም ተሸራርፈው ትናንሽ መንግሥታት ሆነዋል።
ዓለም እነዚህን ሁሉ ለውጦች አድርጋ እውነተኛ ሰላምና ፍትሕ ወደ ሰፈነበትና ምግብና ሀብት ለሁሉም በትክክል ወደሚከፋፈልበት ደረጃ በመድረስ በጣም ተሻሽላለችን? ዓለም ከበፊቱ ይበልጥ ሠልጥናለችን? ወንጀለኞችን ሳትፈራ በመንገድ ላይ መንሸራሸር ትችላለህን? ከእንግዲህ ወዲያ ሰዎችን በዘራቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በፖለቲካ፣ በአኗኗራቸው፣ ወይም በቋንቋቸው ምክንያት እንዳንጠላ የሚያደርግ ትምህርት አግኝተናልን? የተደረገው ለውጥ ለሰብአዊው ቤተሰብ በአጠቃላይና መኖሪያችን ለሆነችው ለምድር እውነተኛ መሻሻል አምጥቷልን? ወዴት እያመራን ነው? የሚከተሉት ርዕሶች እነዚህንና ሌሎችንም ጥያቄዎች ይመረምራሉ።