በመለወጥ ላይ ያለችው ዓለማችን ወዴት እያመራች ነው?
አንዳንድ ለውጦች በሚልዮን በሚቆጠሩ የሰዎች ሕይወት ላይ፣ አልፎ ተርፎም በጠቅላላው የዓለም ሕዝብና በመጪዎቹ ትውልዶች ላይ የጠለቀና ዘላቂ ውጤት ያላቸው ናቸው። ወንጀል በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ፣ በአደንዛዥ ዕጾች ያለ አግባብ መጠቀም፣ የኤድስ መስፋፋት፣ የውኃና የአየር መበከልና የደኖች መጨፍጨፍ በሁላችንም ላይ ተጽዕኖ በማምጣት ላይ ካሉት ሁኔታዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። የቀዝቃዛው ጦርነት ማክተምና ምዕራብ አመጣሹ ዲሞክራሲ ከገበያ ኢኮኖሚው ጋር ኑሮን እየለወጡትና በመጪው ጊዜ ላይም ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው። ከእነዚህ ነገሮች ውስጥ አንዳንዶቹን እንመርምር።
ወንጀል ሕይወታችንን የለወጠው እንዴት ነው?
በአካባቢህ ያሉ መንገዶች እንዴት ናቸው? በምሽት ከቤት ወጥተህ በመንገድ ላይ ብቻህን ብትንሸራሸር ምንም አደጋ እንደማይደርስብህ ትተማመናለህን? ከ30 ወይም ከ40 ዓመታት በፊት ብዙ ሰዎች ቤታቸውን ሳይቆልፉ ሊተውት ይችሉ ነበር። አሁን ግን ጊዜው ተለውጧል። ዛሬ አንዳንድ መዝጊያዎች ሁለት ወይም ሦስት መቀርቀሪያዎች አላቸው። መስኮቶችም በብረት የታጠሩ ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ ሰዎች የሚያምር ልብስ ለብሰውና ጌጣቸውን አድርገው በመንገድ ላይ መሄድ ይፈራሉ። አንዳንድ የከተማ ነዋሪዎች የቆዳ ጃኬታቸውን ወይም ባለጠጉር ኮታቸውን ለመውሰድ ብቻ በሚፈልጉ ሰዎች ተገድለዋል። ሌሎች ደግሞ በአደንዛዥ ዕጽ ሻጮች መካከል በሚደረግ የተኩስ ልውውጥ ሳቢያ ሞተዋል። ብዙ ሕፃናትን ጨምሮ ከምኑም የሌሉ ቆሞ ተመልካቾች በየዕለቱ ይገደላሉ ወይም ይቆስላሉ። ቀበኛ ሌቦችን ለማጨናገፍ የሚያስችል አንድ ዓይነት መሣሪያ ከሌላቸው በቀር መኪናዎችን ያለ ሥጋት በመንገድ ላይ አቁሞ መሄድ አይቻልም። በዚህ የተጣመመ የዓለም ሁኔታ ሰዎችም ተለውጠዋል። ሐቀኝነትና ታማኝነት የተረሱ ባሕሎች ወደመሆን ተቃርበዋል። መተማመን ጠፍቷል።
ወንጀልና ዓመፅ ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ሆነዋል። ከተለያዩ ምንጮች የተገኙ የሚከተሉት አርዕስተ ዜናዎች ይህን ሐቅ ያረጋግጣሉ:- “ፖሊሶች፣ ቀማኞች፣ ዱርዬዎችና መጥፎ ምግባር፤ ሞስኮ እነዚህ ሁሉ አሉባት” “በኮሪያ ወንጀልን አስከትሎ አዲስ ዘመን መጥቷል” “የመንገድ ላይ ወንጀል የፕሬግን ዕለታዊ ሕይወት እያቃወሰው ነው”፤ “ጃፓን በሕዝብ ረብሻ ላይ ቁጣዋን ገለጸች፣ ረብሸኞቹም መልሰው ተዋጉ”፤ “የኦክቶፐሱ ግጥሚያ — የኢጣሊያ ከፍተኛ የማፊያ ተዋጊ ተቃጠለ።” እንግዲያውስ ወንጀል የትም ቦታ ያለ ችግር ነው።
የአሁኑ ጊዜ ወንጀል ከቀድሞው ይበልጥ አሠቃቂ ነው። ሕይወት ረክሷል። በብራዚል ሪዮ ዴ ጃኔሮ በከተማው ዳርቻ የሚገኝ ቆሻሻ ሠፈር “በዓለም ውስጥ ካሉት ዓመፅ የሚካሄድባቸው ቦታዎች ሁሉ የበለጠ መሆኑ በተባበሩት መንግሥታት እውቅና አግኝቷል። በዚህ ቦታ በያመቱ 2,500 ሰዎች ይገደላሉ።” (ዎርልድ ፕሬስ ሪቪው) በኮሎምቢያ ውስጥ የአደንዛዥ ዕጽ ወንጀል መሪዎች በልዩ ዓይነት ፈጣን የሞት ቅጣት አማካኝነት ከተፎካካሪዎቻቸውና ከባለ ዕዳዎቻቸው ጋር ያላቸውን ሒሳብ ለመዝጋት ቅጥረኛ ገዳዮችን ያሰማራሉ። ብዙውን ጊዜም በኮሎምቢያም ሆነ በሌላ ሥፍራ ወንጀል ተፈጽሟል ብለህ ከተናገርክ ወዮልህ። ምክንያቱም ወንጀለኞቹ አንተንም የሚቀጥለው ዒላማቸው ሊያደርጉህ ይችላሉ።
ሌላው ትልቅ ለውጥ ደግሞ የሚገድሉ አውቶማቲክ የጦር መሣሪያዎችን የሚይዙ ወንጀለኞች ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ሲሆን ለራስ መከላከያ እየተባለ መሣሪያ የሚይዘው ሕዝብም ቁጥሩ እየጨመረ መሆኑ ነው። ይህ የጦር መሣሪያ ትጥቅ እየጨመረ መሄዱ ደግሞ በወንጀልም ሆነ በድንገት የሚሞቱትንና የሚቆስሉትን ሰዎች ቁጥር ከፍ ያደርገዋል። በአሁኑ ጊዜ በኪስ ወይም በቤት ውስጥ ያለ መሣሪያ ማንንም ሰው ነፍሰ ገዳይ ሊያደርገው የሚችል መሆኑ ያደባባይ ሚስጥር ነው።
ወንጀልና አደንዛዥ ዕጽ
ከሃምሳ ዓመታት በፊት አደንዛዥ ዕጾች የዓለም ችግር ይሆናሉ ብሎ ያሰበ ማን ነበረ? ዛሬ ግን የወንጀልና የዓመጽ ዋና መንስኤ ከሆኑት ነገሮች ውስጥ ናቸው። ሪቻርድ ክላተርባክ የሚባሉ ጸሐፊ ቴረሪዝም፣ ድራግስ ኤንድ ክራይም ኢን ዩሮፕ አፍተር 1992 በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ “የአደንዛዥ ዕጾች ንግድ ዕድገት ውሎ አድሮ ለሰው ሥልጣኔ ከምንም ነገር የበለጠ ስጋት ሊፈጥር ይችላል። . . . ከሽያጩ የሚገኘው ትርፍ ለአደንዛዥ ዕጽ መሳፍንት [ለዚህ ግልጽ ምሳሌ የምትሆነው ኮሎምቢያ ናት] ከፍተኛ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኃይል የሚሰጣቸው መሆኑ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ አሰቃቂ የሆነ ወንጀል ለማስፈጸም የሚያስችለውን ወጪ ሊሸፍን የሚችል ነው” በማለት ችግሩን አስቀድመው ተገንዝበውታል። በተጨማሪም “በዓለም ላይ ያለውን ሽብር ፈጣሪነትና የወንጀለኝነት ዓመፅ ከሚወልዱት ዋነኛ ነገሮች መካከል በኮሎምቢያ ካሉት የኮካ እርሻዎች የሚመረተው ኮኬይን በአውሮፓና በዩናይትድ ስቴትስ ላሉት ሱሰኞች ለመሸጥ የሚደረገው ንግድ ነው” በማለት ተናግረዋል።
የትም ተስፋፍቶ የሚገኘው የወንጀል ማዕበልና በዓለም የእስረኞች ቁጥር መጨመር የወንጀለኝነት ዓላማ ያላቸውና ለመለወጥ ምንም ፍላጎት የሌላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መኖራቸውን ያመለክታል። የሚበዙት ወንጀለኞች ወንጀል እንደሚጠቅማቸው አይተዋል። በውጤቱም ዓለማችን ወደ ከፋ ሁኔታ ተለውጣለች። ከበፊቱ የበለጠ አደገኛም ሆናለች።
ኤድስ፤ ለውጥ ያስከትል ይሆን?
በመጀመሪያ ግብረ ሰዶማውያንን ብቻ የሚያጠቃ መስሎ የታየው ይህ በሽታ ማንኛውም ዓይነት ዘርና አኗኗር ያላቸውን ሰዎች የሚያጠቃ መቅሰፍት ሆኗል። ከአሁን ወዲያ ኤድስ የሚመርጠው የተለየ ቡድን የለም። በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ኤድስ ግንኙነታቸውን በተቃራኒ ፆታዎች መካከል ብቻ የሚወስኑትን አብዛኞቹን ሰዎች በመደምሰስ ላይ ነው። በዚህም የተነሳ በሥነ ምግባራዊ ምክንያት ሳይሆን በበሽታ መለከፍን በመፍራት ብቻ የሩካቤ ሥጋ ልክስክስነት በድንገት ጊዜው ያለፈበት ነገር መስሎ መታየት ይዟል። በአሁኑ ጊዜ በበሽታው ከመለከፍ ለመዳን የሚስተጋባው መፈክር ግንኙነትን “አንድ ላንድ መወሰን” የሚል ሲሆን በመከላከያነት የሚቀርበው ዋና ምክር ደግሞ በኮንዶም መጠቀም ነው። ከዝሙት መቆጠብ እምብዛም ተወዳጅነት የሌለው መከላከያ ነው። ይሁንና ኤድስ በመጪው ቅርብ ጊዜ ሰብአዊውን ቤተሰብ እንዴት ይነካው ይሆን?
ታይም መጽሔት በቅርቡ እንደሚከተለው በማለት ዘግቧል:- “እስከ 2000 ዓመተ ምህረት ድረስ ኤድስ የ1918ቱን የኢንፍሉዌንዛ (የኅዳር በሽታ) መቅሰፍት የሚያስንቅ የዚህ መቶ ዘመን ታላቅ ወረርሽን ሊሆን ይችላል። ያ የኢንፍሉዌንዛ መዓት 20,000,000 ሰዎችን፣ ወይም ከዓለም ሕዝብ 1 በመቶ የሚሆኑትን ገድሏል። ይኸውም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ከሞቱት ወታደሮች ቁጥር በእጥፍ ይበልጣል።” አንድ ውስጥ አዋቂ “ይህ ወረርሽኝ ታሪካዊ ስፋት ያለው ነው” ብለዋል።
ለኤድስ ምርምርና ጥናት በሚልዮን የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላርና የሌሎችም አገሮች ገንዘብ ቢፈስስም ምንም መፍትሔ አልተገኘም። በቅርቡ በኔዘርላንድስ አምስተርዳም በኤድስ ላይ ለመነጋገር የተደረገ ስብሰባ ስለ ችግሩ ለማጥናት 11,000 የሳይንስ ሊቃውንትንና ሌሎችንም ጠበብቶች አንድ ላይ አሰባስቦ ነበር። “ሁኔታው ተስፋ መቁረጥ፣ ያልተሳካ ጥረትና እየጨመረ የሚሄድ አሳዛኝ መከራ የሰፈነባቸውን አሥርተ ዓመታት የሚያሳይ ጭልምልም ያለ ነበር። . . . የሰው ዘር ለኤድስ መፍትሔ መፈለግ ከተጀመረበት ጊዜ ይልቅ አሁን ኤድስን ድል ለማድረግ ወደሚችልበት ጊዜ አልተቃረበ ይሆናል። ክትባት የለም፤ ፈውስም የለም፤ የማያከራክር ውጤታማ የሆነ ሕክምና እንኳን አልተገኘለትም።” (ታይም ) በአሁኑ ጊዜ ኤድስ የተገኘባቸውና እስካሁንም ታመው ሊሆን ለሚችሉ ሰዎች ሁኔታው የጨለመ ነው። በዚህ ረገድም ለውጡ ጥሩ ሳይሆን የከፋ ሆኗል።
በዓለም ፖለቲካ ላይ የተደረገ ለውጥ
ባለፉት አራት ዓመታት በፖለቲካ ሁኔታ የተደረገው ለውጥ ምናልባት ለዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች ድንገተኛ የነበረውን ያህል ባይሆንም ለብዙ መሪዎች ያልታሰበና ድንገተኛ ነበር። ዩናይትድ ስቴትስ በፖለቲካው መስክ ያለ አንዳች ተፎካካሪ ብቻዋን መቅረቷን በድንገት ተገነዘበች። ሁኔታው ከእንግዲህ ከእርሱ ጋር ማንም ግጥሚያ ሊያደርግ እንደማይፈልግ በድንገት ከተገነዘበ በከፍተኛ ስሜት የተነሳሳ ሊሸነፍ የማይችል አንድ የቅርጫት ኳስ ቡድን ጋር የሚመሳሰል ነበር። ይህ ግራ የሚያጋባ ሁኔታ በ1990 ፎሪይን ፖሊሲ በተሰኘ መጽሔት ላይ ቻርለስ ዊልያም ማይኔስ ሜይንስ አዘጋጅ ባሠፈሩት ርዕሰ አንቀጽ እንደሚከተለው ተጠቃልሎአል:- “በአሁኑ ጊዜ የዩናይትድ ስቴትስ ተግባር አገሯን ከአጥፊ ጦርነት ማላቀቅ ሳይሆን በእርሷና በ[ቀድሞዋ] ሶቪየት ህብረት መካከል በድንገት የተገኘውን ያልተጠበቀ ሰላም ሥርዓት ማስያዝ ነው።”
በተለመዱት የጦር መሣሪያዎች የሚደረገው ጦርነት እየተዛመተ ሲሄድ ኑክሌርን የመሥራት ዕውቀትና ብልሃት እየበዛ መሄዱ አዲስ ስጋት ፈጥሯል። ይህም ለዓለም የጦር መሣሪያ ነጋዴዎች ደስታቸው ነው። የሰላም ጥሪ በሚያስተጋባባት ዓለም ውስጥ ብዙ የፖለቲካ መሪዎች ሠራዊታቸውንና የጦር መሣሪያቸውን እያጠናከሩ ነው። ገንዘቡ ሁሉ ተሟጦ ሊራቆት ምንም ያልቀረው የመንግሥታቱ ድርጅት ሥር ለሰደደው የዓለም ክፉ ቁስል እርዳታ የማስተባበር ጥረቱን ቀጥሏል።
የማይለወጠው የብሔራዊ ስሜት እርግማን
ኮሚኒዝም መፍረክረክ ሲጀምር የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የነበሩት ቡሽ “አዲስ የዓለም ሥርዓት” የሚል ጽንሰ ሐሳባቸውን በሕዝብ ዘንድ እንዲታወቅ አደረጉ። ይሁን እንጂ ብዙ የፖለቲካ መሪዎች እንደደረሱበት ያማሩ መፈክሮች ምንም ዋጋ የሌላቸው ርካሽ ናቸው፤ ጠቃሚ ለውጦችን ማድረግ እጅግ አዳጋች ነው። ጄፍሪ ጎልድፋርብ አፍተር ዘ ፎል — ዘ ፐርሱት ኦቭ ዲሞክራሲ ኢን ሴንትራል ዩሮፕ በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ብለዋል:- “ስለ ‘አዲስ የዓለም ሥርዓት’ ሰዎች ያደረባቸው ገደብ የለሽ ተስፋ ከጥንት ጀምሮ የነበሩት ችግሮች አሁንም እንዳልለቀቁን፣ እንዲያውም በቀል ታክሎባቸው አብረውን ያሉ መሆናቸውን እንድንገነዘብ አስገድዶናል። ነፃነት ማግኘት የሚያመጣውን ፍንደቃ . . . ብዙውን ጊዜ ፖለቲካዊ ውጥረት፣ ብሔራዊ ግጭትና ሃይማኖታዊ ወግ አጥባቂነትና ኢኮኖሚያዊ ውድቀት የሚያመጡት ተስፋ መቁረጥ እንደሚያጨልመው ታይቷል።” ዩጎዝላቪያ በመባል ትታወቅ በነበረችው አገር የተነሳው የእርስ በርስ ጦርነት ፖለቲካ፣ ሃይማኖትና ብሔራዊ ስሜት ለሚያመጡት የሚከፋፍል ተጽዕኖ በአብነት እንደሚጠቀስ ጥርጥር የለውም።
ጎልድፋርብ በመቀጠልም እንደሚከተለው ብለዋል:- “የውጭ አገር ሰዎችን መፍራትና የግል ደህንነት ዋስትና ማጣት ለማዕከላዊ አውሮፓ ሰዎች የኑሯቸው ክፍል ሆኖባቸዋል። ዲሞክራሲ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባሕላዊ የሆኑ ሸቀጦችን ባፋጣኝ ካለማቅረቡም በላይ የገበያ ኢኮኖሚም ሀብታምነትን ማብሠር ብቻ ሳይሆን ለማያውቁበት ደግሞ ያደናግራል።”
ይሁን እንጂ እነዚህ ችግሮች በማዕከላዊ አውሮፓና በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ሪፑብሊኮች ብቻ የተወሰኑ አይደሉም። የውጭ አገር ሰዎችን መፍራትና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ዓለም አቀፍ ችግሮች ናቸው። ሰብአዊው ቤተሰብም በስቃይና በሞት ዋጋውን እየከፈለ ነው። መጪው ቅርብ ጊዜም ጥላቻንና ዓመፅን ለሚያመጡት ለእነዚህ ሥር የሰደዱ ችግሮች ምንም የለውጥ ጭላንጭል የለውም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ብዙዎቹ ሰዎች ከወላጆቻቸውም ሆነ ብሔራዊ ስሜት ከተጠናወታቸው የትምህርት ሥርዓቶች የሚያገኙት ትምህርት ጥላቻን፣ አለመቻቻልንና በብሔር፣ በጎሳ ወይም በቋንቋ ላይ የተመሠረተ የበላይነትን አስተሳሰብ እንዲያሳድሩ ስለተደረጉ ነው።
ኤሲያዊክ የሚባል ሳምንታዊ መጽሔት “የመጨረሻው አስቀያሚ ገጽታ” በማለት የጠራው ብሔራዊ ስሜት ጥላቻንና ደም መፋሰስን መቀስቀሳቸውን ከሚቀጥሉት የማይለወጡ ነገሮች አንዱ ነው። ይህ መጽሔት እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ሰርብ በመሆን መኩራት ማለት ክራኦትን መጥላት ማለት ከሆነ፣ ለአንድ አርመን ነፃነት ማግኘት ማለት ቱርክን መበቀል ማለት ከሆነ፣ ለአንድ ዙሉ በራስ የመመራት መብት ማግኘት ቆሳን ማስገበር ማለት ከሆነና ለአንድ ሩማኒያዊ ደግሞ ዲሞክራሲ ማግኘት ሀንጋሪያዊውን ከአገር ማስወጣት ከሆነ እንግዲያውስ ብሔራዊ ስሜት አስቀያሚ መልክ ይዟል ማለት ነው።”
አልበርት አንስታይን በአንድ ወቅት የተናገረውን እናስታውሳለን:- “ብሔራዊ ስሜት የጨቅላነት በሽታ ነው። የሰው ልጅ የኩፍኝ በሽታ ብሎም ስሜት ነው።” ዛሬም ሆነ ነገ ማንንም ሰው የሚለክፍ ሲሆን መዛመቱንም ቀጥሏል። በ1946 እንግሊዛዊው ታሪክ ጸሐፊ አርኖልድ ቶይንቢ “የሀገር ፍቅር . . . በጣም ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ በክርስትና ላይ የበላይነት ያለው የምዕራቡ ዓለም ሃይማኖት ሆኗል” በማለት ጽፈው ነበር።
በአሁኑ ጊዜ ሰው በጠባዩ ላይ ለውጥ እንደሚያደርግ የሚያሳይ ተስፋ አለን? ይህ ለውጥ ሊገኝ የሚችለው ሥር ነቀል ለውጥ በማካሄድ ብቻ ነው ብለው የሚናገሩ አንዳንድ ሰዎች አሉ። የኢኮኖሚ ጠበብት የሆኑት ጆን ኬ ጎልብሬዝ እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “የእድገት የጋራ መለኪያዎቹ ሰዎች ናቸው። ስለዚህ . . . ሰዎች እስካልተሻሻሉ ድረስ መሻሻል አይቻልም። ሰዎች [ከድንቁርና] ነፃ ሲሆኑና ትምህርት ሲያገኙ መሻሻል እንደሚገኝ እርግጠኛ ነገር ነው። . . . መሃይምነትን ድል ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።” የዓለም የትምህርት ሥርዓቶች ጥላቻንና ጥርጣሬን ሳይሆን ፍቅርንና መቻቻልን እንደሚያስተምሩ ምን ተስፋ አለ? ሁላችንም የመጣነው ከአንድ ሰብአዊ ቤተሰብ መሆኑን በመገንዘብ ሥር የሰደዱ የጎሣ ወይም የዘር ጥላቻዎች ጠፍተው በመተማመንና በመግባባት የሚተኩት መቼ ነው?
በግልጽ እንደምናየው ገንቢ ለውጥ ያስፈልጋል። ሳንድራ ፖስቴል ስቴት ኦቭ ዘ ዎርልድ 1992 በተሰኘ መጽሐፍ ላይ “የተሻለ ዓለም ይመጣል የሚል ከእውነታው ያልራቀ ተስፋ እንዲኖረን ከተፈለገ ቀሪው አሥርተ ዓመት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጥልቅና ሰፊ የሆነ ለውጥ የሚደረግበት መሆን አለበት” በማለት ጽፈዋል። ታዲያ ወዴት እያመራን ነው? ሪቻርድ ክላተርባክ እንዲህ ብለዋል:- “ይሁን እንጂ ዓለም ያልተረጋጋና አደገኛ ቦታ ሆኖ ቀጥሏል። የጋለ ብሔራዊና ሃይማኖታዊ ስሜት እንዳለ ይቀጥላል። . . . 1990ዎቹ ዓመታት የዚህ መቶ ዘመን የባሰ አደገኛ ሊሆኑ ወይም ደግሞ ወደር የለሽ መሻሻል የሚታይባቸው ሊሆኑ ይችላሉ።” — ቴረሪዝም፣ ድራግስ ኤንድ ክራይም ኢን ዩሮፕ አፍተር 1992
በመለወጥ ላይ ያለው አካባቢያችን
የሰው ሥራዎች በአካባቢያችን ላይ አደገኛ ውጤት በማምጣት ላይ መሆናቸውን ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ሰዎች ተገንዝበዋል። ደኖች በብዛት መጨፍጨፋቸው ቁጥር ሥፍር የሌላቸው የእንስሳትና የተክሎችን ዝርያ እየደመሰሰ ነው። ደኖች ደግሞ የፕላኔታችን የመተንፈሻ አካል ክፍሎች በመሆናቸው የደኖች ጥፋት ምድር ካርቦን ዳይኦክሳይድ የተባለውን የተቃጠለ አየር ሕይወት ደጋፊ ወደሆነው ኦክስጂን ለመለወጥ ያላትን ችሎታ መቀነስ ማለት ነው። ሌላው ውጤት ደግሞ በመሬት ገጽ ላይ ያለው ለም አፈር ተሸርሽሮ ተክሎችን የማብቀል ኃይሉ እንዲዳከምና በመጨረሻውም በረሃ እንዲሆን ማድረግ ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ አንዳንድ የማስጠንቀቂያ ድምፆች ተስተጋብተዋል። ከእነዚህም አንዱ የዩናይትድ ስቴትስ የፖለቲካ ሰው የሆኑት አል ጎሬ ናቸው። ኧርዝ ኢን ዘ ባላንስ — ኢኮሎጂ ኤንድ ዘ ሂዩማን ስፒሪት በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “የደኖች መጨፍጨፍ አሁን ባለው ፍጥነት ከቀጠለ ሁሉም የሐሩር አውራጃ ዝናባማ ደኖች እስከሚቀጥለው መቶ ዘመን አጋማሽ ድረስ ግማሽ በግማሽ ይጠፋሉ። ይህ ዓይነቱ የደን ጥፋት እንዲደርስ ከፈቀድንለት በፕላኔቲቱ ላይ ያሉትን ብዛት ያላቸው የዘር ሐረግ መረጃዎች ይጠፋሉ፤ በተጨማሪም ለሚያጠቁን ብዙ በሽታዎች ሊሰጡን የሚችሉትን ፈውስ እናጣለን። ዛሬ በጋራ የምንገለገልባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ጠቃሚ መድኃኒቶች በሐሩር አውራጃ ደኖች ካሉት ተክሎችና እንስሳት የተገኙ ናቸው።”
ሰው በአካባቢው ላይ ያደረሰው ተጽዕኖ የሰውን ሕልውና አደጋ ላይ እንደጣለ ጎር ያምናሉ። እንዲህ ብለዋል:- “ወደፈለግንበት ሥርቻ ሁሉ መስፋፋታችንን በቀጠልን ቁጥር የራሳችን ሥልጣኔ ድክመቱ . . . ይበልጥ እየታየን ይሄዳል። በታሪክ ውስጥ የደረሰ ማንኛውም እሳተ ገሞራ ካመጣው ለውጥ ይልቅ በአንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ ብቻ በጣም አስደናቂ በሆነ መንገድ የምድርን ከባቢ አየር ጠባይ ልንለውጥ በምንችልበት አስጊ ሁኔታ ላይ እንገኛለን። ውጤቱም ለሚመጡት መቶ ዘመናት ሁሉ ይቀጥል ይሆናል።”
ጎርና ሌሎችም እንደሚናገሩት ከባቢ አየራችን አስጊ ሁኔታ ላይ መውደቁ ብቻ ሳይሆን ለሕይወት የሚያስፈልገው የውኃ አቅርቦትም በአደጋ ላይ ነው። በተለይም “የውኃ መበከል በኮሌራ፣ በአንጀት ተስቦና በተቅማጥ በሽታ መልክ በሚከሰተው የሟቾች ቁጥር በአሳዛኝ ሁኔታ ከፍ ብሎ በሚታይበት” በማደግ ላይ ባለው ዓለም ጎልቶ ይታያል። ከዚያም በመቀጠል ጎር “ከ1.7 ቢልዮን በላይ የሆኑ ሕዝቦች ንጹሕ የመጠጥ ውኃ እንደሌላቸው አመልክተዋል። ከ3 ቢልዮን በላይ ሕዝቦች ደግሞ ተገቢ የመጸዳጃ አገልግሎት ስለሌላቸው ውኃቸው ሊመረዝ ይችላል። ለምሳሌ ያህል በሕንድ አገር የ114 ትናንሽና ትላልቅ ከተሞች የሽንት ቤትና ያልተጣሩ የፋብሪካ ፍሳሾች በቀጥታ ወደ ጋንጅስ ወንዝ ይገባሉ።” ይህ ወንዝ ደግሞ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የሕይወት አለኝታቸው ነው!
የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ጎታም ኤስ ካጂ በባንግኮክ ከተማ ተሰብስበው ለነበሩ አድማጮች “በምሥራቅ እስያ ያለው የውኃ አቅርቦት በመጪው መቶ ዘመን አወዛጋቢ ችግር ሊሆን እንደሚችል . . . ንጹሕ የመጠጥ ውኃ በጤናና በምርታማነት ረገድ የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ ቢሆንም የምሥራቅ እስያ መንግሥታት በአሁኑ ጊዜ የመጠጥ ውኃ ለማቅረብ የማይችሉ ሕዝባዊ ሥርዓቶች እያጋጠሟቸው መሆኑን . . . ይህም የጤናማ አካባቢ እድገት የተረሳ ጉዳይ እንደሆነ” አስጠንቅቀዋል። በዓለም ዙሪያ ለሕይወት አስፈላጊ ከሆኑት ዋና ዋና ነገሮች ውስጥ አንዱ የሆነው ንጹሕ ውኃ ችላ እየተባለና እየተበላሸ ነው።
እነዚህ ሁሉ በብዙ ቦታዎች ለሰው ልጅ መጪ ሕልውና በጣም አስጊ ወደሆነ አደገኛ የቆሻሻ ማጠራቂሚያነት በመለወጥ ላይ ያለው ዓለም ገጽታዎች ናቸው። ትልቁ ጥያቄ:- መንግሥታትና ታላላቅ የንግድ ድርጅቶች የምድር ሀብቶችን ማሽቆልቆል ለመግታት እርምጃ ለመውሰድ ፍላጎቱና ውስጣዊ ግፊት አላቸውን? የሚል ነው።
ሃይማኖት ዓለምን እየለወጣት ነውን?
የሰው ልጅ ከፍተኛ ውድቀት የሚታየው ምናልባት በሃይማኖት መስክ ሳይሆን አይቀርም። አንድ ዛፍ የሚመዘነው በፍሬው ከሆነ ሃይማኖት በውስጡ ላፈራቸው ጥላቻ፣ አለመቻቻልና ጦርነት ተጠያቂ መሆን አለበት። ሃይማኖት በብዙ ሰዎች ዘንድ እንደ ማስዋቢያ፣ ማለትም ከላይ እንደሚደረብ ሽፋን ብቻ የሚያገለግል ይመስላል። የዘር፣ የብሔራዊ ስሜት ወይም የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ሲያጋጥም ወዲያውኑ ተቀርፎ እንደሚወድቅ ሽፋን ነው።
ክርስትና ‘ባልንጀራህን ውደድ፣ እንዲሁም ጠላትህን ውደድ’ የሚል ሃይማኖት በመሆኑ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ካቶሊኮችና ኦርቶዶክሶች እርስ በርስ የሚጨራረሱት ምን ሆነው ነው? ሰዎቹ ለሚፈጽሙት የግድያ ኃጢያትና ጥላቻ ቀሳውስቶቻቸው ፍታት ይሰጧቸው ይሆን? በሰሜን አየርላንድ ለብዙ መቶ ዘመናት ሲሰጥ የኖረው የ“ክርስትና” ትምህርት ያፈራው ጥላቻንና ግድያን ብቻ ነውን? ክርስቲያን ያልሆኑ ሃይማኖቶችስ? ከክርስትና የተሻለ ፍሬ አፍርተዋልን? የሂንዱዝም፣ የሲኪዝም፣ የቡዲዝም፣ የእስልምናና የሺንቶ ሃይማኖቶች ሰላማዊ የሆነ የእርስ በርስ መቻቻል ታሪክ አስመዝግበዋልን?
ሃይማኖት በሰው ልጅ ሥልጣኔ ላይ ገንቢ ተጽዕኖ ከማሳደር ይልቅ ከልክ ያለፈ የሀገር ፍቅርን በማራገብና ሁለቱን የዓለም ጦርነቶችና ሌሎችንም ብዙ ውጊያዎች በመባረክ የራሱ የሆነ ገደብ የለሽ ሚና ተጫውቷል። ሃይማኖት የመሻሻል ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ኃይል ሆኖ አልተገኘም።
እንግዲያውስ በመጪው ቅርብ ጊዜ ከሃይማኖት ምን ሊጠበቅ ይችላል? እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ ላለው የዓለማችን ሥርዓት መጪው ጊዜ ምን ያመጣለታል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን? ማለትም ምን ለውጦች ይመጡ ይሆን? ሦስተኛው ርዕሳችን እነዚህን ጥያቄዎች ልዩ ከሆነ አቅጣጫ ይመረምራል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወንጀል በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ሌላው የለውጥ ምልክት ነው
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብሔራዊ ስሜትና ሃይማኖታዊ ጥላቻ ለደም መፋሰስ ምክንያት መሆናቸውን ቀጥለዋል
[ምንጭ]
Jana Schneider/Sipa
Malcom Linton/Sipa
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰው አካባቢውን በአግባቡ አለመያዙ ሕይወት ያላቸውን ነገሮችና የአካባቢያቸውን የተስተካከለ ሚዛን እየለወጠው ነው
[ምንጭ]
Laif/Sipa
Sipa
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፓፓ ኑንሲዮ ባሳሎ ዲ ቶሬግሮሳ ሂትለርን ሲጨብጡ፤ 1933። ከታሪክ ለመረዳት እንደሚቻለው ሃይማኖት በፖለቲካና በብሔራዊ ስሜት የተጠላለፈ ነው
[ምንጭ]
Bundesarchiv Koblenz