በመለወጥ ላይ ያለችው ዓለማችን መጪው ጊዜ ምን ይዞላታል?
ዓለማችን ወደ ተሻለ ሁኔታ እንድትለወጥ ከተፈለገ ምን የቀረን ምርጫ አለ? አንዱ አማራጭ የዓለም ገዥዎችና መሪዎች በመጨረሻው ለሌሎች ጥቅም የሚያስቡ ይሆኑና የሰው ልጆችን ወደጋራ መቻቻል፣ መግባባትና ሰላም መምራት ይጀምራሉ ብሎ ማመን ነው።
ይህም ማለት ጎሠኝነትና ብሔረተኝነት ጠፍተው ለዓለም ስምምነትን ሊያመጣ በሚችል፣ ብሔራዊ ድንበርን ንቆና ልቆ በሚሄድ ዝንባሌ ይተካሉ ብሎ ማመን ነው።
በተጨማሪም የካፒታሊስቱ ኢኮኖሚ ሥርዓት መሪዎች ከፍተኛ ሥራ አጥነት፣ ቤት የለሽነትና ከአቅም በላይ የሆነ የሕክምና ክፍያ በሞላባት ዓለም ውስጥ የአትራፊነት ዓላማ ብቻውን የማያዋጣ መርሕ መሆኑን ይገነዘባሉ ብሎ ማመንንም ይጨምራል።
በተጨማሪም የዓለም የጦር መሣሪያ አምራቾች በሙሉ ለዓለም ሰላምን መናፈቅ ይጀምሩና ሰይፋቸውን ማረሻ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ ብሎ ማመንም ነው።
ከዚህም ሌላ የማፊያ ድርጅትን፣ የሩቅ ምሥራቅ የወንጀል ጓዶችንና የደቡብ አሜሪካ የአደንዛዥ ዕጽ ከበርቴዎችን ጨምሮ የዓለም ወንጀለኞች ንስሐ ገብተው ከወንጀላቸው በመመለስ ለውጥ ያደርጋሉ ማለትም ነው!
በሌላ አነጋገር የሕልም እንጀራ በሆነ ሰው ሠራሽ ተምኔት ማመን ማለት ነው። አምላክን ከግምት ካላስገባነው ታሪክ ጸሐፊው ፖል ጆንሰን ኤ ሂስትሪ ኦቭ ሞደርን ዎርልድ በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ ከገለጹት ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ላይ እንገኛለን ማለት ነው። እኚህ ታሪክ ጸሐፊ ላለንበት መቶ ዘመን “መቅሰፍታዊ ውድቀትና አሳዛኝ መከራ” ዋና መንስኤ የሆነው ክፉ ነገር “ወንዶችና ሴቶች የማንም እርዳታ ሳያስፈልጋቸው በራሳቸው የማሰብ ችሎታ የጽንፈ ዓለምን ምስጢሮች ሁሉ ሊፈቱ ይችላሉ የሚለው የማን አለብኝነት እምነት ነው” ብለዋል።—ከኢሳይያስ 2:2–4 ጋር አወዳድር።
ይሁን እንጂ ገንቢ ለውጥ የሚመጣበት አንድ ተገቢ አማራጭ አለ። ይህም የምድር ፈጣሪ የሆነው የፕላኔታችን ባለቤት፣ ታላቁ የለውጥ መሐንዲስ ይሖዋ አምላክ የእጅ ሥራው የሆነችውን ምድር ለማዳን ሲል በሰው ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ መግባቱ ነው። አምላክ በቀድሞዎቹ ዘመናት ዓላማውን ለማራመድ እርምጃ ወስዶ እንደነበረ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ይገልጻል። አሁንም በቅርቡ ለሰው ልጅና ለመሬት የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ ለመፈጸም እርምጃ የሚወስድ መሆኑን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ያመለክታል።—ኢሳይያስ 45:18
የታመነ መረጃ የሚገኝበት ልዩ ምንጭ
መጪው ጊዜ ለሰው ልጆች ምን እንደሚያመጣላቸው የሚገልጽ እውነተኛ እውቀት ልዩ ምንጩ ምን እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢይ የሆነው ኢሳይያስ እንደሚከተለው ገልጾታል:- “የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። በመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ።”—ኢሳይያስ 46:9–11
ይሖዋ አምላክ የሰው ልጆችን የሚመለከቱ ነገሮችን አስቀድሞ ማወቅ የሚኖርበት ለምንድን ነው? ኢሳይያስ በድጋሚ “ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው” በማለት መልስ ይሰጣል። አምላክ ለወደፊቱ ለሰው ልጆች ያለው አሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል።—ኢሳይያስ 55:9
“የሚያስጨንቅ ዘመን”
የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ እኛ ስላለንበት ትውልድ ምን ትንቢት ተናግሮአል? ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ” በማለት አስጠንቅቋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ከ1914ና ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስጨናቂነቱ በሚጨምር ዘመን ውስጥ እንኖራለን። የሰው ልጅ ራስ ወዳድነት፣ ስግብግብነትና ለሥልጣን ያለው ጥማት መሰሎቹ በሆኑት ሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ በራሷ ላይ እየከፋ የሚሄድ ግፍ እንዲፈጽም አድርጎታል። ሰው ለአካባቢው ያሳየው ግዴለሽነት ወደፊት ለሚወለዱት ልጆቹና ለልጅ ልጆቹ ሕልውና የሚያሰጋ ነው።
ይህ አሳሳቢ አደጋ የቀድሞዋ ቼኮዝሎቫኪያ ፕሬዘዳንት የነበሩት ቫክሎቭ ሀቬል በአገራቸው ስለነበረው ሁኔታ በጻፉት ላይ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። የተናገሩት ነገር ለዓለም አቀፍ ሁኔታዎችም ይሠራል:- “ይሁንና እነዚህ መዘዞች . . . ሰው ለዓለም፣ ለሌሎች ሰዎችና ለሕልውና ለራሱ ያለው አመለካከት ውጤት ናቸው። እነዚህ መዘዞች . . . ሁሉንም ነገር መረዳትና ሁሉንም ነገር ማወቅ እችላለሁ ብሎ የሚያምነውና የተፈጥሮና የዓለም ተቆጣጣሪ ነኝ ብሎ ራሱን የሰየመው የዘመናዊው ሰው ማን አለብኝነት ውጤት ናቸው። . . . ከራሱ በላይ የሆነ . . . ምንም ነገር አላውቅም ብሎ አሻፈረኝ ያለው የሰው አስተሳሰብ እንዲህ ያለ ነው።”
ቀደም ሲል የተጠቀሱት አል ጎሬ እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር:- “ብዙ ሰዎች በመጪው ጊዜ ላይ እምነት እንዳጡ አረጋግጫለሁ። ምክንያቱም በማንኛውም የሥልጣኔያችን ገጽታ የወደፊቱ ጊዜ በጣም አጠራጣሪ በመሆኑ አሁን ባሉን ፍላጎቶችና የአጭር ጊዜ ችግሮቻችን ላይ ማተኮር ብልህነት ነው ብለን የምናምን በሚያስመስል መንገድ መኖር እየጀመርን ነው።” (ኧርዝ ኢን ዘ ባላንስ ) በእርግጥም መጪውን ጊዜ ጨለማ አድርጎ ማሰቡ የአብዛኛው ሕዝብ ዝንባሌ ይመስላል።
ይህ ሁኔታ የመጣበት ከፊል ምክንያት ቀጥሎ ያሉት የጳውሎስ ቃላት ስለሚፈጸሙ ነው:- “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ (ውለታቢሶች የ1980 ትርጉም)፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:2–5
የተሻለ አማራጭ
በዚህች ምድር ላይ ያሉ ሁኔታዎች ወደተሻለ ሁኔታ እንዲለወጡ የአምላክ ዓላማ ነው። “ጽድቅ የሚኖርባቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ለማምጣት ቃል ገብቷል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ይሖዋ አምላክ ይህችን የተበከለች ምድር ወደ ገነታዊ ሁኔታ ለመመለስ አስቀድሞ “ምድርን የሚያጠፉትን” ማጥፋት አለበት። (ራእይ 11:18) ይህ የሚከናወነው እንዴት ነው?
በታሪክ ዘመናት ሁሉ ከምንም ነገር የበለጠ በሰው ልጆች ላይ አፍራሽ ኃይል ሆኖ የኖረውን ነገር፣ ማለትም በምድር ዙሪያ በብሔራዊ ስሜት የሚያነድና የሚከፋፍል ተጽዕኖ የሆነውን ሃይማኖት ሥልጣንና ክብሩን እንዲገፉት አምላክ በቅርቡ በፖለቲካ ኃይሎች ልብ፣ በተባበሩት መንግሥታት ልብም ጭምር፣ እንዲገባ የሚያደርግ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌያዊ አነጋገር ያመለክታል።a ማርቲን ቫን ክሬቬልድ ዘ ትራንስፎርሜሽን ኦቭ ዎር በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ በተናገሩት መሠረት “ሃይማኖታዊ ዝንባሌዎች፣ እምነቶችና ጭፍን አክራሪነት የትጥቅ ውጊያን በማነሳሳት ረገድ ባለፉት 300 ዓመታት በምዕራቡ ዓለም ከተጫወቱት ሚና የበለጠ ለወደፊቱ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ የሚያሳዩ ብዙ ፍንጮች አሉ።” ሃይማኖት በፖለቲካዊ ሃይሎች እጅ ጥፋት የሚደርስበት ምናልባት በፖለቲካ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባ ስለሚዘባርቅ ሊሆን ይችላል። የሆነ ሆኖ እነዚህ ኃይሎች ሳይታወቃቸው የአምላክን ፈቃድ ይፈጽማሉ።—ራእይ 17:16, 17፤ 18:21, 24
አምላክ በመቀጠል ትኩረቱን የሰይጣንን ብልሹ የዓለም ሥርዓት ወደሚመሩት በዝባዥና አውሬ መሰል ፖለቲካዊ ኃይሎች እንደሚያዞርና በመጨረሻው በራሱ ጦርነት ማለትም በአርማጌዶን ውጊያ እንደሚገጥማቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። ጨካኞቹ ፖለቲካዊ ሥርዓቶችና የበላይ አንቀሳቃሻቸው ሰይጣን ከተወገዱ በኋላ አምላክ ቃል ለገባው ሰላማዊ አዲስ ዓለም መንገድ ይጠረጋል።b—ራእይ 13:1, 2፤ 16:14–16
የይሖዋ ምስክሮች 80 ለሚያህሉ ዓመታት ስለ እነዚህ መጪ ለውጦች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ሲሰብኩ ቆይተዋል። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የሰው ልጅ ያመጣቸውን ብዙ ለውጦች አይተዋል፣ ቀምሰውማል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈሩትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማክበር ሲሉ በናዚ እሥር ቤቶችና በማጎሪያ ካምፖች ብዙ ሥቃይ አሳልፈዋል። በብዙ የአፍሪካ አገሮች የኑሮ ሥቃይና መከራ፣ የእርስ በርስና የጎሳ ግጭቶች ጭምር፣ አጋጥሟቸዋል። በገለልተኝነት አቋማቸውና ቅንዓት በተሞላበት የስብከት ሥራቸው ምክንያት ብዙዎቹ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ያመጡባቸውን ስደት ተቋቁመዋል። ይህ ሁሉ ቢደርስባቸውም በ1914 ከነበሩበት ጥቂት ሺዎች ተነስተው በ1993 አራት ሚልዮን ተኩል ወደሚያህል ቁጥር በማደጋቸው ዓለም አቀፍ የማስተማር ሥራቸውን አምላክ እንደባረከላቸው አይተዋል።
ባለ ብሩህ ተስፋ ለመሆን የሚያስችሉ ምክንያቶች
ምስክሮቹ ሁኔታዎች ጨለማ አይሆኑባቸውም። ከዚህ ይልቅ ስለ መጪው ጊዜ ባለ ሙሉ ተስፋ ናቸው። ምክንያቱም በቅርብ ጊዜ በዚህች ምድር ላይ እጅግ በጣም ግሩም የሆኑ ታላላቅ ለውጦች እንደሚፈጸሙ ስለሚያውቁ ነው። ከ1914 ወዲህ የተፈጸሙት ሁኔታዎች ኢየሱስ የተናገራቸውን ምልክቶች ስለፈጸሟቸው በመንግሥታዊ ሥልጣኑ ላይ በማይታይ ሁኔታ መገኘቱንና አንድ ፈረንሳዊ ጸሐፊ ለ ሞንድ በተሰኘ ጋዜጣ ላይ ስለመጪው ቅርብ ጊዜ እንደገለጹት በሰው ጥረት ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው “ሥርዓት የለሽ ዓለም” በሚያበቃበት ጊዜ ላይ እንደምንገኝ ያመለክታሉ። ኢየሱስ “ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደቀረበች እወቁ” ብሏል።—ሉቃስ 21:7–32
ሰው ሠራሹ “አዲስ የዓለም ሥርዓት” የሰው ባሕርይ ክፍል የሆኑ ነገሮች ማለትም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የመድረስ ምኞት፣ የሥልጣን ጥማት፣ ስግብግብነት፣ ምግባረ ብልሹነትና የፍትሕ መዛባት ሊያጠቁት የሚችል ነው። የአምላክ አዲስ ዓለም ግን ለፍትሕ መስፈን ዋስትና ይሰጣል። ስለ አምላክ እንደሚከተለው ተጽፎአል:- “እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤ የታመነ አምላክ ክፋትም የሌለበት፣ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው።”—ዘዳግም 32:4
ሰው ሠራሹ “አዲስ የዓለም ሥርዓት” የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ጠበብት የሆኑት ማክጆርጅ ቡንዲ ሲናገሩ “ሥልጣናቸውን ለመጠበቅ ሲሉ የሕዝብን ስሜት ለመሳብ የሚጥሩና የማይፈጽሙትን ተስፋ የሚሰጡ ሰዎች የሚጠቀሙበት የጠባብ ብሔረተኝነት ስሜት” በማለት ለጠሩት ሁኔታ የተጋለጠ ነው። በመቀጠልም እንዲህ ብለዋል:- “ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ውድቀት እንደዚህ ላሉት አክራሪዎች እንዴት ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው ከታሪክ እናውቀዋለን። እንዲህ ዓይነቱ ብሔረተኝነት በየትኛውም ቦታ ቢሆን አደገኛ መሆኑን እናውቃለን።”
የአምላክ አዲስ ዓለም ከሁሉም ጎሣና ብሔር በተውጣጡ ሕዝቦች መካከል ስምምነትና ሰላም ለማምጣት ዋስትና ይሰጣል። ምክንያቱም ሰዎች አድልዎ ስለሌለባቸው የይሖዋ መንገዶችና ፍቅር ትምህርት ስለሚሰጣቸው ነው። “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፣ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል” ሲል ኢሳይያስ ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 54:13) ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጴጥሮስም “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደሆነ በእርግጥ አስተዋልሁ” ብሏል።—ሥራ 10:34, 35
በመጪው ቅርብ ጊዜ ውስጥ ዛሬ በምናውቀው ዓለም ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚደረግ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ከሁሉ የሚበልጡት ለውጦች፣ ዘላቂና ጠቃሚ የሚሆኑት ለውጦች፣ አምላክ እንደሚያመጣ ቃል የገባልን ለውጦች ናቸው። እርሱ ደግሞ “ሊዋሽ አይችልም።”—ቲቶ 1:2 አዓት
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ የደረሰ’ “ታላቂቱ ባቢሎን፣ የጋለሞታዎች እናት” በመባል ተገልጻለች። (ራእይ 17:3–6, 16–18፤ 18:5–7) ስለ ታላቂቱ ባቢሎን ማንነት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በኒው ዮርኩ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን የሰው ልጅ አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ የተሰኘ መጽሐፍ ገጽ 368–71 መመልከት ይቻላል።
b በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በትንቢት ስለተነገረላቸው ስለእነዚህ ሁኔታዎች ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በ1988 በመጠበቂያ ግንብና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን ራእይ — ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተሰኘ መጽሐፍ ከምዕራፍ 30–42 ተመልከት።