በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እየተሠቃዩ ነው እርዳታ ማግኘት ይችሉ ይሆን?
አፍሪካ ውስጥ በሚገኝ የንቁ! ዘጋቢ እንደተጠናቀረው
ኃይሉ ቢኖርህ ኖሮ በሰው ላይ እየደረሰ ያለውን ሥቃይ አታስወግድም ነበርን? ብትችል ኖሮ እንደምታደርገው አያጠራጥርም! ሆኖም ማንኛውም ሰው በዓለም ላይ ያለውን ሥቃይና ጭንቀት በሙሉ ጠራርጎ የሚያጠፋበት አንዳችም ብልሃት የሌለው መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው።
ሆኖም በአካባቢህ በመፈጸም ላይ ካለው ሥቃይ አንዳንዱን ለመቀነስ አልፎ ተርፎም ለመከላከል የሚያስችል ኃይል ሊኖርህ ይችላል። ለምሳሌ በብዙ አገሮች ጥንታዊ በሆነና በጣም ስር በሰደደ ወግና ልማድ ሳቢያ በአሥር ሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሴቶች ከፍተኛ ሥቃይና መከራ እየደረሰባቸው እንዳለ ተገምቷል። በባህሉ መሠረት ወላጆች የሴት ልጆቻቸው የጾታ ብልት ከፊሉ ወይም አብዛኛው ክፍል እንዲቆረጥ ያደርጋሉ፤ ይህን የሚያደርጉት የጠቀሟቸው መስሎ ስለሚታያቸው ነው። ይህ ድርጊት የሴቶች ግዝረት በመባል ሲጠራ ቆይቷል።a ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ አብዛኛዎቹ ኤክስፐርቶች ኤፍ ጂ ኤም [(ፊሜል ጄኒታል ሚውትሌሽን) የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል መቁረጥ] በማለት ይጠሩታል። ልማዱን ይበልጥ ትክክለኛ በሆነ መንገድ የሚገልጽ ቃል ነው።
የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል መቁረጥን አስመልክቶ የወጣው የሆስኪን ሪፖርት የጾታ ብልትን ክፍል የመቁረጥ ልማድ ከምሥራቅ አፍሪካ እስከ ምዕራብ አፍሪካና በአቅራቢያ ባሉ ሥፍራዎች ተንሠራፍቶ የሚገኝ ሰፋ ባለ ክልል ውስጥ የሚዘወተር ልማድ ነው ሲል ይጠቁመናል። ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትለው ይህ የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል የመቁረጥ ተግባር የጤና እክሎችን ሊያመጣና ሕይወትን ትልቅ አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።
የተቃውሞ ድምፆች ተሰምተው ነበር
ይህን ልማድ በመቃወም መናገሩ ቀላል አልነበረም። ዘ ስታንዳርድ የተባለው የኬንያ ጋዜጣ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል መቁረጥ “በምሥጢር ተይዞ ቆይቷል። ቀዶ ሕክምናውን ለማስቆም ለሚፈልጉት ሴቶች ወይም ወንዶች ይህን ልማድ በማውገዝ መናገር አስቸጋሪ አንዳንድ ጊዜም አደገኛ ይሆንባቸው ነበር። ፀረ–ባሕል፣ የቤተሰብ ፀር፣ ፀረ–ሃይማኖት፣ የአገር ፀር፣ ወይም የገዛ ራሳቸውን ሕዝብና ባሕል የሚጠሉ እየተባሉ ብዙ ጊዜ ይወቀሱ ነበር።”
ይኸው የአፍሪካ ጋዜጣ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል መቁረጥ “‘ጉዳት የሌለው ባሕላዊ ልማድ’ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሴቶችና በልጃገረዶች ላይ ለሚደርሰው ምንጊዜም አብሮ ለሚኖረው አካላዊ ጉዳትና ሞት ዋነኛ መንሥኤ ነው። . . . ልጃገረዶች አካላቸው በጥሩ ሁኔታ ተጠብቆና ጤናማ ሆነው የመኖር መብታቸውን የሚጥስ ድርጊት ነው።”
በመላዋ አፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰዎችን ስለዚህ ልማድ ጎጂነት ለማስተማር ጥረት በማድረግ ሌሎች ብዙ ሰዎች ድምጻቸውን እያሰሙ ነው። ይህ ልማድ ልጃገረዶች ከሕጻንነታቸው ጀምሮም እንዲሠቃዩና የአካል ክፍላቸውን እንዲያጡ ያደርጋል። በጤና ረገድ ጥቅም ያስገኛል የሚያሰኝ አንዳችም በቂ ምክንያት የለውም።
ሥቃይ የሚያስከትሉና ምንጊዜም አብረው የሚኖሩ በርካታ በሽታዎችና የሞቱ ሰዎች ቁጥር የጤና ባለሙያዎችንና የብዙ አገሮች መንግሥታትን አሸብሯቸዋል። እንዲያውም የሴቶችን የጾታ ብልት መቁረጥ በአፍሪካ ውስጥ ለኤድስ መዛመት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ሊሆን ይችላል የሚል ሐሳብ ተሰንዝሯል። እንዲሁም ከአፍሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ወደ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ አውሮፓና ዩናይትድ ስቴትስ ያለማቋረጥ በሚጎርፈው ሕዝብ የተነሣ ይህ የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል የመቁረጥ ተግባር በአንዳንድ የምዕራብ አገሮች ውስጥ በሚገኙ የጤና ጣቢያዎች ከፍተኛ የሕዝብ የጤና ችግር እየሆነ መጥቷል። አንድን ሕመም ይበልጥ እንዲባበስ ያደረጉ የጤና እክሎችን ለማስወገድ ለሚደረገው ለረጅም ጊዜ የሚቀጥል ሕክምና የሚወጣው ወጪና በአብዛኛው የሚከሰተው የሥነ ልቦና ቀውስ ቸል ተብሎ የሚታለፍ አይደለም።
ይህን ልማድ ለመግታት መንግሥታት ያወጧቸው ሕጎች ተግባራዊ ሆነዋል፣ እየሆኑም ነው። እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያንና ስዊድን የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል መቁረጥ በሕግ ከታገደባቸው የአውሮፓ አገሮች መካከል አንዳንዶቹ ናቸው። በካናዳ እየታተመ የሚወጣው ዘ ግሎብ ኤንድ ሜል የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል መቁረጥ “የኦንታሪዮን ዶክተሮች በሚመራው የሕግ አውጪ አካል ከታገደ ቆይቷል” በማለት ዘግቧል። በተጨማሪም እንዲህ የሚል ሐሳብ አሥፍሮ ነበር:- “ምንም እንኳን የካናዳ ሕግ የሴቶችን ግዝረት በቀጥታ ባይጠቅስም የመንግሥት ባለሥልጣኖች እንዲህ ዓይነቶቹ ልማዶች በልጆች ላይ እንደሚፈጸም የጭካኔ ድርጊት ወይም የከፋ ወንጀል ተደርጎ መታየት አለበት ብለዋል።”
የዓለም የጤና ድርጅትን የመሰሉ በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል መቁረጥን ለማጣጣል ጥረት አድርገዋል። የሴኔጋል፣ የኡጋንዳና የዚምባብዌን መሪዎች የመሳሰሉ የአፍሪካ አገሮችን ፕሬዘዳንቶች ጨምሮ የዓለም መሪዎች በመስከረም 1990 በልጆች መብቶች ላይ የደረሱባቸውን ስምምነቶች ለመፈራረም በኒው ዮርክ ውስጥ በተገናኙበት ጊዜ አንድ አዲስ ምዕራፍ ላይ ተደረሰ። ይህ ሰነድ የሴቶችን ግዝረት በሰው ላይ አካላዊ ጉዳት በማድረስ የማሠቃየትንና አላግባብ በሰው ላይ የጾታ ነውር የመፈጸምን ያህል ያወግዘዋል።
በለንደን የሚታተመው ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “ይበልጥ ትክክለኛ በሆነ አጠራሩ የሴቶችን ብልት ክፍል መቁረጥ ተብሎ የሚጠራው የሴቶች ግዝረት ለማውራት ከሚሰቀጥጡት በአፍሪካ ውስጥ የሚፈጸሙ እጅግ ዘግናኝ ነገሮች አንዱ በመሆን እስከ ጊዜያችን ድረስ ዘልቋል። ለንደን ውስጥ የሚገኘው ለአናሳ ቡድኖች መብት የሚከራከር ቡድን ባወጣው ሪፖርት መሠረት . . . በየዓመቱ በአሥር ሚልዮኖች የሚቆጠሩ ልጃገረዶች ይህ ድርጊት ይፈጸምባቸዋል።”
ይህ ጽሑፍ ሃሳቡን በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “ይህ ልማድ ቀለል ካለ የሕመም ስሜት አንሥቶ እስከ ሞት ድረስ ሊያደርሱ የሚችሉ ሥቃዮችን የሚያስከትል ነው። በጾታ ግንኙነት ወቅት የጾታ ስሜት የሚቀሰቅሰውን የሴቷን ብልት ክፍልና ሌሎች የጾታ ብልት ክፍሎችን በቢላዋ፣ በብርጭቆ ስባሪና በምላጭ መቁረጥን ሊጨምር ይችላል። ይሁን እንጂ አንዳንዴ እነዚህ የጾታ ብልት ክፍሎች ይደነዝዛሉ። ከወር አበባና ከጾታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ከባድ ችግሮችንና የወሊድ እክሎችን እንዲሁም የሥነ ልቦና መረበሽን አልፎ ተርፎም ሞትን ሊያስከትል ይችላል። . . . በአጉል እምነት የተነሣ በሴቶች የጾታ ስሜት ላይ ይደርሳሉ ተብለው የሚታሰቡ ነገሮችን በመፍራት፣ በልምድና ለንጽሕና ይረዳል በሚል የተሳሳተ እምነት ሳቢያ አሁንም ይህ ልማድ እየተሠራበት ይገኛል።”
ይህ ልማድ አንሠራርቷል
ይህ ልማድ በብዙዎቹ ሴቶች ላይ በተፈጸመባቸው አንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ በጣም አደገኛ የሆነውን የሴትን ብልት ክፍል የመቁረጥ ዘዴ የሚያግድ ሕግ በ1947 ወጥቶ ተግባራዊ ሆኖ ነበር። ይሁን እንጂ አሁንም ይህን ልማድ መከተላቸውን አላቆሙም። ለምን? ምክንያቱም ድርጊቱ ጠቃሚ ነው ብለው የሚያስቡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳሳተ ሐሳብ እየተላለፈላቸው በመሆኑና የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል መቁረጥ ጠቃሚ ነው ብለው በማመን ስለተታለሉ ነው። ለምሳሌ ያህል በዕድሜ የገፉ የመንደር ሴቶች ለልጃገረዶቹ ጥቅም ሲባል የሚደረግ ነገር ነው ብለው ያምናሉ። ዘ ጋርዲያን የተባለው የናይጄሪያ ጋዜጣ እንደዘገበው ማይኖሪቲ ራይትስ ግሩፕ ለአናሳ ቡድኖች መብት የሚከራከር ቡድን “ይህን ልማድ ጠብቀው ያቆዩትን አረጋውያን ሴቶች አስተሳሰብ መለወጥ” አስፈላጊ ነው ያለው በዚህ ምክንያት ነው።
ነርሲንግ ታይምስ የተባለው መጽሔትም ተመሳሳይ የሆነ መደምደሚያ ላይ ደርሷል:- “የሴቶችን ግዝረት መዋጋት የምትችሉት ትምህርት በመስጠት ብቻ ነው።” ይኸው መጽሔት ቆየት ብሎ “ስለጉዳዩ በማሳወቅና ወንዶችን እንዲሁም ሴቶችንም በማስተማር ችግሩ በሙሉ ሊቀረፍ ይችላል” በማለት ገልጿል። ወንዶችንም ማስተማር ያስፈለገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ብዙ አባቶች ሴት ልጆቻቸውን ያልተገረዘች ሴት ለማያገቡ ወንዶች ለመዳር ሲሉ ለቀዶ ጥገናው ስለሚከፍሉ ነው።
ይህ የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል የመቁረጥ ተግባር ሊቀጥል የቻለበት ሌላው ምክንያት ገንዘብ የሚያስገኝ በመሆኑ ነው። ዘ አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ነርሲንግ “ግዝረት ድርጊቱን ለሚፈጽሙት ሰዎች ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ልማዱን ጠብቀው በማቆየታቸው ጥቅም ያገኛሉ” ሲል ይገልጻል። ይህን ድርጊት እንዲያከናውኑ ሲባል ገንዘብ የሚከፈላቸው አረጋውያን ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ አዋላጆችና ጸጉር አስተካካዮችም ጭምር ናቸው። ንጽሕና በጎደላቸው መሣሪያዎች አማካኝነት በሚደረጉ ቀዶ ሕክምናዎች የተነሣ ልጃገረዶቹ ሊደርሱባቸው ከሚችሉት አደገኛ ሁኔታዎችና በሥነ ልቦና ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ከሚችሉ መጥፎ ትዝታዎች መካከል አንዳንዶቹን ለማስወገድ ሲሉ በአንዳንድ የሕክምና ክሊኒኮች ውስጥ የሚገኙ ነርሶችና ሐኪሞችም እንደዚሁ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ ድርጊቱን ማንም ፈጸመው ማን የአካል ክፍልን የመቁረጥ ድርጊት መሆኑ አይቀርም።
በአንዳንድ ሁኔታዎች በጉልምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሴቶች በሚወልዱባቸው ዓመታት ሁሉ በተደጋጋሚ ይህ ቀዶ ጥገና ይፈጸምባቸዋል። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ኢንተርናሽናል እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “ብዙ ሴቶች ልጅ በወለዱ ቁጥር ቀደም ሲል በክር የተሰፋው የጾታ ብልታቸው ክፍል እንዲፈታ ስለሚደረግና ከዚያም እንደገና ስለሚሰፋ እጅግ ይሠቃያሉ። በግዝረት ምክንያት የተከሰተውን ጠባሳ ከወሊድ በፊት ይተረትሩታል፤ ከወሊድ በኋላ ደግሞ እንደገና ይሰፉታል። ይህ ሁኔታ አደገኛ የሆነ የደም መፍሰስ ችግርና የምጥ ጊዜ መራዘምን ያስከትላል። እንዲሁም በማኅፀን ውስጥ ያለው ሕጻን በአእምሮው ላይ ቀውስ ሊደርስበት የሚችልበትን አጋጣሚ ከፍ ያደርገዋል።
ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል:- ብዙ “ትንንሽ ልጃገረዶች እስከ ሞት ድረስ የሚያደርስ ደም የመፍሰስ ችግር ያጋጥማቸዋል። ምክንያቱም ግዝረቱን የሚያከናውኑት ቸልተኛ የሆኑ ሰዎች በጾታ ግንኙነት ወቅት ስሜት በሚቀሰቅሰው የሴቷ ብልት ክፍል ላይ የሚገኘውን ፑዴንዳል የተባለውን ደም ቅዳ ወይም ዶርሳል የተባለውን ደም ቅዳ ስለሚቆርጡት ነው። ሌሎች ደግሞ ግዝረቱ ከተከናወነ በኋላ ራሳቸውን እንደሳቱ በመቅረት ይሞታሉ። ምክንያቱም ራሳቸውን ከሳቱበት ሁኔታ እንዴት ማውጣት እንደሚቻል የሚያውቅ የለም። ሆስፒታል የሚገኝበትም ቦታ ካሉበት ቦታ በጣም የራቀ ነው። ወይም ድርጊቱን የሚፈጽሙት ሰዎች እርዳታ ለመጠየቅ ያቅማማሉ። ምክንያቱም ቸልተኝነት በተሞላበት የግዝረት ሥራቸው ያፍራሉ።”
ያም ሆኖ ድርጊቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው። የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል መቁረጥን አስመልክተው የሚወጡት ሪፖርቶች በአፍሪካና በአውሮፓ ጋዜጦች ላይ መውጣታቸውን ቀጥለዋል። አንድ የአፍሪካ መጽሔት በቅርቡ የሚከተለውን ሪፖርት አድርጓል:- “የጾታ ብልታቸው ክፍል ከተቆረጠባቸው ሴቶች መካከል አብዛኛዎቹ ሕጻናትና ልጃገረዶች ናቸው። ምንም እንኳን ወላጆች ትክክለኛና አስፈላጊ ነው ብለው በማመን ሴት ልጆቻቸውን ቢያስገርዙም ቀዶ ሕክምናውን ከዚያ በኋላ የሚያስከትለው ውጤት በአንድ ሰው ላይ አካላዊ ሥቃይ ከማድረስ አይተናነስም።” ዘ ኢንዲፔንደንት (የሐምሌ 7, 1992 እትም) በተባለው የለንደን ጋዜጣ መሠረት አንድ በቅርቡ የተካሄደ ጥናት “ይህ ልማድ በእንግሊዝ ውስጥ በፊት ይታመንበት ከነበረው በበለጠ ሁኔታ በስፋት ተሰራጭቶ ነበር” ሲል ገልጿል። በብሪታንያ ውስጥ ከ10,000 የሚልቁ ልጃገረዶች “ከእነዚህም መካከል አብዛኛዎቹ ዕድሜያቸው ስምንት ወይም ከዚያ በታች የሆኑት ለሴቶች ግዝረት አደጋ እንደተጋለጡ ተገምቷል።”
በሐሰት ላይ የተመሠረተ ወግና ልማድ
አንዳንዶች የሴቶች የጾታ ብልት ክፍሎች ርኩስ ስለሆኑ እነርሱን ቆርጦ በማውጣት ማንጻት ይገባል የሚለውን የሐሰት ትምህርት ያምናሉ። በጾታ ስሜት በሚገኘው ደስታ የመርካት መብት ያላቸው ወንዶች ብቻ ናቸው ብለው ያስባሉ። የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል መቁረጥ ብዙ ለመውለድ ያስችላል፤ የጾታ ብልግናን ይቀንሳል፤ እንዲሁም አንዲት ልጃገረድ ትዳር ለመመሥረት ያላትን ዕድል ያሰፋላታል ተብሎም ይታመናል። ታይም መጽሔት “ምጸት በተሞላበት አነጋገር” እንዲህ ሲል ገልጿል:- “የሴቶች የጾታ ብልት በመቆረጡ የተነሣ የሴቶቹ የጾታ ስሜት አለመቀስቀሱ ወይም መውለድ አለመቻላቸው ብዙ ባሎች ከሙሽሮቻቸው እንዲርቁ ያደርጋቸዋል።”
በቅርቡ በናይጄሪያ ሌጎስ ውስጥ በኢንተር አፍሪካን ኮሚቴ ኮንፈረንስ ላይ የተገኙ የስብሰባው ተሳታፊዎች የሴቶች ግዝረት ሴቶችን ከአመንዝራነት ይጠብቃቸዋል የሚለውን አባባል ባለማመን ገና በለጋ ዕድሜያቸው የሥነ ምግባር ማሰልጠኛ መስጠቱ ይበልጥ ጠቃሚ ነው ሲሉ ገልጸዋል። መጥፎ ድርጊቶች ሊወገዱ የሚችሉት የአካል ክፍልን በመቁረጥ ሳይሆን ትምህርት በመስጠት ነው። በምሳሌ ለማስረዳት:- ሕጻናት ወደፊት ሌቦች እንዳይሆኑ ለማድረግ እጃቸውን መቁረጥ ይኖርብናልን? ወይም መጥፎ ነገሮች ፈጽሞ እንዳይናገሩ ምላሳቸውን መቁረጥ ይገባናልን?
ናይጄሪያውያን የሆኑ አንድ ባልና ሚስት ሴት ልጃቸው እንዳትገረዝ ከለከሉ። ይህ ድርጊት ልጅቷ ስታድግ አመንዝራ ትሆናለች ብለው ያሰቡትን የባልየውን እናት አስቆጣቸው። ይሁን እንጂ በጥሩ ሥነ ምግባር ታንጻ ስላደገች ልጅቷ ክብረ ንጽህናዋን ጠብቃ ቆየች። በአንጻሩ ቢገረዙም እንኳን ወላጆቻቸው ጊዜ ወስደው በጥሩ ሥነምግባር ስላላሰለጠኗቸው በጥቅሉ አመንዝሮች የሆኑ ይህ ቤተሰብ የሚያውቃቸው አንዳንድ ልጆች አሉ። አያትየው ይህን ሲመለከቱ ቁም ነገሩ መገረዝ ወይም አለመገረዝ ሳይሆን በልጆች ውስጥ የአምላክን የሥነ ምግባር ሕግጋት መትከል እንደሆነ ተገነዘቡ።
ሴት ልጆቻችንን የምናፈቅራቸው ከሆነ የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል መቁረጥ በሕይወታቸው ላይ የሚያመጣቸውን የከፉ መዘዞች በማሰብ ይህንን ልማድ በማንኛውም መንገድ ከመፈጸምም ሆነ ከመደገፍ እንቆጠባለን። በአንዳንድ ቦታዎች ማኅበረሰቡን መፍራት ይህን ወግና ልማድ እንዲከተሉ ከፍተኛ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ይህን እርምጃ መውሰድ ድፍረትን ይጠይቃል።
ከሃይማኖት ጋር ያለው ትስስር
የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል የመቁረጥ ተግባር ታሪኩ በግልጽ የሚታወቅ ነው። ይህ ልማድ ዘመናትን ያስቆጠረና አልፎ ተርፎም በጥንቷ ግብጽ እንዳይፈርሱ በመድኃኒት ተጠብቀው በቆዩ አስከሬኖች ላይ በግልጽ የሚታይ ነገር ነው። ፕላስቲክ ኤንድ ሪኮንስትራክቲቭ ሰርጀሪ የተባለው መጽሔት “የሴቶች ግዝረት በጥንቷ ግብጽ ውስጥ የሚዘወተር ልማድ ነበር። ሁለቱንም ጾታ በያዙ አማልክት ላይ ይካሄድ ከነበረው ፈርኦናዊ እምነትም ጋር የተያያዘ ድርጊት ነበር” ሲል ይገልጻል። እስከ ጊዜያችንም ድረስ ከዚህ የአካል ክፍልን የመቁረጥ ተግባር መካከል ከሁሉ የከፋው ፈርኦናዊ ግዝረት ተብሎ ይጠራል።
በአንዳንድ ቦታዎች ጥንታዊ የሆኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል ከመቁረጥ ጋር የተቆራኙ ናቸው። አንድ የአፍሪካ ባለሥልጣን እንዳብራሩት ከቀድሞ አባቶች አምላክ ጋር የሐሳብ ግንኙነት እንደማድረግ የሚታይ አንድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት አለ። ይህ አምላክ ልጃገረዶቹ ቀዶ ሕክምናው ሲደረግላቸው እንዲረዳቸውና እግረ መንገዱንም የአባቶቻቸውን ጥበብ ለልጆቹ እንዲሰጣቸው ይለምኑታል። — ከ2ኛ ቆሮንቶስ 6:14–18 ጋር አወዳድር።
የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል የመቁረጥ ተግባር በሚዘወተርባቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች ይህን ወግና ልማድ የማይከተሉት ለምን እንደሆነ ማወቅ አስቸጋሪ አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሴቶች ላይ እንዲህ ያለ የአካልን ክፍል የመቁረጥ ተግባር አስፈላጊ መሆኑን የሚጠቁም አንዳችም ነገር የለም። ፈጣሪ ሴቶችን በጋብቻ ዝግጅት ውስጥ በጾታ ስሜት እንዲረኩ አድርጎ እንደፈጠራቸው ግልጽ ነው። የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል የመቁረጥ ተግባር ቅዱሳን ጽሑፎች ከሚያራምዷቸው ከፍቅር፣ የሌላውን ችግር እንደ ራስ ችግር አድርጎ በመመልከት የችግሩ ተቋዳሽ ከመሆንና ከምክንያታዊነት መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ይቃረናል። — ኤፌሶን 5:28, 29፤ ፊልጵስዩስ 4:5
ከሁሉም በላይ የፍቅር አምላክ የሆነው ይሖዋ በዚህ ምክንያታዊ ባልሆነ የአካልን ክፍል የመቁረጥ ተግባርና በዚህም ሳቢያ በሚልዮን በሚቆጠሩ ሴቶችና ትንንሽ ልጃገረዶች ላይ በሚደርሰው ሥቃይ ያዝናል። ማንኛውም ሰው የማይሠቃይበት የአዲስ ዓለም ተስፋ በመስጠቱ ምንኛ ደስተኞች ነን! — ራእይ 21:3, 4
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሰኔ 22, 1985 በወጣው የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት እትም ላይ “ሴቶች የሚገረዙት ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ስለ ወንዶች ግዝረትስ ምን ሊባል ይቻላል?
አንዳንዶች የወንዶች ግዝረትስ ቢሆን የአካልን ክፍል የመቁረጥ ተግባር አይደለም እንዴ? የሚል ጥያቄ ሊያነሡ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በአንድ ወቅት ላይ ወንዶች መገረዝ እንዳለባቸው የሚያሳስብ ሕግ እንደደነገገ ይገልጻል። ከጊዜ በኋላ የክርስቲያን ጉባኤ ሲቋቋም ግዝረት የግድ መደረግ ያለበት ነገር መሆኑ ቢያበቃም ድርጊቱ ግን አልተከለከለም። እያንዳንዱ ግለሰብ እገረዛለሁ ወይም አልገረዝም ወይም ወንዶች ልጆቼን አስገርዛለሁ ወይም አላስገርዝም ብሎ መወሰን የራሱ ፋንታ ነው።
በዛሬው ጊዜ የወንዶች ግዝረት በብዙ ቦታዎች የሚዘወተር ድርጊት ነው። ቀዶ ሕክምና ከብልት ላይ ሸለፈትን የሚያስወግድ መሆኑ አይካድም። ይሁን እንጂ ይህ ልማድ በምንም ዓይነት መንገድ የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል ከመቁረጥ ጋር ሊነጻጸር አይችልም። በአብዛኛው ወንዶች መገረዛቸው ምንም ዓይነት ጉዳት አያመጣባቸውም። በአንጻሩ ግን ሴቶች የጾታ ብልታቸው ክፍል ከተቆረጠ የወር አበባ፣ የጾታ ግንኙነት፣ ልጅ መውለድና ሽንት መሽናትን በመሰሉ የሴቶች ተፈጥሯዊ የአካል አሠራሮች ላይ ብዙውን ጊዜ የዕድሜ ልክ ሥቃይ የሚያስከትሉ እክሎች ያጋጥሟቸዋል። በተጨማሪም በጣም ከባድ የሆነ ምጥ በሚወለደው ሕፃን ላይ አካላዊ ጉዳት ያስከትላል፤ አልፎ ተርፎም ብዙ የሚወለዱ ሕጻናት ሕይወታቸው እንዲያልፍ ያደርጋል።
በጾታ ግንኙነት ጊዜ የሚኖረውን ስሜት በሙሉ ለማስወገድ የራሳቸው ወይም የወንዶች ልጆቻቸው የጾታ ብልት ክፍል እንዲቆረጥ የሚያደርጉና በዚህም ምክንያት በሕይወታቸው በሙሉ የማያቋርጥ ሥቃይና የጤና እክሎች እንዲደርሱባቸው ፈቃደኛ የሚሆኑ ወንዶች ይኖራሉን? የወንዶች ግዝረትና የሴቶችን የጾታ ብልት ክፍል የመቁረጥ ተግባር በምንም ዓይነት ሊነጻጸሩ እንደማይችሉ ግልጽ ነው።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዲት አፍሪካዊት ልጃገረድ እንዲህ ብላለች
‘ስገረዝ ስምንት ዓመቴ ነበር። አሁን 11 ዓመት ሆኖኛል፤ ይሁን እንጂ እስከ አሁን ድረስ የቀዶ ሕክምናውን በደንብ አስታውሰዋለሁ። ስለሱ ማሰቡ እንኳን ይረብሸኛል። አንዳንዴም የሚያስፈሩ ሕልሞችን አልማለሁ። አብዛኛውን ጊዜ ደስተኛ ነኝ፤ ስለዚህ ጉዳይ በማስብብት ጊዜ ግን በውስጤ የሞትኩ ያህል ሆኖ ይሰማኛል።
‘መጀመሪያ ስለሱ ስሰማ ተደስቼ ነበር። ቤተሰቦቼና ዘመዶቼ ብዙ ስጦታዎችን ይሰጡኝ ነበር። የግዝረት ቀዶ ሕክምና ምን እንደሆነ አላውቅም ነበር፤ ይጎዳኛል ብዬም አላሰብኩም ነበር።
‘ደስታዬ ጠፋ። ማልቀስ ጀመርኩ። በጣምም ፈራሁ። አራት ሴቶች እጆቼንና እግሮቼን ይዘውኝ ነበር። አንደኛዋ ሴት በእጅዋ አፌን ያዘችው። ራሴን ለማስለቀቅ ሞከርኩ። ይሁን እንጂ እነርሱ ከእኔ ይበልጥ ጠንካሮች ነበሩ። እንደገና ወደ ታች ተጫኑኝ። ሕመሙ ያንሰፈስፋል።
‘ስለቱ ሲቆርጠኝ አካባቢው በሙሉ ደም በደም ሆነ። አንዳችም ነገር ያን ያህል ያሳምማል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። ከዚያ በኋላ እንቁላልና ስኳር ቀላቅለው ቁስሉ ላይ አደረጉበት። ከዚያም እግሮቼን አንድ ላይ አስረው ወደ መኪናው ተሸክመው ወሰዱኝ። ወደ ሠፈራችን እስክንደርስ ድረስ አለቅስ ነበር።’ — ዘ ስታንዳርድ ከተባለው የኬንያ ጋዜጣ ላይ የተወሰደ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
WHO/OXFAM