በብዙዎች ዘንድ የሚታመንባቸው የተሳሳቱ ግንዛቤዎች
የተሳሳተ ግንዛቤ:- አብዛኛውን ጊዜ ልጆችን በጾታ የሚያስነውሩት እንግዳ የሆኑ ሰዎች ናቸው፤ ልጆችን አፍነው የሚወስዱና ኃይል ተጠቅመው የሚያስነውሩ አእምሯቸው ንክ የሆነ ሰዎች ናቸው።
በጾታ ከሚነወሩት ልጆች መካከል አብዛኞቹ፣ እንዲያውም በአንዳንድ ጥናቶች መሠረት ከ85 እስከ 90 በመቶ የሚገመቱት ልጆች የሚነወሩት በሚያውቁትና በሚያምኑት ሰው ነው። ልጆችን የሚያስነውሩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ኃይል ከመጠቀም ይልቅ የልጆችን የተሞክሮና የማመዛዘን ችሎታ ውስንነት መሣሪያ አድርገው በመጠቀም ቀስ ብለው እያባበሉ እነርሱ የፈለጉትን የጾታ ድርጊት እንዲፈጽሙ ያደርጓቸዋል። (ከ1 ቆሮንቶስ 13:11 እና ከምሳሌ 22:15 NW ጋር አወዳድር።) እንዲህ ዓይነቶቹ ልጆችን የሚያስነውሩ ሰዎች ራሳቸውን ከሌሎች ማግለል የሚመርጡ ንክ ሰዎች አይደሉም። ብዙዎቹ ሃይማኖተኞች፣ የተከበሩና የማኅበረሰቡን ፍቅር ያተረፉ ሰዎች ናቸው። የአሜሪካ ፌዴራል የምርመራ ቢሮ ባለው መሠረት “አንድ ሰው ጥሩ ስለሆነ፣ ቤተ ክርስቲያን ስለሚሄድ፣ ታታሪ ሠራተኛ ስለሆነ፣ እንስሳትን ስለሚወድና ጥሩ ጥሩ የሚባሉ ነገሮችን ስለሚያደርግ ብቻ ልጆችን በጾታ ሊያስነውር አይችልም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።” ልጆችን በጾታ የሚያስነውሩት ወንዶች ብቻ ናቸው ወይም ደግሞ በጾታ የሚነወሩት ልጆች ሴቶች ብቻ ናቸው ብሎ ማሰብም ስህተት እንደሆነ በቅርብ ጊዜ የተካሄዱ ጥናቶች ጠቁመዋል።
የተሳሳተ ግንዛቤ:- ልጆች በጾታ እንደተነወሩ አድርገው ያልማሉ፤ ወይም ሳይነወሩ በውሸት እንደተነወሩ አድርገው ይናገራሉ።
ምንም እንኳ አንዳንድ ትንንሽ ልጆች ጉዳዩን በዝርዝር ለማስረዳት ሊቸገሩ ቢችሉም አብዛኛውን ጊዜ ልጆች ስለ ጾታ ጉዳዮች ብዙም የሚያውቁት ነገር ስለሌለ በውሸት በጾታ እንደተነወሩ አድርገው በግልጽ ሊናገሩ አይችሉም። በጣም ተጠራጣሪ የሆኑት ተመራማሪዎች እንኳ ተፈጸሙ የሚባሉት አብዛኞቹ የማስነወር ድርጊቶች በሐቅ ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑ ያምናሉ። በውሸት ተፈጽመዋል በተባሉ የማስነወር ድርጊቶች ላይ የሚያተኩረውን ሴክስ አብዩዝ ሂስቴሪያ—ሳሌም ዊች ትራያልስ ሪቪዚትድ የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።a ይህ መጽሐፍ የሚከተለውን ሐቅ ተቀብሏል:- “ልጆችን በጾታ የማስነወር ወንጀል በእጅጉ ተስፋፍቷል፤ በልጆች ላይ እንደተፈጸመ የሚነገረው አብዛኛው በጾታ የማስነወር ወንጀል (ምናልባትም 95% ወይም ከዚያ በላይ የሚሆነው) . . . በትክክል የተፈጸመ ድርጊት ሳይሆን አይቀርም።” ልጆች በጾታ እንደተነወሩ መናገር በጣም ይከብዳቸዋል። እንዲያውም ብዙውን ጊዜ በጾታ የማስነወር ወንጀል ተፈጽሞባቸው እያለ አልተፈጸመብንም ብለው ይዋሻሉ እንጂ ሳይፈጸምባቸው ተፈጸመብን አይሉም።
የተሳሳተ ግንዛቤ:- ልጆች የጾታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ከመሆናቸውም በላይ ብዙውን ጊዜ በጾታ ለመነወር የሚዳርጋቸው የራሳቸው ምግባር ነው።
ይህ አባባል በጾታ የተነወሩ ልጆችን ጥፋተኛ አድርጎ የሚወነጅል በመሆኑ የተዛባ አመለካከት ነው። ልጆች ስለ ጾታ ግንኙነት ትክክለኛ የሆነ ጽንሰ ሐሳብ የላቸውም። የጾታ ግንኙነት ምን ትርጉም እንዳለውና በእነርሱ ላይ ምን ለውጥ እንደሚያመጣ የሚያውቁት ነገር የለም። በመሆኑም ይህን ነገር በራሳቸው ምርጫ ትርጉም ባለው መንገድ ለመፈጸም የሚችሉ አይደሉም። ለድርጊቱ ሙሉ ተጠያቂ የሚሆነው በጾታ ያስነወረው ግለሰብ ነው።—ከሉቃስ 11:11, 12 ጋር አወዳድር።
የተሳሳተ ግንዛቤ:- ልጆች በጾታ እንደተነወሩ በሚናገሩበት ጊዜ ወላጆች ስለተፈጸመው ድርጊት ዳግመኛ እንዳያወሩና ‘ነገሩን እርግፍ አድርገው እንዲተዉት’ ሊያሰለጥኗቸው ይገባል።
ልጆቹ ስለተፈጸመባቸው ወንጀል እንዳይናገሩ ቢደረግ ይበልጥ የሚጠቀመው ማን ነው? በጾታ ያስነወረው ግለሰብ አይደለምን? እንዲያውም ስሜታቸውን አፍነው በመያዝ ድርጊቱ ያስከተለባቸውን የሥነ ልቦና ቀውስ ለመቋቋም የሚያደርጉት ጥረት ብዙም እንደማይሰምርላቸው አንዳንድ ጥናቶች አመልክተዋል። እንግሊዝ ውስጥ በልጅነታቸው የማስነወር ወንጀል በተፈጸመባቸው አዋቂዎች ላይ በተደረገ ጥናት ሰዎቹ የደረሰባቸውን የሥነ ልቦና ቀውስ ለመቋቋም ከተጠቀሙባቸው ዘጠኝ ዓይነት ዘዴዎች መካከል ስሜትን አፍኖ የመያዝንና የመደበቅን ወይም ጉዳዩን ለመርሳት የመሞከርን ዘዴ የተጠቀሙት ሰዎች በጉልምስና የዕድሜ ዘመናቸው ከሁሉ የከፋ የሥነ ልቦና ቀውስና ጭንቀት እንደደረሰባቸው ተረጋግጧል። አሠቃቂ የሆነ ጥቃት ቢደርስብህና ስለደረሰብህ ጥቃት ትንፍሽ እንዳትል ቢነገርህ ደስ ይልሃል? ታዲያ ልጆች ለምን እንዲህ እንዲያደርጉ እንመክራቸዋለን? እንዲህ ዓይነቱ አሠቃቂ ድርጊት እንዲያዝኑ፣ እንዲናደዱና እንዲያለቅሱ ሊያደርጋቸው ስለሚችል ይህን ተፈጥሮአዊ ስሜት እንዲገልጹ በመፍቀድ ከጊዜ በኋላ ከደረሰባቸው የሥነ ልቦና ጉዳት እንዲያገግሙ ልንረዳቸው እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ፍቺን የሚመለከቱ ጉዳዮች በችሎት ፊት በሚታዩበት ጊዜ አንዳንዴ ባልና ሚስቱ በፍርዱ ሂደት ለመርታት ሲሉ ልጄ በጾታ ተነውሯል የሚለውን ክስ መሣሪያ አድርገው ይጠቀማሉ።