የምትፈልገው ምን ዓይነት ዓለም ነው?
አቅምና ችሎታ ቢኖርህ ዛሬ መላውን የሰው ልጅ ቀስፈው የያዙት ችግሮች የማይኖሩበት አዲስ ዓለም ትፈጥር ነበርን? አቅምና ችሎታ ያለው አፍቃሪ ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ይፈጥራል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ አይሆንምን?
መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “ለሰው ሁሉ ቸር ነው፣ ለፍጡሮቹም ሁሉ ይራራል። የሚበቃቸውን ያህል ትሰጣቸዋለህ፣ የሁሉንም ፍላጎት ታረካለህ” ይላል። (መዝሙር 145:9, 16 የ1980 ትርጉም) ታዲያ አንዳንዶቹ ፍላጎቶችህ ምንድን ናቸው? እንዲመጣ የምትናፍቀው ምን ዓይነት ዓለም ነው?
አብርሃምና ሮዝ ፍራንዝብላው ኤ ሴን ኤንድ ሃፒ ላይፍ: ኤ ፋሚሊ ጋይድ በተባለው መጽሐፋቸው “የዓለምን ሕዝቦች አስተያየት ብንጠይቅና ሁላችንም እንዴት ባለ ዓለም መኖር እንደምንፈልግ ሐሳብ እንዲሰጡ ብናደርግ ቢያንስ ቢያንስ ሁላችንም ልንስማማባቸው የምንችልባቸውን ነገሮች መጥቀሳቸው የማይቀር ነው” ሲሉ ጽፈዋል።
እነዚህ ዶክተሮች የዘረዘሯቸውን ፍላጎቶች እንመርምርና ከራሳችን ፍላጎቶች ጋር ይመሳሰሉ እንደሆነና እንዳልሆነ እንይ። እግረ መንገዳችንንም አፍቃሪው ፈጣሪያችን እነዚህኑ ፍላጎቶች ለማሟላት የገባውን ቃል እንመለከታለን።
በአንደኛ ደረጃ የሚፈለግ
ዶክተሮቹ በአንደኛ ደረጃ ያስቀመጡት “ጦርነት የሌለበት ዓለም” ነው። አሰቃቂ የሆኑ በርካታ ጦርነቶችን በማሳለፋቸው ምክንያት ውጊያም ሆነ መገዳደል በሌለበት ዓለም ለመኖር የሚናፍቁ ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው። ይህ ተስፋቸው በኒው ዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አደባባይ በተቀረጸው ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም በሚለው ጽሑፍ ተንጸባርቋል።
እነዚህ ቃላት ይሖዋ አምላክ ከሰጠው ተስፋ የተወሰዱ መሆናቸውን ታውቃለህ? እነዚህ ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢሳይያስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 4 ላይ ተመዝግበው ይገኛሉ። በተጨማሪም መዝሙር 46:8, 9ን ብታነብ የጦር መሣሪያዎችን በሙሉ ማጥፋትና ‘እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን መሻር’ የአምላክ ዓላማ እንደሆነ ትገነዘባለህ። አምላክ የሚያመጣው ጦርነት የሌለበትና ሰላም የሰፈነበት ዓለም በሚከተለው አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኛል። “ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።”—ሚክያስ 4:4
አንተስ ልትኖርበት የምትፈልገው ዓለም ሊያሟላቸው ከሚገቡት ብቃቶች አንዱ “ጦርነት የማይኖርበት ዓለም” መሆን ይኖርበታል አትልም? ታላቁ ፈጣሪያችን እንዲህ ያለው ዓለም እንደሚመጣ ቃል ገብቷል!
ሁሉ ነገር የሚትረፈረፍበት ዓለም
በሁለተኛ ደረጃ የምትፈልገው ምንድን ነው? “ረሐብና ችግር ለዘላለም የማይኖርበት ከችጋር የጸዳ ዓለም” ተብሎ ከተገለጸው ጋር የሚመሳሰል ነው? በረሃብ የጠወለገ ሕፃን ፈጽሞ የማይታይበት ጊዜ ቢመጣ አስደሳች አይሆንም? ሁሉ ነገር በተትረፈረፈበት ዓለም ውስጥ ለመኖር እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለውን ዓለም ማን ሊያመጣልን ይችላል?
አምላክ የሰጠንን የተስፋ ቃል ልብ በል:- “በዚያን ጊዜ ምድር ብዙ ፍሬ ትሰጣለች።” “በምድሩ ላይ በቂ እህል ይኑር።” (መዝሙር 67:6፤ 72:16 የ1980 ትርጉም) አዎን፣ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ምግብ ይትረፈረፋል። ይሖዋ “ታላቅ የሰባ ግብዣ፣ ያረጀ የወይን ጠጅ፣ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፣ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ” እንደሚያደርግ መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጣል።—ኢሳይያስ 25:6
ረሐብ የሌለበት ዓለም ማምጣት ከሰው ልጆች አቅም በላይ ቢሆንም ለአምላክ ግን ከአቅሙ በላይ አይሆንበትም። በአምላክ መንግሥት ሥር ለሁሉ ሰው በቂ ምግብ ማቅረብ አስቸጋሪ እንደማይሆን ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በተግባር አሳይቷል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ጥቂት ዳቦዎችንና ጥቂት ዓሦችን በተአምር አብዝቶ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን መግቧል።—ማቴዎስ 14:14-21፤ 15:32-38
በሽታ የማይኖርበት ዓለም
ሁላችንም ልንኖርበት በምንፈልገው ዓለም የሚታመም ሰው ፈጽሞ አይኖርም። ስለዚህ በሦስተኛ ደረጃ የምንፈልገው ነገር እንግዳ ሊሆንብን አይችልም። ዶክተሮቹ “በሽታ የማይኖርበት ዓለም፣ ሁሉ ሰው በሙሉ ጤንነት አድጎ ሊወገዱና ሊፈወሱ የሚችሉ በሽታዎች ሳያሰቃዩት ዕድሜውን የሚጨርስበት ዓለም መሆን ይኖርበታል” ሲሉ ጽፈዋል።
ማንም ሰው ጉንፋን ወይም ምንም ዓይነት የሚያሰቃይ በሽታ ሳይዘው መኖር ምን ያህል እፎይታ እንደሚያመጣ አስብ! የሰው ልጆች በሽታ ማጥፋት ባይሆንላቸውም ለይሖዋ አምላክ ግን የማይቻል አይደለም። አመጣዋለሁ ብሎ ቃል በገባው አምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖር ማንም ሰው “ታምሜአለሁ አይልም።” ይልቁንም “በዚያ ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፣ የድዳም ምላስ ይዘምራል።” (ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6) አዎን፣ አምላክ “እንባዎችን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኃዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።”—ራእይ 21:4
ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ስፋት ባለው መጠን ይፈጸማል ብለን የምንጠብቀውን ሁኔታ በተግባር አሳይቷል። ለዓይነ ስውራን ብርሃን ሰጥቷል። የደንቆሮችን ጆሮ ከፍቷል፣ የድዳዎች አንደበት እንዲፈታ አድርጓል፣ የሽባዎች ጉልበት እንዲጠናና ቆመው እንዲሄዱ አድርጓል፣ ሙታንን እንኳን ወደ ሕይወት መልሷል።—ማቴዎስ 15:30, 31፤ ሉቃስ 7:21, 22
ሁሉ ሰው አርኪ ሥራና ፍትሕ ያገኛል
አንተም ሆንክ ማንኛውም ሌላ ሰው እንዲመጣ የሚፈልገው ዓለም አርኪ ሥራ የሚገኝበትና ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም መሆን እንደሚገባው አያጠራጥርም። በዚህም ምክንያት ዶክተሮቹ እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “አራተኛ፣ ለራሳቸውም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው የሚያስፈልገውን ሠርተው ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ የሚተዳደሩበት ሥራ የሚያገኙበት ዓለም መሆን ይኖርበታል።” በተጨማሪም “አምስተኛ፣ እያንዳንዱ ሰው በሕግ ጥላ ሥር ሆኖ ነጻነትና ፍትሕ የሚያገኝበት ዓለም መሆን አለበት” ብለዋል።
የሰው ልጅ አገዛዝ እነዚህን ለአስደሳች ኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን አሟልቶ አያውቅም። የአምላክ አዲስ ዓለም ግን እነዚህን ሁሉ ያሟላል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚያ ጊዜ ሰዎች ስለሚሠሯቸው ጠቃሚ ሥራዎች የሚከተለውን ተስፋ ይሰጣል:- “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፣ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። . . . እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና። . . . በከንቱ አይደክሙም።”—ኢሳይያስ 65:21-23
ሰው ሁሉ ነጻነትና ፍትሕ ለማግኘት ስለመቻሉስ? ሰብዓዊ ገዥዎች ምንም ያህል ልባዊ ጥረት ቢያደርጉም እነዚህን ነገሮች ለሁሉም ሰው ማዳረስ አልቻሉም። የፍትሕ መጓደልና ጭቆና በመላው ዓለም እንደ ነገሠ ነው። ስለዚህ የሰው ልጆች ይህን ፍላጎት ፈጽሞ ሊያሟሉ አይችሉም። ሁሉን የሚችለው አምላክ ግን ይህን ማድረግ አይሳነውም። አምላክ የሾመው ገዥ ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ይሖዋ ስለ እርሱ ሲናገር “ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ . . . ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል” ብሏል።—ኢሳይያስ 42:1፤ ማቴዎስ 12:18
አዎን፣ በአምላክ መንግሥት ሥር “ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት” እንደሚደርስ መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጣል። (ሮሜ 8:21) ሰው ሁሉ የተሟላ ነጻነትና ፍትሕ የሚያገኝበት ይህ ዓለም እንዴት ያለ አስደሳች ዓለም ይሆናል!
ምቹ ሁኔታዎችና የረፍት ጊዜ
እንዲመጣ በምትፈልገው ዓለም ውስጥ ዜጎች በሙሉ በዘራቸውና በብሔራቸው ምክንያት አድልዎ ሳይደረግባቸው እኩል የሆነ ምቹ ሁኔታዎች እንዲያገኙ እንደምትፈልግ የተረጋገጠ ነው። በዚህም የተነሳ ዶክተሮቹ ከዘረዘሯቸው የአዲስ ዓለም ብቃቶች ስድስተኛው የሚከተለው መሆኑ አያስደንቅም። “እያንዳንዱ የሰው ዘር ችሎታዎቹንና ክህሎቱን በተሟላ ሁኔታ ለማዳበር የሚያስችለው አጋጣሚ የሚያገኝበትና ምንም ዓይነት አድልዎ ሳይደረግበት ከድካሙ ጋር የሚመጣጠን ዋጋ የሚያገኝበት ዓለም መሆን ይኖርበታል።”
የሰው ልጆች ሁሉም ሰው በእኩልነት የሚታይበት ዓለም ለማቋቋም ችለው አያውቁም። አናሳና ተወዳጅነት በሌላቸው ወገኖች ላይ የሚፈጸመው ግፍና አድልዎ አላንዳች ገደብ ቀጥሏል። የአምላክ አዲስ ዓለም ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን “በፍርድ የማያዳላ፣ መማለጃም የማይቀበለውን” የአባቱን የይሖዋን ምሳሌ ይከተላል። (ዘዳግም 10:17፤ ሮሜ 2:11) መጪውን አዲስ ዓለም ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ሁሉም ሰዎች የይሖዋ አምላክን አድሎአዊ ያለመሆን ባሕርይ እንዲከተሉ የሚያስችላቸውን ትምህርት ከመቀበል አልፈው በሥራ የሚያሳዩ መሆናቸው ነው።—ኢሳይያስ 54:13
የብዙ ሰዎች ሕይወት ፋታ በማይሰጥ ድካምና ልፋት የተዋጠ ነው። ስለዚህ አዲሱ ዓለም ሊያሟላቸው ከሚያስፈልጉት ነገሮች የሚከተለው መኖር እንዳለበት እንደምትስማማ የተረጋገጠ ነው። “ሰባተኛ፣ ሁሉ ሰው ደስታ ያስገኛሉ በሚላቸው ነገሮች ለመደሰት የሚያስችለው በቂ የረፍት ጊዜ የሚያገኝበት ዓለም ይሆናል።”
ይሖዋ አምላክ የሰው ልጅ ዕረፍት ማግኘትና መዝናናት እንደሚያስፈልገው ስለሚያውቅ በጥንታዊ ሕጉ ውስጥ ሳምንታዊ የዕረፍት ቀን እንዲኖር አድርጓል። (ዘጸአት 20:8-11) ስለዚህ በአዲሱ ዓለም ውስጥም አምላክ ዕረፍት የማግኘትና ጤናማ በሆኑ መዝናኛዎች የመደሰት ፍላጎታችን እንዲሟላልን እንደሚያደርግ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
በዚያ የሚኖሩት ሰዎች
ዶክተሮቹ ከዘረዘሯቸው አስፈላጊ ነገሮች መካከል የመጨረሻው “ሁላችንም ልንኖር በምንፈልገው ዓለም ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች” ሊያሳዩት የሚገባውን ባሕርይ የሚገልጽ ነው። የዘረዘሯቸው ባሕርያት አስፈላጊ ስለመሆናቸው ትስማማና አትስማማ እንደሆነ ተመልከት። “ስምንተኛ፣ እንደ ብልህነትና የፈጠራ ችሎታ፣ እንደ ክብርና ፍጹም አቋም ጠባቂነት፣ እንደ ፍቅርና ታማኝነት፣ የራስን ክብር እንደመጠበቅና ራስ ወዳድ አለመሆን፣ ለሌሎች ሰዎች አሳቢ እንደመሆን ላሉት ሰውን ከእንስሳት ልዩ የሚያደርጉ ባሕርያት ከፍተኛ ግምት የሚሰጥበት ዓለም መሆን አለበት።”
ሁሉ ሰው ፍጹም አቋም ጠባቂነትን፣ ፍቅርን፣ ታማኝነትን፣ ራስ ወዳድ አለመሆንንና ለሌሎች ሰዎች አሳቢ የመሆንን ባሕርይ በሚያንጸባርቅበት ዓለም ብትኖር አትደሰትም? አንተም የምትፈልገው እንዲህ ያለውን ዓለም እንደሚሆን አያጠራጥርም! እንዲህ ያለውን ዓለም ሊያስገኝ የሚችል ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ገዥ የለም። ይህን ማድረግ የሚችለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። ቃል የተገባልን እንዲህ ያለው የአዲስ ዓለም ተስፋ እውን ሊሆን የማይችል የሕልም እንጀራ ስላልሆነ መፈጸሙ አይቀርም።—መዝሙር 85:10, 11
የሚመጣው መቼ ነው?
ባለፈው ርዕስ እንደተመለከተው አንድ የኢየሱስ የቅርብ ባልደረባ የነበረ “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ [እንደ አምላክ ቃል] እንጠብቃለን” ሲል ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ይህ ተስፋ የሚፈጸመው ኢየሱስ እንዳመለከተው “በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ” ነው።—ማቴዎስ 19:28
አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት፣ አዳምንና ሔዋንን ይኖሩበት የነበረውን የገነት አትክልት እንዲያሰፉ አዝዟቸው ነበር። ልጆችን እንዲወልዱና ከልጆቻቸው ጋር ሆነው ምድርን በሙሉ እንደ ኤደን ገነት እንዲያስውቡ ፈልጎ ነበር። (ዘፍጥረት 1:26-28፤ 2:7-9, 15) አዳምና ሔዋን ይህን የአምላክ ዓላማ ለመፈጸም ባይችሉም ክርስቶስ በመንግሥት በሚገዛበት ዳግመኛ ልደት ወቅት ምድር እንደገና ገነት ትሆናለች። በኤደን የነበረው ሁኔታ ቀስ በቀስ ተስፋፍቶ በመላዋ ምድር ላይ ይሰፍናል። በዚህ መንገድ አፍቃሪው ፈጣሪያችን ሰላምና ጽድቅ የሰፈነበት ዓለም ለማስገኘት የነበረው የቀድሞ ዓላማ ይፈጸማል። ግን ይህ የሚሆነው መቼ ነው?
ብዙ ሰዎች ‘አዎን፣ መምጣቱ አይቀርም፣ ግን በእኛ ዕድሜ የሚሆን ነገር አይደለም’ ብለው እንደሚናገሩት የአንተም አስተሳሰብ እንደዚሁ ዓይነት ነው? እንዴት ማወቅ ትችላለህ? ዘመናችን ተወዳዳሪ በማይገኝለት ጭንቀት የተዋጠ መሆኑ የአምላክ አዲስ ዓለም ቅርብ ለመሆኑ ምልክት ሊሆን ይችላል? እንዴት ማወቅ እንችላለን?
[ምንጭ]
Cubs: Courtesy of Hartebeespoortdam Snake and Animal Park
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሰላም፣ ፍጹም ጤንነትና ብልጽግና ይኖራል
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሰዎች ውጤታማ ሥራ ይሠራሉ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለመዝናናት በቂ ጊዜ ይኖራል