አዲሱ ዓለም የሚመጣው መቼ ነው?
የአምላክ አዲስ ዓለም የሚመጣው ይህ አሁን ያለው ዓለም ካለፈ በኋላ ነው። ይሁን እንጂ ‘በእርግጥ ይህ ዓለም ይጠፋል ብለን ልናምን እንችላለን?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ከአሁን በፊት የጠፋ ዓለም ነበር? ብለን እንጠይቅ።
አዎን፣ ከዚህ በፊት የጠፋ ዓለም እንደነበር የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ “ያን ጊዜ [በኖህ ዘመን] የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ” ይላል። አምላክ “ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ” ከማውረድ ወደ ኋላ አላለም።—2 ጴጥሮስ 2:5፤ 3:6
በዚያ ጊዜ የጠፋው “የኃጢአተኞች ዓለም” ወይም ክፉ የነገሮች ሥርዓት እንደነበረ ልብ በል። ግዑዟ ምድር፣ ከዋክብት የሚታዩበት ጠፈር ወይም ሰብዓዊው ቤተሰብ አልጠፋም። ከጥፋቱ ውኃ የተረፉት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ሌላ ዓለም (አሁን ያለው የእኛ ዓለም) ተገኘ። ይህስ ዓለም ምን ይሆናል?
መጽሐፍ ቅዱስ በኖህ ዘመን የነበረው ዓለም እንደጠፋ ከተናገረ በኋላ “አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከ ሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል” ይላል። (2 ጴጥሮስ 3:7) እሳት የዓለም ጥፋትን ያመለክታል። በእርግጥ “[ይህ የዛሬው] ዓለም ያልፋል።” (1 ዮሐንስ 2:17) ግን መቼ?
የኢየሱስ ሐዋርያት ስለዚህ ጉዳይ ማወቅ ፈልገው ስለነበረ “ንገረን፣ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት።” (ማቴዎስ 24:3) ኢየሱስ በሰጠው መልስ ትንቢቶቹ በሚፈጸሙበት ጊዜ የሚኖሩ ሰዎች አንድ ዓለም የሚጠፋበትና በቦታው አዲስ ዓለም የሚተካበት ጊዜ መቅረቡን ሊያውቁ የሚችሉበትን ምልክት ነገራቸው። ታዲያ ምልክቱ ምን ነበር?
ምልክቱ
ምልክቱ ብዙ ክፍሎች ያሉት፣ አዎን፣ ብዙ ክስተቶች የተተነበዩበት ነው። ምልክቱ ተፈጽሟል ሊባል የሚችለው እነዚህ ነገሮች በሙሉ በአንድ ወቅት፣ በአንድ ትውልድ ዘመን ለሁሉ ሰው ግልጽ በሆነ መንገድ ሲፈጸሙ ነው። (ማቴዎስ 24:34) ታዲያ እነዚህ ክስተቶች ምንድን ናቸው?
ኢየሱስ ከዘረዘራቸው መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ:- “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል።” “በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፣ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። . . . ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች።”—ሉቃስ 21:10, 11፤ ማቴዎስ 24:7-9, 12
ሐዋርያው ጳውሎስም የዚህ ዓለም “መጨረሻ ቀን” ምልክት የሚሆኑ ሌሎች ሁኔታዎች ገልጿል። እንዲህ ሲል ጻፈ:- “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ . . . ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ . . . ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
እነዚህ ነገሮች በሙሉ ሲፈጸሙ እንዳየህ ወይም እንደሰማህ የተረጋገጠ ነው። የቀድሞዎቹን ጦርነቶች ያልነበሩ የሚያስመስሉ ዓለም አቀፋዊ ጦርነቶች፣ ታላላቅ የምድር መንቀጥቀጦች፣ በስፋት የተዛመተ ቸነፈርና የምግብ እጥረት፣ የክርስቶስ ተከታዮች መጠላትና መሰደድ፣ የሕገወጥነት መብዛት፣ ወደር ያልተገኘለት አስጨናቂ ዘመን ታይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ከእነዚህ ነገሮች በተጨማሪ አምላክ ‘ምድርን የሚያበላሹትን እንደሚያጠፋ’ ተንብዮአል። (ራእይ 11:18) የሰው ልጆች በአሁኑ ጊዜ ምድርን እያበላሹ ነው።
በኅዳር ወር 1992 ጋዜጦች “ታዋቂ ሳይንቲስቶች ምድር ልትጠፋ ነው እያሉ ያስጠነቅቃሉ” የሚልና የመሳሰሉ የዜና አምዶችን አውጥተዋል። የኖቤል ተሸላሚና ሥጋት ያደረባቸው ሳይንቲስቶች ኅብረት ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር ሄንሪ ከንዳል “ማስጠንቀቂያው የተጋነነ ወይም ሰዎችን ለማስደንገጥ ብቻ የተነገረ አይደለም” ብለዋል። አንድ ጋዜጣ “ማስጠንቀቂያውን ያረቀቁት 1,575 የሚያክሉ ሳይንቲስቶች ስም ዝርዝር ከዓለም አቀፉ የሳይንስ ማኅበረሰብ የተውጣጡ ታዋቂ የሆኑ ሳይንቲስቶችን ያካተተ ነበር” ሲል ዘግቧል። ምድራችን ፈጽማ ልትጠፋ እንደምትችል የሰጡት ማስጠንቀቂያ ቸል ሊባል የማይችል ነው!
ጉዳዩ ምንም የሚያጠያይቅ አይደለም። ሁሉም የምልክቱ ክፍሎች፣ ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው” አዎን፣ የዚህ ዓለም መጨረሻ “ይመጣል” ሲል የተናገረው ቁልፍ ትንቢት ጭምር በመፈጸም ላይ ነው። (ማቴዎስ 24:14) የአምላክ መንግሥት ምሥራች በመላው ዓለም ከተሰበከ በኋላ መጨረሻው እንደሚመጣ ኢየሱስ ተናግሯል። ይህ የስብከት ሥራ በትንቢት በተነገረው መጠንና ስፋት በይሖዋ ምሥክሮች እየተሰበከ ነው።
ምን ማድረግ ይገባሃል?
እነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች የአምላክ አዲስ ዓለም በጣም ቅርብ መሆኑን ያመለክታሉ። ከዚህ ዓለም ፍጻሜ ለመዳንና በአዲሱ ዓለም ውስጥ በሕይወት ለመኖር የምትፈልግ ከሆነ ማድረግ የሚያስፈልግህ አንድ ነገር አለ። መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለም ያልፋል” ካለ በኋላ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት ካንተ የሚፈለገውን ነገር ይገልጻል።—1 ዮሐንስ 2:17
ስለዚህ የአምላክን ፈቃድ አውቀህ በተግባር ላይ ማዋል ያስፈልግሃል። የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ ደስ እያላቸው ይረዱሃል። በዚህ መንገድ ከዚህ ዓለም ፍጻሜ ልትድንና የአምላክ አዲስ ዓለም በሚያስገኛቸው በረከቶች ለዘላለም ልትደሰት ትችላለህ።
[ምንጭ]
NASA photo
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አዲሱ ዓለም ከመምጣቱ በፊት ከዚህ በፊት ሆኖ የማያውቅ ታላቅ የመከራ ጊዜ ይሆናል