የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g96 1/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ስለ አርማጌዶን የተሰጡ አስተያየቶች
  • ሃይማኖትና ከበሽታ መዳን
  • እጅን በሚገባ መታጠብ
  • ቫቲካንን የገጠማት “እርስ በርሱ የሚቃረን ጉዳይ”
  • የሥነ ልቦና ችግር ያጋጠማቸው ቀሳውስት
  • በአእምሮ በሽታ የተለከፉ ልጆች
  • ዕድሜና አመጋገብ
  • የምግብ እጥረት እንደሚኖር ይጠበቃል
  • በፖሊዮ ላይ በከፊል የተገኘ ድል
  • ከመጠን በላይ መጠጣት ምን ስሕተት አለው?
    ንቁ!—2004
  • ከመጠን በላይ መጠጣት ምን ችግር አለው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1
  • እጅን ታጥቦ ማድረቅ!
    ንቁ!—1999
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—1998
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1996
g96 1/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

ስለ አርማጌዶን የተሰጡ አስተያየቶች

የኦም ሺንሪክዮ ሃይማኖት በመጋቢት ወር በቶኪዮ የምድር ውስጥ የባቡር መጓጓዣ ገዳይ የሆነውን የሳሪን ጋዝ በመልቀቅ በበርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት ካደረሰ ወዲህ በጃፓን የሚገኙ ሃይማኖቶች ስለ አርማጌዶን ያላቸውን አመለካከት ለመግለጽ ተገፋፍተዋል። ዘ ዴይሊ ዮሚዩሪ እንደዘገበው “የሃይማኖታዊው ቡድን መሪ የሆኑት ሾኮ አሳሃራ ለበርካታ ዓመታት . . . ዓለም አርማጌዶንን ማየቱ እንደማይቀር ሲተነብዩ ቆይተዋል።” ምንም እንኳ የኦም እምነት ከቡድሂስት እምነት ጋር የሚመሳሰል ቢሆንም ሁለት የቡድሂዝም ድርጅቶች “ስለ አርማጌዶን የሚገልጸው ጽንሰ ሐሳብ በቡድሂዝም እምነት ውስጥ ፈጽሞ አይታወቅም” ብለዋል ሲል ሜይኒቺ ዴይሊ ኒውስ ዘግቧል። “ሁለቱ ዋነኛ የክርስትና ሃይማኖት ዘርፎች . . . አርማጌዶን ቀርቧል የሚለውን የኦም እምነት እንደማይቀበሉ ገልጸዋል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይህ እምነት በካቶሊኮች ዘንድ ፈጽሞ የማይታወቅ እንደሆነ ሲገልጽ የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን የኦም ሺንሪክዮ ሃይማኖት ‘አርማጌዶን’ ለሚለው ቃል ‘ከመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም ውጭ የሆነ ትርጉም ስለ ሰጠው’ በዚህ ቃል መጠቀም አይገባውም ነበር ብሏል። የዩኒፊኬሽን ቤተ ክርስቲያን ‘ፍርሃት የሚያነሳሱ የሃይማኖት ማሰራጫ ዘዴዎች ተፈላጊዎች አይደሉም’ ብሏል። ሺንዮኤን የተባለው ሃይማኖታዊ ቡድን ደግሞ አንዳንድ አመለካከቶች ከመጠን በላይ ከተጋነኑ ሰዎች ከመጠን ያለፈ ፍርሃት ይሰማቸዋል የሚል አስተያየት ሰጥቷል።” የኦም መሥራች የሆኑት ግለሰብም ቢሆኑ የራሳቸውን ትንቢት እውነተኝነት የተጠራጠሩ ይመስላል። ከዚህ ሃይማኖታዊ ቡድን ዋነኛ መሪዎች አንዱ “የሳሪን ፕሮጀክት ሥራ ላይ እንዲውል የተደረገው የመሪያችን ትንቢት እንዲፈጸም ለማድረግ ይመስለኛል” ብለዋል።

ሃይማኖትና ከበሽታ መዳን

የልብ ቀዶ ጥገና በተደረገላቸው 232 የሚያክሉ አረጋውያን በሽተኞች ላይ የተደረገ ጥናት “ከሃይማኖታዊ አመለካከታቸው ብርታትና መጽናኛ ለማግኘት የቻሉ በሽተኞች ከበሽታቸው ለማገገም ያላቸው አቅም ከሃይማኖታዊ እምነታቸው ምንም ዓይነት ማጽናኛ ካላገኙ በሽተኞች በሦስት እጥፍ እንደሚበልጥ” የፓሪስ ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪብዩን ገልጿል። ቀደም ሲል የተደረጉ ጥናቶች ከወዳጆችና ከቤተሰቦች ጋር የተቀራረበ ዝምድና መኖሩና የእነርሱንም እርዳታና ድጋፍ ማግኘት በጤንነት ረገድ ጠቀሜታ እንዳለው ያረጋገጡ ቢሆንም “ከባድ በሽታ የያዛቸው ሰዎች ሃይማኖታዊ እምነታቸው ጤንነታቸውን የሚያጎለብትላቸው ጥቅም ሊያስገኝላቸው እንደሚችል ያረጋገጠ ጥናት ሲደረግ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ” መሆኑን ትሪብዩን አረጋግጧል። የጥናቱ ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ቶማስ ኦክስማን እንደሚከተለው ብለዋል:- “አስጊ ለሆነና ሕይወትን አደጋ ላይ ለሚጥል ሁኔታ ትርጉም መስጠት መቻል እንዲሁም ከሰው በላይ የሆነ ኃይል መኖሩን ማመን ለጤና ይጠቅማል።”

እጅን በሚገባ መታጠብ

ዶክተሮች አዘውትሮ እጅ መታጠብ “ለጉንፋን፣ ለኢንፍሉዌንዛ፣ ለጉሮሮ ቁስለት፣ ለሆድ ዕቃ መታወክና በጣም ከባድ ለሆኑ ሌሎች በሽታዎች ምክንያት የሚሆኑትን ጀርሞችና ቫይረሶች ለማስወገድ ይረዳል” እንደሚሉ ዘ ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል። ይኸው ጋዜጣ “የሞንትሪያል ኤፒደሚዮሎጂስት የሆኑት ዶክተር ጁልዮ ሶቶ ያደረጉት ጥናት እጆችን በሚገባ መታጠብ በባክቴሪያዎችና በቫይረሶች የሚዛመቱ በሽታዎችን ስርጭት በእጅጉ እንደሚቀንስ፣ የላይኛውን የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ስርጭት 54 በመቶ፣ የተቅማጥ በሽታዎችን ስርጭት 72 በመቶ እንደሚቀንስ ያረጋገጠ” መሆኑን ገልጿል። የካናዳ የሕፃናት ሐኪሞች ማኅበር እጅን በሚገባ መታጠብ እጆችን ከቧንቧ በሚፈስ ውኃ ማርጠብን፣ ከአንድ እስከ 30 ቆጥረህ እስክትጨርስ ድረስ እጆችህን በሳሙና ማሸትን፣ ከአንድ እስከ 5 ቆጥረህ እስክትጨርስ ድረስ እጆችህን እያሸህ ከቧንቧ በሚፈስ ውኃ ማለቅለቅንና በመጨረሻም ሌላ ሰው ባልተጠቀመበት ንጹሕ ፎጣ ወይም ወረቀት እንደ ናብኪን ባሉ ማድረቂያዎች አለዚያም ደግሞ በእጅ በማይነካ የማድረቂያ መሣሪያ ማድረቅን ይጠይቃል። በተለይ በምግብ ቤቶችና፣ ምግብ በሚዘጋጅባቸው ሌሎች ቦታዎች የሚሠሩ ሰዎች እንዲሁም እንደ ሳምቡሳ ያሉ ቀለል ያሉ ምግቦችን እያዘጋጁ የሚሸጡ ሰዎች እጃቸውን በሚገባ መታጠብ እንዳለባቸው ፈጽሞ መዘንጋት አይገባቸውም።

ቫቲካንን የገጠማት “እርስ በርሱ የሚቃረን ጉዳይ”

ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከሮማ ቀሳውስት ጋር በሚያደርጉት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ አንድ ቄስ ሊቀ ጳጳሱን “ቅዱስነትዎ፣ ቫቲካን እስከ አሁን ድረስ ሲጋራ የምትሸጠው ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል። ቄሱ ጥያቄያቸውን በመቀጠል “ይህ ንግድ ጤንነት የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ ራስዎ ለጤንነታችንና ለእረኝነት ሥራችን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንድናደርግ የሚሰጡትን ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ይቃረናል” ብለዋል። ኡጎ ሚሲኒ ለተባሉት ለእኚህ የ76 ዓመት ቄስ ቫቲካን “ማጨስ ጤንነት ይጎዳል” የሚል ጽሑፍ የሰፈረበት ትንባሆና ሲጋራ መሸጥዋ የሊቀ ጳጳሱን መልእክት “የሚቃረን” እና “የሚያስተባብል” ድርጊት ሆኖ ታይቷቸዋል። ኢል መሳጀሪዮ የተባለው የሮም ጋዜጣ እንደዘገበው ሊቀ ጳጳሱ በትንባሆ ረገድ “ሕሊናዬ ንጹሕ ነው” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል። ቢሆንም ቫቲካን ስለምታካሂደው የሲጋራ ሽያጭ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ካርዲናል ጋር እንደሚነጋገሩበት ቃል ገብተዋል።

የሥነ ልቦና ችግር ያጋጠማቸው ቀሳውስት

በጣም እውቅ ከሆኑ የኢጣሊያ ካቶሊክ የሥነ ልቦና ሊቃውንት አንዱ ቫሌርዮ አልቢዜቲ “የሥነ ልቦና ችግር አጋጥሟቸው እኔ ጋ ለሕክምና ከሚመጡት ቀሳውስት መካከል ሃምሳ በመቶ የሚሆኑት ጾታ ነክ ችግር ያለባቸው ናቸው” ብለው መግለጻቸውን ላ ሪፑብሊካ ሪፖርት አድርጓል። በብህትውና የመኖር ግዴታ እንዳለባቸው በቅርቡ ሊቀ ጳጳስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በድጋሚ ያረጋገጡላቸው እነዚህ ሰዎች ከማንኛውም ነገር በላይ የሚያሠቃያቸው ወሲባዊ ስሜታቸውና አባት የመሆን ፍላጎታቸው ነው። አልቢዜቲ ወንዶች በዕድሜ ከገፉ በኋላ ወደ ቅስና ሕይወት እንዲገቡና ወደ መንፈሳዊ ኮሌጆች መግባት የሚቻልበት ዕድሜም ከፍ እንዲል ቢደረግ ጥሩ እንደሚሆን ሐሳብ ሰጥተዋል። “ቄስ የሚሆን ሰው” የጉርምስና ዕድሜውን “ሴቶች በሌሉበት አካባቢ ማሳለፉ በአእምሮ ጤንነቱና በሥነ ልቦናዊ ሚዛኑ ላይ ጉዳት ያስከትላል” ብለዋል። አልቢዜቲ እንደሚሉት “የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ብዙ ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት፣ አንድን ነገር ከመጠን በላይ ከመፈለግ የሚመጣ የአእምሮ መታወክና ከመጠን ያለፈ የምግብ ፍላጎት መጨመር ያስቸግራቸዋል።”

በአእምሮ በሽታ የተለከፉ ልጆች

ዘ ሰንደይ ታይምስ እንዳለው በታላቋ ብሪታንያ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ከ1,000 የሚልቁ ልጆች እንዲሁም ከ10 እስከ 14 ዓመት የሆናቸው 1,200 የሚሆኑ ልጆች የአእምሮ ቀውስ፣ ከባድ የሆነ የመንፈስ ጭንቀት ወይም የምግብ ፍላጎት መዛባት ስላጋጠማቸው ሕክምና እየተሰጣቸው ነው። ራሳቸውን የሚገድሉ ልጆች ቁጥርም እንደዚሁ እያደገ መጥቷል። ዕድሜያቸው ከስድስት ዓመት የማይበልጡ ልጆች እንኳን የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት እየቃጡ ነው። አንዳንድ የአእምሮ ጤንነት ጠበብት ለዚህ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ በልጆችና በወላጆች መካከል ልባዊ ጭውውት አለመኖሩ እንደሆነ ያስባሉ። ጠበብቱ ብዙ ልጆች ለቴሌቪዥን ከፍተኛ ትኩረት በሚሰጥባቸው ቤቶች ውስጥ እንደሚኖሩ አስተውለዋል። በዚህም ምክንያት ልጆች የሚያስጨንቋቸውን ነገሮች ከወላጆቻቸው ጋር ለመወያየት ሳይችሉ ይቀራሉ። አንድ ጠበብት በወላጆችና በልጆች መካከል “የሐሳብ ግንኙነት አለመኖሩ ጭንቀትና ውጥረት እያደገ እንዲሄድና ሕፃኑ ሐዘንተኛ እንዲሆን እንደሚያደርግ” ገልጸዋል።

ዕድሜና አመጋገብ

በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ተመራማሪዎች ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው ሰዎች ከዕድሜያቸው ጋር የመጣባቸው ተጨማሪ ክብደት ሊያሳስባቸው እንደማይገባ የለንደኑ ዘ ታይምስ ሪፖርት አድርጓል። ለምሳሌ ያህል የሸማቾች ማኅበር መጽሔት አዘጋጅ የሆኑት ዴቪድ ዲክንሰን እንደሚከተለው ብለዋል:- “ከቁመቱ ጋር የማይመጣጠን ክብደት ያለው ሁሉ ከመጠን በላይ ወፍራም ስለሆነ ክብደቱን መቀነስ ይኖርበታል የሚለው ምክር ስህተት ነው። ክብደታችሁ ከቁመታችሁ ጋር የሚመጣጠን ቢሆንም እንኳን መክሳታችሁ በጤንነታችሁ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው አብዛኞቹ ሰዎች መክሳት አያስፈልጋቸውም።” የሥርዓተ ምግብና የአመጋገብ ፕሮፌሰር የሆኑት ቶም ሳንደርስ “ውፍረት በጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከመጠን በላይ ተጋኗል። ውፍረት በስኳርና በአርትራይትስ በሽታዎች የመያዝን አጋጣሚ ከፍ የሚያደርግ ቢሆንም በጤንነት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከግምት ውስጥ የሚገባ አይደለም። እንዲያውም ለሴቶች ጠቃሚ ሊሆን ይችላል” ብለዋል። የጤና ጥበቃ መሥሪያ ቤት ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ማርቲን ዋይዝማን እንደሚከተለው በማለት መክረዋል:- “በማንኛውም ዕድሜ በጣም ወፍራም መሆንም ሆነ በጣም ቀጭን መሆን ጥሩ አይደለም። ትክክለኛ ውፍረት ይዞ መኖር የሚቻለው ልከኛ የሆነ አመጋገብ በመከተልና አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ነው። ዕድሜአችን እየገፋ ሲሄድ ግን ከሲታ ከመሆን ወፍራም መሆን የተሻለ ይሆናል።”

የምግብ እጥረት እንደሚኖር ይጠበቃል

የልማት ጠበብትና የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚደንት የሆኑት ግብጻዊው እስማኤል ሰራገልዲን “ቴክኖሎጂውን ለማሻሻል ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ካልተመደበ በጣም አስከፊ የሆነ ችግር ከፊታችን ይጠብቀናል” ብለዋል። ይህን የተናገሩት የመሠረታዊ ምግቦችን ምርት ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ሲገልጹ ነበር። በአሁኑ ጊዜ እንኳን ያለው የመሠረታዊ ምግቦች አቅርቦት ፈጣን የሕዝብ እድገት ለሚታይባቸው ለእስያና ለአፍሪካ አህጉሮች ከሚያስፈልገው ጋር ሊጣጣም አልቻለም። “ምንም ብናደርግ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት የዓለም ሕዝብ ብዛት በሁለት ቢልዮን ይጨምራል። ከዚህ መካከል 95 በመቶ የሚሆነው ጭማሪ የሚከሰተው በድህነት በጣም በተጠቁት አገሮች ነው” ብለዋል። ባለፉት 25 ዓመታት የመሠረታዊ ምግቦች ምርት አስደናቂ በሆነ መጠን ቢጨምርም በአካባቢያዊና በባዮሎጂያዊ ችግሮች ምክንያት ተጨማሪ የምርት እድገት ማግኘት በጣም አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። በተጨማሪም ተባዮችና የዕፀዋት በሽታዎች በጣም ማየላቸውና የመሬትም ለምነት እየቀነሰ በመምጣቱ የምርት ጭማሪ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል። ወርልድ ዎች ኢንስቲትዩት ይህንን ሲያጠናክር እንዲህ ብሏል:- “የሚጠመዱ ዓሣዎች እያነሱ መሄዳቸው፣ የወንዞችና የሐይቆች ጥልቀት እየቀነሰ መሄዱ፣ የአእዋፍ ብዛት መመናመኑ፣ የሙቀት መጠን መጨመሩና የምግብ ክምችት እያሽቆለቆለ መምጣቱ “ዓለም የምድር አካባቢያዊ ሚዛን ሊሸከም በማይችለው የኢኮኖሚ ጎዳና ላይ የምትገኝ መሆንዋን ያሳያል። እነዚህ ዓለምን ካጋጠሟት ችግሮች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።” ድርጅቱ ይህን የገለጸው ስቴት ኦቭ ዘ ወርልድ 1995 በተባለ ሪፖርቱ ላይ ነው።

በፖሊዮ ላይ በከፊል የተገኘ ድል

አብዛኛውን ጊዜ ፖሊዮ ተብሎ የሚጠራው የልጅነት ልምሻ በታሪክ ዘመናት ውስጥ ከ10 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎችን እንደገደለ ወይም አካለ ስንኩል እንዳደረገ ይነገራል። በሽታው የሚያስከትለው ጠንቅ በግብጽ፣ በግሪክና በሮም በተገኙ የጥንት ዘመን ቅርጾች ላይ ተስሎ ይገኛል። አብዛኛውን ጊዜ ሕፃናትን የሚያጠቃው ይህ በሽታ አንዳንድ የአካል ክፍሎች ኦክስጅን እንዳይደርሳቸው ስለሚያደርግ ለሞት ወይም ለሽባነት ምክንያት ይሆናል። አሁን ግን የዓለም ጤና ድርጅት ቅርንጫፍ የሆነው የፓን አሜሪካ ጤና ድርጅት ፖሊዮ ከምዕራባዊው ንፍቀ ክበብ ፈጽሞ የተወገደ መሆኑን ሪፖርት አድርጓል። ለመጨረሻ ጊዜ በፖሊዮ በሽታ የተያዘ ሰው ሪፖርት የተደረገው በ1991 ሲሆን እርሱም አንድ እግሩ ሽባ ሆኖ በሕይወት የተረፈ የፔሩ ሕፃን ነው። ይሁን እንጂ ፖሊዮ በ1977 ከመላው ዓለም እንደተወገደው የፈንጣጣ በሽታ ፈጽሞ ከዓለም ገጽ አልጠፋም። የፖሊዮ ቫይረስ የሚገኝባቸው አካባቢዎች ስላሉ ከእነዚህ አካባቢዎች በሚመጡ ሰዎች አማካኝነት ወደ አሜሪካ አህጉራት ተመልሶ ሊገባ ይችላል። ለመጨረሻ ጊዜ በቀረበው የተሟላ ሪፖርት በአንድ ዓመት ውስጥ በፖሊዮ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 10,000 ነበር። ይህ በሽታ ሙሉ በሙሉ ድል እስኪነሳ ድረስ ክትባት መስጠት እንደሚያስፈልግ የጤና ጠበብቶች ይናገራሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ