የጦርነት ትዝታዎች ሳይጠፉ ለሰላም የቀረቡ ጸሎቶች
ዳግማዊ ፖፕ ጆን ፖል ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ቡድኖችን ያቀፈ ሰፊ ጉባኤ ኅዳር 1994 ቫቲካን ውስጥ ጠርተው ነበር። የጉባኤው ዋነኛ ዓላማ ለዓለም ሰላም ጸሎት ማቅረብ ነበር። ጳጳሱ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ “ከዚህ በፊትም ይሁን በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት ግጭቶች ቢካሄዱም በሃይማኖትና በሰላም መካከል ያለውን ዝምድና ማሳወቁ የጋራ ኃላፊነታችንና ተግባራችን ነው” ብለዋል።
የሚገርመው ግን የዚህ ዓለም ሃይማኖቶች በዚህ ረገድ ያተረፉት ስም መጥፎ ነው። የስብሰባው ዋና ጸሐፊ የሆኑት ዊሊያም ቬንድሊ “ሃይማኖት በተለያዩ የምድር ክፍሎች በሚደረጉ ግጭቶች ውስጥ ተዘፍቋል” በማለት አስታውቀዋል። የሮማ ካቶሊክ እምነት ገንኖ በሚታይባት ሩዋንዳ የተፈጸሙትን ጭፍጨፋዎች ተመልከት።
ዳግማዊ ፖፕ ጆን ፖል ግንቦት 1994 ስለ ሩዋንዳ እልቂት ሲናገሩ “ካቶሊኮች እንኳ ሳይቀሩ በኃላፊነት የሚጠየቁበት የለየለትና እውነተኛ የሆነ የዘር ማጥፋት ዘመቻ” ነበር ብለዋል። የካቶሊኮች በጭፍጨፋው መካፈል ሰዎች በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ያላቸውን እምነት ነክቶባቸዋልን? የቤልጅየም ተወላጅ የሆኑት ኢየሱሳዊ አንድሬ ብዊዮ “ጭፍጨፋው የብዙዎቹን ሰዎች እምነት አናግቷል” ብለዋል። እንደዚህ ያሉበት ጥሩ ምክንያት አላቸው።
በማያሚ ሄራልድ ላይ በወጣው የሮይተር ሪፖርት መሠረት “በዘር ማጥፋት ክስ ፍርድ ከሚጠብቁት 40,000 ሁቱ እስረኞች መካከል ቀሳውስት፣ የቤተ ክርስቲያን ሰባኪዎችና ሴት መነኩሴዎች ይገኙበታል።” ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንዲህ በማለት ሪፖርት አድርጓል:- “አያሌ ሩዋንዳውያን ጳጳሶቻቸውና አቡኖቻቸው ጭፍጨፋውን ቶሎ ብለው ወይም ጠንከር አድርገው እንዳላወገዙና የነፍሰ ገዳይ ቡድኖችን ያሠለጥን ከነበረው የሃብያሪማና መንግሥት ጋር የቅርብ ትስስር እንደነበራቸው ይናገራሉ። አዲሱ ቱትሲ መራሽ መንግሥት በጭፍጨፋው ውስጥ እጃቸውን አስገብተዋል ተብለው የተወነጀሉ ቢያንስ አንድ ቄስ ይዟል።” ታይምስ መጽሔት በመቀጠል እንዲህ አለ:- “አዲሱ መንግሥት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቀድሞ የነበራት ዓይነት ኃይል እንዲኖራት ካለመፈለጉም በላይ ሐሳባቸውን በግልጽ የሚናገሩ እንዲሁም በራሳቸው የሚመሩ ቄሶችን ወታደሮች ማንገላታታቸውና እናስራችኋለን እያሉ መዛታቸው” አያስደንቅም።
የደም ዕዳ ያለባቸው ሃይማኖተኞች ሰላም እንዲመጣ የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሖዋ አምላክ እንዴት ይመለከተዋል? ኢሳይያስ 1:15 “እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፣ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል” በማለት መልሱን ይሰጠናል።
ይህ ሁሉ ሲፈጸም እውነተኞቹ የይሖዋ አገልጋዮች ‘የዓለም ክፍል አልሆኑም፣’ በግጭቶቹም አልተካፈሉም። በሩዋንዳ ጭፍጨፋ በሚካሄድበት ወቅት የሌላው ጎሣ አባላት የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ችግር ላይ የወደቀው ጎሣ አባላት የሆኑትን ምሥክሮች ለማዳን የራሳቸውን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለው ቤታቸው ውስጥ ደብቀዋቸዋል። በዓለም ዙሪያ ከሁሉም ጎሣዎች የተውጣጡት “እጅግ ብዙ ሰዎች” የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ ከመጸለያቸውም በላይ እውነተኛ ሰላምና ደህንነት የሚመጣው በዚህ መንግሥት አማካኝነት ብቻ እንደሆነ በግልጽ ያውጃሉ።— ዮሐንስ 17:14፤ ራእይ 7:9፤ ማቴዎስ 6:9, 10፤ 24:14
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Luc Delahaye/Sipa press