የሳንባ ነቀርሳ አገርሽቷል!
ከ1950ዎቹ ዓመታት ወዲህ በዩናይትድ ስቴትስ በሳንባ ነቀርሳ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በየዓመቱ 5 በመቶ ሲቀንስ ቆይቶ ነበር። ከ1985 ወዲህ ግን የሳንባ ነቀርሳ በሽተኞች ቁጥር 18 በመቶ አድጓል። ከዚህ ይበልጥ አሳሳቢ ሆኖ የተገኘው ደግሞ መድኃኒት የማይበግረው አዲስ የሳንባ ነቀርሳ ዓይነት መኖሩ ነው። በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ በሳንባ ነቀርሳ በሽታ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ሦስት ሚልዮን ደርሷል። የሳንባ ነቀርሳን ለመቆጣጠር የተደረገው ውጊያ ሽንፈት ያጋጠመው ለምንድን ነው?
አንደኛው ምክንያት ብዙ በሽተኞች መድኃኒታቸውን በታዘዙት መሠረት ማለትም አብዛኛውን ጊዜ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወር ለሚደርስ ጊዜ አለመውሰዳቸው ነው። ለምሳሌ ያህል በአንድ ጥናት እንደተረጋገጠው ኒው ዮርክ ከተማ የሳንባ ነቀርሳ በሽታ ካለባቸው 200 በሽተኞች መካከል 89 በመቶ የሚሆኑት መድኃኒታቸውን በታዘዙት መሠረት ወስደው አልጨረሱም። የአሜሪካ የሳንባ ማኅበር ፕሬዚደንት የሆኑት ዶክተር ሊ ራይክማን እንዳሉት “ይህ ሁኔታ በጣም የሚያስደነግጥ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች (ሀ) ከበሽታቸው ሊፈወሱ አይችሉም፣ (ለ) በተለምዶ በምንጠቀምባቸው መድኃኒቶች የማይበገር ዓይነት የሳንባ ነቀርሳ ሊያገረሽባቸው ይችላል።” በተጨማሪም እነዚህ የበሽታው ተሸካሚ የሆኑ ሰዎች የሚጎዱት የራሳቸውን ጤና ብቻ አይደለም። ዶክተር ራይክማን አክለው እንደተናገሩት “መድኃኒታቸውን ባለመውሰዳቸው በሽታውን ወደ ሌሎች ሰዎች ሊያስተላልፉ ይችላሉ።” በየዓመቱ በመላው ዓለም ስምንት ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በሳንባ ነቀርሳ እንዲያዙ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች ይህ አንዱ እንደሚሆን አያጠራጥርም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በዚህ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀኖች’ እንደምንኖር ከሚያሳዩት ምልክቶች አንዱ ‘ቸነፈር በየቦታው መብዛቱ’ እንደሆነ ይገነዘባሉ። (ሉቃስ 21:11፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1) ከዚህ በኋላ ምን ይከተላል? “በዚያ የሚኖር ታምሜአለሁ” የማይልበት አዲስ ምድር ይመጣል። (ኢሳይያስ 33:24) አዎን፣ ይሖዋ አምላክ ጊዜያዊ እፎይታ ለመስጠት ሳይሆን ከበሽታና ከሞት ፈጽሞ እንደሚገላግለን ቃል ገብቶልናል።— ራእይ 21:1-4