ከሰዎች ጋር የመነጋገር ችሎታ ትልቅ ጥበብ ነው
መብላት፣ መተኛት፣ መሥራት የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች ናቸው። ይሁን እንጂ ሌላም መሟላት ያለበት በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር አለ። ይህ አስፈላጊ የሆነ ነገር ምንድን ነው?
ከሰው ሁሉ ተነጥሎና ለሕይወት በጣም አስፈላጊ ከሆኑት መሠረታዊ ነገሮች አንዱን ተነፍጎ ለአምስት ዓመታት ብቻውን የታሰረ አንድ ሰው የተናገረውን ቃል እንመልከት። “የማነጋግረውና የሚያዳምጠኝ፣ ባልንጀራ የሚሆነኝ ሰው ለማግኘት በጣም እጓጓ ነበር። ይህን ብቸኝነቴን ለመቋቋም አንድ ነገር ማድረግ እንደሚኖርብኝ ተገነዘብኩ። ከሰዎች ተገልዬ ብቻዬን መኖሬ አእምሮዬን መንካቱ አይቀርም።”
አዎን፣ ሐሳባችንን ለሌሎች የማካፈል ፍላጎት የተፈጥሮ ባሕርያችን ነው። ይህን ፍላጎት ልናሟላ የምንችለው ደግሞ ሰዎችን በማነጋገር ነው። ዴኒስ አር ስሚዝና ኤል ኬት ዊልያምሰን የተባሉ ተመራማሪዎች “ሳንፈራና ሳንሸማቀቅ ምሥጢራችንን የምናዋያቸው፣ ደስታችንንም ሆነ ሥጋት የሚፈጥሩብንን ነገሮች የምናካፍላቸው፣ በጠቅላላው የምናነጋግራቸው ሰዎች ማግኘት ያስፈልገናል” ብለዋል።
መናገር ያስፈልገናል!
የሰው ልጆች በጣም አስደናቂ የሆነ የንግግር ተሰጥኦ አላቸው። አዎን፣ ከሌሎች ጋር ለመነጋገር የሚያስችል ተፈጥሮ አለን። አንድ ሰው እንደሚከተለው ብሏል:- “አምላክ የፈጠረን በማኅበር እንድንኖር አድርጎ ነው። የመናገር አጋጣሚ ባታገኙ ወይም ሐሳባችሁን የመግለጽ ችሎታችሁን ብትነጠቁ ትልቅ ቅጣት ይሆንባችኋል። ከሌሎች ጋር በምትነጋገሩበት ጊዜ በጣም ጠቃሚ የሆነ ነገር ይፈጸማል። ስለራሳችሁ ጥሩ ግምት ይኖራችኋል። ሌሎች ምን እንደሚያስቡና እንደሚሰማቸው ማወቃችሁም ይጠቅማችኋል።”
የአንድ ተጓዥ አገልጋይ ሚስት የሆነችው ኢሌይን እንዲህ ብላለች:- “ቃላት የስሜት መግለጫ ናቸው። ባልናገርም የትዳር ጓደኛዬ ምን ያህል እንደምወደው ያውቃል ብለን ማሰብ አንችልም። መናገር ይኖርብናል። ጆሮ እነዚህን ቃላት ማዳመጥ ይፈልጋል። መነጋገር ያስፈልገናል።”
የአንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ልጅ የሆነው ዴቪድ እንደሚከተለው በማለት ስለ ራሱ ተናግሯል:- “አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ስለምቆርጥ ስሜቴን መረዳት ያስቸግረኛል። በመጀመሪያ ንግግር ለማቆም እፈልጋለሁ። ይህን ሳደርግ ግን ከፍተኛ ውጥረት ይሰማኛል። ሌላ ሰው ሳነጋግር የታመቀውን ስሜቴን ማስተንፈሻ እንዳገኘሁ ይሰማኛል። በምናገርበት ጊዜ ስለ ራሴ ምን እንደሚሰማኝ የማወቅና መፍትሔውን የመፈለግ እድል አገኛለሁ።”
ከሰዎች ጋር በጥሩ ሁኔታ እንዳንነጋገር የሚያደርጉ እንቅፋቶች
በእርግጥም ከሌሎች ጋር መነጋገር የሚያሟላው ፍላጎት አለ። ቢሆንም እንዲህ እንዳናደርግ እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች አሉ። እንዲያውም አንዳንዶች ከሌሎች ጋር መነጋገር በጣም ከባድ ትግል ስለሚሆንባቸው መራቁን ይመርጣሉ።
ጋሪ “በአብዛኛው የሕይወት ዘመኔ ከጭውውት መሸሽ እንደሚሻለኝ ይሰማኝ ነበር። ይህም የሆነው በራሴ ስለማልተማመን ነበር። አሁንም ቢሆን ከሰዎች ጋር በምነጋገርበት ጊዜ የማይረባ ነገር ብናገር ወይም የሚሰማኝ ሰው ቢያዋርደኝስ ብዬ እፈራለሁ” ብሏል።
ኢሌይን ደግሞ ችግሯ ዐይነ አፋርነት እንደሆነ ትናገራለች። “ያደግኩት ብዙ የንግግር ልውውጥ በማይደረግበት ቤተሰብ ውስጥ ነው። አባቴ በጣም የሚያስፈራ ሰው ነበር። በዚህም ምክንያት ባደግኩ ጊዜ ቁምነገር ያለው ምንም ነገር ልናገር አልችልም የሚል ስሜት ይሰማኝ ጀመር።” አዎን፣ ዓይነ አፋርነት ከሌሎች ጋር በመነጋገር እንዳንደሰት ከባድ እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። እንዲያውም በዝምታ አጥር ውስጥ ተከባችሁ እንድትኖሩ ሊያደርግ ይችላል።
ጆን የተባለ ስለ ራሱ ካለው ዝቅተኛ ግምት ጋር ሲታገል የኖረ ክርስቲያን ሽማግሌ “ልክ እንደ ወረርሽኝ ነው” ብሏል። “ለዐይነ አፋርነት ከተሸነፋችሁ ራሳችሁን ከሌሎች ታገላላችሁ። በአንድ ክፍል ውስጥ መቶ ሰው ቢኖር እንኳን ትንፍሽ አትሉም። ይህም ከፍተኛ ኪሣራ ያስከትልባችኋል!”
በሌላው በኩል ደግሞ ዳንኤል የተባለ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል:- “ከሰዎች ጋር መነጋገር አያስቸግረኝም። ይሁን እንጂ ሳይታወቀኝ የሌሎችን ንግግር አቋርጥና እኔ ብቻ መናገር እጀምራለሁ። እንዲህ ማድረጌን የምገነዘበው የሚስቴ ፊት ለወጥ ሲል ነው። ‘ምን ነካኝ አሁንም አቋረጥኳት’ ብዬ አዝናለሁ። ከዚያ በኋላ ውይይታችን ምንም እንደማይጥማት አውቃለሁ።”
እነዚህንና ሌሎች እንቅፋቶችን ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው? ከሌሎች ጋር የመነጋገርን ጥበብ ለማዳበር የሚያስፈልጉት ባሕርያት ምንድን ናቸው? እነዚህንስ ባሕርያት እንዴት ሥራ ላይ ማዋል ይቻላል?
‘ምን ልል እችላለሁ?’
‘የምናገረው ነገር ይጠፋኛል።’ ‘ምንም ነገር አላውቅም።’ ‘የምናገረውን ለመስማት የሚፈልግ ሰው የለም።’ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ሊኖርህ ቢችልም ይህ አስተሳሰብህ ትክክል ላይሆን ይችላል። ለአንተ አይታወቅህ ይሆናል እንጂ ብዙ ነገር ታውቃለህ። ከእነዚህ ከምታውቃቸው ነገሮች አንዳንዶቹን ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች መኖራቸው አይቀርም። ለምሳሌ ያህል በቅርቡ ወደ አንድ ሥፍራ ተጉዘህ ይሆናል። ይህ የሄድክበት ቦታ እነርሱ ከሚኖሩበት አካባቢ እንዴት እንደሚለይ ወይም እንደሚመሳሰል ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ።
ከዚህም በላይ የተለያዩ ጽሑፎችን በማንበብ ስለ ተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ያለህን እውቀት ልታሳድግ ትችላለህ፣ ማሳደግም ይኖርብሃል። በየቀኑ ጊዜ መድቦ አንድ ነገር ማንበብ ጥሩ ልማድ ነው። በይሖዋ ምሥክሮች የሚዘጋጁ ጽሑፎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስና አጠቃላይ ስለሆኑ ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ያብራራሉ። ያለህ እውቀት በጨመረ መጠን ለሰዎች ልታካፍል የምትችለው መረጃም የዚያኑ ያህል ይጨምራል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን የይሖዋ ምስክሮች የሚጠቀሙበት ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር የተባለው ቡክሌት ነው። ከዚህ ጽሑፍ በየቀኑ የምታስብበትና ከሰዎች ጋር በምታደርገው ጭውውት የምትጠቀምበት አዳዲስ ሐሳብ ታገኛለህ።
ከሰዎች ጋር መነጋገር አለብን ስንል እኛ ብቻ ተናጋሪዎች መሆን አለብን ማለት አይደለም። ሁለቱም ወገኖች ሐሳባቸውን መግለጽ አለባቸው። የሚያዳምጥህ ሰው የበኩሉን እንዲናገር ፍቀድለት። ዝምተኛ ከሆነ በዘዴ አንዳንድ ጥያቄዎች ልታቀርብለት ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል ሸምገል ካለ ሰው ጋር እየተነጋገርክ ነው እንበል። ቀደም ባሉት ዘመናት ስለተፈጸሙ ነገሮች ወይም ዓለም ወይም የቤተሰብ ሕይወት እርሱ ወጣት ከነበረበት ጊዜ ምን ያህል እንደተለወጠ ልትጠይቅ ትችላለህ። የሚናገረውን ማዳመጥ ደስ የሚያሰኝህ ከመሆኑም በላይ ብዙ ትምህርት ታገኝበታለህ።
ጥሩ አዳማጭ ሁን
ጥሩ አዳማጭ መሆን ለጥሩ ጭውውት በጣም አስፈላጊ ነው። ሌሎች የሚናገሩትን በጥሞና ማዳመጣችን የተጫናቸውን ሸክም ለማቅለል የሚያስችል እርዳታ ለማግኘት ለሚጥሩ ሰዎች ጥሩ ድጋፍ ሊሆናቸው ይችላል። ራሱን ‘ለምንም እንደማይረባ’ አድርጎ ይቆጥር የነበረ አንድ ሰው በጣም ተከፍቶ ስለነበር ወዳጁ የሆነ ሰው እንዲረዳው ስልክ ይደውላል። ስልክ የደወለበት ሰዓት በጣም የማያመች ቢሆንም ወዳጁ ለሁለት ሰዓት ያህል በትዕግሥት አዳመጠው! ይህ ሰው የሕይወቱን አቅጣጫ የቀየረለት ይህ ውይይት እንደሆነ ይናገራል። እንዲህ ያለ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ የቻለው ነገር ምንድን ነው? በጥሞና ያዳመጠው ወዳጅ “ጥሩ አዳማጭ መሆኔ ብቻ ነው” ብሏል። “ምንም የተናገርኩት የጥበብ ቃል ትዝ አይለኝም። ‘እንዲህ የተሰማህ ለምንድን ነው?’ ‘ይህስ ያስጨነቀህ ለምንድን ነው?’ ‘ታዲያ ምን ነገር ሊረዳህ ይችላል?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ ሌላ ያደረግኩት ነገር የለም። ለእነዚህ ጥያቄዎቼ መልስ ሲሰጥ የራሱም ጥያቄዎች መልስ አገኙ።”
ልጆች ወላጆቻቸው ጊዜ ገዝተው ሲያነጋግሯቸው በጣም ደስ ይላቸዋል። ስኮት የተባለ አንድ ወጣት “ወላጆች ቀረብ ብለው በአእምሮአችሁ ውስጥ ምን እንደሚጉላላ ለማወቅ ሲፈልጉ በጣም ጥሩ ነው። አባዬ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዲህ እያደረገ ነው። ብቻችሁን ልትቋቋሙ የማትችሏቸው ብዙ ነገሮች ስላሉ ይህ በጣም ይረዳችኋል” ሲል ገልጿል።
አንድ ሰው ደግሞ “ልጆቻችሁ በነጻነት ሊያነጋግሯችሁ የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠር ይኖርባችኋል” የሚል ምክር ሰጥቷል። ይህ ሰው ወላጆች ራሳቸውን በልጆቻቸው ቦታ አድርገው በጥሞና ማዳመጣቸው ለልጆቹ የተስተካከለ እድገትና ስብዕና በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ስለሚሰማው ከአራት ልጆቹ ጋር በየተራ የሚያሳልፈው ጊዜ ይመድባል። የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል። አጋጣሚ ኖሮ ልጃችሁ ሊያነጋግራችሁ ሲፈልግ ለማዳመጥ ዝግጁ ሁኑ። “ምንም ያህል ቢደክማችሁ ወይም ውጥረት ቢኖርባችሁ ዞር እንዲሉላችሁ አትጠይቋቸው!” ብሏል።
ልባዊ የሆነ አሳቢነት ጥሩ ምላሽ ያስገኛል
ብዙ ሰዎች ልባቸውን እንዲከፍቱና ሐሳባቸውን በንግግር እንዲገልጡ የስሜት ድጋፍ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። አንድ ወጣት እንዲህ በማለት ምሬቱን ገልጿል። ‘አንድ የማነጋግረው ሰው የግዴታ ያስፈልገኛል። ግን ማንን ላነጋግር? ሰዎችን ማነጋገር በጣም ይከብደኛል። ስለ እኔ ከልብ የሚያስብ ሰው ያስፈልገኛል።’ ልባዊ የሆነ አሳቢነት ማሳየት የመተማመንና የመረጋጋት ስሜት እንዲኖር ስለሚያስችል አንድን ሰው ከልብ ለማነጋገር ቀላል ይሆናል።
አንድ ሰው እንዲህ በማለት የራሱን ታሪክ ይናገራል:- “ከበርካታ ዓመታት በፊት ቤተሰብን በሚመለከት ችግር አጋጥሞኝ በነበረ ጊዜ አንድ ወዳጄን ስለ ችግሬ ለማዋየት ሞከርኩ። ‘ቀበቶህን ጠበቅ አድርግና ጠንከር ብለህ ተቋቋም፣ ሁሉ ነገር ይስተካከልልሃል’ ከማለት በቀር ምንም ነገር አልተናገረኝም። ምንም ሌላ ያዋየኝ ወይም የተናገረኝ ነገር ባለመኖሩ ምንም አልረዳኝም። እንዲያውም ችግሬን አምቄ እንድይዝ አደረገኝ። በኋላ ግን ከአንድ የይሖዋ ምስክሮች የበላይ ተመልካች ጋር ተነጋገርኩ። የዓይኖቹ አመለካከት፣ የፊቱ ገጽታና ደግነት የተሞላበት አነጋገሩ ራሱን በእኔ ቦታ አድርጎ እንደሚያዳምጠኝ የሚያስገነዝቡ ነበሩ። በዚህም ምክንያት ከልቡ እንደሚያስብልኝ ስለተሰማኝ ልቤን ከፍቼ ችግሬን መናገር ጀመርኩ። ‘በዚህ ባጋጠመህ ሁኔታ አንተን ለመርዳት የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን’ አለኝ። እንደዚህ ላሉ ሰዎች ልብ መክፈትና ጥሩ ምላሽ መስጠት አያስቸግርም።”
እኛስ ልባችንን አስፍተን ሌሎች ከእኛ ጋር ትርጉም ያለው ውይይት እንዲያደርጉ ልንገፋፋ እንችል ይሆን? ዓይነ አፋር በመሆኑ ምክንያት በርከት ያሉ ሰዎች በተሰበሰቡበት ራሱን ከሌሎች ያገለለ ሰው ስንመለከት ይህን ሰው በጭውውታችን ውስጥ ለማስገባት እንሞክራለንን? ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጆን “ራሴን እንዲህ ባለው ሰው ቦታ አድርጌ ስለምመለከት ምን እንደሚሰማው ይገባኛል። ችግሩና ጭንቀቱ ይሰማኛል!” ብሏል። በማከልም “ወደርሱ ቀረብ ብለን በጭውውቱ እንዲካፈል ብናደርግ ምንኛ መልካም ይሆናል! እንዲያውም ስለ ሁኔታው ድምፃችንን ሳናሰማ ልንጸልይ እንችላለን” ብሏል።
ዳን ስለ አንድ ወዳጁ እንዲህ ይላል:- “ሮይ ከሰዎች ጋር ለመነጋገር ባለው ችሎታ ስለማይተማመን ሰዎች ሰብሰብ ብለው በሚነጋገሩበት ቦታ ሁሉ ነጠል ይላል። በዚህ ምክንያት ‘ሮይ፣ ስለዚህ ጉዳይ ምን ነበር የተናገርከው? እስቲ ንገረን’ ብዬ እጠይቀዋለሁ። ከዚያ በኋላ መናገር ይጀምራል። በዚህም የተነሣ ሌሎች ሰዎች ቀደም ሲሉ ሊያውቁ ያልቻሉትን እውነተኛ ባሕርዩን ለማወቅ ችለዋል።” ዳን እንደሚከተለው በማለት አጥብቆ ይመክራል:- “አንድን ሰው ማነጋገር ወይም ሐሳቡን እንዲገልጽ ማድረግ አስቸጋሪ ሲሆን ተስፋ ቆርጣችሁ አትተዉ። በውስጡ ግን መነጋገር የሚፈልግ ጥሩ ሰው እንደሆነ አስቡ። ሐሳቡን እንዲገልጽ ለማድረግ የምታደርጉትን ጥረት አታቋርጡ።”
የዓይነ አፋርነት ችግር ቢኖርብህም ለሌሎች አሳቢ የመሆንና የፍቅር ስሜት ካዳበርክ ብዙ ጥቅም ታገኛለህ። ጆን እንዲህ ማድረጉ ራሱን ከሰዎች የማግለል ዝንባሌውን እንዲያሸንፍ እንዳስቻለው ተገንዝቧል። “ፍቅር የራሱን ጥቅም አይፈልግም” በማለት ያብራራል። (1 ቆሮንቶስ 13:5) “ፍቅር የሚጠይቅብህን ለማድረግ ከሌሎች ጋር መነጋገርና ስለ ሌሎች መጠየቅ ይኖርብሃል። በራስህ ድክመቶች ተሸንፈህ ጸጥ ማለት የሚፈይደው ነገር አይኖርም። በጸሎት በመትጋት ራስህን ለማሸነፍ ትችላለህ።” ምክሩን በመቀጠል “ይህን ከማድረግ የሚገኘው ጥቅም በጣም ታላቅ ነው። ሌሎች ምን ያህል ጥሩ ምላሽ ሲሰጡና እንዳበረታታሃቸው ስትመለከት አንተም ትጽናናለህ። ይህም በሚቀጥሉት ጊዜያት በዚሁ እንድትቀጥል የሚያስችልህን ድፍረት ይሰጥሃል።”
ራስን በሌሎች ቦታ ማስቀመጥ፣ የጥሩ ጭውውት መሠረት ነው
በጣም ከፍተኛ የሆነ ግምት ከሚሰጣቸው የሰው ልጅ ባሕርያት አንዱ ራስን በሌሎች ቦታ አስቀምጦ የማየት ችሎታ ነው። ይሁን እንጂ ራስን በሌሎች ቦታ አድርጎ ማየት ሲባል ምን ማለት ነው? የፔንሲልቫንያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር በርናርድ ገርኒ ራስን በሌሎች ቦታ አድርጎ ማየት ማለት ‘ጉዳዩን ተስማማችሁም አልተስማማችሁ የሌላውን ሰው ስሜትና አመለካከት መረዳት ማለት ነው’ ብለዋል። ራስን በሌሎች ቦታ ማድረግ ለጥሩ ጭውውት ምን ያህል አስፈላጊ ነው? “የመሠረት ድንጋይ ነው! ለሌላው ነገር ሁሉ መሠረት ነው።”
ዶክተር ገርኒ ጥሩ ግንኙነትና ዝምድና ሊኖር የሚችለው እርስ በርስ መነጋገር ሲቻል ነው ሲሉ ገልጸዋል። እርግጥ የአስተሳሰብ ልዩነት መኖሩ የማይቀር ነው። ልዩነቶቹን ለማስወገድና ዝምድናው እንደተጠበቀ እንዲኖር ለማድረግ ስለ ችግሩ ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆን ያስፈልገናል። ብዙዎች ግን ሌላውን ሰው በማያስቆጣና ስህተቱን ለመሸፈን እንዳይሞክር በሚያደርግ መንገድ ማነጋገር ስለማይሆንላቸው ልዩነታቸውን በውይይት ከመፍታት ይታቀባሉ። ዶክተር ገርኒ እንደሚሉት “አብዛኞቹ ሰዎች የአንድን ሰው አቋም ማክበርና መረዳት ከአቋሙ ጋር መስማማት እንዳልሆነ አይረዱም። በዚህም ምክንያት በሐሳብ ሳይግባቡ በሚቀሩበት ጊዜ የሰውዬውን ሐሳብ መረዳትና ማክበር ያቅታቸዋል። ራሳችሁን በሌላው ሰው ቦታ አድርጎ መመልከት በመስማማትና በመረዳት መካከል ልዩነት መኖሩን እንድትገነዘቡ ያስችላችኋል።”
ራስህን በሌላው ሰው ቦታ አድርገህ ስትመለከት እንደዚያ ሰው ለማሰብ ትችላለህ። እሱ የሚሰማው ይሰማሃል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲኖር በአስተሳሰቡና በአቋሙ ባትስማማም እርሱን መረዳት፣ መገንዘብና ማክበር ቀላል ሆኖ ታገኘዋለህ።
የአራት ልጆች እናት የሆነችውን ጃኔትን እንውሰድ። በአንድ ወቅት ለምንም ነገር የማትጠቅም እንደሆነች ይሰማት ስለነበረ ቅስሟ ተሰብሮ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ሌሎችን ለመርዳት ራስን በእነርሱ ቦታ አድርጎ ማየት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝባለች። እንዲህ በማለት ስለራስዋ ትናገራለች:- “የማደርገው ነገር ሁሉ እዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ ይሰማኝ በነበረበት ጊዜ ባለቤቴ እንዴት ባሉ በርካታ መንገዶች ጠቃሚ ሥራ እንዳከናወንኩ ይነግረኝ እንደነበረ አስታውሳለሁ። እያለቀስኩ የምናገረውን ሁሉ እንኳ በፍቅር ካዳመጠኝ በኋላ ያጽናናኝ ነበር። አስተሳሰቤን ቢያቃልልና ‘የማይረባ አስተሳሰብ ነው’ ቢለኝ ኖሮ ግን አፌን ዘግጄ የራሴን መንገድ እከተል ነበር። ከዚህ ይልቅ ግን በዚያ ምሽት የልባችንን አውጥተን ረዘም ላለ ጊዜ ልንነጋገር ችለናል።”
‘ራስን በሌሎች ቦታ አድርጎ መመልከት ለሰዎች የምናስብና የምንጨነቅ መሆናችንን ያሳያል። ለብዙ ሰዎች አስፈላጊ የሆነው ሐሳብ ለሐሳብ ተገላልጦ የመነጋገር መንፈስ እንዲኖር ያስችላል’ በማለት ዶክተር ገርኒ ምክራቸውን ደምድመዋል።
አንተም ልታደርገው ትችላለህ!
አንተም ጥሩ ተጫዋች ለመሆን ትችላለህ። ሰዎችን የማነጋገር ችሎታችንን ለማዳበር አስፈላጊ የሆኑትን ጥቂት ባሕርያት ተመልክተናል። ሆኖም ያልተጠቀሱ በርካታ ባሕርያት አሉ። ከእነዚህም መካከል የወዳጅነት አቀራረብ፣ ቀልድ ማወቅ፣ ዘዴኛ መሆን ይገኙበታል። አንድ ሠዓሊ ከረዥም ጊዜ ሥልጠናና ልምምድ በኋላ በብሩሹ በመጠቀም በጣም የተዋበ ሥዕል እንደሚስል እኛም እነዚህን አስፈላጊ ባሕርያት ለማዳበር ጠንክረን መጣር ይኖርብናል።
ለምሳሌ ያህል ዳንኤል ከሰዎች ጋር የመነጋገር ችሎታውን አዳብሯል። ግን እንዴት ሊያዳብር ቻለ? የሌሎችን ንግግር የማቋረጥና እሱ ብቻ ተናጋሪ የመሆን ዝንባሌውን መቆጣጠር የሚችልበትን መንገድ በመማር ነው። “እኔ ብቻ ተናጋሪ እንዳልሆን ልባዊ ጥረት አድርጌያለሁ። በምላሴ ላይ ልጓም ለማኖር ተገድጃለሁ። ንግግሬን ለማራዘም እንደፈለኩ ሲሰማኝ ምላሴን እቆጣጠራለሁ። የምናገረው ነገር የውይይቱን አቅጣጫ የሚያስለውጥ ወይም ሌላ ሰው ሊናገር ያሰበውን የሚያስጠፋበት መስሎ ሲታየኝ ንግግሬን አቆማለሁ።”
ኢሌይንንስ የረዳት ነገር ምንድን ነው? ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ካገኘች በኋላ ለሰዎች የምትናገረው ዋጋ ያለውና ጠቃሚ ነገር እንዳላት ተገነዘበች። እንዲህ ትላለች:- “ስለ ራሴ ማሰብ ከተውኩና ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ከተነጋገርኩ ከሌሎች ጋር መነጋገር አያስቸግረኝም። በተጨማሪም በየጊዜው የሚደርሱንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ማንበቤ ጠቅሞኛል። እነዚህን ጽሑፎች በየጊዜው እየተከታተልኩ ሳነብ በቀላሉ ከሰዎች ጋር ለመነጋገር የሚያስችሉ አዳዲስ ሐሳቦች አገኛለሁ።”
ከሰዎች ጋር በምትነጋገርበት ጊዜ እነዚህን አስፈላጊ ባሕርያት ለማዳበር ጣር። እንዲህ ካደረግህ አንተም የሌሎችን መንፈስ ማደስና ማስደሰት ትችላለህ። በተጨማሪም ለሰው ልጅ በጣም አስፈላጊ የሆነ አንድ ጥበብ ጠንቅቀህ በማወቅህ እርካታ ታገኛለህ።