ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
እንደ ሌሎች ወጣቶች እንድደሰት የማይፈቀድልኝ ለምንድን ነው?
“እኛ የምንፈልገው ለመደሰት ብቻ ነው፣ ግን አስቸጋሪ ሆኖብናል” በማለት 15 ዓመት የሆነው ጄሰን ያማርራል።
በተለይ በወጣትነት ዕድሜ ለመደሰት መፈለግ ያለ ነገር ነው። ለብዙ ወጣቶች መደሰት ከመብላትና ከመጠጣት ያላነሰ አስፈላጊነት አለው። ወጣቶች በእኩዮቻቸውና በመገናኛ ብዙሐን እየተገፋፉ በተለያዩ የመዝናኛ ዓይነቶች ይካፈላሉ። አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ከሚወዷቸው የምሽት ጊዜ ማሳለፊያዎች መካከል ጓደኞቻቸውን መጠየቅ፣ ቴሌቪዥን መመልከት፣ ሲኒማ ማየት፣ ፓርቲ መሄድና መጨፈር የመጀመሪያ ምርጫዎቻቸው ሆነው ተገኝተዋል። በተጨማሪም ማንበብ፣ የተለያዩ ጨዋታዎች፣ ስፖርትና ሙዚቃ ማዳመጥም ተወዳጅነት አላቸው።
ደስታ የሚያመጡ ስንት ዓይነት እንቅስቃሴዎች እያሉ እንደ ጄሰን ያሉ አንዳንድ ወጣቶች ደስታ እንደቀረባቸው አድርገው ለምን እንደሚያማርሩ ወላጆች ግራ ሊገባቸው ይችላል። ያም ሆነ ይህ ግን አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች እንዲህ ብለው ሲያማርሩ ይሰማል። ኬሲ የተባለች የይሖዋ ምሥክር ወጣት “የትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁ ወደ ፓርቲዎች ሲሄዱና ሌሎች የተለያዩ ነገሮችን ሲያደርጉ ስታዩ ብዙ ነገር እንደቀረባችሁ ይሰማችኋል” ብላለች። ይሁን እንጂ ክርስቲያን ወጣቶች ያሉበት ሁኔታ ይህን ያህል የከፋ ነውን?
መጽሐፍ ቅዱስ መደሰት ይከለክላልን? በፍጹም አይከለክልም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” እንደሆነ ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 አዓት) ስለዚህ ንጉሥ ሰሎሞን “ለሁሉ ዘመን አለው፣ . . . ለማልቀስ ጊዜ አለው፣ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፣ ለመዝፈንም ጊዜ አለው” ማለቱ ሊያስደንቅ አይገባም። (መክብብ 3:1, 4) እዚህ ላይ “መሳቅ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃልና ከዚህ ቃል ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ሌሎች ቃላት “በዓል ማድረግ፣” “መጫወት፣” “ስፖርት መሥራት፣” “ማስደሰት” እና “ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ” የሚል ትርጉም አላቸው።— 2 ሳሙኤል 6:21፤ ኢዮብ 41:5፤ መሳፍንት 16:25፤ ዘጸአት 32:6፤ ዘፍጥረት 26:8
ጥንት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የአምላክ ሕዝቦች ሙዚቃ እንደመጫወት፣ እንደ መዝፈን፣ መጨፈር፣ ጭውውትና የተለያዩ ጨዋታዎችን እንደ መጫወት ባሉ ጤናማ እንቅስቃሴዎች ይካፈሉ ነበር። በተጨማሪም ድግስ አዘጋጅተው የሚገባበዙባቸውና የሚደሰቱባቸው የተለዩ ጊዜያት ነበሯቸው። (ኤርምያስ 7:34፤ 16:9፤ 25:30፤ ሉቃስ 15:25) ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን በሠርግ ድግስ ላይ ተገኝቶ ነበር!— ዮሐንስ 2:1-10
ስለዚህ በዘመናችን ያሉ ክርስቲያን ወጣቶች ጤናማ በሆኑ ነገሮች እንዳይደሰቱ አይከለከሉም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “አንተ ጎበዝ፣ በጉብዝናህ ደስ ይበልህ፣ በጉብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው” ይላል። ይሁን እንጂ ሰሎሞን ይህን ከተናገረ በኋላ “ዳሩ ግን ስለዚህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንዲያመጣህ እወቅ” የሚል ማስጠንቀቂያ አስከትሏል። (መክብብ 11:9) አዎን፣ ለምታደርጋቸው ምርጫዎች ሁሉ በአምላክ ዘንድ በኃላፊነት ትጠየቃለህ። ስለዚህ መዝናኛዎችን በሚመለከት “እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ” የሚለውን ምክር መከተል አስፈላጊ ነው። (ኤፌሶን 5:15, 16) ለምን ቢባል ብዙ ወጣቶች በዚህ ረገድ መጥፎ ምርጫ እያደረጉ ነው።
ደስታ ከቁጥጥር ውጭ በሚሆንበት ጊዜ
በጥንት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የሆነውን እንመልከት። አንዳንድ እስራኤላውያን በመዝናኛዎች ረገድ ሚዛናቸውን ስተው ሌሊቱን ሙሉ ሲጨፍሩ ማደር ጀምረው ነበር! ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ብሏል:- “ስካርን ለመከተል በጥዋት ለሚማልዱ፣ የወይን ጠጅም እስኪያቃጥላቸው እስከ ሌሊት ድረስ ለሚዘገዩ ወዮላቸው! መሰንቆና በገና ከበሮና እምቢልታም የወይን ጠጅም በግብዣቸው አለ።” አንድ ላይ ሆኖ መብላት፣ መጠጣትና መጨፈር በራሱ ስህተት አይደለም። ይሁን እንጂ ኢሳይያስ ስለ እነዚህ ፈንጠዝያ አሳዳጆች “የእግዚአብሔርን ሥራ ግን አልተመለከቱም” ብሏል።— ኢሳይያስ 5:11, 12
በዘመናችን ያሉ ብዙ ወጣቶችም ይህንኑ የሚመስል ነገር ያደርጋሉ። በሚዝናኑበት ወቅት ስለ አምላክ ፈጽሞ አያስቡም። አንዳንዶች የአምላክን የጽድቅ ሕግጋት በድፍረት በመተላለፍ “ለደስታ” ሲሉ ከጋብቻ ውጭ የጾታ ግንኙነት ይፈጽማሉ፣ የሰው ንብረት ያጠፋሉ፣ አደንዛዥ ዕፆች ይወስዳሉ እንዲሁም ብዙ ቅጥ የለሽ ተግባራት ይፈጽማሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቶች ሆን ብለው ክፉ ለማድረግ የማይነሱባቸው ጊዜያት አሉ። ይሁን እንጂ የልከኝነት ገደባቸውን መጠበቅ ያቅታቸዋል። (ምሳሌ 23:20፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:11) በዚህም ምክንያት የሚያደርጓቸው ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ይሆኑባቸዋል።— ከ1 ቆሮንቶስ 10:6-8 ጋር አወዳድር።
በቅርቡ ንቁ! “በአሁኑ ጊዜ በዓለማዊ ፓርቲዎች ምን ዓይነት ነገሮች ይደረጋሉ?” የሚል ጥያቄ ለአንዳንድ ወጣቶች አቅርቦ ነበር። አንዲት ወጣት ልጃገረድ “ይጠጣል፣ አደንዛዥ ዕፆች ይወሰዳሉ። እነዚህ ነገሮች በብዛት ይፈጸማሉ” ብላለች። አንድሩ የተባለ ወጣት ደግሞ በትምህርት ቤቱ ስላሉ ፓርቲ የሚያዘወትሩ ልጆች ሲናገር “ሁልጊዜ ምን ያህል ብዙ እንደጠጡ በጉራ ይናገራሉ” ብሏል። ጄሰን “መጥፎ ነገር የማይፈጸምበት ዓለማዊ ፓርቲ ኖሮ አያውቅም” እስከማለት ደርሷል። “ፈንጠዝያ” ወይም “ስድ የሆነ ድግስ” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተወገዘ በመሆኑ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወጣቶች እንደነዚህ ያሉ ተግባራት ከሚፈጸምባቸው ማኅበራዊ ስብሰባዎች ይርቃሉ።— ገላትያ 5:21 ባይንግተን
ጉዳት የሌላቸው መስለው የሚታዩ መዝናኛዎች እንኳን አደገኞች ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ በርካታ የሆኑ የጊዜያችን ፊልሞች እርቃነ ሥጋ የሚያሳዩ፣ ሩካቤ ሥጋ ሲፈጸም የሚታይባቸውና የሚዘገንኑ የኃይል ድርጊቶች የሚፈጸምባቸው ናቸው። ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፉ ዘፈኖች የብልግና ግጥሞች አሏቸው። የሮክ ሙዚቃ ትርዒቶች በአብዛኛው ዕፅ የሚጨስባቸው፣ ግርግር የሚበዛባቸውና ዓመፅ የሚፈጸምባቸው ቦታዎች ናቸው።a
ወላጆች አይቻልም በሚሉበት ጊዜ
በዚህ ረገድ ልብ ሊባል የሚገባው መሠረታዊ ሐቅ ምንድን ነው? ክርስቲያን ከሆንክ እኩዮችህ የሚያደርጓቸውን ነገሮች በሙሉ ማድረግ አትችልም። ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘የዓለም ክፍል እንደማይሆኑ’ ተናግሯል። ይህ ማለት ደግሞ ከሌሎች ሰዎች የተለየን መሆን አለብን ማለት ነው። (ዮሐንስ 15:19) ወላጆችህ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ከሆኑ ይህን ሐቅ አሳምረው ያውቃሉ። ስለዚህ ወላጆች አንተን ከጉዳት ለመጠበቅ ሲሉ ሌሎች ወጣቶች የሚፈቀድላቸውን ነገር እንዳታደርግ ሊመክሩህ ወይም አጥብቀው ሊከለክሉ ይችላሉ። ይህን መቀበል ሁልጊዜ ቀላል አይሆንም። አንዲት ወጣት ልጃገረድ “ማንም ሰው መደሰት ይፈልጋል! ወላጆቻችንም ቢሆኑ በወጣትነታቸው ይደሰቱ ነበር። አሁን ግን እኛ ልጆቻቸው ተዘግተን እንድንቀመጥ የሚፈልጉ ይመስላል” ብላለች።
የወላጆቻችሁን አመለካከት የማትቃወሙ ብትሆኑም እንደነዚህ ባሉ ጉዳዮች የሚሰጡትን ምክር መከተል አስቸጋሪ ሊሆንባችሁ ይችላል። ያሬድ ብለን የምንጠራው ፈርጠም ያለ ሰውነት ያለው አንድ ወጣት “የትምህርት ቤት ቡድን አባል ሆኜ የቅርጫት ኳስ ለመጫወት ፈለግኩ። እንድጫወት ይገፋፉኝ የነበሩ ሰዎች በርካታ ስለነበሩ ነገሩ አሳስቦኝ ነበር። በዚህ ጊዜ ወላጆቼን አማከርኩ” ይላል። የያሬድ ወላጆች ‘መጥፎ ባልንጀርነት’ የሚያስከትለውን አደጋ ከጠቆሙለት በኋላ በስፖርት መካፈሉ ምን ያህል ጊዜውን እንደሚያባክንበት አሳሰቡት። (1 ቆሮንቶስ 15:33) “ነገሩ በዚህ ቆመ” በማለት ያሬድ በሐዘን ይናገራል። የወላጆቹን ምክር ቢከተልም ሳይጫወት መቅረቱ አሁንም ያሳዝነዋል።
‘ብዙ ነገር እየቀረብኝ ነው!’
አንተም በተመሳሳይ ያለህበት ሁኔታ ምንም ዓይነት ቢሆን የትምህርት ቤት ጓደኞችህ ስላሳለፉት ጊዜ በጉራ ሲናገሩ ቅር ሊልህ ይችላል። ‘ሌሎች ይህን ያህል እንዲደሰቱ የሚፈቀድላቸው ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አዎን፣ ብዙ ነገር እየቀረብኝ ነው የሚለውን በውስጥህ የሚፈጠር ስሜት እንዴት መቋቋም ትችላለህ?
መዝሙር 73ን ማንበብና የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የነበረው አሳፍ ያጋጠመውን ሁኔታ ማሰላሰል ሊጠቅምህ ይችላል። በቁጥር 2 እና 3 ላይ እንደሚከተለው በማለት ስለራሱ ተናዟል:- “እኔ ግን እግሮቼ ሊሰናከሉ፣ አረማመዴም ሊወድቅ ትንሽ ቀረ። የኃጢአተኞችን ሰላም አይቼ በዓመፀኞች ቀንቼ ነበርና።” አዎን፣ አሳፍ ከብዙ ነገሮች ተቆጥቦ ሲኖር ሌሎች ግን የፈለጉትን ሁሉ ሊያደርጉ እንደሚችሉ በጉራ ይናገሩ ነበር። ምንም መጥፎ ነገር የሚደርስባቸውም አይመስልም ነበር። ብዙ ብልጽግና ያላቸው ከመሆኑም በላይ ሀብታቸው ከቀን ወደ ቀን ይጨምር ነበር። (ቁጥር 12) አሳፍ በዚህ ምክንያት ቅሬታ ተሰምቶት “በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁ፣ እጆቼንም በንጽሕና በከንቱ አጠብሁ” ብሏል።— መዝሙር 73:13
ጥሩነቱ ግን አሳፍ ኋላ የሚጸጸትበት የችኮላ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ወደ አእምሮው ተመልሷል። “ወደ እግዚአብሔር መቅደስ” ከገባ በኋላ በዚያ ጤናማ አካባቢ ሆኖ ነገሮችን በጥሞና ማሰላሰል ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ደስታ አሳዳጅ የሆኑ አምላክ የለሽ ሰዎች ስለሚያጋጥማቸው ሁኔታ ጥሩ መደምደሚያ ላይ ሊደርስ ቻለ። “በድጥ ስፍራ አስቀመጥካቸው፣ ወደ ጥፋትም ጣልኻቸው” አለ።— መዝሙር 73:17, 18
ደስታ አሳዳጅ ስለሆኑ እኩዮችህም ተመሳሳይ ነገር መናገር ይቻላል። በአሁኑ ጊዜ ብዙ ደስታ እንደሚያገኙ ያስቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከኃጢአት የሚገኝ ደስታ ጊዜያዊ ነው። (ዕብራውያን 11:25) የመጽሐፍ ቅዱስን ሕግጋት ስለማይከተሉ “በድጥ ላይ” እንደቆሙ ናቸው። ሳያውቁትና ሳይጠነቀቁ ድንገተኛ ውድቀት ይደርስባቸዋል። የአምላክ ቃል “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳል” ይላል። (ገላትያ 6:7) በአንተ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች አለ ዕድሜያቸው በሞት እንደተቀጠፉ፣ በአባለ ዘር በሽታ እንደተለከፉ፣ ላልተፈለገ እርግዝና እንደተዳረጉ ወይም “ለደስታ” ሲሉ ባደረጉት መጥፎ ድርጊት ምክንያት እንደታሠሩ ሳትሰማ አትቀርም። ታዲያ እንደነዚህ ካሉ ነገሮች መራቅህ አልጠቀመህምን?— ኢሳይያስ 48:17
ሰሎሞን “ልብህ በኃጢአተኞች አይቅና፣ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር። በእውነት ፍጻሜ አለህና፣ ተስፋህም አይጠፋምና” በማለት ጥሩ ምክር ሰጥቷል። (ምሳሌ 23:17, 18) ማንኛውም ዓይነት “ደስታ” ቢሆን ገነት በምትሆነው ምድር ለዘላለም ከመኖር ተስፋህ ጋር ሊወዳደር አይችልም።
ይህ ተስፋ እውን እስከሚሆን ግን ተፈጥሮአዊ የሆነውን የመደሰት ፍላጎትህን አልፎ አልፎ ለማርካት የምትችለው እንዴት ነው? ሥነ ምግባር በጠበቀ ሁኔታ መደሰት የሚቻልባቸው መንገዶች አሉን? የገንዘብና የሌሎች ነገሮች ችግር ቢኖርብህስ? ንቁ! በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ አንዳንድ ወጣቶች በዚህ ረገድ ያላቸውን ሐሳብ እንዲገልጹ ጠይቆ ነበር። ይህን በዚሁ አምድ በሚወጣ ቀጣይ ጽሑፍ እናወጣለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በታኅሣሥ 22, 1995 እትም (የእንግሊዝኛ) “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . በሮክ ሙዚቃ ትርዒቶች መገኘት ይገባኛልን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል24]
ዓለም ደስታ ያስገኛሉ በሚላቸው ነገሮች ለመካፈል ባለመቻልህ ብዙ ነገር እንደቀረብህ ሆኖ ሊሰማህ ይገባልን?