ኤድስ በአፍሪካ—ሕዝበ ክርስትና ምን ያህል ተጠያቂ ናት?
በአፍሪካ የሚገኝ የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ “ሕዝበ ክርስትና” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ከመጽሐፍ ቅዱስ ክርስትና የተለየውን የስም ክርስትና ነው።
ሕዝበ ክርስትና
“በአብዛኛው ክርስቲያኖች ነን የሚሉ ሰዎች የሚኖሩባቸው የዓለም ክፍሎች።”— የዌብስተር ኒው ወርልድ ዲክሽነሪ
ኤድስ
“በሽታ ተከላካይ ሴሎች በሪትሮቫይረሶች በመለከፋቸው ምክንያት ሰውነት በሽታ የመከላከል ኃይሉ ሲጓደል የሚከሰት ሁኔታ።”— የዌብስተር ናይንዝ ኒው ኮሌጅዬት ዲክሽነሪ
ኤድስ መላውን ዓለም ያዳረሰ ወረርሽኝ ነው። እስከ አሁን ድረስ ኤድስ አምጪ በሆነው ኤች አይ ቪ የተለከፉ ሰዎች ቁጥር 17 ሚልዮን እንደሚደርስ ይገመታል። በተጨማሪም በፍጥነት በመዛመት ላይ የሚገኝ በሽታ ነው።
ከዚህ በሽታ ጋር ግንኙነት ስላላቸው የሕክምና፣ የፖለቲካና የስሜት ጥያቄዎች ብዙ ትኩረት የተሰጠ ቢሆንም በሽታው ስለሚያስነሳቸው ሃይማኖታዊ ጥያቄዎች እምብዛም ትኩረት አልተሰጠም። ሃይማኖት ከኤድስ ስርጭት ጋር ግንኙነት አለው የሚለው ሐሳብ ለብዙ አንባብያን የማይመስል ነገር ሆኖ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ በአፍሪካ አሕጉር የተከሰተውን ሁኔታ ከተመለከትን የማይመስል ነገር አይሆንም።
የኤድስ ወረርሽኝ በተለይ የአፍሪካን አሕጉር ክፉኛ አጥቅቷል።a አንዳንዶች እንደሚሉት ይህች አሕጉር ከዓለም ጠቅላላ የኤድስ በሽተኞች መካከል 67 በመቶ የሚሆኑት የሚኖሩባት ነች። በቻድ በትክክል የተመዘገቡ የኤድስ በሽተኞች ቁጥር ባለፉት አምስት ዓመታት 100 ጊዜ እጥፍ አድጓል። ይሁን እንጂ ከጠቅላላው የኤድስ በሽተኞች መካከል በትክክል የሚመዘገቡት አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ብቻ እንደሆኑ ተገምቷል። የዓለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት መሠረት በብዙ የአፍሪካ ከተሞች ኤድስ ለጎልማሶች ዋነኛው የሞት ምክንያት ሆኗል።
ሃይማኖት የተጫወተው ሚና አለን?
ክርስትና ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው ሃይማኖት ለዚህ እልቂት በኃላፊነት ሊጠየቅ እንደማይችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ከዚህ በታች እንደተመለከተው “ሕዝበ ክርስትና” የሚለው ቃል ሕዝቦች ክርስቲያን ነን የሚሉባቸውን አገሮች በሙሉ ያቅፋል። ስለዚህ ሕዝበ ክርስትና ኃላፊነት እንዳለባት የሚያጠያይቅ አይደለም። አብያተ ክርስተያናት የኤድስን ቫይረስ ፈጥረዋል ወይም በቀጥታ አሰራጭተዋል ለማለት አይደለም። ነገር ግን ኤድስ በአፍሪካ የተዛመተበት ዋነኛ ምክንያት ሕገወጥ የሆነ ሩካቤ ሥጋ ነው።b ስለዚህ ኤድስ የሥነ ምግባር ችግር ነው ሊባል ይችላል። በመሆኑም አንዳንድ አሳሳቢ የሆኑ ሃይማኖታዊ ጥያቄዎችን ያስነሳል። የአፍሪካ “ክርስትና” የምዕራብ አገሮች ክርስትና ተቀጽላ መሆኑን መካድ አይቻልም። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አፍሪካውያንን ወደራሳቸው ሃይማኖት የለወጡት የራሳቸው ሃይማኖት ከአፍሪካውያን ባሕላዊ አኗኗር የተሻለ ነው በማለት ነበር። ታዲያ የሕዝበ ክርስትና ተጽእኖ የአዳዲስ አማኞችን ሥነ ምግባር በእርግጥ ሊያሻሽል ችሏልን? የኤድስ ወረርሽኝ ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ነገር የተፈጸመ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ያረጋግጣል።
ለምሳሌ ያህል ቻድን እንውሰድ። ከዋነኞቹ አራት ከተሞች መካከል ሦስቱ በርካታ “ክርስቲያኖች” የሚኖሩባቸው ናቸው። አንደኛው ከተማ ግን ሙስሊሞች የሚበዙበት ነው። በአሁኑ ጊዜ የኤድስ ቫይረስ እንደ ሰደድ እሳት በመዛመት ላይ የሚገኘው በሦስቱ “የክርስቲያን” ከተሞች ነው! በመላው የአፍሪካ አሕጉር ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። የክርስቲያን አገሮች ናቸው በሚባሉት በማዕከላዊና በደቡባዊ አፍሪካ ያለው የኤድስ ስርጭት መጠን በአብዛኛው የሙስሊሞች መኖሪያ ከሆነው ከሰሜናዊ አፍሪካ በእጅጉ ይበልጣል።
አፍሪካ “ክርስቲያን” የሆነችው እንዴት ነው?
ይህ ቫይረስ የክርስቶስ ተከታዮች ነን በሚሉ ሕዝቦች መካከል በጣም ሊስፋፋ የቻለው ለምንድን ነው? ክርስቲያን ነን የሚሉ አፍሪካውያን ቁጥር በጣም ብዙ ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የክርስትና የሥነ ምግባር ደንቦች አክብረው የሚኖሩት ጥቂቶች ናቸው። እንዲህ ሊሆን የቻለው የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን አፍሪካውያንን ወደ ክርስትና “ለመመለስ” በተጠቀሙበት ዘዴ ምክንያት ይመስላል።
በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ዘመን ለረዥም ዘመናት ጸንቶ የኖረው የሕዝበ ክርስትና ባህላዊ እምነት ብዙ ጥቃት ደርሶበታል። የመጽሐፍ ቅዱስን ሥነ ጽሑፋዊ ታሪክ፣ የጸሐፊዎቹን ዓላማና ትርጉም ለማወቅ በተደረገው ሥነ ጽሑፋዊ ምርምር መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ሰዎች ዘንድ ተራ የሆነ የጥንት ሥነ ጽሑፍ ሆኖ እንዲታይ አድርጓል። በተጨማሪም የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ በብዙዎች ዘንድ፣ በቀሳውስት ሳይቀር ተቀባይነት ማግኘት ጀመረ። የጥርጣሬ ዘር ተዘራ። በቅዱሳን ጽሑፎች ማመን አጠያያቂ ነገር ሆነ። እንዲህ ያለ ሁኔታ በተስፋፋበት ጊዜ ሕዝበ ክርስትና አፍሪካውያንን ወደ ክርስትና “ለመለወጥ” ያደረገችው ጥረት ዓለማዊ መልክ ይዞ መገኘቱ የሚያስደንቅ አይደለም። የአብያተ ክርስቲያናት ሚስዮናውያን ወደ ክርስትና የተለወጡት ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ሕግጋት ጠብቀው እንዲኖሩ ከመርዳት ይልቅ ሰብዓዊ እርዳታዎችን በመስጠት ሥራ ላይ በማተኮር ማኅበራዊ ወንጌል ይሰብኩ ነበር። እንዲያውም ሚስዮናውያኑ ሳይታወቃቸው ቀደም ሲል የነበረውን የሥነ ምግባር ሕግ ተቀባይነት እንዲያጣ ምክንያት ሳይሆኑ አልቀሩም።
ለምሳሌ ያህል ከአንድ ሚስት በላይ ማግባት በብዙ የአፍሪካ ሥልጣኔዎች ባሕል ሆኖ የኖረ ልማድ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙ ጎሣዎች አመንዝሮችን የሚቀጡበት ጠንካራ ሕግ ስለነበራቸው ከጋብቻ ውጭ የሚደረግ ሩካቤ ሥጋ እምብዛም የተስፋፋ አልነበረም። በቻድ እውቅ የሆነ ጆሴፍ ዳርናስ የተባለ በጡረታ ላይ የሚገኝ አስተማሪ ለንቁ! እንደሚከተለው ብሏል:- “የቤተ ክርስቲያን ሚስዮናውያን ከመምጣታቸው በፊት ምንዝር መዓት ያስከትላል የሚል እምነት ነበር። በዚህም ምክንያት ምንዝር የፈጸሙ ሰዎች በማኅበረሰቡ ላይ መቅሰፍት ያመጣሉ ተብሎ ስለሚታመን እስከ ሞት የሚደርስ ከባድ ቅጣት ይደርስባቸው ነበር።” ይህ አጉል እምነት ነው ሊባል ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ከጋብቻ ውጭ ሩካቤ ሥጋ እንዳይፈጸም የተከላከለ እምነት ነበር።
የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን ከመጡ በኋላስ? ከአንድ ሚስት በላይ ማግባት ትክክል አለመሆኑን ቢሰብኩም የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ሕግጋት ተፈጻሚነት እንዲያገኙ ያደረጉት ነገር አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ ንስሐ ያልገቡ ዘማውያንና አመንዝሮች ከክርስቲያን ጉባኤ መወገድ እንደሚገባቸው ቢናገርም የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በሕግ ተላላፊዎች ላይ የወሰዱት የቅጣት እርምጃ አልነበረም። (1 ቆሮንቶስ 5:11-13) በአሁኑ ጊዜ እንኳን ታላላቅ የአፍሪካ ፖለቲከኞች ከሥነ ምግባር ውጭ በሆነ አኗኗራቸው የሚታወቁ ቢሆኑም ጥሩ የቤተ ክርስቲያን አባላት ሆነው ለመኖር ችለዋል። በአፍሪካ የስም ክርስቲያኖች ዘንድ ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆን እምብዛም የተለመደ አይደለም።
ከዚህም በላይ ቀሳውስት ራሳቸው የሚያሳዩት መጥፎ ምሳሌ አለ። በዚህ ለቤተሰብ ሕይወት ትልቅ ቦታ በሚሰጠው ባሕል አግብቶ ብዙ ልጆች መውለድ የተለመደና ተቀባይነት ያለው ልማድ ነው። ቁጥራቸው በጣም የበዛ የካቶሊክ ቄሶች በንጽሕናና በብሕትውና ለመኖር የገቡትን መሐላ መተላለፍ እንደሚችሉ ሆኖ የተሰማቸው በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በግንቦት 3, 1980 እትሙ “በብዙዎቹ የገጠር አካባቢዎች ቀሳውስትና ጳጳሳት ከአንድ በላይ ሚስቶች አሏቸው” በማለት ዘግቧል።
እንደነዚህ ያሉት ጋብቻዎች ሕጋዊ እውቅና የሌላቸው በመሆናቸው “ሚስቶቻቸው” በቁባትነት የሚኖሩ ናቸው። እንዲህ ያለውን ድርጊት እንደ ቀላል ነገር ተመልክቶ ማለፍ አይቻልም። ታይምስ መጽሔት እንዳለው “አንድ እውቅ የሆኑ የካቶሊክ ቄስ አፍሪካዊው ቄስ የሚታየው የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ እንደሆነ ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን ነው” ብለዋል። እነዚህ ‘ባለ ሥልጣኖች’ የሚያስተላልፉት መልእክት “የምናገረውን እንጂ የማደርገውን አታድርጉ” የሚል ይመስላል።
የምዕራባውያን መዝናኛዎች ያስከተሉት ወረራ
በተጨማሪም በቅርብ ዓመታት ወደ አፍሪካ የጎረፉት የብልግና መዝናኛዎች ያስከተሉት መዘዝ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ ነው። በቻድ ቁጥጥር የማይደረግባቸው የብልግና ቪዲዮዎች በግል ቤቶች፣ በጋራዦችና ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ደግሞ በግቢ ውስጥ ይታያሉ። እነዚህን ፊልሞች ለማየት የሚከፈለው ገንዘብ በጣም አነስተኛ ሲሆን ከ25 ሳንቲም አያልፍም። ትናንሽ ልጆች ሳይቀሩ ይመለከቷቸዋል። እነዚህ ፊልሞች የሚመጡት ከየት ነው? በአብዛኛው የክርስቲያን አገር ነች ከምትባለው ከዩናይትድ ስቴትስ ነው!
ይሁን እንጂ ይህ የምዕራባውያን የባሕል ወረራ በተመልካቾች ላይ ያስከተለው ውጤት አለ? አንድ በማዕከላዊ አፍሪካ ለ14 ዓመታት የኖረ የይሖዋ ምስክር ሚስዮናዊ እንዲህ ብሏል:- “የዚህ አካባቢ ሕዝቦች በቪዲዮ ካሴቶች ከሚመለከቱት ውጭ ስለ ምዕራቡ ዓለም ሊያውቁ የሚችሉበት መንገድ የለም። በእነዚህ ፊልሞች የሚያይዋቸውን ምዕራባውያን ለመምሰል ይፈልጋሉ። ለዚህ አባባሌ በዋቢነት የማቀርበው የጥናት ሰነድ ባይኖረኝም በዚህ አካባቢ ለምንኖረው በርካታ ሰዎች እንደነዚህ ያሉት መዝናኛዎች ወሲባዊ ብልግና እንዲስፋፋ የሚያበረታቱ እንደሆኑ ግልጽ ነው።”
የጤና ጥበቃ ባለ ሥልጣኖች ይህን ቀሳፊ የሆነ በሩካቤ ሥጋ የሚተላለፍ በሽታ ለመግታት መራራ ትግል በሚያደርጉበት ወቅት ክርስቲያን ነን የሚሉ ብሔራት ራስን ለኤድስ የሚያጋልጥ መጥፎ ሥነ ምግባር እንዲስፋፋ የሚያደርግ ፕሮፓጋንዳ እንዲስፋፋ ማድረጋቸው ግራ የሚገባ ነገር ነው! አብያተ ክርስቲያናት በየአገሮቻቸውም ሆነ ከአገሮቻቸው ውጭ የኤድስን ወረርሽኝ ለመግታት ያደረጉት ጥረት እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም እንደ ቻድና ካሜሩን ያሉ አንዳንድ የአፍሪካ መንግሥታት ሌላው ቢቀር የብልግና ፊልሞችና ጽሑፎች ወደ አገሮቻቸው እንዳይገቡ ለማገድ ሞክረዋል። ይሁን እንጂ ሙከራቸው ብዙም ሊሳካ አልቻለም።
በዚህ ሁሉ ምክንያት በአፍሪካ “ክርስቲያኖች” መካከል ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ውድቀት ይታያል። የኢኮኖሚ ድህነትም ያስከተለው ስውር ተጽእኖ አለ። ሥራ በቀላሉ ማግኘት ስለማይቻል ወንዶች ሥራ ለማግኘት ሲሉ ለበርካታ ወራት ከቤተሰቦቻቸው ርቀው ይኖራሉ። እንደነዚህ ያሉት ወንዶች በአካባቢያቸው በሚኖሩ ዝሙት አዳሪዎች በቀላሉ ይጠመዳሉ። ዝሙት አዳሪዎቹም ቢሆኑ ወደዚህ ኑሮ የተሰማሩት በድህነት ምክንያት ነው። በጣም ብዙ ጥሎሽ የሚጠይቁ ወላጆችም ለችግሩ ተጨማሪ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ብዙ ወንዶች የሚጠየቁትን ጥሎሽ መክፈል ስለማይችሉ ሳያገቡ ይኖራሉ። በዚህም ምክንያት በያጋጣሚው ከሚያገኟት ሴት ጋር የጾታ ግንኙነት እየፈጸሙ ይኖራሉ። እንዲህ ባለው የኢኮኖሚና የሥነ ምግባር ሁኔታ ምክንያት ኤድስ በከፍተኛ ፍጥነት ሊያድግ ችሏል።
የችግሩ መፍትሄ
በአፍሪካ ለተስፋፋው የኤድስ ወረርሽኝ ተወቃሽዋ ሕዝበ ክርስትና ብቻ እንዳልሆነች ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ አብዛኛው ኃላፊነት በእርስዋ ላይ የሚወድቅ ከመሆኑ ሐቅ መሸሽ አይቻልም። ይህ ደግሞ ኢየሱስ ‘በእውነት የሚያመልኩ’ ካላቸው ሰዎች መካከል ለመሆን ለሚፈልጉ ሁሉ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል።— ዮሐንስ 4:23
ተወቃሹ ማንም ይሁን ማን የኤድስን ወረርሽኝ ለመግታት ምን ማድረግ ይቻላል? የአፍሪካ መንግሥታት በኮንዶም መጠቀም እንዲስፋፋ በማድረግ የኤድስ መከላከያ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ናቸው። ይሁን እንጂ በናይጄርያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ የሆኑት ዶክተር ሳሙኤል ብሩው ግራቭስ “ግለሰቡ ጤናማ አኗኗር መልመድ ይኖርበታል። . . . ቤተሰቦችም ከወሲባዊ ውስልትና መራቅ አለባቸው” በማለት ግልጽ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ኤድስ እንዲህ እንደዛሬው የትንሽ የትልቁ መነጋገሪያ ከመሆኑ ከበርካታ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ሴሰኝነትን አውግዞ በንጽሕና መኖር፣ ራስን መግዛትና ለትዳር ጓደኛ ታማኝ ሆኖ መኖር አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል። (ምሳሌ 5:18-20፤ 1 ቆሮንቶስ 6:18) እነዚህን ሕግጋት ጠብቆ መኖር ከኤድስም ሆነ ከሌሎች በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች በጣም እንደሚጠብቅ በአፍሪካ የሚኖሩ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምስክሮች በማስረጃነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መስፈርቶች ጠብቀው መኖራቸው ሕዝበ ክርስትናን ያስወነጅላታል። በተጨማሪም እነዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ተስፋቸውን ‘ጽድቅ በሚኖርበት’ መጪ አዲስ ዓለም ላይ ጥለዋል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ለእምነት ሰዎች ኤድስ የተሟላ መፍትሔ የሚያገኘው በዚህ አዲስ ዓለም ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ኤድስ በአፍሪካ፣ ማቆሚያው ምን ይሆን?” የሚለውን የሐምሌ— መስከረም 1995 ንቁ! መጽሔት እትም ተመልከት።
b በሽታው ደም በመውሰድና ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች አንድ መርፌ በመጠቀም ሱስ የሚያስይዙ ዕፆችን በመወጋታቸው ምክንያት ሊተላለፍ ይችላል። አንዳንድ ንጹሐን ክርስቲያኖችም ወሲባዊ ውስልትና ከፈጸሙ ወይም ዕፆችን በደም ሥር ከወሰዱ የትዳር ጓደኞቻቸው ኤድስ ተጋብቶባቸዋል።
[በበገጽ 20 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በብዙ የገጠር አካባቢዎች . . . ቄሶችና ጳጳሳት ከአንድ የበለጡ ሚስቶች አግብተው ይኖራሉ።”
— ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የሚያሳዩት መጥፎ ምሳሌ በአፍሪካ ሴሰኝነት እንደ ሰደድ እሳት እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣቶች “ክርስቲያን” ከሆኑ አገሮች ለሚገቡ የብልግና መዝናኛዎች የተጋለጡ ናቸው