የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 11/8 ገጽ 21-24
  • በመጨረሻ እውነትን አገኘሁ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በመጨረሻ እውነትን አገኘሁ
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጠለቅ ያለ ሃይማኖታዊ ሥልጠና
  • በብጥብጥ መካከል
  • ዓለም ጦርነት ውስጥ ገባች
  • እውነትን ማግኘት
  • ውድ የሆነ መብት
  • ታላላቅ በረከቶች
  • ፈተናዎች ቢፈራረቁብኝም ተስፋዬ አልደበዘዘም
    ንቁ!—2002
  • በይሖዋ መታመንን ተምሬአለሁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • የፍል ውኃ መታጠቢያዎች የሞሉባት ምድር
    ንቁ!—2008
  • በስሎቫኪያ በእምነት ላይ የደረሰ ፈተና
    ንቁ!—2003
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 11/8 ገጽ 21-24

በመጨረሻ እውነትን አገኘሁ

በ1939 በነሐሴ ወር ማብቂያ ላይ ወደ ትውልድ አገሬ ወደ ሀንጋሪ፣ ቡዳፔስት ከተማ ስጓዝ ሞስኮ ላይ ትንሽ ቆይታ አደረግኩ። ከጥቂት ቀናት በፊት ማለትም በነሐሴ 23 ጀርመንና ሶቭየት አንዳቸው ሌላውን ላለመውረር የሰላም ውል ተፈራርመው ስለነበር የክሬምሊን ግንቦች በናዚ የስዋስቲካ ባንዲራዎች አሸብርቀዋል። ሩስያ የነበርኩት ለምንድን ነው? ወደ አገሬ ከተመለስኩ በኋላስ የገጠመኝ ሁኔታ ምን ነበር?

በመጀመሪያ ጥር 15, 1918 ላይ በተወለድኩባት በትንሿ የሀንጋሪ ከተማ በቬስፕሬም የነበረውን ሁኔታ ልንገራችሁ። ከአራት ልጆች መካከል የመጀመሪያው ስሆን ወላጆቻችን ዘወትር ወደ ቤተ ክርስቲያን እንድንሄድ ያደርጉ ነበር። አምስት ዓመት ሲሆነኝ በአንድ የሮማ ካቶሊክ ገዳም ውስጥ በሚካሄድ የቅዳሴ ሥርዓት ላይ አገለግል ነበር። ቤት ውስጥ ከወረቀት የሰራሁትን ልብስ በመልበስ በወንድሞቼና በእህቶቼ ፊት እንደ ቄስ ሆኜ እቀድስ ነበር።

ስምንት ዓመት ሲሞላኝ አባታችን ቤተሰቡን ጥሎ በመሄዱ እናታችን በእናቷ እርዳታ እየታገዘች እኛን ማሳደግ ጀመረች። በቀጣዩ ዓመት እናቴ በካንሰር በሽታ ሞተች። ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት የሙት ልጆች በሚረዱባቸው የተለያዩ ድርጅቶችና ማሳደጊያዎች ተበታተንን። በመጨረሻ የገባሁበት ማሳደጊያ ቡዳፔስት አቅራቢያ የሚገኝ ነበር። ይህ ማሳደጊያ ፍሬር ማሪስት (የማርያም ወንድሞች) በሚባል የፈረንሳይ የካቶሊክ አስተማሪዎች ሃይማኖታዊ ማኅበር የሚተዳደር ነበር። ለአምላክ ልባዊ ፍቅር ስለነበረኝ 13 ዓመት ሲሞላኝ በሃይማኖት ማኅበሩ የሚሰጠውን ትምህርት እንድማር የቀረበልኝን ሐሳብ ተቀበልኩ።

ጠለቅ ያለ ሃይማኖታዊ ሥልጠና

በቀጣዩ ዓመት ወደ ግሪክ ተላክሁ፤ በዚያም በአንድ የፍሬር ማሪስት ትምህርት ቤት በፈረንሳይኛ ቋንቋ የሚሰጠውንና ለአስተማሪነት የሚያበቃኝን ትምህርት ተከታተልኩ። ከአራት ዓመታት በኋላ በ1936 በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለማስተማር ብቁ ሆኜ በሠርተፊኬት ተመረቅኩ። ከተመረቅኩ በኋላ ሦስት ክፍሎችን አጣምሮ የያዘውን የድህነት፣ የታዛዥነትና የድንግልና መሐላ በመፈጸም በሃይማኖታዊ ማኅበሩ ውስጥ ወንድም ሆንኩ። ምንም እንኳ ወንድሞች የሆንነው ሃይማኖታዊ ልብስ የምንለብስና ሃይማኖታዊ ትምህርት የምንሰጥ ብንሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ፈጽሞ አጥንተን አናውቅም።

በዚያው ዓመት የበጋ ወር ላይ በቻይና እንዳስተምር ያቀረብኩት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ። ጥቅምት 31, 1936 በአንድ የመጓጓዣ መርከብ ተሳፍሬ ከፈረንሳይ ማርሴይ ከተማ ተነሳሁ። ታኅሣሥ 3, 1936 ሻንጋይ ደረስኩ። ከዚያም በሰሜናዊ ቻይና ወደምትገኘው ዋና ከተማ ወደ ቤጂንግ በባቡር ተጓዝኩ።

ከቤጂንግ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ተራራማ ክልል ፍሬር ማሪስት የተባለው ሃይማኖታዊ ማኅበር አንድ ትልቅ ትምህርት ቤት፣ ትልልቅ የመኝታ ክፍሎችና የእርሻ ቦታ ሕንፃዎች ነበሩት። ቦታው ንጉሠ ነገሥቱ የበጋ ወራትን በሚያሳልፉበት መኖሪያ አቅራቢያ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ ደስ የሚል የአትክልት ሥፍራና የፍራፍሬ ዛፎች ነበሩበት። እዚያ ከደረስኩ በኋላ የቻይናንና የእንግሊዝኛ ቋንቋዎችን በጥልቀት ማጥናት ጀመርኩ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተን አናውቅም።

በብጥብጥ መካከል

በ1930ዎቹ መጀመሪያ ላይ ጃፓን የቻይና አካል የሆነችውን ማንቹሪያን ያዘች። በሐምሌ 1937 የጃፓንና የቻይና ወታደሮች ቤጂንግ አቅራቢያ ጦር ተማዘዙ። ድል የተቀዳጁት ጃፓናውያን ራሳቸው የመረጧቸውን ቻይናውያን በመሾም አዲስ መንግሥት አቋቋሙ። ይህም በቻይና ደፈጣ ተዋጊዎችና በአዲሱ መንግሥት መካከል ውጊያ ቀሰቀሰ።

ከቤጂንግ ውጪ የሚገኘው ገዳማችን በፈረንሳይ ሥር እንዳለ ተደርጎ ይቆጠር ስለነበር ቀጥተኛ ጥቃት አልተሰነዘረበትም። ሆኖም ተባራሪ ጥይቶች ገዳማችን ላይ ይወድቁ ስለነበር በገዳማችን ውስጥ ተጠልለው ከነበሩት ከ5,000 በላይ የሚሆኑ ቻይናውያን መካከል የተወሰኑት ቆስለው ነበር። በዚህ ወቅት የቻይና ደፈጣ ተዋጊዎች የገጠሩን ክልል ያስተዳድሩ ነበር።

መስከረም 1937 ላይ ወደ 300 የሚጠጉ የቻይና ደፈጣ ተዋጊዎች መሣሪያ፣ ገንዘብና ምግብ ለማግኘት ሲሉ በሕንፃዎቻችን ላይ ጥቃት ሰነዘሩ። በመያዣነት ከታገቱት አሥር አውሮፓውያን መካከል አንዱ እኔ ነበርኩ። ከስድስት ቀናት በኋላ መጀመሪያ ከተለቀቁት ታጋቾች መካከልም አንዱ ነበርኩ። የተመረዘ ምግብ በልቼ በመታመሜ አንድ ወር ያህል ሆስፒታል ተኛሁ።

ከሆስፒታል ከወጣሁ በኋላ ቤጂንግ ውስጥ የተሻለ ጸጥታ ባለበት አካባቢ በሚገኝ በሃይማኖታዊ ማኅበሩ በሚተዳደር አንድ ሌላ ትምህርት ቤት እንዳስተምር ተዛወርኩ። በጥር 1938 በሻንጋይ እንዳስተምር ከተላክሁ በኋላ መስከረም ወር ላይ በቤጂንግ ለማስተማር እንደገና ተመለስኩ። ይሁን እንጂ ይህ የትምህርት ዓመት ከተገባደደ በኋላ ሃይማኖታዊ መሐላዬን አላደስኩም። ለሰባት ዓመታት ሃይማኖታዊ ሕይወትና ትምህርት ስከታተል ብቆይም እውነትን ለማግኘት ባደረግኩት ፍለጋ ልረካ አልቻልኩም። ስለዚህ ወደ ትውልድ አገሬ ወደ ቡዳፔስት ለመመለስ ሃይማኖታዊ ማኅበሩን ለቀቅኩ።

በዚያን ጊዜ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጥላውን እያጠላ ነበር። የበላዮቼ የነበሩት ፈረንሳውያን በሶቭየት ኅብረት የተወሰኑ ክፍሎች በኩል አድርጎ ሳይቤሪያን አቋርጦ የሚያልፈውን የባቡር መስመር እንድጠቀም አበረታቱኝ። ነሐሴ 27, 1939 ሞስኮ የደረስኩትና የክሬምሊን ግንቦች በናዚ ባንዲራዎች አጊጠው የተመለከትኩት በዚህ ጉዞ ወቅት ነበር።

ዓለም ጦርነት ውስጥ ገባች

ነሐሴ 31, 1939 ወደ ትውልድ አገሬ ቡዳፔስት ደረስኩ። በማግሥቱ ጀርመን ፖላንድን ወረረችና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀመረ። ከጊዜ በኋላ ጀርመን ከሶቭየት ኅብረት ጋር የተፈራረመችውን ውል በመጣስ ሰኔ 22, 1941 የሂትለር ሠራዊት ሶቭየት ኅብረትን ወረረ። ከተማዋን መያዝ ሳይችሉ ቢቀሩም እስከ ሞስኮ ዳርቻ ድረስ ሰብረው መግባት ችለው ነበር።

የሀንጋሪ አገረ ገዥ ከጀርመን ጋር የሰላም ስምምነት ተፈራረመና የጀርመን ሠራዊት በሀንጋሪ በኩል እንዲያልፍ ተፈቀደለት። በ1942 ካገባሁ በኋላ በ1943 በሀንጋሪ ጦር ውስጥ እንዳገለግል ተመለመልኩ። ሂትለር ለሚያካሂደው ጦርነት ሀንጋሪ የምትሰጠው ድጋፍ ስላላረካው መጋቢት 1944 ጀርመን ሀንጋሪን ወረረች። በዚያው ዓመት ወንድ ልጃችን ተወለደ። በቡዳፔስት ላይ ይወርድ ከነበረው የቦምብ ውርጅብኝ ለማምለጥ ሚስቴ ከወላጆቿ ጋር ለመኖር ልጃችንን ይዛ ወደ ገጠር ሄደች።

ጦርነቱ አቅጣጫውን በመቀየሩ የሶቭየት ጦር ሠራዊት ወደ ቡዳፔስት በመገስገስ ታኅሣሥ 24, 1944 ወደ ከተማዋ ደረሰ። በሩስያዎች ተያዝኩና የጦር ምርኮኛ ሆንኩ። በሺዎች የምንቆጠረው እስረኞች ሀንጋሪ ውስጥ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ ቦዮ በእግራችን እንድንጓዝ ተደረገ። እዚያ ስንደርስ በከብቶች ማጓጓዣ ባቡር ታጭቀን ወደ ቲሚሽዋራ ተወሰድንና በአንድ ትልቅ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ተከተትን። ከ45,000 እስረኞች መካከል ቢያንስ ቢያንስ 20,000 የሚሆኑት በ1945 መጀመሪያ ላይ በአንጀት ተስቦ ወረርሽኝ አልቀዋል።

በነሐሴ ወር በካምፑ ውስጥ የተረፉት 25,000 የሚሆኑ ምርኮኞች ወደ ሙት ባሕር ተወሰዱ። ከዚያም 20,000 የሚሆኑት ወደ ሶቭየት ኅብረት እንዲሄዱ ተደረገ። ይሁን እንጂ እኔን ጨምሮ 5,000 የምንሆነው የታመምን ሰዎች ወደ ሀንጋሪ ተመለስንና በነፃ ተለቀቅን። በምርኮኛነት ያሳለፍኳቸው ስምንት አስከፊ ወራት በዚህ መንገድ ተደመደሙ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ከሚስቴና ከልጄ ጋር ተገናኘንና ወደ ቡዳፔስት ሄደን በዚያ መኖር ጀመርን።

ከጦርነቱም በኋላ ብዙዎች ከሥቃይና ከመከራ መላቀቅ አልቻሉም። ምግብ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ የገንዘብ ዋጋ ማሽቆልቆሉ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሎ ነበር። በ1938 አንድ የሀንጋሪ ፔንጎ ይገዛው የነበረውን ነገር በ1946 ለመግዛት ከአንድ ኖኒሊየን (1,000,000,000,000,000,000,000,000,000,000) በላይ ፔንጎ ያስፈልግ ነበር! ከጊዜ በኋላ በአንድ ባቡር ጣቢያ ውስጥ የቢሮ ሥራ በማግኘቴ ኑሯችን ተሻሻለ።

እውነትን ማግኘት

በ1955 ቡዳፔስት ውስጥ እኛ በምንኖርበት ሕንጻ ላይ የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር ከሚስቴ ከአና ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት ጀመረ። መጽሐፍ ቅዱስ ሲኦል የመሰቃያ ቦታ ነው ብሎ እንደማያስተምር አና ስትነግረኝ እኔም የማጥናት ፍላጎት አደረብኝ። (መክብብ 9:5, 10፤ ሥራ 2:31) ካቶሊክ በነበርኩበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ አጥንቼ አላውቅም፤ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤቶች ልዩ ሥልጠና በወሰድኩበት ጊዜ እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ አላጠናሁም። እንደ እሳታማ ሲኦል ያሉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ የካቶሊክ ትምህርቶች እንዲሁ ነው የተቀበልኩት። ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች በተለይ ደግሞ ስለ አምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት አምላክ ምድርን ገነት ለማድረግ ያለውን ዓላማ እንዴት እንደሚፈጽም ለሚገልጹት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ፍቅር አደረብኝ። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ ሉቃስ 23:42, 43፤ ራእይ 21:3, 4) ከዚያ ቀደም ተሰምቶኝ የማያውቅ ልዩ የሆነ የደስታ ስሜት ተሰማኝ።

በዚያ ወቅት በሀንጋሪ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጹትን እውነቶች በድፍረት በማስተማራቸው እየታደኑ ይታሰሩ ነበር። ያገኘኋቸውን በሀንጋሪ ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎቻቸውን በሙሉ አነብ ነበር፤ ወደ ሀንጋሪ ቋንቋ ያልተተረጎሙ በእንግሊዝኛና በፈረንሳይኛ የተዘጋጁ ጽሑፎቻውንም ማግኘት ችዬ ነበር። እነዚህን ሁለት ቋንቋዎች በመማሬ እጅግ ተጠቅሜያለሁ!

ጥቅምት 1956 ሀንጋሪያውያን ሩስያዎች ባቋቋሙት የኮሙኒስት አገዛዝ ላይ ዓመፁ። በቡዳፔስት የነበረው ውጊያ የተፋፋመ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ ብዙዎች ከእስር ቤት ተለቀቁ። በዚህ ወቅት እኔና ሚስቴ ራሳችንን ለይሖዋ አምላክ መወሰናችንን ለማሳየት ተጠመቅን። ከአንድ ሳምንት በኋላ የሩስያ ወታደሮች አብዮቱን አፈኑት። ተለቀው የነበሩት ምሥክሮች እንደገና ወደ ወኅኒ እንዲወርዱ ተደረገ።

ውድ የሆነ መብት

በስብከቱ ሥራ ኃላፊነት የነበራቸው አብዛኞቹ ምሥክሮች ታስረው ስለነበር አንድ ክርስቲያን ወንድም ቀርቦ አነጋገረኝና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን በመተርጎሙ ሥራ የተወሰነ እርዳታ ማድረግ እችል እንደሆነ ጠየቀኝ። በመጀመሪያ በፈረንሳይኛ ታይፕ የተደረጉ የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎችን የያዙ የግል ደብዳቤዎች ከስዊዘርላንድ ይደርሱኝ ነበር። እነዚህን ጽሑፎች ወደ ሀንጋሪ ቋንቋ እተረጉምና የተተረጎሙት ጽሑፎች ቅጂዎች ለጉባኤዎች ይከፋፈሉ ነበር።

የሀንጋሪ ቅርንጫፍ ቢሮ አገልጋይ የሆነው ያኖሽ ኮኖራድ በክርስቲያናዊ ገለልተኝነቱ ምክንያት ለ12 ዓመታት ታስሮ በ1959 ሲለቀቅ ተርጓሚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። ከዚያም የሚተረጎም የእንግሊዝኛ ጽሑፍ ይደርሰኝ ጀመር። ብዙውን ጊዜ ጽሑፉ ይደርሰኝ የነበረው ስሟን በማላውቀው አንዲት መልእክተኛ አማካኝነት ነበር። በመሆኑም ብያዝና ብገረፍ ስሟን ማውጣት አልችልም ነበር።

መጠበቂያ ግንብ ከተረጎምኩ በኋላ ወንድም ኮኖራድ ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ ከእንግሊዝኛው ጋር ያስተያየው ነበር። ከዚያም እህቶች እስከ 12 የሚደርሱ ቅጂዎች ለማዘጋጀት ካርቦን በመጠቀም የተተረጎሙትን ጽሑፎች በስስ ወረቀት ላይ ታይፕ ያደርጓቸዋል። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ የሚገኙ ሁሉ በታይፕ የተጻፈ አንድ አንድ ቅጂ ይደርሳቸዋል። ከዚያም ቅጂዎቹን ለሌላ የጥናት ቡድን ያስተላልፉ ነበር። ብዙውን ጊዜ ግን ለእያንዳንዱ የጥናት ቡድን ማዘጋጀት የምንችለው አንድ የመጠበቂያ ግንብ ቅጂ ብቻ ነበር። ስለዚህ በጥናቱ ላይ የሚገኙት ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይቱ ሙሉ በሙሉ መጠቀም እንዲችሉ በጥሞና ማዳመጥና ማስታወሻ መያዝ ነበረባቸው።

መተርጎም ከጀመርኩበት ከ1956 አንስቶ እስከ 1978 ባሉት ጊዜያት መጠበቂያ ግንብ በሀንጋሪ ቋንቋ ይሰራጭ የነበረው በታይፕ እየተጻፈ ነበር። ከ1978 እስከ 1990 ድረስ ደግሞ በማባዣ መሣሪያ እየተባዛ ይሰራጭ ነበር። ከጥር 1990 ጀምሮ ደግሞ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ባለ ሙሉ ቀለም ሆነው ውብ በሆነ መንገድ በሀንጋሪ ቋንቋ እየታተሙ መውጣታቸው ታላቅ በረከት ነው!

በኮሙኒስቱ አገዛዝ ዘመን እያንዳንዱ ሰው የግድ ሰብዓዊ ሥራ ሊኖረው ይገባ ነበር። ስለዚህ በ1978 ከሰብዓዊ ሥራ ጡረታ እስከወጣሁበት ጊዜ ድረስ ለ22 ዓመታት የትርጉም ሥራውን አከናውን የነበረው ከሰብዓዊ የሥራ ሰዓቴ ውጪ ነበር። ብዙውን ጊዜ ይህን አደርግ የነበረው ማለዳ እየተነሳሁና ማታ እያመሸሁ ነበር። ጡረታ ከወጣሁ በኋላ በተርጓሚነት በሙሉ ጊዜ ማገልገል ጀመርኩ። በዚያ ወቅት እያንዳንዱ ተርጓሚ በየቤቱ ይሠራ የነበረ ሲሆን በእገዳው ምክንያት እርስ በርስ ግንኙነት ማድረጉ በጣም አስቸጋሪ ነበር። በ1964 ፖሊስ የተርጓሚዎችን ቤቶች በሙሉ በአንድ ጊዜ በመውረር ጽሑፎቻችንን ወረሰብን። ከዚያ በኋላ በርከት ላሉ ዓመታት ፖሊሶች በተደጋጋሚ ወደየቤታችን እየመጡ ይፈትሹ ነበር።

ታላላቅ በረከቶች

በ1969 ፓስፖርት እንዲሰጠኝ ያቀረብኩት ማመልከቻ ተቀባይነት በማግኘቱ “ሰላም በምድር” በተባለው ዓለም አቀፍ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከያኖሽ ኮኖራድ ጋር ወደ ፓሪስ መጓዝ ችዬ ነበር። ከሌሎች አገሮች የመጡ መሰል ምሥክሮችን ማግኘቱና በስዊዘርላንድ፣ በርን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የተወሰኑ ቀናት ማሳለፉ እንዴት ያለ ታላቅ በረከት ነበር! በ1970ዎቹ ዓመታት በሀንጋሪ ያሉ ብዙ ምሥክሮች በኦስትሪያና በስዊዘርላንድ በተካሄዱ ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ችለው ነበር።

መንግሥት ለብዙ ዓመታት እገዳ ጥሎ ከቆየ በኋላ በ1986 በቡዳፔስት ካመራርዶ ዩዝ ፓርክ ውስጥ የመጀመሪያውን በመንግሥት እውቅና ያገኘ ትልቅ ስብሰባ አደረግን። በስብሰባው ላይ ተገኝተው የነበሩ ከ4,000 የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች ከወንድሞቻቸውና ከእህቶቻቸው ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡና እንኳን ደህና መጣችሁ የሚለው ጽሑፍ በፓርኩ መግቢያ ላይ ተሰቅሎ ሲመለከቱ ዓይኖቻቸው የደስታ እንባ አቅርረው ነበር።

በመጨረሻ፣ ሰኔ 27, 1989 ላይ መንግሥት ለይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና ሰጠ። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ዜናው በሀንጋሪ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ሲበሰር የተሰማቸው ደስታ ወሰን አልነበረውም። በሥራችን ላይ እገዳ ከተጣለ ወደ 40 ከሚጠጋ ዓመት በኋላ በዚያ ዓመት የመጀመሪያዎቹን የአውራጃ ስብሰባዎቻችንን ያላንዳች ገደብ ማካሄድ ቻልን። በቡዳፔስት በተካሄደው ስብሰባ ላይ ከ10,000 የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች የተገኙ ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ በተካሄዱት በሌሎች አራት የአውራጃ ስብሰባዎችም ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ተገኝተዋል። ታናሽ ወንድሜ ላስሎና ሚስቱ በቡዳፔስት በመጠመቃቸው የተሰማኝ ደስታ ልዩ ነበር!

ከዚያም ሐምሌ 1991 አልመነው የማናውቀውን ታላቅ በረከት አገኘን፤ ከ40,000 የሚበልጡ ልዑካን በተገኙበት ቡዳፔስት ውስጥ በሚገኘው ግዙፍ ኔፕሽታዲዮን የአውራጃ ስብሰባ አደረግን። በዚያ ስብሰባ ላይ በብሩክሊን ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት የመጡ ወንድሞች ያቀረቧቸውን ንግግሮች የማስተርጎም መብት አግኝቻለሁ።

በአሁኑ ጊዜ እኔና አና እንዲሁም ከ50 የሚበልጡ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በቡዳፔስት ዳርቻ በሚገኘው ውብ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንሠራለን። በዚህ ቅርንጫፍ ቢሮ በትርጉም ክፍላችን ውስጥ ደስ ከሚሉ ወጣቶች ጋር በማገልገል ላይ ነኝ፤ አና ደግሞ በሕንጻዎቹ ውስጥ የቤት ውስጥ ሥራዎች ትሠራለች።

በልጃችን ልብ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመትከል ጥረት ብናደርግም ካደገ በኋላ እውነትን አልተቀበለም። ሆኖም አሁን ለእውነት ጥሩ አመለካከት ያለው በመሆኑ ውሎ አድሮ ይሖዋን ያገለግላል የሚል ተስፋ አለን።

እኔና ሚስቴ ስለ አፍቃሪው አምላክ ስለ ይሖዋ የሚገልጸውን እውነት በማግኘታችንና ከ40 ዓመታት በላይ ልናገለግለው በመቻላችን እጅግ ደስተኞች ነን።—ኤንድሬ ሳንዪ እንደተናገረው

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሚስቴ ጋር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ