ብዙዎች ደም ለመውሰድ የማይፈልጉበት ምክንያት
የኦንታሪዮ ፍርድ ቤት ታላቅ ምዕራፍ ከፋች በተባለለት ውሳኔው የካናዳ ቀይ መስቀልን ለሁለት ሰዎች በኤች አይ ቪ መለከፍ ተጠያቂ አድርጓል። ሰዎቹ በዚህ ቫይረስ ሊለከፉ የቻሉት ሁለቱም ከአንድ ሰው የተለገሰ የተበከለ ደም ስለተሰጣቸው ነበር። “የተበከለ ደምን በመሰለ አደገኛ ነገር የደም ወሳጆች ሕይወት አደጋ ላይ ሲወድቅ አፋጣኝ እርምጃ መውሰዱ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ዳኛው ስቴፈን ቦረንስ ተናግረዋል።
በ1980ዎቹ ዓመታት በተበከለ ደምና የደም ተዋፅኦ ምክንያት 1,200 የሚሆኑ ካናዳውያን በኤች አይ ቪ ሲለከፉ 12,000 የሚሆኑ ሌሎች ደግሞ ሄፐታይተስ ሲ በተባለው የጉበት በሽታ ተይዘዋል። በበሽታዎች የሚለከፉትን ሰዎች ቁጥር ለመቀነስ ሲባል በደም ለጋሾች ላይ ይበልጥ ጥንቃቄ የተሞላበት ምርመራ በመካሄድ ላይ ነው። ሆኖም ስለ ጾታ ምግባራቸው በሐቀኝነት የሚናገሩት ሁሉም ለጋሾች አይደሉም። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደ አንድ ጥናት ከ50 ደም ለጋሾች መካከል አንዱ ግብረ ሰዶምን ወይም ደግሞ ከዝሙት አዳሪ ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸምን የመሰሉ አደገኛ ሁኔታዎችን እንደሚሸሽግ አመልክቷል።
በደም ላይ የሚካሄደው ምርመራ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ አለመሆኑ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል። ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት እንዳለው ከሆነ “አንድ ሰው በኤች አይ ቪ ከተለከፈ በኋላ ባሉት ሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ደም ቢሰጥ ቫይረሶቹ በምርመራ ሊገኙ አይችሉም። ሄፐታይተስ ሲ ደግሞ እስከ ሁለት ወር ድረስ በምርመራ ውጤት ላይ ላይታይ ይችላል።”
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደም ለመስጠትም ሆነ ለመውሰድ ፈቃደኛ የሆኑ ካናዳውያን ቁጥር በእጅጉ እየቀነሰ መጥቷል። የአንድ ጋዜጣ ዓምድ አዘጋጅ የሆኑት ፖል ሽራትስ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ደም ለመለገስ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰና ደም መለገስ የማይችሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በሄደበት በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የደም ምትክ በሆኑ መድኃኒቶች ላይ በግንባር ቀደምትነት የሚያካሂዱት ምርምር ተመስገን የሚያሰኝ ነው።”
የሚያስገርመው ነገር ዘ ቶሮንቶ ስታር እንደዘገበው በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ 40 የሚጠጉ ሰዎች “በካናዳ ሆስፒታሎች ውስጥ ሕክምና ሲደረግላቸው ደም ላለመውሰድ ሲሉ በውሸት የይሖዋ ምሥክሮች ነን ብለዋል።” ጥናቶች እንዳመለከቱት 90 በመቶ የሚሆኑት ካናዳውያን የሌላ ሰው ደም ከመውሰድ ይልቅ ሌላ አማራጭ ሕክምና እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ ናቸው። በመሆኑም ደምን የመውሰድና ያለ መውሰድ ጉዳይ ሃይማኖታዊ ጥያቄ ብቻ መሆኑ እየቀረ ነው።