ኤድስን እንዴት መከላከል ይቻላል?
በአሁኑ ጊዜ ኤድስን ሊፈውስ የሚችል መድኃኒት የለም። የሕክምና ሳይንስም በቅርቡ ፈዋሽ መድኃኒት ያገኛል ተብሎ አይታሰብም። የበሽታውን እድገት የሚያዘገዩ አዳዲስ መድኃኒቶች ቢኖሩም ገና ከመጀመሪያው በሽታውን ማስወገዱ ከሁሉ የተሻለ ነው። በሽታውን ስለመከላከል ከመነጋገራችን በፊት የኤድስ ቫይረስ (ኤች አይ ቪ) ከሰው ወደ ሰው የሚጋባበትንና የማይጋባበትን መንገድ እንመልከት።
አንድ ሰው በአራት ዋና ዋና መንገዶች በኤድስ ቫይረስ ሊለከፍ ይችላል:- (1) በተበከለ መርፌ ወይም ሲሪንጅ በመጠቀም፣ (2) በበሽታው ከተለከፈ ሰው ጋር ማንኛውንም ዓይነት ወሲባዊ ግንኙነት በመፈጸም፣ (3) ደምንና የደም ተዋዕጾዎችን በመውሰድ፤ እርግጥ ነው በአሁኑ ጊዜ በበለጸጉ አገሮች ለበሽተኞች የሚሰጥ ደም አስቀድሞ የኤች አይ ቪ ፀረ እንግዳ አካል ያለው መሆኑ አስቀድሞ ስለሚጣራ በዚህ መንገድ የሚመጣው አደጋ በእጅጉ ቀንሷል፣ (4) በኤች አይ ቪ የተለከፈች እናት ከመውለድዋ በፊት ወይም በወሊድ ጊዜ ወይም በምታጠባበት ጊዜ ወደ ልጅዋ በማስተላለፍ።
የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (ሲ ዲ ሲ) እንደሚለው እስካሁን በተገኘው ሳይንሳዊ መረጃ መሠረት የኤድስ ቫይረስ (1) ጉንፋንና ኢንፉሌንዛ በሚጋባበት መንገድ አይጋባም፣ (2)ኤድስ በያዘው ሰው አጠገብ በመቀመጥ ወይም የኤድስን ሕመምተኛ በመንካት ወይም በማቀፍ አይጋባም፣ (3) በበሽታው የተለከፈ ሰው የነካውን፣ ያዘጋጀውን ወይም ያቀረበውን ምግብ በመብላት አይጋባም፣
(4) በሽንት ቤት፣ በስልክ፣ በልብስ ወይም በመመገቢያና በመጠጫ ዕቃ አይጋባም። ከዚህም በላይ ቫይረሱ በትንኝ ወይም በሌላ በማንኛውም ዓይነት ነፍሳት አማካኝነት እንደማይጋባ ሲ ዲ ሲ ይናገራል።
ቁልፍ የሆኑ የመከላከያ ዘዴዎች
የኤድስ ቫይረሶች በሕመምተኛው ደም ውስጥ ተሸሽገው ይቀመጣሉ። ቫይረሱ ያለበት ሰው መርፌ ከተወጋ ቫይረሱ ያለባቸው ጥቂት የደም ቅንጣቶች በመርፌው ወይም በሲሪንጁ ውስጥ ይቀራሉ። በዚህ መንገድ በተበከለው መርፌ ሌላ ሰው ሲወጋ ቫይረሱ ሊተላለፍበት ይችላል። ስለምትወጉበት መርፌ ወይም ሲሪንጅ ከተጠራጠራችሁ ዶክተሩን ወይም ነርሷን ከመጠየቅ ወደ ኋላ አትበሉ። የማወቅ መብት አላችሁ፤ የሕይወት ጉዳይ ነውና።
በተጨማሪም የኤድስ ቫይረስ በቫይረሱ በተለከፉት ሰዎች የወንዴ ዘር ፈሳሽ ወይም በሴት ብልት ፈሳሽ ውስጥ ይገኛል። በዚህም ምክንያት ሲ ዲ ሲ የሚከተለውን የመከላከያ ምክር ይሰጣል:- “ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ የሆነው የመከላከያ ዘዴ ከወሲባዊ ግንኙት ጨርሶ መታቀብ ብቻ ነው። ወሲባዊ ግንኙነት የምትፈጽሙ ከሆነ በቫይረሱ ካልተበከለ ግለሰብ ጋር እንደ ጋብቻ ያለ ዘላቂነት ያለውና አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ የምትሆኑበት ዝምድና እስከምትመሠርቱ ድረስ ቆዩ።”
ኤድስን ለመከላከል “አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ የምትሆኑበት ዝምድና” መኖር እንዳለበት አስተውሉ። አንዳችሁ ታማኝ ብትሆኑና ተጓዳኛችሁ ግን ታማኝ ባይሆን ከአደጋ የተጠበቃችሁ አትሆኑም። ይህ ሁኔታ ወንዶች በወሲባዊ ግንኙነትም ሆነ በኢኮኖሚ የበላይነት በሚኖራቸው ኅብረተሰቦች ውስጥ በሚኖሩ ሴቶች ላይ ችግር ይፈጥራል። በአንዳንድ አገሮች ሴቶች ችግር ስለማያስከትል ወሲባዊ ግንኙነት ከወንዶች ጋር መደራደር ይቅርና ስለ ወሲብ መነጋገር እንኳን አይፈቀድላቸውም።
ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ አቅመ ቢሶች የሆኑት ሁሉም ሴቶች አይደሉም። በአንድ ምዕራብ አፍሪካ በሚገኝ አገር የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው በገንዘብ ረገድ ራሳቸውን የቻሉ ሴቶች ብዙ ጠብ ሳይፈጠር በኤድስ ቫይረስ ከተለከፉ ባሎቻቸው ጋር ወሲብ ከመፈጸም ለመታቀብ ችለዋል። በኒው ጀርሲ፣ ዩ ኤስ ኤ አንዳንድ ሴቶች ወንድዬው ኮንዶም ለማድረግ እምቢተኛ ከሆነ ወሲብ ላለመፈጸም ወስነዋል። ከላቴክስ የተሠሩ ኮንዶሞች ከኤች አይ ቪ እና ከሌሎች የአባለ ዘር በሽታዎች መከላከል ቢችሉም በአግባቡና ያለማሰለስ መደረግ ይኖርባቸዋል።
ምርመራ መደረግ የሚኖርበት መቼ ነው?
ከዚህ በፊት በነበረው ጽሑፍ ላይ የተጠቀሰችው ካረን ራሷን ከበሽታው ለመከላከል ማድረግ የምትችለው ነገር አልነበረም። ባልዋ የተለከፈው ከመጋባታቸው ከበርካታ ዓመታት በፊት ሲሆን የተጋቡት ደግሞ የኤድስ ወረርሽኝም ሆነ የኤች አይ ቪ ምርመራ ገና ባልተስፋፋበት ጊዜ ነበር። አሁን ግን በአንዳንድ አገሮች የኤች አይ ቪ ምርመራ የተለመደ ሂደት ሆኗል። ስለዚህ አንድ ሰው በኤች አይ ቪ ረገድ የሚጠራጠረው ነገር ከኖረ ከተቃራኒ ጾታ ጋር መቀጣጠርና አብሮ መዋል ከመጀመሩ በፊት ምርመራ ቢያደርግ ጥበብ ይሆናል። ካረን የሚከተለውን ምክር ትሰጣለች:- “የትዳር ጓደኛ የሚሆናችሁን ሰው በጥንቃቄ ምረጡ። የተሳሳተ ምርጫ ብታደርጉ ከባድ ኪሣራ፣ አዎን ሕይወት እስከማጣት የሚያደርስ ኪሣራ ሊያደርስባችሁ ይችላል።”
ምንዝር በሚፈጸምበት ጊዜ ምርመራ ማድረጉ ንጹሕ የሆነውን ወገን ከበሽታ ሊጠብቅ ይችላል። አንድ ሰው በኤች አይ ቪ ቫይረስ ከተለከፈ እስከ ስድስት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ በበሽታው መያዙን በምርመራ ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ ስለማይቻል ተደጋጋሚ ምርመራ ማድረጉ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። የጾታ ግንኙነት ማድረግ ከጀመሩ (ይህም ምንዝር የፈጸመው ወገን ይቅር መባሉን ያመለክታል) በኮንዶም መጠቀም በበሽታው ከመለከፍ ሊጠብቅ ይችላል።
ትምህርት ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው የኤድስ ወረርሽኝ ከመከሰቱ ከብዙ፣ ብዙ ዓመታት በፊት ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ጠብቆ መኖር ከበሽታ ሊጠብቅ ይችላል። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ከጋብቻ ውጭ ወሲብ መፈጸምን ያወግዛል፣ ባለ ትዳሮች አንዳቸው ለሌላው ታማኝ እንዲሆኑ ያዝዛል እንዲሁም ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንደነርሱ የሚያከብሩ ግለሰቦችን ብቻ ማግባት እንደሚኖርባቸው ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 7:39፤ ዕብራውያን 13:4) በተጨማሪም አካልን የሚያረክስ ማንኛውንም ነገር ደም መውሰድንም ቢሆን ይከለክላል።—ሥራ 15:20፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1
ኤች አይ ቪ ከያዘው ግለሰብ ጋር የሚኖረን ንክኪ ምን ዓይነት አደጋዎች ሊያስከትል እንደሚችል በቂ ትምህርት ማግኘትም ጥበብ ነው። ሰዎች ስለ ኤድስ በቂ ትምህርት ካገኙ ራሳቸውን ከበሽታው መጠበቅ ይችላሉ።
ኤድስ አክሽን ሊግ የተባለው ድርጅት እንዲህ ይላል:- “አብዛኛውን ጊዜ ራስን ከኤድስ መጠበቅ ይቻላል። ፈዋሽ መድኃኒት እስከሚገኝለት ድረስ ከሁሉ የሚሻለውና ለጊዜው ያለን የኤድስ መከላከያ ትምህርት ነው።” (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ወላጆች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከልጆቻቸው ጋር ስለ ኤድስ በግልጽ ቢነጋገሩ ጥሩ ነው።
ምን የሕክምና አማራጮች አሉ?
አብዛኛውን ጊዜ የበሽታ ምልክቶች መታየት የሚጀምሩት አንድ ሰው በኤች አይ ቪ ከተለከፈ ከስድስት እስከ አሥር ዓመት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ነው። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በአካሉ ውስጥ ከፍተኛ ውጊያ ሲካሄድ ይቆያል። እያንዳንዱ ቫይረስ እየተባዛ በሽታ ተከላካይ ሴሎችን መግደል ይጀምራሉ። በሽታ ተከላካይ ሴሎችም የበኩላቸውን ውጊያ ያካሂዳሉ። ውሎ ሲያድር ግን በየቀኑ በቢልዮን የሚቆጠሩ አዳዲስ ቫይረሶች ሲፈጠሩ በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ተሸንፈው እጃቸውን ይሰጣሉ።
በሽታ ተከላካይ ሴሎችን ይረዳሉ የሚባሉ የተለያዩ መድኃኒቶች ተሠርተዋል። የእነዚህ መድኃኒቶች ስሞች በጣም ረዥምና ለማንበብ የሚከብዱ በመሆናቸው የሚታወቁት በምሕጻረ ቃላት ነው። ኤ ዜድ ቲ፣ ዲ ዲ አይ እና ዲ ዲ ሲ ይባላሉ። እነዚህ መድኃኒቶች አስደናቂ ውጤት እንደሚያስገኙና እንዲያውም ሊፈውሱ እንደሚችሉ ያመኑ ሰዎች ቢኖሩም ተስፋቸው ሁሉ እንደ ጠዋት ጤዛ ረግፎ ጠፍቷል። የመድኃኒቶቹ ኃይል ከጊዜ በኋላ እየተዳከመ ከመሄዱም በላይ በአንዳንድ ሰዎች ላይ የደም ሴሎች መመናመን፣ የደም መርጋት ችግር፣ የእጅና የእግር ነርቮች መዳከምና የመሳሰሉትን ከባድ ችግሮች አስከትለዋል።
አሁን ደግሞ ፕሮቲየስ ኢንሂቢተርስ የሚባሉ የመድኃኒት ዓይነቶች ተገኝተዋል። ዶክተሮች ሦስት ዓይነት መድኃኒቶች ከሌሎች ፀረ ቫይረስ መድኃኒቶች ጋር እንዲወሰዱ ያዛሉ። ይህ ዓይነቱ ባለ ሦስት ጣምራ ሕክምና ቫይረሶቹን ባይገድልም በሰውነት ውስጥ የሚያደርጉትን መራባት እንደሚቀንስ ወይም ጨርሶ እንደሚያስቆም በምርመራ ተረጋግጧል።
ባለ ሦስቱ ጣምራ ሕክምና በበሽተኞች ላይ ከፍተኛ የሆነ መሻሻል አስገኝቷል። ይሁን እንጂ ሕክምናው ጥሩ ውጤት የሚያስገኘው ቀደም ተብሎ፣ የበሽታው ምልክቶች ከመታየታቸው በፊት ከተሰጠ እንደሆነ ሊቃውንቱ ያምናሉ። በዚህ ጊዜ ከተሰጠ ኢንፌክሽኑ ወደ ኤድስነት ደረጃ እንዳይሸጋገር ለረዥም ጊዜ፣ ምናልባትም ላልተወሰነ ጊዜ መከላከል ይቻላል። ሕክምናው ገና አዲስ በመሆኑ ኢንፌክሽኑን ተቆጣጥሮ ሊያቆይ የሚችለው ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ የሚታወቀው ገና ወደፊት ነው።
ባለ ሦስቱ ጣምራ ሕክምና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው። የሦስት ፀረ ቫይረስ መድኃኒቶችና የላቦራቶሪ ምርመራ ዋጋ በዓመት በአማካኝ 12,000 ዶላር (ወይም 85,000 ብር) ይደርሳል። ከገንዘቡ ውድነት በተጨማሪ ባለ ሦስት ጣምራ ሕክምና የሚወስድ በሽተኛ በቀን ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት ወደ ማቀዝቀዣ ደጋግሞ መሄድ ይኖርበታል። ምክንያቱም መድኃኒቶቹ መቀመጥ ያለባቸው በማቀዝቀዣ ውስጥ ነው። በሽታው የያዘው ሰው አንዳንዶቹን መድኃኒቶች በቀን ሁለት ጊዜ ሌሎቹን ደግሞ በቀን ሦስት ጊዜ መውሰድ ይኖርበታል። አንዳንዶቹ መድኃኒቶች በባዶ ሆድ የሚወሰዱ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ከምግብ በኋላ የሚወሰዱ ናቸው። ከዚህም በላይ የኤድስ በሽተኛ ለብዙ ኢንፌክሽኖች የተጋለጠ ስለሚሆን ለእነዚህ በሽታዎች ተጨማሪ መድኃኒቶች በሚወስድበት ጊዜ ሕክምናው ይበልጥ የተወሳሰበ ይሆናል።
ዶክተሮችን በዋነኛነት የሚያሳስባቸው አንድ በሽተኛ ባለ ሦስቱን ጣምራ ሕክምና ቢያቋርጥ ምን ይሆናል የሚለው ነው። ቫይረሶቹ አላንዳች እንቅፋት መራባት ይጀምራሉ። በዚህም ምክንያት ከሕክምናው የተረፉት ቫይረሶች ግለሰቡ ከዚያ ቀደም ይወስዳቸው የነበሩትን መድኃኒቶች የመቋቋም ኃይል ያላቸው ይሆናሉ። መድኃኒቶችን የመቋቋም ችሎታ ያዳበሩትን ቫይረሶች ማከም ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆናል። ከዚህም በላይ እነዚህ ጉልበተኛ ቫይረሶች ወደ ሌሎች ሰዎች ሊተላለፉ ይችላሉ።
መፍትሔው ክትባት ይሆን?
ዓለም አቀፉን የኤድስ ወረርሽኝ ለመግታት ቁልፉ ጉዳት የማያስከትልና ውጤታማ የሆነ ክትባት ማግኘት ብቻ እንደሆነ አንዳንድ የኤድስ ተመራማሪዎች ያምናሉ። አቅማቸው እንዲዳከም ከተደረጉ ቫይረሶች ቢጫ ወባን፣ ኩፍኝን፣ ጆሮ ደግፍንና የጀርመን ኩፍኝን (rubella) የሚከላከሉ አስተማማኝ ክትባቶች ተሠርተዋል። አቅሙ የተዳከመ ቫይረስ ወደ ሰውነት እንዲገባ በሚደረግበት ጊዜ የሰውነት በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ቫይረሶቹን ከመግደላቸውም በተጨማሪ ትክክለኞቹ ቫይረሶች ጥቃት በሚሰነዝሩበት ጊዜ ሰውነት ሊያሸንፋቸው የሚያስችለውን መከላከያ ገንብተው ይቆያሉ።
በቅርቡ በዝንጀሮዎች ላይ የተደረጉ ሁለት ጥናቶች እንዳመለከቱት ኤች አይ ቪን አስቸጋሪ የሚያደርገው፣ የተዳከመው ቫይረስ እንኳን ተለውጦ ገዳይ ሊሆን መቻሉ ነው። በሌላ አነጋገር ክትባቱ ራሱ እንዲከላከል የታሰበውን በሽታ ሊያመጣ ይችላል።
ክትባት ለማግኘት የተደረገው ጥረት ሁሉ ከንቱና ተስፋ አስቆራጭ ሆኗል። ኤች አይ ቪ ሌሎች ቫይረሶችን ሊገድሉ እንደሚችሉ በተመሰከረላቸው በደርዘን የሚቆጠሩ መድኃኒቶች ሊበገር አልቻለም። ከዚህ በላይ ደግሞ ኤች አይ ቪ በየጊዜው ስለሚለዋወጥ በቀላሉ ዒላማ ውስጥ ሊገባ አልቻለም። (በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ቢያንስ አሥር የሚያክሉ የኤች አይ ቪ ዝርያዎች አሉ።) ችግሩን ይበልጥ የሚያባብሰው ደግሞ ቫይረሱ በክትባቱ ይጎለብታሉ ተብለው የታሰቡትን በሽታ ተከላካይ ሴሎች በቀጥታ የሚያጠቃ መሆኑ ነው።
በተጨማሪም የገንዘብ ጉዳይ በሚደረጉት ምርምሮች ላይ ጫና ያሳድራል። በዋሽንግተን የሚገኘው ዓለም አቀፍ የኤድስ ክትባት እንቅስቃሴ “ከግሉ ክፍለ ኢንዱስትሪ የተሰጠው ትኩረት በጣም ዝቅተኛ ነው” ይላል። ይህ የሆነው ክትባቱ በአብዛኛው የሚሸጠው ባልበለጸጉ አገሮች ስለሚሆን ብዙ ትርፍ አያስገኝም የሚል ሥጋት ስላለ ነው።
በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ተመራማሪዎች ክትባት ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት አላቆሙም። በአሁኑ ሁኔታ ግን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ክትባት የሚገኝ አይመስልም። ተስፋ የተጣለበት ክትባት ከቤተ ሙከራዎች ብቅ ቢል እንኳን ብዙ ድካም፣ ወጪና አደጋ ሊያስከትል የሚችል ሙከራ በሰዎች ላይ መደረግ ይኖርበታል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በኤች አይ ቪ በመለከፍ ላይ ያሉት እነማን ናቸው?
በመላው ዓለም በየቀኑ 16,000 የሚያክሉ ሰዎች ይለከፋሉ። ከእነዚህ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት በታዳጊ አገሮች የሚኖሩ እንደሆኑ ይነገራል። ከአሥሩ አንዱ ዕድሜው ከ15 ዓመት በታች የሆነ ሕፃን ነው። የቀሩት ለአካለ መጠን የደረሱ ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በ15 እና በ24 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።—የዓለም ጤና ድርጅትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤች አይ ቪ/ኤድስ ጥምር ፕሮግራም
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንድ ሰው በበሽታው መለከፉ እንዴት ይታወቃል?
አንድን ሰው ከውጭ በማየት ብቻ በቫይረሱ የተለከፈ መሆኑንና አለመሆኑን ለማወቅ አይቻልም። የበሽታው ምልክቶች ገና ያልታዩባቸው የኤች አይ ቪ ተሸካሚዎች ፍጹም ጤነኛ መስለው ቢታዩም ቫይረሱን ወደ ሌሎች ሰዎች ሊያስተላልፉ ይችላሉ። አንድ ሰው ቫይረሱ ፈጽሞ ሊኖረኝ አይችልም ስላለ ብቻ ታምኑታላችሁ? ላይታመን ይችላል። ብዙዎቹ ኤች አይ ቪ ያለባቸው ሰዎች ቫይረሱ ያለባቸው መሆኑን ራሳቸው እንኳን አያውቁም። ቢያውቁም እንኳን ሊደብቁ ወይም ሊዋሹ ይችላሉ። በዩናይትድ ስቴትስ በተደረገ አንድ ጥናት በኤች አይ ቪ ከተለከፉ 10 ሰዎች መካከል አራቱ ስለ ሁኔታቸው ለወሲብ ጓደኞቻቸው እንዳልተናገሩ ታውቋል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የኤች አይ ቪ እና የኤድስ ዝምድና
ኤች አይ ቪ “ሂውማን ኢምዩኖዴፊሽየንሲ ቫይረስ” የሚለውን የእንግሊዝኛ ስያሜ የሚወክል ምህጻረ ቃል ሲሆን የሰውነትን በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ቀስ በቀስ ለሚያጠፉት ቫይረሶች የተሰጠ ስያሜ ነው። ኤድስ ደግሞ “አኳየርድ ኢምዩኖዴፍሽየንሲ ሲንድረም” ማለት ነው። ይህ የኤች አይ ቪ ኢንፌክሽን መጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሶ ለሞት በሚያቃርብበት ጊዜ የሚኖረውን ሁኔታ የሚያመለክት ነው። ይህ ስም ኤች አይ ቪ በሰውነት በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማስከተሉ ምክንያት በሽተኛው ጤነኛ በነበረበት ጊዜ በበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት አማካኝነት በቀላሉ ይቋቋማቸው ለነበሩት በሽታዎች መሸነፉን ያመለክታል።
[ምንጭ]
CDC, Atlanta, Ga.
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ ጋብቻ ከማሰብ በፊት የኤች አይ ቪ ምርመራ ማድረግ ጥበብ ነው