የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 9/8 ገጽ 3-5
  • መክዳት የሚያስከትለው አስከፊ መዘዝ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መክዳት የሚያስከትለው አስከፊ መዘዝ
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የስሜት ናዳ
  • ንዴትና የስሜት መረበሽ
  • የጥፋተኝነት ስሜትና የመንፈስ ጭንቀት
  • እጥፍ በደል
  • ዕርቅ ሊወርድ ይችላልን?
    ንቁ!—1999
  • ምርጫችሁ ፍቺ በሚሆንበት ጊዜ
    ንቁ!—1999
  • ከፍቺ ጋር በተያያዘ ልታውቋቸው የሚገቡ አራት ነገሮች
    ንቁ!—2010
  • ትዳር በቋፍ ላይ በሚሆንበት ጊዜ
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 9/8 ገጽ 3-5

መክዳት የሚያስከትለው አስከፊ መዘዝ

ስልክ ደወለና “ከዛሬ ጀምሮ ተለያይተናል” አላት። የፓትa ባል ከዚህ ቀደም እንዲህ ቅስም የሚሰብር ነገር ተናግሯት አያውቅም ነበር። “ጆሮዬን ማመን አልቻልኩም” ስትል ተናግራለች። “ባሌ ሌላ ወድዶ ጥሎኝ እንዳይሄድ በጣም እሰጋ ነበር። የፈራሁት አልቀረም ጥሎኝ ሄደ።”

የ33 ዓመቷ ፓት ትዳሯ የሰመረ እንዲሆን ከልቧ ትመኝ ነበር፤ ባሏ ፈጽሞ ጥሏት እንደማይሄድ አረጋግጦላት ነበር። “ምንም ይምጣ ምን ላንለያይ ተማምለን ነበር” ስትል ፓት ወደ ኋላ መለስ ብላ በማስታወስ ትናገራለች። “ከልቡ ቃል እንደገባልኝ አድርጌ አስቤ ነበር። ግን አልሆነም። አሁን ብቻዬን ነኝ። የቤት እንስሳ እንኳ የለኝም!”

ሂሮሺ እናቱ ከሌላ ሰው ጋር የጀመረችው አጓጉል ግንኙነት ይፋ የወጣበትን ቀን ፈጽሞ አይረሳውም። “ገና የ11 ዓመት ልጅ ነበርኩ” ሲል መለስ ብሎ ያስታውሳል። “እማዬ በንዴት እየተንደረደረች መጣች። አባዬ ከኋላ ከኋላዋ እየተከተለ ‘እስቲ አትጣደፊ። መጀመሪያ እንነጋገርበት’ ይላት ነበር። አንድ ትልቅ ችግር እንደተፈጠረ ተረዳሁ። አባዬ ቅስሙ ተሰበረ። ሙሉ በሙሉ ማገገም አልቻለም። በዚህ ላይ ደግሞ የልቡን ሊያካፍለው የሚችለው ሰው አልነበረውም። ስለዚህ ችግሩን ሁሉ ለእኔ ያካፍለኝ ጀመር። በ40ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰው ከ11 ዓመት ልጁ ማጽናኛና አዘኔታ ለማግኘት ሲጥር የሚኖረውን ሁኔታ እስቲ አስቡት!”

በትዳር ላይ መወስለት የንጉሣውያን ቤተሰቦችን፣ የፖለቲከኞችን፣ የፊልም ተዋንያንንና የሃይማኖት መሪዎችን ሕይወት በማናጋትም ሆነ ቤተሰቦችን ከፍተኛ ሐዘን ላይ በመጣል በአሁኑ ጊዜም ከባድ ኪሳራ በማስከተል ላይ ይገኛል። “ምንዝር” ይላል ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ፣ “በእጅጉ የተስፋፋ ከመሆኑም በላይ በአንዳንድ ሁኔታዎች የትዳርን ያህል የተለመደ ነገር ሆኗል።” አንዳንድ ተመራማሪዎች ከ50 እስከ 75 በመቶ የሚሆኑት ባለ ትዳሮች በአንድ ወቅት በትዳራቸው ላይ እንደወሰለቱ ይገምታሉ። በትዳር ሕይወት ላይ ጥናት የሚያካሄዱት ዜልዳ ዌስት-ሚድስ አብዛኛው ውስልትና ተሸፋፍኖ የሚቀር ቢሆንም እንኳ “በትዳር ላይ የመማገጥ ልማድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ ማስረጃዎቹ ይጠቁማሉ” ብለዋል።

የስሜት ናዳ

በትዳር ላይ የሚፈጸመውን ውስልትናና ፍቺን በተመለከተ የሚወጡት አኃዛዊ መረጃዎች አስደንጋጭ ቢሆኑም እንኳ እነዚህ ሁኔታዎች በሰዎች ዕለታዊ ሕይወት ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ አይደሉም። እነዚህ ሁኔታዎች የሚያስከትሉትን ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ወደ ጎን ትተን ከእነዚህ አኃዛዊ መረጃዎች በስተጀርባ ያለውን የስሜት መደቆስ፣ እንደ ጎርፍ የሚፈሰውን እንባ፣ የሚፈጠረውን ከፍተኛ የስሜት ዝብርቅ፣ ሐዘን፣ ጭንቀትና ሥቃይ እንዲሁም የቤተሰቡ አባላት ስሜታቸው በጣም ከመረበሹ የተነሳ እንቅልፍ በዓይናቸው ሳይዞር የሚያሳልፏቸውን በርካታ ሌሊቶች ለአንድ አፍታ አስቡት። ተጠቂዎቹ ከዚህ ሥቃይ ማገገም ቢችሉም እንኳ የደረሰባቸው የመንፈስ ስብራት ለረጅም ጊዜ አብሯቸው ሊኖር ይችላል። ቁስሉ በቀላሉ አይሽርም።

“ብዙውን ጊዜ ትዳር ሲፈርስ ከፍተኛ የስሜት ግንፋሎት ማስከተሉ አይቀርም” ሲል ሃው ቱ ሰርቫይቭ ዲቮርስ የተባለው መጽሐፍ ይገልጻል፤ “ይህ የስሜት ግንፋሎት አንዳንድ ጊዜ ምናባዊ ዕይታህን የሚጋርድ ሊሆን ይችላል። ማድረግ ያለብህ ነገር ምንድን ነው? ምን ዓይነት ምላሽ ነው የምትሰጠው? ይህን ፈታኝ ሁኔታ መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው? አንዴ እርግጠኛ ትሆናለህ አንዴ ትጠራጠራለህ፣ አንዴ በቁጣ ትገነፍላለህ አንዴ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማሃል፣ አንዴ እምነት ያድርብሃል አንዴ ደግሞ በጥርጣሬ ዓይን ማየት ትጀምራለህ።”

ፔድሮ ሚስቱ ታማኝነቷን ማጉደሏን ሲያውቅ የተሰማው የዚህ ዓይነት ስሜት ነበር። “በትዳር ላይ ውስልትና ሲፈጸም ግራ የሚያጋቡ ስሜቶች ይፈራረቁብሃል” ሲል ተናግሯል። ሁኔታውን ብዙም የማይረዱት በጉዳዩ ውስጥ የሌሉበት ሰዎች ይቅርና ራሳቸው የችግሩ ሰለባዎችም የሚደርስባቸውን የስሜት ቀውስ ለመረዳት አዳጋች ይሆንባቸዋል። “የሚሰማኝን ስሜት ሊረዳልኝ የሚችል ሰው የለም” ስትል ፓት ተናግራለች። “ባሌ ከእሷ ጋር መሆኑን ሳስበው ለማንም ልገልጸው የማልችለው ከባድ አካላዊ ሕመም ይሰማኛል።” እንዲህ ስትል አክላ ተናግራለች:- “አንዳንድ ጊዜ የማብድ ሆኖ ይሰማኛል። ዛሬ ሁኔታውን መቋቋም እንደምችል ሆኖ ከተሰማኝ ነገ ሁሉ ነገር ከአቅሜ በላይ ሆኖ ይታየኛል። ዛሬ ሲናፍቀኝ ከዋለ ነገ ደግሞ የሸረበው ሴራ፣ ውሸቱና የደረሰብኝ ውርደት ወደ አእምሮዬ እየመጣ ይበጠብጠኛል።”

ንዴትና የስሜት መረበሽ

እንዲህ ዓይነት በደል የደረሰበት አንድ ሰው “አንዳንድ ጊዜ በንዴት ትበግናለህ” ሲል ተናግሯል። ንዴቱ የሚመጣው በተፈጸመው ስህተትና ድርጊቱ ባስከተለው ጉዳት ብቻ አይደለም። ይልቁንም አንዲት ጋዜጠኛ እንደገለጸችው “እጅግ አስደሳች ሊሆን ይችል የነበረ ትዳር መፍረሱም ያበሳጫል።”

በተጨማሪም እንዲህ ዓይነት ሰዎች ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የሚመለከቱ ከመሆኑም በላይ ለምንም ነገር እንደማይበቁ ሆኖ ይሰማቸዋል። ፔድሮ እንዲህ ሲል በግልጽ ተናግሯል:- “‘እኔ ማራኪ ሰው አይደለሁም ማለት ነው? የሚጎድለኝ ነገር አለ?’ የሚል ስሜት ወደ አእምሮህ ይመጣል። ጉድለትህን ለማግኘት ራስህን መመርመር ትጀምራለህ።” የብሪታንያ ብሔራዊ የትዳር መምሪያ ምክር ቤት ባልደረባ የሆኑት ዜልዳ ዌስት-ሚድስ ቱ ላቭ፣ ኦነር ኤንድ ቢትሬይ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “በጣም ፈታኝ ከሆኑት ነገሮች አንዱ . . . ለራስህ ያለህ አክብሮት በእጅጉ የሚቀንስ መሆኑ ነው” ሲሉ አረጋግጠዋል።

የጥፋተኝነት ስሜትና የመንፈስ ጭንቀት

ብዙውን ጊዜ እነዚህን ስሜቶች ተከትሎ የሚመጣው ነገር ከባድ የጥፋተኝነት ስሜት ነው። በሐዘን ስሜት የተዋጠች አንዲት ሚስት “በጥፋተኝነት ስሜት በእጅጉ የሚሰቃዩት ሴቶች ይመስሉኛል። ‘ምን አጥፍቼ ይሆን?’ ብለህ ራስህን ትወቅሳለህ።”

ሚስቱ የከዳችው አንድ ባል ድንገተኛ የስሜት ለውጥ ብሎ የገለጸውን ሌላ ገጽታ ጠቁሟል። “የመንፈስ ጭንቀት ድንገት እንደ ጭጋግ ጥላውን ያጠላባችኋል” ሲል ተናግሯል። አንዲት ሚስት ባሏ ጥሏት በሄደ ጊዜ ሳታለቅስ የዋለችበት አንድም ቀን እንዳልነበረ ታስታውሳለች። “ባሌ ጥሎኝ ከሄደ ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ምንም ሳላለቅስ የዋልኩበትን የመጀመሪያ ቀን በደንብ አስታውሰዋለሁ” ስትል ተናግራለች። “ምንም ሳላለቅስ አንድ ሙሉ ሳምንት ማሳለፍ የቻልኩት ደግሞ ከተወሰኑ ወራት በኋላ ነበር። እነዚያ ምንም ሳላለቅስ ያሳለፍኳቸው ቀናትና ሳምንታት ማገገም የቻልኩበትን አዲስ የሕይወት ምዕራፍ የከፈቱ ነበሩ።”

እጥፍ በደል

ብዙውን ጊዜ ምንዝር የፈጸመው ግለሰብ በትዳር ጓደኛው ላይ እጥፍ በደል መፈጸሙን ብዙዎች አይገነዘቡም። በደሉ እጥፍ የሚሆነው በምን መንገድ ነው? ፓት “በጣም ከብዶኝ ነበር። ለብዙ ዓመታት ባሌ ብቻ ሳይሆን የቅርብ ጓደኛዬም ጭምር ነበር” ስትል ገልጻለች። አዎን፣ አብዛኛውን ጊዜ ሚስት ችግሮች ሲገጥሟት የባሏን እርዳታ ለማግኘት ትጥራለች። በዚህ ጊዜ ግን ከፍተኛ የስሜት ቀውስ የሚያስከትልባት ከመሆኑም በላይ ከእሱ ታገኘው የነበረውን እጅግ አስፈላጊ የሆነ እርዳታም እንድታጣ ያደርጋታል። የአእምሮ ሰላሟንም ሆነ የምትተማመንበትን የምሥጢር ጓደኛዋን በአንድ ጊዜ ታጣለች።

በመሆኑም በትዳር ጓደኞቻቸው እንዲህ ዓይነት በደል የደረሰባቸው ሰዎች የተፈጸመባቸው ክህደትና እምነት የማጉደል ድርጊት አእምሯቸውን ክፉኛ ይበጠብጠዋል። አንዲት የትዳር አማካሪ በትዳር ላይ የሚፈጸም ውስልትና ስሜትን ሊያሽመደምድ የሚችለው ለምን እንደሆነ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “እምነት ልንጥልበትና ድጋፍ ሊሆነን የሚችል ሰው በመፈለግ . . . እምነታችንን፣ ተስፋችንንና ሕልማችንን ሁሉ በትዳር ላይ እንጥላለን። . . . እምነታችንን የጣልንበት ነገር ሁሉ በአንድ ጊዜ እንዳልነበረ ከሆነ ግን የተማመንበት ነገር ሁሉ ንፋስ ጠራርጎ እንደወሰደው በካርቶን የተሠራ ቤት ይሆናል።”

ሃው ቱ ሰርቫይቭ ዲቮርስ በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው ተጠቂዎቹ “የሚሰማቸውን የተዘበራረቀ ስሜት ለማስተካከል እርዳታ ያስፈልጋቸዋል . . . ምን ምርጫ ሊያደርጉ እንደሚችሉና ምርጫቸውን እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ለመወሰን ይችሉ ዘንድ እርዳታ ያስፈልጋቸው ይሆናል።” ይሁን እንጂ ያሏቸው ምርጫዎች ምንድን ናቸው?

‘ዕርቅ መፍጠሩ የተሻለ ይሆን? ወይስ መፋታት ይሻላል?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። በተለይ ትዳሩ ውጥረት ነግሶበት ከነበረ ለችግሩ መፍትሔው ፍቺ ነው ብለህ በችኮላ ለመወሰን ልትፈተን ትችላለህ። ‘መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን በትዳር ላይ ውስልትና ከተፈጸመ ፍቺን ይፈቅዳል’ ብለህ ታስብ ይሆናል። (ማቴዎስ 19:9) በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ የግድ ፍቺ መፈጸም አለበት እንደማይል ታስብ ይሆናል። በመሆኑም ዕርቅ ፈጥሮ ትዳሩን እንደገና መገንባቱና ማጠናከሩ የተሻለ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል።

የወሰለተውን የትዳር ጓደኛ መፍታት አለመፍታቱ የግል ውሳኔ ነው። ሆኖም ምን ብታደርግ እንደሚሻል ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ዕርቅ ማውረድ ይቻል እንደሆነና እንዳልሆነ ማወቅ እንድትችል የሚረዱህን አንዳንድ ነገሮች መርምር።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ