ዕርቅ ሊወርድ ይችላልን?
“በግብታዊነት ለፍቺ መነሳት ቀላል ነው” ይላል “ካፕልስ ኢን ክራይስስ” የተባለው መጽሐፍ፤ “ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት ቢደረግ ግን አስደሳችና የተዋጣላቸው ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ትዳሮች አሉ።”
ይህ አስተያየት ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቺን አስመልክቶ ከሰጠው ብዙ ዘመናት ያስቆጠረ ትምህርት ጋር ይስማማል። በትዳር ላይ በተፈጸመ ውስልትና ሳቢያ በደሉ የተፈጸመበት ወገን የትዳር ጓደኛውን ሊፈታ እንደሚችል የገለጸ ቢሆንም እንኳ እንዲህ ማድረጉ ግዴታ ነው አላለም። (ማቴዎስ 19:3-9) ታማኙ የትዳር ጓደኛ ትዳሩን ከውድቀት ለመታደግ እንዲሞክር የሚገፋፉ ምክንያቶች ይኖሩት ይሆናል። በዳዩ አሁንም ሚስቱን ይወድ ይሆናል።a ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟልቶ የሚያቀርብ አሳቢ ባልና አፍቃሪ አባት ሊሆን ይችላል። ታማኟ የትዳር ጓደኛ የራሷንና የልጆቿን ፍላጎቶች ግምት ውስጥ በማስገባት ከመፋታት ይልቅ ዕርቅ ማውረዱን ትመርጥ ይሆናል። እንደዚህ ለማድረግ የምትመርጥ ከሆነ ሊጤኑ የሚገባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ትዳሩን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የሚያጋጥሙ ፈታኝ ሁኔታዎችን በተሳካ ሁኔታ መወጣት የሚቻለውስ እንዴት ነው?
ከሁሉ በፊት ፍቺም ሆነ ዕርቅ ቀላል አለመሆኑን መጥቀሱ ተገቢ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ አመንዝራውን የትዳር ጓደኛ እንዲሁ ይቅር ብሎ ማለፍ በትዳሩ ውስጥ ላሉት መሠረታዊ ችግሮች መፍትሔ አይሆንም። ብዙውን ጊዜ አንድን ትዳር ከውድቀት ለማዳን ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶ በሚገባ ራስን መመርመር፣ በግልጽ መነጋገርና ተግቶ መሥራት ይጠይቃል። አብዛኛውን ጊዜ ባልና ሚስቶች የሻከረን የትዳር ግንኙነት መልሶ ለመገንባት ምን ያህል ጊዜና ጉልበት እንደሚጠይቅ አይገነዘቡም። ሆኖም ብዙዎች ያለመታከት ጥረት በማድረጋቸው የኋላ ኋላ የሰከነ ትዳር መምራት ችለዋል።
መልስ የሚያሻቸው ጥያቄዎች
አንዲት ታማኝ የትዳር ጓደኛ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ማድረግ እንድትችል ስሜቶቿንና ያሏትን አማራጮች ቆም ብላ መመርመር ይኖርባታል። እንዲህ እያለች ራሷን ብትጠይቅ ጥሩ ሊሆን ይችላል:- መመለስ ይፈልጋል? ከሌላዋ ሴት ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቋርጧል ወይስ ይህን እርምጃ ወዲያውኑ መውሰድ ከብዶታል? ይቅርታ ጠይቋል? ጠይቆ ከሆነ በፈጸመው ድርጊት ከልቡ በመጸጸት እውነተኛ ንስሐ ገብቷል? ወይስ ለፈጸመው ድርጊት እኔን ተጠያቂ ለማድረግ ይሞክራል? በፈጸመው በደል ከልቡ አዝኗል? ወይስ ያበሳጨው ነገር ሕገ ወጥ ግንኙነቱ ይፋ መውጣቱና መፋለሱ ነው?
ስለ ወደፊቱ ጊዜስ ምን ማለት ይቻላል? ምንዝር ለመፈጸም ያበቁትን አመለካከቶችና ድርጊቶች ማረም ጀምሯል? ስህተቱን ላለመድገም ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል? ወይስ አሁንም የማሽኮርመምና ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተገቢ ያልሆነ ስሜታዊ ቅርርብ የመፍጠር ዝንባሌ ይታይበታል? (ማቴዎስ 5:27, 28) ትዳሩን መልሶ የመገንባት ልባዊ ፍላጎት አለው? ካለው ይህን የሚያሳይ ምን ነገር እያደረገ ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ ማግኘቱ ትዳሩን መልሶ መገንባት ይቻላል ብሎ ለማመን የሚያበቃ መሠረት ሊሆን ይችላል።
ወሳኝ የሆነ የሐሳብ ልውውጥ
“ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል” ሲል አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ገልጿል። (ምሳሌ 15:22) የተበደለችው የትዳር ጓደኛ ስለተፈጸመው ውስልትና ከባሏ ጋር መነጋገር እንዳለባት በሚሰማት ጊዜ ይህ አባባል በእጅጉ ይሠራል። ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ጠልቆ መግባት ባያስፈልግ እንኳ እውነቱን ለማውጣትና የተሳሳቱ ግምታዊ ሐሳቦችን ለማስወገድ በሐቀኝነትና ከልብ በመነጨ ስሜት ሊወያዩ ይችላሉ። ባልና ሚስቱ እንዲህ ማድረጋቸው የተሳሳተ ግምት አድሮባቸውና ቅሬታቸውን ለረጅም ጊዜ በውስጣቸው አምቀው ይዘው ይበልጥ እየተራራቁ እንዳይሄዱ ጥሩ መከላከያ ሊሆናቸው ይችላል። እርግጥ ነው፣ ባልየውም ሆነ ሚስትየዋ እንዲህ ዓይነቱን ውይይት ማድረጉ በጣም ሊከብዳቸው ይችላል። ሆኖም ብዙዎች ይህን የመሰለ ውይይት ማድረግ እርስ በርስ የመተማመንን መንፈስ መልሶ በማስፈን ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተገንዝበዋል።
ስኬታማ ዕርቅ ለማውረድ ሌላው ሊወሰድ የሚገባ እርምጃ በትዳሩ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ማለትም ሁለቱም የትዳር ጓደኞች ሊያሻሽሏቸው የሚገቡ ነገሮችን ለይቶ ለማወቅ መጣር ነው። ዜልዳ ዌስት-ሚድስ የሚከተለውን ምክር ሰጥተዋል:- “በጉዳዩ ላይ በደንብ ተወያይታችሁ ሕገወጥ ግንኙነቱ ሙሉ በሙሉ እንደቆመ ከተሰማችሁና ትዳራችሁ እንዲቀጥል የምትፈልጉ ከሆነ መስተካከል ያለበትን ነገር ሁሉ ለማስተካከልና ትዳሩን ለማደስ ጣሩ።”
ምናልባት አንዳችሁ ለሌላው ብዙም አድናቆት አይኖራችሁ ይሆናል። መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ችላ ተብለው ሊሆን ይችላል። አንድ ላይ ሆናችሁ በቂ ጊዜ አታሳልፉ ይሆናል። የትዳር ጓደኛችሁ የሚያስፈልገውን ያህል ፍቅራችሁን፣ ከልብ የመነጨ አሳቢነታችሁን፣ ምስጋናችሁንና አክብሮታችሁን አትገልጹለት ይሆናል። አንድ ላይ ሆናችሁ ግቦቻችሁንና የምትመሩባቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች መለስ ብላችሁ መመርመራችሁ ይበልጥ የሚያቀራርባችሁ ከመሆኑም በላይ ወደፊት ተመሳሳይ የሆነ ውስልትና እንዳይፈጸም ለመከላከል ይረዳል።
ሙሉ በሙሉ ይቅር ለማለት መጣር
በደል የደረሰባት የትዳር ጓደኛ ከልቧ ጥረት ብታደርግም እንኳ ባሏንም ሆነ ከባሏ ጋር የማገጠችውን ሴት ይቅር ለማለት ልትቸገር ትችላለች። (ኤፌሶን 4:32) ሆኖም ቀስ በቀስ ቅሬታንና ብስጭትን ማስወገድ ይቻላል። “ታማኙ የትዳር ጓደኛ ቅሬታውን ሁሉ አስወግዶ አዲስ ሕይወት የሚጀምርበት ወቅት እንደሚመጣ መገንዘብ አለበት” ሲል አንድ መጽሐፍ ምክር ለግሷል። “በመካከላችሁ ክርክር በተነሳ ቁጥር የቀድሞ ኃጢአቱን እያነሱ የትዳር ጓደኛን ማቁሰል ተገቢ አይደለም።”
ብዙ ባለ ትዳሮች በውስጣቸው የታመቀውን ሥር የሰደደ ቅሬታ ለማለዘብና ብሎም ለማጥፋት ጥረት በማድረግ ውሎ አድሮ በደሉን በፈጸመባቸው የትዳር ጓደኛቸው ላይ ያደረባቸውን የጥላቻ ስሜት ማስወገድ ችለዋል። እንዲህ ማድረጉ ትዳርን መልሶ ለመገንባት ወሳኝ እርምጃ ነው።
እንደገና እምነት መጣልን መማር
“በመካከላችን የነበረውን እርስ በርስ የመተማመን መንፈስ መልሰን መገንባት እንችል ይሆን?” ስትል አንዲት መንፈሷ በጣም የተረበሸ ሚስት ጭንቀቷን ገልጻለች። ያመነዘረው ባሏ የፈጸመው የማታለል ድርጊት በእሱ ላይ የነበራትን እምነት ያንኮታኮተው ወይም ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ያመነመነው በመሆኑ መስጋቷ አግባብነት ያለው ነው። በአንድ ሰው ላይ ያለን እምነት ልክ እንደ አንድ ውድ የሸክላ ዕቃ በቀላሉ የሚሰበር መልሶ ለመጠገን ግን በእጅጉ የሚያስቸግር ነገር ነው። አንድ ዝምድና ከውድቀት እንዲድን ብቻ ሳይሆን እየጠነከረ እንዲሄድ ከተፈለገ እርስ በርስ የመተማመንና የመከባበር መንፈስ ሊኖር ይገባል።
ብዙውን ጊዜ ይህ ሁኔታ እንደገና እምነት መጣልን መማር ይጠይቃል። ጥፋተኛው የትዳር ጓደኛ እምነት ሊጣልብኝ ይገባል በማለት በጭፍን ከሚያስብ ይልቅ ስለሚያደርገው እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ግልጽና ሐቀኛ በመሆን እንደገና የመተማመን መንፈስ እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላል። ክርስቲያኖች ‘ውሸትን እንዲያስወግዱና እርስ በርሳቸው እውነትን እንዲነጋገሩ’ ተመክረዋል። (ኤፌሶን 4:25) የትዳር ጓደኛህን አመኔታ ለማትረፍ እንድትችል መጀመሪያ “ስለምታደርገው እንቅስቃሴ ምንም ሳታስቀር ሐቁን ንገራት” ይላሉ ዜልዳ ዌስት-ሚድስ። “የት እንደምትሄድና መቼ እንደምትመለስ ንገራት። እሄዳለሁ ወዳልከው ቦታ ለመሄድህ እርግጠኛ መሆን አለብህ።” ዕቅድህን ከለወጥክ አሳውቃት።
ተበዳዩ ወገን ቀደም ሲል ለራሱ የነበረውን ጥሩ ግምት መልሶ ለመገንባት ጊዜና ጥረት ሊጠይቅበት ይችላል። ጥፋተኛው የትዳር ጓደኛ ሚስቱን እንደሚያደንቃትና እንደሚወዳት አዘውትሮ በመግለጽ ፍቅሩን የሚያካፍላትና የሚያሞግሳት ከሆነ ለራሷ ጥሩ ግምት እንዲያድርባት ሊረዳት ይችላል። አንዲት የታወቀች የትዳር አማካሪ የሚከተለውን ምክር ሰጥታለች:- “ለምታደርገው ነገር ሁሉ አመስግኑአት።” (ምሳሌ 31:31 የ1980 ትርጉም) ሚስትየዋም በምታከናውናቸው ጥሩ ጥሩ ነገሮች ላይ በማተኮር በራስ የመተማመንን ባሕርይ መልሳ ለመገንባት ጥረት ማድረግ ትችላለች።
ጊዜ ይወስዳል
በትዳር ላይ የሚፈጸም ውስልትና ከሚያስከትለው ከባድ ሥቃይ አንጻር ሲታይ ከብዙ ዓመታት በኋላም አእምሮን የሚረብሹ ተቀርጸው የቀሩ ትዝታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ቁስሉ ቀስ በቀስ እየጠገገ ሲሄድ ሁለቱም ትሕትና፣ ትዕግሥትና ጽናት በማሳየት በመካከላቸው እርስ በርስ የመተማመንንና የመከባበርን መንፈስ መልሰው መገንባት ይችላሉ።—ሮሜ 5:3, 4፤ 1 ጴጥሮስ 3:8, 9
ቱ ላቭ፣ ኦነር ኤንድ ቢትሬይ የተባለው መጽሐፍ “በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ላይ የሚኖረው ከባድ ሥቃይ ለረጅም ጊዜ አይዘልቅም” ሲል ያረጋግጣል። “ቀስ በቀስ እየከሰመ ይሄዳል . . . እንዲያውም ከጊዜ በኋላ ለቀናት፣ ለሳምንታት፣ ለወራት አልፎ ተርፎም ለዓመታት ምንም ትዝ ላይላችሁ ይችላል።” የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በትዳራችሁ ውስጥ ተግባራዊ ማድረጋችሁንና የአምላክን በረከትና አመራር ለማግኘት መጣራችሁን ስትቀጥሉ ‘አእምሮን ሁሉ የሚያልፈው የእግዚአብሔር ሰላም’ ዕረፍት እንደሚሰጣችሁ ምንም ጥርጥር የለውም።—ፊልጵስዩስ 4:4-7, 9
“ወደ ኋላ መለስ ብዬ ስመለከት” ይላል ፔድሮ፣ “የደረሰው ሁኔታ የኑሮ ጎዳናችንን እንደለወጠው መገንዘብ ችያለሁ። አሁንም ቢሆን አልፎ አልፎ ትዳራችንን በመጠኑ ማደስ ያስፈልገናል። ሆኖም ከባዱን የፈተና ጊዜ አልፈነዋል። አሁን አብረን በደስታ በመኖር ላይ ነን።”
ይሁን እንጂ ተበዳይዋ በትዳሩ ላይ የወሰለተውን ባሏን ይቅር ለማለት የምትችልበት መሠረት ባይኖራትስ? ወይም ደግሞ ቅሬታዋን ሙሉ በሙሉ በማስወገድ ባሏን ይቅር ብትለውም እንኳ አጥጋቢ በሆኑ ምክንያቶች የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ በሚፈቅደው መሠረት ለመፋታት ብትመርጥስ?b ፍቺ ምን ነገሮች ሊጠይቅ ይችላል? ፍቺ ምን ነገሮችን እንደሚያስከትልና አንዳንዶች እነዚህን ነገሮች እንዴት መቋቋም እንደቻሉ ተመልከት።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a አንባቢዎችን ግራ ላለማጋባት ስንል ሚስትን ታማኝ የትዳር ጓደኛ አድርገን ተጠቅመናል። ይሁን እንጂ የተጠቀሱት መሠረታዊ ሥርዓቶች ሚስቶቻቸው ለከዷቸው ባሎችም ይሠራሉ።
b እባክህ በነሐሴ 8, 1995 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት:- ምንዝር—ይቅር ማለት ወይስ አለማለት?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ትርጉም ያለው ድጋፍ
ሊጤኑ የሚገባቸው ጉዳዮች በርካታ ከመሆናቸው አንጻር ሲታይ ተሞክሮ ያለውንና ሚዛናዊ የሆነን አማካሪ እርዳታ ለማግኘት መጣር ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ምሥክሮች ደግና ርኅሩኅ የሆኑ የጉባኤ ሽማግሌዎችን እርዳታ ማግኘት ይችላሉ።—ያዕቆብ 5:13-15
አማካሪዎች፣ ጓደኞችና ዘመዶች የራሳቸውን አመለካከት ማራመድ ወይም ደግሞ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለውን ፍቺ እንዲፈጽሙም ሆነ ዕርቅ እንዲፈጥሩ መገፋፋት አይኖርባቸውም። ከባሏ የተፋታች አንዲት ክርስቲያን ሴት “የሚያስፈልገው ነገር በቂ እርዳታ መስጠት ነው፤ ከዚያ በኋላ ውሳኔውን ለእኛ ተዉልን” ስትል አጥብቃ አሳስባለች።
ምክሩ ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። “ምን ሊሰማቸው እንደሚገባና እንደማይገባ ከመናገር ይልቅ የልባቸውን አውጥተው እንዲናገሩ አድርጓቸው” ስትል አንዲት ከባሏ የተፋታች ሴት ተናግራለች። አሳቢነት፣ ወንድማዊ ፍቅርና ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ በትዳር ላይ የሚፈጸም ውስልትና የሚያስከትለው ሥር የሰደደ ቁስል እንዲጠግ አስተዋጽኦ ያደርጋል። (1 ጴጥሮስ 3:8) አንድ ልምድ ያካበተ አማካሪ “እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፤ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው” ሲል ገልጿል።—ምሳሌ 12:18
አንድ ታማኝ ባል “ርኅራኄ፣ ማጽናኛና ማበረታቻ አስፈልጎኝ ነበር” ሲል ያሳለፈውን ሁኔታ መለስ ብሎ በመመልከት ተናግሯል። “ሚስቴ ደግሞ እያደረገችው የነበረውን ጥረት የሚያደንቅና ግልጽ የሆኑ መመሪያዎች የሚሰጣት፣ በሌላ አነጋገር በጥረቷ መግፋት እንድትችል ከጎኗ ቆሞ አይዞሽ የሚላት ሰው ያስፈልጋት ነበር።”
አንድ ሰው ጉዳዩን በጥሞናና በጸሎት ካሰበበት በኋላ ቅዱስ ጽሑፋዊ በሆነ ምክንያት ለመፋታት ወይም ለመለያየት ቢወስን ግለሰቡ ጥፋተኛ እንደሆነ ሆኖ እንዲሰማው በሚያደርግ መንገድ ምክር ሊሰጠው አይገባም። ከዚህ ይልቅ ግለሰቡ አግባብነት የሌለውን የጥፋተኝነት ስሜት መቋቋም እንዲችል እርዳታ ሊሰጠው ይገባል።
እንዲህ ዓይነት በደል የደረሰበት አንድ ሰው ሲናገር “ትርጉም ያለው ማጽናኛ መስጠት ከፈለጋችሁ የግለሰቡን ጥልቅ ስሜቶች ግምት ውስጥ አስገቡ” ብሏል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዳንዶች አብረው ለመኖር የሚመርጡበት ምክንያት
በብዙ ማኅበረሰቦች ውስጥ ንስሐ ከማይገባ አመንዝራ የትዳር ጓደኛቸው ጋር ከመኖር ሌላ ምንም አማራጭ የሌላቸው ሚስቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል በጦርነት በሚታመሱ ወይም ዝቅተኛ ገቢ ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አንዳንድ ክርስቲያን ሚስቶች አማኝ ባይሆንም እንኳ በሌሎች ጉዳዮች ረገድ ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ከሚጥረው ታማኝ ያልሆነ የትዳር ጓደኛቸው ጋር ለመኖር መርጠዋል። በመሆኑም ታማኝ ባይሆንም እንኳ አብረው በመኖራቸው መኖሪያ፣ ጥበቃ፣ ቋሚ የሆነ ገቢና በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ የተረጋጋ ኑሮ ማግኘት ችለዋል። ምቹ ወይም ቀላል ሆኖ አግኝተውት ባይሆንም እንኳ ከባለቤታቸው ጋር ለመኖር መምረጣቸው እነሱ ካሉበት ሁኔታ አንጻር ሲታይ ብቻቸውን ለመኖር ቢመርጡ ሊፈጠር ከሚችለው ሁኔታ በተሻለ ኑሯቸውን መምራት እንዳስቻላቸው ይናገራሉ።
ከእነዚህ ሚስቶች መካከል አንዳንዶቹ ለተወሰነ ጊዜ፣ አንዳንዴም ለብዙ ዓመታት በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ጸንተው ከኖሩ በኋላ በመጨረሻ ባሎቻቸው አካሄዳቸውን ለውጠው ታማኝና አፍቃሪ ክርስቲያን ባሎች ሲሆኑ የመመልከት አስደሳች በረከት አግኝተዋል።—ከ1 ቆሮንቶስ 7:12-16 ጋር አወዳድር።
እንግዲያው ንስሐ ባይገባም እንኳ ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ለመኖር የሚመርጡ ሰዎች ሊተቹ አይገባም። ከባድ ውሳኔ ለማድረግ የተገደዱ በመሆናቸው አስፈላጊ የሆነውን እርዳታና እገዛ ሁሉ ማግኘት አለባቸው።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ተጠያቂው ማን ነው?
እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ የተበዳዩ ወገን ድክመቶች በትዳር ጓደኛሞቹ መካከል ያለው ዝምድና ውጥረት እንዲነግሥበት አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች” ይላል። (ያዕቆብ 1:14, 15፤ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አንድ ሰው ምንዝር እንዲፈጽም አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ዋነኛው ምክንያት ግን የ“ራሱ ምኞት” ነው። አንድ ሰው የትዳር ጓደኛው ያሉባት ድክመቶች በትዳራቸው ውስጥ ችግር ቢፈጥሩም እንኳ ምንዝር መፈጸሙ መፍትሔ ሊሆን አይችልም።—ዕብራውያን 13:4
ከዚህ ይልቅ ባልየውም ሆነ ሚስትየዋ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋቸውን ከቀጠሉ በትዳራቸው ውስጥ የተፈጠሩት ችግሮች ሊወገዱ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ‘መቻቻልንና ይቅር መባባልን’ ይጨምራል። በተጨማሪም “ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትን፣ ትዕግሥትን” የመሳሰሉ ባሕርያትን ዘወትር ለማሳየት መትጋት አለባቸው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ‘ፍጹም የአንድነት ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን መልበስ’ ይኖርባቸዋል።—ቆላስይስ 3:12-15 የ1980 ትርጉም
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው በጥሞና መደማመጣቸው ትዳራቸውን መልሰው ለመገንባት ሊረዳቸው ይችላል