የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 6/8 ገጽ 4-9
  • በሕፃናት ላብ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በሕፃናት ላብ
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የችግሩ ስፋት
  • ሕፃናትን ለጉልበት ብዝበዛ የሚዳርጉ ነገሮች
  • የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ዓይነቶች
  • የተበላሸ የልጅነት ሕይወት
  • ልጆቻችሁን ከጥቃት መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው?
    ንቁ!—2007
  • ልጆቻችሁን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ አሠልጥኗቸው
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
  • ልጆች የሚወደዱ እና የሚፈለጉ መሆናቸው እንዲሰማቸው ማድረግ ይገባል
    ንቁ!—2000
  • ልጃችሁ የደረሰበትን ሐዘን እንዲቋቋም እርዱት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 6/8 ገጽ 4-9

በሕፃናት ላብ

“በአሁኑ ጊዜ በምርት ሂደት ውስጥ እየተካፈሉ ያሉት ሕፃናት እንደ ኢኮኖሚያዊ ሸቀጥ እንጂ የወደፊቱ አገር ተረካቢዎች እንደሆኑ ተደርገው አይታዩም።”—ቺራ ሆንግላዳሮም፣ የታይላንድ የሰው ኃይል ተቋም ዲሬክተር

የበሚቀጥለው ጊዜ ለሴት ልጅህ አሻንጉሊት ስትገዛ አሻንጉሊቱ በደቡባዊ ምሥራቅ እስያ በሚገኙ ሕፃናት የተሠራ ሊሆን እንደሚችል አስታውስ። ወንድ ልጅህ የእግር ኳስ ሲመታ ስታይ ኳሱ ከእናቷና ከአራት እህቶቿ ጋር ሆና እየሠራች በቀን 0.75 የአሜሪካ ዶላር በምታገኝ የሦስት ዓመት ልጅ የተሰፋ ሊሆን እንደሚችል አስብ። በሚቀጥለው ጊዜ ምንጣፍ ስትገዛ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ሥር ሆነው ዕለት ተዕለት ለረጅም ሰዓታት በመሥራት ኑሯቸውን በሚገፉ የስድስት ዓመት ወንዶች ልጆች ቀልጣፋ እጆች የተሠራ ሊሆን እንደሚችል አስብ።

የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ምን ያህል ተስፋፍቷል? በሕፃናትስ ላይ ምን እያስከተለ ነው? ለችግሩ መፍትሔ ለማምጣት ምን ሊደረግ ይችላል?

የችግሩ ስፋት

ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (አይ ኤል ኦ) እንደሚለው ከሆነ በታዳጊ አገሮች ውስጥ በሥራው ዓለም የተሰማሩ ከ5 ዓመት እስከ 14 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ቁጥር 250 ሚልዮን እንደሚሆን ይገመታል።a ከእነዚህ መካከል 61 በመቶ የሚሆኑት በእስያ፣ 32 በመቶዎቹ በአፍሪካና 7 በመቶዎቹ ደግሞ በላቲን አሜሪካ እንደሚገኙ ይታመናል። የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች ውስጥም ይታያል።

እንደተሠማሩ ለማወቅ የሚያስችል ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት በስፋት የሚሠራበት መመዘኛ ይህ ነው።

በደቡባዊ አውሮፓ በተለይ እንደ ግብርናና አነስተኛ ወርክሾፖች በመሳሰሉ በወቅቶች ላይ የተመሠረቱ ሥራዎች ላይ ተቀጥረው የሚሠሩ በርካታ ሕፃናት አሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመካከለኛውና በምሥራቅ አውሮፓ ከኮሙኒዝም ወደ ካፒታሊዝም ሥርዓት የተደረገውን ሽግግር ተከትሎ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ እየተስፋፋ ሄዷል። በዩናይትድ ስቴትስ ባለው ይፋዊ መረጃ መሠረት በጉልበት ሥራ ላይ የተሠማሩ ሕፃናት ቁጥር 5.5 ሚልዮን ነው። ሆኖም ይህ አኃዝ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በትናንሽ ፋብሪካዎች ተቀጥረው የሚሠሩትን ወይም በትላልቅ እርሻዎች ላይ ጊዜያዊ ሠራተኛ ሆነው ወይም ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወሩ የሚሠሩትን ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ብዙ ሕፃናት አይጨምርም። እነዚህ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት የሠራተኛው ኃይል አካል ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው?

ሕፃናትን ለጉልበት ብዝበዛ የሚዳርጉ ነገሮች

የድህነት ማነቆ። ዘ ስቴት ኦቭ ዘ ወርልድስ ችልድረን 1997 “ከሁሉ ይበልጥ ሕፃናት አደገኛ በሆነና ጉልበትን በሚያሟጥጥ ሥራ እንዲሠማሩ የሚያስገድዳቸው ነገር የድህነት ማነቆ ነው” ሲል ገልጿል። “በድህነት የሚማቅቁ ቤተሰቦች ልጃቸው ተቀጥሮ የሚያመጣት አነስተኛ ገቢ ወይም ደግሞ የቤቱን ሥራ በመሥራት ወላጆቹ ሥራ ውለው እንዲመጡ ማድረጉ ጦም ከማደር ይልቅ ያገኟትን መቃመስ እንዲችሉ ስለሚረዳ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም።” በጉልበት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሕፃናት ወላጆች ብዙውን ጊዜ ሥራ የሌላቸው ወይም በዝቅተኛ ሥራ የሚተዳደሩ ናቸው። ቋሚ ገቢ ያስገኝ እንጂ ማንኛውንም ዓይነት ሥራ ከመሥራት ወደ ኋላ አይሉም። ታዲያ የሥራው ዕድል ለወላጆች ሳይሆን ለሕፃናት የሚሰጠው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሕፃናት በአነስተኛ ክፍያ ሊሠሩ የሚችሉ በመሆናቸው ነው። ሕፃናት ይበልጥ ታዛዦችና ገራሞች በመሆናቸው ነው። ብዙዎቹ ያለምንም ማንገራገር የተባሉትን ሁሉ የሚያደርጉና ብዙውን ጊዜም ጭቆናን ለመቃወም ዓመፅ የማነሳሳት ዝንባሌ የሌላቸው በመሆናቸው ነው። በተጨማሪም ሲመቱ አጸፋውን የማይመልሱ በመሆናቸው ነው።

መማር አለመቻል። በህንድ የሚኖረው የ11 ዓመቱ ሱድሂር ትምህርት አቋርጠው ሥራ ከጀመሩት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት አንዱ ነው። ትምህርቱን ያቋረጠው ለምንድን ነው? “በትምህርት ቤት አስተማሪዎቹ በደንብ አያስተምሩም” ይላል። “ፊደል እንዲያስተምሩን ከጠየቅናቸው ይገርፉናል። ክፍል ውስጥ ይተኛሉ። . . . ያልገባንን አያስረዱንም።” ሱድሂር ትምህርት ቤትን በማስመልከት የሰጠው አስተያየት ትክክል ሆኖ መገኘቱ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው። በታዳጊ አገሮች ውስጥ ለማኅበራዊ ጉዳዮች የሚመደበው በጀት መቀነሱ የትምህርቱን መስክ ክፉኛ ጎድቶታል። ተመድ በ1994 በዓለም አቀፍ ደረጃ በድህነት የመጨረሻ ረድፍ ላይ በተቀመጡ 14 አገሮች ላይ ያካሄደው ጥናት አንዳንድ ትኩረት የሚስቡ እውነታዎችን ይፋ አድርጓል። ለምሳሌ ያህል ከእነዚህ መካከል ግማሽ ያህል በሚሆኑት አገሮች ውስጥ ከ10 የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል መቀመጫ የሚያገኙት አራቱ ብቻ ናቸው። ከተማሪዎቹ መካከል ግማሽ ያህሉ የመማሪያ መጻሕፍት የላቸውም። ግማሽ ያህል የሚሆኑት የመማሪያ ክፍሎች ደግሞ ጥቁር ሰሌዳ የላቸውም። በእንዲህ ዓይነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩት ብዙዎቹ ሕፃናት ትምህርታቸውን አቋርጠው ሥራ መጀመራቸው ምንም አያስደንቅም።

በኅብረተሰቡ መካከል ሰፍኖ የቆየ አመለካከት። ሥራው ይበልጥ አደገኛና ጉልበት የሚጠይቅ በሚሆንበት ጊዜ አናሳ ጎሳዎች፣ ዝቅተኛ የመደብ ክፍሎች፣ አስከፊ የኑሮ ደረጃ ያላቸውና ድሃ የሆኑ ሰዎች እንዲሠሩት ይደረጋል። የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት በእስያ ውስጥ የሚገኝን አንድ አገር አስመልክቶ ሲናገር “አንዳንድ ሰዎች ሥልጣን ተቆናጥጠው እንዲገዙና የአእምሮ ሥራ እንዲሠሩ ሆነው እንደተወለዱና ብዙሃኑ ግን የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ ሆነው እንደተፈጠሩ ተደርጎ ሲታመን ቆይቷል” ብሏል። በምዕራቡም ዓለም ቢሆን ተመሳሳይ አመለካከት የሚታይበት ጊዜ አለ። የበላይ የሆኑት መደቦች የራሳቸው ልጆች ለአደጋ የሚያጋልጥ ሥራ እንዲሠሩ አይፈልጉ ይሆናል፤ አናሳ የሚባሉ ብሔረሰቦች ወይም ጎሳዎች ወይም ደግሞ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ልጆች እንዲህ ዓይነቱን ሥራ ሲሠሩ ግን ቅንጣት ታክል አይቆረቁራቸውም። ለምሳሌ ያህል በሰሜናዊ አውሮፓ ብዙውን ጊዜ የጉልበት ሥራ ለቱርክ አለዚያም ለአፍሪካ ሕፃናት የተተወ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ለእስያውያን ወይም ለላቲን አሜሪካውያን ሊሆን ይችላል። ዕቃዎችን የማግበስበስ ሱስ የተጠናወተው ዘመናዊው ኅብረተሰብ ለሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል። ምርቶችን በዝቅተኛ ዋጋ የማግኘት ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው። እነዚህ ምርቶች ማንነታቸው በማይታወቅ በሚልዮን በሚቆጠሩ ሕፃናት ጉልበት የተመረቱ መሆናቸው ግድ የሚሰጠው ሰው ያለ አይመስልም።

የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ዓይነቶች

የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ምን ዓይነት መልኮች አሉት? በጥቅሉ ሲታይ አብዛኞቹ ሕፃናት በቤት ውስጥ ሥራ የተሰማሩ ናቸው። እነዚህ የጉልበት ሠራተኞች “ፈጽሞ የተረሱ የዓለማችን ሕፃናት” የሚል ስያሜ ወጥቶላቸዋል። በመሠረቱ የቤት ውስጥ ሥራዎች ለአደጋ የሚያጋልጡ ባይሆኑም ብዙውን ጊዜ አደጋ ሲያስከትሉ ይታያል። በቤት ውስጥ በባርነት የሚያገለግሉ ልጆች ክፍያቸው በጣም አነስተኛ ነው። አለዚያም ደግሞ ከናካቴው ላይከፈላቸው ይችላል። የሥራቸው ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በጌቶቻቸው ምርጫና ፍላጎት ላይ የተመካ ነው። ፍቅር፣ የትምህርት ዕድል፣ ጨዋታና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ የተነፈጉ ናቸው። በተጨማሪም ለአካላዊና ለወሲባዊ ጥቃት የተጋለጡ ናቸው።

ሌሎች ሕፃናት ደግሞ በዕዳ ሳቢያ ተገድደው በባርነት ቀንበር ውስጥ የወደቁ ናቸው። በደቡባዊ እስያ እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች ብዙውን ጊዜ ዕድሜያቸው ከስምንት ወይም ከዘጠኝ ዓመት የማይዘል ሕፃናት ወላጆቻቸው ለተበደሩት አነስተኛ ገንዘብ በለውጥ መልክ ለፋብሪካ ባለቤቶች ወይም ለወኪሎቻቸው ይሰጣሉ። ሕፃናቱ ዕድሜ ልካቸውን በባርነት የሚሰጡት አገልግሎት ሌላው ቀርቶ ዕዳውን እንኳ አይቀንሰውም።

ሕፃናትን በጾታ ንግድ በማሰማራት መጠቀሚያ ስለማድረግስ ምን ለማለት ይቻላል? በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ ቢያንስ ቢያንስ አንድ ሚልዮን ልጃገረዶች ተታልለው በጾታ ንግድ ይሰማራሉ። ወንዶች ልጆችም ቢሆኑ ከዚህ ዓይነቱ የጾታ ንግድ ነፃ አይደሉም። ይህ ዓይነቱ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት አካላዊና ስሜታዊ ጉዳት ማስከተሉ ብቻ ሳይሆን ለኤች አይ ቪም የሚያጋልጣቸው መሆኑ እጅግ አደገኛ ከሆኑት የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ዓይነቶች ተርታ ያሰልፈዋል። “ኅብረተሰቡ ከዱርዬዎች ለይቶ አያየንም” ስትል በሴኔጋል የምትኖር አንዲት የ15 ዓመት ዝሙት አዳሪ ተናግራለች። “ማንም ሰው እኛን መተዋወቅም ሆነ አብሮን መታየት አይፈልግም።”b

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕፃናት ጉልበታቸው በኢንዱስትሪውና በግብርናው መስክ ይበዘበዛል። እነዚህ ሕፃናት ለአዋቂዎች እንኳ አደገኛ ናቸው በሚባሉ የማዕድን ቁፋሮ ሥራዎች ተሰማርተው ላባቸው ጠብ እስኪል ድረስ ይሠራሉ። ብዙዎቹ በሳምባ ነቀርሳ፣ በብሮንካይተስ እና በአስም በሽታዎች ይሠቃያሉ። በግብርናው መስክ በጉልበት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሕፃናት ለተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶች፣ ለእባብና ለተለያዩ ተናዳፊ ሶስት አፅቄዎች የተጋለጡ ናቸው። አንዳንዶቹ በገጀራ ሸንኮራ አገዳ ሲቆርጡ የገዛ ራሳቸውን አካል ቆርጠው ጥለዋል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሕፃናት ደግሞ ጎዳናዎችን የሥራ ቦታቸው አድርገዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል ከቆሻሻ መጣያ አንዳንድ ነገሮችን እየለቃቀመች በመሸጥ የተካነችውን የአሥር ዓመቷን ሺሪንን እንውሰድ። ትምህርት ቤት ገብታ የማታውቅ ብትሆንም እንኳ እንዴት ሕይወቷን ጠብቃ ማቆየት እንደምትችል ጠንቅቃ ታውቃለች። ከ30 አስከ 50 ሳንቲም የሚያወጣ የተጣለ ወረቀት ወይም ፌስታል ከሸጠች ምሳዋን ቻለች ማለት ነው። የምታገኘው ሳንቲም ከዚያ ካነሰ ደግሞ ሳትበላ ትውላለች። ብዙውን ጊዜ በቤት ውስጥ በሚፈጸምባቸው በደል ተማርረው ወይም ደግሞ የወላጆቻቸውን እንክብካቤ በማጣታቸው ከቤት ወጥተው የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑ ሕፃናት በጎዳና ላይ ተጨማሪ በደልና ግፍ ይፈጸምባቸዋል። በአንድ የእስያ ከተማ አውራ ጎዳናዎች ላይ ጣፋጭ ነገሮች እያዞረች የምትሸጥ ጆዚ የተባለች የአሥር ዓመት ልጅ “ክፉ ሰው እጅ ላይ እንዳልወድቅ በየዕለቱ እጸልያለሁ” ስትል ተናግራለች።

የተበላሸ የልጅነት ሕይወት

እንዲህ ያሉ በሕፃናት ላይ የሚደርሱ የጉልበት ብዝበዛ ዓይነቶች በአሥር ሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሕፃናትን አስከፊ ለሆኑ አደጋዎች አጋልጠዋቸዋል። ለዚህ ምክንያቱ የሥራው ጠባይ ወይም ሥራውን የሚያከናውኑበት ሁኔታ ደረጃውን ያልጠበቀ መሆኑ ሊሆን ይችላል። ሕፃናትና ሌሎች በለጋ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሠራተኞች ብዙውን ጊዜ ከአንድ ዐዋቂ ሰው በከፋ ሁኔታ በሥራ ወቅት ለሚደርሱ አደጋዎች የተጋለጡ ናቸው። ይህ የሆነው የአንድ ሕፃን የሰውነት መዋቅር ከዐዋቂዎች የተለየ በመሆኑ ነው። የሚሠራው ከባድ ሥራ የአከርካሪ አጥንቱን ወይም የዳሌውን ቅርጽ በቀላሉ ሊያበላሸው ይችላል። በተጨማሪም ሕፃናት አደገኛ ለሆኑ ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች ወይም ለጨረር በሚጋለጡበት ጊዜ ከአዋቂዎች ይበልጥ ይጎዳሉ። ከዚህም በላይ የሕፃናት ሰውነት አድካሚና አሰልቺ የሆነን ሥራ ለረጅም ሰዓት ለመሥራት የሚችል አይደለም። ሆኖም ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሥራ ለመሥራት ሲገደዱ ይታያል። አብዛኛውን ጊዜ ሊደርስባቸው ስለሚችለው አደጋ የሚያውቁት ነገር አይኖርም፤ ወይም ደግሞ አስቀድመው ሊወስዷቸው ስለሚገቡት ጥንቃቄዎች እምብዛም አያውቁም።

በተጨማሪም የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ በሥነ ልቦና፣ በስሜትና በእውቀት ብስለታቸውም ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። እንዲህ ዓይነቶቹ ሕፃናት ፍቅር የተነፈጉ ናቸው። ነጋ ጠባ ይደበደባሉ፣ የስድብ መዓት ይወርድባቸዋል፣ አሠሪዎቻቸው ምግብ በመከልከል ይቀጧቸዋል እንዲሁም በጾታ ይነወራሉ። አንድ ጥናት እንዳመለከተው 250 ሚልዮን ገደማ ከሚሆኑት በጉልበት ሥራ ላይ የተሠማሩ ሕፃናት መካከል ግማሽ ያህሉ ትምህርት ያቋረጡ ናቸው። ከዚህም ሌላ ለረጅም ሰዓታት የሚሠሩ ሕፃናት የመማር ችሎታቸው ሊዳከም እንደሚችል ተደርሶበታል።

ይህ ሁሉ ምን ማለት ነው? በጉልበት ሥራ ላይ የተሰማሩ አብዛኞቹ ሕፃናት ለዕድሜ ልክ ድህነት፣ መከራ፣ ሕመም፣ መሃይምነትና ማኅበራዊ ቀውስ የተዳረጉ መሆናቸውን ያሳያል። ወይም ደግሞ ሮቢን ራይት የተባሉት ጋዜጠኛ እንደገለጹት “ምንም እንኳ ዓለማችን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ብትደርስም በ20ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ የተስተካከለ ሕይወት የመምራት ተስፋ የሌላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት አፍርታለች። በ21ኛው መቶ ዘመንም የተሻለ ነገር አይጠበቅም።” እነዚህ ሊጤኑ የሚገባቸው አስተያየቶች የሚከተሉትን ጥያቄዎች ያስነሳሉ:- ሕፃናት መያዝ ያለባቸው እንዴት ነው? ሕፃናትን ለከፋ መከራ የሚዳርገው ይህ ችግር በቅርብ ጊዜ ውስጥ እልባት የሚያገኝበት መንገድ ይኖር ይሆን?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በጥቅሉ ሲታይ አይ ኤል ኦ ማንኛውም ሰው የግድ ሊያጠናቅቀው የሚገባውን የትምህርት ደረጃ ለመጨረስ 15 ዓመት በቂ እንደሆነ በማሰብ ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ፈጽሞ በሥራ ዓለም መሠማራት እንደሌለባቸው ይደነግጋል። በዓለም ዙሪያ ምን ያህል ሕፃናት በሥራው ዓለም እንደተሠማሩ ለማወቅ የሚያስችል ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት በስፋት የሚሠራበት መመዘኛ ይህ ነው።

b ልጆችን ለወሲብ መጠቀሚያ ማድረግን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የመጋቢት 1998 የንቁ! መጽሔት እትም ገጽ 25-29 ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ሲባል ምን ማለት ነው?

በሁሉም ኅብረተሰቦች ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ሕፃናት በሆነ መልኩ መሥራታቸው አይቀርም። የሚሠሩት ሥራ ዓይነት እንደየኅብረተሰቡና እንደየወቅቱ ይለያያል። ሥራ የሕፃናት ትምህርት ዋና ክፍልና ከወላጆቻቸው ጠቃሚ ሙያ የሚቀስሙበት ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ አገሮች ሕፃናት ብዙውን ጊዜ በወርክሾፖችና አነስተኛ ግልጋሎት በሚሰጡ ድርጅቶች ውስጥ በመሥራት ቀስ በቀስ በኋለኛው የሕይወት ዘመናቸው የተካኑ ሠራተኞች የሚያደርጋቸውን እውቀት ይቀስማሉ። በሌሎች አገሮች ደግሞ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የኪስ ገንዘብ ለማግኘት በሳምንት ጥቂት ሰዓት ይሠራሉ። የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት እንዲህ ዓይነቱ ሥራ “ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ አንድ ልጅ የሚያገኘው ትምህርት፣ መዝናኛና ዕረፍት ሳይስተጓጎል አካላዊ፣ አእምሯዊ፣ መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ወይም ማኅበራዊ ዕድገቱ እንዲፋጠን የሚያደርግ” እንደሆነ ገልጿል።

በሌላ በኩል ግን የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ የሚለው አነጋገር ብዙውን ጊዜ ጤናቸውን በሚጎዱ ሁኔታዎች ሥር ሆነው በአነስተኛ ዋጋ ለረጅም ሰዓታት የሚሠሩትን ሕፃናት የሚመለከት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሥራ “ጎጂ ወይም ጉልበታቸው አላግባብ እንዲበዘበዝ የሚያደርግ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም” ሲል ዘ ስቴት ኦቭ ዘ ወርልድስ ችልድረን 1997 ገልጿል። “በማንኛውም ሁኔታ ሥር ሕፃናትን በዝሙት አዳሪነት በማሰማራት መጠቀሚያ ማድረግ ተቀባይነት ያለው ድርጊት ነው ብሎ ሽንጡን ገትሮ የሚከራከር ሊኖር አይችልም። ወላጆቻቸው ወይም አያቶቻቸው የገቡትን ዕዳ እንዲከፍሉ ለማድረግ ሲባል በባርነት ቀንበር የሚጠመዱትን ሕፃናት በተመለከተ ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። በተጨማሪም ጤናንም ሆነ ደህንነትን ለአደጋ የሚያጋልጡትን ኢንዱስትሪዎች በተመለከተም ሁኔታው የተለየ አይደለም። . . . በአጭር አነጋገር ለአደጋ የሚያጋልጥ ሥራ ፈጽሞ ለሕፃናት የሚሆን አይደለም።”

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“ገና ብዙ መሠራት አለበት”

ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (አይ ኤል ኦ) እጅግ አስከፊ የሆኑትን የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ዓይነቶች ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጀምሯል። አይ ኤል ኦ ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት በጉልበት ሥራ ላይ እንዳይሠማሩ የሚያግድ ሕግ እንዲያወጡ በመንግሥታት ላይ ግፊት ያደርጋል። በተጨማሪም ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ሠራተኞችን የሚያግዱና የሕፃናት ጉልበት የሚበዘበዝባቸውን እጅግ አደገኛ ሥራዎች በሕግ የሚያግዱ አዳዲስ ውሎች እንዲፈረሙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ስለ እነዚህ ጥረቶች ስኬታማነት ይበልጥ ለማወቅ የንቁ! ዘጋቢ በዩናይትድ ስቴትስ የሥራ መምሪያ የዓለም አቀፉን የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ጉዳይ የሚከታተለው ፕሮግራም ዲሬክተር የሆኑትን ሶንያ ሮዘንን አነጋግሮ ነበር። እኚህ ሴት ከተለያዩ የአይ ኤል ኦ ፕሮግራሞች ጋር በቅርብ ሠርተዋል። ከውይይቱ ተቀንጭቦ የተወሰደው እነሆ:-

ጥያቄ:- የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለመዋጋት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው?

መልስ:- ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ የሆነ መልስ መስጠት ያስቸግራል። ሆኖም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተነጋገርንባቸው ጉዳዮች ቁልፍ ነገሮች ናቸው። እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት የሚያግድ የጠበቀ ሕግ መደንገግና በተቻለ መጠን ግዴታ የሆነና ከክፍያ ነፃ የሆነ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት በዓለም አቀፍ ደረጃ መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበታል። ወላጆች ጥሩ ሥራ እንዲያገኙ ማድረጉም በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።

ጥያቄ:- የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለመዋጋት እስካሁን በተወሰደው እርምጃ ረክተዋል?

መልስ:- አልረካሁም። አንድም ሕፃን አስከፊ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ሆኖ መሥራት የለበትም ነው የምንለው። በአይ ኤል ኦ ፕሮግራሞች ብዙ ማከናወን ችለናል። ሆኖም አሁንም ገና ብዙ መሠራት አለበት።

ጥያቄ:- የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለማስወገድ እየተካሄዱ ላሉት ጥረቶች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምን ምላሽ እየሰጠ ነው?

መልስ:- ይሄን ጥያቄ እንዴት እንደምመልስ እየቸገረኝ መጥቷል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ እልባት የሚያሻው ችግር መሆኑ በተወሰነ ደረጃ ተቀባይነት አግኝቷል። ሆኖም እዚህ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ያሉ ይመስለኛል:- ይህ ጉዳይ እልባት ማግኘት ያለበት እንዴትና መቼ ነው? አንዳንድ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ዓይነቶችን ለማስወገድ የሚያስችሉት ከሁሉ የተሻሉ ዘዴዎች ምንድን ናቸው? ትልቁ ፈተናችን ይሄ ይመስለኛል።

ጥያቄ:- ሕፃናት ሠራተኞች ወደፊት በተስፋ ሊጠብቁት የሚችሉት ነገር ይኖራል?

መልስ:- በዚህ ዓመት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አገሮች እጅግ አስከፊ የሆኑትን የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ዓይነቶች የሚያግድ አዲስ ውል ለማጽደቅ ጄኔቫ ላይ ስብሰባ ይቀመጣሉ። ይህ ታላቅ ተስፋ ነው። የሠራተኞች ድርጅቶችንና የአሠሪዎችን ድርጅቶች ጨምሮ ሁሉም አገሮች የሚያጸድቁት ውል ይሆናል። ይህ ስምምነት እጅግ አስከፊ የሆኑትን የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ዓይነቶች ለማስወገድ የሚያስችል አዲስ መዋቅር ይፈጥራል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል።

የሶንያ ሮዘን ዓይነት ብሩህ ተስፋ የሚታያቸው ግን ሁሉም አይደሉም። ሕፃናት አድን የተባለው ድርጅት ፕሬዚዳንት የሆኑት ቻርልስ መኮርመክ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥርጣሬ አላቸው። “የፖለቲካ ኃይሎች ዝግጁነትም ሆነ ሰዉ ስለ ጉዳዩ ያለው እውቀት ችግሩን ለማስወገድ የሚያስችል ዓይነት አይደለም” ብለዋል። ለምን? የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት ፈንድ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ የተወሳሰበ ችግር ነው። ችግሩን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ኃይሎች አሉ። ብዙ አሠሪዎች፣ ከእንዲህ ዓይነቱ አሠራር ተጠቃሚ የሆኑ ወገኖችና ለነፃ ገበያ እንቅፋት የሚሆን ነገር ሁሉ መወገድ አለበት የሚል አመለካከት ያላቸው የኢኮኖሚ ጠበብት እንዲሁም የአንዳንድ ሕፃናት ኅብረተሰባዊ ክፍል ወይም መደብ ራሱ አንዳንድ መብቶችን እንዲነፈጉ ያደርጋቸዋል የሚል እምነት ያላቸው ወግ አጥባቂዎች ችግሩን ይበልጥ ያወሳስቡታል።”

[ሥዕል]

ሶንያ ሮዘን

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕሎች]

በጉልበት ሥራ የተሠማሩ ሕፃናት በማዕድን ማውጫዎችና በጥጥ ፋብሪካዎች ውስጥም ላባቸው ጠብ እስኪል ይሠራሉ

[ምንጭ]

U.S. National Archives photos

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከቆሻሻ ውስጥ መለቃቀም

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እጅግ አድካሚ የሆነው ለማገዶ የሚሆን እንጨት የመሰብሰብ ሥራ

[ምንጭ]

UN PHOTO 148046/J. P. Laffont-SYGMA

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በድርና ማግ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥሮ መሥራት

[ምንጭ]

CORBIS/Dean Conger

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተለያዩ ነገሮችን በጎዳናዎች ላይ እያዞሩ የሚሸጡ ሕፃናት በቀን ስድስት ሳንቲም ብቻ እየተከፈላቸው ይሠራሉ

[ምንጭ]

UN PHOTO 148027/Jean Pierre Laffont

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአንድ የእንጨት ሥራ ድርጅት ውስጥ መሥራት

[ምንጭ]

UN PHOTO 148079/J. P. Laffont-SYGMA

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በልቶ ለማደር የሚደረግ ትግል

[ምንጭ]

UN PHOTO 148048/J. P. Laffont-SYGMA

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ