ወጣቶቸ የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ...
ስለ ውፍረት ይህን ያህል የምጨነቀው ለምንድን ነው?
“አእምሮዬ ውስጥ ከቁጥጥሬ ውጭ የሆነ ሙግት እየተካሄደ ነው። በአንድ በኩል መብላት እፈልጋለሁ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እወፍራለሁ ብዬ ስለምፈራ ከመብላት እቆጠባለሁ።”—ጄይሚ
ከምንም ነገር በላይ የሚያስፈራችሁ ምንድን ነው? ብዙ ልጃገረዶች ውፍረት ብለው እንደሚመልሱ ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲያውም በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣት ሴቶች ከኒዩክሌር ጦርነት፣ ከካንሰር አልፎ ተርፎም ወላጆቻቸውን በሞት ከማጣትም እንኳ ይበልጥ የሚያስፈራቸው ውፍረት መሆኑን አንድ ጥናት ጠቁሟል!
በጣም የሚገርመው አንዳንዶች ስለ ውፍረት መጨነቅ የሚጀምሩት ገና በልጅነታቸው ነው። ብዙ ልጃገረዶች አሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ከመድረሳቸው በፊት እንኳ አንድ ላይ ተሰባስበው “ስለ ውፍረት እንደሚያወሩ” ማለትም አንዳቸው የሌላዋን የሰውነት ቅርጽ በመተቸት እንደሚጨዋወቱ ዶክተር ካተሪን ስቴይነር አዴይር ተናግረዋል። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ነገሩ በወሬ ብቻ አያበቃም። በ2,379 ልጃገረዶች ላይ በተደረገ ጥናት መሠረት 40 በመቶ የሚሆኑት ውፍረታቸውን ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነበር። ጥናቱ የተካሄደባቸው ልጃገረዶች የዘጠኝና የአሥር ዓመት ዕድሜ ብቻ ነበሩ!
ከጊዜ በኋላ ከእነዚህ ወጣቶች አብዛኞቹ ውፍረት ለመቀነስ በሚል ፈሊጥ ለየት ያለ የአመጋገብ ፋሽን መከተል ይጀምራሉ። ከዚህ የከፋው ደግሞ አንዳንዶች መጨረሻቸው እንደ 20 ዓመቷ ጄን ይሆናል። ቁመቷ አንድ ሜትር ከ60 የሆነው ይህች ወጣት ክብደቷ 40 ኪሎ ግራም ብቻ ነው! ጄን “መብላት የሚባል ነገር ያስጠላኛል። እኔ እንዲያውም በጣም የሚያሳስበኝ ነገር ቢኖር ለሦስት ዓመት ያህል ለመክሳት ከጣርኩ በኋላ እንደገና እንደ ልብ መብላት ብጀምር በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተመልሼ እንደዱሮዬ እንዳልሆን ነው” ስትል ገልጻለች።
ምናልባት የጄንን ስሜት ትረጂላት ይሆናል። አንቺም ሽንቅጥ ያልሽ ልጅ ሆነሽ ለመታየት መቅጠን ትፈልጊ ይሆናል። እርግጥ ነው ስለ ቁመናሽ ማሰብሽ ምንም ስህተት የለውም። ሆኖም ጄን ሸንቃጣ ለመሆን የነበራት ፍላጎት ሕይወቷን ሊያሳጣት ነበር። እንዴት?
ራስን በረሃብ አለንጋ መግረፍ
ጄን አኖሬክሲያ ነርቮሳ ከሚባል አደገኛ የሆነ የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት ጋር ግብግብ ገጥማለች። መግቢያው ላይ የተጠቀሰችው የጄይሚ ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። እነዚህ ልጃገረዶች ለተወሰነ ጊዜ ቃል በቃል ራሳቸውን በረሃብ አለንጋ ቀጥተዋል፤ ግን እነሱ ብቻ አይደሉም። ከ100 ልጃገረዶች መካከል አንዷ በአኖሬክሲያ እንደምትሰቃይ ይገመታል። ይህም በሚልዮን የሚቆጠሩ ወጣት ሴቶች የበሽታው ተጠቂዎች ናቸው ማለት ነው። ምናልባትም አንቺ ራስሽ የምታውቂያት ሴት ትኖር ይሆናል!a
አኖሬክሲያ እንዲሁ እንደ ዋዛ ሊጀምር ይችላል። አንዲት ልጃገረድ ትንሽ ኪሎ ለመቀነስ ብላ ምንም ጉዳት የሌለው የሚመስል የአመጋገብ ሥርዓት መከተል ትጀምር ይሆናል። ሆኖም ያሰበችው ግብ ላይ ስትደርስ በዚያ አትረካም። ራስዋን በመስተዋት እየተመለከተች “አሁንም በጣም ወፍራም ነኝ!” በማለት በቁመናዋ አለመደሰቷን ትገልጻለች። ስለዚህ አሁንም የተወነሱ ኪሎዎች ለመቀነስ ትወስናለች። ከዚያም እንደገና ትንሽ። አሁንም ትንሽ። በመጨረሻም ይህ ልማድ ይሆንና አኖሬክሲያ ይይዛታል።
እርግጥ ነው ምግብ የቀነሱ ሁሉ የአኖሬክሲያ ተጠቂዎች ናቸው ማለት አይደለም። አንዳንዶች ስለ ውፍረታቸው መጨነቃቸው ተገቢ ይሆናል፤ ለእነሱ የተወሰኑ ኪሎዎች መቀነሱ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ብዙ ልጃገረዶች ስለ ቁመናቸው የተዛባ አመለካከት አላቸው። ኤፍ ዲ ኤ ከንሲውመር የተባለው መጽሔት መጥፎ የሰውነት ቅርጽ እንዳላቸው አድርገው የሚያስቡ ልጃገረዶች በምናባቸው የሚታያቸው ምስል ሰዎችን ለማዝናናት ሲባል ቅርጽን አዛብቶ እንዲያሳይ ተደርጎ በሚሠራ መስተዋት ከሚታየው ምስል የተለየ አይደለም ሲል ገልጿል። “መስተዋቱ የሚያሳያችሁ ምስል የሌላችሁን ውፍረት እንዳላችሁ አድርጎ ነው” ሲል መጽሔቱ ገልጿል።
ከዚህ የተነሳ የአኖሬክሲያ ተጠቂ የሆነችው ሴት በጣም ቀጭን ብትሆንም እንኳ ክብደት እጨምራለሁ የሚል ስጋት ያድርባታል። ክብደት ለመቀነስ ብላ ከባድ የአካል እንቅስቃሴ ታደርግ ይሆናል። እንዲሁም “ኪሎ እየጨመረች” እንዳልሆነች ለማረጋገጥ በቀን አሥር ጊዜ ክብደቷን ትለካ ይሆናል። መብላት ሲያሰኛት በጣም ጥቂት ትመገባለች። አሊያም ከናካቴው ላትበላ ትችላለች። “በየቀኑ ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ እናቴ ያዘጋጀችልኝን ምሳ ይዤ እሄዳለሁ። ሆኖም በቀን በቀን ማለት ይቻላል የወሰድኩትን ምግብ እደፋዋለሁ” ስትል ሂተር ተናግራለች። “ብዙም ሳይቆይ አለመብላት ልማድ ሆነብኝና መብላት ብፈልግ እንኳ ወስፋቴ ይዘጋ ጀመር። ጭራሽ የረሐብ ስሜቴ ጠፋ።”
እንደ ሂተር ያሉ የአኖሬክሲያ ተጠቂዎች መጀመሪያ ላይ ክብደታቸው ሲቀንስ ሲያዩ ይፈነድቃሉ። ሆኖም የኋላ ኋላ ተመጣጣኝ ምግብ አለመመገባቸው ጉዳት ማስከተል ይጀምራል። የአኖሬክሲያ ተጠቂዋ ወጣት ፈዛዛና ልፍስፍስ ትሆናለች። የትምህርት ቤት ውጤቷ ማሽቆልቆል ይጀምራል። የወር አበባዋም ሊቋረጥ ይችላል።b ከጊዜ በኋላ የልቧ ምትና የደም ግፊቷ በአስጊ ሁኔታ ሊቀንስ ይችላል። ሆኖም የአኖሬክሲያ ተጠቂዋ ምንም ዓይነት አደጋ አይታያትም። እንዲያውም እሷ የምትሰጋው ከቀነሰችው ትንሽም እንኳ ቢሆን መልሳ እንዳትጨምር ነው።
ይሁን እንጂ ከአኖሬክሲያ ይበልጥ በብዙዎች ላይ የሚታዩ ሌሎች የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት ችግሮች አሉ። ቡሊሚያ ነርቮሳ በአኖሬክሲያ ከተለከፉ በሦስት እጥፍ የሚበልጡ ልጃገረዶችን የሚያጠቃ መቅሰፍት ነው። ከዚያም ከቡሊሚያ ጋር የቅርብ ዝምድና ያለው አለልክ የመብላት ሱስ የሚባል ነገር አለ። እስቲ የእነዚህን በሽታዎች ምንነት እንመልከት።
ስውር መቅሰፍት
“አንዲት ጓደኛዬ ማንም ሳያያት ምግብ ወስዳ ተደብቃ እንደምትበላ በቅርቡ አጫውታኛለች። ከዚያም የበላችውን ታስታውከዋለች። ይህንንም ለሁለት ዓመታት ያህል ታደርግ እንደነበር ተናግራለች።” አንዲት ወጣት ለአንድ መጽሔት የምክር መስጫ ዓምድ ከላይ ያለውን በመጻፍ ቡሊሚያ የሚባለውን የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት በሽታ ምልክቶች ገልጻለች።
የቡሊሚያ ተጠቂ የሆነች ሴት በአንድ ጊዜ ብዙ ትበላለች። ከዚያም የበላችውን ምግብ ሁሉ እየጓጎጠች ታስወጣዋለች።c መቼም በዚህ መንገድ እየጓጎጡ ማስወጣት የሚያስጠላ ነገር ሊመስል እንደሚችል የታወቀ ነው። ሆኖም የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኛ የሆኑት ናንሲ ጄ ኮሎድኒ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በተደጋጋሚ ቁንጣን እስኪይዛችሁ በበላችሁና ባስመለሳችሁ መጠን እንዲህ ማድረጉ ቀላል እየሆነላችሁ ይመጣል። መጀመሪያ የነበራችሁ የመዘግነን ወይም የፍራቻ ስሜት ወዲያውኑ ተለውጦ እነዚህን የቡሊሚያ ሂደቶች በተደጋጋሚ እንድታደርጉ ግፊት ያድርባችኋል።”
አኖሬክሲያ እና ቡሊሚያ “የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች” ተብለው ተጠርተዋል። ምንም እንኳ ሁለቱ የአመጋገብ ሥርዓት መዛባቶች ፍጹም የተለያዩ ምልክቶች ቢኖሯቸውም ሁለቱም ከምግብ ጋር በተያያዘ ከልክ በላይ በሚፈጠር ጭንቀት የሚከሰቱ ነገሮች ናቸው።d ሆኖም ከአኖሬክሲያ ይልቅ ቡሊሚያን ደብቆ መያዝ በጣም ቀላል ነው። ደግሞም የበሽታው ተጠቂ ብዙ መብላቷ ክብደት እንዳትቀንስ የሚያደርጋት ሲሆን ምግቡን ማስወጣቷ ደግሞ ክብደት እንዳትጨምር ይረዳታል። ከዚህ የተነሳ የቡሊሚያ ተጠቂዋ ላትወፍርም ላትከሳም ትችላለች። ስለዚህ ለሚያያት ሰው የአመጋገብ ልማድዋ የተስተካከለ ሊመስል ይችላል። “ለዘጠኝ ዓመታት ያህል” ትላለች ሊንዚ የተባለች ሴት “በቀን አራቴ ወይም አምስቴ በጣም ብዙ እበላና መልሼ አወጣው ነበር። . . . የቡሊሚያ ተጠቂ መሆኔን ማንም አያውቅም ነበር። ምክንያቱም ጤናማና ደስተኛ እንደሆንኩ እንዲሁም ተገቢ የሰውነት ክብደት እንዳለኝ ከሚያሳይ ገጽታ ጀርባ በጥንቃቄ ሰውሬው ስለነበር ነው።”
ይሁን እንጂ ያለ ልክ የመብላት ሱስ የተጠናወታት ሴት ሁኔታ በመጠኑ ቢሆን ከዚህ ይለያል። እንደ ቡሊሚያ ተጠቂዋ ሁሉ ይህች ሴት በአንዴ ብዙ ምግብ ትበላለች። ዘ ኒው ቲንኤጅ ቦዲ ቡክ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ይህ ቁንጣን እስኪይዝ ድረስ የመብላት ልማድ ምግቡን ማስወጣት ስለማይጨምር አለልክ የመብላት ሱስ ያለባት ሴት ውፍረቷ በመጠኑ ሊጨምር አሊያም ከልክ በላይ ልትወፍር ትችላለች።”
በጤንነት ላይ የሚደቀን አደጋ
ሦስቱም የአመጋገብ ሥርዓት መዛባቶች በአንድ ሰው ጤንነት ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ። አኖሬክሲያ ስር የሰደደ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሊያስከትል የሚችል ሲሆን በብዙ አጋጣሚዎች ደግሞ፣ አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ እስከ 15 በመቶ ድረስ ገዳይ ሊሆን ይችላል። ቁንጣን እስኪይዝ መብላት፣ በኋላ ምግቡ ወጣም አልወጣ ለጤና አደገኛ ነው። ከልክ በላይ መወፈር በመጨረሻ ለሕይወት አስጊ የሆነ የልብና የስኳር በሽታ አልፎ ተርፎም አንድ ዓይነት የካንሰር በሽታ ሊያስከትል ይችላል። እየጓጎጡ ማስመለስ ጉሮሮን ሊሰነጥቅ የሚችል ሲሆን በሚያስቀምጥ ወይም በሚያሸና መድኃኒት አላግባብ መጠቀም ደግሞ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ሲደርስ የልብ ድካም ሊያስከትል ይችላል።
ሆኖም ግምት ውስጥ መግባት ያለበት ሌላ የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት ዘርፍ አለ። አኖሬክሲያ፣ ቡሊሚያና አለልክ የመብላት ሱስ የተጠናወታቸው ሰዎች በጥቅሉ ደስተኞች አይደሉም። ለራሳቸው ዝቅተኛ ግምት የሚኖራቸው ሲሆን በጭንቀት ወይም በድባቴ የመሰቃየታቸው አጋጣሚ ከፍተኛ ስለሆነ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ የተዛባ የአመጋገብ ልማድ ያላቸው ሰዎች ስለ ውፍረት ከመጨነቅ እንዲላቀቁ መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው? ይህ ጥያቄ ወደፊት በሚወጣ ርዕስ ላይ መልስ ያገኛል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a አኖሬክሲያ በወንዶችም ላይ ሊከሰት ይችላል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የአኖሬክሲያ ተጠቂዎች ሴቶች ስለሆኑ በሽተኞቹን የምንጠቅሰው በአንስታይ ጾታ ይሆናል።
b ከሕክምና አንጻር አንዲት ሴት የሰውነቷ ክብደት ከትክክለኛው መጠን በታች ቢያንስ 15 በመቶ ከቀነሰና ለሦስት ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ወራት የወር አበባዋ ከተቋረጠ የአኖሬክሲያ ተጠቂ ነች።
c የሚያስቀምጥ ወይም ብዙ የሚያሸና መድኃኒት በመውሰድ የበሉት ምግብ ከሰውነታቸው እንዲወገድ የሚያደርጉም አሉ።
d በርካታ የበሽታው ተጠቂዎች የአኖሬክሲያና የቡሊሚያ የአመጋገብ ልማዶች ይፈራረቁባቸዋል።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ስለ ራስ ቁመና የተዛባ አመለካከት መያዝ
አብዛኞቹ ልጃገረዶች ስለ ውፍረት የሚጨነቁት እንዲያው ከመሬት ተነስተው ነው። በአንድ ጥናት መሠረት በ5 እና በ17 ዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ልጃገረዶች መካከል 58 በመቶ የሚሆኑት ወፍራም እንደሆኑ ቢሰማቸውም በትክክል ወፍራም የሆኑት ግን 17 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ነበሩ። በሌላ ጥናት መሠረት ደግሞ ኪሎአቸው ከተገቢው በታች የሆነ 45 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በጣም ወፍራም እንደሆኑ ይሰማቸዋል! በካናዳ የተካሄደ አንድ ጥናት በዚያ የሚኖሩ 70 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ውፍረት በጣም እንደሚያሳስባቸው ደርሶበታል። እንዲሁም 40 በመቶ የሚሆኑት አንዴ ውፍረታቸውን እንዲጨምር አንዴ ደግሞ እንዲቀንስ የሚያደርግ የአመጋገብ ሥርዓት የሚከተሉ ናቸው።
በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ስለ ራስ ቁመና የተዛባ አመለካከት መያዝ አንዳንድ ልጃገረዶችን በማያስጨንቅ ነገር ከልክ በላይ እንዲጨነቁ ሊያደርጋቸው ይችላል። “ለመክሳት የሚረዱ እንክብሎችን በብዛት የምትወስድ ጓደኛ አለችኝ። እንዲሁም የአኖሬክሲያ ተጠቂ እንደሆኑ የማውቃቸው ጥቂት ልጃገረዶችም አሉ” ስትል የ16 ዓመቷ ክሪስቲን ተናግራለች። በመቀጠልም “በፍጹም አንዳቸውም ወፍራም አይደሉም” ብላለች።
ከዚህ የተነሳ ኤፍ ዲ ኤ ከንሲውመር የተባለው መጽሔት የሚከተለውን ምክር ይሰጣል:- “‘ሁሉም ሰው’ የሚያደርገው ነው በሚል ወይም አንቺ የምትፈልጊውን ያህል ሸንቃጣ ባለመሆንሽ ምክንያት የምግብ መጠንሽን ከመቀነስ ይልቅ በመጀመሪያ የሰውነትሽ ክብደት በጣም ከፍተኛ መሆኑን ወይም ከዕድሜሽና ከቁመትሽ አንጻር ብዙ የተጠራቀመ ስብ እንዳለሽ ለማወቅ ሐኪም ወይም የስነ ምግብ ባለሙያ አማክረሽ ለማወቅ ሞክሪ።”
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙዎች ስለ ውፍረት የሚጨነቁት አላንዳች ምክንያት ነው