የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 9/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ድምፅ የሚያስከትለው መዘዝ
  • የአውሮፓ መጠነ ወሊድ እያሽቆለቆለ ነው
  • አሳቢ አባቶች ያሏቸው ወንዶች ልጆች ደስተኞች ናቸው
  • ብርድ ልብስ ውስጥ ሆኖ ማንበብ
  • በእንፋሎት የሚሠራ ባቡር ዳግም ሥራ ላይ ይውል ይሆን?
  • አስቀድሞ ማወቅ ሕይወት ያተርፋል
  • አብሮ መመገብ
  • የአዘቦት ልብስ ለብሶ ቤተ ክርስቲያን መሄድ
  • ለከፋ ድህነት የሚዳርጉ የቀብር ሥርዓቶች
  • ላለመውደቅ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሥራት
  • በዛሬው ጊዜ ያለው ሥነ ምግባር ምን ይመስላል?
    ንቁ!—2000
  • ፈገግታ—ብዙ ጥቅም ያስገኝልሃል!
    ንቁ!—2000
  • ፈገግታ የሚያሳድረው ስሜት
    ንቁ!—2003
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—1997
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 9/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

ድምፅ የሚያስከትለው መዘዝ

ሕንድ ወደ አንድ ቢልዮን የሚጠጋ ሕዝብ አላት። በሕንድ ቻንዲጋር ውስጥ በሚገኘው የድሕረ ምረቃ ኢንስቲትዩት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ኤስ ቢ ኤስ ማን እንዳሉት ከሆነ ከ10 ሰዎች አንዱ ወይም ደግሞ አንድ መቶ ሚልዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በሆነ መልኩ የመስማት ችግር አለባቸው። የሕንድ ከአንገት በላይ ሐኪሞች ማኅበር ባካሄደው ዓመታዊ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ዶክተር ማን ባደረጉት ንግግር ከመኪኖች ጥሩንባ፣ ከሞተሮች፣ ከማሽኖችና ከአውሮፕላኖች የሚወጣው ኃይለኛ ድምፅ ለዚህ የጤና እክል ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል። በይበልጥ ደግሞ በበዓል ቀናት በብዛት የሚተኮሱት ርችቶች ዋነኛ መንስኤ ተደርገው ሊጠቀሱ እንደሚችሉ ዶክተር ማን ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል በዳሴራ ክብረ በዓል ወቅት በመላ አገሪቱ በኅብረተሰቡ ውስጥ አሉ ተብለው የሚታሰቡትን ክፉ ኃይሎች የሚወክሉ በርችቶች የተሞሉ ግዙፍ የሂንዱ አፈ ታሪካዊ ገጸ ባሕርያት ምስሎች አገሪቷን በከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ ይንጧታል። ይህን ወቅት ተከትሎ የሚመጣው ለአምስት ቀናት የሚቆየው የዲፓቫሊ ክብረ በዓል ደግሞ በሚልዮኖች በሚቆጠሩ ርችቶች ፍንዳታ የተሞላ ነው።

የአውሮፓ መጠነ ወሊድ እያሽቆለቆለ ነው

“የአውሮፓ ኅብረት አገሮች መጠነ ወሊድ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ያለፈውን ዓመት ያህል ቀንሶ አያውቅም” ሲል ሱትዶይቼ ሳይቱንግ ዘግቧል። ዩሮስታት የተባለው የአውሮፓ ኀብረት የእስታትስቲካዊ መረጃ ድርጅት በ1998 የአውሮፓ ኅብረት አባል በሆኑ አገሮች ውስጥ አራት ሚልዮን ገደማ ሕፃናት የተወለዱ መሆናቸውን ያስታወቀ ሲሆን በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ ይህ አኃዝ በዓመት ስድስት ሚልዮን ገደማ ነበር። በአማካይ ሲታይ በአውሮፓ ኅብረት አገሮች ውስጥ በየዓመቱ በ1,000 ሰዎች መካከል 10.7 ሕፃናት ይወለዳሉ ማለት ነው። የመጨረሻው ዝቅተኛ መጠነ ወሊድ የተመዘገበባት አገር ማን ናት? ምንም እንኳ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የወሊድ ቁጥጥርን የምታወግዝ ቢሆንም ዝቅተኛውን መጠነ ወሊድ ያስመዘገበችው ኢጣሊያ ናት። በ1,000 ነዋሪዎች መካከል የተወለዱት ሕፃናት 9.2 ብቻ ናቸው። አየርላንድ ከፍተኛውን መጠነ ወሊድ ያስመዘገበች ሲሆን በ1,000 ሰዎች መካከል 14.1 ሕፃናት ተወልደዋል።

አሳቢ አባቶች ያሏቸው ወንዶች ልጆች ደስተኞች ናቸው

የሚያሳስቧቸውን ነገሮች፣ ትምህርታቸውንና ማኅበራዊ ኑሯቸውን በቅርብ የሚከታተሉ አባቶች ያሏቸው ወንዶች ልጆች “ነቃ ያሉና አዎንታዊ አመለካከት የሚንጸባረቅባቸው እንዲሁም በራስ የመተማመን መንፈስና ብሩህ ተስፋ ያላቸው ናቸው” ሲል ዘ ታይምስ የተባለው የለንደን ጋዜጣ ዘግቧል። የነገዎቹ ባለ አደራዎች የተባለው ፕሮጀክት ከ13 እስከ 19 ዓመት ዕድሜ ላይ በሚገኙ 1,500 ወንዶች ልጆች ላይ ያካሄደው አንድ ጥናት አባቶቻቸው ከእነሱ ጋር ጊዜ እንደሚያሳልፉና ዕድገታቸውን በቅርብ እንደሚከታተሉ ሆኖ ከሚሰማቸው ልጆች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት “ከፍተኛ የሆነ በራስ የመተማመን መንፈስ እንዳላቸውና ደስተኞች” እንደሆኑ አመልክቷል። በአንጻሩ አባቶቻቸው እምብዛም ትኩረት እንደማይሰጧቸው ወይም ደግሞ ለእነሱ ግድ እንደሌላቸው ሆኖ ከሚሰማቸው ልጆች መካከል 72 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች ልጆች “በራስ የመተማመን መንፈሳቸው በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ ጭንቀት እንዳለባቸው፣ ትምህርት እንደሚያስጠላቸውና ከፖሊስ ጋር እንደሚጋጩ” ተረጋግጧል። በነገዎቹ ባለ አደራዎች ፕሮጀክት ውስጥ የሚሠሩት አድሪን ካትስ አባትየውና ልጁ አብረው የሚያሳልፉት ጊዜ የግድ ረጅም መሆን የለበትም ሲሉ ገልጸዋል። “ዋናው ነገር ልጁ ተፈላጊና ተወዳጅ እንደሆነ እንዲሁም የሚያደምጠው እንዳለ እንዲሰማው ማድረግ ነው” ብለዋል።

ብርድ ልብስ ውስጥ ሆኖ ማንበብ

ብርድ ልብስ ውስጥ ሆኖ በደብዛዛ ብርሃን ማንበብ የአንድን ልጅ ዓይን ሊጎዳ እንደሚችል አፖቴከን ኡምሾው የተባለው የጀርመን የጤና በራሪ ወረቀት ዘግቧል። በቱቢንገን ዩኒቨርሲቲ በጫጩቶች ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት እይታ በትንሹም ቢሆን በሚዛባበትና ብርሃን በሚደበዝዝበት ጊዜ የአይነኳስ እድገት እክል ሊገጥመው እንደሚችል አመልክቷል። አንድ ልጅ ብርድ ልብስ ውስጥ ሆኖ በሚያነብበት ጊዜ ሁለቱም ሁኔታዎች ይፈጠራሉ:- መጽሐፉን ወደ ዓይኑ በጣም በሚያስጠጋበት ጊዜ ዓይኑ በትክክል ማየት ስለማይችል እይታው ይዛባል፤ የሚያገኘው ብርሃንም ደብዛዛ ነው። “በአሁኑ ጊዜ ያሉት በአሥራዎቹ ዓመታት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የእጅ ባትሪ በመያዝ ብርድ ልብስ ውስጥ ሆነው የሚወዷቸውን ታሪኮች በጉጉት ያነባሉ። እንዲህ ማድረጋቸው ለሥነ ጽሑፍ ትምህርታቸው መሠረት የሚጥልላቸው ቢሆንም ከርቀት የማየት ችሎታቸውንም የሚያዳክም ነው” ሲል በራሪ ወረቀቱ ገልጿል።

በእንፋሎት የሚሠራ ባቡር ዳግም ሥራ ላይ ይውል ይሆን?

በባቡር መጓዝ የሚወዱ ሰዎች በቀድሞዎቹ ዘመናት የነበሩትን በእንፋሎት የሚሠሩ አስደናቂ ባቡሮች ሲያስቡ በስሜት ይዋጣሉ። እነዚህ የቀደምት ዘመን ባቡሮች ብቃታቸው አጥጋቢ ባለመሆኑና ከፍተኛ ብክለት የሚያስከትሉ በመሆናቸው ከትራንስፖርቱ ዓለም ወደ መገለል ደረጃ ቢደርሱም በአንድ የስዊስ የባቡር ፋብሪካ ውስጥ በኤንጂኒየርነት የሚያገለግሉት ሮዤ ቫለር የእንፋሎት ኃይል ወደፊት በሰፊው ጥቅም ላይ የመዋል ተስፋ እንዳለው ያምናሉ። በአሁኑ ጊዜ በእንፋሎት የሚሠሩ ስምንት የኩባንያው ባቡሮች በአልፕስ ተራራማ ቦታዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ቤርሊነር ሳይቱንግ ዘግቧል። ከዚህም በተጨማሪ ቫለር በቅርቡ በእንፋሎት የሚሠራ አንድ የድሮ ባቡር በዘመናዊዎቹ ሃዲዶች ላይ ግልጋሎት መስጠት እንዲችል አሻሽለው ሠርተውታል። ይህ ተሻሽሎ የተሠራው ባቡር በከሰል ሳይሆን በነዳጅ የሚሠራ በመሆኑ ብክለትን ሊቀንስ ችሏል። በተጨማሪም ሰበቃውን ለመቀነስ እንክብል ኩሽኔታ የተገጠመለት ከመሆኑም በላይ የሚጠፋውን ጉልበትና የማሞቂያ ጊዜ በእጅጉ የሚቀንስ ጥሩ የሙቀት ማገጃ አለው። “ከፍተኛ ወጪ የማይጠይቅ ከመሆኑም በተጨማሪ ከየትኛውም በዲዝል ከሚሠራ ባቡር ይበልጥ ለአካባቢያዊ ሁኔታ ተስማሚ ነው” ሲሉ ቫለር ገልጸዋል።

አስቀድሞ ማወቅ ሕይወት ያተርፋል

“ለካንሰር በሽታዎች ተገቢውን ክትትልና ሕክምና ለማግኘት ቁልፉ አስቀድሞ በሽታውን ማወቅ ነው” ሲል ታይምስ ኦቭ ዛምቢያ በተባለው ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ዘገባ ገልጿል። የሚያሳዝነው ግን በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች ምርመራ ቢያደርጉ ኖሮ አስቀድሞ ሊታወቁ ይችሉ በነበሩ የካንሰር በሽታዎች ይሞታሉ። አብዛኛውን ጊዜ በሴቶች ላይ የሚከሰቱት የካንሰር በሽታዎች የማኅፀን ካንሰርና የጡት ካንሰር ናቸው። በወንዶች ላይ በብዛት የሚከሰቱት ደግሞ የፕሮስቴት እጢ ካንሰርና የአንጀት ካንሰር ናቸው። በዚህም የተነሳ የዛምቢያ ማዕከላዊ የጤና ቦርድ ሕዝቡ ወደ ሆስፒታሎች በመሄድ የካንሰር ምርመራ እንዲያደርግ ምክር ለግሷል። አስቀድሞ ማወቁ “በታማሚውም ላይ ሆነ በቤተሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ሥቃይና የስሜት ቀውስ ይቀንሰዋል። ሐኪሞችም በወቅቱ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንዲችሉ ይረዳቸዋል” ሲል ታይምስ ገልጿል።

አብሮ መመገብ

በብዙ አገሮች ወላጆች ልጆቻቸው ተዘጋጅተው የሚሸጡ ፈጣን ምግቦችን መመገብ የሚመርጡ በመሆኑ እምብዛም አብረዋቸው እንደማይመገቡ በምሬት ይናገራሉ። በፈረንሳይ ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ላ ክርዋ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ እንዳለው ከሆነ በፈረንሳይ ውስጥ ካሉት ቤተሰቦች መካከል 84 በመቶ የሚሆኑት እራታቸውን አብረው እንደሚበሉ በቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናት አመልክቷል። እንዲያውም ጥናቱ እንዳረጋገጠው ከ12 እስከ 19 ዓመት ድረስ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ወጣቶች መካከል 95 በመቶዎቹ ቤተሰቡ አብሮ በሚመገብበት ጊዜ የሚኖረው መንፈስ ገንቢ እንደሆነ ያምናሉ። ጠበብት ዘወትር በቤተሰብ ደረጃ አንድ ላይ ሆኖ መብላት በጣም ጠቃሚ እንደሆነ አጥብቀው ይናገራሉ። የፈረንሳይ የጤና ትምህርት ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ፍራንስዋ ቦድዬ “የምግቡ ሰዓት የመመገቢያ ጊዜ ብቻ ሳይሆን የሐሳብ ልውውጥ የሚደረግበትም ጊዜ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የአዘቦት ልብስ ለብሶ ቤተ ክርስቲያን መሄድ

በዩናይትድ ስቴትስ የአዘቦት ልብስ ለብሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ አሶሲዬትድ ፕሬስ ዘግቧል። አንዳንድ ቄሶች ቁምጣ፣ ጂንስ፣ ወይም ሌሎች የአዘቦት ልብሶችን ለብሰው በቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ የሚገኙ ምዕመናንን መመልከቱ በጣም ይረብሻቸዋል። የቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣናት የአዘቦት ልብስ እየለበሱ የሚመጡትን አዳዲስ አባላት ማባረርም ሆነ እንዲህ ዓይነት አለባበስ ያላቸውን ቋሚ ምእመናን ማስቆጣት ስለማይፈልጉ ምን እንደሚያደርጉ ግራ ገብቷቸዋል። አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ “ወደ 30 በመቶ የሚጠጉት አሜሪካውያን ዘና ያለ መንፈስ የሰፈነባቸውና ዘመናዊ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ ሥነ ሥርዓቶች የሚመርጡ ሲሆን” ባሕላዊውን የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት የሚመርጡት ግን 21.5 በመቶዎቹ ናቸው።

ለከፋ ድህነት የሚዳርጉ የቀብር ሥርዓቶች

“ኑሮ እየተወደደ ቢሄድም” ይላል ታይምስ ኦቭ ዛምቢያ፣ “ከቀብር ሥርዓት ጋር በተያያዘ የሚወጣው ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ መጥቷል።” ዛምቢያን ጨምሮ በብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች አብዛኛውን ጊዜ የቀብር ሥርዓቶች ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ዘመድ አዝማዶች መጥተው ለሳምንት ወይም ከዚያ በላይ በሚቆየው የለቅሶ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲገኙ ሲባል እንዲዘገዩ ይደረጋል። ብዙውን ጊዜ በቀብር ሥርዓቱ ላይ የሚገኘው ዘመድ አዝማድ በሙሉ ኀዘን ላይ የተቀመጠው ቤተሰብ ምግብና ማረፊያ እንደሚያቀርብለት እርግጠኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የሟቹ ቤተሰብ ችግረኛ የሆኑት ዘመዶች ወደ ቤታቸው የሚመለሱበትን የትራንስፖርት ወጪ መሸፈን ይጠበቅበታል። እንዲህ ዓይነት የቀብር ሥርዓቶች ሐዘን የደረሰባቸውን ብዙ ቤተሰቦች ለከፋ ድህነት ይዳርጓቸዋል። “ዘመናዊ የቀብር ሥርዓቶች” ይላል ዘገባው፣ “በምንም መልኩ እገዛ የማያደርጉ በርካታ ለቀስተኞች የሚስተናገዱባቸው በመሆኑ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ሆነዋል።” የሟቹን ቤተሰብ ሸክም ማቅለል ይቻል ዘንድ የቀብር ሥርዓቶች ግለሰቡ ከሞተ በኋላ ወዲያውኑ ቢከናወኑ የተሻለ እንደሚሆን ጋዜጣው የበኩሉን ሐሳብ ሰንዝሯል።

ላለመውደቅ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሥራት

“ከ65 ዓመት ዕድሜ በላይ ከሆናቸው ሰዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ቢያንስ ቢያንስ በዓመት አንዴ የሚወድቁ ሲሆን ብዙዎቹም ሙሉ በሙሉ ላይድኑ የሚችሉ እንደ ዳሌ ስብራት የመሳሰሉ ጉዳቶች ይደርሱባቸዋል” ይላል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ። ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ ሰውነታችን ያለበትን ሁኔታ የመለየት ችሎታው እየቀነሰ ስለሚሄድ ሚዛናችንን ለመጠበቅ እንቸገራለን። በቅርቡ በኮኔቲከት የሕክምና ፋኩልቲ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደ አንድ ጥናት በአንድ እግር መቆምን ወይም በተጋደመ ጣውላ ላይ መሄድን የመሳሰሉ ሚዛንን ለመጠበቅ የሚረዱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ዘወትር መሥራት በዕድሜ የገፉ ሰዎች ሚዛናቸውን የመጠበቅ ብቃታቸውን ሊያሻሽልላቸው እንደሚችል አመልክቷል። ይሁን እንጂ የሱሊቫንና የክሮምዌል የአካል ብቃት ማሠልጠኛ ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ጂና አልቺን ሚዛንን ለመጠበቅ የሚረዱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ቀስ በቀስ ጀምሮ እያንዳንዱን ክፍለ ጊዜ በአሥር ደቂቃ ብቻ በመወሰን በሳምንት ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ መሥራቱ የተሻለ እንደሚሆን ገልጸዋል። “እንዲህ ዓይነቱ ልምምድ ቀላል ሊመስል ቢችልም ልምምዱን ከልክ በላይ የምትሠሩ ከሆነ ልትዝሉና የሰውነት ቁስለት ሊያስከትልባችሁ ይችላል” ብለዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ