ጤናማ አመለካከት ይዘህ መኖር የምትችልበት መንገድ
አካላዊ ጤናችን በአብዛኛው የተመካው በምንመገበው ምግብ ላይ ነው። አንድ ሰው ዘወትር አሸር ባሸር የሆነ ምግብ የሚመገብ ከሆነ ውሎ አድሮ ጤንነቱ መጎዳቱ አይቀርም። የአእምሯችንን ጤና በተመለከተም ይኸው መሠረታዊ ሥርዓት ይሠራል።
ለምሳሌ ያህል ወደ አእምሯችን የምናስገባውን ነገር እንደ አእምሮ ምግብ አድርገህ ልትወስደው ትችላለህ። የአእምሮ ምግብ? አዎን፣ የምንበላው ምግብ በሰውነታችን ላይ ለውጥ እንደሚያስከትል ሁሉ ከመጻሕፍት፣ ከመጽሔቶች፣ ከቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ከቪዲዮዎች፣ ከቪዲዮ ጨዋታዎች፣ ከኢንተርኔትና ከዘፈን ግጥሞች የምንቀስመው መረጃ በአስተሳሰባችንና በባህሪያችን ላይ ለውጥ ሊያስከትል ይችላል። እንዴት?
በአንድ ወቅት የማስታወቂያ ሥራ ኃላፊ የነበሩት ጄሪ ማንደር ቴሌቪዥን በሕይወታችን ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በተመለከተ ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል:- “ቴሌቪዥን ከሚያሳድረው ተጽእኖ ሁሉ የከፋው በአእምሯችን ውስጥ አንድ ምስል ትቶ የሚያልፍ መሆኑ ነው።” ይሁን እንጂ እነዚህ አእምሮ ውስጥ ተቀርጸው የሚቀሩ ምስሎች ከማዝናናትም በተጨማሪ የሚያከናውኑት ነገር አለ። ዘ ፋምሊ ቴራፒ ኔትወርከር የተባለው መጽሔት እንዲህ ይላል:- “የመገናኛ ብዙሃን ቋንቋ፣ ምስል፣ ድምፅ፣ አመለካከት፣ ባሕርይ፣ ሁኔታ፣ ደንብና ጽንሰ ሐሳብ የአስተሳሰባችንና የስሜታችን ዋና አካል ይሆናሉ።”
አዎን፣ አወቅነውም አላወቅነው አስተሳሰባችንና ስሜታችን በቴሌቪዥንም ሆነ በሌሎች የመዝናኛ ዓይነቶች በምንመለከተው ነገር ቀስ በቀስ ሊቀረጽ ይችላል። አደጋው ያለው እዚህ ላይ ነው። ማንደር እንዳሉት “ሰዎች ስንባል ቀስ በቀስ በአእምሯችን ውስጥ የተቀረጸውን ምስል የመምሰል ዝንባሌ አለን።”
አእምሮን የሚመርዝ
ብዙ ሰዎች ለሚመገቡት ምግብ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያደርጉ ቢሆንም እንኳ በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የሚቀርብላቸውን የአእምሮ ምግብ ምንም ሳይመርጡ የሚያግበሰብሱ ናቸው። ለምሳሌ ያህል “ደሞ በቴሌቪዥን ምን የሚታይ ደህና ነገር አለ!” ብሎ ሲናገር የሰማኸው ሰው አለ? አንዳንዶች የቴሌቪዥን ምርኮኛ በመሆናቸው አንድ ጠቃሚ የሆነ ነገር ይታይ ይሆናል በሚል ተስፋ ቴሌቪዥን ላይ አፍጥጠው ይውላሉ። ቴሌቪዥኑን የመዝጋት ሐሳብ ፈጽሞ ወደ አእምሯቸው አይመጣም!
ብዙዎቹ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ጊዜ ከመብላታቸውም በላይ ክርስቲያኖች ሊርቋቸው የሚገቡ ተገቢ ያልሆኑ መልእክቶች ያዘሉ ናቸው። የኪነ ጥበብ ደራሲ የሆኑት ጋሪ ኮልቱኪያን ፕሮግራሞቹ “ጸያፍ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ከቀድሞው በበለጠ ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ የቴሌቪዥን መስኮቶችን ያጣበቡት አከራካሪና ወሲባዊ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው” ብለዋል። እንዲያውም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናት ብዙ ሰዎች ቴሌቪዥን በሚመለከቱበት ወቅት ላይ በየሰዓቱ በአማካይ 27 ጊዜ ጾታዊ ይዘት ያላቸው ትዕይንቶች እንደሚቀርቡ አመልክቷል።
አንድ ሰው ይህ ሁሉ በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ ማሰቡ አይቀርም። በጃፓን አንድ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማ የብዙ ሰዎችን ቀልብ በመሳብ “ምንዝር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲስፋፋ” አድርጓል በማለት የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል። በተጨማሪም ዎቺንግ አሜሪካ የተባለው መጽሐፍ ደራሲዎች “በዛሬው ጊዜ አብዛኛው ጾታዊ ምግባር ... ተቀባይነት ያለው የግል አኗኗር ምርጫ እንደሆነ ተደርጎ በመታየት ላይ ነው” ብለዋል።
ሆኖም ጾታዊ መልእክት የሚያስተላልፉ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች የችግሩ አንድ አካል ብቻ ናቸው። ቁልጭ ባለ መንገድ የሚቀርቡት የዓመፅ ድርጊቶችም የተለመዱ ናቸው። ይበልጥ የሚያሳስበው ደግሞ የዓመፅ ድርጊቶችን የሚያሳዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች ያየውን ነገር ሁሉ በቀላሉ የሚቀበል አእምሮ ባላቸው ሕፃናት ላይ ሊያሳድሩ የሚችሉት ጎጂ ተጽዕኖ ነው። የጦር ሠራዊት ጡረተኛ መኮንንና በግድያ ወንጀል የሥነ ልቦና ጠበብት የሆኑት ዴቪድ ግሮስማን “ትንንሽ ልጆች በቴሌቪዥን አንድ ሰው በጥይት ሲመታ፣ በስለት ሲወጋ፣ በጾታ ሲነወር፣ ኢሰብዓዊ ድርጊት ሲፈጸምበት፣ ሲዋረድ ወይም ሲገደል ሲመለከቱ በእውን እየተፈጸመ እንዳለ አድርገው ያስባሉ” ብለዋል። ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን ይህንኑ ችግር አስመልክቶ የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥቷል:- “እስከ 3 እና 4 ዓመት ድረስ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ብዙዎቹ ልጆች በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ የሚቀርቡትን እውነታዎች ከልብ ወለዶቹ መለየት ስለማይችሉ ትልልቅ ሰዎች ቢነግሯቸውም እንኳ ሊረዱት አይችሉም።” በሌላ አነጋገር አንድ ወላጅ ልጁን ‘እነዚህ ሰዎች የሞቱ ለማስመሰል ብለው ነው እንጂ አልሞቱም’ ቢለው እንኳ የልጁ አእምሮ ልዩነቱን ሊገነዘብ አይችልም። ልጁ በቴሌቪዥን የሚያየውን የዓመፅ ድርጊት ሁሉ በእውን እንደሚፈጸም ነገር አድርጎ ይወስደዋል።
ታይም መጽሔት “በመገናኛ ብዙሃን የሚታየው የዓመፅ ድርጊት” ያሳደረውን ተጽዕኖ ጠቅለል አድርጎ በመግለጽ እንዲህ ብሏል:- “በአሁኑ ጊዜ በቴሌቪዥንና በፊልሞች የሚታየው ደም መፋሰስ በሚመለከቱት ሕፃናት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አሳስቧቸው የሚከራከሩ ተመራማሪዎች እምብዛም የሉም።” ይህ ምን ዓይነት ተጽዕኖ አለው? “ላለፉት አሥርተ ዓመታት በመዝናኛዎች ሲተላለፍ የቆየው የዓመፅ ድርጊት የሰዉን አመለካከትና የሥነ ምግባር መሥፈርት አዛብቶታል” ሲሉ የፊልም ሃያሲ የሆኑት ማይክል ሜድቬድ ተናግረዋል። አክለውም “አንድ ኅብረተሰብ መጥፎ ነገር ሲያይ የማይሰቀጥጠው ከሆነ አዝማሚያው ጥሩ አይደለም” ብለዋል። አንድ ደራሲ አንድን የአራት ዓመት ልጅ የዓመፅ ድርጊት ሲፈጸም የሚያሳይ ፊልም እንዲመለከት ማድረግ “አእምሮውን መመረዝ ነው” ማለታቸው ምንም አያስደንቅም።
እርግጥ ይህ ማለት ሁሉም የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች መጥፎ ናቸው ማለት አይደለም። መጻሕፍትን፣ መጽሔቶችን፣ ቪዲዮዎችን፣ የኮምፒዩተር ጨዋታዎችንና ሌሎች የመዝናኛ ዓይነቶችን በተመለከተም ይኸው አባባል ይሠራል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ግን መዝናኛ ተብሎ የሚጠራው አብዛኛው ነገር ጤናማ አመለካከት ይዘው ለመኖር ለሚፈልጉ ሰዎች የሚስማማ አይደለም።
መዝናኛን በጥበብ ምረጥ
በዓይናችን አማካኝነት ወደ አእምሯችን የምናስገባው ምስል በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል። ለምሳሌ ያህል አእምሯችንን አዘውትረን ምግባረ ብልሹ መዝናኛ የምንመግበው ቢሆን ኖሮ “ከዝሙት ሽሹ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ለመከተል ያለን ቁርጥ አቋም ሊላላ ይችል ነበር። (1 ቆሮንቶስ 6:18) በተመሳሳይም ‘ዓመፅን የሚያደርጉ ሰዎችን’ የሚያሳይ መዝናኛ የምንመለከት ከሆነ ‘ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር’ ልንቸገር እንችላለን። (መዝሙር 141:4፤ ሮሜ 12:18) ይህን ለማስወገድ ዓይናችንን ከ“ክፉ” ነገር ዞር ማድረግ አለብን።—መዝሙር 101:3፤ ምሳሌ 4:25, 27
ሁላችንም በወረስነው አለፍጽምና ምክንያት ትክክል የሆነውን ነገር ማድረጉ ትግል እንደሚጠይቅብን የታወቀ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል በግልጽ ተናግሯል:- “በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፣ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።” (ሮሜ 7:22, 23) ይህ ማለት ጳውሎስ ለሥጋዊ ድክመቱ እጁን ሰጥቶ ነበር ማለት ነውን? በፍጹም! “ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጐሰምሁ አስገዛዋለሁ” ሲል ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 9:27
እኛም አለፍጽምናችንን ለኃጢአት ማመካኛ አድርገን መጠቀም የለብንም። የመጽሐፍ ቅዱሱ ጸሐፊ ይሁዳ “ወዳጆች ሆይ፣ ... ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” ሲል ተናግሯል። (ይሁዳ 3, 4) አዎን፣ ‘መጋደልና’ መጥፎ ነገር እንድንሠራ ከሚገፋፋን መዝናኛ መራቅ ይኖርብናል።a
መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት ጣር
በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ጤናማ አመለካከት ማዳበር ሁልጊዜ ቀላል አይሆንም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በአእምሮም ሆነ በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆኖ መኖር እንደሚቻል ያረጋግጥልናል። እንዴት? መዝሙር 119:11 ላይ “አንተን እንዳልበድል፣ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ” የሚል ቃል እናነባለን።
የአምላክን ቃል በልብ መሰወር ማለት እንደ ውድ ነገር መመልከት ወይም ከፍ ያለ ግምት መስጠት ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል የማናውቅ ከሆነ ቃሉን ከፍ አድርጎ መመልከቱ አስቸጋሪ እንደሚሆንብን የታወቀ ነው። የአምላክን ቃል ትክክለኛ እውቀት በመመገብ የአምላክን አስተሳሰብ እንቀስማለን። (ኢሳይያስ 55:8, 9፤ ዮሐንስ 17:3) ይህም በምላሹ በመንፈሳዊ የሚያበለጽገን ከመሆኑም በላይ አስተሳሰባችንን ያሻሽለዋል።
በአእምሮና በመንፈሳዊ ጤናማ የሆነን ነገር ማወቅ የሚቻልበት አስተማማኝ መስፈርት አለ? አዎን! ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል:- “እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፣ እነዚህን አስቡ።”—ፊልጵስዩስ 4:8
ሆኖም የተሟላ ጥቅም ማግኘት እንድንችል ስለ አምላክ ከማወቅ በተጨማሪ የሚያስፈልገን ነገር አለ። ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈስ አነሳሽነት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።” (ኢሳይያስ 48:17፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) አዎን፣ መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት መጣር ብቻ ሳይሆን ያገኘነውን እውቀትም ተግባራዊ ማድረግ አለብን።
በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ጥቅም ማግኘት የምንችልበት ሌላው መንገድ ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነውን ይሖዋን በመለመን ነው። (መዝሙር 65:2፤ 66:19) ፈጣሪያችንን ከልብ በመነጨ ስሜትና በትሕትና ከቀረብነው ልመናችንን ይሰማል። ‘ብንፈልገውም ይገኝልናል።’—2 ዜና መዋዕል 15:2
እንግዲያው በዚህ ዓመፀኛ በሆነና ሥነ ምግባር በጎደለው ዓለም ውስጥ የአእምሯችንን ጤና ጠብቀን መኖር እንችላለን? በሚገባ እንችላለን! አእምሯችን በዚህ ዓለም መዝናኛ እንዲደነዝዝ ባለመፍቀድ፣ የማሰብ ችሎታችንን በአምላክ ቃል ጥናት በማጠናከርና መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት በመጣር ጤናማ አመለካከት ይዘን መኖር እንችላለን!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ጤናማ መዝናኛ መምረጥን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የግንቦት 22, 1997 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 8-10 ተመልከት።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ብዙዎቹ ልጆች በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ የሚቀርቡትን እውነታዎች ከልብ ወለዶቹ መለየት አይችሉም”
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ላለፉት አሥርተ ዓመታት በመዝናኛዎች ሲተላለፍ የቆየው የዓመፅ ድርጊት የሰዉን አመለካከትና የሥነ ምግባር መሥፈርት አዛብቶታል”
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለልብ በሽታ የምትጋለጥበትን ሁኔታ መቀነስ የምትችልበት መንገድ
ኒውትሪሽን አክሽን ሄልዝሌተር የሚከተሉትን እርምጃዎች በመውሰድ ለልብ በሽታ የምትጋለጥበትን ሁኔታ መቀነስ እንደምትችል ይገልጻል።
• ሲጋራ ማጨስ አቁም። ዛሬውኑ ሲጋራ እርግፍ አድርገህ መተውህ የሰውነትህ ክብደት ቢጨምርም እንኳ ለልብ በሽታ የምትጋለጥበት አጋጣሚ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይቀንሳል።
• የሰውነትህን ክብደት ቀንስ። ከሚገባው በላይ ወፍረህ ከሆነ ከሁለት እስከ አራት ኪሎ ግራም መቀነስ እንኳ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።
• የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርግ። ቋሚ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ (ቢያንስ ቢያንስ በሳምንት ሦስት ጊዜ እንኳ) ብታደርግ በሰውነትህ ውስጥ ያለውን ጤናማ ያልሆነ የኮሌስትሮል መጠን (ኤል ዲ ኤል) ለመቀነስ፣ የደም ግፊትህ እንዳይጨምርና የሰውነትህ ክብደት ከልክ በላይ እንዳይጨምር ይረዳሃል።
• የቅባት መጠናቸው አነስተኛ የሆነ ምግቦች ተመገብ። በሰውነትህ ውስጥ ያለው የኤል ዲ ኤል መጠን ከፍተኛ ከሆነ የምትበላው ሥጋ የስብ መጠኑ አነስተኛ መሆን አለበት። በተጨማሪም 2 በመቶ ቅባት ያለው ወተት ከመጠጣት ይልቅ የቅባት መጠኑ ከ1 በመቶ የማይበልጥ (አነስተኛ ቅባት ያለው) ወተት ወይም አሬራ (ቅባት የሌለው ወተት) ለመጠጣት ሞክር።
• የምትወስደውን የአልኮል መጠን ቀንስ። ቀይ ወይን ጠጅ ሳያበዙ በመጠኑ የሚጠጡ ሰዎች ለልብ በሽታ የሚጋለጡበትን ሁኔታ ሊቀንሱ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ፍንጮች ተገኝተዋል።
• ፍራፍሬ፣ አትክልቶችና በሟሚ አሰር የዳበሩ ሌሎች ምግቦች በብዛት ተመገብ።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቴሌቪዥን የሚታየው የዓመፅ ድርጊት ለአንድ ሕፃን አእምሮ መርዝ ነው
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንድ ጊዜ ልጆች በቴሌቪዥን የሚያዩትን የዓመፅ ድርጊት ይኮርጃሉ
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆች የተለያዩ ጥሩ ጥሩ ጽሑፎችን በማቅረብ ልጆቻቸውን ሊረዷቸው ይችላሉ