‘ሰይፋቸውን ማረሻ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ’—መቼ?
በኒው ዮርክ ከተማ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሕንፃ አጠገብ የቆመ አንድ የታወቀ ሐውልት አንድ ሰው ሰይፉን ማረሻ ለማድረግ ሲቀጠቅጥ ያሳያል። ሐውልቱ በኢሳይያስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 4 እና በሚክያስ ምዕራፍ 4 ቁጥር 3 ላይ በሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ የተመሠረተ ነው። ታዲያ እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት እንዴትና መቼ ነው?
በቅርቡ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “ዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያ ሽያጭ ወደ 30 ቢልዮን ዶላር አሻቀበ” የሚል ርዕሰ አንቀጽ ይዞ ወጥቶ ነበር! በ1999 በጦር መሣሪያ ሽያጭ ቀዳሚውን ስፍራ የያዙት የትኞቹ አገሮች ነበሩ? ዩናይትድ ስቴትስ 11.8 ቢልዮን ዶላር ገቢ በማግኘት ገበያውን ትመራ ነበር። ሩሲያ የዚህን ግማሽ በማግኘት በሁለተኛነት ትከተል የነበረ ሲሆን በቅርቡ ግን የጦር መሣሪያ ሽያጭ ገቢዋን ከቀድሞው በእጥፍ አሳድጋለች። ጀርመን፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታኒያ እና ኢጣሊያ ከሦስት እስከ ሰባት ያለውን ደረጃ ይዘው ይከተሉ ነበር። መጽሔቱ ዘገባውን ሲቀጥል “እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በግምት ሁለት ሦስተኛ የሚያክለው ጦር መሣሪያ የተሸጠው በማደግ ላይ ላሉ አገሮች ነው” ብሏል።
አንድ ሰው በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሙትና ቁስለኛ ካደረጉት ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶችና በ20ኛው መቶ ዘመን ከተካሄዱት ሌሎች ብዙ ትላልቅ ጦርነቶች በኋላ “ብሔራት ከጦርነት ይልቅ ስለ ሰላም መማር የሚጀምሩት መቼ ይሆን?” የሚል ጥያቄ በአእምሮው ይመላለስበት ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ፊታቸውን ወደ ሰላም የሚያዞሩት ‘በዘመኑ ፍጻሜ’ እንደሆነ ይጠቁማል። (ኢሳይያስ 2:2) እንዲያውም ይህ ትንቢት ወደ ስድስት ሚልዮን የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች ‘ከይሖዋ ለመማር’ ራሳቸውን ባቀረቡበት በዚህ ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ነው። በዚህ ምክንያት ‘ሰላም በዝቶላቸዋል።’—ኢሳይያስ 54:13
ይሖዋ በቅርቡ ‘ምድርን የሚያበላሿትን ስለሚያጠፋ’ የጦር መሣሪያዎችንና ጦርነቶችን እንዲሁም ጠብ አጫሪዎችን ያስወግዳቸዋል። አስደናቂ ስለሚሆነው ስለዚህ ለውጥ ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ከፈለግህ በአካባቢህ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ቀርበህ መጠየቅ ወይም በዚህ መጽሔት ገጽ 5 ላይ ከሚገኙት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው መጻፍ ትችላለህ።—ራእይ 11:18