የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 9/13 ገጽ 14-15
  • ዜንግ ሂ ዜንግ ሂ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዜንግ ሂ ዜንግ ሂ
  • ንቁ!—2013
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የበላይነት፣ ንግድና ግብር
  • የርዕስ ማውጫ
    ንቁ!—2013
  • ኢንተርኔት ተጠቃሚ ወጣቶች!
    ንቁ!—2007
  • ታሪክን የቀየረ የአየር ሁኔታ
    ንቁ!—2011
  • በባሕር ላይ የሚመላለሱት “የኪቲም መርከቦች”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2013
g 9/13 ገጽ 14-15

የታሪክ መስኮት

ዜንግ ሂ ዜንግ ሂ

“በተንጣለለው ባሕር ላይ ከአንድ መቶ ሺህ ሊa የሚበልጥ ርቀት ተጉዘናል፤ እንደ ተራራ የገዘፉና ሰማይ ጠቀስ የሆኑ ማዕበሎችን ተመልክተናል። በጉዟችን ላይ በጣም ርቀው የሚገኙ ያልሠለጠኑ ሕዝቦች የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች ተመልክተናል። . . . የመርከቦቻችን ሸራዎች እንደ ደመና ቀንና ሌት ተዘርግተው በከዋክብት ፍጥነት ሲከንፉ ነበር። ግርግር በሚበዛበት የከተማ መንገድ ላይ የምናልፍ ያህል እነዚህን ኃይለኛ ሞገዶች እያቋረጥን ተጉዘናል።”—ዜንግ ሂ በአሥራ አምስተኛው መቶ ዘመን እንደጻፈው የሚታሰብ በቻንግል ፉጃን፣ ቻይና የሚገኝ የተቀረጸ ጽሑፍ

ቻይና በብዙ ነገር ታላቅ አገር ነች። በሕዝብ ብዛት አንደኛ ስትሆን በዓለም ላይ ሰፊ የቆዳ ስፋት ካላቸው አገሮች መካከልም አንዷ ናት። ሕዝቦቿ በታሪክ ውስጥ ከታዩት ታላላቅ ግንባታዎች መካከል አንዱ የሆነውን የቻይናን ታላቅ ግንብ ሠርተዋል። የቻይና የሚንግ ሥርወ መንግሥት ነገሥታት የነበሩት ዮንግሌ እና ሽዋንዴ በርካታ ግዙፍ መርከቦችን ገንብተዋል፤ ከዚያ በኋላ ባሉት አምስት ዘመናት የዚህን ያህል ብዛት ያላቸው መርከቦችን የገነባ የለም። የመርከቦቹ አዛዥ የደቡብ ምዕራብ ቻይና ተወላጅና የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነው ዜንግ ሂ ነበር።

የበላይነት፣ ንግድና ግብር

በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ በከፊል የተጠቀሰው የተቀረጸ ጽሑፍ እንደሚገልጸው የዜንግ ሂ ተልእኮ “የመንግሥቱ ተገዥ መሆን ያለውን ጥቅም ማሳየትና ርቀው የሚገኙ ሕዝቦችን በደግነት መያዝ” ነበር። በእነዚህ ጉዞዎች ምክንያት “ከአድማስ ባሻገርና እስከ ምድር ዳር ድረስ የሚገኙ አገሮች [ለቻይና] ተገዝተዋል። . . . ባሕር ማዶ የሚኖሩ ያልሠለጠኑ ሕዝቦች . . . ቤተ መንግሥት ቀርበው እጅ በመንሳት ውድ የሆኑ ዕቃዎችንና ስጦታዎችን አቅርበዋል።”

የዜንግ ሂ መርከቦች የደረሱባቸው አንዳንድ ወደቦች

የሚንግ ሥርወ መንግሥት ነገሥታት እነዚህን ጉዞዎች ያደረጉበት ዓላማ ብዙዎችን አጨቃጭቋል። አንዳንዶች ዜንግ ሂ ኃያል ግን ሰላማዊ የሆነን አገር የሚወክል የባሕልና የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ነበር ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ተልእኮው ደካማ በሆኑ መንግሥታት ላይ የፖለቲካ የበላይነት ማግኘት እንደሆነ ያስባሉ። በእርግጥም ዜንግ ሂ እጃቸውን ዘርግተው ለተቀበሉት ገዥዎች በርካታ ስጦታዎችን ይሰጥና የፖለቲካ ድጋፍ ያደርግ ነበር፤ ለሚንግ ሥርወ መንግሥት ለመገዛትና ለመገበር እምቢተኛ የሆኑ አገሮችን ግን በቁጥጥሩ ሥር በማዋል ሰዎቹን እስረኛ አድርጎ ይወስድ ነበር። ዜንግ ሂ ባደረጋቸው ጉዞዎች ምክንያት በሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ የነበሩ በርካታ ገዥዎች የቻይናን ንጉሥ እጅ ለመንሳት አምባሳደሮቻቸውን ልከዋል።

ያም ሆነ ይህ፣ የዜንግ ሂ መርከቦች የሚንግ ሥርወ መንግሥት ሙያተኞች የሠሯቸውን ወደር የማይገኝላቸው የእንጨትና የሸክላ ጌጣ ጌጦችን እንዲሁም የሐር ምርቶችን ርቀው በሚገኙ ወደቦች ላይ ይነግዱ ነበር። ሲመለሱ ደግሞ የከበሩ ድንጋዮች፣ የዝሆን ጥርስ፣ ቅመማ ቅመም፣ የቆላ እንጨቶችንና ቻይናውያን ትልቅ ቦታ የሚሰጧቸውን የቅንጦት ዕቃዎች ይዘው ይመጡ ነበር፤ እንዲያውም አንድ ጊዜ ዜንግ ሂ ቀጭኔ በማምጣቱ ቻይናውያንን አስገርሞ እንደነበር ይነገራል። በዚህ መንገድ ቻይናውያን ሸቀጦቻቸውንና እውቀታቸውን ለሌሎች ማስተላለፋቸው የቀረው ዓለም የቻይናን የ15ኛ መቶ ዘመን አስደናቂ ሥልጣኔ በትንሹም ቢሆን ለማየት አስችሎታል።

እነዚህ አስደናቂ ጉዞዎች ለረጅም ጊዜ አልዘለቁም። ዜንግ ሂ ጉዞ ከጀመረ ከአሥር ዓመታት በኋላ ቻይና ለውጭ ንግድና ዲፕሎማሲ ጀርባዋን ሰጠች። አዲስ የተነሳው ንጉሥና የኮንፊሽየስ እምነት ተከታይ የነበሩት አማካሪዎቹ ቻይና ከድንበሯ ውጭ መመልከት እንደማያስፈልጋት ስለተሰማቸው አገሪቷን ከውጭ ተጽዕኖ ለመከላከል በሯን እንድትዘጋ አደረጉ። እንዲሁም መርከቦቹ ተረስተው እንዲቀሩ አድርገዋል፤ ምናልባትም ስለ ጉዞዎቹ የሚተርኩት መዛግብት ሌላው ቀርቶ መርከቦቹን ራሳቸውን ሳያጠፏቸው አልቀረም። በቻይና ውስጥም ሆነ ከአገሪቱ ውጭ የሚኖሩ ሰዎች የዜንግ ሂ ግዙፍ መርከቦች ስላደረጓቸው ታሪካዊ ጉዞዎች ማወቅ የቻሉት በቅርቡ ነው።

a ሊ የቻይናውያን የርቀት መለኪያ ሲሆን መጠኑ በተለያዩ ዘመናት ሲለዋወጥ ቆይቷል። በዜንግ ሂ ዘመን አንድ ሊ ግማሽ ኪሎ ሜትር ገደማ ይሆናል።

አጭር መረጃ

  • በዜንግ ሂ ይመሩ የነበሩት የሚንግ ሥርወ መንግሥት መርከቦች ከ1405 እስከ 1433 ባሉት ዓመታት ሰባት ረጃጅም ጉዞዎችን አድርገዋል።

  • የመርከቦቹ ብዛት 200 ወይም ከዚያ በላይ እንደሚሆን የሚታሰብ ሲሆን ከእነሱ መካከል የጦር መርከቦች፣ የዕቃ ማጓጓዣ መርከቦች፣ የውኃ መጫኛ እንዲሁም ፈረሶችንና ሌሎች ነገሮችን የሚጭኑ መርከቦች ይገኙበታል። መርከቦቹ ከ27,000 የሚበልጡ ባሕረኞችን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ ወታደሮችን፣ ነጋዴዎችን፣ የጥገና ሠራተኞችንና ሌሎችን ይጭኑ ነበር።

  • ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት ከዜንግ ሂ መርከቦች ጋር የሚተካከል ቁጥር የነበረው አንድም ሌላ አገር አልነበረም። የዜንግ ሂ መርከቦች በሩቅ ምሥራቅና በሕንድ ውቅያኖስ ወደሚገኙ የባሕር ወደቦች አልፎ ተርፎም እስከ ምሥራቅ አፍሪካ ድረስ ተጉዘዋል።

  • በዜንግ ሂ ሥር ሆነው የሚሠሩ ሦስት ሰዎች ዜንግ ሂ ያደረጋቸውን ጉዞዎች አስመልክቶ በዓይናቸው የተመለከቷቸውን ነገሮች የሚተርኩ ዘገባዎች በየፊናቸው አዘጋጅተዋል።

የዜንግ ሂ መርከቦች መጠንና ብዛት

ስለ ሚንግ ሥርወ መንግሥት የሚገልጹ የታሪክ መዛግብት የዜንግ ሂ መርከቦች በጣም ግዙፍ እንደነበሩ ይኸውም 136 ሜትር ርዝመትና 56 ሜትር ስፋት እንዳላቸው ይናገራሉ። ምሁራን ይህ አኃዝ ለማመን እንደሚያስቸግርና ለማረጋገጥም እንደሚከብድ ይናገራሉ፤ ምክንያቱም ከ90 ሜትር የበለጠ ርዝመት ያለው ከእንጨት የተሠራ መርከብ በአስተማማኝ ሁኔታ በውኃ ላይ ይሄዳል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው።

ስለዚህ ጉዳይ የሚናገር አንድ ጽሑፍ “የመርከቡን ግዙፍነት የሚጠቅሱት ዘገባዎች የተጋነኑ እንደሆኑ ግልጽ ነው” ብሏል። “መርከቦቹ 135 ሜትር ርዝመት እንዳላቸው ከመናገር ይልቅ ከ60-75 ሜትር ርዝመት እንዳላቸው ቢገለጽ ኖሮ ይበልጥ አሳማኝ ይሆን ነበር” ብሏል። ያም ሆነ ይህ ከ60 ሜትር የሚበልጥ ቁመት ያለው መርከብ በ15ኛው መቶ ዘመን መሠራቱ በእርግጥም አስገራሚ ነው፤ ከዜንግ ሂ መርከቦች ውስጥ 62 የሚሆኑት ደግሞ እንዲህ ያሉ ነበሩ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ