ወላጆች ለልጆቻቸው ሊያደርጓቸው የሚገቡ ነገሮች
ወላጆች ማንም ሰው ሙሉ በሙሉ ሊረዳው የማይችል አንድ ትልቅ ክስተት እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን ሚና ይጫወታሉ። እያንዳንዱ ወላጅ የአካሉን ክፋይ ያበረክታል። በዚህም የተነሳ በእናቲቱ ሰውነት ውስጥ የተሟላ አካል ያለው ሕያው ሰው ያድጋል። ከዚህ አንጻር አንድ ሕፃን ሲወለድ ሰዎች ብዙውን ጊዜ “ልጅ መውለድ ተአምር” እንደሆነ መናገራቸው ምንም አያስገርምም።
ይሁንና ልጅ መውለድ በወላጆች ላይ ብዙ ኃላፊነት ያስከትላል። መጀመሪያ ላይ ሕፃናት ሕልውናቸው ሙሉ በሙሉ የተመካው ወላጆቻቸው በሚያደርጉላቸው እንክብካቤ ላይ ነው ማለት ይቻላል፤ ይሁን እንጂ እያደጉ ሲሄዱ አካላዊ ፍላጎታቸውን ከማሟላት በተጨማሪ የሚያስፈልጋቸው ነገር አለ። በአእምሮ፣ በስሜትና በሥነ ምግባር እንዲሁም በመንፈሳዊ ማደግና መታነጽ እንዲችሉ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
በተለይ ደግሞ ልጆች ጥሩ እድገት እንዲያደርጉ የወላጆቻቸውን ፍቅር ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። ፍቅርን በአንደበት መግለጽ አስፈላጊ ቢሆንም የፍቅር መግለጫው በተግባር የተደገፈ ሊሆን ይገባል። አዎ፣ ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ አርዓያ መሆን ያስፈልጋቸዋል። ልጆች ሕይወታቸውን እንዴት መምራት እንዳለባቸው የሚያስገነዝቡ ሥነ ምግባራዊ መመሪያዎች ያስፈልጓቸዋል። እነዚህን መመሪያዎች ማግኘት ያለባቸው ደግሞ ከለጋ ዕድሜያቸው ጀምሮ ነው። ልጆች ተገቢውን እርዳታ ሳያገኙ ካደጉ እጅግ አሳዛኝ የሆነ ነገር ሊደርስባቸው ይችላል፤ ደግሞም ይደርስባቸዋል።
ከሁሉ የላቁ መመሪያዎች ሊገኙ የሚችሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ሥልጠና መስጠት ተወዳዳሪ የሌለው ጥቅም ያስገኛል። ልጆች እንዲህ ዓይነት ሥልጠና ማግኘታቸው እየተማሩት ያለው ነገር እንዲሁ አንድ ሰው የተናገረው ሳይሆን ፈጣሪያቸው የሆነው የሰማዩ አባታቸው የተናገረው እንደሆነ እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል። ይህ ደግሞ ምክሩ በልጆቹ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዲያሳድር አስተዋፅኦ ያበረክታል።
መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች፣ በልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ ትክክለኛ መመሪያዎችን ለመቅረጽ ጠንክረው እንዲሠሩ ያበረታታል። ይሁን እንጂ ልጆች እያደጉ ሲሄዱ ብዙውን ጊዜ ወላጆች በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ከልጆቻቸው ጋር መነጋገር አዳጋች ይሆንባቸዋል። ከታላቁ አስተማሪ ተማር የተሰኘው ይህ መጽሐፍ እንዲህ ያለ ችግር እንዳይፈጠር ለማድረግ እንዲረዳ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። መጽሐፉ እናንተና ልጆቻችሁ አንድ ላይ ሆናችሁ የምታነቡት መንፈሳዊ ትምህርት ይዞላችሁ ቀርቧል። ከዚህም በላይ በልጆችና አብረዋቸው ይህን መጽሐፍ በሚያነቡ ሰዎች መካከል ውይይት እንዲኖር ያደርጋል።
መጽሐፉ ልጆቹ ሐሳብ እንዲሰጡ በሚያነሳሳ መንገድ የተዘጋጀ ነው። በጽሑፉ ውስጥ አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ላይ የቀረቡ ብዙ ጥያቄዎች አሉ። እነዚህ ጥያቄዎች ላይ ስትደርሱ የሰረዝ ምልክት (—) ታያላችሁ። ይህ ምልክት የተደረገው ቆም እንድትሉና ልጁ መልስ እንዲሰጥ እንድታበረታቱት ታስቦ ነው። ልጆች በውይይት ውስጥ መሳተፍ ይወዳሉ። ይህ ካልሆነ ግን ልጁ ወዲያውኑ ሊሰለቸውና የመከታተል ፍላጎቱ ሊጠፋ ይችላል። መጽሐፉን የምታነቡት ለሴት ልጅ ከሆነ እባካችሁ ንባቡን ወደ አንስታይ ጾታ ለውጣችሁ አንብቡ። ለምሳሌ ያህል፣ ምዕራፍ አንድ ገጽ 11 ላይ የሚገኘው የመጀመሪያው አንቀጽ የመጨረሻ ዓረፍተ ነገር “አንቺም አባትሽንና እናትሽን በማዳመጥ እንደ ኢየሱስ መሆን ትችያለሽ” ተብሎ ሊነበብ ይችላል።
ከሁሉ በላይ ደግሞ ልጁ ሐሳብ እንዲሰጥ ማድረጋችሁ በልቡ ውስጥ ያለውን ነገር እንድታውቁ ይረዳችኋል። እርግጥ ነው፣ ልጁ የተሳሳቱ መልሶች ሊሰጥ ይችላል። ይሁን እንጂ ከእያንዳንዱ ጥያቄ ቀጥሎ የቀረበው ሐሳብ ልጁ ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዲያዳብር ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
በመጽሐፉ ውስጥ ያሉት ከ230 የሚበልጡ ሥዕሎች መጽሐፉን ልዩ ገጽታ አላብሰውታል። ከእነዚህ ሥዕሎች ውስጥ አብዛኞቹ ልጁ ባየውና ባነበበው ነገር ላይ ተመሥርቶ መልስ እንዲሰጥ የሚያነሳሱ ጥያቄዎች አሏቸው። ስለዚህ ሥዕሎቹንም ከልጁ ጋር አብራችሁ ተወያዩባቸው። ሥዕሎቹ ልጁ እየተሰጠው ያለውን ትምህርት የሚያስጨብጡ ጥሩ የማስተማሪያ ዘዴ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ።
ልጁ ማንበብ ሲችል መጽሐፉን ለእናንተም ሆነ ለራሱ እንዲያነብ አበረታቱት። መጽሐፉን ደጋግሞ ባነበበው መጠን በውስጡ ያለው ጥሩ ምክር በአእምሮውና በልቡ ውስጥ ይሰርጻል። ይሁንና በእናንተና በልጆቻችሁ መካከል ያለውን ፍቅርና አክብሮት ለማጠናከር ከተፈለገ መጽሐፉን አብራችሁ ማንበብ ያለባችሁ ከመሆኑም በላይ ይህን አዘውትራችሁ ማድረግ ይኖርባችኋል።
ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት ፈጽሞ ሊታሰብ በማይችል መልኩ ልጆች በአሁኑ ጊዜ ለጾታ ብልግና፣ ለመናፍስታዊ ድርጊትና ለሌሎችም ወራዳ ተግባሮች ተጋልጠዋል። ስለዚህ ልጆች ጥበቃ ማግኘት የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ይህ መጽሐፍ ልጆች ሊደረግላቸው የሚገባውን ጥበቃ ክብር ባለው ሆኖም ግልጽ በሆነ መንገድ ያቀርባል። ከሁሉ ይበልጥ ግን ልጆች የጥበብ ሁሉ ምንጭ ወደሆነው ወደ ሰማዩ አባታችን ወደ ይሖዋ አምላክ እንዲቀርቡ ማድረግ ያስፈልጋል። ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ ሁልጊዜ ያደርግ የነበረው ይህንኑ ነው። ይህ መጽሐፍ እናንተም ሆናችሁ ቤተሰባችሁ ሕይወታችሁን ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ እንድትመሩና ዘላለማዊ በረከት እንድታገኙ ይረዳችኋል ብለን ከልብ ተስፋ እናደርጋለን።