የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 27—ዳንኤል
ጸሐፊው:- ዳንኤል
የተጻፈበት ቦታ:- ባቢሎን
ተጽፎ ያለቀው:- 536 ከክ. ል. በፊት ገደማ
ታሪኩ የሚሸፍነው ጊዜ:- ከ618 እስከ 536 ከክ. ል. በፊት ገደማ
የዳንኤል መጽሐፍ፣ የምድር መንግሥታት በሙሉ በጥፋት አፋፍ ላይ በቆሙበት በዚህ ዘመን ለምንኖረው ሰዎች ከፍተኛ ቁም ነገር ያዘሉ ትንቢታዊ መልእክቶች ይዞልናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑት የሳሙኤልና የነገሥት እንዲሁም የዜና መዋዕል መጻሕፍት፣ የአምላክን አገዛዝ ይወክል ስለነበረው የዳዊት ሥርወ መንግሥት በወቅቱ የነበሩ ሰዎች በጻፉት ታሪክ ላይ የተመሠረቱ ዘገባዎች ሲሆኑ የዳንኤል መጽሐፍ ግን በዓለም መንግሥታት ላይ ያተኩራል። መጽሐፉ ከዳንኤል ዘመን አንሥቶ እስከ “ፍጻሜው ዘመን” ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በሚነሡት ታላላቅ ሥርወ መንግሥታት መካከል የሚኖረውን የሥልጣን ሽኩቻ የሚገልጽ ራእይ ይዟል። የዳንኤል መጽሐፍ ከብዙ ዘመናት አስቀድሞ የተጻፈ የዓለም ታሪክ ነው። መጽሐፉ “በኋለኛው ዘመን” ስለሚሆነው ነገር በመግለጽ ትኩረት በሚስብ መንገድ ይደመደማል። እንደ ናቡከደነፆር ሁሉ ብሔራትም፣ “ልዑሉ በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛ” እንዲሁም እነዚህን መንግሥታት “የሰውን ልጅ የሚመስል” ለተባለው መሲሕና ገዢ ማለትም ለክርስቶስ ኢየሱስ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው በግድ እንዲገነዘቡ ይደረጋሉ። (ዳን. 12:4፤ 10:14 የ1954 ትርጉም፤ 4:25፤ 7:13, 14፤ 9:25፤ ዮሐ. 3:13-16) በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው የዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ትንቢቶች ፍጻሜ በትኩረት መከታተላችን፣ የይሖዋን ትንቢት የመናገር ችሎታ እንዲሁም ሕዝቦቹን ለመጠበቅና ለመባረክ የሰጠውን ማረጋገጫ ይበልጥ እንድንገነዘብ ያደርገናል።—2 ጴጥ. 1:19
2 መጽሐፉ የተሰየመው በጸሐፊው ስም ነው። “ዳንኤል” (በዕብራይስጥ ዳኒየል) የሚለው ስም “ፈራጄ አምላክ ነው” የሚል ትርጉም አለው። በዳንኤል ዘመን ይኖር የነበረው ሕዝቅኤል፣ ከኖኅና ከኢዮብ ጋር ዳንኤልን አብሮ መጥቀሱ ዳንኤል በእርግጥም በሕይወት የነበረ ሰው መሆኑን ያረጋግጥልናል። (ሕዝ. 14:14, 20፤ 28:3) ዳንኤል መጽሐፉን የጀመረው “የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በነገሠ በሦስተኛው ዓመት” መሆኑን ገልጿል። ኢዮአቄም፣ የናቡከደነፆር ገባር ንጉሥ ሆኖ መግዛት የጀመረበት ሦስተኛ ዓመት 618 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው።a ዳንኤል፣ እስከ ቂሮስ ሦስተኛ የግዛት ዓመት ማለትም እስከ 536 ከክርስቶስ ልደት በፊት ድረስ ትንቢታዊ ራእዮችን መመልከቱን ቀጥሎ ነበር። (ዳን. 1:1፤ 2:1፤ 10:1, 4) በዳንኤል የሕይወት ዘመን፣ ትኩረት የሚስቡ ብዙ ታላላቅ ድርጊቶች ተፈጽመዋል! ይህ ነቢይ የልጅነት ሕይወቱን ያሳለፈው በይሁዳ በሚገዛው የአምላክ መንግሥት ሥር ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ፣ እንደ እርሱው መሳፍንት ከሆኑ አይሁዳዊ ጓደኞቹ ጋር ወደ ባቢሎን ተወሰደ። ባቢሎን በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የተጠቀሰው ሦስተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት ሲሆን ይህ መንግሥት ከተነሣበት ጀምሮ እስከ ወደቀበት ጊዜ ድረስ ዳንኤል በዚህ አገር ኖሯል። ነቢዩ በአራተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት ማለትም በሜዶ ፋርስ ግዛት ሥርም የመንግሥት ባለ ሥልጣን ሆኖ አገልግሏል። ዳንኤል መቶ ዓመት ገደማ ሳይኖር አይቀርም።
3 የዳንኤል መጽሐፍ አይሁዳውያን ከነበሯቸው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ መጻሕፍት ዝርዝር መካከል ጠፍቶ አያውቅም። የዳንኤል መጽሐፍ ቁርጥራጮች በሙት ባሕር አካባቢ ከተገኙት ተቀባይነት ያላቸው ሌሎች መጻሕፍት መካከል የተገኙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የተጻፉ ናቸው። የመጽሐፉን እውነተኝነት የሚያረጋግጠው ከዚህ የበለጠው ማስረጃ ግን ዳንኤል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ መጠቀሱ ነው። ኢየሱስ ‘የዓለምን መጨረሻ’ በተመለከተ በተናገረው ትንቢት ውስጥ ዳንኤልን በስሙ የጠቀሰው ከመሆኑም በላይ ከዳንኤል መጽሐፍ በተደጋጋሚ ጊዜ ጠቅሷል።—ማቴ. 24:3፤ በተጨማሪም ዳን. 9:27፤ 11:31 እንዲሁም 12:11—ማቴ. 24:15 እና ማር. 13:14፤ ዳን. 12:1—ማቴ. 24:21፤ ዳን. 7:13, 14—ማቴ. 24:30 ተመልከት።
4 የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች፣ የዳንኤል መጽሐፍ ከታሪክ አንጻር ትክክል ስለመሆኑ ጥያቄ ቢያነሡም ለበርካታ ዓመታት የተሰበሰቡት አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች የተሠነዘሩትን ሐሳቦች ሁሉ ውድቅ አድርገዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ናቦኒደስ ገዢ እንደነበረ በሚታመንባቸው ዓመታት ውስጥ የባቢሎን ንጉሥ ቤልሻዛር እንደነበረ በመጻፉ በዳንኤል ላይ ትችት ተሰንዝሮ ነበር። (ዳን. 5:1) ሆኖም ቤልሻዛር በእርግጥ በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑንና በባቢሎናውያን ግዛት የመጨረሻ ዓመታት ላይ ከናቦኒደስ ጋር ይገዛ እንደነበር አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃዎች በማያሻማ መንገድ አረጋግጠዋል። ለአብነት ያህል፣ “የናቦኒደስ ዝርዝር ታሪክ” ተብሎ የተጠራው የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፈ ጥንታዊ ጽሑፍ፣ ቤልሻዛር በባቢሎን ንጉሣዊ ሥልጣን እንደነበረው በግልጽ ከማስቀመጡም በላይ ከናቦኒደስ ጋር ተባባሪ ገዥ የነበረው በምን መንገድ እንደሆነ ያብራራል።b የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፈ ሌላ ማስረጃም ቤልሻዛር ንጉሣዊ ሥራ ያከናውን እንደነበር ይገልጻል። በናቦኒደስ 12ኛ የግዛት ዓመት የተጻፈ አንድ የድንጋይ ጽላት፣ በንጉሡ በናቦኒደስና በንጉሡ ልጅ በቤልሻዛር ስም ስለተፈጸመ መሐላ ይገልጻል፤ ይህም ቤልሻዛር ከአባቱ ጋር ሥልጣን እንደተጋራ ያሳያል።c ከዚህም በላይ፣ በግድግዳው ላይ የተጻፈውን ጽሑፍ ትርጉም ከገለጸለት “የመንግሥት ሦስተኛ ገዥ” እንደሚያደርገው ቤልሻዛር ለዳንኤል ቃል የገባለት ለምን እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል። ናቦኒደስ የመጀመሪያውን ቦታ ይይዛል፣ ከዚያ ቀጥሎ ያለው ቦታ የቤልሻዛር ሲሆን ሦስተኛውን ቦታ ደግሞ ዳንኤል እንደያዘ በአዋጅ ይነገርለታል። (5:16, 29) አንድ ተመራማሪ እንዲህ ብለዋል:- “የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተጻፉ ጽሑፎች ቤልሻዛርን በተዘዋዋሪ መንገድ መጥቀሳቸው እርሱ የተጫወተው ሚና ይበልጥ ግልጽ እንዲሆን በማድረጉ፣ ይህ ግለሰብ በታሪክ ውስጥ ያለው ቦታ በደንብ ሊታወቅ ችሏል። ቤልሻዛር ከናቦኒደስ የማይተናነስ ሥልጣንና ክብር እንደነበረው የሚጠቁሙ ብዙ ጽሑፎች አሉ። ወደ መጨረሻ ገደማ በነበሩት በአብዛኞቹ የባቢሎን ግዛቶች ውስጥ ጥምር አስተዳደር እንደነበረ ተረጋግጧል። ናቦኒደስ፣ በአረቢያ ቴማ በሚገኘው ቤተ መንግሥቱ ሆኖ በበላይነት ያስተዳድር የነበረ ሲሆን ቤልሻዛር ደግሞ ባቢሎንን ማዕከል አድርጎ በትውልድ አገሩ ይገዛ ነበር። ቤልሻዛር የአንድ ግዛት ተራ ሹም እንዳልነበረ ግልጽ ነው፤ ‘የንግሥና’ ሥልጣን የተሰጠው ሰው ነበር።”d
5 አንዳንዶች ስለ እቶን እሳት (ምዕ. 3) የሚገልጸው የዳንኤል ዘገባ የፈጠራ ታሪክ እንደሆነ በመግለጽ ሊያጣጥሉት ሞክረዋል። አንድ የቆየ የባቢሎናውያን ደብዳቤ በከፊል እንዲህ ይነበባል:- “ጌታህ ሪም ሲን እንዲህ ይላል:- እርሱ ብላቴናውን ባሪያ እሳት ውስጥ ስለጣለ አንተም ባሪያውን እቶን ውስጥ ትጨምረዋለህ።” ጂ. አር. ድራይቨር ይህ ቅጣት “በሦስቱ ቅዱሳን ሰዎች ታሪክ ውስጥ ይገኛል (ዳን. III 6, 15, 19-27)” ብለው መናገራቸው ትኩረት የሚስብ ነው።e
6 አይሁዳውያን፣ የዳንኤልን መጽሐፍ የፈረጁት ከትንቢቶች ጋር ሳይሆን ከሌሎች መጻሕፍት ጋር ነበር። በሌላ በኩል ግን የእንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ፣ የግሪክኛውን ሰብዓ ሊቃናት እና የላቲኑን ቩልጌት ቅደም ተከተል በመጠቀም የዳንኤልን መጽሐፍ ከትላልቆቹና ትናንሾቹ የትንቢት መጻሕፍት መካከል አስገብቶታል። መጽሐፉ ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን ከምዕራፍ 1-6 ያለው የመጀመሪያው ክፍል፣ ዳንኤልና ጓደኞቹ በአስተዳደር ሥራ ባገለገሉባቸው ከ617 እስከ 538 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባሉት ዓመታት ውስጥ ያጋጠሟቸውን ነገሮች በቅደም ተከተል ይዘግባል። (ዳን. 1:1, 21) ከ7-12 ያሉትን ምዕራፎች የያዘው ሁለተኛው ክፍል ደግሞ፣ ዳንኤል ከ553 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማf እስከ 536 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ ባለው ጊዜ ውስጥ በግሉ ስለተመለከታቸው ራእዮችና ከመላእክት ጋር ስላደረጋቸው ውይይቶች በመግለጽ በስሙ ያሰፈረው ዘገባ ነው። (7:2, 28፤ 8:2፤ 9:2፤ 12:5, 7, 8) እርስ በርሱ ስምም የሆነው የዳንኤል መጽሐፍ የእነዚህ ሁለት ክፍሎች ጥምረት ነው።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
19 ባዕድ በሆነው ዓለም ውስጥ ፍጹም አቋማቸውን ጠብቀው ለመኖር የቆረጡ ሁሉ ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ የተዉትን መልካም ምሳሌ መመርመራቸው ጠቃሚ ነው። እነዚህ ወጣቶች ጭካኔ የተሞላበት ማስፈራሪያ ቢደርስባቸውም አምላክ ላወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ከመገዛት ወደ ኋላ አላሉም። ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቆ በነበረበት ጊዜም እንኳ ዳንኤል እርምጃ የወሰደው “በጥበብና በዘዴ” ሲሆን ንጉሡ ለነበረው ከፍተኛ ሥልጣን አክብሮት እንዳለው አሳይቷል። (2:14-16 ) አከራካሪ ጉዳይ በተነሣ ጊዜ ሦስቱ ዕብራውያን ጣዖት ከማምለክ በእቶን እሳት ውስጥ መቃጠልን የመረጡ ሲሆን ዳንኤልም ወደ ይሖዋ የመጸለይ መብቱን ከማጣት በአንበሳ ጉድጓድ መጣልን መርጧል። በሁለቱም አጋጣሚዎች ይሖዋ አገልጋዮቹን ጠብቋቸዋል። (3:4-6, 16-18, 27፤ 6:10, 11, 23) ዳንኤል ራሱ በጸሎት ወደ ይሖዋ አምላክ በመቅረብና በእሱ በመታመን ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል።—2:19-23፤ 9:3-23፤ 10:12
20 ዳንኤል የተመለከታቸውን ራእዮች መከለሳችን የሚያስደስትና እምነት የሚያጠነክር ነው። እስቲ በመጀመሪያ የዓለም ኃያል መንግሥታትን በተመለከተ ያያቸውን አራት ራእዮች እንመልከት:- (1) የመጀመሪያው ስለ አንድ አስፈሪ ምስል የሚገልጸው ራእይ ነበር፤ ከወርቅ የተሠራው የዚህ ምስል ራስ ከናቡከደናፆር ጀምሮ ያሉትን የባቢሎን ነገሥታት ሥርወ መንግሥት የሚያመለክት ሲሆን ቀሪዎቹ የምስሉ አካሎች ደግሞ ከእነዚህ ነገሥታት በኋላ የሚነሱ ሌሎች ሦስት መንግሥታትን ያመለክታሉ። አንድ “ድንጋይ” እነዚህን መንግሥታት ካደቀቃቸው በኋላ “ፈጽሞ የማይፈርስ . . . መንግሥት” ሆነ፤ ይህም የአምላክ መንግሥት ነው። (2:31-45) (2) ከዚያ በኋላ ዳንኤል ራሱ የተመለከታቸው ራእዮች ተገልጸዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው፣ አራት ‘መንግሥታትን’ ስለሚወክሉት አራት አራዊት የሚናገረው ራእይ ነው። አራዊቱ አንበሳ፣ ድብና አራት ራስ ያለው ነብር የሚመስሉ እንዲሁም ትላልቅ የብረት ጥርስና አሥር ቀንድ ያለው በኋላም አንድ ትንሽ ቀንድ ያበቀለ አውሬ ናቸው። (7:1-8, 17-28) (3) ቀጥሎ ደግሞ የአውራው በግ (ሜዶ ፋርስ)፣ የአውራው ፍየል (ግሪክ) እና የአንድ ትንሽ ቀንድ ራእይ ተገልጿል። (8:1-27) (4) በመጨረሻም የደቡቡን ንጉሥና የሰሜኑን ንጉሥ ራእይ እናገኛለን። ዳንኤል 11:5-19 እስክንድር በ323 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሞት በግሪክ ግዛት ውስጥ በተነሡት የግብፅና የሴሉሲድ ነገሥታት መካከል የነበረውን ግጭት በትክክል ይገልጻል። ትንቢቱ ከቁጥር 20 አንሥቶ በደቡቡ ንጉሥና በሰሜኑ ንጉሥ ቦታ ስለሚነሱት ብሔራት መዘርዘሩን ይቀጥላል። ኢየሱስ የእርሱን መገኘት ስለሚጠቁሙት ምልክቶች በተናገረው ትንቢት ውስጥ ‘ጥፋትን ስለሚያመጣው የጥፋት ርኩሰት’ (11:31) መግለጹ በእነዚህ ሁለት ነገሥታት መካከል የሚደረገው የሥልጣን ሽኩቻ እስከ ‘ዓለም መጨረሻ’ ድረስ እንደሚዘልቅ ያሳያል። (ማቴ. 24:3) “መንግሥታት ከተመሠረቱበት ጊዜ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ የመከራ ጊዜ” በሚሆንበት በዚያ ወቅት ለአምላክ አክብሮት የሌላቸውን ብሔራት ለማጥፋትና ታዛዥ ለሆኑት የሰው ልጆች ሰላምን ለማምጣት ሚካኤል ራሱ እንደሚነሣ ይህ ትንቢት የሚሰጠው ማረጋገጫ እንዴት የሚያጽናና ነው!—ዳን. 11:20 እስከ 12:1
21 ዳንኤል ስለ ‘ሰባ ሱባዔ’ የተናገረው ትንቢትም አለ። በትንቢቱ መሠረት ከ69 ሱባዔ ወይም ሳምንታት በኋላ “ገዥው መሲሕ” ይገለጣል። ኢየሩሳሌምን ለመጠገን “ዐዋጁ ከወጣ” ከ483 ዓመታት (69 ሲባዛ 7 ዓመታት) በኋላ የናዝሬቱ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ተጠምቆ በመንፈስ ቅዱስ በመቀባት ክርስቶስ ወይም መሲሕ (የተቀባ ማለት ነው) ሆነ። ንጉሥ አርጤክስስ ኢየሩሳሌም እንድትጠገን አዋጅ ያስነገረው በ20ኛው የግዛት ዘመኑ ሲሆን ነህምያም አዋጁን ተግባራዊ አድርጎታል።g ኢየሱስ መሲሕ ሆኖ የተገለጠው በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነበር። ከዚያ በኋላ ዳንኤል አስቀድሞ በትንቢት እንደተናገረው ኢየሩሳሌም በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ስትደመሰስ “ፍጻሜ” (የ1954 ትርጉም) ሆኗል።—ዳን. 9:24-27፤ ሉቃስ 3:21-23፤ 21:20
22 በዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው ናቡከደነፆር ስለተቆረጠው ዛፍ ባየው ሕልም ላይ እንደተገለጸው፣ ይሖዋ አምላክ፣ ባከናወናቸው ነገሮች የተኩራራውንና በኃይሉ የተመካውን ንጉሥ አዋርዶታል። ይህ ንጉሥ “ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ሁሉ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለውና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ” እስኪያውቅ ድረስ እንደ ዱር አራዊት እንዲኖር ተደርጓል። (ዳን. 4:32) እኛስ እንደ ናቡከደነፆር ባገኘናቸው ስኬቶች በመኩራራትና በሰዎች ኃይል በመመካት የአምላክ ቅጣት የሚገባን ሰዎች እንሆናለን? ወይስ አምላክ በሰው ልጆች መንግሥት ላይ ሥልጣን እንዳለው በመገንዘብ በእርሱ መንግሥት እንተማመናለን?
23 የአምላክ መንግሥት ተስፋ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ እምነትን በሚያጎለብት መንገድ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል! ይሖዋ አምላክ፣ ፈጽሞ የማይፈርስና ሌሎች መንግሥታትን ሁሉ የሚያደቅቅ መንግሥት የሚያቋቁም ሉዓላዊ ገዥ መሆኑ ተገልጿል። (2:19-23, 44፤ 4:25) አረማዊ የነበሩት ንጉሥ ናቡከደነፆርና ንጉሥ ዳርዮስ እንኳ የይሖዋን የበላይነት አምነው ለመቀበል ተገደዋል። (3:28, 29፤ 4:2, 3, 37፤ 6:25-27) ይሖዋ በመንግሥቱ ላይ ለተነሣው አከራካሪ ጉዳይ እልባት በማበጀት ‘የሰውን ልጅ ለሚመስለው’ የዘላለም ‘ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል እንደሚሰጠውና በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች እንዲሰግዱለት’ እንደሚያደርግ በዘመናት የሸመገለ ንጉሥ ተደርጎ ተወድሷል እንዲሁም ክብር ተሰጥቶታል። “የሰው ልጅ” ተብሎ ከተገለጸው ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በመንግሥቱ የሚካፈሉት “የልዑሉ ቅዱሳን” ናቸው። (ዳን. 7:13, 14, 18, 22፤ ማቴ. 24:30፤ ራእይ 14:14) በመንግሥት ሥልጣኑ ተጠቅሞ የዚህን አሮጌ ዓለም መንግሥታት ሁሉ የሚያደቅቀውና የሚያጠፋው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ነው። (ዳን. 12:1፤ 2:44፤ ማቴ. 24:3, 21፤ ራእይ 12:7-10) ጽድቅ ወዳድ የሆኑ ሰዎች እነዚህን ትንቢቶችና ራእዮች መረዳታቸው፣ ንቁ እንዲሆኑ እንዲሁም በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈውና ጠቃሚ በሆነው የዳንኤል መጽሐፍ አማካኝነት የተገለጡልንን ስለ አምላክ መንግሥት ዓላማዎች የሚገልጹትን እውነተኛዎቹን “አስደናቂ ነገሮች” ለማወቅ የአምላክን ቃል እንዲመረምሩ ሊያነሳሳቸው ይገባል።—ዳን. 12:2, 3, 6
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 1269
b ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1፣ ገጽ 283
c አርኪኦሎጂ ኤንድ ዘ ባይብል 1949፣ ጆርጅ ባርተን ገጽ 483
d ዘ ያል ኦሪየንታል ሲሪስ ሪሰርችስ፣ ጥራዝ XV, 1929
e አርኪቭ ፈር ኦሪየንትፎርሹንግ፣ ጥራዝ 18, 1957-1958 ገጽ 129
f ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ቤልሻዛር ከአባቱ ጋር ሆኖ መግዛት የጀመረው ከናቦኒደስ ሦስተኛ ዓመት አንሥቶ ነው። ናቦኒደስ ደግሞ ግዛቱን የጀመረው በ556 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደሆነ ስለሚታመን የግዛቱ ሦስተኛ ዓመት እና ‘የቤልሻዛር የመጀመሪያ ዓመት’ 553 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደሚሆን ግልጽ ነው።—ዳንኤል 7:1፤ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 283፤ ጥራዝ 2 ገጽ 457 ተመልከት።
g ነህምያ 2:1-8፤ በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2፣ ገጽ 899-901 ተመልከት።