የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 33—ሚክያስ
ጸሐፊው:- ሚክያስ
የተጻፈበት ቦታ:- ይሁዳ
ተጽፎ ያለቀው:- ከክ. ል. በፊት ከ717 ቀደም ብሎ
ታሪኩ የሚሸፍነው ጊዜ:- ከክ. ል. በፊት ከ777 ገደማ እስከ 717
ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ያገለገለ በሳል ሰው ነው። ለአገሩ መሪዎች “መልካሙን ጠላችሁ፤ ክፉውንም ወደዳችሁ፤ . . . የሕዝቤን ሥጋ በላችሁ፤ ቈዳቸውን ገፈፋችሁ” ብሎ በድፍረት ሊናገር የቻለ ሰው ነው። የተናገራቸው ኃይለኛ ቃላት በሙሉ ከይሖዋ የመጡና በይሖዋ መንፈስ የተነገሩ መሆናቸውን ያሳወቀ ትሑት ሰው ነው። እንዲህ ካለው ሰው ጋር ብትተዋወቅ ደስ አይልህም? እንዲህ ካለው ሰው በጣም ብዙ እውቀትና ጠቃሚ ምክር ሊገኝ ይችላል! ነቢዩ ሚክያስ እንዲህ ያለ ሰው ነበር። ዛሬም ቢሆን በስሙ ከሚጠራው መጽሐፍ ምርጥ የሆኑ ምክሮች ማግኘት እንችላለን።—ሚክ. 3:2, 3, 8
2 እንደ ሌሎቹ በርካታ ነቢያት ሁሉ በመጽሐፉ ውስጥ ስለ ሚክያስ የተገለጸልን ነገር በጣም አነስተኛ ነው። ትኩረት የተሰጠው ለመልእክቱ እንጂ ለነቢዩ አይደለም። ሚክያስ የሚለው መጠሪያ ሚካኤል ወይም ሚካያህ የሚሉት ስሞች አጭር አጠራር ነው። ሚካኤል “እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” የሚል ትርጉም ሲኖረው ሚካያህ ደግሞ “እንደ ይሖዋ ያለ ማን ነው?” ማለት ነው። ሚክያስ በነቢይነት ያገለገለው በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት (ከ777 እስከ 717 ከክርስቶስ ልደት በፊት) ስለሆነ ኢሳይያስና ሆሴዕ ከተባሉት ነቢያት ጋር በአንድ ዘመን ኖሯል። (ኢሳ. 1:1፤ ሆሴዕ 1:1) ትንቢት የተናገረባቸውን ዓመታት በእርግጠኝነት ማወቅ ባይቻልም ከ60 ዓመት እንደማያልፍ የተረጋገጠ ነው። ስለ ሰማርያ መፍረስ የሚገልጸው ትንቢት ከተማይቱ በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከመፍረሷ በፊት የተነገረ መሆን ይኖርበታል፤ በተጨማሪም መጽሐፉ የሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ካበቃበት ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ717 ቀደም ብሎ ተጽፎ ሳይጠናቀቅ አልቀረም። (ሚክ. 1:1) ሚክያስ ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ ምዕራብ በሚገኘው ሸፊላ የተባለ ለም አካባቢ፣ ሞሬት በተባለ መንደር ውስጥ የሚኖር የገጠር ነቢይ ነበር። ሰዎች መልእክቱን ልብ እንዲሉ የተጠቀመባቸው ምሳሌዎች የገጠሩን ኑሮ በደንብ የሚያውቅ ሰው እንደነበረ ያመለክታሉ።—2:12፤ 4:12, 13፤ 6:15፤ 7:1, 4, 14
3 ሚክያስ ይኖር የነበረው በጣም አደገኛና ወሳኝ በሆነ ዘመን ነበር። የእስራኤልና የይሁዳ መንግሥታት ጥፋት በጣም የቀረበ መሆኑን የሚያመለክቱ በርካታ ክንውኖች የተፈጸሙበት ዘመን ነበር። በእስራኤል ምድር ምግባረ ብልሹነትና የጣዖት አምልኮ ሥር ሰድዶ ስለነበር ይህች ብሔር በአሦራውያን ልትጠፋ ችላለች። ይህ ጥፋት የደረሰው ሚክያስ በሕይወት እያለ ነበር። ይሁዳ በንጉሥ ኢዮአታም ዘመን ትክክለኛውን ጎዳና ብትከተልም በዓመጽ በተሞላው የአካዝ የንግሥና ዘመን ልክ እንደ እስራኤል ወደ ክፋት አምርታለች፤ በሕዝቅያስ ዘመን ደግሞ እንደገና ወደ መልካም ምግባር ተመልሳለች። ይሖዋ በሕዝቡ ላይ ስለሚያመጣው ጥፋት እንዲያስጠነቅቅ ሚክያስን አስነሳው። የሚክያስ ትንቢቶች የኢሳይያስንና የሆሴዕን ትንቢቶች አጠናክረዋል።—2 ነገ. 15:32 እስከ 20:21፤ 2 ዜና ምዕ. 27 እስከ 32፤ ኢሳ. 7:17፤ ሆሴዕ 8:8፤ 2 ቆሮ. 13:1
4 የሚክያስ መጽሐፍ ትክክለኛ መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች አሉ። አይሁዳውያን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል መሆኑን ተጠራጥረው አያውቁም። ኤርምያስ 26:18, 19 የሚክያስን ቃላት በቀጥታ በመጥቀስ “ጽዮን እንደ ዕርሻ ትታረሳለች፤ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች” ይላል። (ሚክ. 3:12) በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት የባቢሎን ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር ድምጥማጧን ‘ባጠፋት’ ጊዜ ይህ ትንቢት በትክክል ተፈጽሟል። (2 ዜና 36:19) በተመሳሳይም ሰማርያ “የፍርስራሽ ክምር” እንደምትሆን የተነገረው ትንቢት ተፈጽሟል። (ሚክ. 1:6, 7) አሦራውያን በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሰማርያን አጥፍተው የሰሜኑን የእስራኤል መንግሥት በግዞት ወስደዋል። (2 ነገ. 17:5, 6) ቆየት ብሎም በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ሰማርያ በታላቁ እስክንድር የተወረረች ሲሆን በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በቀዳማዊ ጆን ሂርካነስ መሪነት አይሁዳውያን ወርረው አውድመዋታል። ዘ ኒው ዌስትሚኒስተር ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል፣ 1970 በገጽ 822 ላይ ሰማርያ ለመጨረሻ ጊዜ ስለጠፋችበት ሁኔታ ሲናገር “ድል አድራጊዎቹ በዚያ ኮረብታ ላይ የተመሸገ ከተማ እንደነበረ የሚያሳይ አንዳች ማስረጃ እንዳይቀር በማሰብ አውድመዋታል” ይላል።
5 በአርኪኦሎጂ የተገኘ ማስረጃ የሚክያስ ትንቢት በትክክል የተፈጸመ ስለመሆኑ ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሰጣል። ሰማርያ በአሦራውያን መጥፋትዋ በአሦራውያን ዜና ታሪክ ውስጥ ተመዝግቧል። ለምሳሌ ያህል፣ የአሦራውያን ንጉሥ የነበረው ሳርጎን “ሰማርያን (ሳሚሪና) ከከበብኩ በኋላ ድል አድርጌያታለሁ” በማለት በጉራ ተናግሯል።a ይሁን እንጂ ከከበባው በኋላ የመጨረሻውን ድል የተቀዳጀው ከሳርጎን በፊት የነበረው ንጉሥ ስልምናሶር አምስተኛ ሳይሆን አይቀርም። አንድ የባቢሎናውያን ዜና መዋዕል ስለ ስልምናሶር ሲናገር “ሰማርያን አወደማት” ይላል።b ይሁዳ በሚክያስ ትንቢት መሠረት በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት መወረሯን ሰናክሬብ በሚገባ አስመዝግቦታል። (ሚክ. 1:6, 9፤ 2 ነገ. 18:13) በነነዌ በነበረው ቤተ መንግሥቱ ግድግዳ ላይ ባሠራው ባለ አራት ማዕዘን ትልቅ ቅርጽ ላይ ለኪሶ ስትወረር የሚያሳይ ሥዕላዊ መግለጫ ይገኛል። በተጨማሪም እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “ከጠንካራ ከተሞቹ መካከል 46ቱን ከበብኩ። . . . ከከተሞቹ ውስጥ 200,150 የሚያክሉ ሰዎችን አስወጣሁ። . . . እርሱንም ንጉሣዊ መኖሪያው በነበረችው በኢየሩሳሌም ውስጥ በጎጆዋ እንዳለች ወፍ እስረኛ ሆኖ እንዲኖር አደረግኩ።” በተጨማሪም ምንም እንኳ መጠኑን አጋንኖ ቢያቀርብም ሕዝቅያስ የሰጠውን ግብር ዘርዝሯል። በራሱ ሠራዊት ላይ የደረሰውን መቅሰፍት ግን አልጠቀሰም።c—2 ነገ. 18:14-16፤ 19:35
6 በሚክያስ 5:2 ላይ መሲሑ ስለሚወለድበት ቦታ የሚናገረው ጎላ ብሎ የሚታይ ትንቢት የሚክያስ መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ስለመሆኑ የሚነሳውን ጥርጥር ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል። (ማቴ. 2:4-6) በተጨማሪም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚክያስ መጽሐፍ ጋር የሚመሳሰሉ ሐሳቦች አሉ።—ሚክ. 7:6, 20፤ ማቴ. 10:35, 36፤ ሉቃስ 1:72, 73
7 ሚክያስ ከይሁዳ ገጠራማ አካባቢ የመጣ ሰው ቢሆንም ሐሳቡን የመግለጽ ችግር አልነበረበትም። በአምላክ ቃል ውስጥ ከሠፈሩት ግሩም አነጋገሮች መካከል አንዳንዶቹ የሚገኙት በሚክያስ መጽሐፍ ውስጥ ነው። ምዕራፍ 6 የተጻፈው በውይይት መልክ ነው። ሚክያስ ከአንዱ ነጥብ ወደ ሌላው ነጥብ፣ ከበረከት ወደ መርገም እንዲሁም ከመርገም ወደ በረከት በፍጥነት ሲሸጋገር የአንባቢውን ስሜት ይመስጣል። (ሚክ. 2:10, 12፤ 3:1, 12፤ 4:1) ሥዕላዊ የሆኑ መግለጫዎች በብዛት ይገኛሉ:- ይሖዋ ሲመጣ “ተራሮች ከሥሩ ይቀልጣሉ፤ ሸለቆዎችም ይሰነጠቃሉ፤ በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፣ በገደል ላይ እንደሚወርድ ፈሳሽ ይሆናሉ።”—1:4፤ በተጨማሪም 7:17ን ተመልከት።
8 መጽሐፉ በሦስት ሊከፈል የሚችል ሲሆን በእያንዳንዱ ክፍል የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር ላይ ሕዝቡ “ስሙ” ተብለዋል። በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ ተግሣጽ የተሰጠባቸው፣ ጥፋት እንደሚመጣ ማስጠንቀቂያ የተነገረባቸውና በረከት እንደሚያገኙ ተስፋ የተሰጠባቸው ሐሳቦች ይገኛሉ።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
16 ከዛሬ 2,700 ዓመታት ገደማ በፊት የሚክያስ ትንቢት ‘ለመገሠጽ የሚጠቅም’ መጽሐፍ መሆኑ ተረጋግጧል፤ የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ሕዝቅያስ የሚክያስን መልእክት ሰምቶ መላው ብሔር ንስሐ እንዲገባና ሃይማኖታዊ ተሐድሶ እንዲያደርግ ማነሳሳት ችሏል። (ሚክ. 3:9-12፤ ኤር. 26:18, 19፤ ከ2 ነገሥት 18:1-4 ጋር አወዳድር።) ዛሬም ቢሆን ይህ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ትንቢት የበለጠ ጠቀሜታ አለው። አምላክን እናመልካለን የሚሉ ሁሉ ሚክያስ ስለ ሐሰት ሃይማኖት፣ ስለ ጣዖት አምልኮ፣ ስለ መዋሸትና ስለ ዓመጽ የሰጠውን ግልጽ ማስጠንቀቂያ መስማት ይኖርባቸዋል! (ሚክ. 1:2፤ 3:1፤ 6:1) ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 6:9-11 ላይ እውነተኛ ክርስቲያኖች ታጥበው የነጹ በመሆናቸው እንዲህ ያሉትን ድርጊቶች የሚፈጽም ማንኛውም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት እንደማይገባ በመግለጽ የሚክያስን ማስጠንቀቂያ ትክክለኛነት አረጋግጧል። ሚክያስ 6:8 ግልጽና ቀላል በሆነ አነጋገር፣ ይሖዋ ከሰው የሚፈልገው ፍትሕንና ምሕረትን እንዲያደርግ እንዲሁም በትሕትና እንዲመላለስ መሆኑን ይናገራል።
17 ሚክያስ መልእክቱን ይናገር የነበረው ሕዝቡ በጣም ከመከፋፈሉ የተነሳ “የሰው ጠላቶች የገዛ ቤተ ሰዎቹ” በሆኑበት ማኅበረሰብ ውስጥ ነበር። እውነተኛ ክርስቲያኖችም ብዙውን ጊዜ የሚሰብኩት ከዚህ ጋር በሚመሳሰሉ ሁኔታዎች ውስጥ ነው፤ እንዲያውም አንዳንዶች የገዛ ቤተሰቦቻቸው ይክዷቸዋል እንዲሁም ኃይለኛ ስደት ያደርሱባቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ምንጊዜም ‘አዳኛቸው የሆነውን አምላክ’ በትዕግሥት መጠበቅ ይኖርባቸዋል። (ሚክ. 7:6, 7፤ ማቴ. 10:21, 35-39) በድፍረት በይሖዋ የሚታመኑ ሰዎች ስደት ሲገጥማቸው ወይም አስቸጋሪ የሆነ ኃላፊነት ሲሰጣቸው እንደ ሚክያስ ‘በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይልን ተሞልተው’ መልእክቱን ይናገራሉ። ሚክያስ በተለይ ‘የያዕቆብ ትሩፍ’ ይህን የመሰለ ድፍረት እንደሚኖረው ተንብዮአል። እነዚህም “በብዙ አሕዛብ መካከል . . . እንዳለ አንበሳ” እንዲሁም ከይሖዋ ዘንድ እንደሚወርድ ካፊያ ይሆናሉ። በእርግጥም እነዚህ ባሕርያት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ አባላት በሆኑት ‘የእስራኤል (የያዕቆብ) ቅሬታዎች’ ላይ በግልጽ ታይተዋል።—ሚክ. 3:8፤ 5:7, 8፤ ሮሜ 9:27፤ 11:5, 26
18 በሚክያስ ትንቢት መሠረት ኢየሱስ በቤተ ልሔም መወለዱ መጽሐፉ በአምላክ መንፈስ የተጻፈ መሆኑን ከማረጋገጡ በተጨማሪ በዚህ ቁጥር ዙሪያ የተገለጹት ሐሳቦች በክርስቶስ ኢየሱስ በሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት ግዛት ሥር የሚኖረውን ሁኔታ የሚተነብዩ መሆናቸውን ያመለክታል። ከቤተ ልሔም (የዳቦ ቤት ማለት ነው) የሚወጣውና በመሥዋዕቱ ለሚያምኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኘው ኢየሱስ ነው። “በእግዚአብሔር ኀይል . . . መንጋውንም ይጠብቃል” የተባለለትና ዳግመኛ በሚቋቋመውና አንድ በሚሆነው የአምላክ መንጋ መካከል እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ታላቅ በመሆን ሰላም እንዲመሠረት የሚያደርገው እርሱ ነው።—ሚክ. 5:2, 4፤ 2:12፤ ዮሐ. 6:33-40
19 ሚክያስ “ብዙ አሕዛብ” የይሖዋን መመሪያ ስለሚፈልጉበት ‘የመጨረሻ ዘመን’ የተናገረው ትንቢት በጣም የሚያጽናና ነው። “ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጉታል። አንዱ መንግሥት በሌላው መንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ከእንግዲህም የጦርነት ትምህርት አይማሩም። እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም፤ የእግዚአብሔር ጸባኦት አፍ ተናግሮአልና።” ከማንኛውም የሐሰት አምልኮ ወጥተው ከሚክያስ ጋር በመተባበር “እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም እንሄዳለን” ይላሉ። በእርግጥም የሚክያስ ትንቢት እነዚህ ታላላቅ ክንውኖች የሚፈጸሙበትን ሁኔታ በመተንበዩ እምነት ያጠነክራል። በተጨማሪም ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ ዘላለማዊ ገዥና ንጉሥ መሆኑን ስለሚገልጽ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መጽሐፍ ነው። “ከዚያች ቀን አንሥቶ እስከ ዘላለም፣ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ በእነርሱ ላይ ይነግሣል” የሚሉት ቃላት ምንኛ የሚያስደስቱ ናቸው!—ሚክ. 4:1-7፤ 1 ጢሞ. 1:17
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ኤንሸንት ኒር ኢስተርን ቴክስትስ፣ በጀምስ ቢ ፕሪቻርድ የተዘጋጀ፣ 1974 ገጽ 284
b አሲርያን ኤንድ ባቢሎንያን ክሮኒክልስ፣ በኤ ኬ ግሬይሰን የተዘጋጀ፣ 1975 ገጽ 73
c ኤንሸንት ኒር ኢስተርን ቴክስትስ፣ 1974 ገጽ 288፤ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 894-895