የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • bsi07 ገጽ 21-23
  • የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 34—ናሆም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 34—ናሆም
  • “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ” ትክክለኛና ጠቃሚ ናቸው፣ ጥራዝ 15
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
“ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ” ትክክለኛና ጠቃሚ ናቸው፣ ጥራዝ 15
bsi07 ገጽ 21-23

የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 34​—⁠ናሆም

ጸሐፊው:- ናሆም

የተጻፈበት ቦታ:- ይሁዳ

ተጽፎ ያለቀው:- ከክ. ል. በፊት ከ632 ቀደም ብሎ

የናሆም ትንቢት የሚጀምረው “ስለ ነነዌ ጥፋት የተነገረ ንግር” በሚሉት አስደንጋጭ ቃላት ነው። (ናሆም 1:1) ይሁን እንጂ ናሆም ይህን የጥፋት መልእክት ያወጀው ለምን ነበር? ስለ ጥንቷ ነነዌ ምን የሚታወቅ ነገር አለ? ናሆም ነነዌን ‘የደም ከተማ’ ብሎ በመጥራት ታሪኳን በሁለት ቃላት አጠቃልሎ ገልጾታል። (3:1) የጥንትዋ ነነዌ በነበረችበት ቦታ ላይ ይኸውም በሰሜናዊ ኢራቅ ካለችው ከዛሬዋ የሞሱል ከተማ ባሻገር በጤግሮስ ወንዝ ምሥራቃዊ ዳርቻ ላይ ሁለት ጉብታዎች ይታያሉ። ነነዌ ታላቅ ቅጥር የነበራት ከመሆኑም በላይ ከተማዋን ከጥቃት ለመከላከል ሲባል በግንቡ ዙሪያ ተቆፍሮ ውኃ በተሞላ ጥልቅና ሰፊ ጉድጓድ ተከብባ ነበር። ከተማዋ ከመጥፋቷ በፊት በነበሩት ዓመታት ነነዌ የአሦር ግዛት ዋና ከተማ ነበረች። ይሁን እንጂ ከተማይቱ የተቆረቆረችው “በእግዚአብሔር ፊት [“ይሖዋን በመቃወም፣” NW] ብርቱ አዳኝ” እንደሆነ በተነገረለት በናምሩድ ዘመን ሲሆን እርሱም “ወደ አሦር ወጥቶ ነነዌን . . . መሠረተ።” (ዘፍ. 10:9-12) ይህም ነነዌ የተመሠረተችበት መንገድ ጥሩ እንዳልነበረ ያሳያል። ከተማዋ ገናና የሆነችው በአሦር መንግሥት የመጨረሻ ዘመናት በተለይም በሳርጎን፣ በሰናክሬብ፣ በአስራዶንና በአሹርባኒጳል ዘመነ መንግሥት ነበር። ነነዌ ከጦርነትና ከወረራ በተሰበሰቡ ምርኮዎች ከመበልጸጓም በላይ ገዥዎቿ ሥፍር ቁጥር በሌላቸው ምርኮኞቻቸው ላይ በሚፈጽሙት ሰብዓዊነት የጎደለው የጭካኔ ድርጊት በጣም የታወቀች ሆነች።a ከርት ዊሊ ማሬክ ጎድስ፣ ግሬቭስ ኤንድ ስኮላርስ (1954) በተባለው መጽሐፋቸው ገጽ 266 ላይ እንዲህ ብለዋል:- “ነነዌ በሰው ዘሮች ዘንድ የምትታወሰው በግድያ፣ በዘረፋ፣ በጭቆና፣ በደካሞች ላይ ግፍ በመፈጸም፣ በጦርነትና በተለያዩ የዓመጽ ድርጊቶች እንዲሁም ሕዝቡን በማስፈራራት አስጨንቆ የሚገዛው ደም አፍሳሽ ሥርወ መንግሥት በሚፈጽማቸው ተግባሮች ብቻ ነው። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ገዥዎች ከእነርሱ ይበልጥ ጨካኝ በሆኑ ተፎካካሪዎቻቸው ይገለበጡ ነበር።”

2 ስለ ነነዌ ሃይማኖትስ ምን ሊባል ይችላል? በርካታ አማልክት ይመለኩባት የነበረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ ከባቢሎን የተወሰዱ ነበሩ። ገዥዎቿ ለማጥፋትና ለማውደም በሚዘምቱበት ጊዜ ወደ እነዚህ አማልክት ይጸልዩ ነበር፤ ስግብግብ የሆኑት ካህናቶችዋም ከምርኮ የሚያገኙትን ሀብት በመናፈቅ ከተማዋን ለዘመቻና ለጦርነት ያነሳሱ ነበር። ደብልዩ ቢ ራይት ኤንሸንት ሲቲስ (1886 ገጽ 25) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው ብለዋል:- “[የነነዌ ሰዎች] የሚያመልኩት ጥንካሬን ሲሆን የሚጸልዩትም በጣም ግዙፍ ለሆኑ የድንጋይ ጣዖቶች ብቻ ነበር። በአንበሳና በኮርማ ቅርጽ የተሠሩት እነዚህ ጣዖቶች፣ የፈረጠሙ እጆችና እግሮች፣ የንሥር ክንፎች እንዲሁም የሰው ጭንቅላት ያላቸው ሲሆን ይህም የጥንካሬ፣ የድፍረትና የድል ምሳሌ ነበር። የአገሪቱ ዋነኛ ሥራ ውጊያ ሲሆን ካህናቶቹም ያለማቋረጥ ለጦርነት ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር። ዘራፊ የሆኑት የዚህች አገር ሰዎች በጣም ሃይማኖተኞች በመሆናቸው ምንጊዜም ቢሆን በምርኮ የተገኘው ሀብት ለሌሎች ከመከፋፈሉ በፊት የተወሰነው ክፍል ለካህናቶቹ ይሰጥ ነበር፤ የካህናቶቹ ዋነኛ መተዳደሪያም ይኸው ነበር።”

3 የናሆም ትንቢት አጭር ቢሆንም ትኩረት የሚስቡ በርካታ ነገሮችን ያካተተ ነው። “የኤልቆሻዊው የናሆም የራእዩ መጽሐፍ ይህ ነው ናሆም 1:1” ከሚለው የትንቢቱ የመክፈቻ ሐሳብ የበለጠ ስለ ነቢዩ የግል ሕይወት የምናውቀው ነገር የለም። ስሙ (በዕብራይስጥ ናኹም) “አጽናኝ” ማለት ነው። የተናገረው መልእክት ለነነዌ ነዋሪዎች አጽናኝ እንዳልነበረ ግልጽ ቢሆንም ምንጊዜም ከማይበርድለት ኃያል ጠላታቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚገላገሉ በእርግጠኝነት ለተነገራቸው የአምላክ እውነተኛ ሕዝቦች ግን የናሆም ትንቢት አጽናኝ ነበር። በተጨማሪም ናሆም ስለ ራሱ ሕዝብ ኃጢአት ምንም የተናገረው ነገር አለመኖሩ የሚያጽናና ነው። ኤልቆሽ ይገኝ የነበረበትን ቦታ በእርግጠኝነት ማወቅ ባይቻልም ትንቢቱ የተጻፈው በይሁዳ ይመስላል። (ናሆም 1:15) ነነዌ የወደቀችው ናሆም ትንቢቱን ከጻፈ ከብዙ ጊዜ በኋላ ማለትም በ632 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሆን፣ ነቢዩ የነነዌን ውድቀት ከኖእ አሞን (በግብፅ የምትገኘው ቴብስ) ውድቀት ጋር አነጻጽሮታል። ይህቺ ከተማ የወደቀችው ከነነዌ ጥቂት ቀደም ብላ ነበር። (3:8) ስለዚህ ናሆም ትንቢቱን የጻፈው በዚህ ጊዜ አካባቢ መሆን ይኖርበታል።

4 የመጽሐፉ አጻጻፍ ለየት ያለ ነው። በናሆም ትንቢት ውስጥ የማያስፈልጉ አገላለጾች አይገኙም። አጻጻፉ ኃይል ያለውና ተጨባጭ ሁኔታዎችን የሚገልጽ መሆኑ፣ ይህ መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት አንዱ መሆኑን ያሳያል። የናሆም ትንቢት ገላጭ፣ ስሜታዊና ሥዕላዊ በሆነ ቋንቋ መጻፉ እንዲሁም ክብር ያለው አገላለጹ፣ የምሳሌዎቹ ግልጽነትና ስሜት የሚነኩ አነጋገሮቹ የላቀ ደረጃ እንዲኖረው አድርጎታል። (1:2-8, 12-14፤ 2:4, 12፤ 3:1-5, 13-15, 18, 19) የመጀመሪያው ምዕራፍ አብዛኛው ክፍል በዕብራይስጥ ፊደላት ቅደም ተከተል መሠረት የተቀናበረ ግጥም ይመስላል። (1:8 የኣዲስ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) የናሆም ትንቢት አንድ ጭብጥ የተከተለ መሆኑ ለአጻጻፉ ጥራት አስተዋጽኦ አድርጓል። ናሆም፣ የእስራኤል አደገኛ ጠላት ለሆነችው ብሔር ከፍተኛ ጥላቻ አለው። የነነዌን ውድመት ከማየት የበለጠ የሚመኘው ነገር የለም።

5 የናሆም ትንቢት በተነገረው መሠረት መፈጸሙ፣ የመጽሐፉን ትክክለኛነት ያረጋግጣል። በናሆም ዘመን፣ የይሖዋ ነቢይ ካልሆነ በስተቀር የዓለም ኃያል መንግሥት የነበረው የአሦር ዋና ከተማ የሆነችው እብሪተኛዋ ነነዌ ‘በወንዙ በር’ በኩል እንደምትጠቃና ቤተ መንግሥቷ እንደሚፈርስ እንዲሁም ‘ተበዝብዛና ተዘርፋ እንደምትራቆት’ ሊተነብይ የሚደፍር ማን ይኖራል? (2:6-10) የተፈጸሙት ሁኔታዎች በእርግጥም ትንቢቱ በአምላክ መንፈስ የተነገረ መሆኑን ያረጋግጣሉ። ናቦፖላሳር የተባለው የባቢሎን ንጉሥ ዜና መዋዕል፣ ነነዌ በሜዶናውያንና በባቢሎናውያን ስለ መማረኳ ሲተርክ ‘ከተማይቱን የፍርስራሽ ቁልል፣ የቆሻሻ ክምር አደረጓት’ ይላል።b ነነዌ ሙሉ በሙሉ ስለወደመች ለበርካታ መቶ ዘመናት የት እንደነበረች እንኳ በውል አይታወቅም ነበር። በዚህ ምክንያት አንዳንድ ተቺዎች፣ ነነዌ የምትባል ከተማ ፈጽሞ እንዳልነበረች በመግለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እስከ ማፌዝ ደርሰው ነበር።

6 ይሁን እንጂ ነነዌ የነበረችበት ሥፍራ ታውቆ በ19ኛው መቶ ዘመን በዚያ ቦታ የመሬት ቁፋሮ በመጀመሩ የናሆም ትንቢት ትክክለኛነት የበለጠ ሊረጋገጥ ችሏል። የከተማይቱን ፍርስራሽ ሙሉ በሙሉ ለማግኘት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ቶን የሚመዘን አፈር ማውጣት እንደሚያስፈልግ ተገምቶ ነበር። ታዲያ በነነዌ ምን ተገኘ? የናሆምን ትንቢት ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ በርካታ ነገሮች በቁፋሮ ወጥተዋል! ለምሳሌ ያህል፣ ጭካኔዋን የሚያረጋግጡ ሐውልቶችዋና በሐውልቶቹ ላይ የተቀረጹት ጽሑፎች እንዲሁም ክንፍ ያላቸው ኮርማዎችና አንበሶች ግዙፍ ምስሎች ፍርስራሾችም ተገኝተዋል። ናሆም ይህቺን ከተማ “የአንበሶቹ ዋሻ” ብሎ መጥራቱ አያስደንቅም!—2:11c

7 አይሁዳውያን፣ የናሆምን ትንቢት በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል አድርገው መቀበላቸው መጽሐፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መሆኑን ያረጋግጣል። የናሆም ትንቢት ከቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማል። ትንቢቱ በይሖዋ ስም የተነገረ ሲሆን ስለ ይሖዋ ባሕርያትና ታላቅነት ግሩም ምሥክርነት ይሰጣል።

ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት

11 በናሆም ትንቢት ውስጥ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተጠቅሰዋል። የራእዩ የመክፈቻ ሐሳብ፣ አምላክ ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል ሁለተኛውን ትእዛዝ የሰጠበትን ምክንያት በድጋሚ ሲገልጽ “እግዚአብሔር ቀናተኛ [“ይሖዋ እርሱ ብቻ እንዲመለክ የሚሻ፣” NW] . . . አምላክ ነው” ይላል። ከዚያ በማስከተል “ባላጋራዎቹን ይበቀላል” በማለት ይሖዋ የበቀል እርምጃ መውሰዱ የማይቀር መሆኑን ያረጋግጣል። የአሦር እብሪትና ጭካኔ እንዲሁም አረማዊ አማልክቶቿ ከይሖዋ ፍርድ ሊያድኗት አይችሉም። በተመሳሳይም ይሖዋ በቀጠረው ጊዜ በክፉዎች ሁሉ ላይ ፍርዱን እንደሚፈጽም እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። “እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ በኀይሉም ታላቅ ነው፤ እግዚአብሔር በደለኛውን ሳይቀጣ አያልፍም።” ይሖዋ ኃያሏን አሦር በማጥፋቱ ፍትሑና ታላቅነቱ ከፍ ብሎ ታይቷል። ነነዌም “ተበዝብዛለች፤ ተዘርፋለች፤ ተራቍታለች።”—1:2, 3፤ 2:10

12 ናሆም፣ ‘ፈጽማ ከጠፋችው’ ከነነዌ በተቃራኒ ‘የእስራኤልና የያዕቆብ ክብር’ እንደሚመለስ አስታውቋል። በተጨማሪም ይሖዋ “እነሆ፤ የምሥራች የሚያመጣው፣ ሰላምን የሚያውጀው ሰው እግር፣ በተራሮች ላይ ነው” በማለት ለሕዝቦቹ አስደሳች ዜና ልኳል። ይህ የሰላም ምሥራች ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዘ ነው። እንዴት እናውቃለን? ኢሳይያስም እነዚህኑ ቃላት ከጠቀሰ በኋላ “መልካም ዜና የሚያበስሩ፣ ድነትን የሚያውጁ፣ ጽዮንንም፣ “አምላክሽ ነግሦአል” የሚሉ [እግሮች] እንዴት ያማሩ ናቸው” በማለት አክሎ ተናግሯል። (ናሆም 1:15፤ 2:2፤ ኢሳ. 52:7) ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ይህ ትንቢት፣ ይሖዋ ምሥራቹን እንዲያሰራጩ በሚልካቸው ክርስቲያን ሰባኪዎች ላይ እንደሚሠራ በሮሜ 10:15 ላይ ገልጿል። እነዚህ ክርስቲያኖች ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ ይሰብካሉ። (ማቴ. 24:14) ናሆም ከአምላክ መንግሥት የሚመጣውን ሰላምና መዳን ለሚፈልጉ ሁሉ ከፍተኛ መጽናኛ በመስጠት ከስሙ ጋር የሚስማማ ነገር አድርጓል። እነዚህ ሰዎች ‘እግዚአብሔር መልካም፣ በጭንቅ ጊዜም መሸሸጊያ እንደሆነና ለሚታመኑበት እንደሚጠነቀቅላቸው’ ይገነዘባሉ።—ናሆም 1:7

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 201

b ኤንሸንት ኒር ኢስተርን ቴክስትስ፣ በጄ ቢ ፕሪቻርድ የተዘጋጀ፣ 1974 ገጽ 305። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 958

c ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 955

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ