ጥር
እሁድ፣ ጥር 1
ከእኔ የሰማኸውን . . . ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ፤ እነሱም በበኩላቸው ሌሎችን ለማስተማር ብቃቱን ያሟላሉ። —2 ጢሞ. 2:2
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ በብዙ ጉባኤዎች ውስጥ ወጣቶችንም ሆነ በዕድሜ ከፍ ያሉትን ወንድሞች አሠልጥኖ ለኃላፊነት በማብቃት ረገድ ብዙ የሚቀር ነገር እንዳለ አስተውለዋል። ይሁንና ይህን ኃላፊነት መወጣት የራሱ ተፈታታኝ ነገሮች አሉት። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ክርስቲያን ሽማግሌ ከሆንክ ሌሎችን በግለሰብ ደረጃ ማሠልጠን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ሳትገነዘብ አትቀርም። አሁን ያሉት ጉባኤዎች በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነው እንዲቀጥሉ ብሎም አዳዲስ ጉባኤዎች እንዲቋቋሙ ከተፈለገ ተጨማሪ ወንድሞች እንደሚያስፈልጉ የታወቀ ነው። (ኢሳ. 60:22) በተጨማሪም የአምላክ ቃል ‘ሌሎችን እንድታስተምር’ ማሳሰቢያ እንደሰጠህ ታውቃለህ። ያም ሆኖ ሌሎችን ማሠልጠን ከብዶህ ሊሆን ይችላል። የቤተሰብህን ፍላጎት ማሟላትን፣ ሰብዓዊ ሥራ መሥራትንና የጉባኤ ኃላፊነት መወጣትን ጨምሮ ሌሎች አጣዳፊ ሥራዎች እንዳሉብህ ስታስብ ሌሎችን ለማሠልጠን ጊዜ እንደሌለህ ይሰማህ ይሆናል። ይሁንና የተጠመቁ ወንዶች በጉባኤ ውስጥ ለበለጠ ኃላፊነት እንዲበቁ ሥልጠና ማግኘታቸው አስፈላጊ ነው። እንዲህ ከሆነ ሁሉም ጥቅም ማግኘት ይችላሉ። w15 4/15 1:2, 3
ሰኞ፣ ጥር 2
በጌታ ልጄ የሆነውን የምወደውንና ታማኝ የሆነውን ጢሞቴዎስን የምልክላችሁ ለዚህ ነው። እሱም . . . አገልግሎቴን የማከናውንባቸውን ዘዴዎች ያሳስባችኋል።—1 ቆሮ. 4:17
በጉባኤ ውስጥ አንድ ዓይነት ኃላፊነት በቅርቡ የተቀበለ ወንድም ቶሎ ብሎ የራሱን መንገድ ለመከተል መሞከር የለበትም፤ በሌላ አባባል ከዚህ በፊት የነበረውን አሠራር ሙሉ በሙሉ መቀየር እንዳለበት ሊሰማው አይገባም። አንድ አሠራር መለወጥ ያለበት በአንድ ሰው ፍላጎት መሆን የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የጉባኤው ጥቅምና ከይሖዋ ድርጅት የምናገኘው መመሪያ ነው። አንተም ኃላፊነት ከተሰጠህ ሽማግሌዎቹ ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ዘዴዎች ተግባራዊ ማድረግህን በመቀጠል የእምነት ባልንጀሮችህ እንዲተማመኑብህ ማድረግ እንዲሁም ተሞክሮ ላካበቱ ሽማግሌዎች አክብሮት እንዳለህ ማሳየት ትችላለህ። ተሞክሮ እያገኘህ ስትሄድ ጉባኤው ወደፊት እየገሰገሰ ከሚሄደው የይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል እንዲራመድ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ግልጽ ነው። እንዲያውም ይሖዋ ታማኝ እስከሆናችሁ ድረስ ውሎ አድሮ አስተማሪዎቻችሁ ካከናወኑት የበለጠ ነገር እንድትሠሩ ሊጠቀምባችሁ ይችላል።—ዮሐ. 14:12፤ w15 4/15 2:17
ማክሰኞ፣ ጥር 3
ጥልቅ ማስተዋል እሰጥሃለሁ፤ ልትሄድበት የሚገባውንም መንገድ አስተምርሃለሁ። ዓይኔን በአንተ ላይ አድርጌ እመክርሃለሁ።—መዝ. 32:8
ከባድ ፈተና ሲያጋጥምህ አንተም ልክ እንደ ጳውሎስ “አንበሳ አፍ” ውስጥ እንደገባህ ወይም ልትገባ እንደተቃረብክ ያህል ሊሰማህ ይችላል። (2 ጢሞ. 4:17) በይሖዋ መታመን በጣም አስቸጋሪ ሆኖም በጣም አስፈላጊ የሚሆነው በዚህ ጊዜ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በጠና የታመመ የቤተሰብህን አባል እየተንከባከብክ ይሆናል። ምናልባትም ይሖዋ ጥበብና ብርታት እንዲሰጥህ ጸልየህ ሊሆን ይችላል። ታዲያ በዚህ ረገድ የምትችለውን ሁሉ ካደረግክ በኋላ፣ የይሖዋ ዓይን በአንተ ላይ እንደሆነና በታማኝነት ለመጽናት የሚያስፈልግህን ነገር እሱ እንደሚሰጥህ በማወቅህ ውስጥህ አይረጋጋም? ይሁንና በተለያዩ ሁኔታዎች የተነሳ እንዲህ ማድረግ እንደማትችል ይሰማህ ይሆናል። ሐኪሞች የተለያየ አስተያየት ሊሰጡህ አሊያም ደግሞ ያጽናኑኛል ብለህ ያሰብካቸው ዘመዶችህ ሁኔታው ይበልጥ ከባድ እንዲሆንብህ ሊያደርጉ ይችላሉ። በዚህ ወቅት እርዳታ ለማግኘት ምንጊዜም በይሖዋ ታመን። ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ ጥረት አድርግ። (1 ሳሙ. 30:3, 6) ውሎ አድሮ፣ ይሖዋ ችግሮችህን እንዴት እንዳቃለለልህ ስትገነዘብ ከእሱ ጋር ያለህ ዝምድና ይበልጥ ይጠናከራል። w15 4/15 4:10, 11
ረቡዕ፣ ጥር 4
[ሰይጣንን] ተቃወሙት።—1 ጴጥ. 5:9
የይሖዋ አገልጋዮች በመሆናችን ሰይጣን የለም በሚለው አመለካከት አልተታለልንም። ሔዋንን በእባቡ ተጠቅሞ ያነጋገራት ሰይጣን ስለሆነ ዲያብሎስ በእውን ያለ አካል መሆኑን እናውቃለን። (ዘፍ. 3:1-5) ሰይጣን ከኢዮብ ጋር በተያያዘ በይሖዋ ላይ ተሳልቋል። (ኢዮብ 1:9-12) ኢየሱስን ሊፈትነው የሞከረውም ሰይጣን ነው። (ማቴ. 4:1-10) እንዲሁም በ1914 የአምላክ መንግሥት ከተወለደ በኋላ ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር ‘መዋጋት’ የጀመረው ሰይጣን ነው። (ራእይ 12:17) ሰይጣን የ144,000ዎቹን ቀሪዎችና የሌሎች በጎችን እምነት ለማጥፋት እየጣረ በመሆኑ ይህ ጦርነት አሁንም ቀጥሏል። በዚህ ጦርነት ለማሸነፍ፣ በእምነት ጸንተን በመቆም ሰይጣንን መቃወም ይኖርብናል። ሰይጣን ፈጽሞ ሊያንጸባርቀው የማይችለው ባሕርይ ቢኖር ትሕትና ነው። ለነገሩ ይህ መንፈሳዊ ፍጡር የይሖዋን ሉዓላዊ ገዢነት መገዳደሩና ራሱን አምላክ ለማድረግ መድፈሩ ምን ያህል በኩራትና በትዕቢት እንደተወጠረ የሚያሳይ ነው። በመሆኑም ሰይጣንን መቃወም የምንችልበት አንዱ መንገድ ከኩራት መራቅና ትሕትናን ማዳበር ነው።—1 ጴጥ. 5:5፤ w15 5/15 2:3, 4
ሐሙስ፣ ጥር 5
ይሖዋ ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።—ኢሳ. 25:8
ክርስቲያኖች ተስፋችን በሰማይ መኖርም ይሁን በምድር፣ ተስፋችንን በዓይነ ሕሊናችን መመልከታችን ያበረታታናል። አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች ስታገኝ ይታይሃል? አምላክ የሰጠው ተስፋ በሚፈጽምበት ወቅት ምን እንደምታደርግ ማሰላሰልህ ልብህን በደስታ እንደሚሞላው ጥርጥር የለውም። በምድር ላይ ለዘላለም ስትኖር በዓይነ ሕሊናህ ማየት ትችል ይሆናል። ከሌሎች ጋር ተባብረህ ምድርን ወደ ገነት ስትለውጥ ይታይህ። ጎረቤቶችህም እንደ አንተ ይሖዋን ይወዳሉ። ጤናማና ጠንካራ ከመሆንህም ሌላ አዎንታዊ አመለካከት አለህ። ምድርን ወደ ቀድሞው ሁኔታዋ የመመለሱን ሥራ በበላይነት የሚመሩትም ስለ አንተ ከልባቸው ስለሚያስቡ ሕይወት አስደሳች ነው። በተጨማሪም የምታከናውናቸው ነገሮች በሙሉ ሌሎችን የሚጠቅሙና አምላክን የሚያስከብሩ ስለሆኑ ባለህ ተሰጥኦና ችሎታ መጠቀም ያስደስትሃል። ለምሳሌ ያህል፣ ከሞት የሚነሱትን ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ ትረዳለህ። (ዮሐ. 17:3፤ ሥራ 24:15) ይህ፣ እንዲያው ከንቱ ምኞት አይደለም። በዓይነ ሕሊናችን የምንስለው እንዲህ ያለው አስደሳች ሕይወት ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ ወደፊቱ ጊዜ በሚናገሩት እውነት ላይ የተመሠረተ ነው።—ኢሳ. 11:9፤ 33:24፤ 35:5-7፤ 65:22፤ w15 5/15 3:15
ዓርብ፣ ጥር 6
የድግሱ አሳዳሪም ወደ ወይን ጠጅ የተለወጠውን ውኃ ቀመሰ።—ዮሐ. 2:9
ኢየሱስ ለብዙ ሕዝብ የሚበቃ በርከት ያለ ጥሩ የወይን ጠጅ በተአምር አቅርቧል። (ዮሐ. 2:6-11) ድንጋዮቹን ወደ ዳቦ እንዲቀይር ዲያብሎስ በፈተነው ጊዜ ክርስቶስ ተአምር የመፈጸም ችሎታውን የራሱን ጥቅም ለማርካት እንዳልተጠቀመበት ልብ ሊባል ይገባል። (ማቴ. 4:2-4) ይሁንና ሌሎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ኃይሉን ተጠቅሞበታል። እኛስ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ለሌሎች አሳቢነት በማሳየት ረገድ ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ የአምላክን አገልጋዮች “ስጡ” በማለት አበረታቷቸዋል። (ሉቃስ 6:38) እኛስ ሌሎችን ቤታችን ጠርተን ምግብ በመጋበዝና በመንፈሳዊ በመተናነጽ ግሩም ባሕርይ የሆነውን ልግስናን ማሳየት እንችላለን? እገዛ የሚያስፈልጋቸውን በመርዳት ለምሳሌ ከስብሰባ በኋላ አንድ ወንድም ንግግሩን ሲለማመድ በማዳመጥ፣ ጊዜያችንን በልግስና መስጠት እንችላለን? በአገልግሎት እገዛ የሚያስፈልጋቸውንስ እንዴት መርዳት እንችላለን? አዎ፣ አቅማችን በፈቀደ መጠን ለሌሎች ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ነገሮችን በልግስና በማካፈል የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። w15 6/15 1:3, 4, 6
ቅዳሜ፣ ጥር 7
በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው “ታምሜአለሁ” አይልም።—ኢሳ. 33:24
ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን የምንመላለስ ከሆነ እስከ ዛሬ ከተፈጸሙት ታላላቅ ተአምራት አንዱ የሆነውን ተአምር በዓይናችን ማየት ይኸውም ታላቁን መከራ በሕይወት ማለፍ እንችላለን። የአርማጌዶን ጦርነት ከተካሄደ ብዙም ሳይቆይ፣ የሰው ልጆች የተሟላ ጤንነት እንዲኖራቸው የሚያደርጉ ተጨማሪ ተአምራት ይከናወናሉ። (ኢሳ. 35:5, 6፤ ራእይ 21:4) ሰዎች መነጽራቸውን፣ ከዘራቸውን፣ ምርኩዛቸውን፣ ተሽከርካሪ ወንበራቸውን፣ ለመስማት የሚረዷቸውን መሣሪያዎችና እነዚህን የመሳሰሉትን ነገሮች ሲጥሉ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ከአርማጌዶን የሚተርፉት ሰዎች የሚጠብቃቸው ሥራ አለ። የአምላክ ስጦታ የሆነችውን ምድራችንን ወደ ገነትነት የመቀየሩን ሥራ በቅንዓት ማከናወን ይችላሉ። (መዝ. 115:16) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሕመምተኞችን መፈወሱ፣ በዘመናችን ያሉ ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት ከማንኛውም በሽታ እንደሚፈወሱ ባላቸው አስደሳች ተስፋ ላይ ይበልጥ እንዲተማመኑ ያደርጋቸዋል። (ራእይ 7:9) የአምላክ የበኩር ልጅ የታመሙትን መፈወሱ ለሰው ልጆች በጥልቅ እንደሚያስብና በጣም እንደሚወዳቸው ያሳያል። (ዮሐ. 10:11፤ 15:12, 13) ኢየሱስ ያሳየው ርኅራኄ ይሖዋ ለእያንዳንዱ አገልጋዩ እንደሚያስብ የሚያረጋግጥ ልብ የሚነካ ማስረጃ ነው።—ዮሐ. 5:19፤ w15 6/15 2:16, 17
እሁድ፣ ጥር 8
ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል።—ራእይ 12:12
በ1914 በአውሮፓ በሚገኙ አገራት መካከል ጦርነት ተቀሰቀሰ፤ ጦርነቱም በመስፋፋቱ በመላው ዓለም ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። በ1918 ጦርነቱ ሲያበቃ ከባድ የምግብ እጥረት ተከሰተ፤ ቀጥሎም በጦርነቱ ከሞቱት የሚበልጥ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች የጨረሰ የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ ተነሳ። በመሆኑም ኢየሱስ የምድር አዲሱ ንጉሥ ሆኖ በማይታይ ሁኔታ መገኘቱን እንደሚጠቁም የሚያሳየው “ምልክት” መፈጸም ጀመረ። (ማቴ. 24:3-8፤ ሉቃስ 21:10, 11) ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘አክሊል የተሰጠው’ በ1914 መሆኑን የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃ አለ። “እሱም ድል እያደረገ ወጣ፤ ድሉንም ለማጠናቀቅ ወደ ፊት ገሰገሰ።” (ራእይ 6:2) ኢየሱስ በሰይጣንና በአጋንንቱ ላይ ጦርነት በማወጅ ሰማይን ያጸዳ ሲሆን እነሱንም ወደ ምድር አካባቢ ወረወራቸው። ከዚያ ጊዜ ወዲህ የሰው ልጆች፣ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ሐሳብ እውነተኝነት እየተመለከቱ ነው። w15 6/15 4:13
ሰኞ፣ ጥር 9
ከጌታ የተቀበልኳቸውን ተአምራዊ ራእዮችና ጌታ የገለጠልኝን መልእክቶች እናገራለሁ።—2 ቆሮ. 12:1
የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ መቶ ዓመት እንኳ ሳይሞላው፣ አስቀድሞ እንደተነገረው ክህደት መስፋፋት ጀመረ። (ሥራ 20:28-30፤ 2 ተሰ. 2:3, 4) ከዚያ በኋላ አምላክን በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ በትክክል እያገለገሉ ያሉትን ሰዎች ማንነት መለየት አስቸጋሪ እየሆነ ሄደ። ይሖዋ፣ በተሾመው ንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ነገሮች ግልጽ እንዲሆኑ ያደረገው ከዘመናት በኋላ ነው። የይሖዋን ሞገስ ያገኙትና በመንፈሳዊው ቤተ መቅደሱ እያገለገሉ ያሉት እነማን እንደሆኑ በ1919 በግልጽ ታወቀ። እነዚህ ክርስቲያኖች ለአምላክ የሚያቀርቡት አገልግሎት በእሱ ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነት እንዲኖረው በመንፈሳዊ ሁኔታ ነጽተዋል። (ኢሳ. 4:2, 3፤ ሚል. 3:1-4) ሐዋርያው ጳውሎስ ከበርካታ ዘመናት በፊት የተመለከተው ራእይ በዚህ ጊዜ በተወሰነ መንገድ ፍጻሜ ማግኘት ጀመረ። ጳውሎስ የተመለከተው ራእይ በ2 ቆሮንቶስ 12:2-4 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። ጳውሎስ የተመለከተውን ተአምራዊ ራእይ፣ የተገለጠ መልእክት በማለትም ገልጾታል። የተመለከተው ነገር በእሱ ዘመን የነበረ ሳይሆን ወደፊት የሚፈጸም ነው። w15 7/15 1:6-8
ማክሰኞ፣ ጥር 10
በዚያ ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ደምቀው ያበራሉ።—ማቴ. 13:43
ይህ ሲባል ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ይነጠቃሉ” ማለት ነው? ብዙ የሕዝበ ክርስትና አባላት “መነጠቅ” የሚለው ትምህርት ክርስቲያኖች ሥጋዊ አካላቸውን እንደለበሱ ከምድር መወሰዳቸውን እንደሚያመለክት ያምናሉ። ከዚያም ኢየሱስ በሚታይ መንገድ በመመለስ ምድርን እንደሚገዛ ይጠብቃሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ” እንደሚታይ እንዲሁም ኢየሱስ “በሰማይ ደመና” እንደሚመጣ በግልጽ ይናገራል። (ማቴ. 24:30) ሁለቱም አገላለጾች የሚያመለክቱት በዓይን የማይታይ ሁኔታን ነው። በተጨማሪም “ሥጋና ደም የአምላክን መንግሥት አይወርስም።” በመሆኑም ወደ ሰማይ የሚወሰዱ ሰዎች “የመጨረሻው መለከት በሚነፋበት ወቅት ድንገት፣ በቅጽበተ ዓይን [መለወጥ]” ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮ. 15:50-53) በምድር የቀሩት ታማኝ ቅቡዓን በቅጽበት ወደ ሰማይ ይሰበሰባሉ። w15 7/15 2:14, 15
ረቡዕ፣ ጥር 11
በጉባኤ መካከልም አወድስሃለሁ።—መዝ. 22:22
የመንግሥት አዳራሽ በአንድ አካባቢ ለሚካሄደው ንጹሕ አምልኮ ማዕከል ነው። ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ለመመገብ ካደረጋቸው ዝግጅቶች መካከል በመንግሥት አዳራሾች ውስጥ የሚከናወኑት ሳምንታዊ ስብሰባዎች ይገኙበታል። በድርጅቱ በኩል አስፈላጊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብና መመሪያ የሚሰጠን በስብሰባዎቻችን ላይ ነው። “ከይሖዋ ማዕድ” እንድንመገብ ሁልጊዜም ግብዣ ይቀርብልናል፤ ይህ መሆኑ ግን ግብዣውን አቅልለን እንድንመለከተው በፍጹም ሊያደርገን አይገባም። (1 ቆሮ. 10:21) ይሖዋ፣ ለአምልኮና እርስ በርስ ለመበረታታት የሚያስችሉን እነዚህ አጋጣሚዎች በጣም አስፈላጊ እንደሆኑ ስለሚያውቅ መሰብሰባችንን ቸል እንዳንል የሚያሳስብ መልእክት ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት እንዲጽፍ አድርጓል። (ዕብ. 10:24, 25) በማይረባ ምክንያት ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የምንቀር ከሆነ ለይሖዋ አክብሮት እያሳየን ነው ማለት እንችላለን? በሌላ በኩል ግን ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በመዘጋጀትና በሙሉ ልብ ተሳትፎ በማድረግ ለይሖዋና ለዝግጅቱ ምን ያህል አድናቆት እንዳለን ማሳየት እንችላለን። w15 7/15 4:3, 4
ሐሙስ፣ ጥር 12
ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።—ማቴ. 24:42
ኢየሱስ እንዲህ እንድናደርግ መናገሩ በራሱ በተስፋ ለመጠባበቅ የሚያነሳሳን አጥጋቢ ምክንያት ነው! ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የይሖዋ ድርጅት ምሳሌ ይሆነናል። በየጊዜው በሚያወጣቸው ጽሑፎች አማካኝነት ‘የይሖዋን ቀን መምጣት እንድንጠብቅና በአእምሯችን አቅርበን እንድንመለከት’ እንዲሁም አምላክ ባዘጋጀው አዲስ ዓለም ላይ ትኩረት እንድናደርግ በተደጋጋሚ ሲያሳስበን ቆይቷል። (2 ጴጥ. 3:11-13) ጥንት የነበሩት ክርስቲያኖች በተስፋ መጠባበቃቸው አስፈላጊ የነበረ ቢሆንም በተለይ በአሁኑ ጊዜ ይህን ማድረግ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም የምንኖረው ክርስቶስ በሥልጣኑ በተገኘበት ጊዜ ላይ ነው። ከ1914 ጀምሮ የመገኘቱ ምልክት በግልጽ እየታየ ነው። ብዙ ገጽታዎች ያሉት ይህ ምልክት፣ የዓለም ሁኔታ እየተባባሰ መሄዱን እንዲሁም የመንግሥቱ የስብከት ሥራ በዓለም ዙሪያ መከናወኑን ይጨምራል፤ የምልክቱ መፈጸም ደግሞ የምንኖረው “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” በተባለው ጊዜ ላይ መሆኑን ያሳያል። (ማቴ. 24:3, 7-14) ኢየሱስ የሥርዓቱ መደምደሚያ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ መጨረሻው እስከሚመጣ ድረስ ምን ያህል ጊዜ እንደሚያልፍ አልተናገረም፤ በመሆኑም ይበልጥ ንቁዎች መሆን ይኖርብናል። w15 8/15 2:4, 5
ዓርብ፣ ጥር 13
በይሖዋ ሐሴት አድርግ።—መዝ. 37:4
በአዲሱ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀ እርካታ የምናገኘው መንፈሳዊ ፍላጎታችን በመሟላቱ ነው። (ማቴ. 5:3) ከሁሉ በላይ ቅድሚያ የምንሰጠው ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ሲሆን በይሖዋ ሐሴት እንደምናደርግ እናሳያለን። እንግዲያው በአሁኑ ጊዜ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ ወደፊት ለምናገኘው እውነተኛ ሕይወት እንዘጋጃለን። (ማቴ. 6:19-21) በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች በመካፈል የምናገኘውን ደስታ ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ መንፈሳዊ ግቦችን በማውጣት ነው። ወጣት ከሆንክና በይሖዋ አገልግሎት በሙሉ ጊዜህ ለመሰማራት በቁም ነገር እያሰብክ ከሆነ ስለተለያዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች የወጡ አንዳንድ ጽሑፎችን ለምን አትከልስም? ከዚያም ከእነዚህ በአንዱ ለመካፈል ግብ ልታወጣ ትችላለህ። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ብዙ ዓመታት ያሳለፉ አንዳንድ ወንድሞችን ማነጋገርም ትችላለህ። ይሖዋን በማገልገል የምታሳልፈው ሕይወት፣ በአዲሱ ዓለም ውስጥ አምላክን ማገልገልህን እንድትቀጥል ያዘጋጅሃል፤ አሁን ያገኘኸው ቲኦክራሲያዊ ሥልጠና እና ያዳበርከው ልምድ በዚያ ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል። w15 8/15 3:13, 14
ቅዳሜ፣ ጥር 14
የመንፈስ ፍሬ ፍቅር . . . ነው።—ገላ. 5:22
እንደ ገርነት፣ ራስን መግዛትና ትዕግሥት ያሉት የመንፈስ ፍሬ ሌሎች ገጽታዎችም በጣም አስፈላጊ ናቸው። (ገላ. 5:22, 23) አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት እንዳይበሳጭ እንዲሁም ቅስም የሚሰብሩ አሳዛኝ ነገሮች ሲደርሱበት ተስፋ ሳይቆርጥ እንዲጸና ሊረዱት ይችላሉ። የግል ጥናት በሚያደርግበት ጊዜ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችል የሚረዱትን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማግኘት ያለማሰለስ ምርምር ያደርጋል። ከዚያም በሕይወቱ ውስጥ የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች መንፈሳዊ ጉልምስና እንዳለው የሚያሳዩ ይሆናሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናው የሚነግረውን ያዳምጣል። ይህ ክርስቲያን በራሱ ከመመራት ይልቅ ይሖዋ ባወጣቸው መመሪያዎችና መሥፈርቶች መመራት ምንጊዜም የተሻለ እንደሆነ አምኖ በመቀበል ትሕትና እንዳለው ያሳያል። ምሥራቹን በቅንዓት ይሰብካል፤ እንዲሁም ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ ያበረክታል። ይሖዋን ለረጅም ዓመታት ያገለገልንም እንሁን ለአጭር ጊዜ፣ እያንዳንዳችን ‘የኢየሱስን አርዓያ በጥብቅ በመከተልና መንፈሳዊ እድገት በማድረግ ረገድ አሁንም ማሻሻያ ማድረግ የምችልባቸው አቅጣጫዎች ይኖራሉ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። w15 9/15 1:6, 7
እሁድ፣ ጥር 15
አንተ እምነት የጎደለህ! ለምን ተጠራጠርክ?—ማቴ. 14:31
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት፣ ኢየሱስ በገሊላ ባሕር ላይ ሲራመድ አዩት። ጴጥሮስ ኢየሱስን ጠርቶ በውኃው ላይ እየተራመደ ወደ እሱ መምጣት ይችል እንደሆነ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲመጣ ሲነግረው ጴጥሮስ ከጀልባዋ ላይ ወርዶ በሚናወጠው ውኃ ላይ በተአምር እየተራመደ ወደ ኢየሱስ ሄደ። ብዙም ሳይቆይ ግን ጴጥሮስ መስመጥ ጀመረ። ለምን? ምክንያቱም ማዕበሉን ሲያይ ፈራ። ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ እንዲረዳው ጮኸ፤ እሱም ወዲያውኑ እጁን ዘርግቶ ያዘውና ከላይ ያለውን ተናገረ። (ማቴ. 14:24-32) ጴጥሮስ ከጀልባዋ ወርዶ በውኃው ላይ እንዲራመድ ያስቻለው እምነት ነው። ኢየሱስ ጴጥሮስን ሲጠራው ጴጥሮስ የአምላክ ኃይል ኢየሱስን እንደረዳው ሁሉ እሱንም ሊረዳው እንደሚችል ተማምኖ ነበር። እኛም በተመሳሳይ ራሳችንን ለይሖዋ እንድንወስንና እንድንጠመቅ ያስቻለን እምነታችን ነው። ኢየሱስ የእሱ ተከታዮች እንድንሆን ይኸውም ፈለጉን እንድንከተል ጠርቶናል። ኢየሱስም ሆነ አምላክ በተለያዩ መንገዶች እንደሚረዱን በመተማመን በእነሱ ላይ እምነት እንዳለን ማሳየት ይኖርብናል።—ዮሐ. 14:1፤ 1 ጴጥ. 2:21፤ w15 9/15 3:1, 3
ሰኞ፣ ጥር 16
እሱ የታማኝ አገልጋዮቹን ሕይወት ይጠብቃል፤ ከክፉዎች እጅ ይታደጋቸዋል።—መዝ. 97:10
አንድ አፍቃሪ አባት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ነገሮች አንዱ ቤተሰቡን ከጉዳት ወይም አደጋ ሊያደርስ ከሚችል ነገር መጠበቅ ወይም መታደግ እንደሆነ ግልጽ ነው። በሰማይ የሚኖረው አባታችን ይሖዋ ከዚህ ያነሰ ነገር እንደማያደርግ የታወቀ ነው። አንድ ምሳሌ እንመልከት። መቼም ለዓይንህ በጣም እንደምትሳሳ ግልጽ ነው! ይሖዋ ለሕዝቡ ያለው ስሜትም ልክ እንደዚህ ነው። (ዘካ. 2:8) በእርግጥም አምላክ ለሕዝቡ በጣም ይሳሳል! እርግጥ ነው፣ ይሖዋ እንደ እስጢፋኖስ ያሉ ታማኝ አገልጋዮቹ በጠላቶቻቸው እጅ ሕይወታቸው እንዲያልፍ የፈቀደበት ጊዜ አለ። ይሁንና አምላክ የሰይጣንን መሠሪ ዘዴዎች መቋቋም እንዲችሉ ወቅታዊ ማስጠንቀቂያዎችን በመስጠት ሕዝቡን በአጠቃላይ ከአደጋ ይጠብቃል። (ኤፌ. 6:10-12) ይሖዋ በቃሉና ድርጅቱ በሚያዘጋጃቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አማካኝነት ሀብት ስላለው የማታለል ኃይል፣ ብልግናና ዓመፅ ስለተሞላባቸው መዝናኛዎች፣ ተገቢ ስላልሆነ የኢንተርኔት አጠቃቀምና ስለመሳሰሉት ነገሮች እውነቱን መገንዘብ እንድንችል ይረዳናል። ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደምንችለው ይሖዋ ልክ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት ሕዝቡን ከአደጋ ይጠብቃል። w15 9/15 4:15, 17
ማክሰኞ፣ ጥር 17
የይሖዋ እጅ ማዳን ይሳናት ዘንድ አላጠረችም።—ኢሳ. 59:1
የይሖዋ ምሥክሮች ‘ለምሥራቹ ሲሟገቱና በሕግ የጸና እንዲሆን ለማድረግ’ ሲጥሩ የተሳካ ውጤት ማግኘታቸው የይሖዋ ኃያል እጅ እንደሚረዳቸው የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው። (ፊልጵ. 1:7) አንዳንድ መንግሥታት የአምላክን ሕዝቦች ሥራ ሙሉ በሙሉ ለማስቆም ጥረት አድርገዋል። ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮች ከ2000 አንስቶ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የተቀዳጇቸውን 24 ድሎችን ጨምሮ በከፍተኛ ፍርድ ቤት የታዩ 268 ጉዳዮችን ማሸነፋቸው የአምላክን እጅ መግታት የሚችል አንድም ሰው እንደሌለ በግልጽ ያሳያል። (ኢሳ. 54:17) በዓለም ዙሪያ ምሥራቹን የመስበኩ ሥራ ሊሳካ የቻለው የአምላክ እጅ ስላለበት ነው። (ማቴ. 24:14፤ ሥራ 1:8) በተጨማሪም ከሁሉም ብሔራት በተውጣጡ የይሖዋ አገልጋዮች መካከል የሚታየው አንድነት እውን ሊሆን የቻለው በይሖዋ እርዳታ ብቻ ነው። ይህ በዓለም ታይቶ የማይታወቅ አንድነት ነው! ይሖዋን የማያመልኩ ሰዎች እንኳ “አምላክ በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” ለማለት ተገደዋል። (1 ቆሮ. 14:25) ስለዚህ ጉዳዩን ጠቅለል አድርገን ስንመለከት አምላክ ሕዝቡን እየረዳ እንደሆነ የሚያሳይ ከበቂ በላይ ማስረጃ አለን።—ኢሳ. 66:14፤ w15 10/15 1:13, 14
ረቡዕ፣ ጥር 18
በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች አትውደዱ።—1 ዮሐ. 2:15
ዓለም በሚያቀርባቸው ነገሮች ከልክ በላይ መጠቀም አደጋ አለው። (1 ቆሮ. 7:29-31) አንድ ክርስቲያን በራሳቸው ስህተት ባይኖራቸውም እንደ ትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ፣ መጻሕፍትን እንደ ማንበብ፣ ቴሌቪዥን እንደ መመልከት፣ የተለያዩ ቦታዎችን እንደ መጎብኘት፣ በየሱቁ እየዞሩ ዕቃዎችን እንደ ማየትና አዳዲስ የኤሌክትሮኒክስ ወይም የቅንጦት ዕቃዎችን እንደ ማፈላለግ ባሉ እንቅስቃሴዎች ከመጠን በላይ ጊዜ ሊያጠፋ ይችላል። ማኅበራዊ ድረ ገጾችን ማሰስ፣ የስልክ መልእክቶችን መለዋወጥ፣ ኢሜይሎችን መላላክና አዳዲስ ዘገባዎችን ወይም ከስፖርት ጋር የተያያዙ ወቅታዊ መረጃዎችን በየሰዓቱ መከታተል ጊዜያችንን ሊያባክንብን እንዲያውም ሱስ ሊሆንብን ይችላል። (መክ. 3:1, 6) እምብዛም አስፈላጊ ባልሆኑ ጉዳዮች በምናጠፋው ጊዜ ላይ፣ ገደብ ካላደረግን ከምንም በላይ አስፈላጊ የሆነውን ማለትም ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ ችላ ልንል እንችላለን። (ኤፌ. 5:15-17) ሰይጣን እሱ የሚገዛውን ዓለም ያዋቀረው የሰዎችን ትኩረት እንዲስብና እንዲከፋፍል አድርጎ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዲህ ያለ ሁኔታ ከነበረ ዛሬማ ምን ያህል የከፋ ይሆን! (2 ጢሞ. 4:10) በመሆኑም በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ምክር መከተል ይኖርብናል። w15 10/15 3:7, 8
ሐሙስ፣ ጥር 19
ምን ማድረግ እንዳለብን መመሪያ ይስጠን።—መሳ. 13:8
ማኑሄና ሚስቱ ወንድ ልጅ ሊወልዱ ነው! ማኑሄ በጣም እንደተደሰተ ጥያቄ የለውም፤ ሆኖም በጫንቃው ላይ የወደቀው ኃላፊነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ተገንዝቧል። በክፋት በተሞላው ብሔር ውስጥ እሱና ባለቤቱ ልጃቸውን ሲያሳድጉ የይሖዋ አምላኪ እንዲሆን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው? ማኑሄ “እባክህ ልከኸው የነበረው ያ የእውነተኛው አምላክ ሰው [መልአኩ] እንደገና ወደ እኛ ይምጣና የሚወለደውን ልጅ በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለብን መመሪያ ይስጠን” በማለት ይሖዋን ተማጸነ። (መሳ. 13:1-8) ወላጅ ከሆናችሁ ማኑሄ እንዲህ ያለ ልመና ያቀረበው ለምን እንደሆነ መረዳት አይከብዳችሁም። እናንተም ልጃችሁ ይሖዋን እንዲያውቅና እንዲወድ የመርዳት ከባድ ኃላፊነት ተጥሎባችኋል። (ምሳሌ 1:8) ክርስቲያን ወላጆች ይህን ግብ ለመምታት፣ ትርጉም ያለው እንዲሁም ልጆቻቸው ይሖዋን ይበልጥ እያወቁትና እየወደዱት እንዲሄዱ የሚረዳ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም እንዲኖራቸው ሊያደርጉ ይገባል። እርግጥ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ እንዲቀረጽ በየሳምንቱ የቤተሰብ ጥናት ማድረግ ብቻ በቂ እንዳልሆነ መገንዘብ ይኖርባችኋል። (ዘዳ. 6:6-9) በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ እውነትን ለመቅረጽ ጥረት ስታደርጉ የሚያጋጥሟችሁን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት ትችላላችሁ? w15 11/15 1:1, 2
ዓርብ፣ ጥር 20
ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ ይኸውላችሁ!—ዮሐ. 1:47
ወላጆች እንደ ኢየሱስ ልብ ማንበብ የማትችሉ ቢሆንም በአምላክ እርዳታ፣ በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ ያለውን ነገር ማስተዋል ትችላላችሁ። አስተዋይ በመሆን በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙት ልጆቻችሁ ያላቸውን መልካም ጎን ለመመልከት ትጥራላችሁ? ማንም ቢሆን “ችግር ፈጣሪ” የሚል ስም እንዲሰጠው አይፈልግም። እናንተም ስለ ልጃችሁ ያላችሁ አመለካከትና የምትናገሩት ነገር ልጁን እንደ “ዓመፀኛ” ወይም “አስቸጋሪ” አድርጋችሁ እንደምትመለከቱት የሚያሳይ እንዳይሆን ተጠንቀቁ። ልጃችሁ ጥፋት ቢሠራም እንኳ ያሉትን መልካም ባሕርያት እንደምታውቁና ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ከልቡ የሚፈልግ መሆኑን እንደምትገነዘቡ ንገሩት። ለውጥና መሻሻል እያደረገ እንዳለ የሚጠቁም ነገር ስትመለከቱ አመስግኑት። የሚቻል ከሆነ ተጨማሪ ኃላፊነት በመስጠት ያሉትን መልካም ባሕርያት እንዲያዳብር እርዱት። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በተያያዘ እንዲህ አድርጓል። ኢየሱስ ከናትናኤል ጋር ከተገናኘ ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በኋላ ናትናኤልን ሐዋርያ አድርጎ የመረጠው ሲሆን እሱም ቀናተኛ ክርስቲያን መሆኑን አስመሥክሯል። (ሉቃስ 6:13, 14፤ ሥራ 1:13, 14) ልጃችሁን ማመስገናችሁና ማበረታታታችሁ ልጁ የሚጠበቅበትን የማያሟላ ሰው እንዳልሆነ እንዲገነዘብ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ሊጠቀምበት የሚችል ብቁ ክርስቲያን እንደሆነ እንዲሰማው ያደርጋል። w15 11/15 2:15, 16
ቅዳሜ፣ ጥር 21
ቀንና ሌሊት [ለአምላክ] ቅዱስ አገልግሎት እያቀረቡለት ነው።—ራእይ 7:15
የመጨረሻዎቹ ቀናት በ1914 ሲጀምሩ በዓለም ዙሪያ የነበሩት የይሖዋ አገልጋዮች በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ ነበሩ። አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ቅቡዓን ቀሪዎች ለባልንጀሮቻቸው ባላቸው ፍቅር ተነሳስተውና በአምላክ መንፈስ እየተመሩ የመንግሥቱን ስብከት ሥራ በጽናት አከናውነዋል። በመሆኑም ምድራዊ ተስፋ ያለው እጅግ ብዙ ሕዝብ እየተሰበሰበ ነው። በአሁኑ ጊዜ በመላው ምድር ከ115,400 በላይ በሚሆኑ ጉባኤዎች ውስጥ የታቀፉ ከ8,000,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ያሉ ሲሆን ቁጥራችንም መጨመሩን ቀጥሏል። ለምሳሌ በ2014 የአገልግሎት ዓመት ከ275,500 የሚበልጡ ሰዎች ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል፤ ይህም በአማካይ በየሳምንቱ 5,300 የሚያህሉ ሰዎች ይጠመቃሉ ማለት ነው። በዛሬው ጊዜ የምናየው አስደናቂ እድገት የተገኘው በአምላክ ላይ እምነት ስላለን እንዲሁም ይሖዋ በመንፈሱ መሪነት በተአምር ያስጻፈውን መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ ስለምንቀበል ነው። (1 ተሰ. 2:13) “የዚህ ሥርዓት አምላክ” የሆነው ሰይጣን የይሖዋን ሕዝብ የሚጠላና የሚቃወም ቢሆንም እንኳ መንፈሳዊ ብልጽግና ማግኘታችን አስገራሚ ነው።—2 ቆሮ. 4:4፤ w15 11/15 4:12, 14, 16
እሁድ፣ ጥር 22
የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።—ኢሳ. 40:8
የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን በሺዎች የሚቆጠሩ የቅዱሳን መጻሕፍት ቁርጥራጮችን፣ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ቅጂዎችንና ትርጉሞችን አነጻጽረዋል፤ እንዲሁም በከፍተኛ ጥንቃቄ አጥንተዋል። ያከናወኑት ጥናት ከጥቂቶች በቀር ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ትክክለኛ መሆናቸውን አረጋግጧል። ምሁራኑ እርግጠኛ ያልሆኑባቸው ጥቂት ጥቅሶች ቢኖሩም እነዚህ ጥቅሶች አጠቃላዩን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት አይለውጡትም። በጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ላይ የተደረጉት ጥናቶች፣ ዛሬ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ በመንፈሱ መሪነት መጀመሪያ ያሰፈረውን ሐሳብ የያዘ መሆኑን ቅን ልብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንዲያምኑ አድርገዋቸዋል። ጠላቶች የአምላክን ቃል ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤ ያም ቢሆን ይሖዋ፣ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ በስፋት በመተርጎም ረገድ የአምላክ ቃል ተወዳዳሪ የሌለው መጽሐፍ እንዲሆን አድርጓል። ብዙዎች በአምላክ በማያምኑበት ዘመን እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ በብዛት ከተሸጡ መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ ይዟል፤ እንዲሁም በከፊልም ሆነ በሙሉ ከ2,800 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል። እርግጥ ነው፣ ግልጽ ወይም እምነት የሚጣልበት በመሆን ረገድ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የሚጎድላቸው ነገር ቢኖርም ተስፋ የሚሰጠውንና ስለ መዳን የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና መልእክት የትኛውንም ትርጉም በማንበብ መረዳት ይቻላል። w15 12/15 1:13, 14
ሰኞ፣ ጥር 23
ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል።—ምሳሌ 12:18
ቃላት ሰዎችን የመጉዳት አሊያም የመፈወስ ኃይል አላቸው። በሰይጣን ዓለም ውስጥ በቃላት ተጠቅሞ ሌሎችን መጉዳት የተለመደ ነው። የመዝናኛው ዓለም፣ ሰዎች “ምላሳቸውን እንደ ሰይፍ [እንዲስሉ]” እንዲሁም “መርዘኛ ቃላቸውን እንደ ቀስት [እንዲያነጣጥሩ]” ያበረታታል። (መዝ. 64:3) አንድ ክርስቲያን እንዲህ ካለው ጎጂ ልማድ መራቅ ይኖርበታል። ‘መርዘኛ ቃላት’ ተብለው ሊፈረጁ ከሚችሉት አነጋገሮች አንዱ ሽሙጥ ነው፤ ሽሙጥ ሌሎችን ለማቃለል ወይም ለመዝለፍ ተብሎ የሚሰነዘር ስሜትን የሚጎዳ አነጋገር ነው። ብዙውን ጊዜ ለቀልድ ተብሎ የሚነገር ቢሆንም ሳይታሰብ መልኩን ሊቀይርና ሌሎችን የሚያንኳስስ ወይም ስድብ አዘል መልእክት የሚያስተላልፍ ሊሆን ይችላል። መርዘኛ የሆነ ሽሙጥ፣ ስድብ በመሆኑ ክርስቲያኖች ‘ሊያስወግዱት’ ይገባል። ቀልድ ጨዋታን ሊያጣፍጥ ቢችልም ሌሎችን በነገር በመውጋትና ስሜታቸውን የሚጎዳ ወይም እነሱን የሚያንቋሽሽ አሽሙር በመናገር ለማሳቅ ከመሞከር መቆጠብ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይመክረናል፦ “እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል መልካም ቃል ብቻ እንጂ የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ።”—ኤፌ. 4:29, 31፤ w15 12/15 3:10
ማክሰኞ፣ ጥር 24
ከእነዚህ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ከራቃችሁ መልካም ይሆንላችኋል። ጤና ይስጣችሁ!—ሥራ 15:29
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል ለጉባኤዎች በጻፈው ደብዳቤ መጨረሻ ላይ የሰፈረው ይህ የመሰናበቻ ሐሳብ “ጠንካራ ሁኑ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። እኛም ‘ጤናማ’ እና ጠንካራ ሆነን ታላቁን አምላካችንን ማገልገል እንደምንፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። የምንኖረው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ከመሆኑም ሌላ ሁላችንም ፍጹማን አይደለንም፤ በመሆኑም ሕመም ማናችንም ልናመልጠው የማንችለው ነገር ነው። በአሁኑ ወቅት ከሕመማችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንደምንድን አንጠብቅም። ይሁንና ራእይ 22:1, 2 ፍጹም ጤና የምናገኝበት ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። ሐዋርያው ዮሐንስ “የሕይወት ውኃ ወንዝ” እና “ሕዝቦችን ለመፈወስ የሚያገለግሉ” ቅጠሎች ያሏቸውን “የሕይወት ዛፎች” በራእይ ተመልክቶ ነበር። ይህ በዛሬው ጊዜም ሆነ ወደፊት የሚኖርን ከዕፀዋት የተዘጋጀ መድኃኒት አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ለመስጠት በኢየሱስ በኩል ያደረገውን ዝግጅት ያመለክታል፤ በእርግጥም ይህ በጉጉት የምንጠብቀው ነገር ነው።—ኢሳ. 35:5, 6፤ w15 12/15 4:17, 18
ረቡዕ፣ ጥር 25
አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን።—ዘካ. 8:23
ይሖዋ የምንኖርበትን ዘመን አስመልክቶ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል፦ “በዚያን ጊዜ ከብሔራት ቋንቋዎች ሁሉ የተውጣጡ አሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ አጥብቀው በመያዝ ‘አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን’ ይላሉ።” (ዘካ. 8:23) በዚህ ምሳሌያዊ አገላለጽ ላይ እንደተጠቀሱት አሥር ሰዎች ሁሉ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም “የአንድን አይሁዳዊ ልብስ አጥብቀው” ይዘዋል። ይሖዋ ቅቡዓኑን እየባረካቸው እንደሆነ ስለሚያውቁ በመንፈስ ከተቀቡት ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት ጋር መተባበራቸው ያኮራቸዋል። (ገላ. 6:16) እንደ ነቢዩ ዘካርያስ ሁሉ ኢየሱስም በአምላክ ሕዝቦች መካከል የሚኖረውን አስደሳች አንድነት አጉልቷል። ተከታዮቹ “ትንሽ መንጋ” እና “ሌሎች በጎች” ተብለው በሁለት ቡድኖች እንደሚከፈሉ ገልጿል፤ ያም ቢሆን ሁለቱም ‘በአንድ እረኛ’ የሚመሩ “አንድ መንጋ” እንደሚሆኑ ተናግሯል።—ሉቃስ 12:32፤ ዮሐ. 10:16፤ w16.01 4:1, 2
ሐሙስ፣ ጥር 26
[እነዚህን ነገሮች] ማሰባችሁን አታቋርጡ።—ፊልጵ. 4:8
እኛ ክርስቲያኖች መንፈሳዊነታችንን መጠበቅ ያስፈልገናል። የምንኖረው ሰይጣን ዲያብሎስ በሚቆጣጠረው ዓለም ውስጥ ከመሆኑም ሌላ ፍጹማን አይደለንም፤ በመሆኑም የዓለምን የተሳሳተ አስተሳሰብና ምግባር በቀላሉ ልንኮርጅ እንችላለን። የዓለም መንፈስ፣ ወደማንፈልገው አቅጣጫ ሊወስደን ከሚታገል ወንዝ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ወንዙ ይዞን እንዳይሄድ ከፈለግን ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ ለመዋኘት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለብን። በተመሳሳይም የሰይጣን ዓለም መንፈስ እንዳይወስደን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ምሥራቹን ስንሰብክ እምነታችንን በሚሸረሽሩ ሐሳቦች ላይ ሳይሆን አስፈላጊና ጠቃሚ በሆኑ መንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ እናተኩራለን። የስብከቱ ሥራ አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎችና ፍቅር የሚንጸባረቅባቸውን መሥፈርቶቹን እንድናስታውስ ስለሚረዳን እምነታችንን ያጠናክርልናል። መንፈሳዊ የጦር ትጥቃችን እንዳይላላም ይረዳናል። (ኤፌ. 6:14-17) በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችን መጠመዳችን በራሳችን ችግሮች ላይ ከልክ በላይ እንዳናተኩር ይረዳናል፤ ይህ ደግሞ ጥበቃ ይሆነናል። w16.01 5:12, 13
ዓርብ፣ ጥር 27
ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል።—ሩት 1:16
ሩት ለይሖዋ ፍቅር እንደነበራት ልብ በል። ሩት በይሖዋ ክንፎች ሥር ለመጠለል በመፈለጓ ከጊዜ በኋላ ቦዔዝ አድንቋታል። (ሩት 2:12) ቦዔዝ የተጠቀመበት አገላለጽ፣ ጥላ ከለላ ለማግኘት በወላጆቿ ክንፎች ሥር የምትሸሸግን ጫጩት እንድናስብ ያደርገን ይሆናል። (መዝ. 36:7፤ 91:1-4) ይሖዋ ለሩት እንደነዚህ ወላጆች ሆኖላታል። ስላሳየችው እምነት ወሮታዋን የከፈላት ሲሆን በውሳኔዋ እንድትቆጭ የሚያደርግ ምንም ነገር አላጋጠማትም። በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ስለ ይሖዋ ቢያውቁም እሱን መጠጊያቸው ለማድረግ ያመነታሉ። ራሳቸውን ወስነው በመጠመቅ እሱን ከማገልገል ወደኋላ ይላሉ። ራስህን ለይሖዋ ለመወሰን የምታመነታ ከሆነ ምክንያትህ ምን እንደሆነ ቆም ብለህ አስበህበት ታውቃለህ? ማንኛውም ፍጡር የሚያመልከው አካል መኖሩ አይቀርም። (ኢያሱ 24:15) ታዲያ ሊመለክ የሚገባውን ብቸኛ አምላክ ለምን መጠጊያህ አታደርገውም? ለይሖዋ ራስህን መወሰንህ፣ በእሱ ላይ እምነት እንዳለህ ማሳየት የምትችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ነው። ይሖዋ ከውሳኔህ ጋር ተስማምተህ መኖር እንድትችልና የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንድትወጣ ይረዳሃል። አምላክ ለሩት እንዲህ አድርጎላታል። w16.02 2:6, 7
ቅዳሜ፣ ጥር 28
እባክህ አሁን አንድ ጊዜ ብቻ በጦር ወግቼ ከመሬት ጋር ላጣብቀው፤ መድገም አያስፈልገኝም።—1 ሳሙ. 26:8
አቢሳ ወደ ሳኦል የጦር ሰፈር በገባበት ወቅት ታማኝነት ያሳየው ለተገቢው አካል አልነበረም። አቢሳ ለዳዊት ያለው ታማኝነት ንጉሥ ሳኦልን ለመግደል እንዲነሳሳ አድርጎት ነበር፤ ዳዊት ግን “ይሖዋ በቀባው ላይ” እጅ ማንሳት ተገቢ እንዳልሆነ ስለተገነዘበ ይህን እንዳያደርግ አቢሳን ከልክሎታል። (1 ሳሙ. 26:9-11) ከዚህ ዘገባ የምናገኘው አንድ ጠቃሚ ትምህርት አለ፦ ለተለያዩ አካላት ታማኝ መሆናችን ተገቢ ቢሆንም በዋነኝነት ታማኝ መሆን የሚገባን ለማን እንደሆነ ለመወሰን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራት ይኖርብናል። ታማኝነት የሚመነጨው ከልብ ነው፤ የሰው ልብ ግን ከዳተኛ ነው። (ኤር. 17:9) በመሆኑም ለአምላክ ታማኝ የሆነ አንድ ሰው፣ የቅርብ ጓደኛው ወይም ዘመዱ መጥፎ ድርጊት እየፈጸመ ቢሆንም ለእሱ ታማኝ መሆን እንዳለበት ሊሰማው ይችላል። ይሁንና እውነትን የተወው በጣም የምንቀርበው ሰው ቢሆንም እንኳ ከማንም በላይ ታማኝ መሆን ያለብን ለይሖዋ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል።—ማቴ. 22:37፤ w16.02 4:5, 6
እሁድ፣ ጥር 29
ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ [አረጋግጡ]።—ሮም 12:2
በሮም የሚገኙ ክርስቲያኖች ቀድሞውኑ የተቀበሉትን ነገር ማረጋገጥ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንመልከት። ጢሞቴዎስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። እናቱና አያቱ “ከጨቅላነት” ዕድሜው አንስቶ አስተምረውታል። ያም ቢሆን ጳውሎስ “በተማርካቸውና አምነህ በተቀበልካቸው ነገሮች ጸንተህ ኑር” በማለት አሳስቦት ነበር። (2 ጢሞ. 3:14, 15) አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ‘መቀበል’ ተብሎ የተተረጎመው ቃል በበኩረ ጽሑፉ “አንድ ነገር እውነት መሆኑን ማመንና እርግጠኛ መሆን” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ጢሞቴዎስ እውነትን የራሱ አድርጓል። እንዲህ ያደረገው እናቱና አያቱ ስላስገደዱት ሳይሆን በተማረው ነገር ላይ በሚገባ ካሰበበት በኋላ አምኖ ስለተቀበለው ነው። (ሮም 12:1) በተመሳሳይ አንተም ትጋት የተሞላበት የግል ጥናት ማድረግህ ለሚቀርቡልህ ጥያቄዎች መልስ እንድትሰጥ፣ ማንኛውንም ጥርጣሬ እንድታስወግድ እንዲሁም እምነትህን እንድታጠናክር ሊረዳህ ይችላል።—ሥራ 17:11፤ w16.03 2:3, 4, 7
ሰኞ፣ ጥር 30
በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም የመሄድ ልማድ ነበራቸው።—ሉቃስ 2:41
በጥንት ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን ዓመታዊ በዓል በሚከበርበት ወቅት ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ተገኝተው ይሖዋን ሲያወድሱ ይታይህ። ለጉዞ መዘጋጀት፣ በጉዞ ወቅት እርስ በርስ መረዳዳት ከዚያም ቤተ መቅደስ ውስጥ ይሖዋን በአንድነት ማምለክ ነበረባቸው። ይህ ሁሉ ትብብር የሚጠይቅ ነገር ነው። እኛም ወደ አዲሱ ዓለም በምናደርገው ጉዞ ላይ እርስ በርስ መስማማትና መተባበር ያስፈልገናል። እስቲ ስለሚጠብቁን በረከቶች አስብ! በአሁኑ ጊዜ እንኳ በዓለም ውስጥ ከሚታየው መከፋፈልና ግራ መጋባት ተገላግለናል። ኢሳይያስና ሚክያስ የተናገሩት ትንቢት ሲፈጸም እየተመለከትን ነው፤ የአምላክ ሕዝቦች አንድ ላይ ሆነው “ወደ ይሖዋ ተራራ” እየወጡ ነው። (ኢሳ. 2:2-4፤ ሚክ. 4:2-4) በእርግጥም “በዘመኑ መጨረሻ” ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ እጅግ የላቀ ነው። ወደፊት ደግሞ የሰው ዘር በሙሉ እርስ በርስ ተስማምቶና ተባብሮ ሲኖር የምናገኘው ደስታና እርካታ ምንኛ ታላቅ ይሆናል! w16.03 3:16, 17
ማክሰኞ፣ ጥር 31
ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው።—መክ. 3:1
አንዳንድ ሽማግሌዎች ጊዜ መድበው ሌሎችን ማሠልጠን ከባድ ይሆንባቸዋል። እንዲህ ብለው ያስቡ ይሆናል፦ ‘ሌሎችን ማሠልጠን አስፈላጊ ቢሆንም ጊዜ ከማይሰጡ ሌሎች የጉባኤ ሥራዎች አንጻር ሲታይ ያን ያህል አጣዳፊ አይደለም። ሥልጠናውን በሌላ ጊዜ ባደርገው ጉባኤው ላይ የሚያመጣው ጉዳት የለም።’ የአንድን ሽማግሌ ጊዜ የሚፈልጉ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው እውነት ቢሆንም ሥልጠናውን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ የጉባኤውን መንፈሳዊ ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል። ሽማግሌዎች ሊያከናውኗቸው የሚገቡ በርካታ አጣዳፊ ጉዳዮች አሉ። ሆኖም ሽማግሌዎች ሥልጠናውን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፋቸውን ከቀጠሉ ይዋል ይደር እንጂ ጉባኤው አስፈላጊ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ብቃት ያላቸው ወንድሞችን በማጣት መቸገሩ አይቀርም። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሥልጠና መስጠት ‘ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም’ የሚለውን አስተሳሰብ ማስወገድ ይኖርብናል። ልምድ የሌላቸውን ወንድሞች ለማሠልጠን ጊዜያቸውን መሥዋዕት የሚያደርጉና አርቆ አሳቢ የሆኑ ሽማግሌዎች ጥበበኛ መጋቢዎች ከመሆናቸውም በላይ ለጉባኤው በረከት ናቸው።—1 ጴጥ. 4:10፤ w15 4/15 1:4, 6, 7