የካቲት
ረቡዕ፣ የካቲት 1
ወደ አምላክ ቅረቡ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። —ያዕ. 4:8
ራስህን ወስነህ የተጠመቅህ የይሖዋ ምሥክር ነህ? ከሆነ አንድ ውድ ነገር አለህ፤ ይህም በግለሰብ ደረጃ ከአምላክ ጋር የመሠረትከው ወዳጅነት ነው። ይሁንና የሰይጣን ዓለም ብቻ ሳይሆን ፍጹም ያልሆነው ሥጋችንም በዚህ ወዳጅነት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። እንዲህ ያለው ፈታኝ ሁኔታ የሚያጋጥማቸው ሁሉም ክርስቲያኖች ናቸው። እንግዲያው ከይሖዋ ጋር ያለን ግንኙነት በተቻለ መጠን ጠንካራ መሆን አለበት። አንተስ ከይሖዋ ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ያህል ጠንካራ ነው? ይበልጥ ልታጠናክረው ትፈልጋለህ? በያዕቆብ 4:8 ላይ ያለው የዕለቱ ጥቅስ ሐሳብ ይህን ማድረግ የምንችልበትን መንገድ ይጠቁመናል። ይህ ጥቅስ ከሁለቱም ወገኖች የሚጠበቅ ነገር መኖሩን እንደሚጠቁም ልብ በል። ወደ አምላክ ለመቅረብ እርምጃ ስንወስድ እሱም በበኩሉ ወደ እኛ ይቀርባል። እንዲህ ያለውን እርምጃ በተደጋጋሚ ስንወስድ ይሖዋ ይበልጥ እውን ይሆንልናል፤ ከእሱ ጋር ያለን ግንኙነትም የበለጠ እየተጠናከረ ስለሚሄድ ኢየሱስ “የላከኝ በእውን ያለ ነው፤ . . . አውቀዋለሁ” ብሎ ሲናገር የነበረው ዓይነት የመተማመን ስሜት ይኖረናል።—ዮሐ. 7:28, 29፤ w15 4/15 3:1, 2
ሐሙስ፣ የካቲት 2
መከራን በጽናት ተቋቋሙ። ሳትታክቱ ጸልዩ።—ሮም 12:12
አንድ የቤተሰብህ አባል ተወገደ እንበል። ከተወገዱ ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ምን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ተምረሃል። (1 ቆሮ. 5:11፤ 2 ዮሐ. 10) ይሁንና ግለሰቡ እንዲወገድ የተደረገውን ውሳኔ መደገፍ በጣም ከባድ አልፎ ተርፎም የማይቻል የሚመስልበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ታዲያ ውገዳን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መመሪያ በማክበር ረገድ ጽኑ አቋም ለመያዝ የሚያስፈልግህን ጥንካሬ በሰማይ ያለው አባትህ እንደሚሰጥህ መተማመን ትችላለህ? ይህ ሁኔታ ወደ ይሖዋ በመቅረብ ከእሱ ጋር ያለህን ዝምድና ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል አጋጣሚ እንደሆነ ይሰማሃል? ይህ ሲባል ታዲያ የቤተሰባችንን አባላት ከልብ ልንወዳቸው አይገባም ማለት ነው? በፍጹም! ሆኖም ከማንም በላይ ልንወደው የሚገባው ይሖዋን ነው። (ማቴ. 22:37, 38) የቤተሰባችን አባላት በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን እያገለገሉ ሆኑም አልሆኑ የሚጠቅማቸው ይህን ማድረጋችን ነው። የተወገደው የቤተሰብህ አባል በተከተለው ጎዳና የተነሳ ስለ እሱ በጣም የምትጨነቅ ከሆነ የውስጥህን አውጥተህ ለይሖዋ በጸሎት ንገረው።—ፊልጵ. 4:6, 7፤ w15 4/15 4:14, 16
ዓርብ፣ የካቲት 3
ባሳያችሁት ጽናትና እምነት የተነሳ በአምላክ ጉባኤዎች መካከል እኛ ራሳችን ስለ እናንተ በኩራት እንናገራለን።—2 ተሰ. 1:4
ሌሎች ባከናወኑት ነገር መደሰት ሌላው ቀርቶ በተወሰነ መጠን በራሳችን መኩራት እንኳ ስህተት አይደለም። በቤተሰባችን፣ በባሕላችን ወይም ባደግንበት አካባቢ ማፈር አይኖርብንም። (ሥራ 21:39) በሌላ በኩል ግን ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነትም ሆነ ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ቀስ ቀስ የሚያበላሽ ኩራት አለ። እንዲህ ያለው ኩራት አስፈላጊ የሆነ ምክር ሲሰጠን በትሕትና ከመቀበል ይልቅ ቅር እንድንሰኝ ወይም ምክሩን እንዳንቀበል ሊያደርገን ይችላል። (መዝ. 141:5) ይህ ዓይነቱ ኩራት “ራስን ከሚገባው በላይ ከፍ አድርጎ መመልከት” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል፤ ወይም ደግሞ “ከሌሎች የተሻሉ እንደሆኑ የሚሰማቸው ሰዎች (ብዙውን ጊዜ እንዲህ ለማሰብ የሚያበቃ ምክንያት ባይኖራቸውም) የሚያሳዩት የትዕቢት ዝንባሌ” ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። ይሖዋ ከልክ ያለፈ ኩራትን ይጠላል። (ሕዝ. 33:28፤ አሞጽ 6:8) ሰይጣን ግን እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የእሱን የእብሪት ዝንባሌ የሚያንጸባርቅ በመሆኑ ሰዎች ሲታበዩ ማየት ያስደስተዋል። እንደ ናምሩድ፣ ፈርዖንና አቢሴሎም ያሉት ሰዎች በመታበይ ተገቢ ያልሆነ ኩራት ሲያሳዩ ምንኛ ፈንጥዞ ይሆን!—ዘፍ. 10:8, 9፤ ዘፀ. 5:1, 2፤ 2 ሳሙ. 15:4-6፤ w15 5/15 2:5, 6
ቅዳሜ፣ የካቲት 4
አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታሟላለህ።—መዝ. 145:16
‘የአምላክ ኃይል የሆነው ክርስቶስ’ የአብን ምሳሌ በመከተል እጆቹን ዘርግቶ የተከታዮቹን ፍላጎት ብዙ ጊዜ አሟልቷል። (1 ቆሮ. 1:24) ይህን ያደረገው ኃይሉን ለማሳየት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ተአምራት እንዲፈጽም ያነሳሳው ለሌሎች ያለው ልባዊ አሳቢነት ነው። ማቴዎስ 14:14-21ን እንመልከት። ደቀ መዛሙርቱ በቂ ምግብ አለመኖሩን ለኢየሱስ ነገሩት። ይህን ያደረጉት እነሱ ራሳቸው ስለራባቸው ሊሆን ይችላል፤ በተጨማሪም ኢየሱስን ተከትለው ከየከተማዎቹ በእግር የመጡት ሰዎች ርቧቸውና ደክሟቸው ስለሚሆን ይህ ሁኔታ ደቀ መዛሙርቱን አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 14:13) ታዲያ ኢየሱስ ምን አደረገ? በአምስት ዳቦና በሁለት ዓሣ፣ ከሴቶችና ከልጆች ሌላ 5,000 ወንዶችን መገበ! መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም በልተው ጠገቡ” ይላል። ይህም የተትረፈረፈ ምግብ እንደነበር ይጠቁማል። ኢየሱስ በደግነት ለሕዝቡ ያቀረበው ምግብ እንዲያው ቅምሻ ብቻ ሳይሆን ወደ ቤታቸው ለሚያደርጉት ረጅም ጉዞ ኃይል የሚሰጣቸው ነበር። (ሉቃስ 9:10-17) የተረፈውም ምግብ 12 ቅርጫት ሙሉ ሆነ! w15 6/15 1:8, 9
እሁድ፣ የካቲት 5
የሰው ልጆች ብልሹ ምግባርን [ያስፋፋሉ]።—መዝ. 12:8
የብልግና አኗኗር በጣም በመስፋፋቱ ‘ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን ጠብቆ መኖር ይቻላል?’ የሚለው ነገር ያሳስብህ ይሆናል። አዎ፣ በይሖዋ እርዳታ ይቻላል። ንጹሕ ሆነን ለመኖር ግን በመጀመሪያ የብልግና ምኞቶችን ማስወገድ ይኖርብናል። መንጠቆ ላይ የሚንጠለጠለው ምግብ ዓሣዎችን እንደሚማርክ ሁሉ አንድ ክርስቲያንም የብልግና ሐሳቦችንና አስነዋሪ ምኞቶችን ወዲያውኑ ከአእምሮው ካላስወገደ በምኞቱ ሊማረክና ሊታለል ይችላል። እንዲህ ያሉት ምኞቶች ኃጢአተኛ የሆነውን ሥጋችንን በመማረክ ወደ ሥነ ምግባራዊ ብልግና ሊመሩን ይችላሉ። ውሎ አድሮም የኃጢአት መስህብ እየበረታ ስለሚሄድ ርኩስ የሆኑ ምኞቶች በውስጣችን ይፀነሳሉ። አንድ የይሖዋ አገልጋይም እንኳ እዚህ ደረጃ ከደረሰ፣ አጋጣሚውን ሲያገኝ ምኞቱን ሊፈጽም ይችላል። አዎ፣ “ምኞት . . . ኃጢአትን ትወልዳለች።” (ያዕ. 1:14, 15) መጥፎ ምኞት ከባድ ኃጢአት ወደ መፈጸም ሊያመራ የሚችል መሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው። ይሁንና ርኩስ የሆኑ ምኞቶች ሥር እንዳይሰዱ ከተከላከልን ከሥነ ምግባር ብልግና እንዲሁም ብልግና ከሚያስከትላቸው አስከፊ መዘዞች መራቅ እንደምንችል ማወቁ ምንኛ የሚያበረታታ ነው።—ገላ. 5:16፤ w15 6/15 3:1-3
ሰኞ፣ የካቲት 6
ፈቃድህ . . . በምድርም ላይ ይፈጸም።—ማቴ. 6:10
ከዛሬ 6,000 ዓመታት ገደማ በፊት የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ፍጹም በሆነ ሁኔታ ተፈጽሞ ነበር። ይሖዋ፣ ለሰዎች ሁሉን ነገር ካመቻቸላቸው በኋላ ሁኔታውን ተመልክቶ “እጅግ መልካም ነበር” ያለው ለዚህ ነው። (ዘፍ. 1:31) ይሁንና ሰይጣን ዓመፀ፤ ከዚያን ጊዜ ወዲህ የአምላክን ፈቃድ በምድር ላይ ያደረጉት ሰዎች ቁጥር በአንጻራዊ ሁኔታ ጥቂት ነው። በዛሬው ጊዜ ግን ስምንት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም ከመጸለይ አልፈው ከዚህ ጸሎት ጋር ተስማምተው ለመኖር ጥረት እያደረጉ ነው፤ በእርግጥም በዚህ ዘመን በመኖራችን ታድለናል። እነዚህ ሰዎች በአኗኗራቸው እንዲሁም ደቀ መዛሙርት በማፍራቱ ሥራ በቅንዓት በመካፈል ከጸሎታቸው ጋር በሚስማማ መንገድ እንደሚኖሩ ያሳያሉ። የአምላክ መንግሥት ጠላቶች ከምድር እስኪወገዱ ድረስ፣ የአምላክ ፈቃድ እንዲፈጸም መጸለያችንን እንቀጥላለን። ከዚያም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት ተነስተው ገነት በሆነች ምድር ላይ በሚኖሩበት ጊዜ የአምላክ ፈቃድ ይበልጥ በተሟላ መንገድ ሲፈጸም እንመለከታለን። (ዮሐ. 5:28, 29) በሕይወት ኖረን፣ በሞት ያጣናቸውን የምንወዳቸውን ሰዎች መቀበል መቻል እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው! w15 6/15 4:15, 17
ማክሰኞ፣ የካቲት 7
እግሬ የሚያርፍበትንም ስፍራ አከብራለሁ።—ኢሳ. 60:13
“መንፈሳዊ ገነት” የሚለው ሐሳብ ከምንጠቀምባቸው ቲኦክራሲያዊ አገላለጾች አንዱ ሆኗል። ይህ አገላለጽ ከአምላክና ከወንድሞቻችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን የሚያደርገውን ልዩ የሆነና በመንፈሳዊ የበለጸገ ሁኔታ ያመለክታል። እርግጥ ነው፣ “መንፈሳዊ ገነት” እና “መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ” የሚሉት ሐሳቦች አንድ እንደሆኑ አድርገን ልንደመድም አይገባም። መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ የሚባለው አምላክ ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዘ ያደረገው ዝግጅት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ መንፈሳዊው ገነት አምላክ ሞገሱን የሚያሳያቸውን እንዲሁም በመንፈሳዊው ቤተ መቅደሱ እሱን የሚያገለግሉትን ሰዎች በግልጽ ለመለየት ይረዳል። (ሚል. 3:18) ከ1919 ጀምሮ ይሖዋ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች በምድር ላይ ያለውን መንፈሳዊ ገነት በማልማት፣ በማጠናከርና በማስፋፋት ከእሱ ጋር አብረው እንዲሠሩ መፍቀዱን ማወቃችን ምንኛ የሚያስደስት ነው! በዚህ አስደናቂ ሥራ የበኩልህን ድርሻ እያበረከትክ እንዳለ ይሰማሃል? እንዲሁም የይሖዋን ‘የእግር ማሳረፊያ’ በማስከበር ረገድ ከእሱ ጋር አብረህ መሥራትህን ለመቀጠል ትነሳሳለህ? w15 7/15 1:10, 11
ረቡዕ፣ የካቲት 8
በአንተ አማካኝነት በፊታቸው ራሴን [እቀድሳለሁ]።—ሕዝ. 38:16
ጎግ፣ ቀሪዎቹ የ144,000 አባላት ወደ ሰማይ ከመወሰዳቸው ትንሽ ቀደም ብሎ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራል። ታዲያ ይህ ጥቃት ምን ያስከትላል? በምድር ላይ ያሉት የአምላክ ሕዝቦች ለጥቃት የተጋለጡ ይመስላሉ። እነዚህ የአምላክ ሕዝቦች በንጉሥ ኢዮሳፍጥ ዘመን የተሰጠውን መመሪያ ይታዘዛሉ፦ “እናንተ ይህን ጦርነት መዋጋት አያስፈልጋችሁም። ቦታ ቦታችሁን ይዛችሁ ዝም ብላችሁ ቁሙ፤ ይሖዋ ለእናንተ ሲል የሚወስደውን የማዳን እርምጃ ተመልከቱ። ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፣ አትፍሩ ወይም አትሸበሩ።” (2 ዜና 20:17) በሰማይ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። ራእይ 17:14 ቅቡዓን በሙሉ ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ የአምላክ ሕዝቦች ጠላቶች ስለሚያደርጉት ነገር ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “እነዚህ ከበጉ ጋር ይዋጋሉ፤ ሆኖም በጉ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለሆነ ድል ይነሳቸዋል። ከእሱ ጋር ያሉት የተጠሩት፣ የተመረጡትና የታመኑትም ድል ያደርጋሉ።” ኢየሱስ በሰማይ ካሉት 144,000 ተባባሪ ገዢዎቹ ጋር በመሆን በምድር ላይ ያሉትን የአምላክ ሕዝቦች ይታደጋል። w15 7/15 2:16
ሐሙስ፣ የካቲት 9
ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው።—መክ. 3:1
ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለጋበዘን አምላክ አክብሮት እንዳለን ጨዋነት በሚንጸባረቅበት ምግባራችን፣ በአለባበሳችንና በአጋጌጣችን ልናሳይ ይገባል። አክብሮት ካለን ከተለመደው ወጣ ያሉ ነገሮችን ከማድረግም እንቆጠባለን። ይሖዋ አገልጋዮቹም ሆነ ተጋባዦች በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ነፃነት እንዲሰማቸው ይፈልጋል። በሌላ በኩል ግን ወደ አዳራሾቻችን የሚመጡ ሰዎች በአለባበሳቸው ግዴለሽ የሚሆኑ፣ ስብሰባ እየተካሄደ በስልክ መልእክት የሚጽፉ፣ የሚያወሩ፣ የሚበሉ፣ የሚጠጡ ወይም የመሳሰሉትን ነገሮች የሚያደርጉ ከሆነ ለስብሰባው አክብሮት እንደጎደላቸው እያሳዩ ነው። በተጨማሪም የመንግሥት አዳራሹ ልጆች የሚሯሯጡበት ወይም የሚጫወቱበት ስፍራ እንዳልሆነ ወላጆቻቸው ሊያስገነዝቧቸው ይገባል። ኢየሱስ በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ያካሂዱ በነበሩት ሰዎች በጣም ስለተቆጣ አባርሯቸዋል። (ዮሐ. 2:13-17) የመንግሥት አዳራሾቻችንም ንጹሕ አምልኮ የሚከናወንባቸውና መንፈሳዊ ትምህርት የምናገኝባቸው ቦታዎች ናቸው። በመሆኑም ንግድን ጨምሮ ከመንፈሳዊ ነገሮች ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ በዚያ ማከናወን አይኖርብንም።—ከነህምያ 13:7, 8 ጋር አወዳድር፤ w15 7/15 4:7, 8
ዓርብ፣ የካቲት 10
በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ።—2 ጢሞ. 3:1
መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ክፋት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚባባስ ይነግረናል። (2 ጢሞ. 3:13፤ ማቴ. 24:21፤ ራእይ 12:12) በመሆኑም ዓለም በአሁኑ ጊዜ መጥፎ ሁኔታ ላይ ቢሆንም ወደፊት ከዚህም እየከፋ እንደሚሄድ መጠበቅ እንችላለን። ይሁንና ‘ታላቁ መከራ’ ከመጀመሩ በፊት ነገሮች ምን ያህል የከፉ እንደሚሆኑ ትጠብቃለህ? (ራእይ 7:14) ለምሳሌ በየአገሩ ጦርነት እንደሚነሳ፣ ማንም ሰው የሚላስ የሚቀመስ እንደማያገኝና በየቤቱ የታመመ ሰው እንደሚኖር ትጠብቃለህ? ሁኔታዎች እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሱ ተጠራጣሪዎች እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ እንዳለ አምነው ለመቀበል ይገደዳሉ። ሆኖም ኢየሱስ አብዛኞቹ ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ከመጠመዳቸው የተነሳ እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ የመገኘቱን ምልክት ፈጽሞ ‘እንደማያስተውሉ’ ተናግሯል። (ማቴ. 24:37-39) ቅዱሳን መጻሕፍት፣ በመጨረሻዎቹ ቀናት በዓለም ላይ የሚኖረው ሁኔታ እጅግ መጥፎ ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች መጨረሻው መቅረቡን እንዲያምኑ የሚያደርግ ነገር እንደሚኖር አይገልጹም።—ሉቃስ 17:20፤ 2 ጴጥ. 3:3, 4፤ w15 8/15 2:6, 7
ቅዳሜ፣ የካቲት 11
ታማኝ ፍቅርህ ከሕይወት [ይሻላል]።—መዝ. 63:3
አምላክ ለሚያመጣው አዲስ ዓለም በመዘጋጀት ጊዜያችንን ማሳለፋችን በዛሬው ጊዜ የተሻለ ወይም ይበልጥ የሚያረካ ሕይወት እንዳናገኝ ያደርገን ይሆን? በጭራሽ! አንድ ሰው ይሖዋን ማገልገሉ ከምንም በላይ አርኪ የሆነ ሕይወት ለመምራት ያስችለዋል። አምላክን የምናገለግለው ታላቁን መከራ በሕይወት ለማለፍ ስንል ግዴታ ሆኖብን አይደለም። የተፈጠርነው ይሖዋን እያገለገልን እንድንኖር ከመሆኑም ሌላ ይህን ማድረጋችን የላቀ ደስታ ያስገኝልናል። የይሖዋን መመሪያ ማግኘትና ታማኝ ፍቅሩን መቅመስ ከእሱ ርቀን ከምንመራው ሕይወት እጅግ የተሻለ ነው። (መዝ. 63:1, 2) እርግጥ ነው፣ ይሖዋን በሙሉ ልብ ማገልገል የሚያስገኘውን መንፈሳዊ በረከት ለማጣጣም አዲሱን ዓለም መጠበቅ አያስፈልገንም፤ አሁንም ቢሆን በረከቱን ማጣጣም እንችላለን! በእርግጥም አንዳንዶቻችን ይህን በረከት ለብዙ አሥርተ ዓመታት ስናጭድ ቆይተናል፤ እንዲሁም ከዚህ የላቀ እርካታ የሚያስገኝ ሌላ የሕይወት መንገድ እንደሌለ ከተሞክሮ ተገንዝበናል።—መዝ. 1:1-3፤ ኢሳ. 58:13, 14፤ w15 8/15 3:16
እሁድ፣ የካቲት 12
የዳናችሁት በእምነት አማካኝነት . . . ነው።—ኤፌ. 2:8
እምነት በሰብዓዊ ዓይን ሲታይ የማይቻል የሚመስሉ ነገሮችን እንድናደርግ ያስችለናል። (ማቴ. 21:21, 22) ለምሳሌ ያህል፣ አብዛኞቻችን የቀድሞ ማንነታችንን ያውቁ የነበሩ ሰዎች ሊለዩን እስከማይችሉ ድረስ አስተሳሰባችንና ድርጊታችን በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል። ይሖዋ በእሱ በመታመን እነዚህን እርምጃዎች በመውሰዳችን ጥረታችንን ባርኮልናል። (ቆላ. 3:5-10) በእምነት ተነሳስተን ራሳችንን ለይሖዋ ከወሰንን በኋላ ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ችለናል፤ ይህ ደግሞ በራሳችን ኃይል ልናደርገው የምንችለው ነገር አይደለም። እምነታችን ምንጊዜም ጠንካሮች እንድንሆን ያደርገናል። ከሰው በላይ ኃይል ያለው ጠላታችን ዲያብሎስ የሚሰነዝርብንን ጥቃት መቋቋም የቻልነው በእምነት ነው። (ኤፌ. 6:16) በተጨማሪም በይሖዋ መታመናችን ፈታኝ በሆኑ ወቅቶች ከልክ በላይ በጭንቀት እንዳንዋጥ ይረዳናል። ይሖዋ በእምነት ተነሳስተን ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የምናስቀድም ከሆነ ቁሳዊ ፍላጎታችንን እንደሚያሟላልን ቃል ገብቷል። (ማቴ. 6:30-34) ከዚህ በላይ ደግሞ እምነታችን፣ የትኛውም ሰው በራሱ ጥረት ሊያገኝ የማይችለውን ስጦታ ይኸውም የዘላለም ሕይወት ያስገኝልናል።—ዮሐ. 3:16፤ w15 9/15 3:4, 5
ሰኞ፣ የካቲት 13
[አምላክ] አስቀድሞ ስለወደደን እኛም ፍቅር እናሳያለን።—1 ዮሐ. 4:19
አምላክ ‘አስቀድሞ የወደደን’ በምን መንገድ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ እንዲሞትልን በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል” ብሏል። (ሮም 5:8) ፍቅር የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ ነው፤ በመሆኑም ኢየሱስ፣ አምላክ የሰጠው የመጀመሪያው ትእዛዝ የቱ እንደሆነ ጥያቄ ላቀረበለት ሰው “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ” በማለት መልስ የሰጠው ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። (ማር. 12:30) ኢየሱስ፣ አምላክን ስለ መውደድ ሲናገር መጀመሪያ ላይ የጠቀሰው ልብን እንደሆነ መመልከት እንችላለን። ይሖዋ የተከፈለ ልብ አያስደስተውም። ይሁን እንጂ በሙሉ ነፍሳችን፣ በሙሉ አእምሯችንና በሙሉ ኃይላችን አምላክን መውደድ እንዳለብንም መዘንጋት አይኖርብንም። ይህም ማለት ለአምላክ ያለን እውነተኛ ፍቅር እንዲሁ ከልባችን ብቻ የሚመነጭ ስሜት እንዳልሆነ ያስገነዝበናል። ለአምላክ ያለን ፍቅር ከልብ የሚመነጭ ከመሆንም አልፎ መንፈሳዊና አካላዊ ችሎታዎቻችንን በሙሉ የሚጨምር መሆን አለበት። ነቢዩ ሚክያስ በገለጸው መሠረት ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ይህን ነው።—ሚክ. 6:8፤ w15 9/15 5:1-3
ማክሰኞ፣ የካቲት 14
ጆሮዬ ስለ አንተ ሰምታ ነበር፤ አሁን ግን በገዛ ዓይኔ አየሁህ።—ኢዮብ 42:5
በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን እጅ በግልጽ ማየት የሚሳነን ለምን ሊሆን ይችላል? የሕይወት ውጣ ውረዶች አስተሳሰባችንን ሊቆጣጠሩት ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ይሖዋ ከዚህ በፊት እንዴት እንደረዳን ማየት ሊሳነን ይችላል። ንግሥት ኤልዛቤል፣ ነቢዩ ኤልያስን እንደምትገድለው በዛተች ጊዜ ኤልያስ፣ አምላክ ከዚህ በፊት ያደረገለትን ነገር ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ዘንግቶ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኤልያስ “እንዲሞትም መለመን ጀመረ” ይላል። (1 ነገ. 19:1-4) ኤልያስ ያጋጠመው ችግር መፍትሔ ምን ነበር? ይሖዋ ብርታት እንዲሰጠው መጠየቅ ነበረበት። (1 ነገ. 19:14-18) ኢዮብም ባስጨነቁት ጉዳዮች ከመዋጡ የተነሳ ነገሮችን ከአምላክ አንጻር መመልከት ተስኖት ነበር። (ኢዮብ 42:3-6) እኛም አምላክ እንዲታየን እንደ ኢዮብ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ቅዱሳን መጻሕፍት በሚፈነጥቁልን ብርሃን ተጠቅመን ባጋጠመን ሁኔታ ላይ በማሰላሰል ነው። ይሖዋ እንዴት እየረዳን እንዳለ ስንገነዘብ እሱ ይበልጥ እውን ይሆንልናል። w15 10/15 1:15, 16
ረቡዕ፣ የካቲት 15
አንተ ሰው፣ በእናንተ መካከል ፈራጅና ዳኛ እንድሆን ማን ሾመኝ?—ሉቃስ 12:14
ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ትኩረቱን ሊከፋፍሉ የሚችሉ ብዙ ነገሮች አጋጥመውት ነበር፤ እሱ ግን ለእነዚህ ነገሮች አልተሸነፈም። በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ በቅፍርናሆም ብዙ ሕዝብ ካስተማረና ተአምር ከፈጸመ በኋላ የከተማዋ ነዋሪዎች እዚያው እንዲቆይ ለመኑት። ታዲያ ኢየሱስ ሰዎቹ ባቀረቡለት በዚህ ጥያቄ ተሸንግሎ ይሆን? በፍጹም፤ “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 4:42-44) ኢየሱስ ልክ እንደተናገረው እየሰበከና እያስተማረ በመላው የፓለስቲና ምድር ተዘዋውሯል። ፍጹም ቢሆንም እንኳ እንደ ማንኛውም ሰው መሠረታዊ ነገሮች ያስፈልጉት ነበር፤ እንዲሁም በአምላክ አገልግሎት በትጋት በመካፈሉ በጣም የደከመው ጊዜ ነበር። (ሉቃስ 8:23፤ ዮሐ. 4:6) በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ ተከታዮቹ የሚያጋጥማቸውን ተቃውሞ እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ እያስተማራቸው ሳለ አንድ ሰው በንግግሩ መሃል ጣልቃ ገብቶ “መምህር፣ ወንድሜ ውርሳችንን እንዲያካፍለኝ ንገረው” አለው። ኢየሱስ ግን እዚህ ጭቅጭቅ ውስጥ መግባት አልፈለገም።—ሉቃስ 12:13-15፤ w15 10/15 3:10, 11
ሐሙስ፣ የካቲት 16
አምላክ ፍቅር ነው።—1 ዮሐ. 4:8
ፍቅር ዋነኛውና ከሁሉ የላቀው የአምላክ ባሕርይ ነው። ይሖዋ አፍቃሪ ብቻ ሳይሆን የፍቅር ተምሳሌት ነው። የጽንፈ ዓለምና የሁሉም ሕይወት ያላቸው ነገሮች ፈጣሪ የፍቅር አምላክ መሆኑን ማወቅ ምንኛ የሚያስደስት ነው! ይሖዋ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። አምላክ ለፍጡራኑ ደግነት የሚንጸባረቅበትና ጥልቅ የሆነ ፍቅር ያለው መሆኑ፣ ለሰው ዘር ቤተሰብ ያለው ዓላማ በሙሉ ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንደሚፈጸምና ይህም በእሱ አገዛዝ ሥር ላሉ ሁሉ ወደር የሌለው ጥቅም እንደሚያስገኝ ለመተማመን ያስችለናል። ለምሳሌ፣ ይሖዋ “በሾመው ሰው [በኢየሱስ ክርስቶስ] አማካኝነት በዓለም ሁሉ ላይ በጽድቅ ለመፍረድ ዓላማ ያለው ሲሆን ይህን ለማድረግም ቀን ወስኗል”፤ እንዲህ ያደረገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። (ሥራ 17:31) ይህ ዓላማው መፈጸሙ እንደማይቀር እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውና ታዛዥ የሆኑ ሰዎች መልካም ፍርድ የሚበየንላቸው ሲሆን ይህም በበረከት የተሞላና ማብቂያ የሌለው ዘላለማዊ ሕይወት ያስገኝላቸዋል። w15 11/15 3:1, 2
ዓርብ፣ የካቲት 17
ንግግራችሁ ምንጊዜም በጨው የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው ይሁን።—ቆላ. 4:6
የስብከቱን ሥራ ስናከናውን ሰዎች የተለያየ ምላሽ ይሰጡናል፤ አንዳንዶች ይቀበሉናል፤ ሌሎች ደግሞ ይቃወሙናል። ሰዎች የሚሰጡት ምላሽ ምንም ይሁን ምን የይሖዋ አገልጋዮች ምንጊዜም ሊኖራቸው የሚገባውን አቋም የአምላክ ቃል ይገልጻል። ስለ ተስፋችን፣ ምክንያት እንድናቀርብ ለሚጠይቀን ሰው መልስ የምንሰጠው “በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት” ሊሆን ይገባል፤ ምክንያቱም ባልንጀራችንን እንወዳለን። (1 ጴጥ. 3:15) የምናነጋግራቸው ሰዎች መልእክቱን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ተቆጥተው ቢጮኹብንም እንኳ ለባልንጀራችን ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። ኢየሱስ “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ለሚፈርደው [ለይሖዋ] ራሱን በአደራ” ሰጥቷል፤ እኛም የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን። (1 ጴጥ. 2:23) ከእምነት ባልንጀሮቻችንም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ትሕትና በማሳየት የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ እናደርጋለን፦ “ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ አትመልሱ። ከዚህ ይልቅ ባርኩ።”—1 ጴጥ. 3:8, 9፤ w15 11/15 4:17, 18
ቅዳሜ፣ የካቲት 18
ልጆቻቸውን የሚወዱ [እንዲሆኑ ምከር]።—ቲቶ 2:4
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንደሚወዳቸው ከመናገር ወደኋላ አላለም። (ዮሐ. 15:9) ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በመቀራረብና ከእነሱ ጋር አዘውትሮ ጊዜ በማሳለፍም ፍቅሩን አሳይቷል። (ማር. 6:31, 32፤ ዮሐ. 2:2፤ 21:12, 13) እናንተም ልጆቻችሁን እንደምትወዷቸው ንገሯቸው፤ እንዲሁም ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንደምትሰጧቸው አዘውትራችሁ ግለጹላቸው። (ምሳሌ 4:3) በአውስትራሊያ የሚኖረው ሳሙኤል እንዲህ ብሏል፦ “ትንሽ ልጅ እያለሁ አባዬ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ ከተባለው መጽሐፍ ላይ ሁልጊዜ ማታ ማታ ያነብልኝ ነበር። ጥያቄዎቼን ይመልስልኛል፤ አስተኝቶኝ ከመሄዱ በፊት እቅፍ አድርጎ ይስመኛል። አባቴ፣ ልጆችን ማቀፍና መሳም ያን ያህል የተለመደ ባልሆነበት ቤተሰብ ውስጥ እንዳደገ ከጊዜ በኋላ ሳውቅ በጣም ተገረምኩ! እሱ ግን እንደሚወደኝ ለማሳየት ልባዊ ጥረት ያደርግ ነበር። ይህም አባቴን በጣም እንድቀርበው ብሎም ደስተኛ እንድሆንና እንዳልፈራ አድርጎኛል።” እናንተም አዘውትራችሁ ልጃችሁን “እወድሃለሁ” የምትሉት ከሆነ እንደ ሳሙኤል ሊሰማው ይችላል። ለልጆቻችሁ ፍቅራችሁን ግለጹላቸው። አዋሯቸው፣ አብራችሁ ተመገቡ እንዲሁም አጫውቷቸው። w15 11/15 1:3, 4
እሁድ፣ የካቲት 19
በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?—ማቴ. 24:45
ባለፈው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ጥቂት ቁጥር ያላቸው ትጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆነው በተሾሙበት ወቅት ‘ለቤተሰቡ’ አባላት በአብዛኛው ምግብ የሚያቀርቡት በእንግሊዝኛ ነበር። ይህ “ባሪያ” መንፈሳዊውን ምግብ በብዙ ቋንቋዎች ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን አሁን ከ700 በሚበልጡ ቋንቋዎች መንፈሳዊ ምግብ እያቀረበ ነው። በተጨማሪም የጥንቶቹ ቅዱሳን መጻሕፍት የያዙትን ሐሳብ በትክክለኛና በዘመናዊ ቋንቋ የሚያስተላልፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነበር። በመሆኑም የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ኮሚቴው ከ1950 እስከ 1960 ባሉት አሥር ዓመታት ውስጥ የትርጉም ሥራውን በስድስት ጥራዞች አወጣ። ወንድም ናታን ሆመር ኖር፣ የዚህ ትርጉም የመጀመሪያ ጥራዝ መውጣቱን ነሐሴ 2, 1950 ሲናገር፣ ይህ ትርጉም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በመንፈሳዊ እንደሚረዳ ያለውን ምኞት ገልጿል። w15 12/15 1:15, 17
ሰኞ፣ የካቲት 20
ሰብሳቢው ደስ የሚያሰኙ ቃላትን ለማግኘትና የእውነትን ቃል በትክክል ለመመዝገብ ጥረት አደረገ።—መክ. 12:10
“ደስ የሚያሰኙ ቃላትን” መናገር አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ይሆንብሃል? ከሆነ የምታውቃቸውን ቃላት ብዛት ለማሳደግ ጥረት ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል። ይህን ማድረግ የምትችልበት አንዱ መንገድ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስና በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ላይ ቃላት እንዴት እንደሚሠራባቸው ማስተዋል ነው። የማታውቃቸውን አገላለጾች ትርጉም ለማወቅ ሞክር። ከሁሉ በላይ ደግሞ ቃላትን ሌሎችን በሚያንጽ መንገድ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ተማር። በይሖዋና በበኩር ልጁ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ‘[ኢየሱስ] ለደከመው ትክክለኛውን ቃል በመናገር እንዴት መልስ መስጠት እንደሚችል ያውቅ ዘንድ ይሖዋ የተማሩ ሰዎችን አንደበት ሰጥቶታል።’ (ኢሳ. 50:4) ከመናገራችን በፊት፣ ምን እንደምንል ቆም ብለን ማሰላሰላችን ተገቢ ቃላት ለመጠቀም ያስችለናል። (ያዕ. 1:19) ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘እነዚህ ቃላት ሐሳቤን በትክክል ያስተላልፋሉ? የምጠቀምባቸው ቃላት በሚያዳምጡኝ ሰዎች ላይ ምን ስሜት ይፈጥራሉ?’ w15 12/15 3:12
ማክሰኞ፣ የካቲት 21
[ኢየሩሳሌም] መጥፊያዋ እንደቀረበ እወቁ።—ሉቃስ 21:20
ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ኢየሩሳሌም “በጦር ሠራዊት ተከባ” ሲመለከቱ በይሁዳ በተለይ ደግሞ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ነበረባቸው። ኢየሱስ፣ እነዚህ ነገሮች መፈጸም ሲጀምሩ በፍጥነት መሸሽ እንዳለባቸው አስጠንቅቋቸዋል። (ሉቃስ 21:21-24) ኢየሱስ ይህን ትንቢት ከተናገረ በኋላ በነበሩት 28 ዓመታት ውስጥ በእስራኤል የሚኖሩ ታማኝ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ብዙ ተቃውሞና ስደት የደረሰባቸው ቢሆንም ተቋቁመውታል። (ዕብ. 10:32-34) ይሁን እንጂ ጳውሎስ ከእምነታቸው ጋር በተያያዘ በቅርቡ በጣም ከባድ ፈተና እንደሚያጋጥማቸው ያውቃል። (ማቴ. 24:20, 21፤ ዕብ. 12:4) ስለዚህ ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ማንኛውም ነገር እንዲዘጋጁ ፈልጓል። የሚያጋጥማቸውን ነገር ለመቋቋም የተለየ ጽናት ብሎም በሕይወት የሚያኖር ጠንካራ እምነት ያስፈልጋቸዋል። (ዕብ. 10:36-39) ስለሆነም ጳውሎስ እነዚህ ውድ ወንድሞችና እህቶች የሚያስፈልጋቸውን ለየት ያለ እርዳታ ለመስጠት የሚያስችል ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው ይሖዋ በመንፈሱ መርቶታል። ይህ ደብዳቤ በአሁኑ ወቅት የዕብራውያን መጽሐፍ ተብሎ ይጠራል። w16.01 1:1, 2
ረቡዕ፣ የካቲት 22
የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ አምላክ የወደደን በዚህ መንገድ ከሆነ እኛም እርስ በርሳችን የመዋደድ ግዴታ አለብን።—1 ዮሐ. 4:11
አምላክ እንዲወደን ከፈለግን ወንድሞቻችንን የመውደድ ግዴታ እንዳለብን አምነን መቀበል ይኖርብናል። (1 ዮሐ. 3:16) ታዲያ ፍቅራችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ እንመልከት። በምድር ላይ ባከናወነው አገልግሎቱ ወቅት፣ ዝቅ ተደርገው ለሚታዩ ሰዎች ልዩ ትኩረት ይሰጥ ነበር። የአካል ጉዳተኛ የሆኑትን ለምሳሌ አንካሶችን፣ ዓይነ ስውሮችን፣ መስማት የተሳናቸውንና ዱዳዎችን ፈውሷል። (ማቴ. 11:4, 5) በጊዜው የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ‘የተረገሙ’ አድርገው የሚመለከቷቸውን በመንፈሳዊ የተራቡ ሰዎች ማስተማር ያስደስተው ነበር። (ዮሐ. 7:49) ዝቅ ተደርገው የሚታዩትን እነዚህን ሰዎች ይወዳቸውና እነሱን ለማገልገል በትጋት ይሠራ ነበር። (ማቴ. 20:28) እናንተስ በጉባኤያችሁ ስላሉት ወንድሞችና እህቶች ጊዜ ወስዳችሁ ታስባላችሁ? ይህን ስታደርጉ ፍቅር ብታሳዩአቸው የሚጠቀሙ ሰዎች እንዳሉ ማስተዋላችሁ አይቀርም። ምናልባትም እርዳታ የሚያሻቸው አረጋውያን ወንድሞችና እህቶች ይኖሩ ይሆናል። የአምላክ ፍቅር ለወንድሞቻችን ፍቅራችንን ለማሳየት ሊያነሳሳን ይገባል። w16.01 2:12-14
ሐሙስ፣ የካቲት 23
ከዚህ ጉረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነሱንም ማምጣት አለብኝ፤ . . . ሁሉም አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ አንድ እረኛም ይኖራቸዋል።—ዮሐ. 10:16
የሌሎች በጎች አባላት በዛሬው ጊዜ የሚገኙትን የሁሉንም ቅቡዓን ስም ማወቅ ያስፈልጋቸዋል? አያስፈልጋቸውም። ለምን? ምክንያቱም አንድ ሰው ሰማያዊ ጥሪ ቢያገኝ እንኳ ግለሰቡ የተቀበለው ግብዣ እንጂ ሽልማቱን እንደሚያገኝ የሚያሳይ የመጨረሻ ማረጋገጫ አይደለም። ሰይጣን ‘ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ እንዲያስቱ ሐሰተኛ ነቢያትን የሚያስነሳው’ ለዚህ ነው። (ማቴ. 24:24) አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን፣ ሰማያዊ ሽልማት ማግኘት ይገባው እንደሆነ ይሖዋ እስኪወስን ድረስ ግለሰቡ ይህን ሽልማት ማግኘቱን ማንም ሰው ማወቅ አይችልም። ይሖዋ ይህን ውሳኔ የሚያስተላልፈውና የመጨረሻውን ማኅተም የሚያደርግበት፣ ግለሰቡ በታማኝነት ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ አሊያም ‘ታላቁ መከራ’ ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ነው። (ራእይ 2:10፤ 7:3, 14) እንግዲያው በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ሰው ከአምላክ አገልጋዮች መካከል የ144,000ዎቹ አባል የሚሆኑትን በእርግጠኝነት ለማወቅ መሞከሩ ምንም ትርጉም የለውም። w16.01 4:2, 3
ዓርብ፣ የካቲት 24
[ቃሌ] የተላከበትንም ዓላማ በእርግጥ ይፈጽማል።—ኢሳ. 55:11
ምሥራቹን የመስበኩ ሥራ ይሖዋ ለሰው ልጆች ካለው ፍቅር የተንጸባረቀበት ዓላማ ጋር እንዴት እንደሚያያዝ አስብ። የአምላክ ዓላማ የሰው ልጆች ፈጽሞ ሞትን ሳያዩ በምድር ላይ እንዲኖሩ ነው፤ አዳም ኃጢአት ቢሠራም ይሖዋ ይህን ዓላማውን አልቀየረም። እንዲያውም የሰው ልጆች ከኃጢአትና ከሞት ኩነኔ ነፃ የሚወጡበትን ዝግጅት አደረገ። ይህንን ዓላማ ከዳር ማድረስ እንዲቻል ኢየሱስ ወደ ምድር መጥቶ ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል። ይሁንና የሰው ልጆች ታዛዥ እንዲሆኑ አምላክ ከእነሱ ምን እንደሚጠብቅባቸው ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። በመሆኑም ኢየሱስ የአምላክን መሥፈርቶች ለሰዎች አስተምሯል፤ ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ እንዲያደርጉ ትእዛዝ ሰጥቷል። እኛም ሰዎች ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ ስንረዳ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ይሖዋ ባደረገው ፍቅራዊ ዝግጅት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ይኖረናል። በተጨማሪም እንዲህ ማድረጋችን ለእነሱም ሆነ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ያሳያል፤ የይሖዋ “ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።”—1 ጢሞ. 2:4፤ w16.01 5:15, 16
ቅዳሜ፣ የካቲት 25
[አካዝ] ወንዶች ልጆቹን በእሳት አቃጠለ።—2 ዜና 28:3
የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ በምሬትና በቁጣ ሊሞላ ብሎም በአምላክ ላይ ሊያምፅ ይችል ነበር። የዚህን ያህል የከፋ ሁኔታ ያላጋጠማቸው ሰዎች እንኳ ‘በይሖዋ ላይ ተቆጥተዋል’ ወይም በድርጅቱ ላይ አማረዋል። (ምሳሌ 19:3) አንዳንዶች ደግሞ አስተዳደጋቸው መጥፎ በመሆኑ እነሱም የወላጆቻቸውን ስህተት በመድገም መጥፎ ሕይወት መምራታቸው እንደማይቀር ያስባሉ። (ሕዝ. 18:2, 3) እንዲህ ያሉት አመለካከቶች ትክክል ናቸው? በፍጹም! የሕዝቅያስ ሕይወት ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ይሆናል። በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ሰዎች ለሚደርሱባቸው መጥፎ ነገሮች ተጠያቂው ይሖዋ ስላልሆነ እሱን ለማማረር የሚያበቃ ምንም ዓይነት ምክንያት ሊኖር አይችልም። (ኢዮብ 34:10) እርግጥ ነው ወላጆች፣ በበጎም ይሁን በመጥፎ በልጆቻቸው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። (ምሳሌ 22:6፤ ቆላ. 3:21) ይህ ሲባል ግን አንድ ሰው በሕይወቱ የሚከተለው ጎዳና በአስተዳደጉ ላይ የተመካ ነው ማለት አይደለም። ይሖዋ ለሁላችንም ውድ ስጦታ ይኸውም የመምረጥ ችሎታ ሰጥቶናል፤ በመሆኑም ምን ዓይነት አካሄድ መከተል ወይም ምን ዓይነት ሰው መሆን እንደምንፈልግ መምረጥ እንችላለን።—ዘዳ. 30:19፤ w16.02 2:8-10
እሁድ፣ የካቲት 26
ጨካኝ ሰዎችም ሕይወቴን ይሻሉ።—መዝ. 54:3
አበኔር፣ አምላክ ዳዊትን የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን እንደመረጠው ቢያውቅም ሳኦል ዳዊትን ለመግደል ጥረት ሲያደርግ ተባባሪ ሆኗል። (1 ሳሙ. 26:1-5) ሳኦል ከሞተ በኋላ አበኔር፣ የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ሳይሆን ዳዊትን በመደገፍ ትሑትና ለአምላክ ታማኝ መሆኑን ማሳየት ይችል ነበር። ከጊዜ በኋላ ከንጉሥ ሳኦል ቁባት ጋር ግንኙነት የፈጸመ ሲሆን ይህም ንግሥናውን ለራሱ መውሰድ እንደፈለገ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። (2 ሳሙ. 2:8-10፤ 3:6-11) በተመሳሳይም የዳዊት ልጅ የነበረው አቢሴሎም፣ ትሕትና ስላልነበረው ለአምላክ ታማኝ ሳይሆን ቀርቷል። እንዲያውም “አቢሴሎም ሠረገላ፣ ፈረሶችና ከፊቱ የሚሮጡ 50 ሰዎች አዘጋጀ”! (2 ሳሙ. 15:1) በተጨማሪም የሕዝቡን ልብ ሰረቀ። ልክ እንደ አበኔር፣ አቢሴሎምም ዳዊትን ለመግደል ተነስቶ ነበር፤ ይህን ያደረገው ይሖዋ ዳዊትን የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን እንደሾመው እያወቀ ነው። (2 ሳሙ. 15:13, 14፤ 17:1-4) ከአበኔርና ከአቢሴሎም ታሪክ መመልከት እንደሚቻለው የሥልጣን ጥመኝነት፣ አንድ ሰው ለአምላክ ታማኝ እንዳይሆን ሊያደርገው ይችላል። ማንኛውም ታማኝ የሆነ የይሖዋ አገልጋይ፣ እንዲህ ያለ ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት የክፋት አካሄድ እንደማይከተል የታወቀ ነው። w16.02 4:9-11
ሰኞ፣ የካቲት 27
በሥራ ያልተደገፈ [እምነት] በራሱ የሞተ ነው።—ያዕ. 2:17
ስለምታምንበት ነገር እርግጠኛ ከሆንክ ይህ በምግባርህ ላይ መንጸባረቁ አይቀርም። ወጣቶችም ቢሆኑ “ቅዱስ ሥነ ምግባር” ሊኖራቸው ይገባል። (2 ጴጥ. 3:11) ይህን ለማድረግ ደግሞ ከሥነ ምግባር አኳያ ንጹሕ መሆን አለባቸው። በዚህ ረገድ የአንተ ሁኔታ ምን ይመስላል? ለምሳሌ ያለፉትን ስድስት ወራት መለስ ብለህ አስብ። ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ለመለየት የሠለጠነ “የማስተዋል ችሎታ” እንዳለህ ያሳየኸው እንዴት ነው? (ዕብ. 5:14) ፈተናዎችን ወይም የእኩዮችን ተጽዕኖ የተቋቋምክባቸውን አጋጣሚዎች ታስታውሳለህ? በትምህርት ቤት የምታሳየው ምግባር ስለምታምንበት ነገር ጥሩ ምሥክርነት ይሰጣል? ሌሎች እንዳያሾፉብህ ስትል ብቻ አብረውህ ከሚማሩ ልጆች ጋር ለመመሳሰል ከመሞከር ይልቅ ለምታምንበት ነገር ጥብቅና ትቆማለህ? (1 ጴጥ. 4:3, 4) እርግጥ ነው፣ ፍጹም የሆነ ሰው የለም። ይሖዋን ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ሰዎችም እንኳ አንዳንድ ጊዜ በሕዝብ ፊት ስለሚያምኑበት ነገር በይፋ መናገር ሊያስፈራቸው ይችላል። ይሁንና ራሱን ለይሖዋ የወሰነ አንድ ሰው የአምላክን ስም በመሸከሙ ኩራት ይሰማዋል፤ ይህንንም በምግባሩ ያሳያል። w16.03 2:10, 11
ማክሰኞ፣ የካቲት 28
መንገዱ ይህ ነው። በእሱ ሂድ።—ኢሳ. 30:21
በታሪክ ዘመናት ሁሉ ይሖዋ ዝርዝር መመሪያዎች ወይም ትእዛዛት ሲሰጥ ቆይቷል። ለምሳሌ በኤደን ገነት የዘላለም ሕይወትና ዘላቂ ደስታ ሊያስገኝ የሚችል ግልጽ መመሪያ ለአዳምና ለሔዋን ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍ. 2:15-17) እነዚህ ባልና ሚስት መመሪያውን ቢታዘዙ ኖሮ ችግር ላይ አይወድቁም ነበር፤ ባለመታዘዛቸው ምክንያት ግን በመከራ የተሞላ እንዲሁም ያለምንም ተስፋ በሞት የሚደመደም ሕይወት ለመምራት ተገደዋል። ሔዋን መመሪያውን በመታዘዝ ፋንታ ከአንድ ተራ እንስሳ የመጣ የሚመስለውን ምክር ተቀብላለች። አዳምም ቢሆን ሟች የሆነችው ሔዋን የነገረችውን ነገር ሰማ። ሁለቱም አፍቃሪ የሆነው አባታቸው የሰጣቸውን መመሪያ አልተቀበሉም። በዚህም የተነሳ የሰው ልጆች ወደ ሞት በሚመራ ጎዳና ላይ መጓዝ ጀመሩ። ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ሕዝቦቹን እየመራ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስዳቸውንና አደጋ የሌለበትን መንገድ ይጠቁማቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ አፍቃሪ እረኛ እንደመሆኑ መጠን በጎቹ አደገኛ የሆነ ጎዳና ከመከተል እንዲርቁ አስፈላጊውን መመሪያና ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል። w16.03 4:2, 3