ታኅሣሥ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 1
ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የሚኖራቸው እሱን የሚፈሩ ሰዎች ናቸው። —መዝ. 25:14
አብርሃም የይሖዋ ወዳጅ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሦስት ጊዜ ተጠቅሷል። (2 ዜና 20:7፤ ኢሳ. 41:8፤ ያዕ. 2:23) መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ የይሖዋ ወዳጅ ብሎ የጠራው ብቸኛው ሰው ታማኙ አብርሃም ነው። ይህ ሲባል ግን ‘ከሰዎች መካከል የይሖዋ ወዳጅ የሆነው አብርሃም ብቻ ነው’ ብለን መደምደም ይኖርብናል? በፍጹም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንም ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መመሥረት እንደምንችል ይጠቁማል። የአምላክ ቃል ይሖዋን ስለሚፈሩ፣ በእሱ ላይ እምነት ስላላቸውና ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ስለመሠረቱ በርካታ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች የሚገልጹ ዘገባዎችን ይዟል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” እንደሆኑ የጠቀሳቸው ሰዎች አሉ። (ዕብ. 12:1) የተለያየ ዓይነት ሕይወት የነበራቸው እነዚህ ሰዎች፣ የአምላክ ወዳጆች የመሆን ግሩም መብት አግኝተዋል። እነዚህን ሰዎች በእምነታቸው መምሰላችንን እንቀጥል። (ዕብ. 6:11, 12) ይህን ስናደርግ ታላቅ ሽልማት እንደምናገኝ ይኸውም ለዘላለም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንደሚኖረን እርግጠኞች መሆን እንችላለን! w16.02 2:1, 2, 19
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 2
የመጣሁት የራሴን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ነው።—ዮሐ. 6:38
አንድ ወዳጅህ መኪና በስጦታ ሰጠህ እንበል። ሊብሬውን ካስረከበህ በኋላ “ቁልፉን አልሰጥህም። ደግሞም መኪናውን የምትነዳው አንተ ሳትሆን እኔ ነኝ” አለህ እንበል። ምን ይሰማሃል? አሁን ደግሞ ይሖዋ ራሱን ከወሰነ ሰው ምን እንደሚጠብቅበት አስብ፤ ግለሰቡ “ሕይወቴን ሰጥቼሃለሁ። የአንተ ንብረት ነኝ” በማለት ራሱን ለይሖዋ ይወስናል። ሆኖም ይህ ሰው ሁለት ዓይነት ሕይወት የሚመራ ቢሆንስ? ምናልባት ከማያምን ሰው ጋር በድብቅ መጠናናት ቢጀምርስ? አሊያም ደግሞ በአገልግሎት ወይም በስብሰባዎች ላይ ለይሖዋ የሙሉ ነፍስ አገልግሎት ማቅረብ እንዲሳነው የሚያደርግ ሥራ ቢቀጠርስ? እንዲህ ማድረግ ‘የመኪናውን ቁልፍ አልሰጥህም’ ከማለት ተለይቶ ይታያል? ራሱን ለይሖዋ የሚወስን ግለሰብ እንዲህ የሚል ያህል ነው፦ “ሕይወቴ የእኔ ሳይሆን የአንተ ንብረት ነው። አንተ በምትጠብቅብኝና እኔ ማድረግ በምፈልገው ነገር መካከል ልዩነት ከተፈጠረ ምንጊዜም የአንተ ምርጫ ይቀድማል።” ይህ አመለካከት ኢየሱስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል። w16.03 1:16, 17
እሁድ፣ ታኅሣሥ 3
ከአንተ አልለይም።—2 ነገ. 2:2
ወደ 3,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ነቢዩ ኤልያስ፣ ኤልሳዕ የተባለን አንድ ወጣት አገልጋዩ እንዲሆን ጠይቆት ነበር። ኤልሳዕም ግብዣውን ወዲያውኑ በመቀበል ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን በማከናወን በዕድሜ የገፋውን ነቢይ በታማኝነት ማገልገል ጀመረ። (2 ነገ. 3:11) ኤልሳዕ ለስድስት ዓመት ያህል ከሠለጠነ በኋላ ኤልያስ በእስራኤል ውስጥ የሚያከናውነው አገልግሎት ሊያበቃ እንደሆነ ተገነዘበ። በዚህ ወቅት ኤልያስ በደንብ የሠለጠነው አገልጋዩ እሱን መከተሉን እንዲያቆም ጠየቀው፤ ኤልሳዕ ግን ከአስተማሪው ጋር የሚችለውን ያህል ረጅም ጊዜ ለማሳለፍ ቆርጦ ነበር። ወጣት ወንድም ከሆንክ የኤልሳዕን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው? ዝቅ ተደርገው የሚቆጠሩ ሥራዎችን ጨምሮ ማንኛውም ኃላፊነት ሲሰጥህ ሥራውን ለማከናወን ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ነው። አስተማሪህን እንደ ጓደኛ ተመልከተው፤ እንዲሁም አንተን ለመርዳት የሚያደርገውን ጥረት እንደምታደንቅ ንገረው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የተሰጠህን ማንኛውንም ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ታማኝ መሆንህን አሳይ። ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነት እንድትቀበል የሚፈልግ መሆኑን ሽማግሌዎቹ እርግጠኞች የሚሆኑት ታማኝና እምነት የሚጣልበት ሰው መሆንህን ስታስመሠክር ነው።—መዝ. 101:6፤ 2 ጢሞ. 2:2፤ w15 4/15 2:13, 14
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 4
ጉዳት ላይ ሊጥለው ቢችልም እንኳ ቃሉን አያጥፍም።—መዝ. 15:4
ሳኦል፣ በዳዊት ፋንታ ንጉሥ እንዲሆን ዮናታንን ይገፋፋው ነበር። (1 ሳሙ. 20:31) ሆኖም ዮናታን ለአምላክ ያለው ታማኝነት፣ ንግሥናውን የራሱ ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ ከዳዊት ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርት አነሳስቶታል። ዮናታን ለዳዊት የገባውን ‘ቃል አላጠፈም።’ እኛም በተመሳሳይ የገባነውን ቃል ማጠፍ አይኖርብንም። ለምሳሌ ያህል፣ አንድን የንግድ ስምምነት መፈጸም ካሰብነው በላይ ከባድ በሚሆንብን ጊዜ ለአምላክ ያለን ታማኝነትና ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለን አክብሮት ቃላችንን እንድንጠብቅ ሊያነሳሳን ይገባል። የትዳር ሕይወት ከጠበቅነው በላይ ከባድ ቢሆንብንስ? ለአምላክ ያለን ፍቅር ለትዳር ጓደኛችን ታማኞች እንድንሆን ያደርገናል። (ሚል. 2:13-16) በተጨማሪም ለአምላክ ሕዝቦች ሌላው ቀርቶ ቅር ላሰኙን ሰዎች ታማኝ በመሆን ለይሖዋ ታማኝነታችንን እናሳይ። በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳ ለይሖዋ አምላክ ታማኝ ከሆንን ልቡን ደስ ማሰኘት እንችላለን። (ምሳሌ 27:11) ለይሖዋ ታማኞች ሆነን ከቀጠልን፣ እሱ ለሚወዱት ሁሉ ምንጊዜም የተሻለውን ነገር እንደሚያደርግላቸው በሕይወታችን መመልከት እንችላለን። w16.02 3:16, 17
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 5
እሱን በተስፋ የሚጠባበቁ ሁሉ ደስተኞች ናቸው።—ኢሳ. 30:18
ይሖዋ አቅማችን ምን ያህል እንደሆነ በደንብ ያውቃል። (መዝ. 103:14) ስለዚህ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በራሳችን ኃይል እንድንወጣቸው አይጠብቅብንም፤ ከዚህ ይልቅ ልክ እንደ አባት እርዳታ ይሰጠናል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ፈተናውን መቋቋም የማንችልበት ደረጃ ላይ እንደደረስን ይሰማን ይሆናል። ያም ቢሆን ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ከሚችሉት በላይ እንዲፈተኑ ፈጽሞ እንደማይፈቅድ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። እንዲያውም “መውጫ መንገዱን” ያዘጋጅልናል። (1 ቆሮ. 10:13) እንግዲያው ይሖዋ መሸከም የምንችለው ምን ያህል እንደሆነ በትክክል እንደሚያውቅ ለመተማመን የሚያበቃ ምክንያት አለን። እርዳታ ለማግኘት ከጸለይን በኋላ ወዲያውኑ ምላሽ እንዳላገኘን ከተሰማን፣ እኛን ለመርዳት መቼ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የሚያውቀውን አምላካችንን በትዕግሥት እንጠብቅ። ይሖዋ እኛን ለመርዳት በጣም ስለሚጓጓ እሱም ቢሆን መታገሥ እንደሚያስፈልገው እናስታውስ። “ይሖዋ ሞገስ ሊያሳያችሁ በትዕግሥት ይጠባበቃል፤ ምሕረት ሊያሳያችሁም ይነሳል። ይሖዋ የፍትሕ አምላክ ነውና።” w15 4/15 4:8, 9
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 6
ተስፋቸውን በአምላክ ላይ የጣሉ በቀድሞ ጊዜ የነበሩ ቅዱሳን ሴቶች ራሳቸውን ለባሎቻቸው በማስገዛት በዚህ ዓይነት ሁኔታ ራሳቸውን ያስውቡ ነበር።—1 ጴጥ. 3:5
በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ወቅት ቤተሰቡ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ ቤተሰቡ አንድነት እንዲኖረው ያስችላል። በዚህ ወቅት ለመስክ አገልግሎት ልምምድ ማድረግ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመስበክ የታጠቁ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። ከዚህም ሌላ የአንድ ቤተሰብ አባላት ለአምላክ ፍቅር ያላቸውና የእሱን ፈቃድ ማድረግ የሚፈልጉ እንደመሆናቸው መጠን ከአምላክ ቃል ባገኟቸው ሐሳቦች ላይ መወያየታቸው እርስ በርስ እንደሚያቀራርባቸው መገመት አያዳግትም። ባለትዳሮች እርስ በርስ በመተባበር ለይሖዋ ውዳሴ ለማምጣት ምን ማድረግ ይችላሉ? ሁለቱም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸው ደስታና አንድነት ያስገኝላቸዋል። አብርሃምና ሣራ፣ ይስሐቅና ርብቃ እንዲሁም ሕልቃናና ሐና ለትዳር ጓደኛቸው ያላቸውን ፍቅር ገልጸዋል። እኛም የእነሱን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል። (ዘፍ. 26:8፤ 1 ሳሙ. 1:5, 8) ይህም ከትዳር ጓደኛችን ጋር አንድነት እንዲኖረን የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ በሰማይ ወዳለው አባታችን ይበልጥ እንድንቀርብ ያስችለናል።—መክ. 4:12፤ w16.03 3:12, 13
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 7
በእምነት ጸንታችሁ በመቆም [ሰይጣንን] ተቃወሙት።—1 ጴጥ. 5:9
ሰይጣን በቅቡዓን ቀሪዎችና ‘በሌሎች በጎች’ ላይ ጦርነት አውጇል። (ዮሐ. 10:16) የዲያብሎስ ዓላማ በቀረው ጥቂት ጊዜ ውስጥ ከይሖዋ አገልጋዮች መካከል የቻለውን ያህል ብዙዎችን መዋጥ ነው። (ራእይ 12:9, 12) ታዲያ ከሰይጣን ጋር በምናደርገው ውጊያ ማሸነፍ እንችላለን? እንዴታ! መጽሐፍ ቅዱስ “ዲያብሎስን . . . ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል” ይላል። (ያዕ. 4:7) ብዙዎች ሰይጣን አለ ብሎ ማመን ቂልነት እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች ሰይጣንና አጋንንቱ በልብ ወለድ መጻሕፍት፣ በአስፈሪ ፊልሞችና በቪዲዮ ጨዋታዎች ውስጥ የሚገኙ ምናብ የፈጠራቸው ገጸ ባሕርያት እንደሆኑ ያስባሉ። የማመዛዘን ችሎታ ያለው ማንኛውም ሰው በክፉ መናፍስት እንደማያምን ይናገራሉ። ታዲያ ሰይጣን፣ እሱና በዓይን የማይታዩት ግብረ አበሮቹ በተረት ዓለም ውስጥ የሚገኙ ባለታሪኮች ብቻ እንደሆኑ ተደርገው መቆጠራቸው ቅር የሚያሰኘው ይመስልሃል? ይህ የሚያስከፋው አይመስልም! እንዲያውም ሰይጣን፣ እሱ መኖሩን የሚጠራጠሩ ሰዎችን አእምሮ ማሳወር ይቀለዋል። (2 ቆሮ. 4:4) ሰይጣን ሰዎችን ለማሳሳት ከሚጠቀምባቸው በርካታ ዘዴዎች አንዱ መንፈሳዊ ፍጥረታት የሉም የሚለውን ሐሳብ ማስፋፋት ነው። w15 5/15 2:1, 2
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 8
[ሙሴ] ቅቡዕ ሆኖ የሚደርስበት ነቀፋ በግብፅ ከሚገኝ ውድ ሀብት የላቀ እንደሆነ አስቧል፤ የሚከፈለውን ወሮታ በትኩረት ተመልክቷልና።—ዕብ. 11:26
የሙሴ ወላጆች ስለ ይሖዋ እንዲሁም ዕብራውያንን ከባርነት ነፃ አውጥቶ ተስፋይቱን ምድር ለመስጠት ስላለው ዓላማ ሙሴን አስተምረውት መሆን አለበት። (ዘፍ. 13:14, 15፤ ዘፀ. 2:5-10) ሙሴ፣ ይሖዋ ለእስራኤላውያን ቃል ስለገባው ነገር በጥልቅ ባሰላሰለ መጠን በአምላክ ላይ ያለው እምነትና ለእሱ ያለው ፍቅር እያደገ ሄዷል። ፈሪሃ አምላክ እንዳላቸው ሌሎች ሰዎች ሁሉ እሱም፣ ይሖዋ የሰውን ዘር ከሞት ባርነት ነፃ የሚያወጣበትን ጊዜ በዓይነ ሕሊናው ተመልክቶ ሊሆን ይችላል። (ኢዮብ 14:14, 15፤ ዕብ. 11:17-19) ሙሴ፣ ለዕብራውያንም ሆነ ለመላው የሰው ዘር ርኅራኄ ያለውን አምላክ መውደዱ የሚያስገርም አይደለም። በመላው ሕይወቱ ይሖዋን እንዲያገለግል የረዳው፣ እምነትና ፍቅር ያለው መሆኑ ነው። (ዘዳ. 6:4, 5) ፈርዖን እንደሚገድለው ቢዝትበትም እንኳ እምነቱ፣ ለአምላክ ያለው ፍቅርና ምናልባትም ወደፊት የሚጠብቀውን ግሩም ሕይወት በአእምሮው መሳሉ ፈርዖንን በድፍረት ለመጋፈጥ አጠናክሮታል።—ዘፀ. 10:28, 29፤ w15 5/15 3:11-13
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 9
የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል።—ዮሐ. 2:3
ኢየሱስ የመጀመሪያ ተአምሩን የፈጸመው በገሊላ በምትገኘው በቃና በተከናወነ የሠርግ ድግስ ላይ ነው። በድግሱ ላይ ከተጠበቀው በላይ ብዙ እንግዶች መጥተው ሊሆን ይችላል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን የወይን ጠጅ አለቀ። ከተጠሩት እንግዶች መካከል የኢየሱስ እናት ማርያም ትገኝበታለች። ማርያም ስለ ልጇ በተነገሩት ትንቢቶች ላይ ለዓመታት ስታሰላስል እንደቆየች ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም ልጇ ‘የልዑሉ አምላክ ልጅ’ ተብሎ እንደሚጠራ ታውቃለች። (ሉቃስ 1:30-32፤ 2:52) ማርያም፣ ኢየሱስ ለሰዎች እስካሁን ያላሳየው ኃይል እንዳለው ተማምና ይሆን? ያም ሆነ ይህ ማርያምና ኢየሱስ ለአዲሶቹ ተጋቢዎች እንዳዘኑላቸውና ከእፍረት ሊታደጓቸው እንደፈለጉ አሳይተዋል። ተጋቢዎቹ ለእንግዶች ጥሩ መስተንግዶ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ኢየሱስ ያውቃል። በመሆኑም 380 ሊትር የሚሆነውን ውኃ በተአምር ወደ ‘ጥሩ የወይን ጠጅ’ ለወጠው። (ዮሐ. 2:6-11) ኢየሱስ ይህን ተአምር የመፈጸም ግዴታ ነበረበት? በፍጹም። ይህን ያደረገው ለሰዎች ስለሚያስብና ለጋስ የሆነውን በሰማይ ያለውን አባቱን ምሳሌ ስለተከተለ ነው። w15 6/15 1:3
እሁድ፣ ታኅሣሥ 10
ጌታ ሆይ፣ ለእስራኤል መንግሥትን መልሰህ የምታቋቁመው በዚህ ጊዜ ነው?—ሥራ 1:6
ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ሐዋርያቱ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ጥያቄ ጠየቁት። ኢየሱስ የሰጣቸው መልስ፣ የአምላክ መንግሥት መግዛት የሚጀመርበትን ወቅት የሚያውቁበት ጊዜ እንዳልደረሰ የሚያሳይ ነው። ደቀ መዛሙርቱ ሊያከናውኑት በሚገባው አስፈላጊ ሥራ ይኸውም በስብከቱ ተልእኮ ላይ እንዲያተኩሩ ነገራቸው። (ሥራ 1:7, 8) ያም ቢሆን ኢየሱስ፣ የአምላክ መንግሥት የሚመጣበትን ጊዜ በጉጉት እንዲጠባበቁ ተከታዮቹን አስተምሯቸዋል። በመሆኑም ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ክርስቲያኖች ይህ መንግሥት እንዲመጣ ሲጸልዩ ኖረዋል። ኢየሱስ የሚያስተዳድረው የአምላክ መንግሥት ከሰማይ ሆኖ መግዛት የሚጀምርበት ጊዜ ሲደርስ፣ ይሖዋ ነገሮች የሚከናወኑበትን ጊዜ እንዲያውቁ ሕዝቡን ረድቷቸዋል። በ1876 ቻርልስ ቴዝ ራስል የጻፈው አንድ ርዕስ ባይብል ኤግዛሚነር በተባለ መጽሔት ላይ ወጥቶ ነበር። “የአሕዛብ ዘመናት የሚያበቁት መቼ ነው?” የሚል ጭብጥ ያለው ይህ ርዕስ 1914 ልዩ ዓመት መሆኑን ጠቁሞ ነበር። በዳንኤል ትንቢት ላይ የተገለጹት “ሰባት ዘመናት” ኢየሱስ ከጠቀሳቸው “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በዚህ ርዕስ ላይ ተብራርቷል።—ዳን. 4:16፤ ሉቃስ 21:24፤ w15 6/15 4:11, 12
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 11
ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።—ዮሐ. 11:35
ኢየሱስ የሌሎችን ሥቃይ ሲመለከት ከልቡ ያዝን ነበር። ወዳጁ አልዓዛር በመሞቱ ሌሎች ምን ያህል እንዳዘኑ ሲያይ ስሜቱ በጥልቅ በመነካቱ “እጅግ አዘነ፤ ተረበሸም።” እንዲህ የተሰማው፣ አልዓዛርን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከሞት እንደሚያስነሳው እያወቀ ነው። (ዮሐ. 11:33-36) ኢየሱስ፣ በጣም እንዳዘነ ሰዎች ማየታቸው አላሳፈረውም። በዙሪያው የነበሩት ሰዎች ኢየሱስ ለአልዓዛርና ለቤተሰቡ ያለውን ፍቅር ማየት ይችሉ ነበር። ኢየሱስ ከአምላክ ያገኘውን ኃይል ተጠቅሞ ወዳጁን ከሞት በማስነሳት ሩኅሩኅ መሆኑን አሳይቷል። (ዮሐ. 11:43, 44) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለ ኢየሱስ ሲናገር የፈጣሪ ‘ማንነት ትክክለኛ አምሳያ’ መሆኑን ይገልጻል። (ዕብ. 1:3) በመሆኑም ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት እሱም ሆነ አባቱ፣ በሽታና ሞት የሚያስከትሉትን ሥቃይ የማስወገድ ፍላጎት እንዳላቸው ያረጋግጣሉ። ይሖዋና ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የምናገኛቸውን ጥቂት ትንሣኤዎች በማከናወን ብቻ አይገደቡም። ኢየሱስ “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ . . . ይወጣሉ” ብሏል።—ዮሐ. 5:28, 29፤ w15 6/15 2:13, 14
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 12
ሕዝቦች ታላቅ ስምህን ያወድሱ።—መዝ. 99:3
ምድርን ለቀው ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ አምላክን እንደሚያወድሱ አድርገው በተሳሳተ መንገድ ከሚያስቡ አንዳንድ ሃይማኖተኛ ሰዎች በተቃራኒ ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች በአሁኑ ወቅት እዚሁ ምድር ላይ አምላክን የማመስገንን አስፈላጊነት ተገንዝበዋል። እንዲህ በማድረግ በመዝሙር 99:1-3, 5 ላይ የተገለጹትን የይሖዋን ታማኝ አገልጋዮች ምሳሌ እንከተላለን። ይህ መዝሙር እንደሚጠቁመው ሙሴ፣ አሮንና ሳሙኤል በዘመናቸው የነበረውን የእውነተኛ አምልኮ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ ደግፈዋል። (መዝ. 99:6, 7) በዛሬው ጊዜም በምድር ያሉት የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች በሰማይ ከእሱ ጋር ካህናት ሆነው ለማገልገል ከመሄዳቸው በፊት በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ በታማኝነት እያገለገሉ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩት “ሌሎች በጎች” በታማኝነት ይደግፏቸዋል። (ዮሐ. 10:16) ቅቡዓንና ሌሎች በጎች ያላቸው ተስፋ የተለያየ ቢሆንም የአምላክ የእግር ማሳረፊያ በሆነችው በምድር ላይ ሁለቱም ቡድኖች ይሖዋን በአንድነት እያመለኩ ነው። ይሁንና ‘ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ያደረገውን ዝግጅት በተሟላ ሁኔታ እየደገፍኩ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው። w15 7/15 1:4, 5
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 13
በተስፋ ጠብቀው!—ዕን. 2:3
ከጥንት ዘመን ጀምሮ የይሖዋ አገልጋዮች በመንፈስ መሪነት የተነገሩ ትንቢቶችን ፍጻሜ ለማየት ይጠባበቁ ነበር። ኢሳይያስ፣ ይሁዳ ባድማ ከሆነች በኋላ ይሖዋ ሕዝቡን ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ እንደሚመልስ ትንቢት ሲናገር “እሱን በተስፋ የሚጠባበቁ ሁሉ ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ኢሳ. 30:18) ጥንት ስለነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ትንቢት የተናገረው ሚክያስም “ይሖዋን በጉጉት እጠባበቃለሁ” በማለት የራሱን አቋም ገልጿል። (ሚክ. 7:7) የአምላክ አገልጋዮች ስለ መሲሑ ወይም ስለ ክርስቶስ የተነገሩ ትንቢቶችን ፍጻሜም ለዘመናት በተስፋ ሲጠባበቁ ቆይተዋል። (ሉቃስ 3:15፤ 1 ጴጥ. 1:10-12) ከመሲሑ ጋር የተያያዙ ትንቢቶች አሁንም እየተፈጸሙ በመሆናቸው በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦችም የእነዚህን ትንቢቶች ፍጻሜ ለማየት በተስፋ ይጠባበቃሉ። በቅርቡ ይሖዋ በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት ክፉዎችን በማጥፋት የሰው ልጆችን መከራ ያስወግዳል፤ እንዲሁም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ካለው ከዚህ ያልተረጋጋ ዓለም ሕዝቡን ነፃ ያወጣል። (1 ዮሐ. 5:19) በመሆኑም የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በፍጥነት እየተቃረበ እንደሆነ በመገንዘብ ምንጊዜም ንቁ ሆነን እንጠብቅ። w15 8/15 2:1, 2
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 14
ለቤትህ ያለኝ ቅንዓት ይበላኛል።—ዮሐ. 2:17
እስራኤላውያን የይሖዋን መመሪያ በመከተል የማደሪያውን ድንኳን ሠርተዋል። (ዘፀ. 25:8) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ለይሖዋ አምልኮ ቤተ መቅደስ ገነቡ። (1 ነገ. 8:27, 29) አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ከተመለሱ በኋላ በምኩራቦች ውስጥ አዘውትረው ይሰበሰቡ ነበር። (ማር. 6:2፤ ዮሐ. 18:20፤ ሥራ 15:21) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ደግሞ በጉባኤ አባላት ቤት ውስጥ ይሰበሰቡ ነበር። (ሥራ 12:12፤ 1 ቆሮ. 16:19) በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ሕዝቦች ከእሱ ለመማርና እሱን ለማምለክ በዓለም ዙሪያ በአሥር ሺዎች በሚቆጠሩ የመንግሥት አዳራሾች ውስጥ ይሰበሰባሉ። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ለነበረው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ታላቅ ፍቅር ያለው ከመሆኑም ሌላ በጣም ከፍ አድርጎ ይመለከተው ነበር፤ በመሆኑም አንድ የወንጌል ጸሐፊ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለው ትንቢት በኢየሱስ ላይ እንደተፈጸመ ገልጿል። (መዝ. 69:9) እርግጥ ነው፣ በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ ጋር በሚመጣጠን ደረጃ “የይሖዋ ቤት” ሊባል የሚችል አንድም የመንግሥት አዳራሽ የለም። (2 ዜና 5:13፤ 33:4) ያም ቢሆን በዘመናችን ያሉትን የአምልኮ ቦታዎች እንዴት ልንጠቀምባቸው እንደሚገባና ለእነዚህ ቦታዎች ሊኖረን የሚገባውን አክብሮት የሚያሳዩ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እናገኛለን። w15 7/15 4:1, 2
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 15
ፍቅርን ልበሱ።—ቆላ. 3:14
በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት አንዳችን ሌላውን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ መያዝ እንችል ይሆን? አሁን በነፃ ይቅር የምንባባል እንዲሁም በመካከላችን የሻከረ ግንኙነት እንዳይኖር የምንጥር ከሆነ ያን ጊዜ ይህን ማድረግ አይከብደንም። (ቆላ. 3:12, 13) በአዲሱ ዓለም ውስጥ የምንፈልገውን ነገር ሁሉ በፈለግነው ጊዜ እናገኛለን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በዚያ በምንኖርበት ጊዜ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን፣ ፍቅር ለሚንጸባረቅበት የይሖዋ ሉዓላዊነት መገዛት ለሚያስገኝልን ጥቅም አመስጋኝ መሆንና ባለን መርካት ይኖርብናል። ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እንድናዳብራቸው እያስተማረን ያሉትን ባሕርያት ማሳየትም ያስፈልገናል። በዚያን ጊዜ እንደምንኖር በምናስበው መንገድ አሁን የምንኖር ከሆነ ለዘላለም ልናንጸባርቃቸው የሚገቡ ባሕርያትን እያዳበርን ነው። እንዲሁም ‘መጪው ዓለም’ እውን እንደሚሆን ያለንን እምነት እያጠናከርን ነው። (ዕብ. 2:5፤ 11:1) በተጨማሪም በምድር ላይ የሚኖረውን ጽድቅ የሰፈነበት ሁኔታ ለማየት ምን ያህል እንደምንጓጓ እናሳያለን። በእርግጥም በአምላክ አዲስ ዓለም ለምናገኘው የዘላለም ሕይወት እየተዘጋጀን ነው ማለት ይቻላል። w15 8/15 3:11, 12
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 16
[ከኢየሱስ] ጋር በአንድነት መመላለሳችሁን ቀጥሉ።—ቆላ. 2:6
ገበያ ወጥተህ የበሰሉ ፍራፍሬዎችን ስታማርጥ ሁሉም ፍራፍሬዎች አንድ ዓይነት እንዳልሆኑ ማስተዋልህ አይቀርም። ያም ሆኖ ሁሉም መብሰላቸው የሚታወቅበት መንገድ አለ። በተመሳሳይም የጎለመሱ ክርስቲያኖች በብሔር፣ በአስተዳደግ፣ በአካላዊ ጤንነት፣ በዕድሜና በልምድ ሊለያዩ ይችላሉ። አልፎ ተርፎም የባሕርይ ወይም የባሕል ልዩነት አላቸው። ይሁንና በመንፈሳዊ እድገት የሚያደርጉ ሁሉ የጎለመሱ መሆናቸውን የሚያሳዩ ባሕርያትን ያንጸባርቃሉ። እንዴት? አንድ የጎለመሰ የይሖዋ አገልጋይ በአኗኗሩ ኢየሱስን ለመምሰልና ‘የእሱን ፈለግ በጥብቅ ለመከተል’ ጥረት ያደርጋል። (1 ጴጥ. 2:21) ኢየሱስ ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ አድርጎ የገለጸው ነገር ምንድን ነው? ይሖዋን በሙሉ ልብ፣ ነፍስና አእምሮ መውደድ እንዲሁም ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ ነው። (ማቴ. 22:37-39) አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ይህን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ይጥራል። አኗኗሩ ከይሖዋ ጋር ለመሠረተው ዝምድና ቅድሚያ እንደሚሰጥና ለሌሎች የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር እንዳለው ያሳያል። w15 9/15 1:3-5
እሁድ፣ ታኅሣሥ 17
እውነትን በመግለጥ በአምላክ ፊት የሰውን ሁሉ ሕሊና በሚማርክ መንገድ ራሳችንን ብቁ አድርገን እናቀርባለን።—2 ቆሮ. 4:2
ጥሩ ሕሊና መጥፎ ነገር እንዳንሠራ በማስጠንቀቅ ብቻ አይወሰንም። መልካም ሥራዎች እንድንሠራም ያነሳሳናል። ከቤት ወደ ቤት ሄዶ ማገልገልና መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ከመልካም ሥራዎች መካከል ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ። ጳውሎስ ሕሊናው እንዲህ እንዲያደርግ ገፋፍቶታል። “እንዲህ የማድረግ ግዴታ ተጥሎብኛልና። እንዲያውም ምሥራቹን ባልሰብክ ወዮልኝ!” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮ. 9:16) የእሱን አርዓያ ስንከተል ሕሊናችን ትክክለኛውን ነገር እያደረግን እንዳለን ይነግረናል። ምሥራቹን ስንሰብክ የምናነጋግራቸውን ሰዎች ሕሊና ለመማረክ ጥረት እናደርጋለን። አዎን፣ ሕሊናችን ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ዘወትር የአምላክን ቃል በጥልቀት በማጥናት፣ ባወቅነው ነገር ላይ በማሰላሰልና ያገኘነውን እውቀት በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት በማድረግ ሕሊናችንን ማሠልጠን እንችላለን። እንዲህ ካደረግን ሕሊናችን ለክርስቲያናዊ ሕይወታችን አስተማማኝ መሪ ይሆንልናል! w15 9/15 2:16, 18
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 18
ይሖዋም የሚወዳቸውን ይወቅሳል።—ምሳሌ 3:12
ታሪካቸው ሕያው በሆነ መልኩና በዝርዝር ተመዝግቦ ከምናገኛቸው ግለሰቦች መካከል ዮሴፍ፣ ሙሴና ዳዊት ይገኙበታል። በመከራቸው ወቅት ይሖዋ ከጎናቸው እንዴት እንደነበረና እንዴት በከፍተኛ ሁኔታ እንደተጠቀመባቸው ማንበባችን ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ስለሚያደርግላቸው እንክብካቤም ሆነ ስለሚያሳያቸው ፍቅር ይበልጥ እንድንገነዘብ ይረዳናል። ይሖዋ የሚሰጠን ተግሣጽ የፍቅሩን ሌላ ገጽታም እንድናስተውል ይረዳናል። የተሳሳተ ድርጊት የፈጸመ አንድ ሰው ይሖዋ ሲገሥጸው ለተግሣጹ ምላሽ በመስጠት ንስሐ ከገባ “ይቅርታው ብዙ” የሆነው አምላክ ይቅር ይለዋል። (ኢሳ. 55:7) ይህ ምን ማለት ነው? ዳዊት የይሖዋን ይቅር ባይነት እንዲህ በማለት ስሜት በሚነካ መንገድ ገልጾታል፦ “እሱ በደልሽን ሁሉ ይቅር ይላል፤ ሕመምሽንም ሁሉ ይፈውሳል፤ ሕይወትሽን ከጉድጓድ ያወጣል፤ ታማኝ ፍቅሩንና ምሕረቱን ያጎናጽፍሻል።” (መዝ. 103:3, 4) ይሖዋ የሚሰጠን ምክር አልፎ ተርፎም ተግሣጽ ለእኛ ያለውን ታላቅ ፍቅሩን የሚያንጸባርቅ እንደሆነ በመገንዘብ አፋጣኝ ምላሽ እንስጥ።—መዝ. 30:5፤ w15 9/15 4:13, 14
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 19
ማርያም . . . [ኢየሱስ] የሚናገረውን ታዳምጥ ነበር።—ሉቃስ 10:39
ማርታ፣ ለኢየሱስ ለየት ያለ ምግብ በማዘጋጀት ተጠምዳለች፤ እንዲሁም የማርያም ሁኔታ አበሳጫት። ኢየሱስ፣ ማርታ ብዙ ነገር ለማከናወን እየጣረች እንደሆነ ስላስተዋለ በደግነት “ማርታ፣ ማርታ፣ ስለ ብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ፤ ደግሞም ትጠበቢያለሽ” አላት። አንድ ዓይነት ምግብ ብቻ በቂ እንደሆነ ሐሳብ ሰጣት። ከዚያም ኢየሱስ ትኩረቱን ወደ ማርያም ዞር በማድረግ “ማርያም በበኩሏ ጥሩ የሆነውን ድርሻ መርጣለች፤ ይህም ከእሷ አይወሰድም” በማለት ድርጊቷ እንደ ቸልተኝነት ሊታይ እንደማይገባ ተናገረ። (ሉቃስ 10:38-42) ማርያም በዚህ ልዩ ወቅት የተመገበችውን ምግብ ብዙም ሳይቆይ ትረሳው ይሆናል፤ ይሁንና ትኩረቷ ሳይከፋፈል ኢየሱስን በማዳመጧ የተቸራትን ምስጋናም ሆነ ያገኘችውን ግሩም መንፈሳዊ ምግብ መቼም አትረሳውም። ሐዋርያው ዮሐንስ ከ60 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ “ኢየሱስ ማርታንና እህቷን . . . ይወዳቸው” እንደነበር ጽፏል። (ዮሐ. 11:5) በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ሐሳብ ማርታ፣ ኢየሱስ የሰጣትን ፍቅራዊ እርማት እንደተቀበለችና በቀሪው ሕይወቷ ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል ጥረት እንዳደረገች በግልጽ ያሳያል። w15 10/15 3:3, 4
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 20
ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነው ኃይል . . . ከአምላክ የመነጨ [ነው]።—2 ቆሮ. 4:7
ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ሰዎችን እየረዳ እንደሆነ እንድናምን የሚያደርገን አጥጋቢ ምክንያት አለን። መንፈሳዊ እርዳታ ለማግኘት ጸልየው ጸሎታቸው መልስ ስላገኘ ግለሰቦች የሚገልጹ ተሞክሮዎችን ብዙ ጊዜ እንሰማለን። (መዝ. 53:2) አላን የሚባል አንድ ወንድም በፊሊፒንስ በምትገኝ አንዲት ትንሽ ደሴት ላይ ከቤት ወደ ቤት እያገለገለ ሳለ ያገኛት ሴት ድንገት ማልቀስ ጀመረች። እንዲህ ብሏል፦ “ሴትየዋ የዚያን ዕለት ጠዋት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት እንድትችል ወደ ይሖዋ ጸልያ ነበር። አምላክ ለጸሎቷ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠቱ ስሜቷ በጥልቅ ተነክቷል።” ይህች ሴት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕይወቷን ለይሖዋ ወስናለች። ብዙ የአምላክ አገልጋዮች ከዚህ በፊት ከነበሯቸው እንደ ማጨስ፣ ዕፅ መውሰድ ወይም የብልግና ምስሎችን መመልከት ካሉ መጥፎ ልማዶች መላቀቅ እንዲችሉ አምላክ እንደረዳቸው በግልጽ ማየት ችለዋል። አንዳንዶች በራሳቸው ጥረት ለማቆም በተደጋጋሚ ጊዜ እንደሞከሩና እንዳልተሳካላቸው ተናግረዋል። ሆኖም እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር በማለታቸውና ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ ከእሱ በማግኘታቸው ድክመታቸውን ማሸነፍ ችለዋል።—መዝ. 37:23, 24፤ w15 10/15 1:10, 11
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 21
ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።—ኤፌ. 5:16
አንዳንዶች ለማንበብ፣ ለማሰላሰልና ለመጸለይ በማለዳ ይነሳሉ። ሌሎች በምሳ እረፍታቸው ወቅት እንዲህ ያደርጋሉ። አንተ ደግሞ አመሻሹ ላይ ወይም ከመተኛትህ በፊት ታሰላስል ይሆናል። አንዳንዶች ጠዋት እንዲሁም ማታ ከመተኛታቸው በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ያነብባሉ። በመሆኑም “ቀንም ሆነ ሌሊት” በሌላ አባባል አዘውትረው የአምላክን ቃል ‘ያነብባሉ’ ሊባል ይችላል። (ኢያሱ 1:8) ዋናው ቁም ነገር፣ በአምላክ ቃል ላይ ለማሰላሰል እምብዛም አስፈላጊ ካልሆኑ ነገሮች ላይ ጊዜ መግዛት መቻላችን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአምላክ ቃል ላይ የሚያሰላስሉና የተማሩትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚጥሩ ሰዎች በረከት እንደሚያገኙ ደጋግሞ ይናገራል። (መዝ. 1:1-3) ኢየሱስ “ደስተኞችስ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው!” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 11:28) ከሁሉም በላይ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ በየዕለቱ ማሰላሰላችን አእምሯችንን ድንቅ አድርጎ ለፈጠረው አምላክ ክብር ያመጣል፤ እሱም በአሁኑ ጊዜ ደስተኛ እንድንሆን ያደርገናል፤ ወደፊት ደግሞ ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት በመስጠት ይባርከናል።—ያዕ. 1:25፤ ራእይ 1:3፤ w15 10/15 4:17, 18
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 22
ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው በመውሰድ “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን፤ በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” እያለ ይገሥጸው ጀመር።—ማቴ. 16:22
ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስን በራሱ ላይ እንዳይጨክን ይኸውም ራሱን ለሞት አሳልፎ እንዳይሰጥ የመከረው ለእሱ አስቦ ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ የተናገረው ነገር የተሳሳተ አመለካከት እንዳለው የሚጠቁም መሆኑን አስተውሏል። ኢየሱስ ጴጥሮስንና ሌሎች ደቀ መዛሙርቱን ለመጥቀም ሲል ግልጽ ምክር ሰጥቷል፤ ለራስ መሳሳት ምን እንደሚያስከትል የተናገረ ከመሆኑም ሌላ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚያስገኘውን በረከት ጠቁሟል። (ማቴ. 16:21-27) ጴጥሮስ ከዚህ ምክር ጥቅም እንዳገኘ ግልጽ ነው። (1 ጴጥ. 2:20, 21) በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ በየትኛው አቅጣጫ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ለመረዳት የሚያስችል ማስተዋል እንዲሰጣችሁ ወደ ይሖዋ ጸልዩ። (መዝ. 32:8) ለምሳሌ የልጃችሁ እምነት እየተዳከመ እንደመጣ የሚጠቁሙ ነገሮች ምንድን ናቸው? ደስታው እየጠፋ እንደሆነ፣ የእምነት ባልንጀሮቹን መተቸት እንደጀመረ ወይም ድብቅ እየሆነ እንደመጣ አስተውላችሁ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ነገሮች ‘ከባድ ኃጢአት ፈጽሞ ሁለት ዓይነት ሕይወት እየመራ መሆኑን የሚጠቁሙ ናቸው’ ብላችሁ ለመደምደም አትቸኩሉ። በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን ምልክቶች በቸልታ አትለፏቸው፤ ወይም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ራሱን ማግለሉ በዚህ ዕድሜ የሚያጋጥም የተለመደ ነገር እንደሆነ በማሰብ ሁኔታውን አቅልላችሁ አትመልከቱት። w15 11/15 2:12, 13
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 23
ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ። . . . ፍቅርን ልበሱ፤ ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነውና።—ቆላ. 3:12, 14
የይሖዋ አገልጋዮች በመካከላቸው እውነተኛ ፍቅርና አንድነት መኖሩ የእውነተኛው ሃይማኖት ተከታዮች መሆናቸውን ያሳውቃል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐ. 13:34, 35) ሐዋርያው ዮሐንስም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የአምላክ ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ በግልጽ ይታወቃሉ፦ በጽድቅ ጎዳና የማይመላለስ ሁሉ የአምላክ ወገን አይደለም፤ ወንድሙን የማይወድም የአምላክ ወገን አይደለም። ከመጀመሪያ የሰማችሁት መልእክት እርስ በርሳችን መዋደድ አለብን የሚል ነውና።” (1 ዮሐ. 3:10, 11) የይሖዋ ምሥክሮች የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች መሆናቸውን የሚያሳውቀው፣ ልዩ የሆነ አንድነት የሚያስገኝ ፍቅር ያላቸው መሆኑ ነው፤ ይሖዋ እነዚህን ሕዝቦች በመላው ምድር የመንግሥቱን ምሥራች ለማወጅ እየተጠቀመባቸው ነው።—ማቴ. 24:14፤ w15 11/15 4:10, 11
እሁድ፣ ታኅሣሥ 24
በተገቢው ጊዜ የተነገረ ቃል ከብር በተሠራ ዕቃ ላይ እንዳለ የወርቅ ፖም ነው።—ምሳሌ 25:11
የሰዎች ባሕልና ሃይማኖት ከቦታ ቦታ የሚለያይ በመሆኑ ለመናገር ተገቢ የሆነውን ጊዜ ስንመርጥ አስተዋዮች መሆን አለብን። እንዲህ ማድረግ አስፈላጊ የሚሆንባቸው በርካታ ሁኔታዎች አሉ። ለምሳሌ አንድ ሰው መልካም አስቦ የተናገረው ነገርም እንኳ ቅር ሊያሰኘን ይችላል። የጉዳዩን ክብደት ለማጤንና ግለሰቡን ልናነጋግረው ይገባ እንደሆነ ለመወሰን ጊዜ ወስደን ማሰባችን አስተዋይነት ነው። ቅር ያሰኘንን ሰው ለማነጋገር ከወሰንን፣ በተበሳጨንበትና ነገሮችን ሳናመዛዝን ልንናገር በምንችልበት ወቅት መናገራችን ጥበብ አይሆንም። (ምሳሌ 15:28) በተመሳሳይም ለማያምኑ ዘመዶቻችን እውነትን ስንነግራቸው አስተዋይ መሆን አለብን። ይሖዋን እንዲያውቁ እንደምንፈልግ ግልጽ ነው፤ ሆኖም ትዕግሥተኛ መሆንና ነገሮችን ማመዛዘን ይኖርብናል። በተገቢው ጊዜ ተገቢውን ቃል መናገራችን ልባቸው እንዲነካ ሊያደርግ ይችላል። w15 12/15 3:6, 8, 9
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 25
በዚህ ሥርዓት ውስጥ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ፣ . . . እንድንኖር ያሠለጥነናል።—ቲቶ 2:12
አንድ የሕክምና ዘዴ ከተለመደው ወጣ ያለ ወይም ሚስጥራዊ በሚመስልበት ጊዜ “ጤናማ አስተሳሰብ” መያዝ ወይም አስተዋይ መሆን በጣም አስፈላጊ ይሆናል። ሕክምናውን የሚሰጠው ወይም የሚያስተዋውቀው ግለሰብ ይህ ሕክምና እንዴት እንደሚሠራ አጥጋቢ በሆነ መንገድ ማብራራት ይችላል? ይህ ሕክምና ተቀባይነት ካላቸው እውነታዎች ጋር ይስማማል? ደግሞስ ብቃት ባላቸው ብዙ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት አለው? (ምሳሌ 22:29) ወይስ ግለሰቡ በስሜት ተነሳስተን ውሳኔ እንድናደርግ እየገፋፋን ነው? ምናልባትም ሕክምናው የተገኘው ወይም ጥቅም ላይ የዋለው ራቅ ባለ ቦታ እንደሆነና ዘመናዊ ሕክምና ገና እንዳልደረሰበት ይነገር ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ያለ ሕክምና መኖሩን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች አሉ? አንዳንድ የሕክምና መሣሪያዎች ወይም ዘዴዎች ደግሞ ‘ሚስጥራዊ ንጥረ ነገሮችን’ ወይም ‘የማይታወቅ ኃይልን’ እንደሚጠቀሙ ይገለጻል። እንዲህ ዓይነቱ ሕክምና አደገኛ ሊሆን ይችላል፤ አምላክ ‘ከአስማታዊ ድርጊት’ እና ከመናፍስት ጠሪዎች እንድንርቅ እንደሚያስጠነቅቀን ማስታወስ አስፈላጊ ነው።—ኢሳ. 1:13፤ ዘዳ. 18:10-12፤ w15 12/15 4:16
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 26
ከሴት ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም፤ ሆኖም በመንግሥተ ሰማያት ዝቅተኛ የሆነው እንኳ ይበልጠዋል።—ማቴ. 11:11
ቅዱሳን መጻሕፍትን ስንመረምር መንፈስ ቅዱስ የተሰጣቸው በርካታ የእምነት ሰዎችን እናገኛለን፤ ያም ሆኖ እነዚህ ሰዎች በሰማይ የመኖር ተስፋ አልነበራቸውም። እንዲህ ካሉት ሰዎች መካከል መጥምቁ ዮሐንስ አንዱ ነው። ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስን በእጅጉ ያደነቀው ቢሆንም ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደማይገባ ተናግሯል። ዳዊትም የይሖዋን መንፈስ አግኝቶ ነበር። (1 ሳሙ. 16:13) ዳዊት ጥልቅ መንፈሳዊ እውቀት ያለው ሰው ከመሆኑም ባሻገር አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (ማር. 12:36) ያም ሆኖ ጴጥሮስ በጴንጤቆስጤ ዕለት “ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣም” ብሏል። (ሥራ 2:34) መንፈስ ቅዱስ በእነዚህ ሰዎች በመጠቀም ታላቅ ሥራ አከናውኗል፤ ሆኖም በሰማይ ሕይወት ለማግኘት መመረጣቸውን የሚያሳየውን ልዩ ምሥክርነት አልሰጣቸውም። ይህ መሆኑ ግን ብቃት ጎድሏቸዋል ወይም እንከን አለባቸው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ከሞት አስነስቶ በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል ማለት ነው።—ዮሐ. 5:28, 29፤ ሥራ 24:15፤ w16.01 3:16
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 27
እኔና አብ አንድ ነን።—ዮሐ. 10:30
ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር አብረን ስንሠራ ይበልጥ የምንቀራረብ ከመሆኑም ሌላ ስለ እነሱ በደንብ ማወቅ እንችላለን። ምን ማከናወን እንደሚፈልጉ ብቻ ሳይሆን ይህን የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነም ጭምር መረዳት እንችላለን። ኢየሱስ ከይሖዋ ጋር በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት አብሮ ሳይሠራ አይቀርም፤ በመሆኑም አንዳቸው ለሌላው በጣም ጥልቅ ፍቅር አዳብረዋል፤ እንዲሁም ፈጽሞ ሊበጠስ የማይችል ጠንካራ ወዳጅነት መሥርተዋል። በመካከላቸው አስደናቂ አንድነት ያለ ሲሆን ምንጊዜም የሚሠሩት ፍጹም ስምም ሆነው ነው። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን እንዲጠብቃቸው ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? “እኛ አንድ እንደሆንን ሁሉ እነሱም አንድ እንዲሆኑ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 17:11) ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን ስንኖርና በስብከቱ ሥራ ስንካፈል የይሖዋን አስደናቂ ባሕርያት መረዳት እንችላለን። በእሱ መታመንም ሆነ መመሪያውን መከተል የጥበብ እርምጃ የሆነበትን ምክንያት እንገነዘባለን። ወደ አምላክ ስንቀርብ እሱም ወደ እኛ ይቀርባል። (ያዕ. 4:8) በተጨማሪም ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር እንቀራረባለን፤ ምክንያቱም የሚያጋጥሙን ችግሮች፣ አስደሳች ነገሮች እንዲሁም ግቦቻችን ተመሳሳይ ናቸው። w16.01 5:9, 10
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 28
የባልሽ ወንድም ሚስት ወደ ወገኖቿና ወደ አማልክቷ ተመልሳለች። አብረሻት ተመለሽ።—ሩት 1:15
ናኦሚ ወደ ትውልድ አገሯ ወደ እስራኤል የጀመረችውን ጉዞ ለመቀጠል ቆርጣለች። ከእሷ ጋር የቀረችው ሩት በሕይወቷ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ውሳኔ ተደቅኖባታል። ወደ አገሯና ወደ ሕዝቧ ከመመለስ አሊያም ከአማቷ ከናኦሚ ጋር ወደ ቤተልሔም ከመጓዝ አንዱን መምረጥ ይኖርባታል። (ሩት 1:1-8, 14) ወጣት መበለት የሆነችው ሩት፣ በሞዓብ ቤተሰቦቿ ስላሉ እናቷና ሌሎች ዘመዶቿ ሊያስጠጓት ብሎም ሊንከባከቧት እንደሚችሉ ማሰብ ትችል ነበር። ሞዓብ የትውልድ አገሯ ነው። ባሕሉ፣ ቋንቋውም ሆነ ሕዝቡ ለእሷ አዲስ አይደለም። ሩት በቤተልሔም እነዚህን ነገሮች እንደምታገኝ ናኦሚ ቃል ልትገባላት አትችልም። ናኦሚም ብትሆን ሩትን የመከረቻት በሞዓብ እንድትቀር ነው። ናኦሚ፣ ምራቶቿ ትዳርም ሆነ የራሳቸው ኑሮ እንዲኖራቸው ልትረዳቸው ስለመቻሏ ስጋት አድሮባታል። ታዲያ ሩት ምን ታደርግ ይሆን? “ወደ ወገኖቿና ወደ አማልክቷ” በተመለሰችው በዖርፋና በሩት መካከል ያለውን ልዩነት ልብ በል። (ሩት 1:9-15) ሩት ወገኖቿ ወደሚያመልኳቸው የሐሰት አማልክት ለመመለስ ትወስን ይሆን? በፍጹም እንዲህ አላደረገችም። w16.02 2:4, 5
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 29
ይሖዋ ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን እንድታደርግ፣ ታማኝነትን እንድትወድና ልክህን አውቀህ ከአምላክህ ጋር እንድትሄድ ብቻ ነው!—ሚክ. 6:8
ዳዊትና አቢሳ፣ በውድቅት ሌሊት ጭልጥ ያለ እንቅልፍ በወሰዳቸው 3,000 ወታደሮች መካከል ኮቴያቸውን አጥፍተው እየተጓዙ ነው። ሁለቱ ሰዎች፣ ንጉሥ ሳኦል በጦር ሰፈሩ መሃል ድብን ያለ እንቅልፍ ወስዶት አገኙት። ሳኦል ዳዊትን አግኝቶ ለመግደል በይሁዳ ምድረ በዳ ሲጓዝ ነበር። አቢሳ “አንድ ጊዜ ብቻ [ሳኦልን] በጦር ወግቼ ከመሬት ጋር ላጣብቀው፤ መድገም አያስፈልገኝም” በማለት በሹክሹክታ ተናገረ። ዳዊት የሰጠው መልስ ግን የሚያስገርም ነበር! እንዲህ አለው፦ “ጉዳት እንዳታደርስበት፤ ለመሆኑ ይሖዋ በቀባው ላይ እጁን አንስቶ ከበደል ነፃ የሚሆን ማን ነው? . . . በእኔ በኩል ይሖዋ በቀባው ላይ እጄን ማንሳት በይሖዋ ዓይን ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው!” (1 ሳሙ. 26:8-12) ዳዊት ለአምላክ ታማኝ መሆን ሲባል ምን ነገሮችን እንደሚጨምር ተገንዝቦ ነበር። ሳኦልን የመጉዳት ሐሳብ አልነበረውም። ለምን? ምክንያቱም ሳኦል በአምላክ የተቀባ የእስራኤል ንጉሥ ነበር። የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች እሱ ለሾማቸው ሰዎች አክብሮት አላቸው። በእርግጥም ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ ሁሉ ‘ታማኝነትን እንዲወዱ’ ይጠብቅባቸዋል። w16.02 4:1, 2
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 30
አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል።—መዝ. 40:8
ለመጠመቅ እያሰብክ ያለህ ወጣት ነህ? ከሆነ ይህ በሕይወትህ ልታገኘው ከምትችለው መብት ሁሉ እጅግ የላቀው ነው። ሆኖም ጥምቀት ትልቅ እርምጃ ነው። የይሖዋን ፈቃድ በሕይወትህ ውስጥ ከማንኛውም ነገር በላይ በማስቀደም እሱን ለዘላለም ለማገልገል ቃል መግባትህን በሌላ አባባል ራስህን መወሰንህን ያሳያል። መጠመቅ የሚኖርብህ ይህን ውሳኔ ለማድረግ ብቃቱን ስታሟላ፣ በራስህ ተነሳሽነት ለመጠመቅ ፍላጎቱ ሲኖርህ እንዲሁም ራስን መወሰን ምን ትርጉም እንዳለው ስትረዳ እንደሆነ ግልጽ ነው። ለመጠመቅ ዝግጁ እንደሆንክ የማይሰማህ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? አሊያም ደግሞ አንተ መጠመቅ ብትፈልግም ወላጆችህ ግን መቆየት እንዳለብህ የሚሰማቸው ቢሆንስ? ምናልባትም እንዲህ ያሉት በክርስቲያናዊ ሕይወት ትንሽ ተሞክሮ እንድታገኝ አስበው ሊሆን ይችላል። ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ተስፋ አትቁረጥ። ከዚህ ይልቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጠመቅ ብቁ እንድትሆን አጋጣሚውን እድገት ለማድረግ ተጠቀምበት። w16.03 2:1, 2
እሁድ፣ ታኅሣሥ 31
ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ።—2 ቆሮ. 6:14
አንዳንዶች እውነትን የሰሙት ትዳር ከመሠረቱ በኋላ በመሆኑ የትዳር ጓደኛቸው የይሖዋ ምሥክር ላይሆን ይችላል። ይሁንና በዚህም ሁኔታ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ቤተሰቡ አንድነት እንዲኖረው ይረዳል። ይህም ክርስቲያናዊ አቋምን ሳያላሉ አቅም በፈቀደ መጠን የትብብር መንፈስ ማሳየትን ያካትታል። እርግጥ ይህ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም እንዲህ ማድረግ የሚያስገኘውን ጥቅም አስብ። በተጨማሪም ሰይጣን በቤተሰቦች ላይ ጥቃት እየሰነዘረ በመሆኑ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ በትዳራቸው ውስጥ ጥሩ የትብብር መንፈስ ማሳየታቸው አስፈላጊ ነው። በትዳር ዓለም የቆያችሁት ለምንም ያህል ዓመታት ቢሆን ትዳራችሁን ለማጠናከር በግለሰብ ደረጃ በቃልም ሆነ በተግባር ምን ማድረግ እንደምትችሉ ቆም ብላችሁ አስቡ። በዚህ ረገድ በዕድሜ የጎለመሱ የጉባኤው አባላት ከእነሱ በዕድሜ ለሚያንሱት ድጋፍ ማድረግ፣ ለምሳሌ አንዳንድ ጊዜ ወጣት ባለትዳሮች በቤተሰብ አምልኳቸው ላይ እንዲገኙ ቤታቸው መጋበዝ ይችላሉ። ወጣት ባለትዳሮች ከእናንተ ጋር ጊዜ ሲያሳልፉ አንድ ሰው በትዳር ውስጥ ምንም ያህል ረጅም ጊዜ ቢኖር ፍቅርና አንድነት ትልቅ ዋጋ እንዳላቸው ሊያስተውሉ ይችላሉ።—ቲቶ 2:3-7፤ w16.03 3:14, 15