ኅዳር
ረቡዕ፣ ኅዳር 1
አብርሃም እስትንፋሱ ቀጥ አለ፤ ሸምግሎ፣ በሕይወቱ ረክቶና ዕድሜ ጠግቦ ሞተ።—ዘፍ. 25:8
አብርሃም “በሕይወቱ ረክቶና ዕድሜ ጠግቦ” እንደሞተ ስናነብ ወደፊት ለመኖር እንደማይጓጓ ልናስብ አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አብርሃም ሲናገር “አምላክ ንድፍ ያወጣላትንና የገነባትን፣ እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር” ይላል። (ዕብ. 11:10) አብርሃም ገነት በሆነችው ምድር ላይ መኖር እንዲሁም ከይሖዋ ጋር ያለውን ወዳጅነት ምንጊዜም ማጠናከር ምን ያህል ሊያስደስተው እንደሚችል መገመት ትችላለህ! አብርሃም የተወው የእምነት ምሳሌ፣ እሱ ከሞተ በኋላ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የይሖዋ አገልጋዮችን እንደረዳ ሲያውቅ በጣም እንደሚደሰት ግልጽ ነው! አብርሃም፣ ይስሐቅን ከሞት አፋፍ መልሶ ማግኘቱ ከዚያ ለላቀ ነገር “እንደ ምሳሌ ሆኖ” እንዳገለገለም በገነት በሚኖርበት ጊዜ ይገነዘባል። (ዕብ. 11:19) በተጨማሪም ይስሐቅን መሥዋዕት ለማድረግ ሲዘጋጅ የተሰማው ሥቃይ ይሖዋ፣ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት በሆነበት ወቅት የተሰማውን ሥቃይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ታማኝ ሰዎች እንዲገነዘቡ ረድቷል፤ አብርሃም በገነት ውስጥ ሲኖር ይህንንም ያውቃል።—ዮሐ. 3:16፤ w16.02 1:15, 16
ሐሙስ፣ ኅዳር 2
አንተ የዚያች ዓመፀኛ ሴት ልጅ፣ በራስህም ሆነ በእናትህ ላይ ውርደት ለማምጣት ከእሴይ ልጅ ጋር መወገንህን የማላውቅ መሰለህ?—1 ሳሙ. 20:30
ኃላፊነት ያለው አንድ ሰው ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲፈጽምብን ለአምላክ ያለን ታማኝነት ሊፈተን ይችላል። ዮናታን እንዲህ ያለ ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሞት ሊሆን ይችላል። አምላክ የቀባው ንጉሥ ሳኦል፣ ልጁ ከዳዊት ጋር ጓደኝነት እንደመሠረተ ቢገነዘብም ይህን ያደረገው ለምን እንደሆነ አልገባውም ነበር። በመሆኑም ሳኦል ዮናታንን ተቆጥቶ ኃይለ ቃል በመናገር አዋረደው። ያም ሆኖ ዮናታን አጸፋውን አልመለሰም። ለአምላክም ሆነ ከጊዜ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ ለሚሆነው ለዳዊት ያለውን ታማኝነት አላጓደለም። (1 ሳሙ. 20:31-41) በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ተገቢ ያልሆነ ነገር ሊፈጸምብን የሚችልበት አጋጣሚ በጣም ጠባብ ነው። ሆኖም በመካከላችን ሆነው አመራር የሚሰጡን ወንድሞች ፍጹም ባለመሆናቸው፣ የምናደርገውን ነገር በተሳሳተ መንገድ ሊረዱት ይችላሉ። (1 ሳሙ. 1:13-17) ሰዎች ተገቢ ያልሆነ ነገር በሚፈጽሙብን ወይም በተሳሳተ መንገድ በሚረዱን ጊዜም ለይሖዋ ታማኝ መሆናችንን እንቀጥል። w16.02 3:14, 15
ዓርብ፣ ኅዳር 3
ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ የራሱን የመከራ እንጨት ይሸከም።—ማቴ. 16:24
አንዳንዶች ራስን በመወሰንና በመጠመቅ መካከል ያለው ልዩነት በግልጽ ላይገባቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ወጣቶች ራሳቸውን ለይሖዋ እንደወሰኑ፣ ለመጠመቅ ግን ዝግጁ እንዳልሆኑ ይናገራሉ። ይህ አባባል ያስኬዳል? ራስን መወሰን ማለት ይሖዋን ለዘላለም እንደምታገለግለው በጸሎት መንገር ማለት ነው። አንድ ሰው ሲጠመቅ፣ ራሱን መወሰኑን ሌሎች እንዲያውቁ ያደርጋል። በመሆኑም ጥምቀት፣ ለይሖዋ ባቀረብከው የግል ጸሎት አማካኝነት ቀደም ሲል ራስህን መወሰንህን ሰዎች እንዲያውቁ ማድረግ ማለት ነው። ከመጠመቅህ በፊት ራስን መወሰን ምን ትርጉም እንዳለው በሚገባ መረዳት ይኖርብሃል። በቀላል አነጋገር፣ ራስህን ለይሖዋ ስትወስን ሕይወትህ የአንተ ንብረት መሆኑ ያበቃል ማለት ነው። በሕይወትህ ውስጥ የይሖዋን ፈቃድ ከምንም ነገር በላይ እንደምታስቀድም በመግለጽ ለእሱ ቃል ትገባለህ። መቼም ቢሆን ቃል ስትገባ ጉዳዩን አክብደህ ማየት ይኖርብሃል፤ ይህ ከሆነ ታዲያ ለይሖዋ አምላክ የምትገባውን ቃል እጅግ አክብደህ ልታየው አይገባም?—ማቴ. 5:33፤ w16.03 1:14, 15
ቅዳሜ፣ ኅዳር 4
በሁሉም ነገር . . . በፍቅር እንደግ።—ኤፌ. 4:15
ጳውሎስ የሰውን አካል እንደ ምሳሌ በመጥቀስ የጉባኤው ራስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር አንድነት ሊኖረን እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጿል። ሐዋርያው “አስፈላጊ የሆነውን ነገር በሚያሟላው በእያንዳንዱ መገጣጠሚያ አማካኝነት” መተባበር እንደሚያስፈልግ ተናግሯል። (ኤፌ. 4:16) ልጅ አዋቂ፣ ብርቱ ደካማ ሳይል ሁላችንም ለጉባኤው አንድነትና መንፈሳዊነት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው? ቁልፉ ነገር ኢየሱስ በጉባኤ ውስጥ አመራር እንዲሰጡ የሾማቸውን ሽማግሌዎች ማክበርና ለእነሱ መገዛት ነው። (ዕብ. 13:7, 17) እርግጥ እንዲህ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል። ነገር ግን አምላክ እንደሚረዳን እርግጠኛ በመሆን አመራሩን መጠየቅ እንችላለን። ቅዱስ መንፈሱ የጉባኤውን ዝግጅቶች በሙሉ ልባችን መደገፍ እንድንችል ይረዳናል። ስለዚህ የተሰጠንን አመራር መከተል ከባድ በሚሆንብን ጊዜ በትሕትና መንፈስ ተባባሪ መሆናችን ለጉባኤው አንድነት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ማሰብ ይኖርብናል። በተጨማሪም በዚህ ረገድ መተባበራችን ሁላችንም በፍቅር እንድናድግ ሊረዳን ይችላል። w16.03 3:8, 9
እሁድ፣ ኅዳር 5
የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው።—ዕብ. 4:12
አንዳንድ ወጣቶች በልጅነታቸው መንፈሳዊ ግብ እንዲያወጡ ማበረታቻ አልተሰጣቸውም። እንዲህ ያሉ ወጣቶች በሕይወታቸው ውስጥ ለእውነት ቅድሚያ መስጠት የሚለው ጉዳይ ፈጽሞ አይታያቸውም። (ማቴ. 10:24) በመሆኑም አንድ ሽማግሌ፣ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት እንዲቀበል የሚያስበው ወንድም በጉባኤው ውስጥ ተፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘብ ለማድረግና ከእሱ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ጊዜ ይመድባል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ሽማግሌው ከወንድም ጋር በአንዳንድ ጥቅሶች ላይ በመወያየት ለይሖዋ የገባውን ቃል እንዲያስታውስ ይረዳዋል። (መክ. 5:4፤ ኢሳ. 6:8፤ ማቴ. 6:24, 33፤ ሉቃስ 9:57-62፤ 1 ቆሮ. 15:58፤ 2 ቆሮ. 5:15፤ 13:5) ሽማግሌው ‘ራስህን ለይሖዋ ስትወስን ምን ቃል ገብተህ ነበር?’ ብሎ ሊጠይቀው ይችላል። ‘በተጠመቅክ ጊዜ ይሖዋ ምን ተሰምቶት የነበረ ይመስልሃል?’ ብሎ በመጠየቅ የቀድሞ ፍቅሩ እንዲቀሰቀስ ማድረግ ይችላል። (ምሳሌ 27:11) ከዚያም ‘ሰይጣንስ ምን ተሰምቶት ነበር?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት ይችላል። (1 ጴጥ. 5:8) ሽማግሌዎች በደንብ የታሰበበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማንበባቸው በወንድም ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በፍጹም አቅልለው መመልከት የለባቸውም። w15 4/15 2:9, 11
ሰኞ፣ ኅዳር 6
የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።—1 ጴጥ. 5:7
ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ ለምንጠይቀው ነገር አፋጣኝ ምላሽ የማይሰጠን ለምንድን ነው? ይሖዋ ከእሱ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና በአባትና በልጅ መካከል ካለው ግንኙነት ጋር እንዳመሳሰለው አስታውስ። (መዝ. 103:13) አንድ ልጅ፣ የሚጠይቀውን ነገር ሁሉ ወላጆቹ እንዲያደርጉለት ወይም ፍላጎቱን በሙሉ ወዲያውኑ እንዲያሟሉለት መጠበቁ ተገቢ አይሆንም። ልጁ አንዳንድ ነገሮችን የሚጠይቀው በስሜታዊነት በመሆኑ ብዙም ሳይቆይ ይረሳዋል። የሚጠይቃቸውን ሌሎች ነገሮች ለማድረግ ደግሞ ተገቢው ጊዜ እስኪደርስ መጠበቅ ያስፈልግ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ልጁ የሚፈልገው ነገር እሱንም ሆነ ከእሱ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሌሎች ሰዎች የሚጎዳ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ወላጆች ልጁ የጠየቀውን ነገር ሁሉ ካደረጉለት ግንኙነታቸው የጌታና የባሪያ ዓይነት ይሆንና ልጁ አዛዥ ሆኖ ቁጭ ይላል። በተመሳሳይም ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ ከመስጠቱ በፊት የተወሰነ ጊዜ እንዲያልፍ የሚያደርገው ለእኛ ጥቅም ሲል ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ጥበበኛ ፈጣሪያችን፣ አፍቃሪ ጌታችንና ሰማያዊ አባታችን እንደ መሆኑ መጠን ይህን የማድረግ መብት አለው። የጠየቅነውን ሁሉ ወዲያውኑ የሚያደርግልን ከሆነ በመካከላችን ያለው ግንኙነት ትክክለኛውን አካሄድ የጠበቀ አይሆንም።—ኢሳ. 29:16፤ 45:9፤ w15 4/15 4:6, 7
ማክሰኞ፣ ኅዳር 7
ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል።—ያዕ. 4:7
ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እየተቃረብን በመሆኑ ሰይጣን እንድንዘናጋ ይኸውም ‘በራሳችን ላይ ከመጨከን’ ይልቅ በዚህ ዓለም ውስጥ ለእኛ ተስማሚ የሆነውን ቦታ ለማግኘት በመጣር የጥድፊያ ስሜታችንን እንድናጣ ይፈልጋል። ይህ እንዲደርስባችሁ አትፍቀዱ! ከዚህ ይልቅ “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።” (ማቴ. 16:22, 23፤ 24:42) ሰይጣን፣ መጨረሻው ሩቅ እንደሆነ ወይም ጨርሶ እንደማይመጣ ለሚያስፋፋው አታላይ ፕሮፓጋንዳ ፈጽሞ ጆሮ አትስጡ። ሰይጣን አምላክ ሊወደን እንደማይችልና ኃጢአታችን ይቅር የማይባል እንደሆነ ሊያሳምነን ይፈልጋል። ሰይጣን ከሚያስፋፋው አታላይ ፕሮፓጋንዳ አንዱ ይህ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ይሖዋ በፍጹም ሊወደው የማይችለው አካል ማን ነው? ሰይጣን ነው። በጭራሽ ይቅር ሊባል የማይችለውስ ማን ነው? አሁንም ሰይጣን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ዕብ. 6:10) ይሖዋ እሱን ለማስደሰት የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል፤ ለእሱ የምናቀርበው አገልግሎትም ከንቱ አይደለም። (1 ቆሮ. 15:58) እንግዲያው በሰይጣን አታላይ ፕሮፖጋንዳ ላለመታለል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። w15 5/15 1:16-19
ረቡዕ፣ ኅዳር 8
ከሩቅ አይተው በደስታ ተቀበሉት።—ዕብ. 11:13
አብርሃም ተስፋ የሚያደርገው ነገር እውን እንደሚሆን የሚያረጋግጥ ብዙ ማስረጃ ስለነበረው ገና ያላየውን ነገር እንኳ በዓይነ ሕሊናው መሳል ችሏል! አብርሃም፣ አምላክ ቃል በገባው ነገር ላይ ያለው እምነት መለኮታዊውን ፈቃድ ለመፈጸም ብርታት ሰጥቶታል። ዑርን ለቆ የወጣውና በሄደባቸው የከነዓን ከተሞች ውስጥ ቋሚ መኖሪያ ሳያበጅ የኖረው እምነት ስለነበረው ነው። እንደ ዑር ሁሉ የእነዚህ ከተሞች ገዢዎችም ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች በመሆናቸው ከተሞቹ መጥፋታቸው እንደማይቀር ተገንዝቦ ነበር። (ኢያሱ 24:2) አብርሃም በኖረባቸው በርካታ ዓመታት ሁሉ “አምላክ ንድፍ ያወጣላትንና የገነባትን፣ እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር።” (ዕብ. 11:10) አብርሃም፣ ዘላለማዊ በሆነና ይሖዋ በሚያስተዳድረው ቦታ ሲኖር ይታየው ነበር። አቤል፣ ሄኖክ፣ ኖኅ፣ አብርሃምና እንደ እነሱ ያሉ ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ሙታን እንደሚነሱ ያምኑ ነበር፤ እንዲሁም ‘እውነተኛ መሠረት ባለው ከተማ’ ይኸውም በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በምድር ላይ ለመኖር ይጓጉ ነበር። እነዚህ ሰዎች እንደዚህ ባሉት በረከቶች ላይ ማሰላሰላቸው በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት አጠናክሮላቸዋል።—ዕብ. 11:15, 16፤ w15 5/15 3:8, 9
ሐሙስ፣ ኅዳር 9
[ክርስቶስ] የአምላክ ኃይል . . . ነው።—1 ቆሮ. 1:24
ይሖዋ ኃይሉን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በአስደናቂ መንገዶች አሳይቷል። አራቱ ወንጌሎች ክርስቶስ ስላከናወናቸው አንዳንድ ተአምራት የያዟቸው ዝርዝር ዘገባዎች እምነት የሚያጠናክሩ ናቸው። ኢየሱስ ተመዝግበው ከምናገኛቸው በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ተአምራትንም እንደፈጸመ ግልጽ ነው። (ማቴ. 9:35፤ ሉቃስ 9:11) በእርግጥም የአምላክ ኃይል በኢየሱስ በኩል ተገልጧል። ሐዋርያው ጳውሎስም ‘ክርስቶስ የአምላክ ኃይል ነው’ ብሎ ለመናገር በቂ ምክንያት ነበረው። ይሁንና ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ለእኛ ምን ትርጉም አላቸው? ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ተአምራት እና “ድንቅ ነገሮች” እንዳከናወነ ተናግሯል። (ሥራ 2:22) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የፈጸማቸው ተአምራት በንጉሣዊ አገዛዙ ወቅት ለምናገኛቸው የላቁ በረከቶች እንደ ቅምሻ ናቸው። እንዲሁም በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚፈጽማቸው ተአምራት ጥላ ናቸው! ከዚህም በተጨማሪ የኢየሱስ ተአምራት ስለ እሱም ሆነ ስለ አባቱ ባሕርይ ጥልቅ ማስተዋል ይሰጡናል። w15 6/15 1:1, 2
ዓርብ፣ ኅዳር 10
“ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ” ብላ ታስብ ነበር።—ማር. 5:28
ኢየሱስ፣ ሴትየዋን የፈወሳት አባቱ ይሖዋ እንደሆነ ስለተገነዘበ በደግነት “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ፤ ከሚያሠቃይ ሕመምሽም ተፈወሽ” አላት። (ማር. 5:34) ኢየሱስ እንዴት ደግ ነው! በሕመም ለሚሠቃዩ ሰዎች የሚራራ አንጀት እንዳለው መመልከት እንችላለን። ሰይጣን የማንፈለግና ዋጋ የሌለን ሆኖ እንዲሰማን ለማድረግ ይጥራል። ይሁንና ኢየሱስ ስለ እኛም ሆነ ስላሉብን ችግሮች እንደሚያስብ በፈጸማቸው ተአምራት አማካኝነት በግልጽ አሳይቷል። ንጉሣችንና ሊቀ ካህናችን ምንኛ ሩኅሩኅ ነው! (ዕብ. 4:15) ከባድ የጤና እክል ያለባቸውን ሰዎች ስሜት መረዳት፣ በተለይ ደግሞ እኛ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞን የማያውቅ ከሆነ ይቸግረን ይሆናል። ኢየሱስ ግን እሱ ራሱ ታሞ ባያውቅም እንኳ የታመሙ ሰዎችን ስሜት ይረዳ እንደነበር ማስታወስ ይኖርብናል። የኢየሱስ ምሳሌ እኛም አቅማችን በሚፈቅደው መጠን እንዲሁ እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል።—1 ጴጥ. 3:8፤ w15 6/15 2:11, 12
ቅዳሜ፣ ኅዳር 11
በእናንተ ምክንያት የአምላክ ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባል።—ሮም 2:24
የአምላክን የግል ስም ከማወቅም አልፈን “ለስሙ የሚሆኑ ሰዎች” በመሆን በስሙ መጠራታችን ምንኛ ታላቅ መብት ነው። (ሥራ 15:14፤ ኢሳ. 43:10) በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን “ስምህ ይቀደስ” ብለን እንለምነዋለን። (ማቴ. 6:9) እንዲህ ያለ ልመና ማቅረብህ፣ ቅዱስ የሆነውን የይሖዋን ስም የሚያስነቅፍ ነገር ላለመናገር ወይም ላለማድረግ እንዲረዳህ እሱን ለመጠየቅ ሊያነሳሳህ ይችላል። በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ እንደተገለጸው በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት የሚሰብኩትን ነገር ተግባራዊ እንዳላደረጉት ክርስቲያኖች መሆን እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። የአምላክ ስም ሙሉ በሙሉ እንዲቀደስና ከደረሰበት ነቀፋ ሁሉ ነፃ እንዲሆን ምን ያስፈልጋል? ይሖዋ የእሱን ሉዓላዊነት ሆን ብለው የሚቃወሙትን ሁሉ ማጥፋት ያስፈልገዋል። (ሕዝ. 38:22, 23) ከዚያም የሰው ዘር ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና ይደርሳል። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት በሙሉ የይሖዋን ስም የሚያስቀድሱበትን ጊዜ ለማየት ምንኛ እንጓጓለን! በመጨረሻም አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን “ለሁሉም ሁሉንም ነገር” ይሆናል።—1 ቆሮ. 15:28፤ w15 6/15 4:7, 10
እሁድ፣ ኅዳር 12
ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድር ደግሞ የእግሬ ማሳረፊያ ናት።—ኢሳ. 66:1
“የእግር ማሳረፊያ” የሚለው አገላለጽ ከምድርም በተጨማሪ እስራኤላውያን ይጠቀሙበት የነበረውን የጥንቱን ቤተ መቅደስ ለማመልከት በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ በምሳሌያዊ መንገድ ተሠርቶበታል። (1 ዜና 28:2፤ መዝ. 132:7) በምድር ላይ የነበረው ይህ ቤተ መቅደስ የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል ሆኖ አገልግሏል። በዚህ ምክንያት ይህ ቤተ መቅደስ በአምላክ ዓይን እጅግ ውብ ነበር፤ እንዲሁም ቤተ መቅደሱ መኖሩ በራሱ የይሖዋ እግር የሚያርፍበትን ቦታ ያስከብር ነበር። (ኢሳ. 60:13) በዛሬው ጊዜ የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል በምድር ላይ የሚገኝ ቤተ መቅደስ መሆኑ ቀርቷል። ያም ቢሆን ከማንኛውም ሕንፃ ይበልጥ ይሖዋን የሚያስከብር መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ አለ። ይህ ቤተ መቅደስ በኢየሱስ ክርስቶስ ክህነትና መሥዋዕት አማካኝነት ከአምላክ ጋር ለመታረቅ የሚያስችለውን ዝግጅት ያመለክታል። ቤተ መቅደሱ የተቋቋመው ኢየሱስ በ29 ዓ.ም. ሲጠመቅ ማለትም የይሖዋ ታላቅ ቤተ መቅደስ ሊቀ ካህናት ሆኖ ሲቀባ ነው።—ዕብ. 9:11, 12፤ w15 7/15 1:1-3
ሰኞ፣ ኅዳር 13
የሰው ልጅ በኃይልና በታላቅ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።—ሉቃስ 21:27
ታማኝ የሆኑ ሰዎች በዚያ ወቅት ይሸለማሉ፤ ታማኝ ያልሆኑት ደግሞ ይቀጣሉ። (ማቴ. 24:46, 47, 50, 51፤ 25:19, 28-30) በማቴዎስ ዘገባ ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ የተለያዩ ገጽታዎች ስላሉት ምልክት በተናገረው ሐሳብ መደምደሚያ ላይ የበጎቹንና የፍየሎቹን ምሳሌ ተናግሯል፤ እንዲህ ብሏል፦ “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ በክብራማ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል። ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ሁሉ እሱም ሰዎችን አንዱን ከሌላው ይለያል። በጎቹን በቀኙ፣ ፍየሎቹን ግን በግራው ያደርጋቸዋል።” (ማቴ. 25:31-33) በጎቹና ፍየሎቹ ምን ዓይነት ፍርድ ይሰጣቸዋል? ኢየሱስ ምሳሌውን የደመደመው “[ፍየሎቹ] ወደ ዘላለም ጥፋት ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ” በማለት ነው።—ማቴ. 25:46፤ w15 7/15 2:11, 12
ማክሰኞ፣ ኅዳር 14
እነሆ፣ ወንድሞች በአንድነት አብረው ቢኖሩ ምንኛ መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!—መዝ. 133:1
ያደግንበትን አገር፣ ባሕሉን፣ ቋንቋውን እንዲሁም ምግቡን በተወሰነ መጠን ብንወደው የሚያስገርም አይደለም። ይሁንና “የእኔ ከሁሉም ይበልጣል” የሚል ዓይነት አመለካከት ፈጽሞ ሊኖረን አይገባም። ይሖዋ እኛን ለማስደሰት ሲል እያንዳንዱን ነገር የፈጠረው ብዙ ዓይነቶች እንዲኖሩት አድርጎ ነው። (መዝ. 104:24፤ ራእይ 4:11) ታዲያ አንዱ ነገር ከሌላው የላቀ እንደሆነ ለማሰብ ምን ምክንያት አለን? አምላክ ሁሉም ዓይነት ሰዎች የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙና ለዘላለም መኖር እንዲችሉ ይፈልጋል። (ዮሐ. 3:16፤ 1 ጢሞ. 2:3, 4) ተቀባይነት ያላቸው የተለያዩ አመለካከቶችን ለማስተናገድ አእምሯችንን ክፍት ማድረጋችን ሕይወታችንን አስደሳች የሚያደርገው ከመሆኑም ሌላ ክርስቲያናዊ አንድነታችንን ለመጠበቅ ያስችለናል። ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ጠብቀን ለመኖር በዓለም ላይ ባሉ ውዝግቦች ውስጥ ከመግባት መቆጠብ ይኖርብናል። በወገንተኝነት ላይ የተመሠረተ ታማኝነት በእኛ መካከል ሊኖር አይገባም። በሰይጣን ዓለም ውስጥ ከነገሠው የሚከፋፍል እንዲሁም ኩራትና ፉክክር የሚንጸባረቅበት አመለካከት ይሖዋ ስለገላገለን ምንኛ አመስጋኞች ነን! w15 7/15 3:17, 18
ረቡዕ፣ ኅዳር 15
[አምላክ] ስለ እናንተ ያስባል።—1 ጴጥ. 5:7
ለይሖዋ ያለንን ፍቅር የምናሳይባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በመንግሥቱ የስብከት ሥራ በቅንዓት በመካፈል ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር እንዳለን ማሳየት እንችላለን። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) የእምነት ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ንጹሕ አቋማችንን ከጠበቅን ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። (መዝ. 84:11፤ ያዕ. 1:2-5) የሚያጋጥሙን ፈተናዎች ከባድ በሚሆኑበት ጊዜም እንኳ አምላክ ሥቃያችንን እንደሚያውቅ እንዲሁም እንደሚደግፈን እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ምክንያቱም በእሱ ፊት ውድ ነን። (መዝ. 56:8) ለይሖዋ ያለን ፍቅር በፍጥረት ሥራዎቹ ላይ እንድናሰላስል እንዲሁም ስላደረጋቸው ሌሎች ድንቅ ነገሮች እንድናስብ ይገፋፋናል። መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናት አምላክን እንደምንወደው እንዲሁም ለቃሉ የላቀ አክብሮት እንዳለን እናሳያለን። ለይሖዋ ያለን ፍቅር ይበልጥ በጸሎት እንድንቀርበው ያነሳሳናል። በተጨማሪም አምላክ ለኃጢአታችን ማስተሰረያ እንዲሆን ባደረገው የቤዛ ዝግጅት ላይ ስናሰላስል ለእሱ ያለን ፍቅር የበለጠ ይጨምራል። (1 ዮሐ. 2:1, 2) ይሖዋ ጽኑ ፍቅር ስላሳየን እኛም በምላሹ እሱን እንድንወደው ከሚያደርጉን ብዙ ምክንያቶች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው። w15 8/15 1:6, 17, 18
ሐሙስ፣ ኅዳር 16
ታጋሽ መሆን ይሻላል።—መክ. 7:8
በአዲሱ ዓለም አንዳንድ ነገሮችን በትዕግሥት መጠበቅ ሊያስፈልገን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ግለሰቦች ከሞት እንደተነሱና በዚህም የተነሳ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው እጅግ እንደተደሰቱ እንሰማ ይሆናል። እኛ ግን የምንወዳቸው ሰዎች ከሞት እስኪነሱ መጠበቅ ሊያስፈልገን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ከሌሎች ጋር መደሰትና በትዕግሥት መጠበቅ እንችላለን? (ሮም 12:15) ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች እስኪፈጸሙ ድረስ አሁን በትዕግሥት መጠበቅ ከተማርን በዚያን ጊዜ መታገሥ አያስቸግረንም። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን በተመለከተ ባለን ግንዛቤ ላይ ከሚደረግ ማስተካከያ ጋር በተያያዘ ትዕግሥት በማሳየትም ለአዲሱ ዓለም መዘጋጀት እንችላለን። በዛሬው ጊዜ ቀስ በቀስ እየጠራ የሚሄደውን እውነት በትጋት እናጠናለን? ማስተካከያዎቹ ሙሉ በሙሉ ግልጽ ባይሆኑልንስ ትዕግሥት እናሳያለን? እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ይሖዋ ከሰው ልጆች የሚጠብቀውን ብቃት በየጊዜው ሲያሳውቀን ትዕግሥት ማሳየት አይከብደንም።—ምሳሌ 4:18፤ ዮሐ. 16:12፤ w15 8/15 3:9, 10
ዓርብ፣ ኅዳር 17
እንደ ክርስቶስ የተሟላ የጉልምስና ደረጃ ላይ [ድረሱ]።—ኤፌ. 4:13
ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ያሉ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ እድገት ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ጽፎላቸዋል። “በእምነትና ስለ አምላክ ልጅ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም ወደሚገኘው አንድነት እንዲሁም ሙሉ ሰው ወደ መሆን ይኸውም እንደ ክርስቶስ የተሟላ የጉልምስና ደረጃ ላይ” ለመድረስ እንዲጣጣሩ አበረታቷቸዋል። (ኤፌ. 4:13) ጳውሎስ ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት የኤፌሶን ጉባኤ ከተቋቋመ የተወሰኑ ዓመታት አልፈው ነበር። በዚያ የሚገኙ በርካታ ደቀ መዛሙርት ከፍ ያለ መንፈሳዊ የእድገት ደረጃ ላይ ደርሰው ነበር። አንዳንዶቹ ግን አሁንም ወደ ጉልምስና ደረጃ ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸው ነበር። በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ብዙዎቹ ወንድሞችና እህቶች አምላክን ረዘም ላሉ ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩና በመንፈሳዊ የጎለመሱ ናቸው። ሆኖም ሁሉም የጉልምስና ደረጃ ላይ ደርሰዋል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ሰዎች ይጠመቃሉ፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ መንፈሳዊ ጉልምስና ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። አንተስ እድገት ማድረግ ያስፈልግህ ይሆን?—ቆላ. 2:6, 7፤ w15 9/15 1:2, 3
ቅዳሜ፣ ኅዳር 18
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጥቂቱ ይጠቅማል።—1 ጢሞ. 4:8
ብዙዎች አዘውትሮ የተወሰነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለጥሩ ጤንነት እንደሚጠቅም እንዲሁም ሰውነትንና አእምሮን እንደሚያነቃቃ ያምናሉ። ከሌሎች ጋር አብረን ስፖርት መሥራት ብንፈልግ ከማንኛውም ሰው ጋር ብንሠራ ችግር ይኖረዋል? ምሳሌ 13:20 “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል፤ ከሞኞች ጋር የሚገጥም ግን ጉዳት ይደርስበታል” ይላል። ታዲያ ይህ ጥቅስ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናችን ተጠቅመን የምንዝናናበትን ነገር በጥንቃቄ መምረጥ እንዳለብን አይጠቁምም? በተጨማሪም መቼ ብንዝናና ጥሩ ነው የሚለው ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል። እንደ ስብሰባ፣ መስክ አገልግሎትና የግል ጥናት ላሉ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ቅድሚያ ትሰጣላችሁ? ወይስ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችን ለመዝናኛ በመደባችሁት ጊዜ ውስጥ እንደምንም አጣባችሁ ለማስገባት ጥረት ታደርጋላችሁ? ቅድሚያ የምትሰጡት ለየትኛው ነው? ኢየሱስ “እንግዲያው ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል” ብሏል። (ማቴ. 6:33) ሕሊናችሁ ኢየሱስ ከሰጠው ምክር ጋር በሚስማማ መንገድ መቅደም ያለበትን ነገር እንድታስቀድሙ ይገፋፋችኋል? w15 9/15 2:13, 15
እሁድ፣ ኅዳር 19
ለምን ተናደድክ? ለምንስ አዘንክ? መልካም ወደ ማድረግ ብታዘነብል ኖሮ ሞገስ አታገኝም ነበር? . . . ታዲያ አንተ [ኃጢአትን] ትቆጣጠረው ይሆን?—ዘፍ. 4:6, 7
ይህ በትክክለኛው ጊዜ የተሰጠ ጠቃሚ ምክር ነበር። ይሖዋ ለቃየን ይህን ማስጠንቀቂያ የሰጠው አደገኛ የሆነ አካሄድ እየተከተለ እንደሆነ ስለተገነዘበ ነው። የሚያሳዝነው ግን ቃየን የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሳይቀበል ቀረ፤ ይህም ለከባድ ችግር ዳርጎታል። (ዘፍ. 4:11-13) የኤርምያስ ጸሐፊ የነበረው ባሮክ በተሰላቸና ደስታ በራቀው ጊዜ ይሖዋ የችግሩ መንስኤ ምን እንደሆነ እንዲያስተውል ምክር ሰጥቶታል። ከቃየን በተቃራኒ ባሮክ ይሖዋ የሰጠውን ምክር በመቀበሉ ሕይወቱን ማትረፍ ችሏል። (ኤር. 45:2-5) ጳውሎስ፣ “ይሖዋ የሚወዳቸውን ይገሥጻልና፤ እንዲያውም እንደ ልጁ አድርጎ የሚቀበለውን ሁሉ ይቀጣል” ሲል ጽፏል። (ዕብ. 12:6) ይሁንና ተግሣጽ ሁልጊዜ ቅጣትን ብቻ የሚያመለክት አይደለም። በተለያዩ መንገዶች ሊሰጥ ይችላል። በርካታ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ከባድ ፈተና እንደደረሰባቸው የሚገልጹ ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው እናገኛለን፤ አንዳንዶቹ ፈተናዎች ተግሣጽንና ሥልጠናን ያካተቱ ናቸው። w15 9/15 4:12, 13
ሰኞ፣ ኅዳር 20
እኛ አገልጋዮችህ ለአምላክህ ለይሖዋ ስም ካለን አክብሮት የተነሳ . . . የመጣን ነን፤ ምክንያቱም ዝናውንና በግብፅ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል።—ኢያሱ 9:9
ገባኦናውያን እስራኤላውያንን እየረዳቸው ያለው እውነተኛው አምላክ መሆኑን ተገንዝበው ነበር። ረዓብም እሷ በኖረችበት ዘመን ከተከናወኑት ነገሮች በስተጀርባ የአምላክ እጅ እንዳለ መገንዘብ ችላለች። ይሖዋ ሕዝቡን እንዴት እንዳዳናቸው ከሰማች በኋላ ለሁለቱ እስራኤላውያን ሰላዮች “ይሖዋ ምድሪቱን እንደሚሰጣችሁ አውቃለሁ” ብላቸዋለች። እንዲህ ያለ አቋም መያዟ ሕይወቷን አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆንም ይሖዋ እሷንም ሆነ ቤተሰቧን ማዳን እንደሚችል እምነት እንዳላት አሳይታለች። (ኢያሱ 2:9-13፤ 4:23, 24) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ ሌሎች በርካታ ምሳሌዎችም አምላክን ማየት ወይም በአንድ ጉዳይ ላይ የእሱ እጅ እንዳለበት መመልከት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዱናል። እኛም ይሖዋን እያወቅነው ስንሄድ ባሕርያቱንና ድርጊቱን ‘በልባችን ዓይኖች’ ስለምናስተውል በአንድ ጉዳይ ላይ እጁ እንዳለበት ማየት እንችላለን። (ኤፌ. 1:18) ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚረዳ በግልጽ እንደተመለከቱት በጥንት ጊዜ እንደነበሩትም ሆነ በዘመናችን እንዳሉት ሰዎች መሆን እንደምንፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። w15 10/15 1:6, 7, 9
ማክሰኞ፣ ኅዳር 21
ኢየሱስ ማርታንና እህቷን እንዲሁም አልዓዛርን ይወዳቸው ነበር።—ዮሐ. 11:5
ማርታ፣ ኢየሱስ እንደሚወዳት በስም የተጠቀሰችው ብቸኛዋ ሴት ናት፤ እርግጥ ኢየሱስ አምላክን ለሚታዘዙ ሌሎች ሴቶችም ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ነበረው፤ ለምሳሌ ሥጋዊ እናቱን ማርያምን እንዲሁም የማርታን እህት ማርያምን ይወድዳቸው ነበር። (ዮሐ. 19:25-27) ታዲያ ማርታ በወንጌል ዘገባው ውስጥ በዚህ መንገድ የተገለጸችው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ማርታን ይወዳት የነበረው እንግዳ ተቀባይና ታታሪ በመሆኗ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊነቷም ጭምር እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። በኢየሱስ ትምህርቶች ከልብ የምታምን ሴት ነበረች። ማርታ፣ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ እንደሆነ አምና በመቀበል አስደናቂ እምነት እንዳላት አሳይታለች። (ዮሐ. 11:21-27) ይሁንና እሷም እንደ ሌሎቻችን ሁሉ ፍጽምና ይጎድላታል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ በቤቷ እየተስተናገደ ሳለ ማርታ ትክክል አይደለም ብላ ያሰበችውን አንድ ሁኔታ ለማስተካከል ኢየሱስ ምን ማድረግ እንዳለበት ለመናገር ደፍራ ነበር። ማርታ “ጌታ ሆይ፣ እህቴ ሥራውን ሁሉ ለእኔ ጥላ ስትቀመጥ ምንም ግድ አይሰጥህም? መጥታ እንድታግዘኝ ንገራት እንጂ” አለችው።—ሉቃስ 10:38-42፤ w15 10/15 3:1, 2
ረቡዕ፣ ኅዳር 22
ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።—ያዕ. 4:8
ሁልጊዜ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ የምናሰላስል ከሆነ ለእውነት ያለንን ቅንዓት ይዘን መቀጠል እንችላለን። በዚህ መንገድ ለወንድሞቻችንም ሆነ በመስክ አገልግሎት ለምናገኛቸው ሰዎች የእረፍት ምንጭ እንሆናለን። አምላክ በሰጠን ታላቅ ስጦታ ላይ ማለትም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ማሰላሰላችን ቅዱስ ከሆነው አባታችን ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን የጠበቀ ዝምድና ከፍ አድርገን እንድንመለከት ይረዳናል። (ሮም 3:24) ማርክ የተባለ በደቡብ አፍሪካ የሚኖርና በክርስቲያናዊ ገለልተኛ አቋሙ የተነሳ ለሦስት ዓመት ታስሮ የነበረ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ማሰላሰል በጣም ከሚያስደስት ጉዞ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ይበልጥ ባሰላሰልን መጠን ስለ አምላካችን ስለ ይሖዋ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን እያወቅን እንሄዳለን። አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ስቆርጥ ወይም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ስጨነቅ መጽሐፍ ቅዱሴን አውጥቼ አነባለሁ፤ ከዚያም በጥቅሶቹ ላይ አሰላስላለሁ። በዚህ ጊዜ ውስጤ ይረጋጋል።” w15 10/15 4:15
ሐሙስ፣ ኅዳር 23
ሕግህን እንዳከብርና በሙሉ ልቤ እንድጠብቅ ማስተዋል ስጠኝ።—መዝ. 119:34
ወላጆች ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ፣ አንድ ዓይነት መመሪያ ወይም ውሳኔ ያስተላለፋችሁበትን ምክንያት ለልጆቻችሁ ንገሯቸው። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጃችሁ ስለ ጉዳዩ ያላችሁ አመለካከት ግልጽ ከሆነለት ከልቡ ለመታዘዝ ሊነሳሳ ይችላል። የአራት ልጆች አባት የሆነው ባሪ እንዲህ ብሏል፦ “ምክንያታችሁን መግለጻችሁ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁ እንዲተማመኑባችሁ ያደርጋል፤ ምክንያቱም ውሳኔ የምታደርጉት እንዳሰኛችሁ እንዳልሆነ ወይም ሐሳባችሁን ዝም ብላችሁ እንደማትለዋውጡ ከዚህ ይልቅ ምክንያታዊ እንደሆናችሁ መመልከት ይችላሉ።” በተጨማሪም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ‘የማሰብ ችሎታቸውን’ ተጠቅመው ወደ ጉልምስና እያደጉ መሆኑን አስታውሱ። (ሮም 12:1) ባሪ “በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች በስሜት ሳይሆን በምክንያት ላይ የተመሠረተ ጥሩ ውሳኔ ማድረግን መማር አለባቸው” ብሏል። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ አንድን ውሳኔ ያደረጋችሁበትን ምክንያት በትሕትና ስትገልጹለት፣ ወደ ጉልምስና እያደገ መሆኑን እንደተገነዘባችሁ ማስተዋል ይችላል፤ እንዲሁም ‘የማሰብ ችሎታውን’ ተጠቅሞ የራሱን ውሳኔ ማድረግን ይማራል። w15 11/15 2:11
ዓርብ፣ ኅዳር 24
ለሁሉም፣ በተለይ ደግሞ በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች መልካም እናድርግ።—ገላ. 6:10
በዓለም ዙሪያ ይሖዋን የሚያመልኩ እንዲሁም ስለ እሱና ስለ ዓላማው የሚመሠክሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ታዲያ እያንዳንዱ የይሖዋ አምላኪ ለእምነት ባልንጀራው ምን አመለካከት ሊኖረው ይገባል? (ሮም 12:10) ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እንግዲህ ለእውነት በመታዘዝ ራሳችሁን ስላነጻችሁ ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ አላችሁ፤ በመሆኑም እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ።” ከዚህም በተጨማሪ ጴጥሮስ የእምነት ባልንጀሮቹን “ከሁሉም በላይ አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ” ብሏቸዋል። (1 ጴጥ. 1:22፤ 4:8) አብረውን ይሖዋን ለሚያገለግሉ ባልንጀሮቻችን ጥልቅ ፍቅር ስላለን ልዩ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ሊኖረን ችሏል። በተጨማሪም ይሖዋን ስለምንወድና ሕግጋቱን ስለምንታዘዝ፣ አምላክ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀ ኃይል በሆነው በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ይደግፈናል። ይህ መንፈስ፣ ዓለም አቀፍ በሆነ እውነተኛ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ እንድንታቀፍና አስደናቂ አንድነት እንዲኖረን አስችሎናል።—1 ዮሐ. 4:20, 21፤ w15 11/15 4:8, 9
ቅዳሜ፣ ኅዳር 25
ከብሔራት ቋንቋዎች ሁሉ የተውጣጡ አሥር ሰዎች . . . “አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን” ይላሉ።—ዘካ. 8:23
ይሖዋ ስለ እሱም ሆነ ስለ ዓላማዎቹ ለማወቅ ስንል አንድን ቋንቋ እንድንማር አያስገድደንም። (ራእይ 7:9, 10) የሰው ልጆች የተለያዩ ቋንቋዎችን መጠቀማቸውና የአምላክ ቃል ሲተረጎም ጥቃቅን ልዩነቶች መፈጠራቸው አምላክ ለሰዎች ሐሳቡን እንዳያስተላልፍ እንቅፋት ሆኗል? በፍጹም። ለምሳሌ ኢየሱስ ከተጠቀመባቸው ቃላት መካከል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀጥታ የሰፈሩት ጥቂት ናቸው። (ማቴ. 27:46፤ ማር. 5:41፤ 7:34፤ 14:36) ይሁንና ይሖዋ፣ ኢየሱስ የተናገረው መልእክት በግሪክኛና ውሎ አድሮም በሌሎች ቋንቋዎች እንዲተላለፍ አድርጓል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ አይሁዳውያንና ክርስቲያኖች፣ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን በተደጋጋሚ ጊዜ በመገልበጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ተጠብቀው እንዲቆዩ አደረጉ። እነዚህ ጽሑፎችም ወደ ብዙ ቋንቋዎች ተተረጎሙ። በአራተኛው/በአምስተኛው ምዕተ ዓመት የኖረው ጆን ክሪሶስተም፣ በዘመኑ የኢየሱስ ትምህርቶች ሶርያውያን፣ ግብፃውያን፣ ሕንዳውያን፣ ፋርሳውያን፣ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች በርካታ ሕዝቦች ወደሚናገሯቸው ቋንቋዎች ተተርጉመው እንደነበር ገልጿል። w15 12/15 1:10, 11
እሁድ፣ ኅዳር 26
በትክክለኛው ጊዜ የተነገረ ቃልም ምንኛ መልካም ነው!—ምሳሌ 15:23
የምንናገረው ነገር ለሚሰማን ሰው በጣም አስፈላጊ ቢሆንም እንኳ መቼ መናገር እንዳለብን ካላወቅን ንግግራችን ዋጋ ሊያጣ ይችላል። መጋቢት 2011 በጃፓን ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ በዚያ ወቅት የምሥራቃዊ ጃፓን የተወሰነ ክፍል በምድር መናወጥና በሱናሚ የተመታ ሲሆን አንዳንድ ከተሞች ሙሉ በሙሉ ወደሙ። ከ15,000 የሚበልጡ ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ። በዚያ አካባቢ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችም ልክ እንደ ሌሎቹ ሰዎች በአደጋው የተጠቁ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመው ያዘኑትን ለማጽናናት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመዋል። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች የቡድሂዝምን እምነት በጥብቅ የሚከተሉ ከመሆናቸውም ሌላ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አያውቁም፤ አሊያም እውቀታቸው በጣም ውስን ነው። ወንድሞቻችን፣ ለአካባቢው ሰዎች ስለ ትንሣኤ ተስፋ ለመናገር ጥሩ የሆነው ጊዜ ሱናሚው የተከሰተበት ወቅት እንዳልሆነ አስተዋሉ። በመሆኑም ወንድሞች በንግግር ስጦታቸው ተጠቅመው ሰዎችን በማጽናናትና እንዲህ ያለው መከራ በንጹሐን ሰዎች ላይ የሚደርሰው ለምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ በማብራራት ላይ ትኩረት አደረጉ። w15 12/15 3:7
ሰኞ፣ ኅዳር 27
ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል።—ምሳሌ 14:15
የሚያሳዝነው ይህ ዓለም፣ ሰዎች በሚታመሙበት ወቅት አጋጣሚውን ተጠቅመው ገንዘብ ለማጋበስ በሚሞክሩ ስግብግቦች የተሞላ ነው። ሌሎች ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ደግሞ ትርፍ ለማጋበስ ሲሉ ውድ የሆኑ መድኃኒቶችን እንድንጠቀም ያበረታታሉ። ከሕመሙ እፎይታ ማግኘት ወይም ዕድሜውን ማራዘም የሚፈልግ የታመመ ሰው እነዚህን “መድኃኒቶች” ለማግኘት ሊጓጓ ይችላል። “ብልህ” ሰው፣ በተለይ ብቃቱ አጠያያቂ የሆነ ግለሰብ የሚነግረውን “ቃል” ወይም የሚሰጠውን ምክር ለማመን አይቸኩልም። “ብልህ” ሰው እንደሚከተለው ብሎ ያስባል፦ ‘ግለሰቡ ይህ ቫይታሚን፣ ዕፀዋት ወይም የአመጋገብ ሥርዓት ሌሎችን እንደረዳ ተናግሯል፤ ይሁንና ይህን የሚያረጋግጡ በቂ ምሥክሮች አሉ? ደግሞም የሰዎች ሁኔታ የተለያየ ነው። ሕክምናው እኔን እንደሚረዳኝ ለማመን የሚያበቃ ምክንያት አለኝ? በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርምር ማድረግ አሊያም በዚህ መስክ ሥልጠና ያገኙ ወይም ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን ማማከር ይኖርብኝ ይሆን?’—ዘዳ. 17:6፤ w15 12/15 4:14, 15
ማክሰኞ፣ ኅዳር 28
ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናል።—2 ቆሮ. 5:14
ክርስቶስ ላሳየን ተወዳዳሪ የሌለው ፍቅር የምንሰጠው ምላሽ ለእሱ ለመኖር ግድ እንደሚለን ወይም እንደሚያነሳሳን ጳውሎስ ተገንዝቦ ነበር። ይሖዋ ያደረገልንን ነገር ሙሉ በሙሉ ስንገነዘብና ልባችን ለእሱ ባለን ፍቅር ሲሞላ በሙሉ ነፍሳችን ለክርስቶስ ኢየሱስ የመኖር ፍላጎት ያድርብናል። እንዲህ ያለ ፍላጎት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ለይሖዋ ያለን ፍቅር፣ ክርስቶስን ለመምሰል እንዲሁም ፈለጉን በጥብቅ ለመከተል ግድ ይለናል። (1 ጴጥ. 2:21፤ 1 ዮሐ. 2:6) ታዛዦች በመሆን ለአምላክና ለክርስቶስ ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እኔን የሚወደኝ ትእዛዛቴን የሚቀበልና የሚጠብቅ ነው። እኔን የሚወደኝን ሁሉ ደግሞ አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ።” (ዮሐ. 14:21፤ 1 ዮሐ. 5:3) በመሆኑም ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በሕይወቴ ውስጥ የክርስቶስ ኢየሱስን ፈለግ በመከተል ረገድ በየትኞቹ አቅጣጫዎች ተሳክቶልኛል? ማሻሻያ ማድረግ የሚያስፈልገኝስ በየትኞቹ መስኮች ነው?’ በዚህ መንገድ ራሳችንን መመርመራችን አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም የዓለምን አካሄድ እንድንከተል ያለማቋረጥ ጫና ይደርስብናል።—ሮም 12:2፤ w16.01 2:7-9
ረቡዕ፣ ኅዳር 29
እንደ እሱ እንደምንሆን እናውቃለን፤ ምክንያቱም እሱን በእርግጥ እናየዋለን።—1 ዮሐ. 3:2
በአገልግሎት የተለየ ቅንዓት እንዳለህ ይሰማሃል? “የአምላክን ጥልቅ ነገሮች” መቆፈር የሚያስደስትህ ትጉ የአምላክ ቃል ተማሪ ነህ? (1 ቆሮ. 2:10) በአገልግሎትህ የይሖዋን ልዩ በረከት እንዳገኘህ ይሰማሃል? የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት አለህ? ሌሎችን በመንፈሳዊ የመርዳት ኃላፊነት እንዳለብህ ከልብ ይሰማሃል? በሕይወትህ ውስጥ የይሖዋን እጅ እንዳየህ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ተመልክተሃል? ለእነዚህ ጥያቄዎች በልበ ሙሉነት “አዎ” የሚል መልስ የምትሰጥ ከሆነ ሰማያዊ ጥሪ አለህ ማለት ነው? አይደለም። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ያለ ስሜት የሚሰማቸው ሰማያዊ ጥሪ ያላቸው ሰዎች ብቻ አይደሉም። የይሖዋ መንፈስ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ባላቸው ሰዎች ላይም በእኩል ደረጃ ይሠራል። እንዲያውም ሰማያዊ ጥሪ እንዳለህ ጥያቄ የሚፈጠርብህ ከሆነ ይህ በራሱ እንዲህ ዓይነት ጥሪ እንዳላገኘህ ያሳያል። w16.01 3:14, 15
ሐሙስ፣ ኅዳር 30
በፊቱ ሁልጊዜ ሐሴት አደርግ ነበር።—ምሳሌ 8:30
ኢየሱስ ከአባቱ ጋር አብሮ በደስታ ይሠራ የነበረ ሲሆን ባከናወነው ነገር እንዲሁም ይሖዋ በእሱ ደስ እንደሚሰኝ በማወቁ ሐሴት ያደርግ ነበር። ስለ እኛስ ምን ማለት ይቻላል? ኢየሱስ መቀበልም ሆነ መስጠት ደስታ እንደሚያስገኝ ተናግሯል። (ሥራ 20:35) እውነትን ማግኘታችን አስደስቶናል፤ እውነትን ለሌሎች ማካፈላችንም ደስታ ያስገኝልናል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች የምንነግራቸው በመንፈሳዊ የተራቡ ሰዎች፣ ስለ አምላካችን ሲያውቁና በቃሉ ውስጥ የሰፈሩትን ውድ እውነቶች ሲገነዘቡ ልባቸው በደስታ ይሞላል። እኛም እነዚህ ሰዎች በአስተሳሰባቸው ብቻ ሳይሆን በሕይወታቸው ውስጥም ለውጦች ሲያደርጉ ስንመለከት ልባችን ሐሴት ያደርጋል። ምሥራቹን ለሰዎች የመስበኩ ሥራ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እንገነዘባለን። የስብከቱ ሥራ ከአምላክ ጋር ለሚታረቁ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉበት መንገድ ይከፍታል። (2 ቆሮ. 5:20) ሰዎች የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝላቸውን መንገድ እንዲከተሉ ከመርዳት የሚበልጥ ምን አስደሳችና አርኪ ሥራ ሊኖር ይችላል? w16.01 5:6, 7