ታኅሣሥ
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 1
በዓለም ዙሪያ በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያሉት ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እየደረሰባቸው እንዳለ ተገንዝባችሁ በእምነት ጸንታችሁ በመቆም ተቃወሙት።—1 ጴጥ. 5:9
ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ክርስቲያኖች ሰይጣን የሚያመጣባቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በጽናት እንዲወጡ ለማበረታታት ከላይ ያለውን ጽፏል። “የጸኑት” የአምላክ አገልጋዮች የተዉት ምሳሌ ጽኑ አቋማችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል፤ ሊሳካልን እንደሚችል ማረጋገጫ ይሰጠናል፤ እንዲሁም ታማኞች ከሆንን ሽልማት እንደምናገኝ ያስታውሰናል። (ያዕ. 5:11) ከእውነተኛው አምልኮ ጠላቶች፣ መራራ ተቃውሞ ሌላው ቀርቶ ስደት እየደረሰብህ ነው? ያሉብህ ከባድ ኃላፊነቶች ከአቅምህ በላይ እንደሆኑ የሚሰማህ የጉባኤ ሽማግሌ ወይም የወረዳ የበላይ ተመልካች ነህ? ከሆነ ጳውሎስ በተወው ምሳሌ ላይ አሰላስል። ጳውሎስ ብዙ “ውጫዊ ችግሮች” የደረሱበት ይኸውም ጨካኝ አሳዳጆች ያስጨነቁት ከመሆኑም ሌላ የጉባኤዎች ሐሳብ በየዕለቱ ጫና ይፈጥርበት ነበር። (2 ቆሮ. 11:23-29) ይህ ሁሉ ቢደርስበትም ተስፋ አልቆረጠም፤ የተወው ምሳሌም ለሌሎች የብርታት ምንጭ ነው። (2 ቆሮ. 1:6) አንተም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናት ስትቋቋም የአንተ ምሳሌነት ሌሎችም እንዲጸኑ እንደሚያበረታታቸው አስታውስ። w16.04 2:11, 14
እሁድ፣ ታኅሣሥ 2
ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።—ማቴ. 28:19, 20
የይሖዋ ምሥክሮችን የሚደግፉም ሆነ አምርረው የሚቃወሙ ሰዎች ሊክዱ የማይችሉት አንድ ሐቅ አለ፤ ይኸውም የይሖዋ ምሥክሮች በስብከቱ ሥራቸው በቡድን ደረጃ በስፋት የታወቁ መሆናቸው ነው። በምናምንባቸው ነገሮች ባይስማሙም በምናከናውነው ሥራ እንደሚያከብሩን የሚናገሩ ሰዎች በአገልግሎት ላይ አጋጥመውህ ያውቁ ይሆናል። ኢየሱስ የመንግሥቱ ምሥራች በመላው ምድር እንደሚሰበክ አስቀድሞ እንደተናገረ እናውቃለን። (ማቴ. 24:14) ወንጌሉን ወይም ምሥራቹን እየሰበኩ እንዳሉ የሚሰማቸው በርካታ ሃይማኖታዊ ቡድኖች አሉ። አብዛኛውን ጊዜ ግን የሚያከናውኑት የስብከት ሥራ ስለ ራሳቸው ተሞክሮ ምሥክርነት ከመስጠት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከመስበክ አሊያም በመገናኛ ብዙኃን ይኸውም በቴሌቪዥን ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት ፕሮግራም ከማቅረብ ያለፈ አይደለም። ሌሎች ደግሞ የሚያከናውኗቸውን የበጎ አድራጎት ሥራዎች አሊያም በሕክምና እና በትምህርት መስኮች የሚያደርጉትን እርዳታ ይጠቅሳሉ። ለመሆኑ እነዚህን ነገሮች ስላደረጉ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸውን ትእዛዝ እየፈጸሙ ነው ማለት ይቻላል? w16.05 2:1, 2
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 3
ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!—ሥራ 25:11
ከ1914 ወዲህ ሰብዓዊ መንግሥታት የአምላክ መንግሥት ተቀናቃኝ ሆነዋል፤ ይህ መንግሥት በቅርቡ እነዚህን ብሔራት ያጠፋቸዋል። (መዝ. 2:2, 7-9) አምላክ የዓለም የፖለቲካ መዋቅር እንዲቀጥል የፈቀደው፣ በተወሰነ መጠን መረጋጋት እንዲሰፍን ስለሚያደርግ ነው፤ ይህ ደግሞ የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ ያስችለናል። (ሮም 13:3, 4) አምላክ ለባለሥልጣናት እንድንጸልይ እንኳ አዞናል፤ በተለይ ደግሞ የሚያደርጉት ውሳኔ አምልኳችንን የሚነካ በሚሆንበት ጊዜ ይህን ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። (1 ጢሞ. 2:1, 2) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ፍትሕ እንዲያስፈጽሙልን ወደ መንግሥት ባለሥልጣናት ይግባኝ እንላለን። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን፣ በፖለቲካው ሥርዓት ላይ ሥልጣን እንዳለው ቢናገርም ሰይጣን እያንዳንዱን መሪ ወይም ባለሥልጣን በቀጥታ እንደሚቆጣጠረው አይገልጽም። (ሉቃስ 4:5, 6) በመሆኑም አንድን ባለሥልጣን ለይተን በመጥቀስ በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር እንደሆነ መናገር የለብንም። እንዲያውም ‘ከመንግሥታትና ከባለሥልጣናት’ ጋር በተያያዘ “ስለ ማንም ክፉ ነገር” አንናገርም።—ቲቶ 3:1, 2፤ w16.04 4:5, 6
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 4
የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ።—ኤፌ. 5:17
‘በአምላክ ቃል ውስጥ ቀጥተኛ መመሪያ ያልተሰጠባቸው ጉዳዮች ሲያጋጥሙን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ውሳኔ የትኛው እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?’ የሚል ጥያቄ ይፈጠርብን ይሆናል። ቀጥተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ በማይኖርበት ጊዜ የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ማስተዋል የምንችለው እንዴት ነው? ወደ እሱ በመጸለይና በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እንዲመራን በመፍቀድ ነው። ኢየሱስ፣ አባቱ ከእሱ የሚፈልገውን ነገር ማስተዋል የቻለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ኢየሱስ ከጸለየ በኋላ በተአምር ብዙ ሰዎችን እንደመገበ የሚገልጹ ሁለት ዘገባዎችን እናገኛለን። (ማቴ. 14:17-20፤ 15:34-37) ያም ሆኖ በምድረ በዳ ተርቦ በነበረበት ወቅት ዲያብሎስ ድንጋዩን ዳቦ እንዲያደርግ ያቀረበለትን ጥያቄ ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም። (ማቴ. 4:2-4) ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ የአባቱን አስተሳሰብ በሚገባ ያውቃል፤ በመሆኑም ድንጋዩን ወደ ዳቦ መለወጥ እንደሌለበት ተገንዝቦ ነበር። ኢየሱስ ያለውን ኃይል የግል ፍላጎቱን ለማሟላት እንዲጠቀምበት የአምላክ ፈቃድ እንዳልሆነ ያውቃል። ኢየሱስ ድንጋዩን ወደ ዳቦ ለመለወጥ ፈቃደኛ አለመሆኑ፣ መመሪያም ሆነ የሚያስፈልገውን ነገር ይሖዋ እንደሚሰጠው እምነት እንዳለው ያሳያል። w16.05 3:7, 8
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 5
ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው፤ እንዲሁም . . . ይጠቅማሉ።—2 ጢሞ. 3:16
እርግጥ ነው፣ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መጀመሪያ የተጻፉት ለአንድ ግለሰብ ወይም ለተወሰኑ ሰዎች ነው። የአምላክን ቃል ማንበብ ከመጀመራችን በፊት፣ ለመማር ዝግጁ እንድንሆንና ይሖዋ ሊያስተምረን የሚፈልገውን ትምህርት ለማስተዋል የሚያስችል ጥበብ እንድናገኝ መጸለያችን አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው። (ዕዝራ 7:10፤ ያዕ. 1:5) መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ቆም እያልክ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ራስህን ጠይቅ፦ ‘ይህ ዘገባ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል? ትምህርቱን በሕይወቴ ተግባራዊ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው? ይህን ሐሳብ ሌሎችን ለመርዳት ልጠቀምበት የምችለው እንዴት ነው?’ እንደነዚህ ባሉ ጥያቄዎች ላይ ስናሰላስል ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን ይበልጥ ጥቅም ማግኘት እንደምንችል የታወቀ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንዲያሟሉ የሚጠበቁባቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች እንመልከት። (1 ጢሞ. 3:2-7) አብዛኞቻችን የጉባኤ ሽማግሌዎች ስላልሆንን ይህ ጥቅስ በሕይወታችን ውስጥ ልንጠቀምበት የምንችል ትምህርት እንዳልያዘ ይሰማን ይሆናል። ይሁንና ከዚህ ጥቅስ ሁላችንም የተለያዩ ጥቅሞች ልናገኝ እንደምንችል እንገነዘባለን። w16.05 5:7, 8
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 6
እነሆ፣ በሸክላ ሠሪ እጅ እንዳለ ጭቃ፣ እናንተም በእኔ እጅ እንዲሁ ናችሁ።—ኤር. 18:6
በጥንት ዘመን አይሁዳውያን በግዞት ወደ ባቢሎን ተወስደው ነበር፤ ባቢሎን በጣዖታት የተሞላች ስትሆን ሕዝቧም በመናፍስታዊ ድርጊቶች ተተብትበው ነበር። ያም ቢሆን ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ እንዲሁም ሌሎች ታማኝ አይሁዳውያን ባቢሎናውያን እንዲቀርጿቸው አልፈቀዱም። (ዳን. 1:6, 8, 12፤ 3:16-18) ዳንኤልና ጓደኞቹ፣ ታላቅ ሸክላ ሠሪ የሆነውን ይሖዋን ብቻ ለማምለክ ቆርጠው ነበር። ደግሞም ይህን ማድረግ ችለዋል! ዳንኤል መላ ሕይወቱን ያሳለፈው በባቢሎን ነበር ማለት ይቻላል፤ ያም ቢሆን የአምላክ መልአክ “እጅግ የተወደድክ ሰው” በማለት ጠርቶታል። (ዳን. 10:11, 19) በጥንት ዘመን አንድ ሸክላ ሠሪ፣ ጭቃው እሱ የፈለገውን ቅርጽ እንዲይዝ ለማድረግ ቅርጽ ማውጫ ይጠቀም ነበር። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች፣ ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ እንደሆነ እንዲሁም ሰዎችንና ብሔራትን የመቅረጽ ሥልጣን እንዳለው ይገነዘባሉ። (ኤር. 18:6) በተጨማሪም አምላክ እኛን በግለሰብ ደረጃ የመቅረጽ ሥልጣን አለው። ይሁንና የመምረጥ ነፃነታችንን የሚያከብርልን ሲሆን በእሱ ለመቀረጽ ፈቃደኞች እንድንሆን ይፈልጋል። w16.06 2:1, 2
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 7
አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን።—ዕብ. 13:5
ሰይጣን፣ በሕይወታችን ደስተኛ መሆን ከፈለግን መሠረታዊ ከሆኑት ቁሳዊ ነገሮች ባሻገር ሌሎች ተጨማሪ ነገሮች እንደሚያስፈልጉን ሊያሳምነን ይሞክራል፤ ይህን ለማድረግም የንግዱን ዓለም ይጠቀማል። “የዓይን አምሮት” እንዲያድርብን በማድረግ ረገድ የተካነ ነው። (1 ዮሐ. 2:15-17፤ ዘፍ. 3:6፤ ምሳሌ 27:20) ይህ ዓለም፣ ምርጥ ከሚባሉት አንስቶ እርባና ቢስ እስከሆኑት ነገሮች ድረስ በርካታ ቁሳዊ ነገሮችን ያቀርባል፤ ከእነዚህ አንዳንዶቹ በጣም የሚያጓጉ ሊሆኑ ይችላሉ። አንድን ዕቃ በማስታወቂያ ስላየኸው ወይም ሱቅ ውስጥ የተቀመጠበት መንገድ ቀልብህን ስለሳበው ብቻ ገዝተህ ታውቃለህ? በኋላ ላይ ስታስበው ግን የገዛኸው ነገር ጨርሶ እንደማያስፈልግህ ተገንዝበህ ይሆናል። እንዲህ ያሉት አላስፈላጊ ነገሮች ሕይወታችንን ከማወሳሰብና ጫና ከመፍጠር ባለፈ የሚፈይዱልን ነገር አይኖርም። መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ማጥናት፣ ለስብሰባዎች እንደ መዘጋጀትና በስብሰባዎች ላይ እንደ መገኘት እንዲሁም በአገልግሎት ላይ አዘውትሮ እንደ መካፈል የመሳሰሉ መንፈሳዊ ልማዶቻችንን ሊያስተጓጉሉብንና ወጥመድ ሊሆኑብን ይችላሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ” በማለት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ማስታወሳችን ተገቢ ነው። w16.07 1:3, 4
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 8
ብዙ “አማልክት” . . . ቢኖሩም እንኳ እኛ . . . አንድ አምላክ አብ አለን።—1 ቆሮ. 8:5, 6
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ አይሁዳውያንን፣ ግሪካውያንን፣ ሮማውያንንና ሌሎች ዜጎችን ያቀፈ ነበር። እነዚህ ሰዎች የተለያየ ሃይማኖት፣ ባሕልና ምርጫ ነበራቸው። በዚህም የተነሳ አንዳንዶች አዲሱን የአምልኮ ሥርዓት መከተል ወይም የቀድሞ ልማዶቻቸውን ሙሉ በሙሉ መተው ከብዷቸው ነበር። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ፣ እነዚህ ክርስቲያኖች አንድ አምላክ ብቻ እንዳላቸው ይኸውም ይሖዋን ብቻ ማምለክ እንደሚገባቸው ማሳሰብ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶታል። በዛሬው ጊዜ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለው ሁኔታስ ምን ይመስላል? ነቢዩ ኢሳይያስ “በዘመኑ መጨረሻ” ላይ ከብሔራት ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች በተራራ ወደተመሰለው ወደ እውነተኛው አምልኮ እንደሚጎርፉ ትንቢት ተናግሮ ነበር። እነዚህ ሰዎች “[ይሖዋ] ስለ መንገዶቹ ያስተምረናል፤ በጎዳናዎቹም እንሄዳለን” ይላሉ። (ኢሳ. 2:2, 3) ይህ ትንቢት ሲፈጸም የማየት አጋጣሚ በማግኘታችን እንዴት ታድለናል! ትንቢቱ በመፈጸሙ ጉባኤዎቻችን የተለያየ ዘር፣ ባሕልና ቋንቋ ያላቸውን ወንድሞችና እህቶች ያቀፉ ሆነዋል፤ ይህም ለይሖዋ ውዳሴ ያመጣል። w16.06 3:15, 16
እሁድ፣ ታኅሣሥ 9
ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ስላለን ከእሱ ጋር አስነሳን፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር በሰማያዊ ስፍራ አስቀመጠን።—ኤፌ. 2:6
ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ዙፋን ላይ ተቀምጠው በሚገዙበት ጊዜ ይሖዋ ምን ዓይነት አስደናቂ ነገሮች እንደሚሰጣቸው መገመት ያዳግታል። (ሉቃስ 22:28-30፤ ፊልጵ. 3:20, 21፤ 1 ዮሐ. 3:2) ቅቡዓኑ “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” ይኸውም የክርስቶስ ሙሽራ ይሆናሉ። (ራእይ 3:12፤ 17:14፤ 21:2, 9, 10) እነዚህ ቅቡዓን፣ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ወጥተው ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ በመርዳት ከኢየሱስ ጋር ሆነው ‘ሕዝቦችን ይፈውሳሉ።’ (ራእይ 22:1, 2, 17) የይሖዋ ጸጋ በምድር ላይ ከሚገለጽባቸው አስደናቂ መንገዶች አንዱ ‘በመቃብር’ ያሉ ሰዎች ከሞት መነሳታቸው ይሆናል። (ኢዮብ 14:13-15፤ ዮሐ. 5:28, 29) ክርስቶስ መሥዋዕት ሆኖ ከመሞቱ በፊት በነበሩት ዘመናት የሞቱ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ቀናት በታማኝነት የሚያንቀላፉ “ሌሎች በጎች” ሁሉ ትንሣኤ አግኝተው ይሖዋን ማገልገላቸውን ይቀጥላሉ።—ዮሐ. 10:16፤ w16.07 4:13-15
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 10
ይህ የእንቅልፍና የእረፍት ሰዓት ነው?—ማር. 14:41
“ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ” የሚለውን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ፣ ፍላጎት ብቻ በቂ አይደለም። በጌትሴማኒ የአትክልት ቦታ ደቀ መዛሙርቱ ካጋጠማቸው ሁኔታ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ኢየሱስ ለይሖዋ ምልጃ እንዲያቀርቡ ነግሯቸው ነበር። (ሉቃስ 21:36) እኛም በመንፈሳዊ እንዳናንቀላፋ ከፈለግን በጸሎት ረገድ ምንጊዜም ንቁዎች መሆን አለብን። (1 ጴጥ. 4:7) ኢየሱስ መጨረሻው የሚመጣው ‘ባላሰብነው ሰዓት’ እንደሆነ ስለተናገረ አሁን በመንፈሳዊ የምናሸልብበት እንዲሁም ሰይጣንም ሆነ እሱ የሚቆጣጠረው ዓለም የሚያቀርባቸውን የማይጨበጡና ሥጋችንን የሚያማልሉ ነገሮች የምናሳድድበት ጊዜ አይደለም። (ማቴ. 24:44) ይሖዋና ኢየሱስ፣ ስላዘጋጁልንና በቅርቡ ስለምናገኛቸው በረከቶች እንዲሁም ምንጊዜም ነቅተን መጠበቅ ስለምንችልበት መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነግረውናል። ለመንፈሳዊነታችንና ከይሖዋ ጋር ላለን ዝምድና ትኩረት መስጠት እንዲሁም የአምላክን መንግሥት ማስቀደም አለብን። በቅርቡ የሚፈጸመውን ክንውን ዝግጁ ሆነን መጠበቅ እንድንችል፣ ያለንበትን ጊዜ እንዲሁም በዙሪያችን የሚከናወኑትን ነገሮች ማስተዋል ይኖርብናል። (ራእይ 22:20) በሕይወት መትረፋችን የተመካው ንቁ በመሆናችን ላይ ነው! w16.07 2:15-17
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 11
እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።—ቆላ. 3:13
ጠንካራ ትዳር፣ አንዳቸው የሌላውን ስህተት በትዕግሥት የሚያልፉ ባልና ሚስት ጥምረት ነው። እንዲህ ያሉ ባልና ሚስት ‘እርስ በርስ ይቻቻላሉ፤ እንዲሁም በነፃ ይቅር ይባባላሉ።’ እርግጥ ነው፣ ሁለቱም ስህተት መሥራታቸው አይቀርም። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ባልና ሚስት ከስህተታቸው መማር፣ የትዳር ጓደኛቸውን ይቅር ማለት እንዲሁም “ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ” የሆነውን ፍቅር ማሳየት ይችላሉ። (ቆላ. 3:14) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። . . . ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም” ይላል። (1 ቆሮ. 13:4, 5) አለመግባባቶች በተቻለ ፍጥነት መፈታት አለባቸው። በመሆኑም አንድ ክርስቲያን ባልና ሚስት በመካከላቸው ለተፈጠረው ለማንኛውም ቅራኔ፣ ጀምበር ሳትጠልቅ እልባት ማበጀት ይኖርባቸዋል። (ኤፌ. 4:26, 27) “ስላስከፋሁህ ይቅርታ አድርግልኝ” ብሎ ከልብ ይቅርታ መጠየቅ ትሕትና እና ድፍረት ይጠይቃል፤ ይሁንና የትዳር ጓደኛሞች እንዲህ ማድረጋቸው ችግሮችን በመፍታት ብሎም በመካከላቸው ያለውን ጥምረት በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። w16.08 2:6
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 12
ጥሩ መመሪያ እሰጣችኋለሁ።—ምሳሌ 4:2
ኢየሱስ ዋነኛ ሥራው የመንግሥቱን ምሥራች ማወጅ ነበር። ይሁንና እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሌሎችን ለማሠልጠን ጊዜ መድቧል። (ማቴ. 10:5-7) ፊልጶስ በወንጌላዊነቱ ሥራ ተጠምዶ የነበረ ቢሆንም አራት ሴቶች ልጆቹን፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን ለሌሎች በማካፈሉ ሥራ ውጤታማ እንዲሆኑ እንደረዳቸው አያጠራጥርም። (ሥራ 21:8, 9) በዛሬው ጊዜስ እንዲህ ዓይነቱን ሥልጠና መስጠት ምን ያህል አስፈላጊ ነው? በዓለም ዙሪያ ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። አዲሶች ገና ከመጠመቃቸውም በፊት መጽሐፍ ቅዱስን በግላቸው የማጥናትን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ማድረግ ያስፈልጋል። ለሌሎች ምሥራቹን መስበክና እውነትን ማስተማር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ መማርም ይኖርባቸዋል። በጉባኤዎቻችን ውስጥ ያሉ ወንድሞች፣ የጉባኤ አገልጋዮችና ሽማግሌዎች ለመሆን የሚያስፈልጓቸውን ብቃቶች ለማሟላት እንዲጣጣሩ መበረታታት ያስፈልጋቸዋል። የጎለመሱ ክርስቲያኖች ለአዲሶች “ጥሩ መመሪያ” በመስጠት መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ሊረዷቸው ይችላሉ። w16.08 4:1, 2
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 13
የደከሙትን እጆች አበርቱ፤ የሚብረከረኩትንም ጉልበቶች አጽኑ።—ኢሳ. 35:3
ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን ማገልገላችን አንድነት እንዲኖረን ያደርጋል። በተጨማሪም ዘላቂ ወዳጅነት እንድንመሠርትና የአምላክ መንግሥት በሚያመጣቸው በረከቶች ላይ ያለን እምነት እንዲጠናከር ይረዳናል። የሌሎችን እጅ በምናበረታበት ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎችን እንዲቋቋሙ ብሎም ስለ ወደፊቱ ጊዜ አዎንታዊና ብሩህ አመለካከት እንዲኖራቸው እንረዳቸዋለን። (ኢሳ. 35:4) ከዚህም ሌላ ለሌሎች እንዲህ ዓይነት እገዛ ማድረጋችን እኛም ምንጊዜም መንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት እንድናደርግና አምላክ ያዘጋጀልን ሽልማት እውን ሆኖ እንዲታየን ያደርጋል። በእርግጥም ሌሎችን ስናበረታታ የእኛም እጆች ይበረታሉ። ይሖዋ፣ በጥንት ጊዜ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ታማኝ አገልጋዮቹን እንዴት እንደረዳቸውና ጥበቃ እንዳደረገላቸው መመልከታችን በዛሬው ጊዜ በእሱ ላይ እንድንተማመን ያደርገናል። እንግዲያው ተጽዕኖ ሲደርስባችሁና ችግሮች ሲያጋጥሟችሁ ‘እጆቻችሁ አይዛሉ!’ (ሶፎ. 3:16) ይልቁንም በጸሎት የይሖዋን እርዳታ ጠይቁ፤ እንዲሁም በኃያል እጁ እንዲያጠነክራችሁና የመንግሥቱን በረከቶች ለማግኘት እንዲረዳችሁ ፍቀዱለት።—መዝ. 73:23, 24፤ w16.09 1:16-18
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 14
ማንኛውም ድርጊትና ማንኛውም ተግባር ጊዜ አለው።—መክ. 3:17
የአምላክ አገልጋዮች አለባበስን በተመለከተ ውሳኔ ሲያደርጉ የዛሬውን የዕለት ጥቅስ በአእምሯቸው ይይዛሉ። የአየሩ ጠባይ፣ የወቅቶች መለዋወጥ እንዲሁም የተለያዩ ሁኔታዎች በአለባበሳችን ላይ ተጽዕኖ እንደሚያደርጉ የታወቀ ነው። የይሖዋ መሥፈርቶች ግን እንደ አየሩ ጠባይ አይለዋወጡም። (ሚል. 3:6) በተለይ በሞቃት አካባቢዎች አለባበሳችን ሥርዓታማ እንዲሁም ማስተዋልና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ የተንጸባረቀበት እንዲሆን ማድረግ ፈታኝ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም በጣም የተጣበቀ ወይም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ሰውነትን የሚያጋልጥ ልብስ ከመልበስ ብንቆጠብ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ደስ ይላቸዋል። (ኢዮብ 31:1) በተጨማሪም በባሕር ዳርቻዎች ወይም በመዋኛ ስፍራዎች በምንዝናናበት ጊዜ የዋና ልብሳችን ሥርዓታማ ሊሆን ይገባል። (ምሳሌ 11:2, 20) በዓለም ላይ ብዙዎች ሰውነትን የሚያጋልጥ የዋና ልብስ ቢለብሱም እንኳ እኛ የይሖዋ አገልጋዮች ቅዱስ የሆነውንና የምንወደውን አምላካችንን የሚያስከብር አለባበስ ሊኖረን ይገባል። w16.09 3:11, 12
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 15
ስለ እኔ ማንነት ምን ትላላችሁ?—ማቴ. 16:15
ኢየሱስ ተከታዮቹ ምን ብለው እንደሚያምኑ ከመጠየቅ ወደኋላ አላለም። እናንተም የእሱን ምሳሌ ተከተሉ። ከልጆቻችሁ ጋር ስትጨዋወቱ ስሜታቸውን እንዲገልጹ አበረታቷቸው። ልጃችሁ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተመለከተ ጥርጣሬ ካደረበት፣ ከመቆጣት ወይም እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ እንዳልሆነ እንዲሰማው ከማድረግ ተቆጠቡ። ከዚህ ይልቅ ጉዳዩን በጥሞና እንዲያመዛዝን በትዕግሥት እርዱት። እንደ እውነቱ ከሆነ ልጃችሁ በቅንነት የሚያነሳቸው ጥያቄዎች፣ ለጉዳዩ ትኩረት እንደሰጠውና የማወቅ ፍላጎት እንዳለው ይጠቁማሉ። ኢየሱስ ገና በ12 ዓመቱ ቁም ነገር ያዘሉ ጥያቄዎችን ጠይቋል። (ሉቃስ 2:46) ልጆቻችሁን በሚገባ እወቋቸው፤ ይኸውም አስተሳሰባቸውን፣ ስሜታቸውንና የሚያሳስቧቸውን ነገሮች ለመረዳት ጥረት አድርጉ። አብረዋችሁ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስለሚገኙና በአገልግሎት ስለሚካፈሉ ብቻ በይሖዋ ላይ እምነት እንዳላቸው አድርጋችሁ አታስቡ። ከልጆቻችሁ ጋር አብራችሁ በምታሳልፉት በማንኛውም ጊዜ በውይይታችሁ ውስጥ መንፈሳዊ ነገሮችን ለማካተት ጥረት አድርጉ። ከልጆቻችሁ ጋር ሆናችሁ ጸልዩ፤ እንዲሁም እነሱን በተመለከተ ጸልዩ። ከእምነታቸው ጋር በተያያዘ የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ፈተና ለማስተዋል ጥረት አድርጉ፤ ፈተናውን እንዲወጡትም እርዷቸው። w16.09 5:3-5
እሁድ፣ ታኅሣሥ 16
መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው።—ማቴ. 5:3
በዛሬው ጊዜ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹ “በምድር ላይ ለሚኖር ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ” እንደሚሰበክ የሚገልጸው ራእይ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው። (ራእይ 14:6) አንተስ ሌላ ቋንቋ እየተማርክ ነው? ሚስዮናዊ ሆነህ ወይም ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አገር ሄደህ እያገለገልክ ነው? አሊያም በአገርህ ውስጥ በውጭ አገር ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ላይ መገኘት ጀምረሃል? የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን መንፈሳዊነት ቅድሚያ መስጠት ይኖርብናል። ሆኖም ሕይወታችን በተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተጠመደ ከመሆኑ የተነሳ ትርጉም ያለው የግል ጥናት ማድረግ ከባድ የሚሆንብን ጊዜ አለ። በሌላ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉ ክርስቲያኖች ደግሞ ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች፣ አዲስ ቋንቋ ከመማር በተጨማሪ አዘውትረው ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ መመገብ ይኖርባቸዋል።—1 ቆሮ. 2:10፤ w16.10 2:1-3
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 17
ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ።—ማቴ. 26:52
የይሖዋ ምሥክሮች ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ከባድ ስደት ቢደርስባቸውም ምንጊዜም በተስፋቸው ይደሰታሉ። ለምሳሌ በሲንጋፖር፣ በኤርትራ እና በደቡብ ኮሪያ በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ታስረዋል፤ አብዛኞቹ የታሰሩት ኢየሱስ ሰይፍ እንዳንመዝ የሰጠውን ትእዛዝ በማክበራቸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኞቹ የይሖዋ ሕዝቦች ከባድ ስደት አላጋጠማቸውም። እነሱ የደረሰባቸው የእምነት ፈተና ሌላ ነው። ድህነትን ተቋቁመው የሚኖሩ አሊያም በጦርነት ወይም በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት መከራ የደረሰባቸው በርካታ ወንድሞች አሉ። ሌሎች ደግሞ እንደ ሙሴና የጥንት የእምነት አባቶች፣ በዚህ ዓለም ላይ የተደላደለ ሕይወት ወይም ዝና የማግኘት አጋጣሚያቸውን መሥዋዕት አድርገዋል። ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድና የራሳቸውን ፍላጎት በማሟላት ላይ ያተኮረ ሕይወት እንዲመሩ በሚቀርብላቸው ፈተና ላለመሸነፍ ከፍተኛ ትግል ያደርጋሉ። እነዚህ ወንድሞች እንዲጸኑ የረዳቸው ምንድን ነው? ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር እንዲሁም ይሖዋ ማንኛውንም የፍትሕ መጓደል እንደሚያስተካክልና ታማኝ አገልጋዮቹን ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት በመስጠት እንደሚባርካቸው ያላቸው ጠንካራ እምነት ነው።—መዝ. 37:5, 7, 9, 29፤ w16.10 3:15, 16
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 18
ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ ተስፋ የቆረጡትንም ያድናል።—መዝ. 34:18 ግርጌ
ኤርምያስ በፍርሃት በተዋጠበትና ተስፋ በቆረጠበት ጊዜ ይሖዋ ይህን ታማኝ ነቢይ አደፋፍሮታል። (ኤር. 1:6-10) አረጋዊው ነቢይ ዳንኤል፣ አምላክ አንድ መልአክ ልኮ “እጅግ የተወደድክ” ወይም “እጅግ የተከበርክ” በማለት ባጽናናው ጊዜ ምንኛ ተበረታቶ ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው! (ዳን. 10:8, 11, 18, 19 ግርጌ) አንተስ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አስፋፊዎች፣ አቅኚዎች እንዲሁም በዕድሜ የገፉ ወንድሞችና እህቶች ታበረታታለህ? አምላክ፣ ከሚወደው ልጁ ጋር ለብዙ ዘመናት አብሮ ቢሠራም ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ምስጋናና ማበረታቻ እንደማያስፈልገው አልተሰማውም። እንዲያውም ይሖዋ በሁለት ወቅቶች “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት ስለ ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴ. 3:17፤ 17:5) በዚህ መንገድ አምላክ ኢየሱስን ያበረታታው ከመሆኑም ሌላ ሥራውን እንደሚያደንቅ ገልጾለታል። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ባለው ምሽት በከፍተኛ ጭንቀት ተውጦ በነበረበት ጊዜም ይሖዋ መልአኩን ልኮ አበረታቶታል።—ሉቃስ 22:43፤ w16.11 1:7, 8
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 19
ለቁጣ አትቸኩል።—መክ. 7:9
እንደተናቅን ወይም ተገቢ ያልሆነ ነገር እንደተደረገብን በሚሰማን ጊዜ ስሜታችንን መቆጣጠር ከባድ ሊሆንብን ይችላል። በዘራችን፣ በቆዳችን ቀለም አሊያም በውጫዊ ገጽታችን ምክንያት ብንነቀፍ ስሜታችን በጣም እንደሚጎዳ የታወቀ ነው። ይህን ያደረገው የእምነት ባልንጀራችን ሲሆን ደግሞ ሁኔታው ምንኛ የከፋ ይሆናል! በዚህ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስሜታችንን እንድንቆጣጠር እንዲሁም ቶሎ እንዳንቆጣ የሚሰጠንን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ምንኛ ጠቃሚ ነው! (ምሳሌ 16:32) ማንኛችንም ብንሆን ቶሎ ቅር ላለመሰኘትና ይበልጥ ይቅር ባይ ለመሆን ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልገን ጥርጥር የለውም። ይሖዋና ኢየሱስ ይቅር ባይ መሆንን ትልቅ ቦታ ይሰጡታል። (ማቴ. 6:14, 15) አንተስ ይቅር ባይ ከመሆን ወይም ቁጣህን ከመቆጣጠር ጋር በተያያዘ ይበልጥ መሥራት ያስፈልግህ ይሆን? ቁጣቸውን የመቆጣጠር ችግር ያለባቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ምሬት ያድርባቸዋል። በመሆኑም ሌሎች ይርቋቸዋል። በምሬት የተሞላ ሰው በጉባኤ ውስጥ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።—ዘሌ. 19:17, 18፤ w16.11 3:4-6
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 20
ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ኅብረት አለው? ወይስ ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ያገናኘዋል?—2 ቆሮ. 6:14
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተጠሙት ቻርልስ ቴዝ ራስል እና ተባባሪዎቹ በ1800ዎቹ መገባደጃ አካባቢ መጽሐፍ ቅዱስን በተደራጀ መልኩ ማጥናት ጀመሩ። መጀመሪያ ላይ የወንድም ራስል ዓላማ፣ ታዋቂ ከሆኑት ሃይማኖቶች መካከል እውነቱን የሚያስተምረው የትኛው ሃይማኖት እንደሆነ ማወቅ ነበር። ክርስቲያን ያልሆኑትን ጨምሮ በርካታ ሃይማኖቶች የሚያስተምሩትን ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በጥንቃቄ አነጻጸረው። ከእነዚህ ሃይማኖቶች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ የአምላክን ቃል በጥብቅ እንደማይከተሉ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደበትም። እንዲያውም በአንድ ወቅት በአካባቢው ያሉ የተወሰኑ ቀሳውስትን ሰብስቦ አወያይቷቸው ነበር፤ ይህን ያደረገው እነዚህ ሰዎች፣ እሱና ተባባሪዎቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኟቸውን እውነቶች እንደሚቀበሉና ለጉባኤዎቻቸው አባላት እንደሚያስተምሩ ተስፋ አድርጎ ነው። ቀሳውስቱ ግን ይህን ማድረግ አልፈለጉም። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የሚከተለውን ሐቅ ለመገንዘብ ተገደዱ፦ የሐሰት ሃይማኖትን የሙጥኝ ለማለት ከመረጡ ሰዎች ጋር ተባብሮ መሥራት የማይቻል ነገር ነው። w16.11 4:14
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 21
የአካል ክፍሎቻችሁን ቅዱስ ሥራ ለመሥራት የጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አቅርቡ።—ሮም 6:19
ለአምላክ ጸጋ ያለን አድናቆት ምንዝርንና ስካርን ወይም የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ይፈጽሟቸው የነበሩ ሌሎች ኃጢአቶችን ከማስወገድ ያለፈ ነገር እንድናደርግ ይገፋፋናል። (1 ቆሮ. 6:9-11) ለአምላክ ጸጋ አድናቆት ካለን ከፆታ ብልግና ብቻ ሳይሆን ወራዳ ከሆኑ መዝናኛዎች በሙሉ እንርቃለን። የአካል ክፍሎቻችንን የጽድቅ ባሪያዎች አድርገን ለማቅረብ እንድንችል፣ ከስካር በመራቅ ብቻ ከመወሰን ይልቅ ሞቅ እስኪለን ድረስ ከመጠጣትም እንቆጠባለን። እንዲህ ያሉትን መጥፎ ድርጊቶች ማስወገድ ከፍተኛ ትግል የሚጠይቅ ቢሆንም በትግሉ ማሸነፍ እንችላለን። ግባችን ከከባድ ኃጢአቶችም ሆነ ቀለል ተደርገው ከሚታዩ መጥፎ ድርጊቶች መራቅ ነው። እርግጥ ከእነዚህ ድርጊቶች ሙሉ በሙሉ መራቅ አንችልም። ያም ቢሆን እንደ ጳውሎስ ይህን ለማድረግ መጣር ይኖርብናል። ጳውሎስ ወንድሞቹን “ኃጢአት ለሰውነታችሁ ምኞት ተገዢ እንድትሆኑ በማድረግ ሟች በሆነው ሰውነታችሁ ላይ መንገሡን እንዲቀጥል አትፍቀዱ” በማለት አሳስቧቸዋል።—ሮም 6:12፤ 7:18-20፤ w16.12 1:16, 19-21
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 22
የመንፈስ ፍሬ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው።—ገላ. 5:22, 23
በሰማይ ያለው አባታችን ለሚጠይቁት መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጣቸው ኢየሱስ ቃል ገብቷል። (ሉቃስ 11:10-13) የአምላክ መንፈስ ፍሬ ማለትም የአምላክ መንፈስ የሚያስገኛቸው መልካም ባሕርያት፣ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ማንነት ያንጸባርቃሉ። (ቆላ. 3:10) የዚህን መንፈስ ፍሬ ስታፈራ ከሌሎች ጋር ያለህ ዝምድና ይሻሻላል። ይህ ደግሞ ጭንቀት ሊያስከትሉ የሚችሉ የተለያዩ ሁኔታዎችን ለማስቀረት ይረዳሃል። “ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች” ራስህን ዝቅ ለማድረግም ሆነ ‘የሚያስጨንቅህን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ለመጣል’ ትሕትና እንደሚያስፈልግህ ግልጽ ነው። (1 ጴጥ. 5:6, 7) ትሕትና ካዳበርክ ደግሞ የአምላክን ሞገስና ድጋፍ ታገኛለህ። (ሚክ. 6:8) አካልህ፣ አእምሮህና ስሜትህ መቋቋም የሚችለው ነገር ውስን እንደሆነ ከተገነዘብክ በአምላክ ትታመናለህ፤ ይህም ከልክ በላይ እንዳትጨነቅ ይረዳሃል። w16.12 3:7, 12
እሁድ፣ ታኅሣሥ 23
[ኖኅ] የጽድቅ ሰባኪ [ነበረ]።—2 ጴጥ. 2:5
“የጽድቅ ሰባኪ” የነበረው ኖኅ፣ አምላክ የማስጠንቀቂያ መልእክት እንዲያውጅ የሰጠውን ሥራ በታማኝነት አከናውኗል። ኖኅ እንዲህ ማድረጉ እምነቱን ለማጠናከር እንደረዳው ግልጽ ነው። ከስብከት ሥራው በተጨማሪ ጉልበቱንና የማሰብ ችሎታውን ተጠቅሞ አምላክ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት መርከብ ሠርቷል። (ዕብ. 11:7) ልክ እንደ ኖኅ፣ እኛም ‘የጌታ ሥራ የበዛልን’ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን። (1 ቆሮ. 15:58) ይህ ሥራ፣ የአምልኮ ቦታዎችን መገንባትንና መጠገንን፣ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ በፈቃደኝነት ማገልገልን እንዲሁም በቅርንጫፍ ቢሮ ወይም በርቀት የትርጉም ቢሮዎች ውስጥ ማገልገልን ይጨምራል። ከሁሉም በላይ ግን ምንጊዜም በስብከቱ ሥራ መጠመድ ይኖርብናል፤ ይህም ተስፋችን ይበልጥ ብሩህ እንዲሆንልን ያደርጋል። በእርግጥም በስብከቱ ሥራ መካፈላችን ለሕይወት በምናደርገው ሩጫ ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል።—1 ቆሮ. 9:24፤ w17.01 1:8, 9
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 24
እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል።—ገላ. 6:5
ሌሎችም የራሳቸውን ውሳኔ የማድረግ ነፃነት እንዳላቸው አምነን መቀበል አለብን። ለምን? እያንዳንዱ ክርስቲያን የመምረጥ ነፃነት ስለተሰጠው፣ ሁለት ክርስቲያኖች ሁልጊዜ ፍጹም አንድ ዓይነት ውሳኔ ያደርጋሉ ብሎ መጠበቅ አይቻልም። ይህ ደግሞ በምናሳየው ምግባርና በምናቀርበው አምልኮ ላይም እንኳ ሊንጸባረቅ ይችላል። እያንዳንዱ ክርስቲያን “የራሱን የኃላፊነት ሸክም” መሸከም እንዳለበት ከተገነዘብን ሌሎች ሰዎች ያን ያህል ትልቅ ቦታ በማይሰጣቸው ጉዳዮችም ረገድ የመምረጥ ነፃነታቸውን ተጠቅመው የራሳቸውን ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳላቸው አምነን እንቀበላለን። (1 ቆሮ. 10:32, 33) ይሖዋ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል፤ ይህም እውነተኛ ነፃነት ያስገኝልናል። (2 ቆሮ. 3:17) የመምረጥ ነፃነታችን ይሖዋን ምን ያህል እንደምንወደው የሚያሳዩ ውሳኔዎችን ለማድረግ ስለሚያስችለን ለዚህ ስጦታ ከፍተኛ አድናቆት አለን። ይህን ውድ ስጦታ ለአምላክ ክብር በሚያመጣና ሌሎች ያላቸውን የመምረጥ ነፃነት እንደምናከብር በሚያሳይ መንገድ በመጠቀም ስጦታውን ከፍ አድርገን መመልከታችንን እንቀጥል። w17.01 2:15, 17, 18
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 25
በራሴ ተነሳስቼ አንዳች ነገር እንደማላደርግ ከዚህ ይልቅ እነዚህን ነገሮች የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ መሆኑን ታውቃላችሁ።—ዮሐ. 8:28
የሰዎችን ልብ መማረክ የምንችለው ጉራ በመንዛት ወይም አላስፈላጊ ትኩረት ወደ ራሳችን በመሳብ ሳይሆን “የሰከነና ገር መንፈስ” በማሳየት እንደሆነ እንገነዘባለን። (1 ጴጥ. 3:3, 4፤ ኤር. 9:23, 24) በልባችን ውስጥ የኩራት ስሜት ካለ ውሎ አድሮ በድርጊታችን መታየቱ አይቀርም። ለምሳሌ ያህል፣ ልዩ መብት እንዳለን፣ አንዳንድ ሚስጥሮችን እንደምናውቅ ወይም ኃላፊነት ካላቸው ወንድሞች ጋር የተለየ ቅርርብ እንዳለን ጠቆም እናደርግ ይሆናል። አሊያም ደግሞ የሌሎች አስተዋጽኦ ያለበት አንድ ሐሳብ ወይም ድርጊት የእኛ ብቻ እንደሆነ በሚያስመስል መልኩ ልናወራ እንችላለን። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ኢየሱስ የተናገረው አብዛኛው ነገር በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተወሰደ ነበር። ኢየሱስ በንግግሩ ልኩን እንደሚያውቅ አሳይቷል፤ ይህን ያደረገው አድማጮቹ የሚናገረው ነገር በራሱ እውቀትና ጥበብ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን ከይሖዋ የመጣ እንደሆነ እንዲያውቁ ይፈልግ ስለነበር ነው። w17.01 4:12
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 26
ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ . . . አትብላ።—ዘፍ. 2:17
ይህ ለመረዳት የሚከብድ ሕግ አልነበረም። አዳምና ሔዋን በአትክልቱ ስፍራ የተትረፈረፈ ምግብ ስለነበራቸው ይህን ሕግ መታዘዝ ሊከብዳቸው አይገባም። ሰይጣን ዲያብሎስ በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን በማታለል በሰማዩ አባቷ በይሖዋ ላይ እንድታምፅ አደረጋት። (ዘፍ. 3:1-5፤ ራእይ 12:9) ሰይጣን የአምላክ ሰብዓዊ ልጆች “በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ” መብላት የማይችሉ መሆኑ ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ጥያቄ አነሳ። ሰይጣን ‘የምትፈልጉትን ነገር ማድረግ አትችሉም ማለት ነው?’ ያለ ያህል ነበር። ከዚያም “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም” በማለት ዓይን ያወጣ ውሸት ተናገረ። ቀጥሎም “አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡ . . . ስለሚያውቅ ነው” በማለት ሔዋን አምላክን መታዘዝ እንደማያስፈልጋት ሊያሳምናት ሞከረ። ሰይጣን እንዲህ ሲል፣ ይሖዋ ከፍሬው እንዳይበሉ ያዘዛቸው ልዩ እውቀት እንዳያገኙ ብሎ እንደሆነ አድርጎ መናገሩ ነበር። በተጨማሪም ፍሬውን ቢበሉ “መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ” እንደሚሆኑ በመግለጽ የሐሰት ተስፋ ሰጣቸው። w17.02 1:8, 9
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 27
አምላክህ ይሖዋ ከወንድሞችህ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳልሃል። እናንተም እሱን ማዳመጥ ይኖርባችኋል።—ዘዳ. 18:15
ኢሳይያስ፣ ይህ ነቢይ “መሪና አዛዥ” እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል። (ኢሳ. 55:4) ዳንኤልም “መሪ የሆነው መሲሕ” እንደሚመጣ በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (ዳን. 9:25) በመጨረሻም ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ሕዝቦች “መሪ” እሱ እንደሆነ ገልጿል። (ማቴ. 23:10) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በገዛ ፈቃዳቸው ተነሳስተው የተከተሉት ሲሆን ይሖዋ እሱን እንደመረጠው ያምኑ ነበር። (ዮሐ. 6:68, 69) ይሁንና ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ብለው እንዲያምኑ ያደረጋቸው ምንድን ነው? አጥማቂው ዮሐንስ፣ ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት “ሰማያት ተከፍተው መንፈስ እንደ ርግብ በእሱ ላይ ሲወርድ” ተመልክቶ ነበር። (ማር. 1:10-12) ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ ተአምራትን እንዲፈጽምና ይሖዋ በሰጠው ሥልጣን እንዲናገር መንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰጥቶታል። (ሥራ 10:38) በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ፣ ኢየሱስ እንደ ፍቅር፣ ደስታና ጠንካራ እምነት ያሉትን ባሕርያት እንዲያፈራ ረድቶታል። (ዮሐ. 15:9፤ ዕብ. 12:2) ኢየሱስ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ድጋፍ እንዳለው በግልጽ ታይቷል። ኢየሱስን መሪ እንዲሆን የመረጠው ይሖዋ ነው። w17.02 3:15, 16
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 28
በመካከላችሁ ሆነው አመራር የሚሰጡትን አስቡ።—ዕብ. 13:7
በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ ሐዋርያት ለክርስቲያን ጉባኤ አመራር መስጠት ጀመሩ። በዚያ ወቅት “ጴጥሮስ . . . ከአሥራ አንዱ ጋር ተነስቶ በመቆም” በቦታው ለተሰበሰቡት በርካታ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ሕይወት አድን የሆነውን እውነት ተናገረ። (ሥራ 2:14, 15) ከእነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ አማኞች ሆኑ። ከዚያ በኋላ እነዚህ አዳዲስ ክርስቲያኖች “[የሐዋርያቱን] ትምህርት በትኩረት መከታተላቸውን ቀጠሉ።” (ሥራ 2:42) የጉባኤው ገንዘብ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርጉት ሐዋርያቱ ነበሩ። (ሥራ 4:34, 35) በተጨማሪም የአምላክ ሕዝቦች የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ምግብ ያቀርቡ ነበር፤ ሐዋርያቱ “እኛ . . . በጸሎትና ቃሉን በማስተማሩ ሥራ ላይ ሙሉ በሙሉ እናተኩራለን” ሲሉ ተናግረዋል። (ሥራ 6:4) ከዚህም ሌላ አዳዲስ ወደሆኑ ክልሎች ሄደው የወንጌላዊነቱን ሥራ እንዲያከናውኑ ተሞክሮ ያላቸውን ክርስቲያኖች ይመድቡ ነበር። (ሥራ 8:14, 15) ውሎ አድሮ ሌሎች ቅቡዓን ሽማግሌዎችም ከሐዋርያት ጋር ሆነው ከጉባኤዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መከታተል ጀመሩ። እነዚህ ሽማግሌዎችና ሐዋርያት፣ የበላይ አካል ሆነው ለሁሉም ጉባኤዎች አመራር ይሰጡ ነበር።—ሥራ 15:2፤ w17.02 4:4
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 29
ለሁሉም የሚገባውን አስረክቡ፤ . . . መከበር የሚፈልገውን አክብሩ።—ሮም 13:7
በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያለው መንፈስ በብዙ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። በዚህም ምክንያት ብዙዎች፣ ለሌሎች ሰዎች ተገቢውን አክብሮት ከማሳየት ይልቅ አምልኮ አከል ክብር ይሰጧቸዋል። ለሃይማኖትና ለፖለቲካ መሪዎች፣ ለታዋቂ ስፖርተኞችና በመዝናኛው ዓለም ላሉ ስመ ጥር ሰዎች እንዲሁም ለሌሎች ዝነኛ ግለሰቦች በጣም የተጋነነ አመለካከት ስላላቸው ለሰው ከሚገባው ያለፈ አክብሮት ያሳዩዋቸዋል። ወጣት አዋቂ ሳይል አብዛኛው ሰው እነዚህን ግለሰቦች እንደ አርዓያ በመውሰድ የእነሱን አኳኋን፣ አለባበስ ወይም ምግባር ይከተላል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሰዎች አክብሮት በማሳየት ረገድ እንዲህ ያለ የተዛባ አመለካከት ላለማዳበር ይጠነቀቃሉ። ፍጹም አርዓያ የተወልን፣ ልንመስለው የሚገባ ሰው ክርስቶስ ብቻ ነው። (1 ጴጥ. 2:21) ሰዎችን ከሚገባቸው በላይ ክብር የምንሰጣቸው ከሆነ አምላክን እናሳዝናለን። “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል” የሚለውን እውነታ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። (ሮም 3:23) በእርግጥም አምልኮ አከል ክብር የሚገባው አንድም ሰው የለም። w17.03 1:6-8
እሁድ፣ ታኅሣሥ 30
አሳ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ልቡ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ ነበር።—1 ነገ. 15:14
እያንዳንዳችን ሙሉ ለሙሉ ለአምላክ ያደርን መሆናችንን ለማወቅ ልባችንን መመርመር ይኖርብናል። ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ይሖዋን ለማስደሰት፣ ከእውነተኛው አምልኮ ጎን ለመቆም እንዲሁም የጉባኤውን ንጽሕና ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ?’ ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የምትቀርበው ሰው ቢወገድ ምን ታደርጋለህ? ከዚህ ግለሰብ ጋር ያለህን ግንኙነት በማቋረጥ ቁርጥ ያለ እርምጃ ትወስዳለህ? በዚህ ጊዜ ልብህ ምን እንድታደርግ ይገፋፋሃል? አንዳንድ ጊዜ አንተም እንደ አሳ፣ ልትቋቋመው የማትችለው ዓይነት ፈተና እንደገጠመህ ሆኖ ይሰማህ ይሆናል፤ በዚህ ጊዜ አሳ እንዳደረገው ሁሉ አንተም በአምላክ ላይ በመታመን እሱን በሙሉ ልብህ እንደምታገለግለው ማሳየት ትችላለህ። ለምሳሌ አብረውህ የሚማሩት ልጆች ወይም አስተማሪዎችህ የይሖዋ ምሥክር በመሆንህ ያሾፉብህና ይቀልዱብህ ይሆናል። አሊያም ደግሞ የሥራ ባልደረቦችህ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ስትል እረፍት በመውሰድህ ወይም አዘውትረህ ተጨማሪ ሰዓት ባለመሥራትህ እንደ ሞኝ ሊቆጥሩህ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ አሳ እንዳደረገው ወደ አምላክ ጸልይ። (2 ዜና 14:11) ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግህን ቀጥል። አምላክ አሳን እንዳበረታውና እንደረዳው ሁሉ አንተንም እንደሚያበረታህ አስታውስ። w17.03 3:6-8
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 31
ችኩሎች ሁሉ ግን ለድህነት ይዳረጋሉ።—ምሳሌ 21:5
የአምላክ ቃል፣ ከበድ ያለ ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ እንዳንቸኩል ያሳስበናል። ከምናደርገው ውሳኔ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ወይም ሁኔታዎችን በሙሉ ጊዜ ወስደን በሚገባ መመርመራችን ጥሩ ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል። (1 ተሰ. 5:21) የቤተሰብ ራሶች አንድ ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት በአምላክ ቃልና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎች ላይ ምርምር ማድረጋቸው እንዲሁም ሌሎች የቤተሰባቸው አባላት ያላቸውን አመለካከት ግምት ውስጥ ማስገባታቸው አስፈላጊ ነው። አምላክ፣ አብርሃምን የሚስቱን ሐሳብ እንዲሰማ እንዳሳሰበው አስታውስ። (ዘፍ. 21:9-12) ሽማግሌዎችም ጊዜ ወስደው ምርምር ማድረግ አለባቸው። ምክንያታዊና ትሑት ከሆኑ፣ ውሳኔያቸውን እንደገና ማጤን እንዳለባቸው የሚያሳይ ጠቃሚ የሆነ አዲስ መረጃ ሲያገኙ፣ ሌሎች ለእነሱ ያላቸው አክብሮት እንዳይቀንስ በመፍራት ይህን ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ አመለካከታቸውንና ውሳኔያቸውን ለማስተካከል ፈቃደኞች መሆን አለባቸው፤ ሁላችንም ብንሆን የእነሱን ምሳሌ መከተላችን ጠቃሚ ነው። ይህም በጉባኤ ውስጥ ሰላምና ሥርዓት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ያደርጋል።—ሥራ 6:1-4፤ w17.03 2:16