የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es18 ገጽ 108-118
  • ኅዳር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኅዳር
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2018
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሐሙስ፣ ኅዳር 1
  • ዓርብ፣ ኅዳር 2
  • ቅዳሜ፣ ኅዳር 3
  • እሁድ፣ ኅዳር 4
  • ሰኞ፣ ኅዳር 5
  • ማክሰኞ፣ ኅዳር 6
  • ረቡዕ፣ ኅዳር 7
  • ሐሙስ፣ ኅዳር 8
  • ዓርብ፣ ኅዳር 9
  • ቅዳሜ፣ ኅዳር 10
  • እሁድ፣ ኅዳር 11
  • ሰኞ፣ ኅዳር 12
  • ማክሰኞ፣ ኅዳር 13
  • ረቡዕ፣ ኅዳር 14
  • ሐሙስ፣ ኅዳር 15
  • ዓርብ፣ ኅዳር 16
  • ቅዳሜ፣ ኅዳር 17
  • እሁድ፣ ኅዳር 18
  • ሰኞ፣ ኅዳር 19
  • ማክሰኞ፣ ኅዳር 20
  • ረቡዕ፣ ኅዳር 21
  • ሐሙስ፣ ኅዳር 22
  • ዓርብ፣ ኅዳር 23
  • ቅዳሜ፣ ኅዳር 24
  • እሁድ፣ ኅዳር 25
  • ሰኞ፣ ኅዳር 26
  • ማክሰኞ፣ ኅዳር 27
  • ረቡዕ፣ ኅዳር 28
  • ሐሙስ፣ ኅዳር 29
  • ዓርብ፣ ኅዳር 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2018
es18 ገጽ 108-118

ኅዳር

ሐሙስ፣ ኅዳር 1

ልጄ ሆይ፣ ለሚነቅፈኝ መልስ መስጠት እችል ዘንድ ጥበበኛ ሁን፤ ልቤንም ደስ አሰኘው።—ምሳሌ 27:11

እንደ ሰይጣን አባባል ከሆነ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር ተነሳስቶ ይሖዋን የሚያገለግል ማንም የለም። (ኢዮብ 2:4, 5) ሰይጣን ይህን ግድድር ከሰነዘረ በኋላ ሐሳቡን ቀይሮ ይሆን? በፍጹም! ከሰማይ በተባረረበት ወቅት “ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ” ተብሎ ተጠርቷል። (ራእይ 12:10) ሰይጣን ንጹሕ አቋምን ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ የተነሳውን ጉዳይ አልረሳውም። በመከራ ተሸንፈን ስንወድቅና የአምላክን ሉዓላዊነት መደገፋችንን ስናቆም ለማየት ይጓጓል። እንግዲያው መከራ ሲያጋጥምህ የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። በአንድ ወገን፣ ሰይጣንና አጋንንት ያጋጠመህን መከራ መቋቋም እንደማትችልና እንደምትሸነፍ በመግለጽ ሲጠቋቆሙብህ ይታይህ። በሌላኛው ወገን ደግሞ ይሖዋ፣ በመግዛት ላይ ያለው ልጁ፣ ከሞት የተነሱት ቅቡዓንና እልፍ አእላፋት መላእክት አሉ። ጽናት በማሳየትህና የይሖዋን ሉዓላዊነት በመደገፍህ መደሰታቸውን በመግለጽ እያበረታቱህ ነው። ይሖዋ አንተን በግለሰብ ደረጃ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ እያለህ እንደሆነ አድርገህ አስብ። w16.04 2:8, 9

ዓርብ፣ ኅዳር 2

አንድ ወይም ሁለት ሰው ይዘህ ሂድ።—ማቴ. 18:16

ከእነሱ ጋር ሆነህ ጉዳዩን መፍታት ከቻልክ “ወንድምህን ታተርፋለህ።” ጉዳዩን ለሽማግሌዎች ማቅረብ የሚኖርብህ፣ ከበደለህ ሰው ጋር ያለህን አለመግባባት ለመፍታት ያደረግከው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ ከቀረ ብቻ ነው። በማቴዎስ 18:15-17 ላይ የተገለጹትን ሦስቱንም እርምጃዎች መውሰድ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ብዙ ጊዜ አያጋጥሙም። ይህ ደግሞ ደስ የሚል ነገር ነው፤ ብዙ ጊዜ ኃጢአተኛው ስህተቱን አምኖ የተፈጠረውን አለመግባባት ያስተካክላል፤ በመሆኑም ከጉባኤ አይወገድም። የተበደለው ግለሰብ፣ ከዚህ በኋላ ወንድሙን ለመክሰስ የሚያበቃ ምክንያት አይኖረውም፤ እንዲያውም ወንድሙን ይቅር ለማለት ሊመርጥ ይችላል። ሆኖም አለመግባባት ሲፈጠር ጉዳዩን ቶሎ ወደ ሽማግሌዎች መውሰድ ተገቢ እንዳልሆነ ኢየሱስ የሰጠው ምክር ይጠቁማል። ሽማግሌዎች ጣልቃ ሊገቡ የሚችሉት የመጀመሪያዎቹ ሁለት እርምጃዎች ከተወሰዱና በደል መፈጸሙን የሚያሳምን ተጨባጭ ማስረጃ ከተገኘ ብቻ ነው። w16.05 1:15, 16

ቅዳሜ፣ ኅዳር 3

እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም።—ዮሐ. 17:16

ለአምላክ መንግሥት በታማኝነት ለመገዛት የገለልተኝነት አቋማችንን መጠበቅ ይኖርብናል። እንዲህ የማናደርግ ከሆነ ለሰው ልጆች ችግሮች መፍትሔ የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ የሚገልጸውን ምሥራች በንጹሕ ሕሊና መስበክ እንዴት እንችላለን? በሌላ በኩል ደግሞ በፖለቲካ ውስጥ በመግባት ምዕመኖቻቸው እንዲከፋፈሉ ከሚያደርጉት የሐሰት ሃይማኖቶች በተለየ፣ እውነተኛው አምልኮ የገለልተኝነት አቋማችንን እንድንጠብቅ በመርዳት ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር እንዲኖረን ያደርጋል። (1 ጴጥ. 2:17) የሰይጣን ሥርዓት ወደ መጨረሻው እየተቃረበ ሲሄድ የገለልተኝነት አቋምን መጠበቅ ይበልጥ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል እንጠብቃለን። የምንኖረው “ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ” እንዲሁም ‘ግትር’ የሆኑ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ በመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይህ ዓለም ይበልጥ እየተከፋፈለ መሄዱ አይቀርም። (2 ጢሞ. 3:3, 4) በአንዳንድ አገሮች ፖለቲካዊ ሁኔታዎች በፍጥነት በመለዋወጣቸው፣ ወንድሞቻችን ከገለልተኝነት ጋር የተያያዙ ያልተጠበቁ ፈተናዎች አጋጥመዋቸዋል። እንግዲያው ገለልተኝነታችንን ለመጠበቅ አሁኑኑ አቋማችንን ማጠናከር እንዳለብን አስተዋላችሁ? ፈታኝ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ እጃችንን አጣጥፈን የምንጠብቅ ከሆነ አቋማችንን ልናላላና ገለልተኛ ሳንሆን ልንቀር እንችላለን። w16.04 4:3, 4

እሁድ፣ ኅዳር 4

አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።—ገላ. 6:7

አንዳንዶች፣ የፈለግነውን ውሳኔ ብናደርግ ምንም ለውጥ አያመጣም የሚል አመለካከት አላቸው። ይሁንና ይሖዋን የሚያስደስትና ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ለማድረግ ይሖዋ ባስጻፈው በቃሉ ውስጥ የሚገኙትን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች መመርመር ብሎም ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ደምን አስመልክቶ የሰጠውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ አለብን። (ዘፍ. 9:4፤ ሥራ 15:28, 29) ጸሎት፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ሕጎች ጋር የሚስማማ ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል። በሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋቸው ከበድ ያሉ ውሳኔዎች በመንፈሳዊ ጤንነታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። የምናደርገው እያንዳንዱ ውሳኔ ከይሖዋ ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ጥሩ ወይም መጥፎ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። ጥሩ ውሳኔ ማድረግ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና እንደሚያጠናክረው ሁሉ መጥፎ ውሳኔ ማድረግም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ያበላሸዋል። በተጨማሪም መጥፎ ውሳኔ ማድረጋችን ሌሎች እንዲረበሹ አልፎ ተርፎም እንዲሰናከሉ በማድረግ እምነታቸውን ሊያናጋው ይችላል፤ አሊያም ደግሞ የጉባኤውን ሰላም ያደፈርሰዋል። በእርግጥም የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ለውጥ ያመጣሉ።—ሮም 14:19፤ w16.05 3:4, 5

ሰኞ፣ ኅዳር 5

የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ . . . እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ።—ኢሳ. 48:17

አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና የግል ጥናት በማድረግ ‘ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ ለመጠቀም’ የምናደርገው ጥረት ይሖዋን እንደሚያስደስተው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ኤፌ. 5:15, 16) እርግጥ ነው፣ ለሁሉም መንፈሳዊ ምግብ እኩል ትኩረት የምንሰጠው ሁልጊዜ ላይሆን ይችላል። በመሆኑም ልንጠነቀቅበት የሚገባ ነገር አለ። ይህ ነገር ምንድን ነው? ከሚቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ መካከል አንዳንዱ እኛን እንደማይመለከተን አድርገን የምናስብ ከሆነ የሚያመልጠን ነገር ይኖራል፤ ይህ ደግሞ አደገኛ ነው። ለምሳሌ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እኛን እንደማይጠቅመን ቢሰማንስ? አሊያም ደግሞ አንድ ትምህርት በዋነኝነት የተዘጋጀው ለእኛ ባይሆንስ? ገረፍ ገረፍ አድርገን እናልፈዋለን? ወይም ጨርሶ ሳናነበው እንተወዋለን? እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በጣም ሊጠቅመን የሚችል ትምህርት እያመለጠን ነው። የሚቀርቡልን መንፈሳዊ ትምህርቶች ሁሉ ምንጭ አምላክ መሆኑን ሁላችንም ልናስታውስ ይገባል። w16.05 5:5, 6

ማክሰኞ፣ ኅዳር 6

አንድ ሰው ሳያውቅ የተሳሳተ ጎዳና ቢከተል መንፈሳዊ ብቃት ያላችሁ እናንተ እንዲህ ዓይነቱን ሰው በገርነት መንፈስ ለማስተካከል ጥረት አድርጉ።—ገላ. 6:1

ይሖዋ እኛን በግለሰብ ደረጃ ለመቅረጽ በክርስቲያን ጉባኤና በሽማግሌዎች ይጠቀማል። ለምሳሌ ያህል፣ ሽማግሌዎች ከመንፈሳዊነታችን ጋር በተያያዘ የሆነ ችግር እንዳለብን ካስተዋሉ እርዳታ ሊያደርጉልን ይሞክራሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ግን በሰብዓዊ ጥበብ ላይ ተመርኩዘው አይደለም። ይልቁንም ትሑት በመሆን አምላክ ማስተዋልና ጥበብ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ። ከዚያም የእኛን ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብተው በአምላክ ቃልና በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ላይ ምርምር በማድረግ ከጸሎታቸው ጋር የሚስማማ እርምጃ ይወስዳሉ። ይህም በግለሰብ ደረጃ የሚያስፈልገንን እርዳታ ለመስጠት ያስችላቸዋል። አምላክ እንዴት እንደሚቀርጸን መገንዘባችን፣ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን ጨምሮ በክልላችን ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። አምላክ ለውጥ እንዲያደርጉ ሰዎችን አያስገድድም፤ ይሁንና በፈቃዳቸው ሕይወታቸውን ለመለወጥና ማስተካከያዎችን ለማድረግ እንዲነሳሱ የጽድቅ መሥፈርቶቹን ያሳውቃቸዋል። w16.06 1:13, 14

ረቡዕ፣ ኅዳር 7

አንተ ግን ለራስህ ታላላቅ ነገሮችን ትፈልጋለህ። እንዲህ ያሉ ነገሮችን ፈጽሞ አትፈልግ።—ኤር. 45:5

ሐዋርያው ዮሐንስ፣ አንድ ሰው በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች የሚወድ ከሆነ ይኸውም ‘የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት’ ካለው እንዲሁም “ኑሮዬ ይታይልኝ” የሚል ከሆነ “የአብ ፍቅር በውስጡ የለም” ሲል ተናግሯል። (1 ዮሐ. 2:15, 16) በመሆኑም በዓለም ላይ ያለው መዝናኛና አለባበስ እንዲሁም ዓለማዊ ጓደኞች ልባችንን እየማረኩት መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ አዘውትረን ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል። በሌላ በኩል ደግሞ ከፍተኛ ትምህርት በመከታተል “ታላላቅ ነገሮችን” ለማግኘት የምንጥር ከሆነ ዓለምን እንደምንወድ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። አምላክ ቃል በገባልን አዲስ ዓለም ደፍ ላይ ነን። እንግዲያው ሙሴ በዘዳግም 6:4 ላይ የሰጠውን ጠንከር ያለ ምክር ማስታወሳችን በጣም አስፈላጊ ነው! “አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ” መሆኑን ከተገነዘብንና ከልባችን ካመንን እሱን ብቻ እናመልከዋለን፤ እንዲሁም ተቀባይነት ባለው መንገድ እናገለግለዋለን።—ዕብ. 12:28, 29፤ w16.06 3:14

ሐሙስ፣ ኅዳር 8

ዘወትር [የአምላክን መንግሥት] ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ይሰጧችኋል።—ሉቃስ 12:31

‘የሰው ልጅ፣ በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጉት ነገሮች ጥቂት ሲሆኑ የሚፈልጋቸው ነገሮች ግን ስፍር ቁጥር የላቸውም’ ሲባል እንሰማለን። ብዙዎች፣ በሚያስፈልጓቸው ቁሳዊ ነገሮችና እነሱ በሚፈልጓቸው ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት የሚያስተውሉ አይመስልም። ይሁንና ልዩነቱ ምንድን ነው? “የሚያስፈልገን ነገር” የሚባለው በሕይወት ለመኖር የግድ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው። ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ነገሮች ናቸው። “የምንፈልገው ነገር” የሚባለው ግን ቢኖረን ደስ የሚለን ሆኖም ለዕለት ተዕለት ሕይወታችን የግድ አስፈላጊ ያልሆነ ነገር ነው። ሰዎች የሚፈልጉት ነገር፣ እንደሚኖሩበት አካባቢ ሊለያይ ይችላል። በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የሚፈልጉት ሞባይል ስልክ፣ ሞተር ብስክሌት ወይም አነስ ያለ መሬት መግዛት ሊሆን ይችላል። በበለጸጉ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች ደግሞ ውድ የሆኑ ልብሶች፣ ትልቅ ቤት ወይም ውድ መኪና መግዛት ይፈልጋሉ። የምንኖረው የትም ይሁን የት፣ አደገኛ በሆነው የፍቅረ ንዋይ ወጥመድ ልንወድቅ እንችላለን፤ ይህ ደግሞ የመግዛት አቅሙ ቢኖረንም ባይኖረንም፣ የምንገዛው ነገር ቢያስፈልገንም ባያስፈልገንም ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮችን የመመኘት አባዜ እንዲጠናወተን ሊያደርግ ይችላል።—ዕብ. 13:5፤ w16.07 1:1-3

ዓርብ፣ ኅዳር 9

የሥጋ ፍላጎታችሁን ለማርካት ዕቅድ አታውጡ።—ሮም 13:14

ብዙዎች በዕለት ተዕለት ጉዳዮቻቸው ከመጠን በላይ ስለተጠመዱ “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ” አይደሉም። (ማቴ. 5:3 ግርጌ) እነዚህ ሰዎች፣ ዓለም በሚያቀርባቸው ‘ለሥጋ ምኞትና ለዓይን አምሮት’ እንድንሸነፍ በሚገፋፉ ማራኪ ቁሳዊ ነገሮች ተጠላልፈዋል። (1 ዮሐ. 2:16) እኛ ግን የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ እንዲያሳድርብን ከመፍቀድ ይልቅ የአምላክ መንፈስ ሕይወታችንን እንዲመራው እንፈልጋለን፤ ይሖዋ ከፊታችን ስለሚጠብቁን ነገሮች በመንፈሱ አማካኝነት ግልጽ ግንዛቤ ሰጥቶናል። (1 ቆሮ. 2:12) አንድ ሰው በመንፈሳዊ የሚያንቀላፋው የተለየ ነገር ስላጋጠመው ብቻ እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል፤ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ክፍል የሆኑት የተለመዱ ነገሮችም እንኳ ካልተጠነቀቅን ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምናውለውን ጊዜ ሊሻሙብን ይችላሉ። (ሉቃስ 21:34, 35) ሰዎች ምንጊዜም ነቅተን በመጠበቃችን ያፌዙብን ይሆናል፤ ሆኖም ይህ የጥድፊያ ስሜታችንን ሊያቀዘቅዝብን አይገባም። (2 ጴጥ. 3:3-7) ከዚህ ይልቅ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አዘውትረን በመሰብሰብ የአምላክን መንፈስ ለማግኘት ጥረት ማድረግ አለብን። w16.07 2:13, 14

ቅዳሜ፣ ኅዳር 10

ጸሎት ሰሚ የሆንከው አምላክ ሆይ፣ ሁሉም ዓይነት ሰው ወደ አንተ ይመጣል። . . . መተላለፋችንን ይቅር አልክ።—መዝ. 65:2, 3

ብዙ ሰዎች የሚጸልዩት፣ እንዲሁ የአእምሮ እረፍት ለማግኘት እንጂ አምላክ ጸሎታቸውን እንደሚሰማ ስለሚያምኑ አይደለም። በመሆኑም ይሖዋ “ጸሎት ሰሚ” መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ማንኛውንም ነገር በስሜ ከለመናችሁ እኔ አደርገዋለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 14:14) “ማንኛውንም ነገር” ሲል ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ማንኛውንም ነገር ማለቱ እንደሆነ ግልጽ ነው። ዮሐንስ “በእሱ ላይ ያለን ትምክህት ይህ ነው፤ የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (1 ዮሐ. 5:14) ጸሎት አእምሮን ከማረጋጋት ያለፈ ጥቅም እንዳለውና ወደ ይሖዋ ‘የጸጋ ዙፋን’ ለመቅረብ የሚያስችል ግሩም መንገድ እንደሆነ ሌሎች እንዲያውቁ መርዳት ትልቅ ነገር ነው! (ዕብ. 4:16) ሰዎች በትክክለኛው መንገድ፣ ወደ ትክክለኛው አካል እንዲሁም ተገቢ ስለሆኑ ነገሮች እንዲጸልዩ ስናስተምራቸው ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡና በተጨነቁበት ወቅት መጽናኛ እንዲያገኙ እንረዳቸዋለን።—መዝ. 4:1፤ 145:18፤ w16.07 4:11, 12

እሁድ፣ ኅዳር 11

ታማኝ አገልጋዮችህም ያወድሱሃል። የንግሥናህን ክብር ያውጃሉ፤ ስለ ኃያልነትህም ይናገራሉ፤ ይህም ለሰዎች . . . የንግሥናህን ታላቅ ክብር ያስታውቁ ዘንድ ነው።—መዝ. 145:10-12

እነዚህ ቃላት የሁሉንም ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ስሜት በሚገባ ይገልጻሉ። ነገር ግን ሕመም ወይም የዕድሜ መግፋት የምታቀርበውን አገልግሎት ቢገድቡብህስ? ለሚንከባከቡህ ሰዎችና ለሌሎች ምሥራቹን ስትናገር የምታቀርበው ቅዱስ አገልግሎት ታላቁን አምላካችንን ከፍ ከፍ እንደሚያደርግ አትዘንጋ። በእምነትህ ምክንያት ታስረህ ከሆነ ደግሞ ሁኔታዎች በፈቀዱልህ መጠን ስለ እውነት መመሥከርህ አይቀርም፤ ይህም የይሖዋን ልብ ያስደስተዋል። (ምሳሌ 27:11) በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ሆነህ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን አዘውትረህ ለማከናወን ጥረት ስታደርግም ይሖዋን ታስደስታለህ። (1 ጴጥ. 3:1-4) በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ብትሆንም እንኳ ይሖዋን ማወደስ እንዲሁም መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ትችላለህ። የአምላክን ውድ እውነትና እሱ የሰጠውን ተስፋ ለሰዎች ስታካፍል ይሖዋ እንደሚባርክህ ጥርጥር የለውም። w16.08 3:19, 20

ሰኞ፣ ኅዳር 12

ሚስቶች ለጌታ እንደሚገዙ ሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ፤ ምክንያቱም ክርስቶስ . . . [የጉባኤ] ራስ እንደሆነ ሁሉ ባልም የሚስቱ ራስ ነው።—ኤፌ. 5:22, 23

ባል የሚስቱ ራስ መሆኑ፣ ሚስት የባሏ የበታች እንድትሆን አያደርጋትም። እንዲያውም አምላክ ለሚስት ያሰበውን ድርሻ ለመወጣት ያስችላታል፤ አምላክ ሴትን ሲፈጥር “[አዳም] ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለም። ማሟያ የምትሆነውን ረዳት እሠራለታለሁ” ብሎ ነበር። (ዘፍ. 2:18) ‘የጉባኤ ራስ’ የሆነው ክርስቶስ ፍቅር እንደሚያሳይ ሁሉ አንድ ክርስቲያን ባልም የራስነት ሥልጣኑን በፍቅር ሊጠቀምበት ይገባል። ባል እንዲህ ሲያደርግ ሚስቱ ከስጋት ነፃ ትሆናለች፤ እንዲሁም ባሏን ማክበር፣ እሱን መደገፍና ለእሱ መገዛት ያስደስታታል። የኢየሱስ ተከታዮች እሱን መምሰል ከፈለጉ፣ እሱ እንደወደዳቸው እርስ በርሳቸው መዋደድ ይኖርባቸዋል። (ዮሐ. 13:34, 35፤ 15:12, 13፤ ኤፌ. 5:25) በመሆኑም ክርስቲያን ባለትዳሮች፣ አስፈላጊ ከሆነ አንዳቸው ለሌላው ሕይወታቸውን እንኳ ለመስጠት የሚያነሳሳ ጠንካራ ፍቅር ማዳበር ይኖርባቸዋል። w16.08 2:3, 4

ማክሰኞ፣ ኅዳር 13

በትክክለኛው ጊዜ የተነገረ [ቃል] ምንኛ መልካም ነው!—ምሳሌ 15:23

የምትናገሩት የሚያበረታታ ቃል በሌሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በዚህ መንገድ ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል እንዲነሳሱ ልትረዷቸው ትችላላችሁ። በስብሰባዎች ላይ እጃችሁን አውጥታችሁ የሚያንጽ ሐሳብ መስጠታችሁም ሌሎችን በጣም ያበረታታል። ነህምያና አብረውት የነበሩት ሰዎች የይሖዋን እርዳታ በማግኘታቸው እጃቸውን አበርትተው ሥራውን ማከናወን ችለዋል። በመሆኑም የኢየሩሳሌምን ቅጥር በ52 ቀናት ውስጥ ገንብተው ማጠናቀቅ ችለዋል! (ነህ. 2:18 ግርጌ፤ 6:15, 16) ነህምያ ሥራውን በበላይነት በመከታተል ብቻ ከመወሰን ይልቅ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች መልሶ በመገንባቱ ሥራ ተካፍሏል። (ነህ. 5:16) በተመሳሳይም በርካታ አፍቃሪ ሽማግሌዎች፣ በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በመካፈል ወይም የመንግሥት አዳራሻቸውን በማጽዳቱና በማደሱ ሥራ ላይ በመሳተፍ የነህምያን ምሳሌ ተከትለዋል። በተጨማሪም ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር አብረው ያገለግላሉ እንዲሁም እረኝነት ያደርጉላቸዋል፤ በዚህ መንገድ፣ በጭንቀት የተዋጠ ልብ ያላቸውን አስፋፊዎች የዛሉ እጆች ያበረታሉ።—ኢሳ. 35:3, 4፤ w16.09 1:15, 16

ረቡዕ፣ ኅዳር 14

ፍቅር . . . ጨዋነት የጎደለው ምግባር አያሳይም፤ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም።—1 ቆሮ. 13:4, 5

የአምላክ ሕዝቦች የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ይጥራሉ፦ “በምድር ያሉትን የአካል ክፍሎቻችሁን ግደሉ፤ እነሱም የፆታ ብልግና፣ ርኩሰት፣ ልቅ የሆነ የፍትወት ስሜት . . . ናቸው።” (ቆላ. 3:2, 5) የእምነት ባልንጀሮቻችን ይህን ምክር በተግባር ማዋል ከባድ እንዲሆንባቸው ማድረግ አንፈልግም። ልቅ የፆታ ሥነ ምግባር የነበራቸውና እንዲህ ዓይነቱን ሕይወት የተዉ ወንድሞችና እህቶች የኃጢአት ዝንባሌዎች እንዳያሸንፏቸው መታገል ይኖርባቸው ይሆናል። (1 ቆሮ. 6:9, 10) ታዲያ እኛ ትግሉ ከባድ እንዲሆንባቸው ማድረግ እንፈልጋለን? ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በምንሆንበት ጊዜ ለአለባበሳችን የምንጠነቀቅ ከሆነ ጉባኤው ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃ የሚጠብቁ ሰዎች ያሉበት ቦታ እንዲሆን አስተዋጽኦ እናደርጋለን። እርግጥ የምንለብሰውን ነገር የመምረጥ ነፃነት አለን። ያም ሆኖ ሁላችንም፣ ሌሎች በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነው መመላለስ እንዲሁም በአስተሳሰባቸው፣ በንግግራቸውና በድርጊታቸው የአምላክን የቅድስና መሥፈርቶች መጠበቅ ቀላል እንዲሆንላቸው የሚያደርግ አለባበስ የመምረጥ ኃላፊነት ተጥሎብናል።—1 ጴጥ. 1:15, 16፤ w16.09 3:9, 10

ሐሙስ፣ ኅዳር 15

ወጣት ወንዶችና ወጣት ሴቶች . . . የይሖዋን ስም ያወድሱ።—መዝ. 148:12, 13

“እኛ በይሖዋ እናምናለን ማለት ልጆቻችንም በይሖዋ ያምናሉ ማለት አይደለም። እምነት የሚወረስ ነገር አይደለም። ልጆቻችን ቀስ በቀስ የሚያዳብሩት ነገር ነው።” ይህን የተናገሩት በፈረንሳይ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት ናቸው። አንድ አውስትራሊያዊ ወንድም ደግሞ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ለወላጆች ከምንም በላይ ፈታኝ የሆነው ነገር በልጃቸው ልብ ውስጥ እምነት መገንባት ሳይሆን አይቀርም። . . . ልጃችሁ ላነሳው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ እንደሰጣችሁት ይሰማችሁ ይሆናል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ልጃችሁ ያንኑ ጥያቄ መልሶ ይጠይቃችኋል! ልጃችሁ፣ የሰጣችሁትን መልስ ዛሬ አጥጋቢ ሆኖ ቢያገኘውም ነገ ተጨማሪ ማብራሪያ ሊፈልግ ይችላል። በመሆኑም በአንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ መወያየት ሊያስፈልጋችሁ ይችላል።” ወላጅ ከሆናችሁ ልጆቻችሁ በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው እነሱን የማስተማሩና የመቅረጹ ኃላፊነት ከአቅማችሁ በላይ እንደሆነ ተሰምቷችሁ ያውቃል? ማናችንም ብንሆን ይህን ኃላፊነት በራሳችን ጥበብ መወጣት እንደማንችል ግልጽ ነው! (ኤር. 10:23) አምላክ መመሪያ እንዲሰጠን የምንጠይቀው ከሆነ ግን ሊሳካልን ይችላል። w16.09 5:1, 2

ዓርብ፣ ኅዳር 16

ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አትበል።—ምሳሌ 3:27

ከሌላ አገር የመጡ ሰዎች ከሄዱበት አገር ባሕል ጋር ለመላመድ የተቻላቸውን ጥረት ማድረግ አባቸው። በዚህ ረገድ ሩት ግሩም ምሳሌ ትሆናለች። አንደኛ፣ ለመቃረም ፈቃድ በመጠየቅ፣ ለሄደችበት አገር ባሕል አክብሮት እንዳላት አሳይታለች። (ሩት 2:7) መቃረም መብቷ እንደሆነ ወይም ደግሞ ሌሎች እሷን የመንከባከብ ግዴታ እንዳለባቸው አልተሰማትም። ሁለተኛ፣ ለተደረገላት ደግነት አድናቆቷን ገልጻለች። (ሩት 2:13) የሌላ አገር ዜጎች እንዲህ ያለ መልካም ባሕርይ ካላቸው፣ የአገሩ ነዋሪዎችም ሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻቸው አክብሮት ያሳዩዋቸዋል። ይሖዋ የተለያየ ባሕልና ዜግነት ያላቸው ሰዎች ምሥራቹን እንዲሰሙ አጋጣሚ በመክፈት ጸጋውን ስላሳየን በጣም ደስተኞች ነን። አንዳንዶች በትውልድ አገራቸው መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ወይም ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር በነፃነት የመሰብሰብ አጋጣሚ አላገኙ ይሆናል። አሁን ግን ከእኛ ጋር የመሰብሰብ አጋጣሚ አግኝተዋል፤ ታዲያ በእኛ መሃል ሲሆኑ እንግድነት እንዳይሰማቸው ልንረዳቸው አይገባም? w16.10 1:17-19

ቅዳሜ፣ ኅዳር 17

እሱ ከፊቱ ለሚጠብቀው ደስታ ሲል . . . በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ጸንቷል።—ዕብ. 12:2

በዘመናችን ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአምላክ አገልጋዮች ተስፋቸው ብሩህ ሆኖ እንዲታያቸው በማድረግ እንዲሁም የተለያዩ ፈተናዎች እምነታቸውን እንዲያዳክሙባቸው ባለመፍቀድ የኢየሱስን ምሳሌ ተከትለዋል። በ1925 በጀርመን የተወለደውን ሩዶልፍ ግራይሸንን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ወንድም ሩዶልፍ፣ ቤቱ ግድግዳ ላይ ተሰቅለው የነበሩትን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክቶች የሚያንጸባርቁ ሥዕሎች ያስታውሳል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከሥዕሎቹ መካከል አንዱ ተኩላና የበግ ጠቦት፣ ነብርና የፍየል ጠቦት እንዲሁም አንበሳና ፍሪዳ በሰላም አንድ ላይ ሆነው አንድ ትንሽ ልጅ ሲመራቸው የሚያሳይ ነበር። . . . እንዲህ ዓይነቶቹ ሥዕሎች በውስጤ አንድ የማይፋቅ አሻራ ቀርጸዋል።” (ኢሳ. 11:6-9) ወንድም ሩዶልፍ፣ በመጀመሪያ የናዚ ጌስታፖ በኋላም የምሥራቅ ጀርመኑ ሽታዚ ከባድ ስደት ቢያደርሱበትም ምድር ገነት እንደምትሆን ያለው ጠንካራ እምነት አልተዳከመም። ወንድም ሩዶልፍ ሌሎች መከራዎችም ደርሰውበታል፤ የሚወዳት እናቱ በራቨንስብሩክ ወደሚገኘው የሴቶች ማጎሪያ ካምፕ ከተላከች በኋላ በተስቦ ሞተች፤ እንዲሁም አባቱ እምነቱ በመዳከሙ የተነሳ የይሖዋ ምሥክር መሆኑን እንደካደ በሚገልጽ ሰነድ ላይ ፈረመ። w16.10 3:12-14

እሁድ፣ ኅዳር 18

የአምላክን ቃል ከእኛ በሰማችሁ ጊዜ . . . እንደ አምላክ ቃል አድርጋችሁ ተቀብላችሁታል፤ ደግሞም የአምላክ ቃል ነው።—1 ተሰ. 2:13

የይሖዋ አገልጋዮች፣ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። ሁላችንም ፍጽምና ስለሚጎድለን አልፎ አልፎ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ያስፈልገናል። ታዲያ ምክር ሲሰጠን ምን እናደርጋለን? በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩትን ኤዎድያን እና ሲንጤኪ የተባሉ ክርስቲያኖች እንደ ምሳሌ እንመልከት። በእነዚህ ቅቡዕ እህቶች መካከል ከባድ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። በኤዎድያንና በሲንጤኪ መካከል የተፈጠረው ችግር የጉባኤውን ሰላም ሊያደፈርስ ይችል ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ፣ እነዚህ እህቶች መጨረሻ ላይ ምን እንዳደረጉ ባይገልጽልንም ጳውሎስ በፍቅር ተነሳስቶ ለሰጣቸው ምክር ጥሩ ምላሽ ሰጥተው መሆን አለበት። (ፊልጵ. 4:2, 3) በዛሬው ጊዜም በይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤዎች ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ሆኖም የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምክር በተግባር ካዋልን እንዲህ ያሉ ችግሮችን መፍታት አልፎ ተርፎም እንዳይፈጠሩ ማድረግ እንችላለን። የአምላክን ቃል ከፍ አድርገን የምንመለከት ከሆነ ደግሞ በውስጡ የሚገኙትን መመሪያዎች እንከተላለን።—መዝ. 27:11፤ w16.11 3:1-3

ሰኞ፣ ኅዳር 19

በመከራ ቀን ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል።—ምሳሌ 24:10

ሁላችንም ማበረታቻ ያስፈልገናል። በተለይ ከልጆች ጋር በተያያዘ ይህ እውነት ነው። ቲሞቲ ኤቫንዝ የተባሉ ምሁር “ተክሎች ውኃ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ [ልጆችም] ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል” በማለት ተናግረዋል። አክለውም “አንድ ልጅ ማበረታቻ የሚሰጠው ከሆነ ዋጋ እንዳለውና ሌሎች እንደሚያደንቁት ይሰማዋል” ብለዋል። ይሁንና የምንኖረው በሚያስጨንቅ ዘመን ውስጥ ነው። ሰዎች ራስ ወዳዶችና ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው ስለሆኑ ሌሎችን ማበረታታት የተለመደ አይደለም። (2 ጢሞ. 3:1-5) ሰይጣን ዲያብሎስ፣ ተስፋ ከቆረጥን በመንፈሳዊም ሆነ በሌሎች አቅጣጫዎች እንደምንዳከም ስለሚያውቅ ተስፋ ሊያስቆርጠን ይፈልጋል። ሰይጣን፣ ጻድቁን ኢዮብን ተስፋ ለማስቆረጥ ሲል የተለያዩ መከራዎች ያመጣበት ከመሆኑም ሌላ የሐሰት ውንጀላዎች እንዲሰነዘሩበት አድርጓል፤ ሆኖም ሙከራው አልተሳካለትም። (ኢዮብ 2:3፤ 22:3፤ 27:5) እኛም የቤተሰባችንንና የጉባኤውን አባላት በማበረታታት የዲያብሎስን ሥራ ማክሸፍ እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን ቤታችንንም ሆነ የመንግሥት አዳራሻችንን ደስታ የምናገኝበትና ከመንፈሳዊ አደጋ ነፃ የምንሆንበት ስፍራ ለማድረግ ይረዳል። w16.11 1:4, 6

ማክሰኞ፣ ኅዳር 20

[አምላክ] ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ [ጠርቷችኋል]።—1 ጴጥ. 2:9

ደፋር የሆኑ ጥቂት ሰዎች በ16ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ የአምላክን ቃል ሰፊው ሕዝብ በሚጠቀምበት ቋንቋ መተርጎም ጀመሩ። ሕዝቡ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያገኝ ማንበብ ጀመረ። ይህም በሕዝቡ አእምሮ ውስጥ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ፈጠረ፦ ‘የአምላክ ቃል ስለ መንጽሔና ስለ ፍታት የሚጠቅሰው የት ጋ ነው? ስለ ሊቀ ጳጳሳትና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ የሚናገር ነገርስ የት አለ?’ እንዲህ ያለ ጥያቄ መነሳቱ ቤተ ክርስቲያኗን በጣም አስቆጣት። ቀሳውስቱ ይህ ትልቅ ድፍረት እንደሆነ ተሰማቸው! በመሆኑም ቤተ ክርስቲያኗ የአጸፋ እርምጃ ወሰደች። የቤተ ክርስቲያኗን ትምህርት የተቃወሙ ሰዎች በመናፍቅነት ተወነጀሉ። ቤተ ክርስቲያኗ የሞት ፍርድ ስትበይን መንግሥት ፍርዱን ያስፈጽም ነበር። ይህ የተደረገበት ዓላማ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያነቡና በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ጥያቄ እንዳያነሱ ለማስፈራራት ነው። በጥቅሉ ሲታይ ሴራቸው ተሳክቷል። ይሁን እንጂ ለታላቂቱ ባቢሎን ማስፈራሪያ ያልተንበረከኩ ጥቂት ደፋር ሰዎች ነበሩ። የአምላክን ቃል አንድ ጊዜ ስለቀመሱ ተጨማሪ ነገር የማግኘት ጉጉት አደረባቸው! w16.11 4:13

ረቡዕ፣ ኅዳር 21

ሐቀኛ ምሥክር አይዋሽም።—ምሳሌ 14:5

ማንኛውም ክርስቲያን ሐቀኛ መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው። (ኤፌ. 4:25) “የውሸት አባት” የሆነው ሰይጣን ነው። ሐናንያ እና ሚስቱም ሕይወታቸውን ያጡት ስለዋሹ ነው። እነዚህን ግለሰቦች መምሰል ስለማንፈልግ ከውሸት እንርቃለን። (ዮሐ. 8:44፤ ሥራ 5:1-11) ይሁንና ሐቀኝነት ሲባል ከውሸት መራቅ ማለት ብቻ አይደለም። ለአምላክ ጸጋ ከልባችን አመስጋኞች ከሆንን በሌሎች መንገዶችም ሐቀኞች ለመሆን እንጥራለን። መዋሸት ሲባል እውነት ያልሆነ ነገር መናገር ማለት ነው። ይሁንና ይሖዋ፣ ከሕዝቡ የሚጠብቀው ከውሸት እንዲርቁ ብቻ አይደለም። የጥንቶቹን እስራኤላውያን “እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል” በማለት አሳስቧቸዋል። ከዚያም ቅድስና ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ሲገልጽ “አትስረቁ፤ አታታሉ፤ አንዳችሁ በሌላው ላይ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት አትፈጽሙ” ብሏቸዋል። (ዘሌ. 19:2, 11) የሚያሳዝነው ግን ውሸት ላለመናገር የሚጠነቀቅ ሰውም እንኳ ሌሎችን ሊያታልል ወይም ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ሊፈጽም ይችላል። w16.12 1:17, 18

ሐሙስ፣ ኅዳር 22

ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።—ፊልጵ. 4:7

የአምላክን ቃል ስናነብ ኢየሱስ የተናገራቸውን የሚያጽናኑ ሐሳቦች እናገኛለን። ኢየሱስ ያስተማረው ነገር ለአድማጮቹ እረፍት የሚሰጥ ነበር። ክርስቶስ ልባቸው የተጨነቀውን ያረጋጋ፣ የደከሙትን ያበረታ እንዲሁም መንፈሳቸው የተደቆሰውን ያጽናና ስለነበር በርካታ ሰዎች ወደ እሱ ይመጡ ነበር። (ማቴ. 11:28-30) ኢየሱስ ለሰዎች ፍቅር ስለነበረው ለመንፈሳዊ፣ ለስሜታዊና ለአካላዊ ፍላጎታቸው ትኩረት ይሰጥ ነበር። (ማር. 6:30-32) ኢየሱስ ሰዎችን እንደሚደግፍ የገባውን ቃል በዛሬው ጊዜም ይፈጽማል። አብረውት ይጓዙ እንደነበሩት ሐዋርያት ሁሉ አንተም የዚህን ቃል እውነተኝነት በገዛ ሕይወትህ ልትመለከት ትችላለህ። የኢየሱስን እርዳታ ለማግኘት በአካል ከእሱ ጋር መሆን አያስፈልግህም። በሰማይ ሆኖ የሚገዛው ይህ ንጉሥ ስሜታችንን በመረዳት የሚያስፈልገንን ያደርግልናል። በመሆኑም በምትጨነቅበት ጊዜ ‘ሊደርስልህ’ እንዲሁም ‘እርዳታ በሚያስፈልግህ ጊዜ’ ሊረዳህ ይችላል። በእርግጥም ኢየሱስ አስጨናቂ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚያስችልህ ከመሆኑም ሌላ ልብህ በተስፋና በድፍረት እንዲሞላ ይረዳሃል።—ዕብ. 2:17, 18፤ 4:16፤ w16.12 3:4, 6

ዓርብ፣ ኅዳር 23

ሥጋ ለባሽ የሆነውን ሁሉ ለማጥፋት ወስኛለሁ።—ዘፍ. 6:13

ኖኅ ይኖር የነበረው ‘በዓመፅና’ በሥነ ምግባር ብልግና በተሞላ ዓለም ውስጥ ነበር። (ዘፍ. 6:4, 9-12) ኖኅ የይሖዋን የማስጠንቀቂያ መልእክት በታማኝነት የሰበከ ቢሆንም በዙሪያው ያሉት ክፉ ሰዎች መልእክቱን እንዲቀበሉ ማስገደድም ሆነ የጥፋት ውኃው የሚመጣበትን ጊዜ ማፋጠን አይችልም። ኖኅ፣ ይሖዋ ክፋትን ለማጥፋት የገባውን ቃል በትክክለኛው ጊዜ ላይ እንደሚፈጽም መተማመን ያስፈልገው ነበር። (ዘፍ. 6:17) እኛም የምንኖረው በክፋት በተሞላ ዓለም ውስጥ ሲሆን ይሖዋ ይህን ክፉ ዓለም ለማጥፋት ቃል እንደገባ እናውቃለን። (1 ዮሐ. 2:17) ያም ቢሆን ሰዎች ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ እንዲቀበሉ ማስገደድ አንችልም። ‘ታላቁ መከራ’ የሚጀምርበትን ጊዜ ማፋጠን እንደማንችልም የታወቀ ነው። (ማቴ. 24:14, 21) ልክ እንደ ኖኅ፣ እኛም ይሖዋ በቅርቡ እርምጃ እንደሚወስድ በመተማመን ጠንካራ እምነት እንዳለን ልናሳይ ይገባል። (መዝ. 37:10, 11) ይሖዋ፣ ይህን ክፉ ሥርዓት የሚያጠፋበትን ጊዜ ወስኗል፤ ይህ ጊዜ በአንድ ቀንም እንኳ እንዲራዘም እንደማይፈቅድ እርግጠኞች ነን።—ዕን. 2:3፤ w17.01 1:5-7

ቅዳሜ፣ ኅዳር 24

የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ፣ ልትሄድበትም በሚገባህ መንገድ የምመራህ እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ።—ኢሳ. 48:17

በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች የመምረጥ ነፃነታቸውን አላግባብ ሲጠቀሙበት አልፎ ተርፎም ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ሲያደርጉበት ይታያሉ። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች “የማያመሰግኑ” ሆነዋል። (2 ጢሞ. 3:1, 2) እኛም ይሖዋ የሰጠንን ይህን ውድ ስጦታ አላግባብ እንዳንጠቀምበት እንዲሁም ለዚህ ስጦታ አድናቆት እንዳናጣ እንጠንቀቅ። ይሁንና የመምረጥ ነፃነታችንን አላግባብ እንዳንጠቀምበት ምን ሊረዳን ይችላል? ሁላችንም ከጓደኛ፣ ከአለባበስ፣ ከአጋጌጥ እንዲሁም ከመዝናኛ ምርጫ ጋር በተያያዘ የግላችንን ውሳኔ የማድረግ ነፃነት አለን። ይሁንና ለራሳችን ምኞት ባሪያ ከሆንን ወይም በዓለም ውስጥ ያለውን ቅጥ ያጣ ፋሽን መከተል ከጀመርን የመምረጥ ነፃነታችንን ‘የክፋት መሸፈኛ’ እያደረግነው ነው ሊባል ይችላል። (1 ጴጥ. 2:16) ነፃነታችንን ‘የሥጋን ፍላጎት ለማርካት መጠቀም’ አንፈልግም፤ ከዚህ ይልቅ የምናደርጋቸው ምርጫዎች “ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዱን መሆን ይኖርባቸዋል።—ገላ. 5:13፤ 1 ቆሮ. 10:31፤ w17.01 2:12-14

እሁድ፣ ኅዳር 25

እኔም ይህን ስሰማ . . . በሰማይ አምላክ ፊት ሳዝን፣ ስጾምና ስጸልይ ቆየሁ።—ነህ. 1:4

ነህምያ የተወው ምሳሌ፣ ልካችንን ማወቃችን የሥራ ምድባችን ሲለወጥ ወይም ተጨማሪ ኃላፊነት ሲሰጠን በራሳችን ከመታመን እንድንቆጠብ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ያሳያል። አንድ ሽማግሌ ባካበተው ልምድ ብቻ በመተማመን በቅድሚያ ይሖዋን በጸሎት ሳይጠይቅ የጉባኤ ጉዳዮችን ማከናወን ሊጀምር ይችላል። አንዳንዶች ደግሞ ቀድመው ውሳኔ ካደረጉ በኋላ ይሖዋ ውሳኔያቸውን እንዲባርክላቸው ይጸልያሉ። ሆኖም ይህ ልክን ማወቅ ሊባል ይችላል? ልኩን የሚያውቅ ሰው ምንጊዜም በይሖዋ ፊትና በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ያለውን ቦታ ይገነዘባል። ከይሖዋ አንጻር ሲታይ የእኛ ችሎታ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ እናውቃለን። በተለይም ያጋጠመን ሁኔታ ወይም ችግር ከዚህ በፊት ያለፍንበት ከሆነ በራሳችን እንዳንታመን ልንጠነቀቅ ይገባል። (ምሳሌ 3:5, 6) ሁላችንም የአምላክ ቤተሰብ አባላት ነን፤ በመሆኑም ተጨማሪ ሥልጣን ለማግኘት ወይም ከሌሎች ልቀን ለመታየት ከመሞከር ይልቅ የቤተሰብና የጉባኤ ኃላፊነቶቻችንን በመወጣት ላይ ትኩረት ልናደርግ ይገባል።—1 ጢሞ. 3:15፤ w17.01 4:7, 8

ሰኞ፣ ኅዳር 26

ምድርን . . . ለሰው ልጆች ሰጣት።—መዝ. 115:16

መጀመሪያ ላይ ይሖዋ የሰው ዘር በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖር ዓላማ ነበረው። (ዘፍ. 1:28፤ መዝ. 37:29) አዳምና ሔዋን አስደሳች ሕይወት እንዲመሩ የሚያስችሏቸውን የተለያዩ ውድ ስጦታዎች ሰጥቷቸዋል፤ ይህም ለጋስ እንደሆነ ያሳያል። (ያዕ. 1:17) ይሖዋ የመምረጥ ነፃነት፣ የማመዛዘን ችሎታ እንዲሁም ሌሎችን የመውደድና ጓደኝነት የመመሥረት ችሎታ ሰጥቷቸዋል። ፈጣሪ አዳምን ያነጋግረው የነበረ ሲሆን ትክክል የሆነውን ነገር በተመለከተ መመሪያ ሰጥቶታል። በተጨማሪም የሚያስፈልጉትን ነገሮች እንዴት ማግኘት እንደሚችል ብሎም እንስሳትንና ምድርን እንዴት እንደሚንከባከብ ገልጾለታል። (ዘፍ. 2:15-17, 19, 20) ከዚህም ሌላ ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ሲፈጥራቸው የመቅመስ፣ የመዳሰስ፣ የማየት፣ የመስማትና የማሽተት ችሎታ ሰጥቷቸዋል። በመሆኑም ገነት በሆነችው መኖሪያቸው ውስጥ በሚገኙት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ውብ ነገሮች መደሰት ይችሉ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት፣ በሚያከናውኑት ሥራ እርካታ የማግኘት እንዲሁም በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን የመማር ሰፊ አጋጣሚ ነበራቸው። ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ሲፈጥራቸው ፍጹም የሆኑ ልጆችን የመውለድ ችሎታ ሰጥቷቸዋል። ምድርንም ሆነ በላይዋ የሚገኙትን ውድና ውብ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ለሰው ልጆች ሰጥቷል። ምድር ዘላለማዊ መኖሪያቸው እንድትሆን ዓላማው ነበር። w17.02 1:6, 7

ማክሰኞ፣ ኅዳር 27

የዚህን ሕግ ቅጂ ለራሱ በመጽሐፍ ላይ ይጻፍ። . . . እንዲሁም በዚህ ሕግ . . . ላይ የሰፈሩትን ቃላት በሙሉ በመፈጸም [ይጠብቃቸው]።—ዘዳ. 17:18, 19

የአምላክ ቃል፣ በሕዝቡ ላይ የተሾሙትን ሰዎች ይመራቸው የነበረው እንዴት ነው? ንጉሥ ኢዮስያስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የሙሴ ሕግ መጽሐፍ ከተገኘ በኋላ የኢዮስያስ ጸሐፊ ሕጉን አነበበለት። ኢዮስያስ በአምላክ ቃል በመመራት የጣዖት አምልኮን ለማጥፋት ከፍተኛ ዘመቻ አካሄደ፤ እንዲሁም የፋሲካን በዓል ከዚያ በፊት ታይቶ በማያውቅ መልኩ አከበረ። (2 ነገ. 22:11፤ 23:1-23) ኢዮስያስና ሌሎች ታማኝ መሪዎች፣ በአምላክ ቃል ይመሩ ስለነበር ለሕዝቡ የሚሰጡትን መመሪያ ለማስተካከል ፈቃደኞች ሆነዋል። እነዚህ ለውጦች የጥንቱ የአምላክ ሕዝብ ከእሱ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲመላለስ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ይሁን እንጂ የጥንቶቹን የአምላክ ሕዝቦች ይገዙ ከነበሩት ነገሥታት አንዳንዶቹ የአምላክን መመሪያዎች አልታዘዙም። ይሖዋ ለእነዚህ መሪዎች ተግሣጽ የሰጠባቸው ወይም በሌላ መሪ እንዲተኩ ያደረገባቸው ጊዜያት ነበሩ። (1 ሳሙ. 13:13, 14) እሱ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ደግሞ ከዚህ በፊት ይጠቀምባቸው ከነበሩት መሪዎች ሁሉ የላቀ መሪ ሾመ። w17.02 3:11, 12, 14

ረቡዕ፣ ኅዳር 28

[ሰውን] ከመላእክት በጥቂቱ አሳነስከው፤ የክብርና የግርማ ዘውድም ደፋህለት።—መዝ. 8:5

ሰዎች የተፈጠሩት “በአምላክ መልክ” ነው። (ዘፍ. 1:27) በመሆኑም አብዛኞቹ ሰዎች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የአምላክን አንዳንድ ባሕርያት ያንጸባርቃሉ። የሰው ልጆች አንዳቸው ለሌላው እንደ ፍቅር፣ ደግነትና ርኅራኄ ያሉትን ባሕርያት ማሳየት ይችላሉ። አምላክ የሰው ልጆችን ሲፈጥራቸው ሕሊና ይኸውም ክፉና ደጉን ለመለየት የሚረዳ ተፈጥሯዊ ችሎታ ሰጥቷቸዋል፤ ሕሊና አንዳንድ ጊዜ የተሳሳተ ወይም የተዛባ ምልክት ሊሰጥ ቢችልም እንኳ አብዛኛውን ጊዜ ትክክልና ስህተት፣ እውነትና ውሸት እንዲሁም ተገቢ የሆነና ያልሆነን ነገር ለይተን እንድናውቅ ይረዳናል። (ሮም 2:14, 15) ንጹሕና ውብ የሆነ ነገር ብዙዎችን ይማርካል። በጥቅሉ ሲታይ ሰዎች ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የይሖዋን ክብር በተወሰነ ደረጃ እንደሚያንጸባርቁ የሚያሳይ ነው፤ በዚህም ምክንያት አክብሮት ይገባቸዋል። ይሁን እንጂ ለሰዎች ምን ዓይነት አክብሮት ማሳየት እንደሚገባንና ምን ያህል ልናከብራቸው እንደሚገባ ግራ ሊገባን ይችላል፤ በመሆኑም በዚህ ረገድ ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበራችን አስፈላጊ ነው። w17.03 1:5, 6

ሐሙስ፣ ኅዳር 29

[አምላክ] በእነሱም ላይ አመጣዋለሁ ያለውን ነገር መልሶ በማጤን ጥፋቱን ከማምጣት ተቆጠበ።—ዮናስ 3:10

አምላክ፣ በሚቆጣበት ጊዜም እንኳ ብዙ ሰዎች እንደሚያደርጉት ያልታሰበበት ውሳኔ አያደርግም። ይሖዋ የነነዌ ሰዎች ንስሐ እንደገቡና እንደተለወጡ ሲያይ ውሳኔውን ቀይሯል። ይህን በማድረግ ምክንያታዊ፣ ትሑትና ሩኅሩኅ አምላክ መሆኑን አሳይቷል። እኛም አንዳንድ ጊዜ፣ ያደረግነውን ውሳኔ መለስ ብለን ማጤናችን ጥሩ ይሆናል። እንዲህ ለማድረግ የሚያነሳሳን ሁኔታዎቹ መቀየራቸው ሊሆን ይችላል። ይሖዋም ቢሆን ሁኔታዎች በመለወጣቸው የተነሳ ውሳኔዎቹን የቀየረባቸው ጊዜያት አሉ። (1 ነገ. 21:20, 21, 27-29፤ 2 ነገ. 20:1-5) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ውሳኔያችንን እንድንቀይር የሚያደርግ አዲስ መረጃ እናገኝ ይሆናል። ንጉሥ ዳዊት የሳኦል የልጅ ልጅ የሆነውን ሜፊቦስቴን በተመለከተ የተሳሳተ ወሬ ተነግሮት ነበር። ከጊዜ በኋላ ዳዊት ስለ ሁኔታው ትክክለኛ መረጃ ሲያገኝ ውሳኔውን አስተካክሏል።—2 ሳሙ. 16:3, 4፤ 19:24-29፤ w17.03 2:14, 15

ዓርብ፣ ኅዳር 30

ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን።—ፊልጵ. 4:5

ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመርመርና በተግባር ማዋል ይኖርብናል፤ በእርግጥ ይህን ስናደርግ ሚዛናዊ መሆን ያስፈልገናል። የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላትን አንዲት እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህች እህት ምሥራቹን የመስበክ ኃላፊነት እንዳለባት ታውቃለች። (ሥራ 4:20) ይሁን እንጂ በመስክ አገልግሎት ልትካፈል ባሰበችበት ቀን፣ ባለቤቷ አብረው ጊዜ ካሳለፉ እንደቆዩ በመግለጽ ከእሱ ጋር እንድትውል ጠየቃት እንበል። እህታችን ጥበብ ያዘለ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዷትን ጥቅሶች ትመረምር ይሆናል። አምላክን መታዘዝ እንዳለባት እንዲሁም ኢየሱስ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ እንዳዘዘን ታውቃለች። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሥራ 5:29) በሌላ በኩል ደግሞ አንዲት ሚስት ለባሏ መገዛት እንዳለባትና የአምላክ አገልጋዮች ምክንያታዊ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ማስታወስ ይኖርባታል። (ኤፌ. 5:22-24) ባለቤቷ ጨርሶ አገልግሎት እንዳትወጣ ሊከለክላት እየሞከረ ነው? ወይስ በዚያ ዕለት ብቻ አብረው አንድ ነገር እንዲያከናውኑ መጠየቁ ነው? በእርግጥም የአምላክን ፈቃድ ለማድረግና ጥሩ ሕሊና ይዘን ለመኖር ስንጥር ሚዛናዊ መሆናችን አስፈላጊ ነው። w17.03 4:17

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ