የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es19 ገጽ 7-17
  • ጥር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥር
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2019
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ማክሰኞ፣ ጥር 1
  • ረቡዕ፣ ጥር 2
  • ሐሙስ፣ ጥር 3
  • ዓርብ፣ ጥር 4
  • ቅዳሜ፣ ጥር 5
  • እሁድ፣ ጥር 6
  • ሰኞ፣ ጥር 7
  • ማክሰኞ፣ ጥር 8
  • ረቡዕ፣ ጥር 9
  • ሐሙስ፣ ጥር 10
  • ዓርብ፣ ጥር 11
  • ቅዳሜ፣ ጥር 12
  • እሁድ፣ ጥር 13
  • ሰኞ፣ ጥር 14
  • ማክሰኞ፣ ጥር 15
  • ረቡዕ፣ ጥር 16
  • ሐሙስ፣ ጥር 17
  • ዓርብ፣ ጥር 18
  • ቅዳሜ፣ ጥር 19
  • እሁድ፣ ጥር 20
  • ሰኞ፣ ጥር 21
  • ማክሰኞ፣ ጥር 22
  • ረቡዕ፣ ጥር 23
  • ሐሙስ፣ ጥር 24
  • ዓርብ፣ ጥር 25
  • ቅዳሜ፣ ጥር 26
  • እሁድ፣ ጥር 27
  • ሰኞ፣ ጥር 28
  • ማክሰኞ፣ ጥር 29
  • ረቡዕ፣ ጥር 30
  • ሐሙስ፣ ጥር 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2019
es19 ገጽ 7-17

ጥር

ማክሰኞ፣ ጥር 1

ክፉዎች ፍትሕን መረዳት አይችሉም።—ምሳሌ 28:5

ወደ መጨረሻዎቹ ቀናት መደምደሚያ ይበልጥ እየቀረብን በሄድን መጠን ክፉዎች “እንደ አረም [መብቀላቸውን]” ይቀጥላሉ። (መዝ. 92:7) ከዚህ አንጻር፣ ሰዎች አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ችላ ማለታቸው የሚያስገርም አይደለም። እንዲህ ባለ ዓለም ውስጥ እየኖርን ‘በማስተዋል ችሎታችን የጎለመስን ለክፋት ግን ሕፃናት መሆን’ የምንችለው እንዴት ነው? (1 ቆሮ. 14:20) የዛሬው የዕለት ጥቅስ የዚህን ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። ጥቅሱ በከፊል “ይሖዋን የሚፈልጉ . . . ሁሉን ነገር መረዳት ይችላሉ” ይላል፤ ይህም ሲባል አምላክን ለማስደሰት የሚያስፈልጉ ነገሮችን በሙሉ መረዳት ይችላሉ ማለት ነው። ይሖዋ “ለቅኖች ጥበብን እንደ ውድ ሀብት [እንደሚያከማች]” የሚናገረው በምሳሌ 2:7, 9 ላይ የሚገኘው ሐሳብም ተመሳሳይ መልእክት ያስተላልፋል። በዚህም ምክንያት ቅን የሆኑ ሰዎች “ጽድቅ፣ ፍትሕና ትክክል የሆነውን ነገር ይኸውም የጥሩነትን ጎዳና በሙሉ [መረዳት]” ይችላሉ። ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ እንዲህ ያለውን ጥበብ አግኝተዋል። (ሕዝ. 14:14) በዛሬው ጊዜ ካሉ የአምላክ ሕዝቦች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አንተስ በግለሰብ ደረጃ ይህን ጥበብ አግኝተሃል? ይሖዋን ለማስደሰት የሚያስፈልጉትን ‘ሁሉንም ነገሮች መረዳት’ ችለሃል? ለዚህ ቁልፉ ስለ ይሖዋ ትክክለኛ እውቀት መቅሰም ነው። w18.02 8 አን. 1-3

ረቡዕ፣ ጥር 2

በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠመቁ።—ሥራ 19:5

ማናችንም ብንሆን ልጃችንን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን ወይም ሌላ ማንኛውንም ሰው እንዲጠመቅ ጫና ልናሳድርበት አይገባም። ይሖዋም ቢሆን ማንም ተገድዶ እንዲያገለግለው አይፈልግም። (1 ዮሐ. 4:8) ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ በምናስጠናበት ጊዜ ከአምላክ ጋር በግለሰብ ደረጃ ዝምድና የመመሥረትን አስፈላጊነት ጎላ አድርገን ልንገልጽላቸው ይገባል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ለእውነት ልባዊ አድናቆት ሲያድርበት እንዲሁም የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የመሆንን ቀንበር ለመሸከም ፍላጎት ሲያዳብር ለመጠመቅ ይነሳሳል። (2 ቆሮ. 5:14, 15) አንድ ሰው በስንት ዓመቱ መጠመቅ እንዳለበት የሚገልጽ መመሪያ የለም። ደግሞም እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እድገት የሚያደርግበት ፍጥነት ይለያያል። አንድ ሰው በሚጠመቅበት ዕለት በጣም እንደሚደሰት የታወቀ ነው። ሆኖም በዚያ ዕለት፣ ስላደረገው ውሳኔ በቁም ነገር ማሰቡም ተገቢ ነው። ራስን ሲወስኑ ከገቡት ቃል ጋር ተስማምቶ መኖር ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል። ኢየሱስ የእሱ ደቀ መዝሙር መሆንን፣ ቀንበር ከመሸከም ጋር ያመሳሰለው ለዚህ ነው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “ከእንግዲህ ለራሳቸው ከመኖር ይልቅ ለእነሱ ለሞተውና ለተነሳው [ሊኖሩ]” እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።—2 ቆሮ. 5:15፤ ማቴ. 16:24፤ w18.03 6-7 አን. 14-17

ሐሙስ፣ ጥር 3

እንግዳ መቀበልን አትርሱ፤ አንዳንዶች ይህን ሲያደርጉ ሳያውቁት መላእክትን አስተናግደዋልና።—ዕብ. 13:2

እንግዶችን ከመቀበል ወደኋላ ያልክበት ጊዜ አለ? ከሆነ ከወንድሞችህ ጋር አስደሳች ጊዜ ለማሳለፍና ዘላቂ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችል አጋጣሚ አምልጦሃል። እንግዳ ተቀባይ መሆን የብቸኝነት ስሜትን ለማሸነፍ ከሚረዱ ግሩም መንገዶች አንዱ ነው። ይሁንና አንድ ሰው እንግዳ ተቀባይ እንዳይሆን የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? የተለያዩ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። አንዱ ምክንያት የይሖዋ አገልጋዮች ሥራ የሚበዛባቸው ከመሆኑም ሌላ በአብዛኛው ተደራራቢ ኃላፊነቶች ያሉባቸው መሆኑ ነው። በመሆኑም አንዳንዶች እንግዶችን ለማስተናገድ ጊዜውም ሆነ ጉልበቱ እንደሌላቸው ይሰማቸው ይሆናል። አንተም እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ ፕሮግራምህን መለስ ብለህ መቃኘትህ ጠቃሚ ነው። ሌሎችን በእንግድነት ለማስተናገድ አሊያም የሚቀርብልህን ግብዣ ለመቀበል የሚያስችል ጊዜና ጉልበት እንድታገኝ በፕሮግራምህ ላይ መጠነኛ ማስተካከያ ማድረግ ትችል ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቲያኖች እንግዳ ተቀባይ እንዲሆኑ ያበረታታል። እንግዶችን ለማስተናገድ ጊዜ መመደብ ምንም ስህተት የለውም፤ እንዲያውም እንዲህ ማድረግ ተገቢ ነው። እርግጥ፣ እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን መቀነስ ሊያስፈልግህ ይችላል። w18.03 16 አን. 13-14

ዓርብ፣ ጥር 4

ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው።—ሉቃስ 4:43

መንፈሳዊ አስተሳሰብ በመያዝ ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ የሚሆነን ማን ነው? ኢየሱስ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። የኢየሱስ ሕይወትም ሆነ አገልግሎቱን ያከናወነበት መንገድ አባቱን ይሖዋን መምሰል እንደሚፈልግ የሚያሳይ ነው። የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብና ስሜት የነበረው ሲሆን በድርጊቱም አባቱን መስሏል፤ እንዲሁም ከአምላክ ፈቃድና መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወቱን መርቷል። (ዮሐ. 8:29፤ 14:9፤ 15:10) ነቢዩ ኢሳይያስ የይሖዋን ርኅራኄ የገለጸበትን መንገድ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህን ጥቅስ የወንጌል ጸሐፊው ማርቆስ ስለ ኢየሱስ ከጻፈው ሐሳብ ጋር ማወዳደር እንችላለን። (ኢሳ. 63:9፤ ማር. 6:34) ታዲያ እኛስ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ምንጊዜም ርኅራኄ በማሳየት የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን? ልክ እንደ ኢየሱስ ምሥራቹን በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ ራሳችንን እናስጠምዳለን? መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የርኅራኄ ስሜት ያላቸው ከመሆኑም ባሻገር ሌሎችን ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ። w18.02 21 አን. 12

ቅዳሜ፣ ጥር 5

ልጆቻችሁን . . . በይሖዋ ተግሣጽና ምክር አሳድጓቸው።—ኤፌ. 6:4

ልጆችን ማሳደግ በተለይ ዛሬ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ በጣም ከባድ ነው። (2 ጢሞ. 3:1-5) ልጆች ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር የመለየት ችሎታ ይዘው አይወለዱም። እርግጥ ነው፣ በተፈጥሮ ያገኙት ሕሊና ይኖራቸዋል፤ ሆኖም ሕሊናቸው በትምህርት ወይም በሥልጠና መቀረጽ ያስፈልገዋል። (ሮም 2:14, 15) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሣከሪያ ጽሑፍ “ማሠልጠን” የሚለው የግሪክኛ ቃል “ልጅ ማሳደግ” ተብሎም ሊተረጎም እንደሚችል ይጠቁማል። አብዛኛውን ጊዜ፣ ፍቅራዊ ተግሣጽ የሚሰጣቸው ልጆች የደህንነት ስሜት ይሰማቸዋል። ነፃነታቸው ገደብ እንዳለው እንዲሁም የሚያደርጉት ውሳኔም ሆነ ምግባራቸው ጥሩ አሊያም መጥፎ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ይማራሉ። እንግዲያው ክርስቲያን ወላጆች የይሖዋን አመራር ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው! ልጆችን ማሳደግን በተመለከተ የሚሰነዘሩት ሐሳቦች ከባሕል ባሕል እንደሚለያዩና ዘዴዎቹም ከትውልድ ወደ ትውልድ እንደሚለዋወጡ አትዘንጉ። ሆኖም ወላጆች የአምላክን ምክር የሚሰሙ ከሆነ ለራሳቸው ትክክል መስሎ በታያቸው መንገድ አሊያም በሰብዓዊ ተሞክሮ ወይም አስተሳሰብ ላይ ተመሥርተው ልጆቻቸውን አያሳድጉም። w18.03 30 አን. 8-9

እሁድ፣ ጥር 6

በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግታችሁ ሥሩ።—ፊልጵ. 2:12

የተጠመቅህ ወጣት ከሆንክ ለመዳን የሚያስፈልገውን እርምጃ መውሰድ የአንተ ኃላፊነት ነው፤ የምትኖረው ከወላጆችህ ጋር መሆኑ ይህን እውነታ አይቀይረውም። ይህን ማስታወስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የጉርምስና ዕድሜ ላይ ስትደርስ አዳዲስ ስሜቶች ሊፈጠሩብህ እንዲሁም የተለያዩ ተጽዕኖዎች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ። አንዲት የ18 ዓመት ወጣት ይህ ሊሆን የሚችልበትን መንገድ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ልጅ [ልደቱ ስላልተከበረለት] ብቻ፣ የይሖዋ ምሥክር በመሆኑ የቀረበት ነገር እንዳለ አይሰማው ይሆናል። የፆታ ስሜት የሚያይልበት ዕድሜ ላይ ሲደርስ ግን የይሖዋን ሕጎች መታዘዝ ምንጊዜም የተሻለ አካሄድ ስለመሆኑ ከልቡ ማመን ያስፈልገዋል።” ትልቅ ከሆኑ በኋላ የተጠመቁ ክርስቲያኖችም እንኳ በርካታ ያልተጠበቁ የእምነት ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል። ከትዳር፣ ከጤንነት አሊያም ከሥራ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ፈታኝ ሁኔታዎችን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። በእርግጥም በየትኛውም የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኝ ክርስቲያን ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት የሚፈትኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙታል።—ያዕ. 1:12-14፤ w17.12 24 አን. 4-5

ሰኞ፣ ጥር 7

ተቆጡ፤ ሆኖም ኃጢአት አትሥሩ።—ኤፌ. 4:26

የአምላክ ወዳጅ የሆነው ዳዊት ብዙ ግፍ ደርሶበታል። ያም ሆኖ ምሬት ሕይወቱን እንዲቆጣጠረው አልፈቀደም። እንዲያውም “ከቁጣ ተቆጠብ፤ ንዴትንም ተው፤ ተበሳጭተህ ክፉ ነገር አትሥራ” ሲል ጽፏል። (መዝ. 37:8) ከቁጣ እንድንቆጠብ የሚያነሳሳን ከሁሉ የላቀው ምክንያት ይሖዋን ለመምሰል ያለን ፍላጎት ነው፤ እሱ “እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም።” (መዝ. 103:10) ‘ከቁጣ መቆጠብ’ የሚያስገኛቸው ጥቅሞችም አሉ። ቁጣ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት እንዲሁም የመተንፈሻ አካላት ችግር ሊያስከትል ይችላል። በተጨማሪም በጉበትና በቆሽት (ፓንክሪያስ) ላይ ጉዳት ሊያስከትል ብሎም በጨጓራ ሕመም እንድንሠቃይ ሊያደርገን ይችላል። በምንበሳጭበት ወቅት በትክክል ማሰብ ያቅተን ይሆናል። በቁጣ ገንፍለን የምንናገረው ነገር ወይም የምንወስደው እርምጃ ደግሞ ሌሎችን ይጎዳል፤ ይህም በመንፈስ ጭንቀት እንድንዋጥ ሊያደርገን ይችላል። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ “የሰከነ ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል” ይላል። (ምሳሌ 14:30) ታዲያ ሌሎች ቅር ሲያሰኙን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ከወንድማችን ጋር ሰላም መፍጠር የምንችለውስ እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ጥበብ የተንጸባረቀበት ምክር በተግባር በማዋል ነው። w18.01 10 አን. 14-15

ማክሰኞ፣ ጥር 8

መቃብር ውስጥ አትተወኝምና። ታማኝ አገልጋይህ ጉድጓድ እንዲያይ አትፈቅድም።—መዝ. 16:10

ዳዊት ይህን ያለው፣ እሱ ራሱ ፈጽሞ እንደማይሞት ወይም ወደ መቃብር እንደማይወርድ ለመግለጽ አስቦ አይደለም። ምክንያቱም የአምላክ ቃል፣ ዳዊት በዕድሜ ገፍቶ እንደሞተና ‘በዳዊት ከተማ እንደተቀበረ’ በግልጽ ይናገራል። (1 ነገ. 2:1, 10) ታዲያ መዝሙር 16:10 ስለ ማን እየተናገረ ነው? ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ፣ ጴጥሮስ በመዝሙር 16:10 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ስለ ማን እንደሚናገር አብራርቷል። (ሥራ 2:29-32) ጴጥሮስ በሺዎች ለሚቆጠሩ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ባቀረበው በዚህ ንግግር ላይ ዳዊት እንደሞተና እንደተቀበረ ጠቅሷል። ንግግሩን የሚያዳምጡት ሰዎችም ይህን ያውቁ ነበር። “አምላክ ክርስቶስን በመቃብር እንደማይተወውና ሥጋውም እንደማይበሰብስ” ዳዊት “አስቀድሞ ተረድቶ ስለ [መሲሑ ትንሣኤ]” እንደተናገረ ሐዋርያው አብራርቷል፤ በዚህ ወቅት ከአድማጮቹ መካከል የተቃውሞ ሐሳብ ያነሳ እንደነበረ ዘገባው አይገልጽም። ጴጥሮስ ይህን ነጥብ ለማጠናከር በመዝሙር 110:1 ላይ የሚገኘውን የዳዊትን ሐሳብ ጠቅሷል። (ሥራ 2:33-36) ጴጥሮስ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ ማስረጃ ስላቀረበ፣ የተሰበሰበው ሕዝብ ኢየሱስ “ጌታም ክርስቶስም” መሆኑን አምኖ ተቀብሏል። ከዚህም ባሻገር፣ ሕዝቡ መዝሙር 16:10 ፍጻሜውን ያገኘው ኢየሱስ ከሞት ሲነሳ እንደሆነ ተገንዝቧል። w17.12 10 አን. 10-12

ረቡዕ፣ ጥር 9

እያንዳንዱም ነገር ተቆጥሮ ተመዘነ፤ ክብደቱም ሁሉ ተመዘገበ።—ዕዝራ 8:34

የበላይ አካሉ የሚደረገውን መዋጮ የሚጠቀምበት መንገድ ታማኝና ልባም መሆኑን ያሳያል። (ማቴ. 24:45) የበላይ አካሉ አባላት በዚህ ረገድ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ እንዲረዳቸው ወደ ይሖዋ ይጸልያሉ፤ ከዚያም በጥንቃቄ በጀት ያወጣሉ። (ሉቃስ 14:28) ሐዋርያው ጳውሎስ በይሁዳ የሚገኙ ወንድሞችን ለመርዳት መዋጮ አሰባስቦ ነበር። መዋጮውን የሚያደርሱት ሰዎች ‘በይሖዋ ፊት ብቻ ሳይሆን በሰዎችም ፊት ሁሉንም ነገር በሐቀኝነት እንዲያከናውኑ’ ለማድረግ ተገቢ እርምጃዎችን ወስዷል። (2 ቆሮንቶስ 8:18-21) ድርጅቱም የዕዝራንና የጳውሎስን ምሳሌ በመከተል በአሁኑ ጊዜ የሚዋጣው ገንዘብ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ጥብቅ የሆነ የአሠራር ሂደት ይከተላል። (ዕዝራ 8:24-33) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አስደሳች የሆኑ በርካታ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ታቅደው ነበር። ድርጅቱ በእናንተ ልግስና የተገኘውን መዋጮ በተቻለ መጠን አብቃቅቶ ለመጠቀም ሲል ወጪ መቀነስና ሥራውን ማቅለል የሚቻልባቸውን እርምጃዎች ወስዷል። w18.01 19-20 አን. 12-13

ሐሙስ፣ ጥር 10

የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ።—ቆላ. 3:15

ፍቅርና ደግነት እርስ በርስ ይቅር እንድንባባል ሊረዱን ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የእምነት ባልንጀራችን የተናገረው ወይም ያደረገው ነገር ስሜታችንን ጎዳው እንበል፤ በዚህ ወቅት እኛ ራሳችን ደግነት የጎደለው ነገር የተናገርንባቸውን ወይም ያደረግንባቸውን ጊዜያት ለማስታወስ መሞከራችን ጠቃሚ ነው። በእነዚያ ወቅቶች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስህተታችንን ይቅር በማለት ፍቅርና ደግነት ስላሳዩን አመስጋኞች አይደለንም? (መክ. 7:21, 22) በተለይ ደግሞ ክርስቶስ፣ እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች አንድነት እንዲኖራቸው በማድረግ ላሳየው ደግነት አመስጋኞች ነን። ሁላችንም የምንወደውና የምናመልከው አምላክ አንድ ነው፤ አንድ ዓይነት መልእክት እንሰብካለን፤ የሚያጋጥሙን ብዙዎቹ ችግሮችም አንድ ዓይነት ናቸው። እርስ በርስ ይቅር በመባባል ደግነትና ፍቅር ማሳየታችን ለክርስቲያናዊ አንድነታችን አስተዋጽኦ ያበረክታል፤ እንዲሁም ዓይናችን በሕይወት ሽልማት ላይ እንዲያተኩር ያደርጋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ቅናት ሽልማታችንን ሊያሳጣን ይችላል። ለምሳሌ ቃየን በወንድሙ በአቤል በመቅናቱ የወንድሙን ሕይወት አጥፍቷል። ቆሬ፣ ዳታንና አቤሮን በሙሴ መቅናታቸው እሱን እንዲቃወሙ አድርጓቸዋል። ንጉሥ ሳኦልም ዳዊት ባገኘው ስኬት ስለቀና እሱን ለመግደል ተነሳስቷል። w17.11 27 አን. 9-10

ዓርብ፣ ጥር 11

ጉዳዩን በጥልቀት በመመርመርና በማጣራት ስለ ሁኔታው ማወቅ ይኖርብሃል።—ዘዳ. 13:14

በፍርድ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች፣ ከባድ ኃጢአት የፈጸመው ክርስቲያን ንስሐ መግባት አለመግባቱን በጥንቃቄ ያመዛዝናሉ። አንድ ሰው ንስሐ እንደገባና እንዳልገባ ማወቅ ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል። ግለሰቡ ንስሐ መግባቱን ለማወቅ ስለፈጸመው ድርጊት ያለውን አመለካከት፣ ዝንባሌውንና የልቡን ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። (ራእይ 3:3) ኃጢአት የሠራ ግለሰብ ምሕረት ለማግኘት ንስሐ መግባት ይኖርበታል። ከይሖዋና ከኢየሱስ በተለየ ሽማግሌዎች የሰውን ልብ ማንበብ አይችሉም። ሽማግሌ ከሆንክ አንድ ሰው ከልቡ ንስሐ መግባቱን ማስተዋል የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ ጥበብና ማስተዋል ለማግኘት ጸልይ። (1 ነገ. 3:9) ሁለተኛ፣ ‘በዚህ ዓለም ሐዘን’ እና “አምላካዊ በሆነ መንገድ [በማዘን]” ማለትም ከልብ ንስሐ በመግባት መካከል ያለውን ልዩነት ማስተዋል እንድትችል የአምላክን ቃል እንዲሁም ታማኙ ባሪያ ያወጣቸውን ጽሑፎች መርምር። (2 ቆሮ. 7:10, 11) ቅዱሳን መጻሕፍት ንስሐ የገቡና ንስሐ ያልገቡ ኃጢአተኞችን እንዴት እንደሚገልጿቸው ለማስተዋል ሞክር። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነዚህ ሰዎች ስሜት፣ አመለካከትና ድርጊት ምን ይላል? w17.11 17 አን. 16-17

ቅዳሜ፣ ጥር 12

[ልጆች] ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ . . . ይሆናሉ።—2 ጢሞ. 3:2, 4

በምንኖርበት ዘመን፣ ለወላጆች አለመታዘዝ በመጻሕፍት፣ በፊልሞችና በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ ምንም ችግር እንደሌለው እንዲያውም ተቀባይነት እንዳለው ተደርጎ የሚቀርብበት ጊዜ አለ፤ ይሁንና ለወላጆች አለመታዘዝ የማኅበረሰቡ መሠረት የሆነውን የቤተሰብ ሕይወት ያናጋል። ለወላጆች አለመታዘዝ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ችግር እንደሚፈጥር ቀደም ባሉት ዘመናትም ይታወቅ ነበር። በጥንቷ ግሪክ ወላጆቹን የሚመታ ሰው በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉትን መብቶች በሙሉ ያጣ ነበር፤ በሮም ሕግ መሠረት ደግሞ አባትን መምታት ከግድያ የማይተናነስ ወንጀል ነበር። የዕብራይስጥም ሆነ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩ ይመክራሉ። (ዘፀ. 20:12፤ ኤፌ. 6:1-3) ልጆች፣ ወላጆቻቸው ስላደረጉላቸው ነገሮች ማሰባቸው በዓለም ላይ የሚታየው ያለመታዘዝ ዝንባሌ እንዳይጋባባቸው ለመከላከል ይረዳቸዋል። በተጨማሪም ልጆች፣ የሁላችንም አባት የሆነው ይሖዋ ለወላጆቻቸው እንዲታዘዙ እንደሚጠብቅባቸው ማስታወሳቸው የመታዘዝን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል። ልጆች ስለ ወላጆቻቸው መልካም ነገር መናገራቸው፣ እኩዮቻቸውም ለራሳቸው ወላጆች አክብሮት እንዲኖራቸው ሊያደርጋቸው ይችላል። w18.01 29 አን. 8-9

እሁድ፣ ጥር 13

እያንዳንዱም ከነፋስ እንደ መከለያ፣ ከውሽንፍር እንደ መሸሸጊያ፣ ውኃ በሌለበት ምድር እንደ ጅረት፣ በደረቅ ምድርም እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ ይሆናል።—ኢሳ. 32:2

በዛሬው ጊዜ ከባድ ኃጢአት የፈጸመ ክርስቲያን ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ለማደስ እንዲችል የጉባኤ ሽማግሌዎችን እርዳታ መጠየቅ ይኖርበታል። እንዲህ ማድረጉ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ግለሰቦችን ጉዳይ ሽማግሌዎች እንዲመለከቱ ዝግጅት ያደረገው ይሖዋ ራሱ ነው። (ያዕ. 5:14-16) በሁለተኛ ደረጃ፣ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች የሽማግሌዎችን እርዳታ ማግኘታቸው የአምላክን ሞገስ እንደገና እንዲያገኙ እንዲሁም ኃጢአት መሥራት ልማድ እንዳይሆንባቸው ይረዳቸዋል። (ገላ. 6:1፤ ዕብ. 12:11) በሦስተኛ ደረጃ፣ ሽማግሌዎች ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን ለማጽናናት እንዲሁም ከመጠን ባለፈ የጥፋተኝነት ስሜት እንዳይደቆሱ ለመርዳት የሚያስችል ኃላፊነትና ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል። ይሖዋ፣ ሽማግሌዎች “ከውሽንፍር እንደ መሸሸጊያ” እንደሆኑ ገልጿል። (ኢሳ. 32:2) ይህ ዝግጅት የአምላክ ምሕረት መገለጫ ነው ቢባል አትስማማም? በርካታ የአምላክ አገልጋዮች የሽማግሌዎችን እርዳታ መጠየቃቸውና የተሰጣቸውን እርዳታ መቀበላቸው እፎይታ አስገኝቶላቸዋል። w17.11 9-10 አን. 8-9

ሰኞ፣ ጥር 14

ተግሣጽ . . . ያስከፋል።—ዕብ. 12:11

ከባድ ሊሆንብን ቢችልም ከተወገደ የቤተሰባችን አባል ጋር በስልክ፣ በጽሑፍ መልእክት፣ በደብዳቤ፣ በኢሜይል ወይም በማኅበራዊ ድረ ገጾች አማካኝነት አላስፈላጊ ግንኙነት ከማድረግ መቆጠብ ይኖርብናል። ሆኖም ተስፋ መቁረጥ የለብንም። ፍቅር “ሁሉን ተስፋ ያደርጋል”፤ በመሆኑም ይሖዋን ማምለኩን የተወ የቤተሰባችን አባል አንድ ቀን ወደ ይሖዋ ይመለሳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። (1 ቆሮ. 13:7) ከይሖዋ የራቀው የቤተሰባችሁ አባል ለውጥ እያደረገ እንዳለ የሚጠቁም ነገር ካስተዋላችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ሐሳብ ብርታት እንዲሰጠውና “ወደ እኔ ተመለስ” በማለት ይሖዋ ላቀረበው ግብዣ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ ልትጸልዩለት ትችላላችሁ። (ኢሳ. 44:22) ኢየሱስ ማንኛውንም ሰው ከእሱ የምናስበልጥ ከሆነ የእሱ ተከታዮች ልንሆን እንደማንችል ተናግሯል። የእሱ ደቀ መዛሙርት ግን የቤተሰብ ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም ደፋር በመሆን ለእሱ ታማኞች ሆነው እንደሚቀጥሉ ሙሉ እምነት ነበረው። ኢየሱስን መከተላችሁ በቤተሰባችሁ ውስጥ “ሰይፍ” አምጥቶ ከሆነ ያጋጠማችሁን ተፈታታኝ ሁኔታ በተሳካ መንገድ ለመቋቋም በይሖዋ ታመኑ፤ እሱ እንዲረዳችሁ በጸሎት ለምኑት። (ኢሳ. 41:10, 13) ይሖዋና ኢየሱስ ደስ እንደሚሰኙባችሁና የታማኝነት ጎዳና በመከተላችሁ እንደሚባርኳችሁ በማወቅ ተደሰቱ። w17.10 16 አን. 19-21

ማክሰኞ፣ ጥር 15

ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን . . . ልበሱ።—ቆላ. 3:12

ሰዎች ከአዳም በወረሱት ኃጢአት ምክንያት የሚደርስባቸውን ሥቃይ ስናይ ለእነሱ ርኅራኄ ለማሳየት እንነሳሳለን። እርጅናና ሕመም የሚወገድበትን ጊዜ በናፍቆት እንጠባበቃለን። የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ የምንጸልየውም ለዚህ ነው። እስከዚያው ድረስ ግን እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፍ ለማድረግ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን። እስቲ ይህን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ደራሲ አልዛይመርስ በሽታ የነበረባቸው በዕድሜ የገፉ እናቱ ያጋጠማቸውን ሁኔታ አስመልክቶ ጽፎ ነበር። እኚህ ሴት አንድ ቀን ልብሳቸው ላይ አመለጣቸው። ልብሳቸውን ለማጽዳት እየሞከሩ ሳለ የበሩ ደወል ተደወለ። የመጡት ሰዎች ሴትየዋን አዘውትረው ያነጋግሯቸው የነበሩ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። እነዚህ እህቶች እርዳታ ይፈልጉ እንደሆነ ሴትየዋን ጠየቋቸው። እሳቸውም “የሚያሳፍር ቢሆንም ብትረዱኝ ደስ ይለኛል” በማለት መለሱ። በመሆኑም እህቶች ሴትየዋን ረዷቸው። በኋላም ሻይ ካፈሉላቸው በኋላ ቁጭ ብለው ተጫወቱ። የሴትየዋ ልጅ እነዚህ እህቶች ባደረጉት ነገር ልቡ በጣም ተነካ። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለእነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ጥልቅ አክብሮት አለኝ። የሚሰብኩትን ነገር በሚገባ ይሠሩበታል።” አንተስ ለታመሙና በዕድሜ ለገፉ ሰዎች ያለህ ርኅራኄ ችግራቸውን ለማቅለል አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ እንድታደርግ ይገፋፋሃል?—ፊልጵ. 2:3, 4፤ w17.09 9 አን. 5፤ 12 አን. 14

ረቡዕ፣ ጥር 16

በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።—1 ዮሐ. 3:18

ለወንድሞቻችን ፍቅር እንዳለን የሚያሳዩ ተግባሮችን የሚቻል ከሆነ “በስውር” ማለትም ከሌሎች እይታ ውጭ ለማከናወን ፈቃደኞች መሆን አለብን። (ማቴ. 6:1-4) በተጨማሪም ሌሎችን ለማክበር ቀዳሚ መሆን አለብን። (ሮም 12:10) ኢየሱስ በጣም ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን በማከናወን ሌሎችን በማክበር ረገድ ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። (ዮሐ. 13:3-5, 12-15) ለሌሎች አክብሮት ለማሳየት የሚያስፈልገውን ትሕትና ለማዳበር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። ሐዋርያትም እንኳ ኢየሱስ ያደረጋቸውን ነገሮች ትርጉም ሙሉ በሙሉ የተረዱት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ነው። (ዮሐ. 13:7) ለሌሎች አክብሮት እንዳለን ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ በትምህርት ደረጃችን፣ በቁሳዊ ሀብታችን ወይም በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ባሉን መብቶች ምክንያት ከሌሎች የተሻልን እንደሆንን አድርገን ባለማሰብ ነው። (ሮም 12:3) በተጨማሪም ሌሎች ሲመሰገኑ አንቀናም፤ በጉዳዩ ውስጥ የእኛም አስተዋጽኦ እንዳለበት አሊያም ከእነሱ እኩል ልንመሰገን እንደሚገባ በሚሰማን ጊዜም እንኳ አብረናቸው እንደሰታለን። w17.10 9 አን. 9-10

ሐሙስ፣ ጥር 17

ምሥራቹን ለሌሎች አካፍል ዘንድ ለምሥራቹ ስል ሁሉን ነገር አደርጋለሁ።—1 ቆሮ. 9:23

በርካታ አስፋፊዎች የአምላክን ቃል በአገልግሎት ላይ መጠቀማቸው በሚያነጋግሯቸው ሰዎች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አስተውለዋል። እስቲ አንድ ተሞክሮ እንመልከት። አንድ ወንድም መጽሔቶቻችንን ለበርካታ ዓመታት ላነበቡ አንድ አረጋዊ ሰው ተመላልሶ መጠየቅ አደረገላቸው። ወንድም በቅርቡ የወጣውን መጠበቂያ ግንብ እንዲሁ ሰጥቷቸው ከመሄድ ይልቅ በመጽሔቱ ውስጥ የሚገኘውን 2 ቆሮንቶስ 1:3, 4⁠ን አነበበላቸው። ጥቅሱ “የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ . . . በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል” ይላል። ሰውየው በተነበበላቸው ጥቅስ ልባቸው በጥልቅ ስለተነካ ጥቅሱን በድጋሚ እንዲያነብላቸው ወንድምን ጠየቁት። ከዚያም እኚህ ሰው፣ እሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸው መጽናኛ በጣም ያስፈልጋቸው እንደነበር ገለጹ። ሰውየው በዚህ ጥቅስ ምክንያት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ የማወቅ ፍላጎት አደረባቸው። በእርግጥም የአምላክ ቃል ያለው ኃይል በአገልግሎታችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል ቢባል አትስማማም?—ሥራ 19:20፤ w17.09 26 አን. 9-10

ዓርብ፣ ጥር 18

በአጥንቱና በሥጋው ላይ ጉዳት አድርስበት፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።—ኢዮብ 2:5

ዲያብሎስ በይሖዋ ላይ ያቀረበው ውንጀላ ታማኝ የሆኑትን መንፈሳዊ ፍጥረታት አበሳጭቷቸው፣ አስቆጥቷቸውና አስከፍቷቸው ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። ይሁንና ይሖዋ የችኮላ እርምጃ አልወሰደም። የወሰደው እርምጃ በሚገባ የታሰበበትና ተስማሚ ነበር። ይሖዋ ጉዳዩን የያዘበት መንገድ ለቁጣ የዘገየና ፍትሐዊ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። (ዘፀ. 34:6፤ ኢዮብ 2:2-6) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ይሖዋ የተወሰነ ጊዜ እንዲያልፍ የፈቀደው “ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው”፤ ከዚህ ይልቅ ሁሉም ሰዎች ‘ለንስሐ እንዲበቁ ይፈልጋል።’ (2 ጴጥ. 3:9) ይሖዋ ራስን በመግዛት ረገድ የተወውን ምሳሌ መመርመራችን እኛም ከመናገራችንና እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት ቆም ብለን ማሰብ እንዳለብን ያስገነዝበናል፤ የችኮላ እርምጃ መውሰድ የለብንም። ከበድ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ጥበብ የተንጸባረቀበት እርምጃ መውሰድ እንድትችል ጊዜ ወስደህ በጉዳዩ ላይ አስብበት። ትክክል የሆነውን ነገር ለመናገር ወይም ለማድረግ የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጥህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። (መዝ. 141:3) ተቆጥተህ ባለህበት ሰዓት፣ ስሜታዊ እርምጃ መውሰድ ይቀናህ ይሆናል። ሆኖም አብዛኞቻችን ተቆጥተን ሳለን በተናገርነው ወይም ባደረግነው ነገር ተጸጽተን እንደምናውቅ ጥርጥር የለውም!—ምሳሌ 14:29፤ 15:28፤ 19:2፤ w17.09 4 አን. 6-7

ቅዳሜ፣ ጥር 19

ብርና ወርቅ ወስደህ አክሊል ሥራ፤ ከዚያም በየሆጼዴቅ ልጅ በሊቀ ካህናቱ በኢያሱ ራስ ላይ አድርገው።—ዘካ. 6:11

በሊቀ ካህናቱ በኢያሱ ራስ ላይ አክሊል መደረጉ ኢያሱ ንጉሥ ሆኖ እንደተሾመ የሚጠቁም ነው? አይደለም፤ ምክንያቱም ኢያሱ የተወለደው በዳዊት የንግሥና መስመር ስላልሆነ ንጉሥ ለመሆን ብቃቱን አያሟላም። በመሆኑም በኢያሱ ራስ ላይ አክሊል መደረጉ ወደፊት ለሚመጣው ዘላለማዊ ንጉሥና ካህን ትንቢታዊ ጥላ ነው። ንጉሥ ሆኖ የተሾመው ሊቀ ካህናት ቀንበጥ ተብሎ ይጠራል። መጽሐፍ ቅዱስ ቀንበጥ ተብሎ የተጠራው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ በግልጽ ይናገራል። (ኢሳ. 11:1፤ ማቴ. 2:23 ግርጌ) በሰማይ ያለውን የይሖዋን ሠራዊት የሚመራው፣ ንጉሥም ሊቀ ካህናትም የሆነው ኢየሱስ ነው። የአምላክ ሕዝቦች የሚኖሩት በጥላቻ በተሞላ ዓለም ውስጥ ቢሆንም ኢየሱስ በቡድን ደረጃ ጥበቃ ስለሚያደርግላቸው ያለስጋት መኖር ይችላሉ። (ኤር. 23:5, 6) በቅርቡ ደግሞ ክርስቶስ ግንባር ቀደም ሆኖ መንግሥታትን ድል በማድረግ የአምላክን ሉዓላዊነት እንደሚደግፍ የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ የይሖዋን ሕዝቦች ይታደጋል። (ራእይ 17:12-14፤ 19:11, 14, 15) ይሁንና ቀንበጥ ተብሎ የተጠራው ኢየሱስ የፍርድ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ሊያከናውነው የሚገባ አንድ ትልቅ ሥራ አለ። w17.10 29 አን. 12-14

እሁድ፣ ጥር 20

አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፋችሁ ጣሉ።—ቆላ. 3:9

ልብሳችሁ ቢቆሽሽና መጥፎ ጠረን ቢያመጣ ምን ታደርጋላችሁ? የቆሸሸውን ልብሳችሁን በተቻለ ፍጥነት እንደምታወልቁት ምንም ጥርጥር የለውም። በተመሳሳይም ከአምላክ ባሕርይ ጋር የሚጋጩ ልማዶችን ገፈን እንድንጥል የተሰጠንን መመሪያ ለመታዘዝ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለብን። ጳውሎስ በዘመኑ ለነበሩት ክርስቲያኖች “[እነዚህን ልማዶች] ሁሉ ከእናንተ አስወግዱ” በማለት የሰጠውን ግልጽ መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ እንፈልጋለን። ጳውሎስ ከጠቀሳቸው መጥፎ ልማዶች መካከል አንዱ የፆታ ብልግና ነው። (ቆላ. 3:5-9) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የፆታ ብልግና” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ሕጋዊ ጋብቻ ባልፈጸሙ ሰዎች መካከል የሚደረገውን የፆታ ግንኙነትና ግብረ ሰዶማዊነትን የሚያካትት ነው። ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ ‘የአካል ክፍሎቻቸውን እንዲገድሉ’ ማለትም ‘ከፆታ ብልግና’ ጋር ተያያዥነት ያለውን ማንኛውንም ፍላጎት እንዲያስወግዱ ነግሯቸዋል። ጳውሎስ የተጠቀመበት አገላለጽ መጥፎ ፍላጎቶችን ማስወገድ ጠንካራ እርምጃ መውሰድን እንደሚጠይቅ በግልጽ ያሳያል። ያም ሆኖ በትግሉ ልናሸንፍ እንችላለን። w17.08 18 አን. 5-6

ሰኞ፣ ጥር 21

የሚያድነኝን አምላክ በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ አሳያለሁ።—ሚክ. 7:7 ግርጌ

ነቢዩ ሚክያስ ልክ እንደ እኛ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ መኖር አስፈልጎት ነበር። ይህ ነቢይ የኖረው ክፉው ንጉሥ አካዝ ይገዛ በነበረበት ዘመን ሲሆን በዚያን ወቅት ብዙ መጥፎ ነገሮች ይፈጸሙ ነበር። እንዲያውም በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች “መጥፎ ነገር በማድረግ የተካኑ” ሆነው ነበር። (ሚክ. 7:1-3) ሚክያስ እነዚህ ሁኔታዎች በእሱ ጥረት ሊለወጡ እንደማይችሉ ተገንዝቦ ነበር። እኛም እንደ ሚክያስ ዓይነት እምነት ካለን በፈቃደኝነት ይሖዋን ለመጠበቅ እንነሳሳለን። የእኛ ሁኔታ በታሰረበት ክፍል ውስጥ ሆኖ፣ የሞት ቅጣት የሚቀበልበትን ቀን እንደሚጠብቅ እስረኛ አይደለም። ይህ እስረኛ እየጠበቀ ያለው ከዚህ ሌላ ምንም አማራጭ ስለሌለው ነው፤ ደግሞም ያን ቀን በጉጉት ሊጠባበቀው አይችልም። የእኛ ሁኔታ ግን ከዚህ ምንኛ የተለየ ነው! ይሖዋ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጠን የገባልንን ቃል በትክክለኛውና ከሁሉ በተሻለው ጊዜ እንደሚፈጽም ስለምናውቅ እሱን በፈቃደኝነት እንጠብቃለን! በመሆኑም “በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት [እንቋቋማለን]።” (ቆላ. 1:11, 12) ይሖዋ ቶሎ እርምጃ ባለመውሰዱ እያማረርንና እያጉረመረምን የምንጠብቅ ከሆነ ግን አምላካችን ደስ አይለውም።—ቆላ. 3:12፤ w17.08 4 አን. 6-7

ማክሰኞ፣ ጥር 22

ይሖዋ የዋሆችን ያነሳል።—መዝ. 147:6

ይሖዋ ከሚሰጠን እርዳታ ተጠቃሚ ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ከእሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት ይኖርብናል። ይህን ለማድረግ ደግሞ የዋህነትን ማዳበር አለብን። (ሶፎ. 2:3) የዋህ የሆኑ ሰዎች ማንኛውንም የፍትሕ መጓደል እንዲሁም በራሳቸው ላይ የደረሰውን ጉዳት አምላክ እስኪያስተካክለው ድረስ በትዕግሥት ይጠብቃሉ። ይሖዋ እንዲህ ላሉት ሰዎች ሞገሱን ያሳያቸዋል። በሌላ በኩል ግን አምላክ “ክፉዎችን . . . መሬት ላይ ይጥላል።” (መዝ. 147:6ለ) ይህ እንዴት ያለ ኃይለኛ ሐሳብ ነው! የይሖዋን ታማኝ ፍቅር ለማየትና ከቁጣው ለመሰወር ከፈለግን፣ እሱ የሚጠላቸውን ነገሮች መጥላት ይኖርብናል። (መዝ. 97:10) ለምሳሌ፣ የፆታ ብልግናን መጥላት አለብን። ይህም ሲባል የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን ጨምሮ እንዲህ ወዳለው ኃጢአት ከሚመራ ማንኛውም ነገር መራቅ አለብን ማለት ነው። (መዝ. 119:37፤ ማቴ. 5:28) ይህ ከባድ ትግል ማድረግ የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና የይሖዋን በረከት ለማግኘት ስንል ማንኛውንም ጥረት ብናደርግ የሚያስቆጭ አይሆንም። ይህን ትግል ስናደርግ በራሳችን ሳይሆን በይሖዋ መታመን ይኖርብናል። ወደ ይሖዋ መቅረብና እንዲረዳን መማጸን አለብን። w17.07 19-20 አን. 11-13

ረቡዕ፣ ጥር 23

ለችግረኛ ሞገስ የሚያሳይ ለይሖዋ ያበድራል።—ምሳሌ 19:17

ቁሳዊ ንብረቶችን ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማራመድ በመጠቀም ሀብታችንን ሌሎችን ለመርዳት ልንጠቀምበት እንችላለን። የዚህ ዓለም ሀብት ያላቸውና በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ወይም ወደ ሌላ አገር ተዛውረው ማገልገል ያልቻሉ ክርስቲያኖች፣ የሚያዋጡት ገንዘብ ሌሎችን በአገልግሎታቸው ለመደገፍ እንደሚውል ማወቃቸው ያስደስታቸዋል። በፈቃደኝነት የሚደረጉት መዋጮዎች፣ መንፈሳዊ ጽሑፎችን ለማቅረብ እንዲሁም ድህነት ባጠላባቸው ሆኖም ከፍተኛ መንፈሳዊ እድገት ባለባቸው አካባቢዎች የሚደረገውን የስብከት ሥራ ለመደገፍ ያስችላሉ። ለበርካታ ዓመታት እንደ ማዳጋስካር፣ ሩዋንዳና ኮንጎ ባሉት አገሮች የሚኖሩ ወንድሞች፣ ለቤተሰባቸው የሚሆነውን ምግብ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ከመግዛት አንዱን ለመመረጥ ይገደዱ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለመግዛት ከአንድ ሳምንት ወይም ከአንድ ወር ደሞዛቸው ጋር የሚመጣጠን ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ግን የይሖዋ ድርጅት ብዙዎች የሚያደርጉትን መዋጮ በመጠቀምና ‘የአንዱ ትርፍ የሌላውን ጉድለት እንዲሸፍን’ በማድረግ መጽሐፍ ቅዱሶች ወደተለያዩ ቋንቋዎች እንዲተረጎሙና እንዲሰራጩ አድርጓል፤ ይህም እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል እንዲሁም መንፈሳዊ ጥማት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እንዲያገኙ አስችሏል።—2 ቆሮ. 8:13-15፤ w17.07 9 አን. 11

ሐሙስ፣ ጥር 24

ልጄ ሆይ፣ ለሚነቅፈኝ መልስ መስጠት እችል ዘንድ ጥበበኛ ሁን፤ ልቤንም ደስ አሰኘው።—ምሳሌ 27:11

የኢዮብ ታሪክ ፈተናዎች የሚደርሱብን ይሖዋ ስላዘነብን እንዳልሆነ እንድንገነዘብ ያደርገናል፤ ይህን መገንዘባችን ሊያጽናናን ይችላል። የሚደርሱብን ፈተናዎች የአምላክን ሉዓላዊነት ለመደገፍ የሚያስችል አጋጣሚ ይሰጡናል። መጽናታችን “በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንድናገኝ” እንዲሁም ተስፋችን ብሩህ ሆኖ እንዲታየን ያስችለናል። (ሮም 5:3-5) የኢዮብ ታሪክ “ይሖዋ እጅግ አፍቃሪና መሐሪ እንደሆነ” ያሳያል። (ያዕ. 5:11) በመሆኑም ይሖዋ እኛንም ሆነ ከሉዓላዊነቱ ጎን የሚቆሙ ሰዎችን በሙሉ እንደሚባርክ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይህን ማወቃችን “በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት” እንድንቋቋም ይረዳናል። (ቆላ. 1:11) እርግጥ ነው፣ አንገብጋቢ በሆነው ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል። በመሆኑም ምንም ዓይነት ችግሮች ቢያጋጥሙን የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፋችን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ምንጊዜም ማስታወስ ይኖርብናል። w17.06 25-26 አን. 15-16

ዓርብ፣ ጥር 25

ከስግብግብነትም ሁሉ ተጠበቁ።—ሉቃስ 12:15

በዛሬው ጊዜ ብዙዎች በዋነኝነት የሚያሳስባቸው ፋሽን የሆኑ ነገሮችን፣ አዲስ የወጡ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን ወይም ሌሎች ነገሮችን ማግኘታቸው ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ ክርስቲያን ለእነዚህ ነገሮች ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጥ ለማወቅ ራሱን እንደሚከተለው ብሎ መጠየቅ ይኖርበታል፦ ‘ቁሳዊ ነገሮች በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ ከመያዛቸው የተነሳ ለጉባኤ ስብሰባዎች በመዘጋጀት ከማሳልፈው ጊዜ ይልቅ አዲስ ስለወጡ መኪኖች ወይም ፋሽኖች የሚገልጹ መረጃዎችን በመከታተልና ስለ እነዚህ ነገሮች በማሰብ የማሳልፈው ጊዜ ይበልጣል? በዕለት ተዕለት ጉዳዮች ከሚገባው በላይ ከመጠመዴ የተነሳ ለጸሎትና ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የምመድበው ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል?’ ለቁሳዊ ነገሮች ያለን ፍቅር ለክርስቶስ ካለን ፍቅር እየበለጠ እንደሆነ ካስተዋልን፣ ኢየሱስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሰጠውን ምክር ልናሰላስልበት ይገባል። ኢየሱስ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም” ብሏል። አክሎም “ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም” በማለት ተናግሯል። ይህ የሆነው ሁለቱም “ጌቶች” ሁለንተናችንን እንድንሰጣቸው ስለሚፈልጉ ነው። (ማቴ. 6:24) ማንኛችንም ብንሆን ፍጹማን ባለመሆናችን ፍቅረ ንዋይን ጨምሮ “ከሥጋችን ፍላጎት” ጋር በምናደርገው ትግል ላለመሸነፍ ምንጊዜም ጥረት ማድረግ አለብን።—ኤፌ. 2:3፤ w17.05 25-26 አን. 15-16

ቅዳሜ፣ ጥር 26

ምሥራቹን ለሌሎች አካፍል ዘንድ ለምሥራቹ ስል ሁሉን ነገር አደርጋለሁ።—1 ቆሮ. 9:23

ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን እንደ ሸክላ ዕቃ ነን፤ ሆኖም የምንሰብከው መልእክት ለራሳችንም ሆነ ለሚሰሙን ሰዎች የዘላለም ሕይወት ሊያስገኝ የሚችል ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ለአገልግሎቱ ያለው ፍቅር ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በትጋት እንዲካፈል አነሳስቶታል። (ሮም 1:14, 15፤ 2 ጢሞ. 4:2) በተጨማሪም የደረሰበትን ከባድ ስደት እንዲቋቋም አስችሎታል። (1 ተሰ. 2:2) እኛስ ለአገልግሎታችን እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ሰዎችን ለማነጋገር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በሙሉ ለመጠቀም ንቁ በመሆን ለአገልግሎቱ ያለውን አድናቆት አሳይቷል። እኛም እንደ ሐዋርያትና የጥንት ክርስቲያኖች ሁሉ መደበኛ ባልሆነ መንገድ፣ በአደባባይ እንዲሁም ከቤት ወደ ቤት እንሰብካለን። (ሥራ 5:42፤ 20:20) በተጨማሪም ሁኔታችን በፈቀደልን መጠን ረዳት ወይም የዘወትር አቅኚ በመሆን አገልግሎታችንን ለማስፋት ጥረት እናደርጋለን። ከዚህም ሌላ አዲስ ቋንቋ እንማር አሊያም በአገራችን ውስጥ ወዳለ ሌላ ቦታ ወይም ወደ ሌላ አገር ተዛውረን እናገለግል ይሆናል።—ሥራ 16:9, 10፤ w17.06 10-11 አን. 8-9

እሁድ፣ ጥር 27

ተራሮች ሁሉና ደሴቶች ሁሉ ከቦታቸው ተወገዱ።—ራእይ 6:14

በዚህ ዓለም ላይ አብዛኛውን የክፋት ድርጊት የሚፈጽሙት ግለሰቦች ሳይሆኑ ድርጅቶች ናቸው። የሃይማኖት ድርጅቶች ስለ አምላክ ማንነት፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት፣ ስለ ምድርና ስለ ሰው ልጆች የወደፊት ዕጣ እንዲሁም ስለ ሌሎች በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች የተሳሳተ ትምህርት በማስተማር ብዙዎችን ያታልላሉ። ምግባረ ብልሹ የሆኑ መንግሥታት ደግሞ ጦርነትንና የጎሳ ግጭትን ይቆሰቁሳሉ፤ እንዲሁም ድሆችንና ደካሞችን ይበዘብዛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ስግብግብ የሆኑ የንግድ ድርጅቶች አካባቢን ይበክላሉ፣ የተፈጥሮ ሀብትን ይመዘብራሉ እንዲሁም ደንበኞቻቸውን ያጭበረብራሉ፤ በዚህም ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በድህነት እየማቀቁ ጥቂቶች ተዝቆ የማያልቅ ሀብት ያጋብሳሉ። የአምላክ ቃል መንግሥታትና የአምላክን መንግሥት የማይደግፉ ሌሎች ድርጅቶች በሙሉ ከመሠረታቸው እንደሚናጉ ይናገራል፤ አዎ፣ እነዚህ መንግሥታት ከእነሱ ጎን ከተሰለፉ ድርጅቶች ሁሉ ጋር ይጠፋሉ።—ኤር. 25:31-33፤ w17.04 11 አን. 7-8

ሰኞ፣ ጥር 28

ላመጣበት የነበረውን ጥፋት በእሱ ዘመን አላመጣም።—1 ነገ. 21:29

“ልብን የሚመረምር” አምላክ የሆነው ይሖዋ ለአክዓብ በተወሰነ መጠን ምሕረት አሳይቶታል። (ምሳሌ 17:3) አክዓብ የፈጸመውን አስከፊ ድርጊት የሚያውቁ ሰዎች የይሖዋን ውሳኔ ሲሰሙ ምን ተሰምቷቸው ይሆን? የናቡቴ ቤተሰብና ወዳጆች፣ በአክዓብ ቤተሰብ ላይ የተላለፈው ፍርድ እሱ በሕይወት እያለ እንደማይፈጸም ሲያውቁ እምነታቸው ተፈትኖ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ትሕትና እምነታቸውን እንዳያጡ ረድቷቸው መሆን አለበት፤ ትሑት ከሆኑ አምላካቸው ፈጽሞ ፍትሕን እንደማያጓድል በመተማመን ይሖዋን በታማኝነት ማምለካቸውን ይቀጥላሉ። (ዘዳ. 32:3, 4) ናቡቴ፣ ልጆቹና ቤተሰቦቻቸው ይሖዋ ጻድቃንን ከሞት በሚያስነሳበት ወቅት ፍትሕ በተሟላ ሁኔታ ሲፈጸም ያያሉ። (ኢዮብ 14:14, 15፤ ዮሐ. 5:28, 29) ከዚህም በተጨማሪ ትሑት የሆነ ሰው “እውነተኛው አምላክ እያንዳንዱን የተሰወረ ነገር ጨምሮ ማንኛውንም ሥራ፣ ጥሩም ይሁን መጥፎ ወደ ፍርድ [እንደሚያመጣው]” ይገነዘባል። (መክ. 12:14) በእርግጥም ይሖዋ ፍርድ ሲያስተላልፍ፣ እኛ የማናውቃቸውን ጉዳዮችም ግምት ውስጥ ያስገባል። በመሆኑም ትሑት መሆናችን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት እንዳናጣ ጥበቃ ይሆንልናል። w17.04 24 አን. 8-9

ማክሰኞ፣ ጥር 29

እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው።—ምሳሌ 17:17

የዓለም ሁኔታዎች በመለዋወጣቸው የተነሳ በርካታ ወንድሞቻችን ለስደት ተዳርገዋል። እነዚህ ወንድሞች ከለውጡ ጋር መላመድ በጣም ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። በአንድ በኩል አዲስ ቋንቋና ባሕል መልመድ በሌላ በኩል ደግሞ ከጊዜ አጠቃቀም፣ ከቀረጥና ከሌሎች ነገሮች ክፍያ፣ ከትምህርት ቤት እንዲሁም ልጆችን ከመቅጣት ጋር በተያያዘ ምን እንደሚጠበቅባቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ማወቅ ብሎም ተግባራዊ ማድረግ ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል አስቡት! እንዲህ ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጠሟቸውን ወንድሞችና እህቶች በትዕግሥትና በአክብሮት ልትረዷቸው ትችላላችሁ? (ፊልጵ. 2:3, 4) በተጨማሪም አንዳንድ ጊዜ ባለሥልጣናት፣ እነዚህ ወንድሞች በሄዱበት አካባቢ ከሚገኘው ጉባኤ ጋር መገናኘት አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው ሊያደርጉ ይችላሉ። አንዳንድ መንግሥታዊ ድርጅቶች፣ ወንድሞቻችን ጉባኤ አዘውትረው እንዳይገኙ እንቅፋት የሚሆንባቸውን ሥራ እንዲሠሩ ሊያስገድዷቸው ሞክረዋል፤ ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች ካልሆኑ የሚያደርጉላቸውን ድጋፍ እንደሚያቋርጡባቸው አሊያም ጥገኝነት እንደሚከለክሏቸው ነግረዋቸዋል። ጥቂት ወንድሞች ስለፈሩና ምንም ምርጫ እንደሌላቸው ስለተሰማቸው እንዲህ ያለውን ሥራ ለመሥራት ተስማምተዋል። በመሆኑም ስደተኛ የሆኑ ወንድሞቻችንን፣ በተቻለ መጠን እንደደረሱ ለማግኘት ጥረት ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው። ስለ እነሱ እንደምናስብ እንዲያውቁ ማድረጋችን ጠቃሚ ነው። ርኅራኄ ማሳየታችንና የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ መስጠታችን እምነታቸውን ያጠናክረዋል።—ምሳሌ 12:25፤ w17.05 5 አን. 9-10

ረቡዕ፣ ጥር 30

የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል።—ማቴ. 24:12

ኢየሱስ ‘የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ’ አስመልክቶ ከሰጠው ምልክት ገጽታዎች አንዱ ‘የብዙዎች ፍቅር የሚቀዘቅዝ’ መሆኑ ነው። (ማቴ. 24:3) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን የአምላክ ሕዝብ እንደሆኑ ቢናገሩም ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ቀዝቅዞ ነበር። በሌላ በኩል ግን በወቅቱ የነበሩት አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ‘ስለ ክርስቶስ የሚናገረውን ምሥራች’ በመስበኩ ሥራ በትጋት ይካፈሉ እንዲሁም ለአምላክ፣ ለእምነት ባልንጀሮቻቸውና ለሌሎች ሰዎች ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳይ ነገር ያከናውኑ ነበር። (ሥራ 2:44-47፤ 5:42) ያም ቢሆን በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ የኢየሱስ ተከታዮች ፍቅራቸው ቀዝቅዞ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ በኋላ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኤፌሶን የነበረውን ጉባኤ “የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ይኸውም መጀመሪያ ላይ የነበረህን ፍቅር ትተሃል” ብሎት ነበር። (ራእይ 2:4) እነዚህ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ፍቅራቸውን እንዲተዉ ያደረጋቸው ምን ሊሆን ይችላል? ለዚህ አንዱ ምክንያት፣ በዙሪያቸው ያሉት በሥጋዊ ፍላጎታቸው ላይ የሚያተኩሩ ሰዎች ያሳደሩባቸው ተጽዕኖ ሊሆን ይችላል።—ኤፌ. 2:2, 3፤ w17.05 17 አን. 1-3

ሐሙስ፣ ጥር 31

ለይሖዋ የተሳልከውን ፈጽም።—ማቴ. 5:33

መስፍኑ ዮፍታሔ፣ ኃያል መሪ እና ደፋር ተዋጊ ነበር። የሕልቃና ሚስት የሆነችው ሐና ደግሞ ባሏን የምትንከባከብና ቤቷን በአግባቡ የምትይዝ ትሑት ሴት ነበረች። እነዚህ ሁለት ሰዎች የይሖዋ አምላኪ ከመሆናቸው ባሻገር ምን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ? ሁለቱም ለአምላክ የተሳሉ ሲሆን ስእለታቸውንም በታማኝነት ፈጽመዋል። ዮፍታሔም ሆነ ሐና በዛሬው ጊዜ ለይሖዋ ቃል ለሚገቡ ወይም ለሚሳሉ ሰዎች ግሩም ምሳሌ ትተዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስእለት የሚለው ቃል የተሠራበት ለአምላክ ቃል መግባትን ለማመልከት ነው። አንድ ሰው አንድን ተግባር ለማከናወን፣ ስጦታ ለመስጠት፣ በአንድ ዓይነት አገልግሎት ለመካፈል ወይም ደግሞ ከአንዳንድ ነገሮች ለመታቀብ ቃል ሊገባ ይችላል። ስእለት የሚሳለው ሰው ይህን የሚያደርገው በፈቃደኝነት ወይም በራሱ ፍላጎት ተነሳስቶ ነው። ያም ቢሆን አምላክ፣ ግለሰቡ ቃሉን እንዲፈጽም ይጠብቅበታል። ምክንያቱም ስእለት ቅዱስ ከመሆኑም ሌላ የመሐላን ያህል ክብደት አለው፤ መሐላ አንድ ግለሰብ አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ላለማድረግ የሚገባው ቃል ነው።—ዘፍ. 14:22, 23፤ ዕብ. 6:16, 17፤ w17.04 3 አን. 1-2

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ