የካቲት
ዓርብ፣ የካቲት 1
ኖኅም አምላክ ያዘዘውን ሁሉ በተባለው መሠረት አከናወነ። ልክ እንደዚሁ አደረገ።—ዘፍ. 6:22
ኖህ ከዚህ በፊት መርከብ ሠርቶ አያውቅም። በመሆኑም በይሖዋ በመታመን “ልክ እንደዚሁ” ማለትም ልክ ይሖዋ እንዳዘዘው ማድረግ ነበረበት። ውጤቱስ ምን ሆነ? ኖኅ ከዚህ በፊት ሠርቶ የማያውቀውን ነገር በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ችሏል። ይህ ደግሞ የራሱንና የቤተሰቡን ሕይወት ለማትረፍ አስችሎታል። በተጨማሪም ኖኅ የቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን ያለበትን ኃላፊነት በተሳካ መንገድ የተወጣ ሲሆን ለዚህም ቢሆን የረዳው በአምላክ ጥበብ መታመኑ ነው። በአምላክ መታመኑ ልጆቹን ጥሩ አድርጎ ለማስተማርና ለእነሱ ግሩም ምሳሌ ለመሆን ረድቶታል፤ ከጥፋት ውኃው በፊት በነበረው ክፉ ዓለም ውስጥ እንዲህ ማድረግ በጣም ተፈታታኝ ነበር። (ዘፍ. 6:5) እናንት ወላጆች፣ በአምላክ ፊት “ልክ እንደዚሁ” አድርጋችኋል ሊባልላችሁ የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ የሚላችሁን ስሙ። በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት ስለ ልጆች አስተዳደግ የሚሰጣችሁን መመሪያ ተቀበሉ። እርግጥ ነው፣ ወላጆች የቻሉትን ያህል ጥረት ቢያደርጉም አንዳንድ ልጆች ይሖዋን ሊተዉ ይችላሉ። የሆነው ሆኖ በልጆቻቸው ልብ ውስጥ እውነትን ለመቅረጽ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደረጉ ወላጆች ንጹሕ ሕሊና ይኖራቸዋል። በተጨማሪም ከእውነት መንገድ የራቀው ልጅ አንድ ቀን ወደ ይሖዋ እንደሚመለስ ተስፋ ማድረግ ይችላሉ። w18.03 30 አን. 10-11
ቅዳሜ፣ የካቲት 2
አንዳችሁ ለሌላው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳዩ።—1 ጴጥ. 4:9
እንግዶችን መቀበል ብትፈልግም ይህን ማድረግ ከአቅምህ በላይ እንደሆነ ተሰምቶህ ያውቃል? አንዳንዶች ዓይናፋር ስለሆኑ እንግዶቻቸውን በደንብ ማጫወት እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ የገንዘብ አቅማቸው ውስን ስለሆነ አንዳንድ የጉባኤያቸው አባላት እንደሚያደርጉት እንግዶቻቸውን ጥሩ አድርገው ማስተናገድ እንደማይችሉ ያስባሉ። ቁም ነገሩ ቤታችን ትልቅና በውድ ዕቃዎች የተሞላ መሆኑ አይደለም፤ ቤታችን ንጹሕና ያልተዝረከረከ ከሆነ እንግዶቻችን በግብዣው መደሰታቸው አይቀርም። በእርግጥም በፍቅር ተነሳስታችሁ እንግዶቻችሁን እስካስተናገዳችሁ ድረስ መጨነቅ አያስፈልጋችሁም። ለእንግዶች በግለሰብ ደረጃ ትኩረት መስጠት ምንጊዜም ጥሩ ውጤት እንዳለው አስታውስ። (ፊልጵ. 2:4) አብዛኞቹ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ስላጋጠሟቸው ነገሮች ማውራት ያስደስታቸዋል። ወንድሞቻችን ተሞክሯችንን ለመስማት አጋጣሚ የሚያገኙት አንድ ላይ ሰብሰብ ብለን በምንጫወትበት ጊዜ ብቻ ሊሆን ይችላል። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በጉባኤያችን ውስጥ ያሉ ወንድሞችን ቤቴ መጋበዜ፣ አመለካከታቸውን በተሻለ መንገድ ለመረዳት እንዲሁም ስለ እነሱ ይበልጥ ለማወቅ በተለይም ወደ እውነት እንዴት እንደመጡ ለመስማት አጋጣሚ ይሰጠኛል።” ለእንግዶቻችን ፍቅርና አሳቢነት የምናሳይ ከሆነ ሁላችንም በግብዣው እንደምንደሰት አያጠራጥርም። w18.03 17 አን. 15-17
እሁድ፣ የካቲት 3
ታዲያ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነስና ተጠመቅ።—ሥራ 22:16
ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ እንዲያደርጉ ሊረዷቸው ይፈልጋሉ። ልጆች ለመጠመቅ በሚጠይቁበት ጊዜ ያለበቂ ምክንያት እንዲቆዩ ማድረግ የልጆቹን መንፈሳዊነት ሊጎዳ ይችላል። (ያዕ. 4:17) ያም ሆኖ ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ከመጠመቃቸው በፊት፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን የሚያስከትለውን ኃላፊነት ለመሸከም ዝግጁ እንደሆኑ ማረጋገጥም ይፈልጋሉ። አንዳንድ የወረዳ የበላይ ተመልካቶች፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ወይም በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ከሚገኙ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ጋር በተያያዘ ያሳሰባቸው ነገር እንዳለ ሲናገሩ ይሰማል፤ እነዚህ ወጣቶች በእውነት ቤት ውስጥ ያደጉ ቢሆኑም ገና አልተጠመቁም። አብዛኞቹ፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሲሆን በአገልግሎትም ይካፈላሉ። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክር እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን ይቆጥራሉ። ይሁን እንጂ ሕይወታቸውን ለይሖዋ ከመወሰንና ከመጠመቅ ወደኋላ ይላሉ። እንዲህ የሚያደርጉት ለምን ሊሆን ይችላል? አንዳንድ ጊዜ፣ ሳይጠመቁ እንዲቆዩ የሚመክሯቸው ወላጆቻቸው ናቸው። w18.03 8 አን. 1-2
ሰኞ፣ የካቲት 4
ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ [ይኑራችሁ]።—ሮም 15:5
ክርስቶስን ለመምሰል፣ እሱ የሚያስብበትን መንገድ ማወቅና ማንነቱን በደንብ መረዳት ያስፈልገናል። ከዚያም የእሱን ፈለግ መከተል ይኖርብናል። ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ከአምላክ ጋር ላለው ዝምድና ነው። ስለዚህ ኢየሱስን መምሰላችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ያስችለናል። የኢየሱስን አስተሳሰብ ማዳበራችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው። ታዲያ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ክርስቶስ ተአምራት ሲፈጽም የማየት፣ ሲያስተምር የመስማት፣ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች የሚይዝበትን መንገድ የመመልከት እንዲሁም አምላክ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርግ የማስተዋል አጋጣሚ ነበራቸው። በመሆኑም “ላደረጋቸው ነገሮች ሁሉ እኛ ምሥክሮች ነን” በማለት ተናግረዋል። (ሥራ 10:39) እኛ ግን እንደ እነሱ ክርስቶስን የማየት አጋጣሚ የለንም። ይሁን እንጂ ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ የወንጌል ዘገባዎችን አስጽፎልናል፤ እነዚህ ዘገባዎች ኢየሱስን በአካል የምናውቀው ያህል ሆኖ እንዲሰማን ያደርጉናል። የማቴዎስን፣ የማርቆስን፣ የሉቃስንና የዮሐንስን መጻሕፍት ማንበባችን ብሎም በዘገባዎቹ ላይ ማሰላሰላችን የክርስቶስን አስተሳሰብ ለማወቅ ያስችለናል። ይህን ማድረጋችን “የእሱን ፈለግ በጥብቅ [ለመከተል]” እንዲሁም የክርስቶስን “አስተሳሰብ ለማንጸባረቅ” ይረዳናል።—1 ጴጥ. 2:21፤ 4:1፤ w18.02 22 አን. 15-16
ማክሰኞ፣ የካቲት 5
እምነት የሚገኘው ቃሉን ከመስማት ነው።—ሮም 10:17
ከሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ አንስቶ የእምነት ምሳሌ የሚሆኑ ወንዶችና ሴቶች ስለ አምላክ ማወቅ የቻሉት በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ነው፤ በዓይን የሚታዩትን የፍጥረት ሥራዎች በመመልከት፣ ፈሪሃ አምላክ ካላቸው ሰዎች ተሞክሮ በመማር እንዲሁም ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምቶ መኖር የሚያስገኛቸውን በረከቶች በገዛ ሕይወታቸው በመመልከት ነው። (ኢሳ. 48:18) ኖኅ የፍጥረት ሥራዎችን በመመልከት ስለ አምላክ መኖር ብቻ ሳይሆን ይሖዋ ስላሉት የማይታዩ ባሕርያትም ለምሳሌ ስለ “ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ” በግልጽ ማስተዋል ይችል ነበር። (ሮም 1:20) ይህም በአምላክ መኖር ከማመን ባለፈ በእሱ ላይ ጠንካራ እምነት ማዳበር እንዲችል ረድቶታል። ኖኅ ከዘመዶቹ ብዙ ነገር ተምሮ ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። ከእነዚህ መካከል የእምነት ሰው የነበረውና ለተወሰኑ ዓመታት ያህል ከአዳም ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ላይ የኖረው አባቱ ላሜህ ይገኝበታል። ከአያቱ ከማቱሳላ እንዲሁም ኖኅ 366 ዓመት እስኪሆነው ድረስ በሕይወት ከኖረው ከቅም አያቱ ከያሬድም ስለ ይሖዋ ተምሮ ሊሆን ይችላል። (ሉቃስ 3:36, 37) ኖኅ እነዚህን ነገሮች የሰማበት መንገድ ምንም ይሁን ምን፣ የተማረው ነገር ልቡን የነካው ከመሆኑም ሌላ አምላክን ለማገልገል አነሳስቶታል።—ዘፍ. 6:9፤ w18.02 9 አን. 4-5
ረቡዕ፣ የካቲት 6
ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ።—ኤፌ. 4:26
የእምነት ባልንጀራችን ወይም የቤተሰባችን አባል ተገቢ ያልሆነ ነገር ቢናገረን ወይም ቢያደርግብን ስሜታችን በጣም ሊጎዳ ይችላል። በዚህ ጊዜ ጉዳዩን ችላ ብለን ማለፍ ቢከብደንስ? ለዓመታት ቂም ይዘን እንቆያለን? ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ አለመግባባቶችን ሳንውል ሳናድር እንድንፈታ የሚሰጠውን ምክር እንከተላለን? ከወንድማችን ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ሳንፈታው በቆየን መጠን ሁኔታውን ማስተካከል ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነብን ይሄዳል። ከወንድምህ ጋር ሰላም ለመፍጠር ምን እርምጃ መውሰድ ትችላለህ? በቅድሚያ፣ ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት አቅርብ። ከወንድምህ ጋር በተረጋጋ መንፈስ ለመወያየት እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። ቅር ያሰኘህ ወንድም ከይሖዋ ወዳጆች አንዱ መሆኑን አትዘንጋ። (መዝ. 25:14) ይሖዋ ለወዳጆቹ ደግነት የሚያሳይ ሲሆን እኛም እንዲሁ እንድናደርግ ይጠብቅብናል። (ምሳሌ 15:23፤ ማቴ. 7:12፤ ቆላ. 4:6) ልታደርገው የሚገባው ሌላው ነገር ደግሞ ወንድምህን ምን ብለህ እንደምታነጋግረው አስቀድመህ ማሰብ ነው። ወንድምህ ስሜትህን የጎዳው ሆን ብሎ እንደሆነ አድርገህ አታስብ። አንተም ለተፈጠረው አለመግባባት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አስተዋጽኦ አድርገህ ሊሆን እንደሚችል አስታውስ። w18.01 10 አን. 15-16
ሐሙስ፣ የካቲት 7
እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።—ዮሐ. 13:34
በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች ፍቅር የጎደላቸው ቢሆኑም የይሖዋ አገልጋዮች ግን ለሌሎች ልባዊ ፍቅር ያሳያሉ። ከጥንትም ጀምሮ የአምላክ ሕዝቦች ይህን በማድረግ ይታወቃሉ። ኢየሱስ እንደተናገረው በሙሴ ሕግ ውስጥ፣ ባልንጀራን መውደድ አምላክን ከመውደድ ቀጥሎ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ትእዛዝ ነበር። (ማቴ. 22:38, 39) በተጨማሪም ኢየሱስ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች እርስ በርስ ባላቸው ፍቅር ተለይተው እንደሚታወቁ ተናግሯል። (ዮሐ. 13:35) ክርስቲያኖች ጠላቶቻቸውንም ጭምር እንዲወዱ ይጠበቅባቸዋል። (ማቴ. 5:43, 44) ኢየሱስ ለሌሎች ጥልቅ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። ከከተማ ወደ ከተማ እየሄደ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ይናገር ነበር። ዓይነ ስውሮችን፣ አንካሶችን፣ የሥጋ ደዌ የያዛቸውን እንዲሁም መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ፈውሷል። ሙታንንም አስነስቷል። (ሉቃስ 7:22) ኢየሱስ ለሰው ልጆች ሲል ሕይወቱን ጭምር ሰጥቷል። በእርግጥም ክርስቶስ ፍቅር በማሳየት ረገድ አባቱን ፍጹም በሆነ መንገድ መስሏል። በመላው ዓለም የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ለሌሎች ፍቅር ያሳያሉ። w18.01 29-30 አን. 11-12
ዓርብ፣ የካቲት 8
ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።—ፊልጵ. 4:13
የተጠመቅከው በልጅነትህ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ወደፊት ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሙህ አስቀድመህ ማወቅ የምትችለው ሁልጊዜ አይደለም። ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥምህ ታማኝ ለመሆን እንድትችል የሚረዳህ ነገር አለ፤ ይህም ለይሖዋ ቃል ስትገባ በየትኛውም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እሱን ለማገልገል እንደተሳልክ ምንጊዜም ማስታወስህ ነው። እንዲህ ሲባል ጓደኞችህ ወይም ወላጆችህ ይሖዋን ማገልገላቸውን ቢያቆሙ እንኳ አንተ እሱን ማገልገልህን እንደምትቀጥል ለአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ነግረኸዋል ማለት ነው። (መዝ. 27:10) ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ ይሖዋ ከውሳኔህ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር የሚያስችልህን ብርታት እንድታገኝ ይረዳሃል። (ፊልጵ. 4:11, 12) ይሖዋ፣ ወዳጁ እንድትሆን ይፈልጋል። ሆኖም ከእሱ ጋር የመሠረትከውን ወዳጅነት ጠብቆ ማቆየትና የራስህን መዳን ከፍጻሜ ማድረስ ጥረት ይጠይቃል። እንዲያውም ፊልጵስዩስ 2:12 “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግታችሁ ሥሩ” ይላል። በመሆኑም ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥምህ ከይሖዋ ጋር የመሠረትከውን ወዳጅነት ጠብቀህ የማቆየትንና ለእሱ ታማኝ የመሆንን ጉዳይ ልታስብበት ይገባል። በዚህ ረገድ ከልክ በላይ በራስህ መተማመን አይኖርብህም። ለረጅም ዓመታት አምላክን ያገለገሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችም እንኳ ከእውነት ቤት ወጥተዋል። w17.12 24 አን. 4, 6-7
ቅዳሜ፣ የካቲት 9
በፈቃደኝነት ተነሳስቼ ይህን ሁሉ ነገር ሰጥቻለሁ።—1 ዜና 29:17
ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እየተካሄደ ያለውን ታላቅ ሥራ የመደገፍ መብት በመስጠት አክብሮናል። መንግሥቱን ለመደገፍ በልግስና የምንሰጥ ከሆነ እሱ ደግሞ በረከቱን እንደሚያፈስልን ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ሚል. 3:10) ይሖዋ በልግስና የሚሰጥ ሰው እንደሚበለጽግ ተናግሯል። (ምሳሌ 11:24, 25) በተጨማሪም በልግስና መስጠታችን ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል፤ ምክንያቱም “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።” (ሥራ 20:35) ልጆቻችንም ሆኑ አዲሶች ለጋስ እንዲሆኑ በማበረታታት እንዲሁም እኛ ራሳችን በዚህ ረገድ ምሳሌ በመሆን ልግስና የሚያስገኘውን በረከት እንዲያጣጥሙ ልንረዳቸው እንችላለን። ሁሉንም ነገር ያገኘነው ከይሖዋ ነው። መልሰን ለእሱ መስጠታችን እንደምንወደውና ላደረገልን ነገር ሁሉ አድናቆት እንዳለን ያሳያል። እስራኤላውያን ለቤተ መቅደሱ ግንባታ “በፈቃደኝነት መባ በመስጠታቸው እጅግ [ተደስተው ነበር]።” (1 ዜና 29:9) እኛም በተመሳሳይ ከይሖዋ እጅ ያገኘነውን መልሰን ለእሱ በመስጠት ምንጊዜም ደስታና እርካታ ማግኘት እንችላለን። w18.01 21 አን. 18-19
እሁድ፣ የካቲት 10
እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፦ ክርስቶስ በኩራት ነው፤ በመቀጠል ደግሞ ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ የእሱ የሆኑት ሕያዋን ይሆናሉ።—1 ቆሮ. 15:23
ሰማያዊው ትንሣኤ የሚከናወነው፣ ክርስቶስ በሥልጣኑ ላይ ‘የሚገኝበት ጊዜ’ ከጀመረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነው። በታላቁ መከራ ወቅት በምድር ላይ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘በደመና ይነጠቃሉ።’ (1 ተሰ. 4:13-17፤ ማቴ. 24:31) እነዚህ ቅቡዓን “የመጨረሻው መለከት በሚነፋበት ወቅት ድንገት፣ በቅጽበተ ዓይን [ይለወጣሉ]።” (1 ቆሮ. 15:51, 52) በአሁኑ ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ ታማኝ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ አልተቀቡም፤ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመግዛት ተስፋም የላቸውም። ከዚህ ይልቅ ይህ ክፉ ሥርዓት ‘በይሖዋ ቀን’ የሚደመደምበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። ይህ ቀን መቼ እንደሆነ ማናችንም ብንሆን ማወቅ አንችልም፤ ይሁንና ቀኑ በጣም እንደቀረበ ማስረጃዎቹ ያሳያሉ። (1 ተሰ. 5:1-3) ይህ ሥርዓት ከጠፋ በኋላ፣ ሌላ ዓይነት ትንሣኤ ይከናወናል፤ የሞቱ ሰዎች፣ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለመኖር ትንሣኤ ያገኛሉ። ከሞት የተነሱት ሰዎች፣ ወደ ፍጽምና ደረጃ የመድረስና የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ይኖራቸዋል። w17.12 11 አን. 15፤ 12 አን. 18-19
ሰኞ፣ የካቲት 11
ቅናትና ጠበኝነት ባለበት ሁሉ ብጥብጥና መጥፎ ነገሮችም ይኖራሉ።—ያዕ. 3:16
ልባችን በፍቅርና በደግነት እንዲሞላ ካደረግን በሌሎች ላይ ቶሎ ቅናት አያድርብንም። የአምላክ ቃል “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። ፍቅር አይቀናም” ይላል። (1 ቆሮ. 13:4) ቅናት በልባችን ውስጥ ሥር እንዳይሰድ ለመከላከል የአምላክ ዓይነት አመለካከት ማዳበራችን ይጠቅመናል፤ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር የአንድ አካል ክፍሎች እንደሆንን ይኸውም ሁላችንም የክርስቲያን ጉባኤ አባላት እንደሆንን ማስታወስ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን “አንድ የአካል ክፍል ክብር ቢያገኝ ሌሎቹ የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረውት ይደሰታሉ” ከሚለው በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ ራሳችንን በሌሎች ቦታ እንድናስቀምጥ ይረዳናል። (1 ቆሮ. 12:16-18, 26) እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካለን ሌሎች ባገኙት በረከት ከመቅናት ይልቅ አብረናቸው እንደሰታለን። የንጉሥ ሳኦል ልጅ የሆነውን የዮናታንን ምሳሌ እንመልከት። ዳዊት ንጉሥ ሆኖ በመቀባቱ ዮናታን ቅናት አላደረበትም። እንዲያውም ዳዊትን አበረታቶታል። (1 ሳሙ. 23:16-18) እኛስ እንደ ዮናታን ደግና አፍቃሪ መሆን እንችላለን? w17.11 27 አን. 10-11
ማክሰኞ፣ የካቲት 12
ዓይኑ እንዳየ አይፈርድም ወይም ጆሮው በሰማው ነገር ላይ ብቻ ተመሥርቶ አይወቅስም። ለችግረኞች በትክክል ይፈርዳል።—ኢሳ. 11:3, 4
ይሖዋ ሕጉ፣ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተካትቶ እንዲቆይልን አድርጓል። ይሖዋ በሕጉ ውስጥ ላሉት ዝርዝር ነገሮች ከሚገባው በላይ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ “ይበልጥ አስፈላጊ [የሆኑትን] ነገሮች” ይኸውም ትእዛዛቱ የተመሠረቱባቸውን ላቅ ያሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድናስተውልና ተግባራዊ እንድናደርግ ይፈልጋል። (ማቴ. 23:23) የሙሴ ሕግ “የእውቀትና የእውነት መሠረታዊ [ገጽታዎችን]” ይዟል፤ ሕጉ ስለ ይሖዋና ስለ ጽድቅ መሥፈርቶቹ ያስተምረናል። (ሮም 2:20) ለምሳሌ የመማጸኛ ከተሞች ዝግጅት፣ ‘በእውነተኛ ፍትሕ ላይ ተመሥርቶ መፍረድ’ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ሽማግሌዎችን ያስተምራቸዋል፤ በተጨማሪም ይህ ዝግጅት ‘አንዳችን ለሌላው ታማኝ ፍቅርና ምሕረት’ ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ሁላችንንም ያስተምረናል። (ዘካ. 7:9) እርግጥ ክርስቲያኖች በሕጉ ሥር አይደለንም። ሆኖም ይሖዋ አይለወጥም፤ አሁንም ቢሆን ለፍትሕና ለምሕረት ትልቅ ቦታ ይሰጣል። በራሱ መልክ የፈጠረንንና የእሱን ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ የሰጠንን ብሎም መሸሸጊያ የሚሆነንን አምላክ ስለምናመልክ ምንኛ ታድለናል! w17.11 13-14 አን. 2-3፤ 17 አን. 18-19
ረቡዕ፣ የካቲት 13
ጥበብን የሚያገኝ፣ ጥልቅ ግንዛቤንም የራሱ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው።—ምሳሌ 3:13
ንግግር የሚያቀርቡ ወንድሞች ምንጊዜም ቢሆን የሚያስተምሩት ትምህርት በዋነኝነት ያተኮረው በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ እንዲሆን ጥረት ማድረግ አለባቸው። (ዮሐ. 7:16) ይህ ምን ማድረግን ይጠይቃል? በመጀመሪያ ደረጃ፣ የአድማጮች ትኩረት በምትጠቀምባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ እንዲያርፍ ማድረግ ይኖርብሃል፤ የአድማጮች ትኩረት በሌላ በማንኛውም ነገር ላይ ማለትም በምትጠቀምባቸው ተሞክሮዎች፣ ምሳሌዎች ሌላው ቀርቶ ንግግሩን በምታቀርብበት መንገድ ላይ እንዳያርፍ ጥንቃቄ አድርግ። በተጨማሪም አንድ ሰው ብዙ ጥቅሶችን ስላነበበ ብቻ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አስተምሯል ሊባል እንደማይችል አስታውስ። እንዲያውም ብዙ ጥቅሶችን ማንበብ አድማጮች አንዱንም ሳይጨብጡ እንዲሄዱ ሊያደርግ ይችላል። በመሆኑም ቁልፍ ጥቅሶችን በጥንቃቄ ምረጥ፤ ከዚያም ጥቅሶቹን አንብብ፣ ጥሩ አድርገህ አብራራ፣ ምሳሌዎችን ተጠቀም እንዲሁም ጥቅሶቹ ከትምህርቱ ጋር የሚያያዙት እንዴት እንደሆነ ግለጽ። (ነህ. 8:8) በአስተዋጽኦው ላይ ያሉት ነጥቦች ከጥቅሶቹ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ለማስተዋል ሞክር። ከሁሉም በላይ ግን በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ውድ እውነት ለማስተላለፍ እንዲረዳህ ይሖዋን በጸሎት ጠይቅ።—ዕዝራ 7:10፤ w17.09 26 አን. 11-12
ሐሙስ፣ የካቲት 14
ወደ እኔ ተመለሱ . . . እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ።—ዘካ. 1:3
በ537 ዓ.ዓ. የይሖዋ ሕዝቦች በጣም ተደስተው ነበር። ለ70 ዓመታት ያህል በግዞት ከቆዩ በኋላ ከባቢሎን ነፃ የወጡት በዚህ ዓመት ነው። በመሆኑም በኢየሩሳሌም እውነተኛውን አምልኮ መልሰው ለማቋቋም በከፍተኛ ቅንዓት ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን በ536 ዓ.ዓ. የቤተ መቅደሱ መሠረት ተጣለ። ይሁን እንጂ መሠረቱ ከተጣለ 16 ዓመታት ካለፉ በኋላም እንኳ የይሖዋ ቤተ መቅደስ ግንባታ ካለበት ንቅንቅ አላለም። በእርግጥም የአምላክ ሕዝቦች በግል ጉዳዮቻቸው መጠመዳቸውን ትተው ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ማሳሰቢያ ያስፈልጋቸው ነበር። አምላክ ሕዝቡ መጀመሪያውኑም ከባቢሎን ነፃ የወጣበትን ምክንያት ለማስታወስ ሲል በ520 ዓ.ዓ. ዘካርያስን ነቢይ አድርጎ ላከው። “ይሖዋ አስታውሷል” የሚል ትርጉም ያለው ዘካርያስ የሚለው ስም በራሱ ሕዝቡ አንድ አስፈላጊ እውነት እንዲገነዘብ ሳያደርግ አልቀረም። እስራኤላውያን ይሖዋ እነሱን ለማዳን የወሰደውን እርምጃ ቢዘነጉም ይሖዋ ግን ሕዝቡን አልረሳም። (ዘካ. 1:3, 4) በመሆኑም በፍቅር ተነሳስቶ፣ ንጹሑን አምልኮ መልሰው እንዲያቋቁሙ እንደሚረዳቸው አረጋገጠላቸው፤ በሌላ በኩል ግን በተከፋፈለ ልብ የሚቀርብ አምልኮን ጨርሶ እንደማይታገስ በመግለጽ ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው። w17.10 21-22 አን. 2-3
ዓርብ፣ የካቲት 15
አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ።—ኤፌ. 4:32
የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች ርኅራኄ ማሳየት፣ ጤናችን እንዲሻሻልና ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን እንደሚረዳ ይናገራሉ። የሌሎችን ችግር ለማቅለል ጥረት ማድረጋችን ይበልጥ ደስተኞች እንድንሆንና አዎንታዊ አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል፤ በተጨማሪም የሚሰማንን የብቸኝነት ስሜት መቀነስ እንድንችል እንዲሁም በአሉታዊ አመለካከት እንዳንዋጥ ያደርጋል። በእርግጥም ርኅራኄ ማሳየታችን ራሳችንን ይጠቅመናል። በፍቅር ተነሳስተው ሌሎችን ለመርዳት የሚጣጣሩ ክርስቲያኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ነገር እያደረጉ እንዳለ ስለሚገነዘቡ ጥሩ ሕሊና ይኖራቸዋል። ርኅራኄ ማሳየታችን ጥሩ ወዳጅ፣ የተሻለ የትዳር ጓደኛ እንዲሁም ይበልጥ አፍቃሪ ወላጅ ለመሆን ይረዳናል። ሩኅሩኅ የሆኑ ሰዎች እርዳታና ድጋፍ ሲያስፈልጋቸው በአብዛኛው ሌሎች ሰዎች ይደርሱላቸዋል። (ማቴ. 5:7፤ ሉቃስ 6:38) ርኅራኄ እንድናሳይ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ራሳችንን እንደሚጠቅመን መገንዘባችን መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ የፍቅርና የርኅራኄ ምንጭ የሆነውን ይሖዋ አምላክን ለመምሰልና እሱን ለማስከበር ያለን ፍላጎት መሆን ይኖርበታል።—ምሳሌ 14:31፤ w17.09 12 አን. 16-17
ቅዳሜ፣ የካቲት 16
በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ይገዛል፤ ደግሞም በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ካህን ሆኖ ያገለግላል።—ዘካ. 6:13
ኢየሱስ ንጉሥና ሊቀ ካህናት በመሆን ከሚያከናውነው ሥራ በተጨማሪ “የይሖዋን ቤተ መቅደስ [የመገንባት]” ተልእኮ ተሰጥቶታል። በዘመናችን ኢየሱስ የሚያከናውነው የግንባታ ሥራ እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎችን ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ነፃ ማውጣትንና የክርስቲያን ጉባኤን መልሶ ማቋቋምን ይጨምራል፤ ይህ ሥራ የተከናወነው በ1919 ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ በታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ ላይ የሚከናወነውን ሥራ በበላይነት የሚከታተል “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሾሟል። (ማቴ. 24:45) ከዚህም ሌላ የአምላክ ሕዝቦች ንጹሕ አምልኮ ማቅረብ እንዲችሉ ለመርዳት ሲል እነሱን የማጥራት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። (ሚል. 3:1-3) በሺው ዓመት ግዛት ወቅት ኢየሱስና ከእሱ ጋር አብረው የሚገዙት 144,000 ነገሥታትና ካህናት ታማኝ የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና ደረጃ እንዲደርሱ ይረዷቸዋል። ይህ ከሆነ በኋላ ከክፋት በጸዳችው ምድር ላይ የሚቀሩት፣ እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች ብቻ ይሆናሉ። በመጨረሻም እውነተኛውን አምልኮ መልሶ የማቋቋሙ ሥራ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል! w17.10 29 አን. 15-16
እሁድ፣ የካቲት 17
የተቀባው ሊቀ ካህናት እስኪሞት ድረስ [በመማጸኛ ከተማው] ይቆይ።—ዘኁ. 35:25
ሳያስበው የሰው ሕይወት ያጠፋ ግለሰብ ምሕረት ማግኘት ከፈለገ መውሰድ ያለበት እርምጃ አለ። በአቅራቢያው ወዳለ የመማጸኛ ከተማ መሸሽ ነበረበት። (ኢያሱ 20:4) ይህ ግለሰብ ዘና እንደማይል የታወቀ ነው፤ ሕይወቱን ማዳን ከፈለገ በተቻለ ፍጥነት ወደ መማጸኛ ከተማ መሄድና እዚያው መቆየት አለበት! እርግጥ ይህን ማድረግ መሥዋዕት ያስከፍለዋል። ሥራውንና የሞቀ ቤቱን ትቶ የሚሄድ ከመሆኑም ሌላ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ነፃነቱን ያጣል፤ ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ ወደ ቀድሞ ሕይወቱ መመለስ አይችልም። ይሁንና እንዲህ ዓይነት መሥዋዕት መክፈሉ የሚያስቆጨው አይሆንም። በዛሬው ጊዜም ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች የአምላክን ምሕረት ማግኘት ከፈለጉ እርምጃ መውሰድ አለባቸው። እንዲህ ያሉት ግለሰቦች የሚፈጽሙትን ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ማቆም ይኖርባቸዋል፤ ይህም ሲባል ከከባድ ኃጢአት ብቻ ሳይሆን እንደዚህ ያለ ኃጢአት ወደ መፈጸም ከሚመሩ ቀለል ተደርገው የሚታዩ ኃጢአቶችም መራቅ አለባቸው ማለት ነው። ከኃጢአት ለመራቅ የምንችለውን ሁሉ ማድረጋችን፣ ያለንበት ሁኔታ በጣም እንደሚያሳስበን የሚጠቁም ነው፤ በተጨማሪም ‘ምንም ዓይነት ኃጢአት ብንፈጽም ይሖዋ ምሕረት ያደርግልናል’ የሚል አመለካከት እንደሌለን ያሳያል።—2 ቆሮ. 7:10, 11፤ w17.11 10-11 አን. 10-11
ሰኞ፣ የካቲት 18
ሳታጉረመርሙ አንዳችሁ ለሌላው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳዩ።—1 ጴጥ. 4:9
ይሖዋ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ልግስና እንድናሳይ አዞናል። (1 ዮሐ. 3:17) ይሁንና እንዲህ የምናደርገው ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜትና በትክክለኛ ውስጣዊ ግፊት ተነሳስተን መሆን ይኖርበታል። ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘በዋነኝነት በእንግድነት የምቀበለው የቅርብ ጓደኞቼን፣ የኃላፊነት ቦታ ያላቸውን ወይም በሆነ መንገድ ውለታ ሊመልሱልኝ ይችላሉ ብዬ የማስባቸውን ሰዎች ነው? ወይስ በደንብ ለማላውቃቸው አሊያም ውለታ ሊመልሱልኝ ለማይችሉ ወንድሞችና እህቶች ልግስና ለማሳየት ጥረት አደርጋለሁ?’ (ሉቃስ 14:12-14) በሌላ በኩል ደግሞ የእምነት ባልንጀራችን ጥበብ የጎደለው እርምጃ በመውሰዱ ምክንያት ችግር ውስጥ ወደቀ ወይም ላሳየነው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አመስጋኝ ሳይሆን ቀረ እንበል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በትክክለኛ ውስጣዊ ግፊት ተነሳስቶ መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ ማጣጣም እንችላለን።—ሥራ 20:35፤ w17.10 9 አን. 12
ማክሰኞ፣ የካቲት 19
እንዲህ ያለውን እጅግ መጥፎ ድርጊት በመፈጸም በአምላክ ላይ እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?—ዘፍ. 39:9
የጶጢፋር ሚስት ‘የዳበረ ሰውነትና ያማረ መልክ’ በነበረው በዮሴፍ ላይ ዓይኗን ጣለችበት፤ እንዲሁም ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽም ታባብለው ጀመር። ዮሴፍ ግን ባቀረበችለት ተደጋጋሚ ማባበያ አልተሸነፈም። አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ጊዜ ደግሞ አካባቢውን ጥሎ ሸሽቷል። ዮሴፍ ከተወው ምሳሌ ምን እንማራለን? የአምላክን ሕጎች እንድንጥስ ሊያደርጉን ከሚችሉ ፈተናዎች ለማምለጥ መሸሽ ሊያስፈልገን ይችላል። (ምሳሌ 1:10) አሁን የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ከዚህ በፊት ከልክ በላይ የመብላትና የመጠጣት፣ የማጨስ፣ ዕፅ የመውሰድ፣ የፆታ ብልግና የመፈጸምና የመሳሰሉት ችግሮች ነበሩባቸው። ከተጠመቁ በኋላም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ወደ ቀድሞ ልማዶቻቸው ለመመለስ ሊፈተኑ ይችላሉ። የኃጢአት ዝንባሌዎችን አለመቆጣጠርህ በመንፈሳዊነትህ ላይ ምን አደጋ እንደሚያስከትል ጊዜ ወስደህ ማሰላሰልህ የይሖዋን ሕግ ለመጣስ በምትፈተንበት ወቅት አቋምህን ለማጠናከር ይረዳሃል። ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙህ እንደሚችሉና እነዚህን ፈታኝ ሁኔታዎች መከላከል የምትችለው እንዴት እንደሆነ አስቀድመህ ለማሰብ ሞክር። (መዝ. 26:4, 5፤ ምሳሌ 22:3) እንዲህ ያሉ ፈተናዎች ካጋጠሙህ ደግሞ ይሖዋ ፈተናዎቹን ለመወጣት የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጥህና ራስህን መቆጣጠር እንድትችል እንዲረዳህ ጸልይ። w17.09 4-5 አን. 8-9
ረቡዕ፣ የካቲት 20
በዓመፅ ሀብት ለራሳችሁ ወዳጆች አፍሩ፤ እነሱም የዓመፅ ሀብት ሲያልቅ በዘላለማዊ መኖሪያ ይቀበሏችኋል።—ሉቃስ 16:9
ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መመሥረት የምንችልበት አንዱ መንገድ በንግዱ ዓለም ውስጥ ከሚገባው በላይ ላለመጠላለፍ በመጠንቀቅ እንዲሁም “እውነተኛውን ሀብት” ለመፈለግ በመጣር ነው። በጥንት ዘመን የኖረውና የእምነት ሰው የነበረው አብርሃም፣ የበለጸገችውን ዑርን ለቆ በመውጣት በድንኳን ውስጥ መኖር የጀመረው የይሖዋ ወዳጅ ለመሆን ስለፈለገ ነው። (ዕብ. 11:8-10) አብርሃም እውነተኛ ብልጽግና የሚገኘው ከይሖዋ እንደሆነ ይተማመን ስለነበር ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት አልጣረም፤ እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ በይሖዋ ላይ እምነት እንደሌለው የሚያሳይ ይሆን ነበር። (ዘፍ. 14:22, 23) ኢየሱስ ሌሎችም እንዲህ ያለ እምነት እንዲያዳብሩ አበረታቷል፤ ሀብታም ለሆነ አንድ ወጣት እንዲህ ብሎታል፦ “ፍጹም መሆን ከፈለግክ ሂድና ንብረትህን ሸጠህ ገንዘቡን ለድሆች ስጥ፤ በሰማይም ውድ ሀብት ታገኛለህ፤ ደግሞም መጥተህ ተከታዬ ሁን።” (ማቴ. 19:21) ይህ ወጣት እንደ አብርሃም ያለ እምነት አልነበረውም፤ ሌሎች ግን በአምላክ ሙሉ በሙሉ እንደሚተማመኑ አሳይተዋል። w17.07 10 አን. 12
ሐሙስ፣ የካቲት 21
[አብርሃም] ገና ልጅ ሳይኖረው ለእሱም ሆነ ከእሱ በኋላ ለዘሮቹ ምድሪቱን ርስት አድርጎ እንደሚሰጣቸው [ይሖዋ] ቃል ገባለት።—ሥራ 7:5
የአብርሃም ዘሮች ለአብርሃም ቃል የተገባለትን ምድር የሚወርስ ብሔር ሆነው የተደራጁት አብርሃም ኤፍራጥስን ከተሻገረ ከ430 ዓመታት በኋላ ነበር። (ዘፀ. 12:40-42፤ ገላ. 3:17) አብርሃም፣ ይሖዋ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እርግጠኛ ስለነበር እሱን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ሆኗል። (ዕብ. 11:8-12) የተገባለትን ቃል ሙሉ ፍጻሜ በሕይወት ዘመኑ የማየት አጋጣሚ ባያገኝም ይሖዋን በደስታ ጠብቋል። አብርሃም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ትንሣኤ ሲያገኝ ምን ያህል እንደሚደሰት እስቲ አስቡት። የእሱና የዘሮቹ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ያህል ሰፊ ሽፋን እንደተሰጠው ሲያውቅ እንደሚገረም ምንም ጥርጥር የለውም። ተስፋ ከተሰጠበት ዘር ጋር በተያያዘ ይሖዋ ያለው ዓላማ እንዲፈጸም በማድረግ ረገድ ስለተጫወተው ወሳኝ ሚና ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያውቅ በጣም እንደሚደሰት መገመት እንችላለን! ለረጅም ጊዜ በመጠበቁ ፈጽሞ እንደማይቆጭ የተረጋገጠ ነው። w17.08 6 አን. 10-11
ዓርብ፣ የካቲት 22
በምድር ያሉትን የአካል ክፍሎቻችሁን ግደሉ፤ እነሱም . . . ርኩሰት፣ ልቅ የሆነ የፍትወት ስሜት . . . ናቸው።—ቆላ. 3:5
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ርኩሰት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ከፆታ ብልግና በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ልማዶችን የሚያካትት ሰፊ ትርጉም ያለው ቃል ነው። እንደማጨስና የብልግና ቀልዶችን እንደመናገር ያሉ ጎጂ ልማዶችን ያካትታል። (2 ቆሮ. 7:1፤ ኤፌ. 5:3, 4) እንዲሁም የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ መጻሕፍትን እንደማንበብ ወይም የብልግና ምስሎችን እንደመመልከት ያሉ አንድ ግለሰብ ከሰው እይታ ውጭ ሆኖ የሚያደርጋቸውን ርኩስ ነገሮች ይጨምራል። እነዚህ ነገሮች ርኩስ ልማድ የሆነውን ማስተርቤሽንን ወደመፈጸም ሊያመሩ ይችላሉ። የብልግና ምስሎችን የመመልከት ልማድ ያላቸው ሰዎች በውስጣቸው “ልቅ የሆነ የፍትወት ስሜት” ይቀሰቀሳል፤ ይህም የፆታ ግንኙነት የመፈጸም ሱስ እንዲጠናወታቸው ያደርጋል። በውስጣቸው የብልግና ምስሎችን የመመልከት ኃይለኛ ግፊት ያላቸው ሰዎች፣ የአልኮል መጠጥና የዕፅ ሱስ ካለባቸው ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ምልክት እንደሚታይባቸው በምርምር መረዳት ተችሏል። በእርግጥም የብልግና ምስሎችን መመልከት ብዙ መዘዞች የሚያስከትል መሆኑ አያስገርምም፤ የብልግና ምስሎችን የመመልከት ልማድ ከፍተኛ ለሆነ የኃፍረት ስሜት ይዳርጋል፣ በሥራ ቦታ ውጤታማነትን ይቀንሳል፣ በቤተሰብ ሕይወት የሚገኝ ደስታን ያሳጣል እንዲሁም ለትዳር መፍረስና ራስን ለማጥፋት ምክንያት ሊሆን ይችላል። w17.08 19 አን. 8-9
ቅዳሜ፣ የካቲት 23
እሱ የከተማሽን በሮች መወርወሪያዎች አጠናክሯል፤ በውስጥሽ ያሉትን ወንዶች ልጆች ይባርካል። በክልልሽ ውስጥ ሰላም ያሰፍናል።—መዝ. 147:13, 14
መዝሙራዊው፣ እስራኤላውያን ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሱበት ጊዜ ይሖዋ እንዴት እንደረዳቸው በማሰብ ከላይ ያለውን መዝሙር ዘምሯል። መዝሙራዊው፣ አምላክ ለሕዝቡ ጥበቃ ለማድረግ ሲል የከተማዋን በሮች መወርወሪያዎች እንደሚያጠናክር ማወቁ ምንኛ አበረታቶት ይሆን! አንተም በጣም እንድትጨነቅ የሚያደርጉ ችግሮች በሕይወትህ ውስጥ አጋጥመውህ ይሆናል። ይሖዋ ችግሮቹን ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብ ይሰጥሃል። መዝሙራዊው ስለ አምላክ ሲናገር “ትእዛዙን ወደ ምድር ይልካል፤ ቃሉም በፍጥነት ይሮጣል” ብሏል። ከዚያም መዝሙራዊው፣ ይሖዋ ‘በረዶን እንደሚልክ፣ አመዳዩን እንደሚበትን እንዲሁም የበረዶውን ድንጋይ እንደሚወረውር’ ከገለጸ በኋላ “እሱ የሚልከውን ቅዝቃዜ ማን ሊቋቋም ይችላል?” ሲል ጠይቋል። አክሎም ይሖዋ “ቃሉን ይልካል፤ እነሱም ይቀልጣሉ” ብሏል። (መዝ. 147:15-18) በጥበቡና በኃይሉ ተወዳዳሪ የሌለው እንዲሁም በረዶውንና አመዳዩን የሚቆጣጠረው አምላካችን፣ የሚያጋጥምህን ማንኛውንም እንቅፋት እንድትወጣ ሊረዳህ ይችላል። w17.07 20 አን. 14-15
እሁድ፣ የካቲት 24
ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ . . . ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።—ራእይ 4:11
ይሖዋ ሉዓላዊ ገዢ የመሆን መብት አለው። ከሁሉ የተሻለው አገዛዝ የእሱ አገዛዝ ነው። በመሆኑም የእሱን ሉዓላዊነት በሙሉ ልባችን መደገፍ ይኖርብናል። ለምን? ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው ይሖዋ ነው። ስለዚህ የሰው ልጆችንም ሆነ መንፈሳዊ ፍጡራንን የመግዛት ሙሉ መብት አለው። ሰይጣን የፈጠረው ምንም ነገር የለም። በመሆኑም ጽንፈ ዓለምን የመግዛት መብት ሊኖረው አይችልም። እሱም ሆነ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በይሖዋ ላይ ማመፃቸው ትዕቢተኞች እንደሆኑ ያሳያል። (ኤር. 10:23) የሰው ልጆች ነፃ ምርጫ ያላቸው ፍጥረታት ናቸው ሲባል በአምላክ አገዛዝ ላይ የማመፅ መብት አላቸው ማለት ነው? አይደለም። እርግጥ ነው፣ ሰዎች የመምረጥ ነፃነት ያላቸው መሆኑ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ብዙ ምርጫዎች ለማድረግ ያስችላቸዋል። ሆኖም ፈጣሪያቸውና ሕይወት ሰጪያቸው በሆነው አምላክ ላይ የማመፅ ነፃነት አይሰጣቸውም። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በይሖዋ ላይ ማመፅ የመምረጥ ነፃነትን አላግባብ መጠቀም ነው። ሰዎች እንደመሆናችን መጠን የይሖዋ አመራር ያስፈልገናል። w17.06 27-28 አን. 2-4
ሰኞ፣ የካቲት 25
ሩጫዬን እስካጠናቀቅኩ እንዲሁም . . . የተቀበልኩትን አገልግሎት እስከፈጸምኩ ድረስ ሕይወቴ ምንም አያሳሳኝም።—ሥራ 20:24
አገልግሎታችንን እንደ ውድ ሀብት አድርገን የምንመለከት ከሆነ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ስደት ቢደርስብንም እንኳ መስበካችንን እንቀጥላለን። (ሥራ 14:19-22) በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ወንድሞቻችን ከባድ ስደት ደርሶባቸዋል። ሆኖም ልክ እንደ ጳውሎስ በጽናት መስበካቸውን ቀጥለዋል። ወንድሞች የመስበክ መብታችንን ለማስጠበቅ ሲሉ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት ቀርበው ተሟግተዋል። ወንድም ናታን ኖር በ1943 በዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስለተገኘ ድል ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እነዚህን ድሎች ያገኘነው በእናንተ ጥረት ነው። . . . ይህ ብያኔ የተላለፈው የጌታ ሕዝቦች ጸንተው በመቆም ድል ስለነሱ ነው።” በእርግጥም ለአገልግሎቱ ያለን ፍቅር ስደትን እንድንቋቋም ያስችለናል። አገልግሎታችንን ከይሖዋ እንደተቀበልነው ውድ ሀብት አድርገን የምንመለከት ከሆነ “ሰዓት በመቁጠር” ብቻ አንረካም። ከዚህ ይልቅ ‘ምሥራቹን በተሟላ ሁኔታ ለመመሥከር’ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን።—2 ጢሞ. 4:5፤ w17.06 11-12 አን. 11-12
ማክሰኞ፣ የካቲት 26
አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።—ማቴ. 22:37
ለአምላክ ጥልቅ ፍቅር ማዳበራችን የይሖዋን ትእዛዛት እንድንፈጽም፣ እንድንጸና እንዲሁም ክፉ የሆነውን ነገር እንድንጠላ ያነሳሳናል። (መዝ. 97:10) ይሁን እንጂ ሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም ለአምላክ ያለን ፍቅር እንዲቀዘቅዝ ለማድረግ ይጥራሉ። ዓለም ስለ ፍቅር ያለው አመለካከት የተዛባ ነው። ሰዎች ከፈጣሪ ይልቅ “ራሳቸውን የሚወዱ” ሆነዋል። (2 ጢሞ. 3:2) ሰይጣን በሚመራው በዚህ ዓለም ውስጥ “የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና ኑሮዬ ይታይልኝ [የሚለው መንፈስ]” በስፋት ይታያል። (1 ዮሐ. 2:16) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የእምነት ባልንጀሮቹ ሥጋዊ ምኞቶችን ለማርካት ከመጣር መቆጠብ እንዳለባቸው ሲያሳስብ እንዲህ ብሏል፦ “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሞት ያስከትላልና፤ . . . በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር የአምላክ ጠላት ያደርጋል።” (ሮም 8:6, 7) በእርግጥም ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ ወይም የፆታ ፍላጎታቸውን በማርካት ላይ ያተኮሩ ሰዎች ለሐዘንና ለብዙ ሥቃይ ተዳርገዋል።—1 ቆሮ. 6:18፤ 1 ጢሞ. 6:9, 10፤ w17.05 18 አን. 5-6
ረቡዕ፣ የካቲት 27
መሥራት የማይፈልግ ሁሉ አይብላ።—2 ተሰ. 3:10
ስደተኛ የሆኑ ወንድሞች ሌሎች አንድ ነገር ሊያደርጉላቸው እንደሚገባ ከመጠበቅ ይልቅ ለተደረገላቸው እርዳታ አመስጋኝ ሊሆኑ ይገባል፤ ይህም በእንግድነት የተቀበሏቸው ወንድሞች በመስጠታቸው እንዲደሰቱ ያደርጋል። እርግጥ ነው፣ ስደተኛ የሆኑት ወንድሞች ሁልጊዜ የሌሎችን ልግስና የሚጠብቁ ከሆነ ለራሳቸው ያላቸውን አክብሮት ሊያጡ ብሎም ከወንድሞቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ሊሻክር ይችላል። (2 ተሰ. 3:7-9) ያም ቢሆን ስደተኞች እርዳታ አያስፈልጋቸውም ማለት አይደለም። ይህ ሲባል ግን ብዙ ገንዘብ መስጠት አለብን ማለት አይደለም፤ በዋነኝነት የሚያስፈልጋቸው ነገር ጊዜና ትኩረት ነው። የሕዝብ መጓጓዣ መጠቀም እንዲሁም ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ምግቦችን በርካሽ ዋጋ ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ብናሳያቸው እንደሚጠቀሙ የታወቀ ነው፤ በተጨማሪም ለሥራ ሊገለገሉባቸው የሚችሉ መሣሪያዎችን ማግኘት ወይም ገቢ የሚያስገኝላቸውን ሙያ መማር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ልንጠቁማቸው እንችላለን። እነዚህ ነገሮች ቀላል ቢመስሉም ለስደተኞቹ ትልቅ ጥቅም አላቸው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከአዲሱ ጉባኤያቸው ጋር በደንብ እንዲተዋወቁ ልትረዷቸው ትችላላችሁ። የሚቻል ከሆነ ወደ ጉባኤ ይዛችኋቸው ሂዱ። ከዚህም ሌላ በክልላችሁ ውስጥ የመንግሥቱን መልእክት ለሰዎች እንዴት መንገር እንደሚችሉ ጠቁሟቸው። ስደተኛ የሆኑትን ወንድሞችና እህቶች አገልግሎት ይዛችኋቸው ውጡ። w17.05 5 አን. 11-12
ሐሙስ፣ የካቲት 28
በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኘው ያልተበረዘ ወተት ጉጉት አዳብሩ፤ ይህም በእሱ አማካኝነት ወደ መዳን ማደግ እንድትችሉ ነው።—1 ጴጥ. 2:2
ሥጋዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ይከብዳቸዋል። ለምን? ምክንያቱም በአምላክ ዓይን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ምን እንደሆነ የማስተዋል ችሎታቸው ደንዝዟል። (1 ቆሮ. 2:14) የማስተዋል ችሎታቸው መደንዘዙ ደግሞ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት ይበልጥ ከባድ እንዲሆንባቸው ያደርጋል። (ዕብ. 5:11-14) በመሆኑም አንዳንዶች፣ ሁልጊዜ ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮችን የማግኘት ምኞት ይጠናወታቸዋል፤ መቼም ቢሆን በቃኝ አይሉም። (መክ. 5:10) ደስ የሚለው ነገር ፍቅረ ንዋይን ከማሳደድ አባዜ መላቀቅ የሚቻልበት መንገድ አለ፤ እንደ መርዝ አደገኛ የሆነውን ይህን አስተሳሰብ ለማስወገድ ፍቱን መድኃኒቱ የአምላክን ቃል አዘውትሮ ማንበብ ነው። ኢየሱስ ይሖዋ በገለጣቸው እውነቶች ላይ ማሰላሰሉ ፈተናዎችን ለመቋቋም እንደረዳው ሁሉ፣ እኛም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋችን ፍቅረ ንዋይን ለማሸነፍ ይረዳናል። (ማቴ. 4:8-10) ይህን ስናደርግ ኢየሱስን ከማንኛውም ቁሳዊ ነገር አስበልጠን እንደምንወደው እናሳያለን። w17.05 26 አን. 17