የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es19 ገጽ 118-128
  • ታኅሣሥ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ታኅሣሥ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2019
  • ንዑስ ርዕሶች
  • እሁድ፣ ታኅሣሥ 1
  • ሰኞ፣ ታኅሣሥ 2
  • ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 3
  • ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 4
  • ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 5
  • ዓርብ፣ ታኅሣሥ 6
  • ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 7
  • እሁድ፣ ታኅሣሥ 8
  • ሰኞ፣ ታኅሣሥ 9
  • ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 10
  • ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 11
  • ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 12
  • ዓርብ፣ ታኅሣሥ 13
  • ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 14
  • እሁድ፣ ታኅሣሥ 15
  • ሰኞ፣ ታኅሣሥ 16
  • ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 17
  • ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 18
  • ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 19
  • ዓርብ፣ ታኅሣሥ 20
  • ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 21
  • እሁድ፣ ታኅሣሥ 22
  • ሰኞ፣ ታኅሣሥ 23
  • ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 24
  • ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 25
  • ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 26
  • ዓርብ፣ ታኅሣሥ 27
  • ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 28
  • እሁድ፣ ታኅሣሥ 29
  • ሰኞ፣ ታኅሣሥ 30
  • ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2019
es19 ገጽ 118-128

ታኅሣሥ

እሁድ፣ ታኅሣሥ 1

ሳታጉረመርሙ አንዳችሁ ለሌላው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳዩ።—1 ጴጥ. 4:9

በጥንት ዘመን ሰዎች እንግዶችን ቤታቸው ምግብ በመጋበዝ ማስተናገዳቸው የተለመደ ነበር። (ዘፍ. 18:1-8፤ መሳ. 13:15፤ ሉቃስ 24:28-30) እንግዶቹን አብረዋቸው እንዲመገቡ መጋበዛቸው ከእነሱ ጋር ወዳጅነትና ሰላማዊ ግንኙነት መመሥረት እንደሚፈልጉ የሚያሳይ ነበር። ታዲያ እኛስ ቤታችን ልንጋብዝ የሚገባው እነማንን ነው? በዋነኝነት ከምንጋብዛቸው እንግዶች መካከል በጉባኤያችን ውስጥ ያሉት ወንድሞችና እህቶች ሊገኙበት እንደሚገባ የታወቀ ነው። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን እርስ በርስ መደጋገፋችን አይቀርም። በመሆኑም ከሁሉም ወንድሞቻችን ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረታችንና ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። የወረዳ የበላይ ተመልካቾች እና በቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ክርስቲያኖች እንዲሁም የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ለተወሰነ ጊዜ ማረፊያ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ቤታቸውን ያጡ አንዳንድ ቤተሰቦችም ቤታቸው እንደገና እስኪገነባ ድረስ የሚቆዩበት ቦታ ያስፈልጋቸው ይሆናል። እንዲህ ያሉትን ወንድሞች ማሳረፍ የሚችሉት በጣም ምቹ ቤት ያላቸው ክርስቲያኖች ብቻ እንደሆኑ አድርገን ማሰብ የለብንም፤ እነዚህ ወንድሞች ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ጊዜያት እንግዶችን ተቀብለው ሊሆን ይችላል። አንተስ ቤትህ ትልቅ ባይሆንም እንኳ እንግዶችን መቀበል ትችል ይሆን? w18.03 15 አን. 6፤ 16 አን. 9

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 2

ጻድቅ ሰባት ጊዜ ቢወድቅ እንኳ መልሶ ይነሳል።—ምሳሌ 24:16

ስህተት የሠራ ሰው መልሶ እንዲነሳ የሚረዳው ምንድን ነው? የራሱ ቆራጥነት ብቻ በቂ አይደለም፤ የግድ የአምላክ መንፈስ እርዳታ ያስፈልገዋል። (ፊልጵ. 4:13) ከአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች መካከል ደግሞ ራስን መግዛት የሚገኝበት ሲሆን ይህ ባሕርይ ራስን ከመገሠጽ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። በተጨማሪም ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረባችን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችንና ማሰላሰላችን ይረዳናል። ይሁንና የአምላክን ቃል ማጥናት ተፈታታኝ ቢሆንብህስ? ምናልባትም ማጥናት አትወድ ይሆናል። ሆኖም እስከፈቀድክለት ድረስ ይሖዋ እንደሚረዳህና ለቃሉ ‘ጉጉት እንድታዳብር’ እንደሚያስችልህ አትዘንጋ። (1 ጴጥ. 2:2) በመጀመሪያ፣ ይሖዋ ራስን የመገሠጽ ችሎታ እንድታዳብርና ቃሉን የምታጠናበት ጊዜ እንድትመድብ እንዲረዳህ በጸሎት ጠይቀው። ከዚያም ከጸሎትህ ጋር የሚስማማ እርምጃ ውሰድ፤ ምናልባትም አጠር ያለ የጥናት ፕሮግራም በማውጣት መጀመር ትችል ይሆናል። በጊዜ ሂደት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ቀላልና አስደሳች እየሆነልህ ይሄዳል! ፀጥ ባለ ሁኔታ ውስጥ ሆነህ ውድ በሆኑት የይሖዋ ሐሳቦች ላይ የምታሰላስልበትን ጊዜ በናፍቆት መጠባበቅ ትጀምራለህ።—1 ጢሞ. 4:15፤ w18.03 29 አን. 5-6

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 3

ጥምቀት . . . እናንተን እያዳናችሁ ነው።—1 ጴጥ. 3:21

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከመጠመቁ በፊት ስለ አምላክ፣ ስለ ዓላማዎቹና የሰው ልጆችን ለማዳን ስላደረገው ዝግጅት ትክክለኛ እውቀት ማግኘት እንዲሁም በተማረው ነገር ላይ እምነት ማሳደር ይገባዋል። (1 ጢሞ. 2:3-6) እንዲህ ያለው እምነት፣ ተማሪው አምላክን ከሚያሳዝኑ ድርጊቶች እንዲርቅና ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲኖር ያነሳሳዋል። (ሥራ 3:19) አንድ ግለሰብ የአምላክን መንግሥት እንዳይወርስ በሚያደርግ በማንኛውም ድርጊት እየተካፈለ ራሱን ለአምላክ ቢወስን ይህ እርምጃ ተቀባይነት እንደማይኖረው ጥርጥር የለውም። (1 ቆሮ. 6:9, 10) ሆኖም ላቅ ያሉትን የይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ማክበር ብቻውን በቂ አይደለም። በጽድቅ ጎዳና ላይ መመላለስ የሚፈልግ ግለሰብ፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲሁም ሕይወት አድን በሆነው የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ አቅሙ በፈቀደ መጠን መካፈል ይኖርበታል። (ሥራ 1:8) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እነዚህን እርምጃዎች ከወሰደ በኋላ ራሱን መወሰኑን ለይሖዋ በጸሎት ቢገልጽ ተቀባይነት ይኖረዋል፤ ከዚያም በሕዝብ ፊት መጠመቅ ይችላል። w18.03 6 አን. 12

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 4

[ማርያም] የተባሉትን ነገሮች ሁሉ በልቧ ትይዝ ነበር።—ሉቃስ 2:51

ይሖዋ የኢየሱስ እናት እንድትሆን ማርያምን የመረጣት ለምንድን ነው? መንፈሳዊ አስተሳሰብ ስለነበራት እንደሆነ ጥርጥር የለውም። በአንድ ወቅት ማርያም ዘመዶቿ የሆኑትን ዘካርያስንና ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ ሄዳ ነበር፤ በዚያ እያለች ይሖዋን ለማወደስ የተጠቀመችባቸው አገላለጾች መንፈሳዊ ሰው እንደነበረች በግልጽ ያሳያሉ። (ሉቃስ 1:46-55) ማርያም የተናገረችው ነገር ለአምላክ ቃል ጥልቅ ፍቅር እንደነበራትና የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቃ ታውቅ እንደነበር ይጠቁማል። (ዘፍ. 30:13፤ 1 ሳሙ. 2:1-10፤ ሚል. 3:12) ከዚህም ሌላ ማርያምና ዮሴፍ አዲስ ተጋቢዎች ቢሆኑም እንኳ ኢየሱስን እስክትወልድ ድረስ የፆታ ግንኙነት እንዳልፈጸሙ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከዚህ ምን መረዳት እንችላለን? ማርያምም ሆነች ዮሴፍ የግል ፍላጎታቸውን ከማርካት ይበልጥ ያሳሰባቸው ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖራቸው ነበር። (ማቴ. 1:25) ከዚህም ሌላ ማርያም በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች በትኩረት ትከታተል እንዲሁም የሚናገራቸውን ጥበብ ያዘሉ ሐሳቦች ታስተውል ነበር። አምላክ ከመሲሑ ጋር በተያያዘ የተናገራቸው ነገሮች እንዴት እንደሚፈጸሙ የማወቅ ጉጉት እንደነበራት ግልጽ ነው። ማርያም የተወችው ምሳሌ በሕይወታችን ውስጥ ለአምላክ ፈቃድ ቅድሚያ መስጠት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ቆም ብለን እንድናስብ አያነሳሳንም? w18.02 21 አን. 11

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 5

[ኢዮብ] በንጹሕ አቋም የሚመላለስ ቅን ሰው [ነው]።—ኢዮብ 1:8

ኢዮብ የተወውን የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ ለይሖዋ በመስጠት ነው፤ ምንጊዜም በእሱ መታመንና በሙሉ ልባችን እሱን መታዘዝ ይኖርብናል። ደግሞም እኛ ከኢዮብ አንጻር ሲታይ እንዲህ ለማድረግ የሚያነሳሱ ተጨማሪ ምክንያቶች አሉን! እስቲ አስቡት፦ ስለ ሰይጣንና እሱ ስለሚጠቀምባቸው ዘዴዎች ብዙ ነገር እናውቃለን። (2 ቆሮ. 2:11) መጽሐፍ ቅዱስ በተለይም የኢዮብ መጽሐፍ በእጃችን ስላለ አምላክ በሰዎች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደበትን ምክንያት መረዳት ችለናል። በተጨማሪም የአምላክ መንግሥት በክርስቶስ ኢየሱስ የሚመራ ዓለም አቀፋዊ መስተዳድር እንደሆነ ከዳንኤል ትንቢት ተገንዝበናል። (ዳን. 7:13, 14) ይህ መንግሥት የሚደርሱብንን መከራዎች ሁሉ በቅርቡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚያስወግድም እናውቃለን። የኢዮብ ታሪክ መከራ እየደረሰባቸው ላሉ የእምነት ባልንጀሮቻችን ርኅራኄ ልናሳያቸው እንደሚገባም ያጎላል። አንዳንዶች ልክ እንደ ኢዮብ እንዳመጣላቸው የሚናገሩበት ጊዜ ይኖራል። (መክ. 7:7) በዚህ ጊዜ በእነሱ ላይ ከመፍረድ ይልቅ አስተዋይ በመሆን ርኅራኄ ልናሳያቸው ይገባል። እንዲህ በማድረግ አፍቃሪና መሐሪ የሆነውን አባታችንን ይሖዋን መምሰል እንችላለን።—መዝ. 103:8፤ w18.02 6 አን. 16፤ 7 አን. 19-20

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 6

ትሕትናህም ታላቅ ያደርገኛል።—መዝ. 18:35

አንዳንድ ሰዎች የሚኮሩት መልከ መልካም ወይም ታዋቂ ስለሆኑ አሊያም ጥሩ የሙዚቃ ችሎታ፣ ሥልጣን ወይም ደግሞ አካላዊ ጥንካሬ ስላላቸው ሊሆን ይችላል። ዳዊት እነዚህ ሁሉ ነገሮች ቢኖሩትም በሕይወቱ ሙሉ ትሑት ነበር። ጎልያድን ከገደለ በኋላ ንጉሥ ሳኦል ልጁን ሊድርለት እንደሚፈልግ ሲነግረው ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ ‘ለንጉሡ አማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ሆኜ ነው?’ (1 ሳሙ. 18:18) እንደ ዳዊት ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮችም ትሑት ለመሆን ይጥራሉ። ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀው አካል ቢሆንም እንኳ ግሩም የሆነውን የትሕትና ባሕርይ ያንጸባርቃል፤ ይህን ማወቃችን በአድናቆት እንድንዋጥ ያደርገናል። ይህ ደግሞ “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ያነሳሳናል። (ቆላ. 3:12) በተጨማሪም ፍቅር ‘ጉራ እንደማይነዛና እንደማይታበይ’ እንገነዘባለን። (1 ቆሮ. 13:4) ትሑት መሆናችን ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲሳቡ ሊያደርግ ይችላል። w18.01 28 አን. 6-7

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 7

በልግስና በመስጠት፣ በእርዳታ አገልግሎቱ ለመካፈል መብት እንዲሰጣቸው . . . ይለምኑን እንዲያውም ይማጸኑን ነበር።—2 ቆሮ. 8:4

ለአንድ የተወሰነ ዓላማ መዋጮ ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል። (ሥራ 4:34, 35፤ 1 ቆሮ. 16:2) ለምሳሌ ያህል፣ ለጉባኤያችሁ አዲስ የስብሰባ አዳራሽ ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ ይሆን? ምናልባትም የክልል ስብሰባ ወጪዎችን ለመሸፈን ወይም የተፈጥሮ አደጋ ያጋጠማቸውን ወንድሞች ለመርዳት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ሰምተን ይሆናል። በተጨማሪም በዋናው መሥሪያ ቤትና በተለያዩ የምድር ክፍሎች በሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚከናወነውን ሥራ የሚሠሩትን ወንድሞችና እህቶች ለመደገፍ መዋጮ እናደርጋለን። የምናደርገው መዋጮ ሚስዮናውያንን፣ ልዩ አቅኚዎችንና በወረዳ ሥራ የሚካፈሉትን ለመደገፍም ይውላል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ይሖዋ እያከናወነ ያለውን ሥራ ለመደገፍ ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ ማበርከት እንችላለን። አብዛኛውን ጊዜ መዋጮ ያደረገው ማን እንደሆነ አይታወቅም። የምናደርገውን መዋጮ በስብሰባ አዳራሻችን ውስጥ በሚገኙት ሣጥኖች ውስጥ መጨመር ወይም በjw.org አማካኝነት በኢንተርኔት መላክ እንችላለን፤ ምን ያህል መዋጮ እንዳደረግን ሌሎች አያውቁም። የምናደርገው አነስተኛ መዋጮ ያን ያህል የሚያመጣው ለውጥ እንደሌለ ይሰማን ይሆናል። ይሁንና ድርጅቱ አብዛኛውን ሥራ የሚያካሂደው ጥቂቶች በሚያደርጉት ከፍተኛ መጠን ያለው መዋጮ ሳይሆን ብዙዎች በሚያደርጉት አነስተኛ መጠን ያለው መዋጮ ነው። w18.01 19 አን. 10-11

እሁድ፣ ታኅሣሥ 8

ጥምቀት . . . እናንተን እያዳናችሁ ነው።—1 ጴጥ. 3:21

ጥምቀት ከሁሉም ክርስቲያኖች የሚጠበቅ ብቃት ከመሆኑም በላይ መዳን ለማግኘት አስፈላጊ የሆነ እርምጃ ነው። (ማቴ. 28:19, 20) ጥምቀት፣ ራሳችሁን ለይሖዋ መወሰናችሁን ለማሳየት የወሰዳችሁት እርምጃ ነው። ስትጠመቁ፣ ይሖዋን ለመውደድና የእሱን ፈቃድ ከምንም ነገር በላይ ለማስቀደም ቃል ገብታችኋል። ሕይወታችሁን ለይሖዋ መስጠታችሁ መቼም ቢሆን የተሳሳተ እርምጃ ሊሆን አይችልም። እንዲህ ያለ ውሳኔ ባታደርጉ ኖሮ ሌላው አማራጭ ምን ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስቡት። አንድ ሰው ከይሖዋ ርቆ የሚኖር ከሆነ የሰይጣን ዓለም ክፍል መሆኑ አይቀርም። ሰይጣን ደግሞ የእናንተ መዳን ጨርሶ ግድ አይሰጠውም። እንዲያውም ከእሱ ጎን ሆናችሁ የይሖዋን ሉዓላዊነት ብትቃወሙና የዘላለም ሕይወት ብታጡ ደስታውን አይችለውም። ከሰይጣን ጎን ከመቆም ይልቅ ራሳችሁን ለይሖዋ መወሰናችሁ እና መጠመቃችሁ የሚያስገኛቸውን በረከቶች እስቲ አስቡ። ሕይወታችሁን ለይሖዋ መስጠታችሁ “ይሖዋ ከጎኔ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” ብላችሁ በልበ ሙሉነት ለመናገር ያስችላችኋል። (መዝ. 118:6) ከአምላክ ጎን ከመቆምና የእሱን ሞገስ ከማግኘት ጋር የሚወዳደር ታላቅ መብት በሕይወታችሁ ውስጥ ልታገኙ አትችሉም። w17.12 23-24 አን. 1-3

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 9

ተበሳጭተህ ክፉ ነገር አትሥራ።—መዝ. 37:8

የእምነት ባልንጀሮቻችን በሚናገሩት ወይም በሚያደርጉት ነገር ቅር የምንሰኝባቸው ጊዜያት አሉ፤ እነሱም ቢሆን በእኛ ይከፉ ይሆናል። ይህ ደግሞ ከባድ ፈተና ሊሆንብን ይችላል። ይሁን እንጂ እንደ ሌሎች ፈተናዎች ሁሉ ከወንድሞቻችን ጋር የሚፈጠር አለመግባባትም ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ለማሳየት አጋጣሚ ይሰጠናል፤ እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍጹማን ባይሆኑም ይሖዋ ይወዳቸዋል፤ እኛም ወንድሞቻችንን በመውደድና ከእነሱ ጋር ተስማምተን በመሥራት ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ማሳየት እንችላለን። ይሖዋ፣ በአገልጋዮቹ ላይ ፈተና እንዳይደርስ እንደማይከላከል ከዮሴፍ ታሪክ መመልከት እንችላለን። ዮሴፍ ወጣት እያለ ወንድሞቹ ስለቀኑበት ለባርነት ሸጡት፤ ከዚያም ወደ ግብፅ ተወሰደ። (ዘፍ. 37:28) ይሖዋ ይህን ሁኔታ እንደተመለከተና ጻድቅ የሆነው ወዳጁ በደረሰበት በደል እንዳዘነ ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ ይሖዋ፣ ዮሴፍ እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዳይደርስበት አልተከላከለም። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ዮሴፍ የጶጢፋርን ሚስት ለመድፈር ሞክሯል በሚል ተከስሶ እስር ቤት ተወረወረ፤ በዚህ ጊዜም ቢሆን አምላክ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ አልወሰደም። ይህ ሲባል ግን አምላክ ዮሴፍን ትቶት ነበር ማለት ነው? በጭራሽ፤ እንዲያውም ዮሴፍ “የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ይሖዋ [ያሳካለት]” ነበር።—ዘፍ. 39:21-23፤ w18.01 9-10 አን. 12-14

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 10

የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሳም ማለት ነዋ!—1 ቆሮ. 15:13

‘የሃይማኖታችሁ መሠረታዊ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው?’ ተብለህ ብትጠየቅ ምን ትመልሳለህ? ፈጣሪያችንና ሕይወት ሰጪያችን ይሖዋ መሆኑን እንደምናምን ጎላ አድርገህ ትናገር ይሆናል። ቤዛ ሆኖ በሞተልን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነትም መጥቀስህ አይቀርም። በተጨማሪም ወደፊት ምድር ገነት እንደምትሆንና የአምላክ ሕዝቦችም በዚያ ለዘላለም እንደሚኖሩ ያለንን አስደሳች ተስፋ ትናገር ይሆናል። ይሁን እንጂ ትልቅ ቦታ ከምትሰጣቸው ትምህርቶች መካከል የትንሣኤ ተስፋን እንደ አንዱ አድርገህ ትገልጸዋለህ? ከታላቁ መከራ በሕይወት አልፈን በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የምናደርግ ቢሆንም፣ ቁልፍ ከሆኑት የክርስትና ትምህርቶች አንዱ የትንሣኤ ተስፋ እንደሆነ ለማመን የሚያበቁ ምክንያቶች አሉን። የትንሣኤ ተስፋ ለእምነታችን መሠረት ነው። ክርስቶስ ካልተነሳ ንጉሣችን ሆኖ እየገዛ አይደለም እንዲሁም ስለ ክርስቶስ አገዛዝ የምናስተምረው ትምህርት ከንቱ ነው ማለት ነው። (1 ቆሮ. 15:12-19) እኛ ግን ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ እርግጠኞች ነን። በትንሣኤ ላይ ያለን እምነት ጠንካራ ነው።—ማር. 12:18፤ ሥራ 4:2, 3፤ 17:32፤ 23:6-8፤ w17.12 8 አን. 1-2

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 11

በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን እንደ ፍትሕ፣ ምሕረት . . . ያሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ችላ ትላላችሁ።—ማቴ. 23:23

ፈሪሳውያን ትኩረት የሚያደርጉት ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ ‘ምን ዓይነት የልብ ዝንባሌ አለው?’ በሚለው ላይ ሳይሆን በፈጸመው ድርጊት ላይ ብቻ ነበር። ለምሳሌ፣ ኢየሱስ በማቴዎስ ቤት በተዘጋጀ ግብዣ ላይ መገኘቱን ፈሪሳውያን ሲያዩ ደቀ መዛሙርቱን “መምህራችሁ ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቋቸው። በዚህ ጊዜ የአምላክ ልጅ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም። እንግዲያው ሄዳችሁ ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ የሚለውን ቃል ትርጉም አስተውሉ። እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ልጠራ ነውና።” (ማቴ. 9:9-13) ክርስቶስ ይህን ማለቱ ከባድ ኃጢአትን አቅልሎ እንደሚመለከት የሚያሳይ ነው? በፍጹም። እንዲያውም ኢየሱስ፣ ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ ግብዣ አቅርቧል። (ማቴ. 4:17) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በዚያ ከነበሩት ‘ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኃጢአተኞች’ መካከል ቢያንስ አንዳንዶቹ ለውጥ ማድረግ ይፈልጉ እንደነበር አስተውሏል። እነዚህ ሰዎች ወደ ማቴዎስ ቤት የመጡት ምግብ ለመብላት ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ከእነሱ መካከል “ብዙዎቹ [ኢየሱስን] መከተል ጀምረው ነበር።” (ማር. 2:15) የሚያሳዝነው አብዛኞቹ ፈሪሳውያን፣ ክርስቶስ ለእነዚህ ሰዎች የነበረው ዓይነት አመለካከት አልነበራቸውም። w17.11 13 አን. 2፤ 16 አን. 15

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 12

ፍቅርን ልበሱ፤ ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነውና።—ቆላ. 3:14

የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆን በረከት እንደሆነ ሁላችንም እንስማማለን። በስብሰባዎቻችን ላይ የአምላክን ቃል ማጥናታችን እንዲሁም እርስ በርስ በደግነትና በፍቅር መደጋገፋችን ዓይናችን በሽልማቱ ላይ እንዲያተኩር ይረዳናል። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በጉባኤው አባላት መካከል ውጥረት እንዲነግሥ ሊያደርጉ ይችላሉ። እንዲህ ያሉ ችግሮችን ካልፈታናቸው በወንድሞቻችን ላይ ቂም ወደ መያዝ ሊመሩን ይችላሉ። (1 ጴጥ. 3:8, 9) በሌሎች ላይ ቂም መያዛችን ሽልማታችንን ሊያሳጣን ይችላል፤ ታዲያ ይህ እንዳይሆን ምን ማድረግ እንችላለን? ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል፦ “የአምላክ ምርጦች፣ ቅዱሳንና የተወደዳችሁ እንደመሆናችሁ መጠን ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ። አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።”—ቆላ. 3:12-13፤ w17.11 27 አን. 7-8

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 13

ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ [ይሽሽ]።—ኢያሱ 20:4

ሳያስበው ነፍስ ያጠፋ ግለሰብ፣ ከመማጸኛ ከተሞች ወደ አንዱ በመሸሽ በከተማዋ በር ላይ ቆሞ መጀመሪያ “ለከተማዋ ሽማግሌዎች ጉዳዩን [መናገር]” አለበት። ሽማግሌዎቹም ወደ ከተማቸው ያስገቡታል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ ይህ ግለሰብ የሰው ነፍስ ወዳጠፋበት ከተማ እንዲመለስና የዚያ ከተማ ሽማግሌዎች በጉዳዩ ላይ ፍርድ እንዲሰጡ ይደረጋል። (ዘኁ. 35:24, 25) ግለሰቡ ወደ መማጸኛ ከተማ እንዲመለስ የሚፈቀድለት ሽማግሌዎቹ፣ ነፍስ ያጠፋው ሳያስበው መሆኑን ከፈረዱ ብቻ ነው። ጉዳዩን ሽማግሌዎች የሚመለከቱት ለምንድን ነው? የእስራኤልን ጉባኤ ንጽሕና ለመጠበቅ እንዲሁም ሳያስበው ነፍስ ያጠፋው ግለሰብ ይሖዋ ካደረገው ምሕረት የተንጸባረቀበት ዝግጅት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደገለጹት ግለሰቡ ወደ ሽማግሌዎች ሳይሄድ ከቀረ ‘አምላክ ባደረገለት ጥበቃ የሚያስገኝ ዝግጅት ስላልተጠቀመ ራሱን ለአደጋ ያጋልጣል’ ብለዋል። ሳያውቅ ነፍስ ያጠፋ ሰው እርዳታ ማግኘት የሚችልበት ዝግጅት አለ፤ ሆኖም ከዝግጅቱ ለመጠቀም ጥረት ማድረግና የሚሰጠውን እርዳታ መቀበል አለበት። ይህ ግለሰብ መጠጊያ ለማግኘት፣ ይሖዋ እንዲለዩ ወዳደረጋቸው የመማጸኛ ከተሞች ባይሄድና የሟቹ የቅርብ ዘመድ አግኝቶ ቢገድለው ገዳዩ በደም ዕዳ አይጠየቅም። w17.11 9 አን. 6-7

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 14

ሁሉም መዳን የሚወርሱትን እንዲያገለግሉ የሚላኩ ቅዱስ አገልግሎት የሚያከናውኑ መናፍስት አይደሉም?—ዕብ. 1:14

የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በዘካርያስ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም ሕዝቦቹን ለመጠበቅና ለማጠናከር መላእክቱን ይጠቀማል። (ሚል. 3:6፤ ዕብ. 1:7) ጠላቶች እውነተኛው አምልኮ እንዳይስፋፋ ተቃውሞ ያልሰነዘሩበት ጊዜ የለም፤ ያም ሆኖ መንፈሳዊ እስራኤል በ1919 በምሳሌያዊ ሁኔታ ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ነፃ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ እውነተኛው አምልኮ እድገት ማድረጉንና መስፋፋቱን ቀጥሏል። (ራእይ 18:4) የመላእክት ጥበቃ ስላለን የይሖዋ ድርጅት ዳግመኛ በመንፈሳዊ የባርነት ቀንበር ውስጥ ይገባል ብለን መስጋት አያስፈልገንም። (መዝ. 34:7) ከዚህ ይልቅ በዓለም ዙሪያ ያሉት የአምላክ አገልጋዮች በመንፈሳዊ መበልጸጋቸውን እንደሚቀጥሉ ልንተማመን እንችላለን። ፈረሰኛ የመላእክት ሠራዊት ከጎናችን እንዳለ እናውቃለን። ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ ባለው ወሳኝ ወቅት የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ኃያላን መላእክት፣ አንድ ላይ በመሆን ለአምላክ ሕዝቦች ጥበቃ ያደርጋሉ፤ በተጨማሪም የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚቃወሙትን ሁሉ ያጠፋሉ። (2 ተሰ. 1:7, 8) ያ ዕለት እንዴት ያለ ልዩ ቀን ይሆናል! w17.10 28 አን. 10-11

እሁድ፣ ታኅሣሥ 15

እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ላይ ራሳችሁን ገንቡ፤ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ጸልዩ።—ይሁዳ 20

የቤተሰባችን አባል ከጉባኤ በሚወገድበት ወይም ራሱን በሚያገልበት ጊዜ በከባድ ሐዘን ልንዋጥ እንችላለን። በዚህ ወቅት የሚሰማንን ሐዘን መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? መንፈሳዊ ልማዶቻችሁን አጠናክራችሁ መቀጠላችሁ አስፈላጊ ነው። አዘውትራችሁ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ፣ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በመዘጋጀትና በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት፣ በመስክ አገልግሎት በመካፈልና ለመጽናት የሚያስችላችሁን ኃይል እንዲሰጣችሁ ወደ ይሖዋ በመጸለይ ራሳችሁን ለመገንባት ጥረት አድርጉ። (ይሁዳ 21) ይሁንና እነዚህን ሁሉ ነገሮች ብታደርጉም የሚሰማችሁን ሐዘን መቋቋም ቢከብዳችሁስ? ተስፋ አትቁረጡ! ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ያላችሁ መሆኑ አስተሳሰባችሁንና ስሜታችሁን ለመቆጣጠር ሊረዳችሁ ይችላል። የመዝሙር 73 ጸሐፊ ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ መመልከት እንችላለን። ይህ ግለሰብ የተሳሳተ አመለካከት በመያዙ ምክንያት በጣም የተረበሸበት ወቅት ነበር፤ ይሁንና ወደ አምላክ መቅደስ መግባቱ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል ረድቶታል። (መዝ. 73:16, 17) ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችሁን መቀጠላችሁ እናንተንም ሊረዳችሁ ይችላል። w17.10 16 አን. 17-18

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 16

ፍቅራችሁ ግብዝነት የሌለበት ይሁን።—ሮም 12:9

በኤደን ገነት ውስጥ ሰይጣን ሔዋንን ያነጋገራት ለእሷ ደህንነት የተቆረቆረ በሚመስል መንገድ ነበር፤ ሆኖም ድርጊቱ ከራስ ወዳድነት የመነጨና ግብዝነት የሞላበት ነበር። (ዘፍ. 3:4, 5) የአኪጦፌልን ሁኔታም እንደ ምሳሌ መመልከት እንችላለን። አኪጦፌል የንጉሥ ዳዊት እውነተኛ ወዳጅ አልነበረም፤ ምክንያቱም ጥቅም የሚያስገኝለት ሁኔታ እንደተፈጠረ ሲሰማው ዳዊትን ከድቶታል። (2 ሳሙ. 15:31) ዛሬም በተመሳሳይ በጉባኤው ውስጥ ክፍፍል የሚፈጥሩ ከሃዲዎችም ሆኑ ሌሎች ግለሰቦች አሳቢ መስለው ለመታየት ሲሉ ‘የለሰለሰ አንደበትና የሽንገላ ቃላት’ ይጠቀማሉ፤ እንደ እውነታው ከሆነ ግን እነዚህ ሰዎች የራስ ወዳድነት ፍላጎታቸውን ለማራመድ የሚጥሩ ናቸው። (ሮም 16:17, 18) የውሸት ፍቅር የሚያሳዩ ሰዎች አምላካዊ ባሕርይ የሆነው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያላቸው መስለው ለመታየት ጥረት ማድረጋቸው በጣም አሳፋሪ ነው። እንዲህ ያለው ግብዝነት ሰዎችን ያታልል ይሆናል፤ ይሖዋን ግን በፍጹም ሊያታልለው አይችልም። እንዲያውም ኢየሱስ ግብዞች “ከባድ ቅጣት” እንደሚጠብቃቸው የሚጠቁም ሐሳብ ተናግሯል። (ማቴ. 24:51) ስለዚህ ‘ምንጊዜም ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነና ማታለል የሌለበት እውነተኛ ፍቅር አሳያለሁ?’ በማለት ራሳችንን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው። w17.10 8 አን. 6-8

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 17

ለአምላክ ቅንዓት [አላቸው]፤ ሆኖም ቅንዓታቸው በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አይደለም።—ሮም 10:2

በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በቀጥታ ስናነብላቸው ይሖዋ እንዲያነጋግራቸው እያደረግን ነው ማለት ይቻላል። ለምንወያይበት ርዕሰ ጉዳይ ተስማሚ የሆነ አንድ ጥቅስ እኛ ልንናገር ከምንችለው ከየትኛውም ሐሳብ የበለጠ ኃይል አለው። (1 ተሰ. 2:13) በመሆኑም ‘ምሥራቹን ለምሰብክላቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ለማንበብ የተቻለኝን ሁሉ ጥረት አደርጋለሁ?’ በማለት ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። እርግጥ ነው፣ በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማንበባችን ብቻ በቂ አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በርካታ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው እውቀት በጣም አነስተኛ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለነበሩ ሰዎችም ተመሳሳይ ነገር ሊባል ይችላል። በመሆኑም ለአንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ስላነበብንለት ብቻ ግለሰቡ ጥቅሱን ይረዳዋል ብለን መደምደም አይኖርብንም። የምናነጋግራቸው ሰዎች ነጥቡን እንዲረዱት ለማድረግ ቁልፍ ቃላትን ደግመን በማንበብ ወይም ሌላ ዘዴ በመጠቀም የጥቅሱን ዋና ሐሳብ ነጥለን ማውጣት አለብን፤ ከዚያም ትርጉሙን ማብራራት ያስፈልገናል። እንዲህ ማድረጋችን የአምላክ ቃል ወደምናነጋግራቸው ሰዎች ልብና አእምሮ ዘልቆ እንዲገባ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።—ሉቃስ 24:32፤ w17.09 25 አን. 7-8

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 18

ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ።—1 ጴጥ. 3:8

ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች ለወንድሞቻቸውም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ርኅራኄ እንዲያሳዩ ይጠበቅባቸዋል። (ዮሐ. 13:34, 35) ርኅራኄ የሚለው ቃል ካሉት ትርጉሞች መካከል አንዱ “አብሮ መሠቃየት” የሚል ነው። አንድ ሰው ርኅራኄ ካለው የሌሎችን ሥቃይ ለማስታገሥ እርምጃ ይወስዳል፤ ምናልባትም ይህን የሚያደርገው ችግራቸውን መወጣት እንዲችሉ በመርዳት ሊሆን ይችላል። ርኅራኄ ማሳየት የምትችሉባቸውን አጋጣሚዎች በንቃት ተከታተሉ! ብዙዎች በአደጋ የተጎዱ ሰዎች የሚደርስባቸውን ሥቃይ ሲመለከቱ ርኅራኄ ለማሳየት ይነሳሳሉ። የይሖዋ ሕዝቦች እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ፈጥነው እርዳታ በመስጠት ይታወቃሉ። (1 ጴጥ. 2:17) የአንዲትን ጃፓናዊ እህት ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ ይህች እህት የምትኖርበት አካባቢ በ2011 በከባድ የመሬት መንቀጥቀጥና ሱናሚ ተመቶ ነበር። ከተለያዩ የጃፓን ግዛቶች እንዲሁም ከውጭ አገር የመጡ በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች የተፈጥሮ አደጋው ያስከተለውን ጉዳት ለመጠገን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤ እህት ይህን መመልከቷ ‘በጣም እንዳበረታታትና እንዳጽናናት’ ተናግራለች። እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ይህ ሁኔታ ይሖዋ እንደሚያስብልን እንዳስተውል አድርጎኛል፤ በተጨማሪም የእምነት ባልንጀሮቻችን እርስ በርስ እንደሚተሳሰቡ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በርካታ ወንድሞችና እህቶች እንደሚጸልዩልን እንድገነዘብ ረድቶኛል።” w17.09 11 አን. 12-13

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 19

የመንፈስ ፍሬ . . . ራስን መግዛት ነው።—ገላ. 5:22, 23

ራስን የመግዛት ባሕርይን ማዳበርህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶችን እንመልከት። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ስሜታቸውን መቆጣጠር የሚችሉ ሰዎች በጥቅሉ ሲታይ ለከፍተኛ ችግር የሚዳረጉበት አጋጣሚ ዝቅተኛ እንደሆነ ተስተውሏል። ራሳቸውን የሚገዙ ሰዎች ይበልጥ የተረጋጉ ናቸው፤ ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት ይችላሉ እንዲሁም ስሜታቸውን ከማይቆጣጠሩ ሰዎች አንጻር ሲታይ ለጭንቀት፣ ለብስጭትና ለመንፈስ ጭንቀት የሚዳረጉበት አጋጣሚ አነስተኛ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ፈታኝ ሁኔታዎችን የመቋቋም እንዲሁም ተገቢ ያልሆኑ ስሜቶችን የመቆጣጠር ችሎታ ማዳበራችን የአምላክን ሞገስ ላለማጣት ወሳኝ ነገር ነው። አዳምና ሔዋን ያጋጠማቸው አሳዛኝ ሁኔታ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። (ዘፍ. 3:6) ከአዳምና ከሔዋን በኋላ የኖሩ በርካታ ሰዎችም ራሳቸውን መግዛት ባለመቻላቸው ያጋጠማቸውን አሳዛኝ ሁኔታ ማሰብ እንችላለን። ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች ራስን የመግዛት ባሕርይን ፍጹም በሆነ መንገድ ሊያንጸባርቁ አይችሉም። ይሖዋ አገልጋዮቹ በዚህ ረገድ የሚያደርጉትን ትግል ያውቃል፤ እንዲሁም የኃጢአት ዝንባሌያቸውን መቆጣጠር እንዲችሉ ሊረዳቸው ይፈልጋል።—1 ነገ. 8:46-50፤ w17.09 3-4 አን. 3-4

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 20

አዲሱን ስብዕና ልበሱ።—ቆላ. 3:10

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ፣ የተለያየ የቆዳ ቀለም ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች በነፃነት አብረው መሰብሰብ የማይችሉበት ወቅት ነበር። ይሁንና እሁድ፣ ታኅሣሥ 18, 2011 በደቡብ አፍሪካና በአጎራባች አገሮች የሚኖሩ ከተለያየ ዘር የተውጣጡ ከ78,000 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀላቸው መንፈሳዊ ፕሮግራም ለመካፈል በጆሃንስበርግ በሚገኘው ትልቁ ስታዲየም ውስጥ ተሰብስበው ነበር። ከስታዲየሙ ሥራ አስኪያጆች መካከል አንዱ እንዲህ ሲል አስተያየት ሰጥቷል፦ “እስካሁን ድረስ በዚህ ስታዲየም ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል እንዲህ ያለ ጥሩ ምግባር ያላቸው ሰዎች አጋጥመውኝ አያውቁም። ሁሉም ሥርዓታማ አለባበስ አላቸው። ደግሞም ስታዲየሙን በጣም ጥሩ አድርጋችሁ አጽድታችሁታል። ከሁሉ በላይ ያስገረመኝ ግን ከተለያየ ዘር የተውጣጣችሁ መሆናችሁ ነው።” የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች የሰጡት እንዲህ ያለው አስተያየት ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበራችን በእርግጥም ልዩ እንደሆነ ያሳያል። (1 ጴጥ. 5:9) ይሁንና ከሌሎች ድርጅቶች ልዩ እንድንሆን ያደረገን ምንድን ነው? በአምላክ ቃልና በቅዱስ መንፈሱ እርዳታ ‘አሮጌውን ስብዕና ገፈን ለመጣል’ እና “አዲሱን ስብዕና [ለመልበስ]” ከፍተኛ ጥረት ማድረጋችን ነው።—ቆላ. 3:9፤ w17.08 17-18 አን. 2-3

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 21

እናንተም በትዕግሥት ጠብቁ።—ያዕ. 5:8

መጽሐፍ ቅዱስ ትዕግሥት የሚገኘው በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ እንደሆነ ይናገራል፤ በመሆኑም ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች ያለአምላክ እርዳታ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በትዕግሥት መቋቋም አይችሉም። ትዕግሥት የአምላክ ስጦታ ነው። እኛም ታጋሽ በመሆን አምላክን ምን ያህል እንደምንወደው እናሳያለን። በተጨማሪም ታጋሽ መሆናችን ለሌሎች ያለንን ፍቅር ያሳያል። ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ብዙ ጊዜ ትዕግሥት የምናጣ ከሆነ በመካከላችን ያለው የፍቅር ማሰሪያ ሊላላ ይችላል፤ በአንጻሩ ግን ታጋሾች ከሆንን ፍቅራችን ይጠናከራል። (1 ቆሮ. 13:4፤ ገላ. 5:22) ታጋሽ መሆን ሌሎች ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማንጸባረቅንም ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል፣ ትዕግሥት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አዎንታዊ አመለካከት ይዘን እንድንቋቋም ከሚያስችለን ባሕርይ ማለትም ከጽናት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። (ቆላ. 1:11፤ ያዕ. 1:3, 4) ከዚህም ሌላ ትዕግሥት፣ ምንም ይምጣ ምን ለይሖዋ ታማኝ መሆንን እንዲሁም በደል ሲደርስብን አጸፋ ከመመለስ መቆጠብን ይጨምራል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በትዕግሥት የመጠበቅን አስፈላጊነት አምነን ለመቀበል ፈቃደኞች እንድንሆን ያበረታታናል። በያዕቆብ 5:7, 8 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ትዕግሥትን በተመለከተ ይህን አስፈላጊ ትምህርት እናገኛለን። w17.08 4 አን. 4

እሁድ፣ ታኅሣሥ 22

እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ።—ኢሳ. 41:10

ወጣቶች፣ አንድ ሰው ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ወዴት እንደሚሄድ ማቀድ አለበት ቢባል ሳትስማሙ አትቀሩም። ሕይወትም ከጉዞ ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ ሕይወታችሁን በየትኛው አቅጣጫ መምራት እንደምትፈልጉ ዕቅድ ማውጣት ያለባችሁ ወጣት እያላችሁ ነው። እርግጥ፣ ዕቅድ ማውጣት ቀላል ላይሆን ይችላል። ሆኖም አይዟችሁ! ይሖዋ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የተናገረውን ሐሳብ ልብ በሉ። ይሖዋ ከወደፊት ሕይወታችሁ ጋር በተያያዘ ጥበብ የተንጸባረቀበት ዕቅድ እንድታወጡ ያበረታታችኋል። (መክ. 12:1፤ ማቴ. 6:20) ይሖዋ ደስተኛ እንድትሆኑ ይፈልጋል። የምናያቸው፣ የምንሰማቸውና የምንቀምሳቸው አስደሳች ነገሮችን መፍጠሩ ለዚህ ማስረጃ ነው። በተጨማሪም ምን ያህል እንደሚንከባከበን እንዲሁም ከሁሉ የተሻለ ሕይወት ለመምራት የሚያስችል መመሪያ እንደሚሰጠን አስቡ። ይሖዋ፣ የእሱን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኛ ላልሆኑ ሰዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እኔ የማልደሰትበትንም ነገር መረጣችሁ። . . . እነሆ፣ አገልጋዮቼ ሐሴት ያደርጋሉ፤ እናንተ ግን ኀፍረት ትከናነባላችሁ። እነሆ፣ አገልጋዮቼ ከልባቸው ደስታ የተነሳ እልል ይላሉ።” (ኢሳ. 65:12-14) የይሖዋ አገልጋዮች በሕይወታቸው ውስጥ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ማድረጋቸው እሱን ያስከብረዋል።—ምሳሌ 27:11፤ w17.07 22 አን. 1-2

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 23

[ይሖዋ] ሁሉንም [ከዋክብት] በየስማቸው ይጠራቸዋል።—መዝ. 147:4

እያንዳንዱ ኮከብ በማንኛውም ጊዜ የሚገኝበትን ትክክለኛ ቦታ የሚያውቀው አምላክ አንተንም በግለሰብ ደረጃ በሚገባ ያውቅሃል፤ በሌላ አባባል የት እንዳለህ፣ ምን እንደሚሰማህ እንዲሁም ምን እንደሚያስፈልግህ ሁልጊዜ ጠንቅቆ ያውቃል! ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ስለ አንተ የሚያስብ ከመሆኑም ባሻገር በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ችግሮች ይረዳልሃል፤ እንዲሁም ችግሮችህን እንድትወጣ ለመርዳት የሚያስችል ኃይል አለው። (መዝ. 147:5) በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለህና የተጫነብህ ሸክም ከአቅምህ በላይ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። አምላክ ‘አፈር መሆንህን ስለሚያስታውስ’ ያለብህን የአቅም ገደብ ይገነዘባል። (መዝ. 103:14) ፍጹማን ባለመሆናችን በተደጋጋሚ ጊዜ አንድ ዓይነት ስህተት እንፈጽም ይሆናል። ሁላችንም፣ ሳናስብ በተናገርነው ነገር የተነሳ ተቆጭተን እናውቃለን፤ አሊያም ደግሞ አልፎ አልፎ ብቅ እያለ በሚያስቸግረን የሥጋ ምኞት በመሸነፋችን ወይም በሌሎች የመቅናት ዝንባሌ ስላለን አዝነን እናውቃለን። ይሖዋ እንዲህ ያሉ ድክመቶች ባይኖሩበትም እኛ ያሉብንን ድክመቶች በሚገባ ይረዳልናል፤ በዚህ ረገድ ያለው ማስተዋልም ቢሆን ወሰን የለውም፤ እንዲሁም አይመረመርም! (ኢሳ. 40:28) አንተም ኃያል የሆነው የይሖዋ እጅ፣ ያጋጠመህን ችግር እንድትወጣ እንዴት እንደረዳህ በግል ሕይወትህ ተመልክተህ ታውቅ ይሆናል።—ኢሳ. 41:10, 13፤ w17.07 18-19 አን. 6-8

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 24

ለጋስ ሰው ይባረካል።—ምሳሌ 22:9

በሌላ አገር የሚኖር አንድ ስሪ ላንካዊ ወንድም፣ በአገሩ በሚገኘው የግል ይዞታው ላይ የጉባኤ እንዲሁም ትላልቅ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ እንዲሁም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች እንዲኖሩበት ፈቅዷል። ወንድም ይህን በማድረጉ የሚያጣው ገንዘብ እንዳለ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ይህ ዝግጅት በስሪ ላንካ ያሉትን አነስተኛ ገቢ ያላቸው ወንድሞች በጣም ይጠቅማቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በነፃነት መስበክ በማይችሉበት አገር፣ ወንድሞች ቤታቸው እንደ ስብሰባ አዳራሽ እንዲያገለግል ይፈቅዳሉ፤ ይህም በርካታ አቅኚዎችንና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሌሎች ወንድሞች ጨምሮ ሁሉም አስፋፊዎች ብዙ ወጪ የማያስወጣ መሰብሰቢያ ቦታ እንዲያገኙ ያደርጋል። ለመንግሥቱ ሥራ አዘውትራ መዋጮ የምታደርግ አንዲት እህት ያገኘችውን በረከት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ ‘በቁሳዊ ነገሮች ለጋስ መሆኔ፣ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በሕይወቴ ውስጥ አስገራሚ ለውጦችን እንድመለከት አድርጎኛል። ለጋስ መሆኔ ከሌሎች ጋር የተሻለ ግንኙነት እንዲኖረኝ ረድቶኛል። ይበልጥ ይቅር ባይና ታጋሽ እንድሆን አስችሎኛል፤ እንዲሁም ቅር የሚያሰኙ ነገሮች ሲያጋጥሙኝ ችሎ ማለፍና የሚሰጠኝን ምክር መቀበል ይበልጥ ቀላል ሆኖልኛል።’ w17.07 9 አን. 9-10

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 25

ይሖዋ ሰይጣንን “እነሆ፣ ያለው ነገር ሁሉ በእጅህ ነው። እሱን ራሱን ግን እንዳትነካው!” አለው።—ኢዮብ 1:12

ኢዮብ መከራ ደርሶበት የነበረው ለምን እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ተረድቶ የነበረ ቢሆን እንኳ ‘አምላክ ይህን ያህል እንድሠቃይ የፈቀደው ለምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ አልፎ አልፎ ወደ አእምሮው ሊመጣ ይችላል። ኢዮብ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ይፈጠሩበት ከነበረ አምላክ የሰጠውን ምክር ማስታወሱ እንደሚጠቅመው ጥርጥር የለውም። ይህን ማድረጉ ተገቢውን አመለካከት እንዲይዝና መጽናናት እንዲችል ይረዳዋል። (መዝ. 94:19 ግርጌ) እኛም ብንሆን የኢዮብን ታሪክ መመርመራችን ተገቢውን አመለካከት እንድንይዝና መጽናኛ እንድናገኝ ያስችለናል። ይሖዋ ይህ ታሪክ እስከ ዘመናችን ተጠብቆ እንዲቆይ ያደረገው “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን” አስቦ ነው። (ሮም 15:4) ከዚህ ታሪክ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ዋነኛው ትምህርት ይህ ነው፦ በራሳችን ሕይወት ከልክ በላይ ተጠምደን አንገብጋቢ የሆነውን ነገር ይኸውም የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት የመረጋገጡን ጉዳይ እንዳንዘነጋ መጠንቀቅ አለብን። በተጨማሪም ኢዮብ እንዳደረገው ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም ታማኝነታችንን በመጠበቅ የይሖዋን ሉዓላዊነት እንደምንደግፍ ማሳየት ይኖርብናል። w17.06 24 አን. 9፤ 25 አን. 13-14

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 26

ለብቻችን ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ እንሂድና በዚያ ትንሽ አረፍ በሉ።—ማር. 6:31

ኢየሱስ እረፍት የማድረግን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ነበር። በአንድ ወቅት በስብከቱ ሥራ ላይ ረዘም ያለ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ፣ ለደቀ መዛሙርቱ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ነገራቸው። በእርግጥም መዝናኛ አስፈላጊ ነገር ነው። ሆኖም መዝናናት በሕይወታችን ውስጥ ዋናውን ቦታ እንዳይዝ መጠንቀቅ ያስፈልገናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብዙዎች “ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ” የሚል አመለካከት ነበራቸው። (1 ቆሮ. 15:32) ዛሬም እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት በብዙ የዓለም ክፍሎች በስፋት ይታያል። ለመዝናኛ ያለን አመለካከት ሚዛናዊ መሆን አለመሆኑን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? በአንድ ሳምንት ውስጥ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን በማከናወን ምን ያህል ሰዓት እንዳሳለፍን መመዝገብ እንችላለን። ቀጥሎ ደግሞ በዚያው ሳምንት በመዝናኛ ይኸውም በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች በመካፈል፣ ቴሌቪዥን በመመልከት ወይም የቪዲዮ ጌም በመጫወት ያሳለፍነውን ሰዓት እንመዝግበው፤ ከዚያም በመዝናኛ ያሳለፍነውን ሰዓት ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ካዋልነው ሰዓት ጋር እናወዳድረው። በጊዜ አጠቃቀማችን ረገድ ለውጥ ማድረግ ያስፈልገን ይሆን?—ኤፌ. 5:15, 16፤ w17.05 24-25 አን. 11-13

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 27

መንግሥተ ሰማያት ጥሩ ዕንቁ ከሚፈልግ ተጓዥ ነጋዴ ጋር ይመሳሰላል።—ማቴ. 13:45

ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው ነጋዴ በጣም ውብ የሆነ ዕንቁ ያገኘ ሲሆን ይህን ውድ ዕንቁ ለመግዛት ሲል ያለውን ሁሉ ለመሸጥ ፈቃደኛ ሆኗል። ይህ ነጋዴ ዕንቁውን ምን ያህል ከፍ አድርጎ እንደተመለከተው መገመት ትችላለህ? ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው እውነት በጣም ውድ በሆነው ዕንቁ ሊመሰል ይችላል። ነጋዴው ያንን ዕንቁ የወደደውን ያህል እኛም የአምላክን መንግሥት የምንወድ ከሆነ የመንግሥቱ ተገዢዎች ለመሆን ስንል ማንኛውንም ነገር ለመተው ፈቃደኛ እንሆናለን። (ማር. 10:28-30) ለምሳሌ ዘኬዎስ የቀረጥ ሰብሳቢዎች አለቃ የነበረ ሲሆን ሰዎችን በመበዝበዝ ብዙ ሀብት አካብቶ ነበር። (ሉቃስ 19:1-9) ይሁንና ይህ ኃጢአተኛ ሰው ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ሲሰብክ ሰማ፤ በዚህ ጊዜ የሰማው ነገር ያለውን ውድ ዋጋ ስለተገነዘበ አፋጣኝ እርምጃ ወሰደ። እንዲህ ብሏል፦ “ጌታ ሆይ፣ ካለኝ ሀብት ግማሹን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ከሰው የቀማሁትንም ሁሉ አራት እጥፍ እመልሳለሁ።” ዘኬዎስ ተገቢ ባልሆነ መንገድ የሰበሰበውን ገንዘብ የመለሰ ከመሆኑም ሌላ ለቁሳዊ ነገሮች ያለውን አመለካከት ለማስተካከል ፈቃደኛ ሆኗል። w17.06 10 አን. 3-5

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 28

ልጆቼ በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የበለጠ ደስታ የለኝም።—3 ዮሐ. 4

ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲረዱላቸው ኃላፊነት የሰጧቸው ክርስቲያኖች ምንጊዜም ቢሆን ልጆቹ ለወላጆቻቸው ያላቸው አክብሮት እንዲጨምር መርዳትና ስለ ወላጆቻቸው መልካም ነገር መናገር አለባቸው፤ የእነሱን ኃላፊነት ለመውሰድ መሞከር የለባቸውም። ከዚህም ሌላ እነዚህ ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥም ሆነ ከጉባኤው ውጭ ባሉ ሰዎች ዘንድ ከሥነ ምግባር አንጻር ጥያቄ የሚያስነሳ ምንም ነገር ላለማድረግ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። (1 ጴጥ. 2:12) በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆች ለልጆቻቸው መንፈሳዊ ሥልጠና የመስጠቱን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ለሌሎች መተው የለባቸውም። ወላጆች፣ ሌሎች ክርስቲያኖች ለልጆቻቸው የሚሰጡትን እርዳታ መከታተል እንዲሁም እነሱ ራሳቸው ልጆቻቸውን ማስተማራቸውን መቀጠል አለባቸው። ወላጆች የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ጸልዩ፤ እንዲሁም አቅማችሁ የሚፈቅደውን ሁሉ አድርጉ። (2 ዜና 15:7) ከራሳችሁ ፍላጎት ይልቅ ልጃችሁ ከይሖዋ ጋር የሚኖረውን ወዳጅነት አስቀድሙ። የአምላክ ቃል የልጃችሁን ልብ እንዲነካው ለማድረግ የምትችሉትን ያህል ጣሩ። ልጃችሁ፣ የይሖዋ አገልጋይ ሊሆን እንደሚችል ምንጊዜም እምነት ይኑራችሁ። w17.05 12 አን. 19-20

እሁድ፣ ታኅሣሥ 29

የአባቶቼን ርስት ለአንተ መስጠት በይሖዋ ፊት ተገቢ ስላልሆነ ፈጽሞ የማላስበው ነገር ነው።—1 ነገ. 21:3

እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር። አንድ ሰው በሞት በሚያስቀጣ ወንጀል ተከሷል። በዚህ ሰው ላይ ፍርድ የተበየነው፣ የማይረቡ እንደሆኑ የሚታወቁ ሰዎች የሰጡትን የሐሰት ምሥክርነት መሠረት በማድረግ ነው፤ ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ ይህን ማወቃቸው ምን ያህል እንደሚያስደነግጣቸውና እንደሚያሳዝናቸው መገመት ይቻላል። ፍትሕን የሚወዱ ግለሰቦች፣ ይህ ንጹሕ ሰውና ልጆቹ ሲገደሉ በማየታቸው ስሜታቸው በጣም እንደሚረበሽ ጥያቄ የለውም። ይህ ታሪክ ልበ ወለድ አይደለም። በእስራኤል ንጉሥ በአክዓብ ዘመን ይኖር የነበረ ናቡቴ የተባለ የይሖዋ ታማኝ አገልጋይ ያጋጠመው ሁኔታ ነው። (1 ነገ. 21:11-13፤ 2 ነገ. 9:26) ንጉሥ አክዓብ የናቡቴን የወይን እርሻ ለመግዛት አሊያም የተሻለ የወይን እርሻ ቦታ በምትኩ ለናቡቴ ለመስጠት ፈልጎ ነበር፤ ናቡቴ ግን በዚህ አልተስማማም። ለምን? ናቡቴ የአክዓብን ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነው፣ ይሖዋ የአንድ ነገድ ውርስ ለዘለቄታው እንዳይሸጥ ለእስራኤል ብሔር የሰጠውን ሕግ ስለሚያውቅ ነው። (ዘሌ. 25:23፤ ዘኁ. 36:7) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ናቡቴ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ነበረው። w17.04 23 አን. 1፤ 24 አን. 4

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 30

ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ክፉዎች አይኖሩም፤ በቀድሞ ቦታቸው ትፈልጋቸዋለህ፤ እነሱ ግን በዚያ አይገኙም።—መዝ. 37:10

ክፉ ሰዎች ሲጠፉ በምድር ላይ የሚቀሩት እነማን ይሆናሉ? ይሖዋ “የዋሆች . . . ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል” የሚል አስደሳች ተስፋ ሰጥቷል። በዚሁ መዝሙር ላይ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” የሚል ሐሳብ ሰፍሮ እናገኛለን። (መዝ. 37:11, 29) “የዋሆች” እና “ጻድቃን” የተባሉት እነማን ናቸው? የዋሆች የተባሉት ይሖዋ የሚሰጠውን ትምህርትና መመሪያ በትሕትና የሚቀበሉ ሰዎች ናቸው፤ ጻድቃን የተባሉት ደግሞ በይሖዋ አምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ የሚወዱ ሰዎች ናቸው። በዛሬው ጊዜ የክፉዎች ቁጥር ከጻድቃን በእጅጉ ይበልጣል። ይሁንና በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለ ንጽጽር አይኖርም፤ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ በምድር ላይ የሚኖሩት የዋሆችና ጻድቃን ብቻ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ምድርን ወደ ገነትነት ይቀይራሉ! w17.04 10-11 አን. 5-6

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 31

ለመርዳት የሚያስችል አቅም ካለህ . . . መልካም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አትበል።—ምሳሌ 3:27

“የአምላክ ፍቅር” አንዳችን ለሌላው ፍቅር እንድናሳይ ግድ ይለናል፤ በተለይ ደግሞ አስከፊ ሁኔታዎች ላጋጠሟቸው ወንድሞቻችን ይህን ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። (1 ዮሐ. 3:17, 18) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሁዳ ረሃብ በተከሰተ ጊዜ በይሁዳ የነበሩትን ክርስቲያኖች ለመርዳት የእምነት ባልንጀሮቻቸው ዝግጅት አደረጉ። (ሥራ 11:28, 29) ሐዋርያው ጳውሎስና ጴጥሮስም፣ ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዲያሳዩ ምክር ሰጥተዋል። (ሮም 12:13፤ 1 ጴጥ. 4:9) ክርስቲያኖች ሊጎበኟቸው የሚመጡ ወንድሞችን እንዲቀበሉ የሚጠበቅባቸው ከሆነ በሕይወታቸው ላይ አደጋ የተጋረጠባቸውን ወይም በእምነታቸው ምክንያት ስደት የደረሰባቸውን የእምነት አጋሮቻቸውንማ ሊቀበሏቸው እንደሚገባ ምንም ጥያቄ የለውም! በቅርቡ በምሥራቃዊ ዩክሬን በተነሳው ግጭትና ስደት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ሕይወታቸውን ማጣታቸው የሚያሳዝን ነው። አብዛኞቹን ግን ዩክሬን ውስጥ በሌሎች ቦታዎችና በሩሲያ ያሉ መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው ተቀብለዋቸዋል። በሁለቱም አገሮች ውስጥ የሚገኙት ስደተኛ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ‘የዓለም ክፍል እንዳልሆኑ’ በማስታወስ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ የገለልተኝነት አቋማቸውን ጠብቀዋል፤ እንዲሁም “የአምላክን ቃል ምሥራች” በቅንዓት መስበካቸውን ቀጥለዋል።—ዮሐ. 15:19፤ ሥራ 8:4፤ w17.05 4 አን. 6-7

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ