ኅዳር
ዓርብ፣ ኅዳር 1
ፈሪሃ አምላክ በጎደለው መንገድ መኖርና ዓለማዊ ምኞቶችን መከተል ትተን . . . ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ፣ በጽድቅና ለአምላክ በማደር [እንኑር]።—ቲቶ 2:12
ራስን መገሠጽ፣ በባሕርይና በአስተሳሰብ ረገድ ማሻሻያ ለማድረግ ሲባል ራስን መቆጣጠርን ይጨምራል። በተፈጥሯችን ራሳችንን የመገሠጽ ዝንባሌ የለንም፤ በመሆኑም እንዲህ ያለውን ልማድ ለማዳበር ሥልጠና ያስፈልገናል። ወላጆች ልጆቻቸውን በትዕግሥትና ቀጣይነት ባለው መንገድ “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” ሲያሠለጥኗቸው ልጆቻቸው ጥበብና ራስን የመገሠጽ ልማድ እንዲያዳብሩ እየረዷቸው ነው። (ኤፌ. 6:4) አዋቂ ከሆኑ በኋላ ስለ ይሖዋ ከተማሩ ሰዎች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሰዎች በተወሰነ መጠንም ቢሆን ራሳቸውን የመገሠጽ ልማድ አዳብረው ሊሆን ይችላል። ሆኖም አንድ አዲስ ደቀ መዝሙር በመንፈሳዊ ሁኔታ ሲታይ ገና ሕፃን ነው ሊባል ይችላል። ክርስቶስን የሚመስለውን “አዲሱን ስብዕና” መልበስን እየተማረ ሲሄድ ግን ቀስ በቀስ ወደ ጉልምስና ያድጋል። (ኤፌ. 4:23, 24) አንድ ሰው ወደ ጉልምስና ደረጃ ሲደርስ ከሚያዳብራቸው አስፈላጊ ነገሮች መካከል አንዱ ደግሞ ራስን የመገሠጽ ችሎታ ነው። w18.03 29 አን. 3-4
ቅዳሜ፣ ኅዳር 2
የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል አዳብሩ።—ሮም 12:13
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሁሉ ከመንፈሳዊው ማዕድ አብረውን እንዲካፈሉ እንደተጋበዙ እንግዶች አድርገን እንቀበላቸዋለን። ጋባዦቹ ይሖዋ እና ድርጅቱ ናቸው። (ሮም 15:7) አዲሶች ወደ ስብሰባዎቻችን ሲመጡ እኛም እንደ ጋባዥ ሆነን እነሱን የማስተናገድ መብት እናገኛለን። እንግዲያው እነዚህ ሰዎች አለባበሳቸው ወይም የፀጉር አበጣጠራቸው ምንም ዓይነት ቢሆን ሞቅ ያለ አቀባበል ልናደርግላቸው ይገባል። (ያዕ. 2:1-4) አንድ እንግዳ አጠገቡ ወንድሞች እንደሌሉ ካስተዋልን አብሮን እንዲቀመጥ ልንጋብዘው እንችላለን። ፕሮግራሙን እንዲከታተል ብንረዳው እንዲሁም የሚነበቡትን ጥቅሶች አውጥተን ብናሳየው ደስ እንደሚለው የታወቀ ነው። “የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል [ማዳበር]” ከምንችልባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ ይህ ነው። የሕዝብ ተናጋሪዎች፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና አንዳንድ ጊዜም የቅርንጫፍ ቢሮው ተወካዮች ወደ ጉባኤያችን ሲመጡ እነዚህን ወንድሞች የማስተናገድ አጋጣሚ እናገኛለን። (3 ዮሐ. 5-8) ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ምግብ ወይም ሻይ ቡና መጋበዝ ነው። አንተስ እንዲህ ማድረግ ትችል ይሆን? w18.03 15 አን. 5, 7
እሁድ፣ ኅዳር 3
እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?—ሥራ 8:36
ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረን አንድ አይሁዳዊ ምሳሌ እንመልከት። ይህ ሰው የተወለደው፣ ራሱን ለአምላክ በወሰነ ብሔር ውስጥ ነው። ይሁንና በወቅቱ አይሁዳውያን ከይሖዋ ጋር የነበራቸውን ልዩ ዝምድና አጥተው ነበር። ግለሰቡ ለአይሁዳውያን ሃይማኖታዊ ወጎች ከፍተኛ ቅንዓት ነበረው፤ ሆኖም ከዚያ የላቀ ነገር እንዳለ ተማረ። ለዚህ ሰው የመሠከረለት ከሞት የተነሳውና ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ታዲያ ይህ ግለሰብ ምን ምላሽ ሰጠ? ሐናንያ የተባለ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ያደረገለትን እርዳታ በደስታ ተቀበለ። ከዚያ በኋላ ስለተከናወነው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “ተነስቶ ተጠመቀ” ይላል። (ሥራ 9:17, 18፤ ገላ. 1:14) ይህ ሰው ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ የተጠራው አይሁዳዊው ሳኦል እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን። ሆኖም እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባ አንድ ነገር አለ፤ ጳውሎስ፣ ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ ስለሚጫወተው ሚና እውነቱን እንደተገነዘበ እርምጃ ወስዷል። ጳውሎስ ወዲያውኑ ተጠምቋል። (ሥራ 22:12-16) በዛሬው ጊዜ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳሉ። w18.03 5-6 አን. 9-11
ሰኞ፣ ኅዳር 4
እንደ ሥጋውያን ሰዎች እንጂ እንደ መንፈሳውያን ሰዎች ላነጋግራችሁ አልቻልኩም።—1 ቆሮ. 3:1
የያዕቆብ ሕይወት አስቸጋሪ ነበር። ሥጋዊ አስተሳሰብ የነበረውን ወንድሙን ኤሳውን ችሎ መኖር ቀላል አልነበረም፤ በዚያ ላይ ደግሞ ኤሳው ሊገድለው ይፈልግ ነበር። ያዕቆብ ይህም እንዳይበቃው፣ በተደጋጋሚ ጊዜ ሊያታልለው የሞከረው አማቹ የሚያደርስበትን በደል መቋቋም ነበረበት። በዙሪያው ያሉት ሰዎች “ዓለማዊ” ቢሆኑም ያዕቆብ ግን መንፈሳዊ ሰው ነበር። (1 ቆሮ. 2:14-16) ይህ የአምላክ አገልጋይ፣ ይሖዋ ለአብርሃም በገባው ቃል ላይ እምነት ነበረው፤ በተጨማሪም ቤተሰቡ በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ የሚጫወተው ልዩ ሚና እንዳለ ስለተገነዘበ ቤተሰቡን ለመንከባከብ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል። (ዘፍ. 28:10-15) ያዕቆብ ለአምላክ ዓላማና ለመሥፈርቶቹ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ኤሳው ጥቃት ሊሰነዝርበት እንደሆነ በተሰማው ወቅት ወደ አምላክ እንዲህ ሲል ጸልዮአል፦ “እንድታድነኝ እለምንሃለሁ፤ . . . አንተው ራስህ ‘በእርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፤ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሳ ሊቆጠር እንደማይችል የባሕር አሸዋ አደርገዋለሁ’ ብለኸኛል።” (ዘፍ. 32:6-12) ያዕቆብ፣ ይሖዋ በገባው ቃል ላይ እምነት እንደነበረው እንዲሁም ከአምላክ ፈቃድና ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ ይፈልግ እንደነበር በግልጽ ማየት ይቻላል። w18.02 20 አን. 9-10
ማክሰኞ፣ ኅዳር 5
[እሱ] በንጹሕ አቋም የሚመላለስ ቅን ሰው እንዲሁም አምላክን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ነው።—ኢዮብ 1:8
ኢዮብ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ለውጥ አጋጥሞታል። ከፈተናው በፊት “በምሥራቅ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ሰው” ነበር። (ኢዮብ 1:3) እንዲሁም ባለጸጋ፣ የታወቀና እጅግ የተከበረ ሰው ነበር። (ኢዮብ 29:7-16) ኢዮብ ከፍ ያለ ቦታ የነበረው ቢሆንም ለራሱ የተጋነነ አመለካከት አልነበረውም፤ እንዲሁም አምላክ እንደማያስፈልገው አልተሰማውም። እንዲያውም ይሖዋ “አገልጋዬ” ብሎ ጠርቶታል። ሰይጣን ጭካኔ የተሞላባቸው ጥቃቶች በኢዮብ ላይ በማዥጎድጎድ ኢዮብ መከራ የሚያደርስበት አምላክ እንደሆነ እንዲያስብ ለማድረግ ሞክሯል። (ኢዮብ 1:13-21) ከዚያም ሦስቱ የሐሰት አጽናኞች ወደ እሱ ቀርበው አምላክ የእጁን እየሰጠው እንዳለ በሚያስመስሉ ቅስም የሚሰብሩ ቃላት ጥቃት ሰነዘሩበት! (ኢዮብ 2:11፤ 22:1, 5-10) ይሁንና ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ጠብቋል። ፈተናው ካበቃ በኋላ ይሖዋ ለኢዮብ ከዚያ በፊት የነበረውን ሁሉ እጥፍ አድርጎ የሰጠው ሲሆን በዕድሜው ላይ 140 ዓመት ጨምሮለታል። (ያዕ. 5:11) በእነዚያ ዓመታት ሁሉ ኢዮብ ይሖዋን በሙሉ ልቡ ማምለኩን ቀጥሏል። w18.02 6 አን. 16፤ 7 አን. 18
ረቡዕ፣ ኅዳር 6
ሰዎች . . . ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ . . . በኩራት የተወጠሩ [ይሆናሉ]።—2 ጢሞ. 3:2, 4
ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች እና በኩራት የተወጠሩ ሰዎች፣ ሁልጊዜ ሌሎች እንዲያደንቋቸውና ከፍ ያለ ቦታ እንዲሰጧቸው ይፈልጋሉ። አንድ ምሁር፣ እብሪተኛ ስለሆነ ሰው ሲናገሩ “በልቡ ውስጥ ትንሽ መሠዊያ ሠርቶ ለራሱ ተንበርክኮ ይሰግዳል” ብለዋል። ከልክ ያለፈ ኩራት በጣም የሚጠላ ባሕርይ በመሆኑ፣ ኩሩ የሆኑ ሰዎችም እንኳ እንዲህ ያለ ባሕርይ ያላቸውን ሰዎች እንደማይወዱ አንዳንዶች ሲናገሩ ይሰማል። ይሖዋ ኩራትን እንደሚጸየፍ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። በተጨማሪም ‘ትዕቢተኛ ዓይንን’ እንደሚጠላ ተገልጿል። (ምሳሌ 6:16, 17) ኩራት ወደ አምላክ እንዳንቀርብ እንቅፋት ይሆናል። (መዝ. 10:4) ይህ ባሕርይ የዲያብሎስ መገለጫ ነው። (1 ጢሞ. 3:6) የሚያሳዝነው ግን ታማኝ ከሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹም በኩራት ወጥመድ ወድቀዋል። የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ዖዝያ ለዓመታት ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል። “ይሁን እንጂ ዖዝያ በበረታ ጊዜ ለጥፋት እስኪዳረግ ድረስ ልቡ ታበየ፤ . . . ዕጣን ለማጠን ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ በመግባት በአምላኩ በይሖዋ ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈጸመ።” ንጉሥ ሕዝቅያስም በአንድ ወቅት ልቡ ታብዮ ነበር።—2 ዜና 26:16፤ 32:25, 26፤ w18.01 28 አን. 4-5
ሐሙስ፣ ኅዳር 7
እያንዳንዱ . . . አቅሙ በሚፈቅድለት መጠን የተወሰነ ገንዘብ ያስቀምጥ።—1 ቆሮ. 16:2
ከጥንት ዘመን ጀምሮ የይሖዋ ሕዝቦች የእሱን ሥራ ለመደገፍ መዋጮ ያደርጉ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። ለአንድ የተለየ ፕሮጀክት መዋጮ ያደረጉባቸው ጊዜያትም ነበሩ። (ዘፀ. 35:5፤ 2 ነገ. 12:4, 5፤ 1 ዜና 29:5-9) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩ ወንድሞች በወቅቱ ተከስቶ በነበረው ረሃብ የተነሳ በይሁዳ የሚኖሩ ወንድሞች ችግር ላይ እንደወደቁ ባወቁ ጊዜ “አቅማቸው በፈቀደ መጠን አዋጥተው . . . እርዳታ ለመላክ [ወስነዋል]።” (ሥራ 11:27-30) እርግጥ ነው፣ የአምላክ ሕዝቦች እነዚህን መዋጮዎች ያደረጉት በተለያየ መንገድ ካገኟቸው ቁሳዊ ነገሮች ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች እንደ ርስት ወይም ቤት ያሉ ንብረቶችን በመሸጥ ገንዘቡን ለሐዋርያት ይሰጡ ነበር። ከዚያም ሐዋርያቱ በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ ችግር ላይ ለወደቁ ክርስቲያኖች ያከፋፍላሉ። (ሥራ 4:34, 35) ሌሎች ደግሞ የተወሰነ ገንዘብ ለይተው በማስቀመጥና በቋሚነት መዋጮ በማድረግ ሥራውን ይደግፉ ነበር። በዚህ መንገድ ሀብታም ድሃ ሳይል ሁሉም የይሖዋን ሥራ ለመደገፍ የበኩሉን ድርሻ ያበረክት ነበር።—ሉቃስ 21:1-4፤ w18.01 18 አን. 7፤ 19 አን. 9
ዓርብ፣ ኅዳር 8
ወንዶች ልጆች ይደክማሉ፤ ደግሞም ይዝላሉ።—ኢሳ. 40:30
ምንም ዓይነት ችሎታ ቢኖረን በራሳችን ጥንካሬ ልናከናውን የምንችለው ነገር ውስን ነው። ይህ ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባ ሐቅ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙ ነገሮችን ማከናወን ይችል የነበረ ቢሆንም የሚፈልገውን ሁሉ እንዳያደርግ የሚያግዱት ነገሮች ነበሩ። ይህን ሁኔታ በተመለከተ ወደ አምላክ ሲጸልይ ያገኘው ምላሽ “ኃይሌ ፍጹም የሚሆነው በምትደክምበት ጊዜ ነው” የሚል ነበር። ጳውሎስ፣ ይሖዋ ምን ሊለው እንደፈለገ ገብቶታል። “ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ” በማለት የተናገረውም ለዚህ ነው። (2 ቆሮ. 12:7-10) ይሁንና ጳውሎስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ጳውሎስ ከእሱ በላይ ኃይል ካለው አካል እርዳታ ካላገኘ በቀር ማከናወን የሚችለው ነገር ውስን እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ሐዋርያው በሚደክምበት ጊዜ የሚያስፈልገውን ኃይል የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ሊሰጠው ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ በራሱ ጥንካሬ ፈጽሞ ሊያከናውን የማይችላቸውን ነገሮች እንዲያከናውን የአምላክ መንፈስ ኃይል ይሰጠዋል። ለእኛም እንዲሁ ሊያደርግልን ይችላል። በእርግጥም ይሖዋ፣ ቅዱስ መንፈሱን ሲሰጠን ብርቱዎች መሆን እንችላለን! w18.01 9 አን. 8-9
ቅዳሜ፣ ኅዳር 9
ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ እንድታገኝ የሚያስችሉህን ቅዱሳን መጻሕፍት ከጨቅላነትህ ጀምሮ አውቀሃል።—2 ጢሞ. 3:15
ልጃችሁ የመጠመቅ ፍላጎት ካለው የይሖዋ ድርጅት ለወላጆች ባዘጋጃቸው መሣሪያዎች በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋችኋል። እንዲህ ማድረጋችሁ፣ ራስን ለይሖዋ መወሰን እና መጠመቅ የሚያስከትላቸውን ኃላፊነቶችና የሚያስገኛቸውን በረከቶች ለልጃችሁ ለማስገንዘብ ይረዳችኋል። ወላጆች፣ ልጆቻችሁን “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” የማሳደግ መብት ተሰጥቷችኋል፤ ይህ ግን ከባድ ኃላፊነትም ያስከትላል። (ኤፌ. 6:4) ይህን ማድረግ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ማስተማርን ብቻ ሳይሆን ልጆቹ የተማሩትን ነገር አምነው እንዲቀበሉ መርዳትንም ይጨምራል። ደግሞም ልጆቹ የሚማሩትን ነገር በሚገባ ካመኑበት ራሳቸውን ለይሖዋ ለመወሰንና እሱን በሙሉ ልባቸው ለማገልገል ይነሳሳሉ። የይሖዋ ቃልና መንፈሱ እንዲሁም እናንተ የምታደርጉት ጥረት፣ ልጆቻችሁ “ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ” እንዲያገኙ የሚረዳቸው እንዲሆን ምኞታችን ነው! w17.12 22 አን. 17, 19
እሁድ፣ ኅዳር 10
በዘመኑ ፍጻሜ ዕጣ ፋንታህን ለመቀበል ትነሳለህ።—ዳን. 12:13
በወቅቱ 100 ዓመት ገደማ የሆነው ዳንኤል ወደ ሕይወቱ መገባደጃ እየተቃረበ ነበር። ዳንኤል ትንሣኤ አግኝቶ እንደገና በሕይወት ይኖር ይሆን? እንዴታ! በዳንኤል መጽሐፍ መጨረሻ ላይ አምላክ “አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ። ታርፋለህ” የሚል ማረጋገጫ ለነቢዩ እንደሰጠው ተገልጿል። በዕድሜ የገፋው ዳንኤል ሙታን እንደሚያርፉ እንዲሁም “በመቃብር . . . ዕቅድ፣ እውቀትም ሆነ ጥበብ” እንደሌለ ያውቅ ነበር። ዳንኤልም ወደ መቃብር መሄዱ አይቀርም። (መክ. 9:10) ሆኖም መጨረሻው እዚያው መቅረት አይደለም። ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስደሳች ተስፋ ሰጥቶታል። ለነቢዩ ዳንኤል የተነገረው መልእክት በመቀጠል በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ይዟል። ይህ መቼ እንደሚሆን ዳንኤል የሚያውቀው ነገር አልነበረም። አንድ ቀን በሞት ማንቀላፋቱ እንደማይቀር ያውቃል። ይሁን እንጂ ዳንኤል ወደፊት ‘ዕጣ ፋንታውን ለመቀበል እንደሚነሳ’ የተነገረው መሆኑ፣ እሱ ከሞተ ከረጅም ጊዜ በኋላ ትንሣኤ እንደሚኖር በግልጽ ቃል የተገባ ያህል ነው። ይህ የሚሆነው “በዘመኑ ፍጻሜ” ነው። w17.12 7 አን. 17-18
ሰኞ፣ ኅዳር 11
ማንም ሰው አንድ ግለሰብ በሚሰጠው ምሥክርነት ብቻ በሞት መቀጣት የለበትም።—ዘኁ. 35:30
ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ሽማግሌዎችን የእሱን የላቁ የፍትሕ መሥፈርቶች እንዲከተሉ አሳስቧቸዋል። በመጀመሪያ፣ ሽማግሌዎቹ የተፈጸመውን ነገር በትክክል ለማወቅ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከዚያም ሳያውቅ ነፍስ ያጠፋው ሰው ምሕረት ይገባው እንደሆነ ለመወሰን በሚሞክሩበት ጊዜ የነፍሰ ገዳዩን ዝንባሌ፣ ለሟቹ ያለውን አመለካከትና ከዚያ በፊት ያደረጋቸውን ነገሮች ግምት ውስጥ ያስገባሉ። ሽማግሌዎቹ የአምላክ ዓይነት ፍትሕ ለማሳየት ሲሉ ግለሰቡ፣ የሰው ነፍስ ያጠፋው “በጥላቻ ተነሳስቶ” ወይም “ተንኮል አስቦ” መሆን አለመሆኑን ያጣራሉ። (ዘኁ. 35:20-24) የምሥክሮችን ቃል የሚቀበሉ ከሆነ ደግሞ ግለሰቡ ነፍስ ያጠፋው ሆን ብሎ እንደሆነ ለመፍረድ ቢያንስ የሁለት ሰዎች ምሥክርነት ያስፈልጋል። ሽማግሌዎቹ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ትክክለኛውን መረጃ ካገኙ በኋላ፣ ግለሰቡ በፈጸመው ድርጊት ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ የሰውየውን ማንነት ይኸውም ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ማጤን ይኖርባቸዋል። ሽማግሌዎቹ፣ ማስተዋል ማለትም ከአንድ ሁኔታ በስተ ጀርባ ያለውን ነገር የመመልከትና ጉዳዩን ጠለቅ ብሎ የማየት ችሎታ ያስፈልጋቸዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ያስፈልጋቸዋል፤ ይህ መንፈስ የሚያደርጉት ውሳኔ መለኮታዊ ማስተዋል፣ ምሕረትና ፍትሕ የተንጸባረቀበት እንዲሆን ይረዳቸዋል።—ዘፀ. 34:6, 7፤ w17.11 16 አን. 13-14
ማክሰኞ፣ ኅዳር 12
በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል።—1 ጢሞ. 4:15
ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኘንበት ወቅት ውድ የሆኑ አንዳንድ እውነቶችን ተምረናል። ይሖዋ ፈጣሪያችንና ሕይወት ሰጪያችን እንደሆነ እንዲሁም ለሰው ልጆች ዓላማ እንዳለው ተምረናል። በተጨማሪም አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ ከኃጢአትና ከሞት ነፃ እንድንወጣ ሲል ልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ እንደሰጠን ተምረናል። ከዚህም ሌላ፣ የአምላክ መንግሥት መከራን በሙሉ እንደሚያስወግድ እንዲሁም በመንግሥቱ ግዛት ሥር ሆነን በሰላምና በደስታ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዳለን ተገንዝበናል። (ዮሐ. 3:16፤ ራእይ 4:11፤ 21:3, 4) አንዳንድ ጊዜ ስለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ወይም ጥቅስ ባለን ግንዛቤ ላይ ማስተካከያ ይደረግ ይሆናል። በዚህ ጊዜ የቀረበውን አዲስ ትምህርት ጊዜ ወስደን በጥንቃቄ ማጥናትና ባጠናነው ላይ ማሰላሰላችን ተገቢ ነው። (ሥራ 17:11) የተደረጉትን ትላልቅ ማስተካከያዎች ብቻ ሳይሆን በቀድሞውና በአዲሱ ግንዛቤያችን መካከል ያሉትን ጥቃቅን የሚመስሉ ልዩነቶች ጭምር ለመረዳት ጥረት እናደርጋለን። በዚህ መንገድ አዲሱን እውነት ‘በከበረ ሀብት ማከማቻችን’ ውስጥ ማስቀመጥ እንችላለን። w17.06 12-13 አን. 15-16
ረቡዕ፣ ኅዳር 13
በምድር ያሉትን የአካል ክፍሎቻችሁን ግደሉ፤ እነሱም የፆታ ብልግና፣ ርኩሰት፣ ልቅ የሆነ የፍትወት ስሜት . . . ናቸው።—ቆላ. 3:5
የይሖዋን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንድንጥስ በሚፈትኑ ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን የተለየ ጥንቃቄ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ የሚጠናኑ ክርስቲያኖች እጅ ለእጅ መያያዝን፣ መሳሳምን ወይም ሰዎች በሌሉበት አብሮ መሆንን በተመለከተ፣ ገና መጠናናት ሲጀምሩ ግልጽ የሆኑ ገደቦችን ማስቀመጣቸው ጥበብ ነው። (ምሳሌ 22:3) አንድ ክርስቲያን ለሥራ ወደ ሌላ አካባቢ በሚሄድበት ወይም ከተቃራኒ ፆታ ጋር በሚሠራበት ወቅትም የሥነ ምግባር ፈተና ሊያጋጥመው ይችላል። (ምሳሌ 2:10-12, 16) በተጨማሪም በምናዝንበት ወይም ብቸኝነት በሚሰማን ጊዜ በሥነ ምግባር ፈተና ላለመውደቅ መጠንቀቅ ያስፈልገናል። በዚህ ወቅት ስሜታችንን የሚረዳልንና የሚያስብልን ሰው በጣም ከመፈለጋችን የተነሳ ትኩረት የሚሰጠንን ማንኛውንም ሰው ለመቅረብ እንፈተን ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ የይሖዋንና የሕዝቦቹን እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርግ።—መዝ. 34:18፤ ምሳሌ 13:20፤ w17.11 26 አን. 4-5
ሐሙስ፣ ኅዳር 14
ለራሳችሁ የመማጸኛ ከተሞችን ምረጡ።—ኢያሱ 20:2
በጥንቷ እስራኤል ውስጥ የሚፈጸሙ ከነፍስ ማጥፋት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይሖዋ በጣም አክብዶ ይመለከታቸው ነበር። ሆን ብሎ ነፍስ ያጠፋን ግለሰብ፣ የሟቹ የቅርብ ዘመድ የሚገድለው ሲሆን ይህ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ደም ተበቃይ’ ተብሎ ተጠርቷል። (ዘኁ. 35:19) እንዲህ ዓይነት እርምጃ የሚወሰደው፣ ነፍሰ ገዳዩ ላፈሰሰው ንጹሕ ደም ሕይወቱን እንዲከፍል ሲባል ነው። በዚህ ረገድ አፋጣኝ እርምጃ መወሰዱ ተስፋይቱ ምድር በደም እንዳትበከል ያደርጋል፤ ይሖዋ ለሕዝቡ “[የሰው ደም ማፍሰስ] ምድሪቱን ስለሚበክል ያላችሁባትን ምድር አትበክሉ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘኁ. 35:33, 34) ይሁንና በእስራኤል ውስጥ አንድ ሰው ሳያስበው ነፍስ ቢያጠፋ ምን ይደረግ ነበር? ግለሰቡ አውቆ ባይሆንም እንኳ ንጹሕ ደም አፍስሷል፤ በመሆኑም ከተጠያቂነት አያመልጥም። (ዘፍ. 9:5) ሆኖም እንዲህ ያለው ግለሰብ፣ ደም ተበቃዩ እንዳይገድለው ከስድስቱ የመማጸኛ ከተሞች ወደ አንዱ መሸሽ ይችል ነበር፤ ይህም ምሕረት የተንጸባረቀበት ዝግጅት ነው። በዚያ ከተማ ውስጥ እንዲቆይ እስከተፈቀደለት ድረስ ጥበቃ ያገኛል። ሳያውቅ ነፍስ ያጠፋው ግለሰብ፣ ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ በመማጸኛ ከተማ ውስጥ መቆየት ይገባዋል።—ዘኁ. 35:15, 28፤ w17.11 9 አን. 3-5
ዓርብ፣ ኅዳር 15
ብልህ ሰው ግን ስድብን ችላ ብሎ ያልፋል።—ምሳሌ 12:16
በአውስትራሊያ የምትኖር አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “የባለቤቴ አባት እውነትን በጣም ይቃወም ነበር። በመሆኑም እኔና ባለቤቴ እሱን ልንጠይቀው ከመደወላችን በፊት ወደ ይሖዋ እንጸልያለን፤ እንዲህ የምናደርገው የባለቤቴ አባት ተቆጥቶ በሚናገርበት ወቅት አጸፋውን እንዳንመልስ ይሖዋ እንዲረዳን ነው። ስለ ሃይማኖት የጦፈ ክርክር ውስጥ መግባት ስለማንፈልግ ከእሱ ጋር በምናወራበት ጊዜ ላይ ገደብ እናበጃለን።” ቤተሰቦቻችሁን ስለምትወዷቸውና ምንጊዜም እነሱን ማስደሰት ስለምትፈልጉ ከእነሱ ጋር የሚያጋጫችሁ ሁኔታ ሲፈጠር የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማችሁ ይችላል። ሆኖም ለቤተሰባችሁ ያላችሁ ፍቅር ለይሖዋ ካላችሁ ታማኝነት በልጦ እንዳይገኝ ልትጠነቀቁ ይገባል። እንዲህ ያለ አቋም መያዛችሁ ቤተሰቦቻችሁ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነትን ተግባራዊ ማድረግ መቼም ቢሆን ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ሊረዳቸው ይችላል። ደግሞም ሌሎች እውነትን እንዲቀበሉ ማስገደድ እንደማትችሉ ማስታወስ ይኖርባችኋል። ከዚህ ይልቅ የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ተግባራዊ ማድረግ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ በአኗኗራችሁ እንዲታይ አድርጉ። አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ለእኛ እንዳደረገው ሁሉ ለእነሱም እሱን የማምለክ ምርጫ አቅርቦላቸዋል።—ኢሳ. 48:17, 18፤ w17.10 15-16 አን. 15-16
ቅዳሜ፣ ኅዳር 16
በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።—1 ዮሐ. 3:18
ተግባራዊ እርምጃ መውሰድን የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ፍቅራችንን በአንደበታችን ከመግለጽ ያለፈ ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የእምነት ባልንጀራችን ለኑሮ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮችን አጥቶ ሲቸገር ብናየው እንዲሁ ከንፈር ከመምጠጥ ያለፈ ነገር ልናደርግለት ይገባል። (ያዕ. 2:15, 16) በተጨማሪም ለይሖዋና ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር፣ አምላክ “ወደ መከሩ፣ ሠራተኞች እንዲልክ” ከመለመን ባለፈ በስብከቱ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል። (ማቴ. 9:38) ሐዋርያው ዮሐንስ “በተግባርና በእውነት” መዋደድ እንዳለብን ጽፏል። በመሆኑም ፍቅራችን “ግብዝነት የሌለበት” ሊሆን ይገባል። (ሮም 12:9፤ 2 ቆሮ. 6:6) ጭንብል እንዳጠለቀ ሰው ያልሆንነውን ሆነን ለመታየት ጥረት የምናደርግ ከሆነ እውነተኛ ፍቅር እያሳየን ነው ሊባል አይችልም። ለመሆኑ ግብዝነት ያለበት ፍቅር ሊኖር ይችላል? በፍጹም። እንደ እውነቱ ከሆነ ግብዝነት ያለበት ፍቅር የሚያሳይ ሰው ፍቅር እያሳየ ሳይሆን እያስመሰለ ነው። w17.10 8 አን. 5-6
እሁድ፣ ኅዳር 17
[ይህን] የሕግ መጽሐፍ . . . ቀንም ሆነ ሌሊት በለሆሳስ አንብበው፤ እንዲህ ካደረግክ . . . ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን ትችላለህ።—ኢያሱ 1:8
የአምላክ ቃል በሕይወታችን ላይ ለውጥ እንዲያመጣ ከፈለግን ቃሉን አዘውትረን ማንበባችን አስፈላጊ ነው፤ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ለማንበብ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እርግጥ ነው፣ የአብዛኞቻችን ፕሮግራም በተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተጣበበ ነው። ያም ቢሆን ማንኛውም ነገር፣ ሌላው ቀርቶ የግድ ልንወጣቸው የሚገቡ ኃላፊነቶቻችንም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራማችንን እንዲያስተጓጉሉብን መፍቀድ አይኖርብንም። (ኤፌ. 5:15, 16) በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የሚያነቡበት ጊዜ ለማግኘት የሚያስችላቸውን ዘዴ ቀይሰዋል፤ አንዳንዶች ጠዋት እንቅስቃሴያቸውን ከመጀመራቸው በፊት ማንበቡን አመቺ ሆኖ አግኝተውታል፤ ሌሎች ደግሞ ከመተኛታቸው በፊት አሊያም ቀን ላይ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡበት ጊዜ መድበዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች “ሕግህን ምንኛ ወደድኩ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ” በማለት የተናገረውን የመዝሙራዊውን ሐሳብ ይጋራሉ። (መዝ. 119:97) መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ በተጨማሪ ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰላችን አስፈላጊ ነው። (መዝ. 1:1-3) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጊዜ የማይሽረው ጥበብ በግል ሕይወታችን በሚገባ ልንጠቀምበት የምንችለው ይህን ካደረግን ብቻ ነው። የምናነበው የታተመውንም ይሁን በኤሌክትሮኒክ ቅጂ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዋነኛው ግባችን መልእክቱ ወደ ልባችን ዘልቆ እንዲገባና ለተግባር እንዲያነሳሳን ማድረግ ሊሆን ይገባል። w17.09 24 አን. 4-5
ሰኞ፣ ኅዳር 18
ሁላችሁም . . . ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ።—1 ጴጥ. 3:8
ርኅራኄ ማሳየት ተገቢ የማይሆንበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ሳኦል የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግን አለመግደሉ ርኅራኄ ማሳየት እንደሆነ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ይሁንና ይሖዋ አማሌቃውያንን አንድም ሳያስቀር እንዲያጠፋ ለሳኦል ነግሮት ነበር። ሳኦል ታዛዥ ባለመሆኑ ንግሥናው በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት አጥቷል። (1 ሳሙ. 15:3, 9, 15 ግርጌ) ይሖዋ ጻድቅ ፈራጅ ነው። የሰዎችን ልብ በትክክል ማንበብ ስለሚችል ርኅራኄ ማሳየት ተገቢ የማይሆንበትን ጊዜ ያውቃል። (ሰቆ. 2:17፤ ሕዝ. 5:11) እሱን ለመታዘዝ እምቢተኛ በሆኑ ሁሉ ላይ የፍርድ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ እየቀረበ ነው። (2 ተሰ. 1:6-10) በዚያን ወቅት፣ ክፉ እንደሆኑ ለተፈረደባቸው ሁሉ ምንም ዓይነት ርኅራኄ አያሳይም። እንዲያውም ክፉዎችን ማጥፋቱ ለጻድቃን ማለትም በሕይወት እንዲተርፉ ለሚያደርጋቸው ሰዎች ርኅራኄ እንዳለው የሚያሳይ ይሆናል። እነማን መትረፍ፣ እነማን ደግሞ መጥፋት እንዳለባቸው የመወሰን ሥልጣን እንደሌለን ግልጽ ነው። ሆኖም የፍርድ ቀን ከመምጣቱ በፊት ሰዎችን ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። w17.09 10-11 አን. 10-12
ማክሰኞ፣ ኅዳር 19
የመንፈስ ፍሬ . . . ራስን መግዛት ነው።—ገላ. 5:22, 23
ራስን መግዛት አምላካዊ ባሕርይ ነው። ይሖዋ ፍጹም በሆነ መንገድ ራሱን የመግዛት ችሎታ አለው። የሰው ልጆች ግን ፍጹማን ስላልሆኑ ራሳቸውን መግዛት ተፈታታኝ ይሆንባቸዋል። እንዲያውም በዛሬው ጊዜ በሰዎች ላይ የሚደርሱት አብዛኞቹ ችግሮች የሚመነጩት ራስን ካለመግዛት ነው። አንዳንዶች ራሳቸውን መግዛት ስለሚያቅታቸው ከትምህርት ወይም ከሥራ ጋር በተያያዘ ዛሬ ነገ የማለት ልማድ የሚታይባቸው ከመሆኑም ሌላ የሚጠበቅባቸውን ነገር በትጋት ለማከናወን ይቸገራሉ። በተጨማሪም ራሳቸውን የማይገዙ ሰዎች ተሳዳቢዎች፣ ሰካራሞችና ዓመፀኞች ሊሆኑ፣ አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ ሊዘፈቁ እንዲሁም ለፍቺ፣ ለሱስ፣ ለእስር፣ ለስሜት ቀውስ፣ በፆታ ግንኙነት ለሚተላለፉ በሽታዎችና ላልተፈለገ እርግዝና ሊዳረጉ ይችላሉ፤ እነዚህ ችግሮች ራስን አለመግዛት ከሚያስከትላቸው መዘዞች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። (መዝ. 34:11) የሚያሳዝነው ራስን የመግዛት ችግር ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ነው። ራስን መግዛትን አስመልክቶ በ1940ዎቹ የተደረጉ ጥናቶችን በቅርቡ ከተደረጉ ጥናቶች ጋር በማነጻጸር የተገኘው ውጤት ሰዎች ይበልጥ ራሳቸውን የማይገዙ እንደሆኑ ያሳያል። የአምላክ ቃል ተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን ይህ መሆኑ አያስገርመንም፤ ምክንያቱም “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ እንደምንኖር ከሚያሳዩት ምልክቶች መካከል አንዱ ሰዎች “ራሳቸውን የማይገዙ” መሆናቸው እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—2 ጢሞ. 3:1-3፤ w17.09 3 አን. 1-2
ረቡዕ፣ ኅዳር 20
ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።—ፊልጵ. 4:7
“የአምላክ ሰላም” ሲኖረን ልባችንና አእምሯችን ከስጋት ነፃ ይሆናል። ይሖዋ እንደሚያስብልንና እንዲሳካልን እንደሚፈልግ እናውቃለን። (1 ጴጥ. 5:10) ይህን ማወቃችን ከልክ በላይ በጭንቀት አሊያም በተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዳንዋጥ ይጠብቀናል። በቅርቡ የሰው ልጆች በምድር ላይ ተከስቶ የማያውቅ ታላቅ መከራ ያጋጥማቸዋል። (ማቴ. 24:21, 22) በዚያን ወቅት እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ ምን እንደሚያጋጥመን አናውቅም። ይሁንና በጭንቀት የምንዋጥበት ምንም ምክንያት የለም። ይሖዋ ስለሚወስደው እርምጃ በዝርዝር ባናውቅም አምላካችን ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ እናውቃለን። ከዚህ በፊት ስላደረጋቸው ነገሮች መመርመራችን ይሖዋ ዓላማውን ዳር እንዳያደርስ የሚያግደው ምንም ነገር እንደሌለ እንዲሁም ይህን ዓላማውን ዳር ለማድረስ አንዳንድ ጊዜ ፈጽሞ ያልተጠበቁ ነገሮችን እንደሚያደርግ እንድንገነዘብ አስችሎናል። ይሖዋ በዛሬው ጊዜ የሚያደርግልን ማንኛውም ነገር፣ ‘ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነውን የአምላክን ሰላም’ በሕይወታችን ውስጥ ልዩ በሆነ መንገድ የምናይበት አጋጣሚ ይሰጠናል። w17.08 12 አን. 16-17
ሐሙስ፣ ኅዳር 21
ጌታ እስከሚገኝበት ጊዜ ድረስ በትዕግሥት ጠብቁ።—ያዕ. 5:7
“እስከ መቼ ነው?” ይህን ጥያቄ የጠየቁት ታማኝ ነቢያት የነበሩት ኢሳይያስና ዕንባቆም ናቸው። (ኢሳ. 6:11፤ ዕን. 1:2) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዙሪያው የነበሩትን ሰዎች እምነት የለሽነት አስመልክቶ በተናገረበት ወቅት ይህን ጥያቄ አንስቷል። (ማቴ. 17:17) በመሆኑም እኛም አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለውን ጥያቄ ብንጠይቅ የሚያስገርም አይደለም። ምናልባት አንድ ዓይነት ኢፍትሐዊ ድርጊት ተፈጽሞብን ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ ከዕድሜ መግፋት ወይም ከጤና ማጣት ጋር እየታገልን ይሆናል፤ በተጨማሪም “ለመቋቋም [በሚያስቸግር] በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ መኖራችን የሚያስከትልብንን ጫና ተቋቁሞ መኖር ከብዶን ይሆናል። (2 ጢሞ. 3:1) ወይም ደግሞ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ያላቸው የተሳሳተ አመለካከትና መጥፎ ምግባር እንድንዝል ሊያደርገን ይችላል። ይህን ጥያቄ እንድናነሳ ያደረገን ምክንያት ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ በጥንት ጊዜ የነበሩ ታማኝ አገልጋዮቹን እንዲህ ያለ ጥያቄ በማንሳታቸው እንዳልኮነናቸው ማወቃችን የሚያበረታታ ነው! ይሁንና እንዲህ ካሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር ፊት ለፊት በምንጋፈጥበት ጊዜ ምን ሊረዳን ይችላል? ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ በመንፈስ መሪነት የጻፈው በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘው ሐሳብ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል። w17.08 3-4 አን. 1-3
ዓርብ፣ ኅዳር 22
በዓመፅ ሀብት ለራሳችሁ ወዳጆች አፍሩ።—ሉቃስ 16:9
ኢየሱስ “በዓመፅ ሀብት” ተጠቅመው በሰማይ ወዳጆች እንዲያፈሩ ተከታዮቹን አሳስቧቸዋል። ከቁሳዊ ንብረታችን ጋር በተያያዘ ታማኝ መሆናችንን ማሳየት ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ፣ ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረውን ዓለም አቀፋዊ የስብከት ሥራ በገንዘብ መደገፍ ነው። (ማቴ. 24:14) በሕንድ የምትኖር አንዲት ትንሽ ልጅ፣ በአነስተኛ ሣጥን ውስጥ ሳንቲም ማጠራቀም ጀመረች፤ ይህች ልጅ ገንዘቡን መጫወቻ ለመግዛት እንኳ አላዋለችውም። ሣጥኑ ሲሞላላት ገንዘቡን በሙሉ አውጥታ ለስብከቱ ሥራ እንዲውል መዋጮ አደረገችው። በዚያው በሕንድ የሚኖር የኮኮናት እርሻ ያለው ወንድም ደግሞ ለማላያላም የርቀት የትርጉም ቢሮ ብዛት ያለው ኮኮናት ይሰጣል፤ ምክንያቱም የርቀት የትርጉም ቢሮው ኮኮናት መግዛት ያስፈልገዋል፤ በመሆኑም ኮኮናት በመሸጥ የሚተዳደረው ይህ ወንድም፣ ለቢሮው ገንዘብ ከሚሰጥ ይልቅ ኮኮናቱን ቢሰጥ እንደሚሻል ተሰምቶታል። ይህ አርቆ አሳቢነት ነው። በተመሳሳይም በግሪክ የሚኖሩ ወንድሞች የወይራ ዘይት፣ አይብ እና ሌሎች ምግቦችን ለቤቴል ቤተሰብ አዘውትረው ይሰጣሉ። w17.07 8 አን. 7-8
ቅዳሜ፣ ኅዳር 23
ከጽዮን መዝሙሮች አንዱን ዘምሩልን።—መዝ. 137:3
በባቢሎን ምርኮኞች የነበሩት አይሁዳውያን በዚያ ወቅት መዘመር አላሰኛቸውም። የሚያስፈልጋቸው የሚያጽናናቸው ነገር ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ በትንቢት ባስነገረው መሠረት የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ ታደጋቸው። ቂሮስ፣ ባቢሎንን ድል ያደረገ ሲሆን እንዲህ ሲል አወጀ፦ “ይሖዋ . . . [በኢየሩሳሌም] ቤት እንድሠራለት አዞኛል። ከእሱ ሕዝብ መካከል የሆነ አብሯችሁ የሚኖር ማንኛውም ሰው አምላኩ ይሖዋ ከእሱ ጋር ይሁን፤ እሱም ወደዚያ ይውጣ።” (2 ዜና 36:23) ይህ ሁኔታ በባቢሎን ይኖሩ ለነበሩት እስራኤላውያን ምን ያህል የሚያጽናና እንደነበር መገመት ይቻላል! ይሖዋ እስራኤላውያንን ያጽናናቸው በብሔር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃም ጭምር ነው። ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አምላክ “የተሰበረ ልብ ያላቸውን ይጠግናል፤ ቁስላቸውን ይፈውሳል።” (መዝ. 147:3) በእርግጥም ይሖዋ፣ አካላዊ ችግር ላጋጠማቸውም ሆነ ስሜታቸው ለተደቆሰ ሰዎች ያስባል። ይሖዋ፣ እኛን ለማጽናናትና የተደቆሰውን ስሜታችንን ለመፈወስ ዝግጁ ነው። (መዝ. 34:18፤ ኢሳ. 57:15) የሚያጋጥመንን ማንኛውንም መከራ ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብና ጥንካሬም ይሰጠናል።—ያዕ. 1:5፤ w17.07 18 አን. 4-5
እሁድ፣ ኅዳር 24
ሀብታችሁ ባለበት ልባችሁም በዚያ ይሆናል።—ሉቃስ 12:34
በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ የይሖዋን ያህል ባለጸጋ የለም። (1 ዜና 29:11, 12) ይሖዋ ለጋስ አባት እንደመሆኑ መጠን ብዙ መንፈሳዊ ሀብት ሰጥቶናል። ይሖዋ ከሰጠን መንፈሳዊ ሀብቶች መካከል (1) የአምላክ መንግሥት፣ (2) ሕይወት አድን የሆነው አገልግሎታችን እንዲሁም (3) በቃሉ ውስጥ የሚገኙት ውድ እውነቶች ይገኙበታል፤ ይሖዋ እነዚህን ውድ ሀብቶች ስለሰጠን በጣም አመስጋኞች ነን! ይሁንና ካልተጠነቀቅን ለእነዚህ ውድ ሀብቶች ያለንን አድናቆት ልናጣና እንደ ተራ ነገር ልንመለከታቸው እንችላለን። እነዚህን ውድ ሀብቶች ከፍ አድርገን መመልከታችንን ልንቀጥል የምንችለው በሚገባ ስንጠቀምባቸውና ለእነሱ ያለን ፍቅር እያደገ እንዲሄድ የማያቋርጥ ጥረት ስናደርግ ነው። አብዛኞቻችን የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ለመሆን ስንል በሕይወታችን ውስጥ ትላልቅ ለውጦችን አድርገናል። (ሮም 12:2) ይሁንና ይህ ብቻውን በቂ አይደለም። ለአምላክ መንግሥት ያለን ፍቅር እንዳይጠፋ ከፈለግን እንደ ፍቅረ ንዋይና ተገቢ ያልሆነ የፆታ ፍላጎት ያሉ ነገሮች እንዳይቆጣጠሩን ምንጊዜም ንቁዎች መሆን ይኖርብናል።—ምሳሌ 4:23፤ ማቴ. 5:27-29፤ w17.06 9 አን. 1፤ 10 አን. 7
ሰኞ፣ ኅዳር 25
ይህን ሳታውቅ አትቀርም!—ኢዮብ 38:21
ኢዮብ መከራ የደረሰበት ለምን እንደሆነ አምላክ በግልጽ የተናገረበትን ቦታ አናገኝም። አምላክ ለሚያደርገው ነገር ማብራሪያ መስጠት አይጠበቅበትም፤ ደግሞም ኢዮብን ያነጋገረው መከራ የደረሰበት ለምን እንደሆነ ለማስረዳት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከአምላክ ታላቅነት አንጻር ሲታይ ኢዮብ እዚህ ግባ የሚባል ሰው እንዳልሆነ ሊያስገነዝበው ፈልጓል። እንዲሁም ይበልጥ አሳሳቢ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮች እንዳሉ ኢዮብ እንዲያስተውል ረድቶታል። (ኢዮብ 38:18-20) በመሆኑም ኢዮብ አመለካከቱን ማስተካከል ችሏል። ይሖዋ፣ ኢዮብ ያንን ሁሉ መከራ በጽናት ከተቋቋመ በኋላ እንዲህ ያለ ቀጥተኛ ምክር መስጠቱ አሳቢነት እንደጎደለው የሚያሳይ ነው? በፍጹም፤ ኢዮብም ቢሆን እንዲህ አልተሰማውም። ኢዮብ ይሖዋ የሰጠውን ምክር ማስተዋል ችሎ ነበር። እንዲያውም “በተናገርኩት ነገር እጸጸታለሁ፤ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬም ንስሐ እገባለሁ” በማለት ተናግሯል። ይሖዋ የሰጠው ቀጥተኛ ሆኖም ፍቅር የተንጸባረቀበት ምክር እንዲህ ያለ ውጤት አስገኝቷል። (ኢዮብ 42:1-6) ኢዮብ፣ አምላክ የሰጠውን እርማት ተቀብሎ አመለካከቱን ካስተካከለ በኋላ ይሖዋ ኢዮብ ታማኝነቱን በመጠበቁ እንደተደሰተ ገልጿል።—ኢዮብ 42:7, 8፤ w17.06 24-25 አን. 11-12
ማክሰኞ፣ ኅዳር 26
ማርያም በበኩሏ ጥሩ የሆነውን ድርሻ መርጣለች፤ ይህም ከእሷ አይወሰድም።—ሉቃስ 10:42
ለሰብዓዊ ሥራችን እና ለመንፈሳዊ ኃላፊነቶቻችን ያለን አመለካከት ሚዛናዊ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ‘ሥራዬ አስደሳች እንደሆነ፣ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ግን ያን ያህል እንደማያስደስቱ እንዲያውም አሰልቺ እንደሆኑ ይሰማኛል?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ጥሩ ነው። ስለ እነዚህ ጉዳዮች ያለንን አመለካከት በቁም ነገር መመርመራችን፣ አስበልጠን የምንወደው ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ ያስችለናል። ኢየሱስ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችንና ሌሎች ነገሮችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በማከናወን ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ማርያምንና እህቷን ማርታን ለመጠየቅ ቤታቸው ሄዶ ነበር። ማርታ ምግብ ለማዘጋጀት ጉድ ጉድ እያለች ሳለ ማርያም የኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጣ የሚናገረውን ታዳምጥ ነበር። ማርታ፣ ማርያም ስላላገዘቻት ቅሬታዋን ለኢየሱስ ስትነግረው ኢየሱስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ተናገረ። (ሉቃስ 10:38-42) ኢየሱስ ለማርታ ጠቃሚ የሆነ ትምህርት እየሰጣት ነበር። ትኩረታችን በሰብዓዊ ነገሮች እንዳይከፋፈል ለማድረግ እንዲሁም ለክርስቶስ ፍቅር እንዳለን ለማሳየት፣ ምንጊዜም “ጥሩ የሆነውን ድርሻ” መምረጥ አለብን፤ ይኸውም ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠት ይኖርብናል። w17.05 24 አን. 9-10
ረቡዕ፣ ኅዳር 27
የአባትህን ተግሣጽ አዳምጥ።—ምሳሌ 1:8
ይሖዋ፣ ልጆችን በእውነት ውስጥ የማሳደግን ኃላፊነት የሰጠው ለወላጆች እንጂ ለአያቶች ወይም ለሌላ ለማንም ሰው አይደለም። (ምሳሌ 31:10, 27, 28) ይሁንና የሚኖሩበትን አገር ቋንቋ የማይችሉ ወላጆች የልጆቻቸውን ልብ ለመንካት በሚያደርጉት ጥረት እገዛ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ወላጆች እንዲህ ዓይነት እገዛ ለማግኘት ቢጠይቁ፣ የልጆቻቸውን መንፈሳዊ ፍላጎት የማሟላት ኃላፊነታቸውን ለሌሎች አሳልፈው እንደሰጡ ተደርጎ ሊታይ አይገባም፤ ከዚህ ይልቅ ይህን ማድረጋቸው ልጆቻቸውን “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረት የሚደግፍ ነው። (ኤፌ. 6:4) ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆች የቤተሰብ አምልኳቸውን መምራት እንዲሁም ለልጆቻቸው ጥሩ ጓደኞች መምረጥ የሚችሉበትን መንገድ በተመለከተ የጉባኤ ሽማግሌዎች ሐሳብ እንዲሰጧቸው መጠየቅ ይችላሉ። በቤተሰብ አምልኳቸው ላይ ሌሎች ቤተሰቦች እንዲገኙ አልፎ አልፎ መጋበዝም ይችላሉ። በተጨማሪም ወጣቶች መንፈሳዊ አመለካከት ካላቸው ክርስቲያኖች ጋር መቀራረባቸው እድገት እንዲያደርጉ ሊረዳቸው ይችላል፤ ለምሳሌ አብረው አገልግሎት ሊወጡ እንዲሁም ጤናማ በሆነ መዝናኛ ሊካፈሉ ይችላሉ።—ምሳሌ 27:17፤ w17.05 11-12 አን. 17-18
ሐሙስ፣ ኅዳር 28
ወደ ግብፅ ሽሽ።—ማቴ. 2:13
የይሖዋ መልአክ፣ ንጉሥ ሄሮድስ ኢየሱስን ለመግደል እንዳሰበ ለዮሴፍ ከነገረው በኋላ ሕፃኑ ኢየሱስና ወላጆቹ ወደ ግብፅ ተሰደዱ። ሄሮድስ እስኪሞት ድረስም በዚያው ቆዩ። (ማቴ. 2:14, 19-21) ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በኋላ ደግሞ የጥንቶቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በደረሰባቸው ከባድ ስደት የተነሳ “በይሁዳና በሰማርያ ክልሎች ሁሉ ተበተኑ።” (ሥራ 8:1) ኢየሱስ ከተከታዮቹ መካከል ብዙዎቹ ቤታቸውን ጥለው ለመሸሽ እንደሚገደዱ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። “በአንድ ከተማ ስደት ሲያደርሱባችሁ ወደ ሌላ ከተማ ሽሹ” ብሎ ነበር። (ማቴ. 10:23) ይህ ሁኔታ በሺዎች በሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ተከስቷል። ብዙዎች የሚወዷቸውን ሰዎችና ንብረታቸውን አጥተዋል። አንዳንዶች በሚሸሹበት ጊዜ ወይም ደግሞ በስደተኞች መጠለያ ውስጥ ካሉ ሰካራሞች፣ ቁማርተኞች፣ ሌቦችና ሥነ ምግባር የጎደላቸው ሰዎች አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሟቸዋል፤ ይሁን እንጂ በምድረ በዳ እንደነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ እነሱም ያሉበት ሁኔታ ከጊዜ በኋላ እንደሚቀየር በማስታወስ አዎንታዊ አመለካከት ይዘው መቀጠል ችለዋል።—2 ቆሮ. 4:18፤ w17.05 3-4 አን. 2-5
ዓርብ፣ ኅዳር 29
ሕግህን የሚወዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤ ሊያደናቅፋቸው የሚችል ምንም ነገር የለም።—መዝ. 119:165
በጉባኤ ውስጥ በአንድ የምናውቀው ሰው ወይም በራሳችን ላይ በደል እንደተፈጸመ እንዲሰማን የሚያደርግ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፤ እርግጥ ይህ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ነገር አይደለም። ያም ቢሆን እንዲህ ያለው ሁኔታ እንዲያደናቅፈን መፍቀድ የለብንም። እንዲያውም ምንጊዜም ለአምላክ ታማኝ እንሁን፤ እንዲሁም ይሖዋ እንደሚረዳን በመተማመን ወደ እሱ እንጸልይ። በሌላ በኩል ደግሞ የተሟላ መረጃ ላይኖረን እንደሚችል በመገንዘብ ትሕትና ማሳየት ይኖርብናል። በተጨማሪም ፍጹማን ባለመሆናችን የተነሳ ሁኔታውን በተሳሳተ መንገድ ተረድተነው ሊሆን ይችላል። ሐሜት ማሰራጨት አንድን ችግር የበለጠ ከማባባስ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም፤ ስለዚህ ይህን ከማድረግ እንቆጠባለን። በመሆኑም ችግሩን በራሳችን መንገድ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ምንጊዜም ለይሖዋ ታማኝ በመሆን እሱ ነገሮችን እስኪያስተካክል ድረስ በትዕግሥት እንጠብቅ። እንዲህ ያለውን አካሄድ መከተል የይሖዋን ሞገስና በረከት ያስገኝልናል። በእርግጥም “የምድር ሁሉ ዳኛ” የሆነው ይሖዋ “መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ” ስለሆኑ ምንጊዜም ትክክል የሆነውን ነገር እንደሚያደርግ መተማመን እንችላለን።—ዘፍ. 18:25፤ ዘዳ. 32:4፤ w17.04 22 አን. 17
ቅዳሜ፣ ኅዳር 30
ክፉ ሰው መንገዱን . . . ይተው፤ ምሕረት ወደሚያሳየው አምላካችን ወደ ይሖዋ ይመለስ።—ኢሳ. 55:7
ለመለወጥ እምቢተኛ የሆኑና ታላቁ መከራ እስኪጀምር ድረስ ይህን ሥርዓት የሚደግፉ ሰዎች መጨረሻቸው ምን ይሆናል? ይሖዋ ክፉ ሰዎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከምድር ላይ እንደሚያስወግዳቸው ቃል ገብቷል። (መዝ. 37:10) ክፉዎች ከዚህ ፍርድ ማምለጥ እንደሚችሉ ሆኖ ይሰማቸው ይሆናል። በዛሬው ጊዜ ብዙዎች፣ የሚሠሩት መጥፎ ድርጊት እንዳይታወቅባቸው ማድረግ በመቻላቸው አብዛኛውን ጊዜ ከቅጣት ያመልጣሉ። (ኢዮብ 21:7, 9) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የአምላክ ዓይኖች የሰውን መንገድ ይመለከታሉና፤ ደግሞም እርምጃውን ሁሉ ያያል። ክፉ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች የሚደበቁበት ጨለማም ሆነ ፅልማሞት የለም።” (ኢዮብ 34:21, 22) ከይሖዋ አምላክ መሰወር አይቻልም። ማንኛውም አስመሳይ እሱን ማታለል አይችልም፤ የትኛውም ዓይነት ድርጊት ከእሱ እይታ ውጪ አይደለም። በመሆኑም ከአርማጌዶን በኋላ ክፉዎችን በቀድሞ ቦታቸው ብንፈልጋቸው ልናገኛቸው አንችልም። ከዚያ በኋላ ደብዛቸው አይገኝም!—መዝ. 37:12-15፤ w17.04 10 አን. 5